ፍትህና ነጻነት ለጠለምት አማራ Justice and Freedom for Telemt Amara telemtgondar@gmail.com |
ይድረስ ለተከበርከውና ለጀግናው የጠለምት ሕዝብ
“ የምን ሕዝበ-ውሳኔ…”?
መስከረም 27, 2016 ዓ/ም
ትህነግ ጎንደርንና ትግራይን ክ/ሃገር የሚያዋስነዉን ታሪካዊ ድምበር ተከዜ ወንዝን ተሻግሮ ጠለምትን፣ ወልቃይትን፣ ጠገዴንና ሁመራን በጉልበት ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ የአገሬው ሕዝብ በግፍ ተጨፈጨፉ፣ በትግራይ የማሰቃያ እስር ቤቶች ታጎሩ፣ ንብረታቸው ተዘረፈ፤ መሬታቸው ተወሰደ፣ በብዙ መቶ ሺ የሚቆጠሩ ወደ ሱዳንና የተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተስደዱ። ህዝቡ በቋንቋው እንዳይማር፣ በቋንቋው ፍርድ እንዳያገኝ፣ አስተዳደሩ በትግርኛ እንዲካሄድ፣ ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ሁመራ የሚገኙ የሥራ እንቅስቃሴዎች በሙሉ በትግሬዎች ብቻ እንዲያዙ በማድረግ፣ የክፍለሀገሩን የእርሻ፣ የኢንዱስትሪና የትራስፖርት አገልግሎት ተቆጣጠሩት። ይህን የመግደልና የማፈናቀል ወንጀል በማካሄድ፣ በብዙ ሺ የሚቆጠር ሕዝብ ከትግራይ እያጓጓዘ አሰፈረ። ወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት የትግራይ ግዛቶች ናቸው አለ። በታሪክም የትግራይ ነበሩ በማለት የውሸት ትርክት አስፋፋ። ወያኔ እስከ መተማና ከዚያም አልፎ የትግራይ ግዛት ነው እስከ ማለትም ደረሰ። የጠለምትና የአዲአርቃይ ወረዳዎች በፋሺስቱ ትህነግ ቁጥጥር ስር በነበረበት ወቅት ሕዝቡ ከመቸዉም ጊዜ በከፋ መልኩ እየተገደለ፣እየተሰቃየ፣ ለስደት እየተዳረገና በግዳጅ ወደጦርነት እንዲዘምት ተደርጎ ለእልቂት ተዳርጓል የዘር ማጥፋት ወንጀልም ተፈጽሞበታል።
ማንነቱን በሚመለከት የጠለምት ህዝብ በሰነድ የተደገፈ አቤቱታውን ሲያሰማ ቆይቷል። ከአርባ ዓመታት መራራ ትግል በኋላ በመከላከያ ሰራዊታችን፣ በአማራ ልዩ ሀይል፣ በአማራ ፋኖና ሚሊሺያ፣ እንዲሁም በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከባድ መስዋዕትነት እንዚህ አካባቢዎች ነጻ መውጣታቸዉ የሚታወስ ነው። ሆኖም ግን በከባድ መስውዋዕትነት የተገኘዉን ድል መንግስት ከጠለምትና አዳርቃይ ወረዳዎች ሁሉንም ሕዝባዊ ሃይሎችና አስተዳደሮች ለቀው እንዲወጡ በማድረግ ወራሪውና ተስፋፊው የትህነግ ሰራዊት እንደገና እንዲቆጣጠረው በማድረግ ሕዝቡ ከመቸዉም ጊዜ በከፋ መልኩ ለሞት፣ ለእስራት፣ ለእንግልት፣ ለስደትና ለዳግም ባርነት ሊዳርገው መሆኑን ብቻ ሳይሆን ጠለምትን ወደትግራይ በመቀላቀል የጠለምት ሕዝብ ማንነቱንና ምንነቱን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ዜግነቱንም ለማሳጣል ሽብ ረብ እያለ ይገኛል።
ጀግናው የጠለምት ሕዝብ ሆይ ላለፉት 40 ዓመታት በተስፋፊው ትህነግ ቡድን የደረሰብህን ይህ ነው የማይባል በደልና ግፍ ደምና አጥንትህን ገብረህ የአገኘኽውን ነጻነት የኦሮሙማና የትህነግ ቡድን በመተባበር ሕዝበ ውሳኔ በሚል ማደናገርያ ለባርነት ቀንበር ሊዳርጉህ የወሰኑ መሆናቸውን የአከባቢው ተውላጅ ባንዳዎችም ጭምር በአደባባይ ነግረውናል። ጠለምት ምንም በማያሻማ ታሪክ የጎንደር ክፍለሃገር መሆኑን ዓለም ያወቀው ሃቅ ሆኖ ሳለ ማንነትህን ሳትወድና ሳትፈቅድ በግዴታ ሕዝበ ወሳኔ በሚል እንቆቅልሽ እንድትለውጥ የሚደረገው ድራማ እምቢኝ አሻፈረኝ የምን ሕዝበ ወሳኔ በማለት ከአሁን ቀደም በጉልበትህ ያረጋገጥከዉን ማንነትህን በሕዝበ ወሳኔ ትርክት ታሪክህን፣ ማንነትህን፣ ነጻነትህንና ዳር ድንበርሀን አሳልፈህ መስጠት የለብህም።
ለማንነትህና ለደምበርህ ሆ ብለህ በመነሳት የሃገሬው ህዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሕገ-መንግስታዊ መብቱ እንዲረጋገጥለትና ለ40 ዓመታት ሙሉ የታገለለት አላማ ወደ ሆነው ወደ ነባር አስተዳደሩ ወደ ጎንደር ህጋዊና ፖለቲካዊ ውሳኔ እንዲሰጠው ለፈደረሺን ምክር ቤት ያቀረብከዉን ጥያቄ ተግባራዊ እንዲሆን ከመጠየቅ ዉጭ የማይታሰብ መሆኑንን በድጋሚ አረጋግጥላቸው። ይህ ሳይሆን ቢቀርና ጠለምትን ከአገሬው ተወላጅ ባለፈ ለወያኔ ሰፋሪዎች ለሕዝበ ዉሳኔ ድርድር ለማቅረብ ቢሞከር ታሪክና ትውልድ ይቅር የማይለው ስህተት ከመፈጸም ባሻገር አከባቢዉን የጦርነት ቀጠና እንዲሆን የማድረግ ውሳኔ ከመሆን እንደማያልፍ ማሳሰብ እንወዳለን።
የጠለምት፣ የወልቃይት የጠገዴ፣ የሁመራና የራያ ወረዳዎች ወደትግራይ የተካለሉት 1ኛ/ በሕዝበ ዉሳኔ ሳይሆን ፖለቲካዊ ውሳኔ በመሆኑ 2ኛ/ እነዚህ ክልሎች ወደትግራይ የተካለሉት ህገ-መንግስቱ ከመጽደቁ ቀደም ብሎ በመሆኑ እነዚህ ወረዳዎች ታሪካዊ፣ ባህላዊና ስነልቦናዊ ግንኙነታቸው ከጎንደር ክፍለ ሃገር ጋር በመሆኑ
እኛ በውጩ ዓለም የምንገኝ የጠለምትና የአጎራባች ወረዳዎች የጠለምት የአማራ ማንነትና የወሰን ይገባኛል ጥያቄ ላለፉት በርካታ ዓመታት ለፌደረሺኑ ምክር ቤትና ለአማራ ክልል አስተዳደር በተደጋጋሚ ያቀረበ ቢሆንም ምላሽ አላገኘም። በተለያዩ ድህረ-ገጾች እንደምንሰማው፣ በነዚህ ታሪካዊ የአማራ ክልሎች ወያኔ ባለርስቱን አባሮ ያሰፈራቸው አባሎቹ የሚሳተፉበት ሕዝበ–ውሳኔ ይሰጥ ማለት የማንነት ጥያቄ የቀረበበትን ጉዳይ በቀጥታ ለመፍታት አለመፈለግንና የአማራን ደም ወያኔን ለማባበያ መጠቀም አድርገን እንወስደዋለን። በእንዲህ አይነት ሁኔታ የሕዝብ ድምፅ ውሳኔ የሚለው የመፍትሄ ሃሳብ ሳይጀመር ውጤት እንደማይስጥ በመገንዘብ መንግስት የጠለምት፣ ወልቃይት ጠገዴ፣ የሁመራና ራያ ሕዝብ ጥያቄ ሊፈታ የሚገባው የሕዝቡን ማንነት፣ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ሕዝባዊ ስነልቦናን መሰረት አድርጎ በማየት አሁን ባለበት የአማራ ክልል አስተዳደር እንዲቀጥል የፈደሬሽኑ ምክርቤት አስቸኳይ ዉሳኔ እንዲስጥበት ላማሳሰብ እንወዳለን፡
በመጨረሻም አንዳንድ ሙሁራን ነን የሚሉ የአከባቢው ተወላጅ የብልጽግና ተላላኪዎችና ዘመናዊ ባንዳዎች ህዝበ ዉሳኔውን ለማስፈጸም ከፍተኛ ስራ እየሰሩ መሆናቸዉን በተጨባጭ ደረስንበታል። በመሆኑንም ከዚህ እኩይ ተግባራችሀው እንዲታቀቡ ከወዲሁ ላምስጠንቀቅ እንወዳለን። የማይታቀቡ ከሆነ ግን ስማቸውንና የስራ ድርሳቸዉን ለሕዝብ በማጋለጥ በታሪክ ተጠያቂ መሆናቸውን ሊገነዘቡት ይገባል።
አማራነን እንጂ አማራ እንሁን አላልንም
ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ለዘለአለም ትኑር።
ከፍትህና ነጻነት ለጠለምት አማራ
Justice and Freedom for Telemt Amara