ቁጥር 1 መስከረም 28 ቀን 2016ዓም(09-10-2023)
ፋኖስ ጨለማን አስወግዶ ብርሃን በመለገስ የማይታዩንን እንድናይ የሚረዳን ሲሆን፣ እንደ ፋኖስ በአገራችን በጊዜው የሚታዩና ያልታዩ ጉዳዮችን በማንሳት ውዥንብሮችን ለማስወገድና ለሚከሰቱ ችግሮች ጥንቃቄና የመፍትሔ መንገዶችን ለማሳየት የሚቀርቡ ሃሳቦች የሚስተናገዱበት የስብስባችን ልሳን ነው። በዚህ የመጀመሪያ ዕትሙ የሕዝባዊው፣ በተለይም የፋኖ ትግል ከየት ወዴት? በሚለው እርዕስ ዙሪያ የሚሰነዘሩ የተለያዩ ጥያቄዎችንና ሃሳቦችን የሚያስተናግድ ይሆናል።
የአማራው ሕዝባዊ ትግሉ፣ በተለይም የፋኖ ትግል ለምን ዓላማና በማን ተጀመረ? የመጨረሻ ግቡስ ምን ይሆናል? የፋኖ ትግል ግለሰቦችን ወይም አንድ ጎሳን ለሥልጣን የሚያበቃ ነው ወይ?የግለሰቦች ሚናና ድርሻ ምን መሆን አለበት? ትግሉ የሌላውን ጎሳ ወይም ማህበረሰብ ያካትታል ወይ? በትግሉ ዙሪያ የሚተላለፉ መለዕክቶችና መፈክሮች ምን ዐይነት ይዘት ሊኖራቸው ይገባል?ትግሉ ከውጭ እጅና ተጸዕኖ እንዴት ሊድን ይችላል? ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችና እንቅፋቶች ምንድን ናቸው? እንዴትስ ይወገዳሉ?
ሕዝባዊ ትግሉ መቼ ተጀመረ ለሚለው ጥያቄ የሚሰጠው መልስ ጭቆና ባለበት ቦታ ሁሉ የሕዝብ ትግል ይኖራል የሚለውን አጠቃላይ ግንዛቤ ይዘን ወደ አገራችን ስንገባ የኢትዮጵያ ሕዝብ ባሳለፋቸው ዘመናት በሰፈኑ ስርዓቶች ሲበደልና ሲጨቆን ለመኖሩና ያንንም ለማስወገድ በሚችለው አቅም ትግል ሲያደርግ እንደኖረ የሚካድ አይደለም። አሁን የደረሰበት የትግል ደረጃ ሲጠራቀም በኖረውና ሞልቶ በፈሰሰው በደል ምክንያት የደረሰበት የትግል ምዕራፍ ነው። በተለይም የአማራው ማህበረሰብ የትግሉ ፊታውራሪ ሆኖ በፋኖ አደረጃጀት በማንነቱ ሲያጠፋው፣ ሲገለው፣ ሲጨፈጭፈው፣ ሲያፈናቅለው የኖረውን ላለፉት 32 ዓመታት የሰፈነውን የጎሰኞች ስብስብ ስርዓት ነቅሎ ለመጣልና እራሱንም ሆነ ሌላውንም ወገኑንና አገሩን ኢትዮጵያን ለዘላቂ ሰላምና አንድነት የሚያበቃ ወሳኝ ትግል ለማድረግ በታሪካዊውና ባሕላዊው በፋኖ የጦር ሜዳ አሰላለፉ እምቢ ብሎ ቆርጦ ተነስቶ በመፋለም ላይ ይገኛል። ትግሉን የሚመሩ የአማራው ልጆች በያካባቢው ሕዝቡን እያደራጁ በሚወስዱት የበቀል እርምጃ ለሥርዓቱ የጋለ ምጣድ ሆነውበታል። በአእላፍ አስታጥቆ የሚልካቸው የጥፋት ሠራዊቶቹ ሳይተኩሱ ዶጋመድ እየሆኑ፣ ያደላቸው ደግሞ እዬተማረኩ፣ ሌሎቹም ሰልፋቸውን ቀይረው ፋኖን በመቀላቀል ላይ ይገኛሉ። የሥርዓቱ ዘበኛ ለፋኖ እቤቱ ድረስ መሣሪያ ተሸክሞ የሚያደርስ ተላላኪ ሆኖለታል። ይህ ያስደነገጣቸው የጥፋት ሃይሎችና መሪዎቻቸው በሕዝባዊ ትግሉ ብሎም በፋኖ ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ ከፍተው በሆድ አደሮች በኩል የከፈቱት ዘመቻ እራሳቸውን እያጋለጣቸው ከመሄድ በቀር ያሰቡትን ሊያደርጉ አልቻሉም።
የኦሮሙማው መራሹ አገዛዝ በፋኖ ውስጥ መከፋፈል አለ፣ ትግሉ አሁን መብታቸውን ያረጋገጡትን ሌሎቹን ማህበረሰቦች አግልሎ አማራውን ሥልጣን ላይ ለማውጣት ነው፤ አብይ አህመድን አስወግዶ የፋኖ መሪ(መሪዎችን)ከሥልጣን ላይ ለማውጣት ነው፤ የሚሉ ውዥንብሮችን መንዛት የትግል ስልቱ አድርጎታል።ይህ ግን ለጊዜው ለማወናበድና ውዥንብር ለመፍጠር የሚችል ቢሆንም ዘላቂነት እንደሌለው በየቀኑ የሚታዩት የሕዝቡ ስሜቶች ያረጋግጣሉ። በአሁኑ ጊዜ ያልተጎዳ የለም፤ እራሱ በስሙ የሚነግዱበት ማህበረሰብ ከአማራው ያላነሰ በደል እየደረሰበት ነው። የኑሮ ውድነቱ፣ ድህነቱ፣ ሥራ አጥነቱ፣ እርሃቡና በሽታው፣ ሰላም ማጣቱ፣ ስጋትና ጭንቀቱ፣ ተስፋ መቁረጥና ስደቱ የሁሉም ማህበረሰብ ተወላጅ የጋራ እሴቶች ሆነዋል።የተንደላቀቀ ኑሮ የሚኖሩት ሥልጣኑን የያዙት ጥቂቶቹ ቤተሰቦቻቸውና አጫፋሪዎቻቸው ብቻ ናቸው።
የአማራ ፋኖ ትግል እነዚህን የጋራ ችግሮች ለማስወገድና ሁሉንም ያገሩ፣ የሰላሙ፣ የእኩልነቱና የመብቱ ባለቤት ለማድረግ እንጂ አማራውን ብቻና ግለሰቦችን ለሥልጣን ለማብቃት አይደለም፤ ያንንም መነሻችን አማራነታችን. መድረሻችን ደግሞ ኢትዮጵያዊነታችን ነው ሲል አስረግጦ ገልጾታል፤ በተግባርም እያሳየ ነው።ሌላውን ማህበረሰብ በትግሉ ውስጥ ለማካተት ያላሰለሰ ጥሪ አድርጓል፤ በማድረግም ላይ ነው። መልስ መስጠት የሚኖርበት ጥሪ የተደረገለት ማህበረሰብ ነው። አብረው ያላጨዱትን መሰብሰብ አይቻልምና ለጋራ ነጻነት አብሮ መታገል የግድ ይላል።
ትግሉ ጎሳን በጎሳ የመተካት አይደለም። ግለሰቦችንም ለሥልጣን ለማብቃት አይደለም፤ መሆንም የለበትም።ትግሉ የሕዝብ እንደመሆኑ መጠን ሥልጣኑም የሕዝቡ ነው። መሣሪያ ያነገበ ቤተመንግሥት ገብቶ የሥልጣን ባለቤት እንዳይሆንም ከወዲሁ መጠንቀቅ ተገቢና አስፈላጊ ነው። የሰፈነውን ሥርዓት ካስወገዱ በኋላ ሳይውል ሳያድር የአደራ(ሁሉንም ያካተተ የሽግግር መንግሥት) መመሥረት ለቀጣዩ ሥርዓት መንደርደሪያ የመሰናጃ ጊዜና ዕድል ይሰጣል።
በትግሉ የመሪነት ሚና የሚጫወቱትን ግለሰቦች ከማይገባው በላይ ማግዘፍም ሆነ ማኮሰስ አይገባም።በሚሠሩት ልክ መከበር ይኖርባቸዋል። መሪዎችን እንደ ታቦት መቁጠርና ማወደስ፣ ከስማቸው ሌላ ተቀጣይ እያወጡ መጥራት ለአምባገነንነት በር ይከፍታል። እነሱም ሆኑ ተራው ታጋይ ያለው አንድ ነፍስ ነው፤የተሰለፉትም ለአንድ ዓላማ ነው። ለትግሉ አመራር ስለሚያስፈልገውና የሥራ ክፍፍል በመኖሩ እንጂ ማንም ከሌላው በልጦ ወይም አንሶ የሚያደርገው ትግል፣ የሚከፍለውም መስዋዕትነት የለም።
በመፈክርና በቅስቀሳ የሚሰሙት መልእክቶች ሊታሰብባቸው ይገባል። አንዳንዶቹ ከማወቅም ይሁን ካለማወቅ ፋኖ አራት ኪሎ ቤተመንግሥት ግባ! አማራው ሥልጣኑን ይጨብጥ! የሚሉት ህሳቤዎች ጠላት የሚጠቀምባቸው ሊሆኑ ይችላሉና ከማለት መቆጠብ ይመረጣል። የትግሉም ዓላማ ይህ አይደለም። ሥልጣን በጠመንጃ ሳይሆን በምርጫ ካርድ የሚስተናገድበት የዴሞክራሲ ባሕል እንዲኖረን እንጂ በኖርንበትና ለዚህ ቀውስ ለዳረገን ሥርዓት ዐይነት የሚደረግ ትግል አይደለም።
በመጨረሻም ትግሉና ለውጡ ከውጭ ኃይሎች እጅ የጸዳ መሆን አለበት። ያለፉትን ሥርዓቶች ለረዱት ሃይሎች መጠቀሚያና ባርያ፣ ተለዋጭ ጎማ ላለመሆን መጠንቀቅ ተገቢ ነው። ከሁሉም አገራት ጋር የሚኖረው ግንኙነት የጋራ ጥቅምን መርህ ባደረገ፣ ልዑላዊነትንና ነፃነትን ባስከበረ መልኩ ሊሆን ይገባል።
በመጨረሻ ላይ ልናሳስብ የምንወደው ቢኖር በትግሉ ሜዳ የተሰለፉት ፋኖዎች ህብረታቸው የጸና፣ በአንድ የጋራ አመራር የሚመሩ፣,ከወታደራዊው ስልት ጎን ለጎን አብሮ የሚሄድ የፖለቲካ ፍኖተ-ካርታና ርዕዮተ-ዓለም ሊኖራቸው እንደሚገባ ነው። ፋኖ በጫካ ሲታገል በከተማና በያገሩ የሚኖረው የትግሉ አጋርም በአንድ ጣራ ሥር ተሰባስቦ፣ የገንዘብና የቁሳቁስ፣ እንዲሁም የዲፕሎማሲ ድጋፍ ለማድረግ የሚንቀሳቀስ ሊሆን ይገባዋል።አሁን የሚታዩት የተለያዩ አካሄዶች ምንም እንኳን ለመልካም ሥራ ነው ቢባልም የኋላ ኋላ ሌላ መልክ ለመያዝ ስለሚያስችሉ ከአሁኑ መፍትሔ ሊሰጥባቸው ይገባል።
ለሥርዓት ለውጥ በንቃትና በእውቀት ላይ የተመረኮዘ ሕዝባዊ ትግል ወሳኝ ነው!