የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ምዕራባውያን አገራት በተለያዩ አገሮች ውስጥ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነትና ዓላማቸውን ለማስፈጸም በሚሠሩበት ጊዜ እንቅፋት ይሆንብናል የሚሉትን አካል እንዴት እንደሚያጠቁ በጥቂቱ መዳሰስ ነው፡፡ ጽሑፉ ምንም እንኳ ቀድሞ ከተጻፉት መሰል ጽሑፎች የተለየ ሀሳብ ባይዝም ነገር ግን የኢትዮጵያን እና የአማራን ፈተና ከቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ እና የሰርብ ህዝብ ሁኔታ ከወቅታዊ የኢትዮጵያ ችግር ጋር በማነጻጸር ለማሳየት የተሞከረበት ነው፡፡ ጽሑፉ በተለይ ትኩረት የሚያደርገውም ምዕራባውያን በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ የሰርብ ዘሮችን እንዴት የጥቃታቸው ዒላማ ውስጥ እንዳስገቧቸውና አገሪቱን ለመበታተን እንደሠሩ፤ በተመሳሳይ መልኩም ኢትዮጵያን ከተቻለ እንደ ዩጎዝላቪያ ወደ ብዙ ደካማ ትንንሽ አገርነት ለመቀየት፤ ካልሆነ ደግሞ ሳትበታተን ፍጹም ደካማና የውጪ ተጽዕኖን ለመቋቋም የማትችል አገር ሆና እንድትቀጥል ለማድረግ በአገሪቱ ውስጥ የአማራን ዘር እንዴት ሲያጠቁ እንደነበር፣ አሁንም እየሠሩ ያለውን ሴራ በማነጻጸሪያነት በጥቂቱ ማየት ነው፡፡ ጽሑፉ እግረመንገዱንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንም በጠላትነት ስለመፈረጇም በጥቂቱ ያነሳል፡፡
ምዕራባውያን በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ለምን ሰርቦችን የጥቃት ዒላማቸው ውስጥ አስገቧቸው? አማራንና ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንንስ በኢትዮጵያ ውስጥ የጥቃት ዒላማ እንዲሆኑ ለምን መረጧቸው?
ወደ ዋናው ንጽጽራችን ከመግባታችን በፊት የሚከተለውን የቆየ የምዕራባውያን የጥናት ግኝት እንመልከት፡፡ ኢትዮጵያ ጣልያንን በዓድዋ ጦርነት ከማሸነፏ በፊት የዓለም ስርዓት በቅኝ ገዢና ተገዢነት የነበረ ሲሆን ገዢዎቹ እንደ መብት ተገዢዎቹ ደግሞ እንደ ተፈጥሯዊ እጣ ፈንታቸው ቆጥረውት ባለበት ቀጥሎ ነበር፤ በተለይም በአፍሪካ፡፡ ይህ የዓለም ስርዓት የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. በዓድዋ በጀግኖቹ የኢትዮጵያ ልጆች ድል ምክንያት ከፍተኛ የመሠረት መናጋት ደረሰበት፡፡ ድሉ ከፍ ያለ የዓለምአቀፍ ግንኙነት አንድምታም ነበረው፡፡ በዚህ ምክንያትም ከቀጥታ ወደ እጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ስልት መዞር ግድ ብሏቸው ነበር፡፡
ምንም እንኳ እድለ ቢሷ ጣሊያን መራራ የሽነፈት ጽዋን ለመጎንጨት ብትበቃም ጦርነቱ የተደረገው ከሌላ አውሮፓዊ አገር ከእንግሊዝ፣ ፈረናሳይ፣ ስፔንና ከመሳሰሉት ጋር ቢሆንም ኖሮ ድሉ የኢትዮጵያ መሆኑ አይቀርም ነበር፡፡ ምክንያቱም ጦርነትን ለማሸነፍ የሚያበቁት የአገር ፍቅር እና አንድነት ባላቸው ኢትዮጵያውያን የተደረገ ስለነበር ነው፡፡ እናም የቅኝ አገዛዝ ሥርዓት በኢትዮጵያ ምክንያት ጥያቄ ውስጥ የወደቀባቸው ምዕራባውያን ከዓድዋ ድል ማግስት ጀምሮ የኢትዮጵያን የማሸነፍ ምክንያት ወደ ማጥናት ገብተው ነበር፡፡ በጥናታቸው ካገኟቸው ግኝቶች መካከልም የሚከተሉት ሁለቱ ዋና ነጥቦች ተብለው ተቀምጠዋል፡፡
- ኢትዮጵያ ጠንካራ ማእከላዊ መንግስት የነበራት መሆኑ፤
- የተለያየ ጎሳና ቋንቋ የነበረውን ህዝብ ለጦርነቱ መጥራት፣ በቀላሉ ማሰባሰብና ማንቀሳቀስ የቻለችው፣ እንዲሁም ታቦት ይዛ በመዝመት ጦሩን ከጎኑ ሆና በማበርታት ለድሉ መገኘት ታላቅ ሚና የነበራት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መኖሯ ነበሩ፡፡
በጥናታቸው መሠረትም የቀጥታ ቅኝ ግዛት ስርዓትን ያፈረሰችባቸው ኢትዮጵያ ጠንካራ አገር መሆን ከቻለች የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ስርዓትንም ሊገዳደር የሚችል ተጽዕኖ በተለይም በአፍሪካ ልትፈጥር ስለምትችል በተለያዩ ምክንያቶች ሰላም የሌላትና ቁሳዊ እድገት ማምጣት የማትችል፣ በእነሱ እርዳታ ላይ ጥገኛ ሆና የምትኖር አገር እንድትሆን መሥራት ግድ በሏቸዋል፡፡ ስለሆነም፤ ኢትዮጵያ ጠንካራ መንግስት እንዳይኖራት አንዱ መንገድ ህዝቡ በማንነቱ እንዲከፋፈል ማድረግ ሲሆን ክፍፍሉ አገር ማፍረስ የሚችልበት ደረጃ እንዲደርስ የተጠቂና አጥቂ፣ የበዳይና ተበዳይ ትርክት መፍጠር ግድ ስለነበር በአገሩ ነጻነትና አንድነት ላይ ቁርጥ አቋም እንዳለው በጥናታቸው የለዩት አማራን በሌሎች በጠላትነት እንዲታይ መሥራት ግድ ነበርና አማራን ጨቋኝ፣ ሌላውን ህዝብ ደሞ ተጨቋኝ አድርጎ የሚያሳይ እኩይ ትርክት ተደረሰና ለተግባራዊነቱም ተሠራ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ለዓድዋ ጦርነት ድል ትልቅ ሚና የተጫወተችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተከርስቲያንን ለማዳከም ልክ አንደ አገሪቱ ሁሉ የመከፋፈል ሴራ ተዘጋጅቶ ሲሠራ ነበር፤ አሁንም ተጠናክሮ እየተሠራ ነው፡፡ ቋንቋ አንዱ መሳሪያ ተደርጎ እንደ ፖለቲካው ሁሉ ቤተ ክርስቲያን ውስጥም በጎሳ ለይተው በአማርኛና በግእዝ ብቻ መቀደስ የለበትም በሚል ሰበብ የተነሳው ሴራ አድጎና ጎልምሶ በጎሳ ማንነት ላይ የተመሠረቱ በርካታ ሲኖዶሶችን ለመፍጠርና ኦርቶዶክስን ለማፈራረስ ተሞከረ፡፡ ምንም እንኳ ኦርቶዶክስን ለማፍረስ እየሞከሩ የምናያቸው ዘረኛ ፖለቲከኞች ቢሆኑም የሴራው ዋና የዘንዶ ራስ ያለው በምዕራቡ ዓለም ነው፡፡ እዚህ የምናየው ደመ ነፍሳቸውን የሚሯሯጡ ፖለቲከኞች አውቀውና ሳያውቁም የጠላትን ዓላማ የሚያስፈጽሙ መሣሪያዎች ናቸው፡፡
ከላይ ያሉትን እንደ መግቢያ ካነሳን ቀጥሎ ደሞ የሰርቦችና የአማራን ሁኔታ እናነጻጽር፡-
- ሰርቦች በዩጎዝላቪያ ውስጥ ብዙ ቁጥር የነበራቸውና በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የሚገኙ ነበሩ፡፡ በጠንካራ ቤተሰባዊና ማኅበራዊ ትስስራቸው እንዲሁም ለነጻነታቸው በመዋጋትም የሚታወቅ ታሪክ አላቸው፡፡ ለምሳሌም ያህል ከኦቶማን ቱሪኮች እና ከጀርመን ናዚዎች ጋር በመዋጋት ለነጻነታቸው ብዙ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ ለነጻነታቸው ተዋጊ ስለሆኑም የኦቶማን ቱርኮችም ሆኑ የጀርመን ናዚዎች ብዙ ግድያና መፈናቀል አድርሰውባቸው ነበር፡፡ ሰርቦች ለዩጎዝላቪያ መመሥረት ትልቅ ሚና የነበራቸውና በአገሪቱ አንድነት ላይም ጠንካራ አቋም ስለነበራቸው ምዕራባውያን በአገሪቱ ላይና በአካባቢው እንዲኖራቸው ለሚፈልጉት የበላይነት እንቅፋት ተደርገው በመቆጠራቸው በምዕራባውያን የጠላትነት ዝርዝር ውስጥ ሊገቡ ችለዋል፡፡
አማራ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ቁጥር ያለው፤ በትክክል ቢቆጠር በብዛት አንደኛ ደረጃ ቁጥር ሊኖረው የሚችል ህዝብ ሲሆን አገሪቱን ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ለማቅናት በሙሉ ኢትዮጵያ በመዘዋወሩ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ይኖራል፡፡ ኢትዮጵያን ለመውረር የመጡ የውጭ ኃይሎችን በመዋጋት ጉልህ ሚና ነበረው፤ አሁንም አለው፡፡ እንዲሁም ቅኝ ገዢዎች ኢትዮጵያን ለመውረር ሲሞክሩ ከባድ ሽንፈት እንዲገጥማቸው አማራ ከፍተኛ ድርሻ ሰለነበረውና ኢትዮጵያን የፍቃዳቸው አዳሪ ለማድረግ በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ትልቅ እንቅፋት ሆኖ ስለታያቸው በጠላትነት መዝገባቸው ውስጥ በቀይ አድምቀው ጽፈውታል፡፡ ለዚህ አንዱ ማሳያ የሚሆነውም፤ ሩዶልፎ ግራዚያኒ በአብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም የመግደል ሙከራ ስለተደረገበት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ለ3 ቀናት በተፈጸመው የበቀል ዘመቻ ከሰላሳ ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንን ካስገደለ በኋላ ወደ ሮም በላከው የቴሌግራፍ መልዕክቱ ውስጥ በሦስት ቀናት ያደረገውን ሲገልጽ ህዝቡን ጥሩ ቅጣት እንደቀጣና በተለይም “የአማራ ሹማምንትን ልክ አስገብቼአቸዋለሁ” በማለት ጽፏል፡፡
- ምዕራባውያኑ በሰርቦች ላይ ጥቃት ሲጀምሩ፤ በዩጎዝላቪያ ውስጥ የበላይ እንደሆኑ፣ በሰርብ ብሔረተኝነት ተለክፈው በሌላው ዘር ላይ የበላይነት እንደሚሰማቸው፣ ወሳኝ የፖለቲካ ስልጣኖችን ጠቅልለው እንደያዙና በኢኮኖሚም የተሻለ ተጠቃሚ እንደሆኑ ወዘተ አሉታዊ የሐሰት ወሬዎችን በመንዛት በጋራ ለመኖር ፈቅደው ዩጎዝላቪያን የመሠረቱት የተለያዩ ዘሮች ሰርቦችን በጥርጣሬ ብሎም በጠላትነት ዐይን እንዲያዩዋቸው አደረጉ፡፡ በዚህም ምክንያት ሌላው ዘር በሰርቦች ላይ እንዲነሳ የሠሩት ሥራ ጊዜ ሲሄድ መሳካት ጀመረና ሌሎች ዘሮች ከሰርቦች ጋር በአንድ አገር ውስጥ አንኖርም እራሳችንን ችለን አገር እንሆናለን ብለው ተነሱ፡፡ በተለይም ከሰርቦች በመቀጠል ብዙ ቁጥር የነበራቸው የክሮሺያ መሪዎች ለእርቅም እንኳ አልመች ብለው የመገንጠል ሀሳብ በማራመዳቸውና የጥላቻ ቅስቀሳ ውስጥ በመግባታቸው በየክልሎች በሰርቦች ላይ ጥቃቶች ስለበዙ ዩጎዝላቪያ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ተዘፈቀች፡፡ ችግሩን ለመፍታት በተባበሩት መንግስታትና በወዳጅ አገሮች የተደረገው ጥረትም በአሜሪካና አጋሮቿ ሴራ ሳይሳካ ቀረና ግጭቱ ቀጠለ፡፡
ለዓመታት የቆየውና ብዙ ደም ያፋሰሰው የእርስ በርስ ጦርነት ሲጠናቀቅም በኢንዱስትሪ እድገቷ ትታወቅ የነበረችው፣ ትልቋና ከሶቬት ኅብረት መፈራረስ በኋላ በምስራቅ አውሮፓ ጠንካራ ሆና የወጣችው ዩጎዝላቪያ ፈራርሳ ሰባት ትንንሽና ምዕራባውያንን ሊገዳደሩ የማይችሉ አገሮች ተፈጠሩ፡፡ በጦርነቱም ሂደት ተገንጣይ ኃይሎችን በማሰልጠንና በማስታጠቅ ምዕራባውያን ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ሲሆን ወደ ጦርነቱ ማብቂያ ላይም በአሜሪካ የበላይነት በሚመራው በሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት (NATO) ስም ያውም የጸጥታው ምክር ቤት እንኳ ለጣልቃ-ገብነቱ ፍቃድ ሳይሰጥ ጦርነቱን ተቀላቅለው አገሪቱን በተለይም የአሁኗ ሰርቢያ ያለችበትን ምድር በአየር ጥቃት ብዙ ውድመት አደረሱበት፡፡
የጣልቃ-ገብነቱ ዓላማ ዩጎዝላቪያን ከመበታተን በተጨማሪ ሰርቢያን ማፈራረስና ማውደምም ሰለነበር የኔቶ የጦር ጄቶች ኢላማ የጦር ሰፈሮች ብቻ ሳይሆኑ እንደ ድልድይ እና መንገዶች የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶች ጭምር ነበሩ፡፡ ከጦርነቱ ማብቃት በኋላም የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ የመጨረሻ መሪ የነበሩትና ከሰርብ ዘር የተወለዱት ስሎቦዳን ሚሎሶቪች (Slobodan Milosevic) በበቀለኛ ጠላቶቻቸው ምዕራባውያን ተይዘው በእነሱ በሚዘወረውና ዘሄግ በሚገኘው ዓለምአቀፍ ፍ/ቤት ቀርበው ከአምስት ዓመታት በላይ ያለምንም እልባት በቀጠለ የተንዛዛ የክርክር ሂደት ውስጥ ከቆዩ በኋላ በእስር ቤት ሳሉ እስካሁንም መግባባት ላይ ባልተደረሰበትና ከጀርባው ብዙ የሴራ ትርክቶች በበዙበት ሁኔታ በእስር ቤት ሳሉ ሞተዋል፡፡
አማራ ምንም እንኳ አንዳንዶች በቋንቋው እየተናገሩና በባህሉ እየደመቁበት “አማራ የሚባል ህዝብ የለም” ሲሉ ቢሰሙም፤ አማራ ከአገር ማቅናት ጀምሮ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በማስጠበቅ ጭምር የብዙ ዓመታት ታሪክ ያለው ህዝብ ሲሆን በፊትም አሁንም በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ጠንካራና የማይለዋወጥ ወጥ አቋም ያለው፤ አኩሪ የሆኑና የኢትዮጵያ መገለጫ እስከመሆን የደረሱ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶችም ባለቤት ነው፡፡ ይህ የሚያኮራ ጠንካራ ማንነቱና የአገር ፍቅሩ ምዕራባውያን በአፍሪካ ቀንድና በመላው አፍሪካ እንዲኖራቸው ለሚፈልጉት ሚናና የበላይነት እንቅፋት ተደርጎ ተቆጠረ፡፡ በዚህ ምክንያትም የአማራን ዘር ለማጥቃት ልክ በዩጎዝላቪያ በሰርቦች ላይ እንዳደረጉት ሁሉ፤ ኢትዮጵያ በአማራ የበላይነት ተጽእኖ ሥር የወደቀች እንደሆነች፣ አማራ ሌላውን ዘር እየጨቆነ እንደነበር፣ ሌላውን ዘር የሚንቅ ትምክህተኛ እንደሆነ፣ በኢትዮጵያ ውስጥም በኢኮኖሚ ልዩ ተጠቃሚ እንደሆነና ሌሎችም መሰል የሐሰትና የጥላቻ ትርክቶችን በማስፋፋት ለጥቃታቸው ዒላማ እንዲሆን አመቻቹት፡፡ ለዚህ ዓላማቸው መፈጸምም ከቡችላነቱ ጀምሮ አቅፈውና ደግፈው ያሳደጉትን፤ በመጨረሻም ለስልጣን ያበቁትን ሕወሓትንና የግብር ልጆቹን የኦሮሞ ጽንፈኛ መሪዎችን እየተጠቀሙባቸው ነው፡፡
ሕወሓት በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲኖረው ለሚፈልገው የበላይነት ይገዳደረኛል ብሎ የሚፈራውና አምርሮ የሚጠላውን የአማራን ህዝብ ለማጥቃት ምቹ ሁኔታ ስለተፈጠረለት ትርክታቸውን ለማራመድና ለማስፈጸም ምንም ሳያመነታ ተቀበለ፡፡ ከዚያም በጫካ ሽፍታ እያለ ጀምሮ ሲነድፍ የቆየውን አማራውንና ኦርቶዶክስን የማጥፋት የሴራ እቅዱን እውን ለማድረግ ስልጣን እንደጨበጠ ሥራውን ጀመረ፡፡ እናም አማራን ከተቻለ ዘሩን ማጥፋት፣ ይህ ካልተቻለ ደግሞ ከስልጣንና ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዲገለል፣ የራሱን እድል ጨምሮ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የመወሰን ምንም ሚና እንዳይኖረው በማድረግ ማዳከም የሚለው ውጥኑን አጠናክሮ ሲተገብር ነበር፡፡ ከዓመታት በኋላም ዘሩን የማጥፋት እቅዳቸው ባይሳካም የማዳከም እቅዳቸው እንደሠራ ያመኑ አንዳንድ የሕወሓት ባለስልጣናት በግልጽና በአደባባይ “አማራን እንዳይነሳ አድርገን አርቀን ቆፍረን ቀብረነዋል” እና “አማራን ከእግራችን በታች ጥለን እንደ ሲጋራ ተርኩሰነዋል” የመሳሰሉ የእብሪት ንግግሮችንም አድርገው ያውቃሉ፡፡ ሕወሓቶች ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንንም ለማጥፋት በሠሩት እኩይ ሥራ ምክንያት አሁን ላለችበት ውስብስብ ችግር ያበቃትን የመርዝ ፍሬ ዘርተውባታል፡፡ አሁን ደሞ የኦሮሞ ዘረኞች በተራቸው አማራን እና የኦርቶዶክሰ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ከተቻለ ለማጥፋት ካልተቻለ ደሞ ለማዳከም ከዚህ ቀደም ከነበረውና ከተደረገው በከፋ መልኩ ዘመቻ ከፍተው በአምስት ዓመታት ውስጥ ሚሊዮኖች ላይ ግድያ፣ ማፈናቀል፣ ንብረትን መዝረፍና ሌሎች ከባድ ወንጀሎችን ፈጽመዋል፣ እየፈጸሙም ናቸው፡፡ እነሱ “ክልልህ” ብለው ከወሰኑለት የእስር ቤት ውጪ የሚኖር አማራ ላይ ተጠያቂነት የሌለበት ብዙ በደል ከፈጸሙ በኋላ አሁን ደሞ “ክልሉ” ባሉት ውስጥ የሚኖረው አማራን ለማጥፋት የክተት ዘመቻ አውጀዋል፡፡
- የምዕራባውያን ጸረ-ሰርቦች ትርክት ፍሬ ማፍራት ሲጀምር ከሰርቢያ ክልል ውጪ ያሉ የሰርብ ዘሮች ላይ ጥቃቶች ተስፋፉ፣ ብዙዎችም ሕይወታቸውንና ንብረታቸውን አጡ፣ ከመኖሪያቸው ተፈናቀሉ፡፡ በጊዜው ሌሎች ዘሮች የሰርብ ተወላጅ በነበሩት ሚሎሶቪች አስተዳደር ቅሬታ ሲሰማቸውና ሲቆጡ በቅርባቸው ያሉ ሰርቦችን ያጠቁ ነበር፡፡
በተመሳሳይም በኢትዮጵያ ውስጥ በሕወሓት የበላይነት ይዘወር በነበረው ኢህአዴግ የአገዛዝ ዘመንና አሁን በኦሮሞዎች የተረኝነት ጊዜም ምዕራባውያን ትርክታቸው ፍሬ አፍርቶ አማራው ቀድሞ በነበሩት ስርዓቶች እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንዳልተጨቆነ ሁሉ እንደ ጠላት እንዲቆጠር በተሠራው ሰፊ ቅስቀሳ ምክንያት ብዙ ቁጥር ያላቸው ንጹሃን አማራዎች በሕወሓትና አሁን ደሞ በብልጽግና ዘመን በየክልሉ በሚኖሩ አጋሮቻቸው በተደረገ የተቀናጀ ጥቃት ተገድለዋል፣ ተወልደው ካደጉበት አካባቢ ተፈናቅለዋል፣ ንብረታቸውን ተቀምተዋል፣ ወድሟል… ወዘተ፡፡ እንዲያውም በአንድ አጋጣሚ በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አንደበት ሲነገር እንደሰማነው ጉራ ፋርዳ ከሚባል አካባቢ አማራዎችን ለማፈናቀል ሲባል “ደን ጨፍጭፈዋል” የሚል ምክንያት ተጠቅሶ ለዘመናት ቤተሰብና ሀብት አፍርተው ከኖሩበት አገር እንደተፈናቀሉ ታሪክ መዝግቦታል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ያውም በአማራ ላይ ካልሆነ በቀር ደን የጨፈጨፈ ሰው ደን መጨፍጨፍ በሚያስቀጣው ሕግ መሠረት ይቀጣል እንጂ ከቀዬው እንዲባረር ተደርጎ አያውቅም፡፡ እንዲያውም የአሁን ባለጊዜዎች ዛፍ ሳይሆን በጠራራ ጸሓይ አማራን እየጨፈጨፉ እንኳን ከቀያቸው ሊባረሩ የገላመጣቸው የለም፡፡
በተጨማሪም መንግስት የፖለቲካ ትኩሳት ሲገጥመው ትኩሳቱን ለማብረድ፣ የህዝብ ጥያቄ ተነስቶበት ሲወጠር የትኩረት አቅጣጫን ለማስቀሰየር አማራ መስዋዕት ሲደረግ ኖሯል፡፡ በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ቡድኖች “ጥያቄያችን አልተመለሰም” ብለው በመንግስት ላይ ሲቆጡ በቅርባቸው ያለውን አማራና ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖችን በጅምላ በመግደል ንዴታቸውን ሲወጡ ነበር አሁንም እያደረጉት ነው፤ ወደፊትም ተመሳሳይ እንደማይሆን ዋስትና የለም፡፡ አዲስ ጀማሪ ፖለቲከኛ ህዝብ ፊት ቀርቦ ንግግር ማድረግ ሲጀምርም “የፖለቲካ አዋቂነት መለኪያውና ተቀባይነት ማግኛው የመጀመሪያው ደረጃ አማራን መስደብ ነው” የሚል ሕግ ያለ እስኪመስል ድረስ አማራ የብዙዎች ያልተገረዘና ጎልዳፋ አንደበት መፍቻ ሆኗል፡፡ ብዙ ፖለቲከኞች በአደባባይ በሚያደርጉት ንግግር አማራ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም በግልጽ ሲሰብኩ ያስቆማቸው የለም፤ በንግግራቸው ምክንያትም አማራው ሲገደል፣ ሲፈናቀል፣ ንብረቱ ሲወድምና ሲዘረፍ ተጠያቂ አልተደረጉም፡፡ በመሆኑም እጅግ ብዙ አማራዎች ደማቸው የውሻ ደም ሆኖ ቀርቷል፡፡
- ምዕራባውያን ከላይ እንዳየነው በአማራ ላይ ሲደረግ የነበረንና እየተደረገ ያለውን እንዳላወገዙ ሁሉ በዩጎዝላቪያ የእርስ በርስ ጦርነት ጊዜና ከጦርነቱ በፊት በሰርቦች ላይ የሚደረጉ ጥቃቶችንና ወንጀሎችን በዝምታ ሲያልፉ ቆይተዋል፡፡ ሰርቦች ሌላው ዘር ላይ ጉዳት ሲያደርሱ ግን ከፍተኛ የሆነ ውግዘትና ለፍርድ ይቅረቡ ድምጽ ከምዕራባውያን ይሰማ የነበረ ሲሆን በእነሱ ላይ የሚፈጸም ማንኛውም ግፍና ወንጀል ግን እንዳይሰማ ይታፈናል፤ ቢሰማም የተለያዩ ምክንያቶች ይሰጡና ሰርቦች ፍትሕ እንዲያጡ ይደረግ ነበር፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው በክሮሺያ ክልል ውስጥ ለሚኖሩ ብዙ የሰርብ ተወላጆች ሞት ተጠርጥረው የነበሩ ሁለት የክሮሺያ ጄኔራሎችን እ.አ.አ. በ1995 በሄግየሚገኘውና በምዕራባውያን የሚዘወረው ዓለምአቀፍ ፍርድ ቤት የጄኔራሎቹን ድርጊት ከመረመረ በኋላ “ለነጻነት የተደረገ ትግል እንጂ ወንጀል አይደለም” ሲል በነጻ በማሰናበት አድሏዊ የሆነ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ እዚህ ላይ ሕወሓት አማራ ክልል ዘልቆ ገብቶ ብዙ ወንጀሎችን ሲፈጽም ምዕራባውያን የሕወሓት ድርጊት ወንጀል ሳይሆን “እራስን ከከበባ ነጻ የማድረግ ትግል ነው” ማለታቸው የሚታወስ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ቦስኒያ ውስጥ ሰርቦች የቦስኒያ ሙስሊሞችን ጨፈጨፉ ተብለው ሲከሰሱና መሪያቸው የነበሩት ራዶቫን ካራዲች (Radovan Karadzic) እና የጦር አዛዣቸው የነበሩት ራትኮ ሚላዲች (Ratko Mladic) ተይዘው በዓለምአቀፍ ፍ/ቤት እድሜ ይፍታህ ሲፈረድባቸው በቦስኒያ ውስጥ ይኖሩ ለነበሩ ሰርቦች ሞት ተጠያቂ የተደረገ እንድም የሌላ ዘር ተወላጅ ስለመኖሩ ምንም መረጃ የለም፡፡ በተጨማሪም የጦር ወንጀሎችን ለመዳኘት ከተቋቋሙ ፍ/ቤቶች የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ሰርቦችን ጉዳይ እንደተመለከተው ፍ/ቤት ፍርደ-ገምድል ችሎት ላይገኝ ይችላል፡፡ በዚህ ችሎት በፊት ያልነበሩና አዲስ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፍቺዎች ተፈጥረዋል፡፡ ዳኞቹ የተፈጸመ ድርጊት ቢያጡ እንኳ ሀሳብ እንደ ዘር ማጥፋት የተቆጠረበት ችሎት ነበር፡፡ ይህም ሰርቦችን ለመበቀል ምዕራባውያን የሄዱትን ርቀት የሚያስረዳ ነው፡፡ ይህ የምዕራባውያን ድርጊት የሚያረጋግጠው ወደ ፊት የሕወሓትና የብልጽግና ወንጀለኞች በዓለምአቀፍ ፍ/ቤት እንዲጠየቁ ለማድረግ ቢሞከር ዋጋ ቢስ ሊሆን እንደሚችልና ለፍርድ መቅረብ ካለባቸውም ኢትዮጵያ ውስጥ ሊሆን እንደሚገባ ነው፡፡ በተጨማሪም አሁን ለአማራው የሚታገሉና የሚሟገቱ ግለሰቦች፣ የፋኖ እና ልዩ ኃይል መሪዎች፣ እንዲሁም የድርጅት መሪዎች ወደፊት ምዕራባውያን በጦር ወንጀለኝነትና በዘር ማጥፋት የሐሰት ውንጀላ ሊያሳድዷቸው እንደሚችሉ ሊጠብቁና እራሳቸውን ለፈተናው ሊያዘጋጁ ይገባል፡፡
በሕወሓት የአገዛዝ ዘመን አማራ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሰበብ አየተፈለገ ተወልዶ ካደገበት ቀዬ ሲባረር፤ ታፍኖ እየተወሰደ ሲገደል ወይም ደብዛው ሲጠፋ እያወቁ ምንም አላሉም፡፡ አጠቃላይ ሕወሓት አገሪቱን በገዛበት 27 ዓመታት በሚሊዮን የሚቆጠሩ አማራዎች ተገድለውና ያለምንም ፍንጭ ደብዛቸው ጠፍቶ ከኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥር ውስጥ ለዘለቄታው ተቀንሰዋል፡፡ የአማራ ወንዶች በየሰበቡ እስር ቤት እንዲገቡ ተደርጎ ዘራቸው እንዳይቀጥል ሲኮላሹ፣ የአማራ ሴቶች እንዳይወልዱም በወሊድ መከላከያ፣ በክትባትና በህክምና ሰበብ መካን የሚያደርግ መድኃኒት እየተሰጣቸው መዋቅራዊ በሆነ ሴራ የጸጥታ ዘር ማጥፋት (Silent Genocide) ሲፈጸምባቸው እንደኖረ እያወቁ ምንም አላሉም፡፡ አሁንም የኦሮሞ ጽንፈኞች በሚቆጣጠሩት በብልጽግና ዘመን እነዚህና ከላይ የተጠቀሱት ግፍና ወንጀሎ በአማራ ላይ ሲፈጸሙ ምዕራባውያን አንዲትም የውግዘት ቃል ወጥቷቸው አያውቅም፡፡ ይልቁንም ኢትዮጵያ ውስጥ የጤና ሚኒስትር በነበረ ጊዜ አማራዎች ላይ ለተፈጸመው የዘር ማጥፋት አንዱ ተጠያቂ ለሆነው ቴዎድሮስ አድሃኖም የዓለም የጤና ድርጅት ኃላፊ በማድረግ ለዓላማቸው መሳካት ለተጫወተው ጉልህ ሚና ሽልማት አበርክተውለታል፤ አሁን ወንጀል እየፈጸሙ ያሉትም ጊዜው ደረሶ ወንበራቸው ሲከዳቸው ተመሳሳይ ሽልማት ይጠብቃቸው እንደሆን እንጂ ለፍርድ ይቀርባሉ ብሎ ማመን አይቻልም፡፡
- ይህ በእንዲህ እያለ ሕወሓት በ2010 ዓ.ም. ከስልጣኑ ከተወገደ በኋላ በኃይል ወደ ስልጣን ለመመለስ ባደረገው ጥረት በ2013 ዓ.ም. በመንግስት የሰሜን እዝ ጦር ላይ ጥቃት ካደረሰ በኋላ (በዚህ ጥቃትም የአማራ ዘር የሆኑ ወታደሮች ላይ እየተመረጡ የተፈጸመው አረመኔያዊ ወንጀል የሚታወስ ነው) ወደ አማራም ክልል በመሄድ ለማጥቃት ሲንቀሳቀስ ሽንፈት ገጥሞት ካፈገፈገ በኋላ የአማራ ልዩ ኃይል በመንግስት ውሳኔ ለመከላከያ ሰራዊቱ እገዛ እያደረገ ወደ ትግራይ ክልል ሲገባ ምዕራባውያን አገሮች በመገናኛ ብዙሃኖቻቸው “አማራው ደም ለማፍሰስና ለብቀላ ወደ ትግራይ ገባ”በማለት ዘግበዋል (ዘቴሌግራፍ በጊዜው የጻፈውን ለምሳሌ ማየት ይቻላል)፡፡ እንዲሁም በገለልተኛ ወገን ምንም ዓይነት ምርመራ እና ማጣራት ሳይደረግ የአማራ ሰራዊት ትግራይ ክልል ውስጥ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል ሲሉም በሰፊው ዘግበዋል፡፡ ሆኖም ግን አማራውን በወነጀሉበት በተመሳሳይ ጊዜ በትግራይ ክልል ውስጥ በማይካድራ በሕወሓት የገዳይ ቡድን (ሳምሪ) በአማራ ተወላጆች ላይ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት ለመዘገብ የአየር ሰዓታቸው ጊዜ አልነበረውም፡፡
በመቀጠልም፤ የኢትዮጵያ መንግስት ሠራዊት ከትግራይ ክልል ከወጣ በኋላ የሕወሓት ወታደሮች የአማራን ክልል ብዙ ቦታዎች በመውረር ብዙ አሰቃቂና ለመስማት የሚከብዱ ወንጀሎችን ሲፈጽሙ ምዕራባውያን በዝምታ አልፈዋል፡፡ ለወራት በቀጠለው ጥቃትም የሰው ልጅ ሊያደርጋቸው ቀርቶ ሊያስባቸው ይችላሉ ተብለው የማይገመቱ፤ በዓለም ላይ የታወቁ ጸረ-ሰውና ጸረ-ማኅበረሰብ ተብለው የተፈረጁ ቡድኖች እንኳ ፈጸሙት ተብሎ ያልተሰማ አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ታቦተ ጽዮን ካለችበት ምድር በበቀሉ አረማውያን በአማራ ህዝብ ላይ ሲፈጸምም ለይምሰል እንኳ ሊያወግዙ አልሞከሩም፡፡
አማራ በሕወሓትም ሆነ በብልጽግና ጊዜም እንደሚታየው በወለጋ፣ በሸዋና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የዘር ማጥፋትና ማጽዳት ሲፈጸምበት አላወገዙም፡፡ ጥቃቱ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ባሉ ባለሥልጣናትና በሕዝቡ ውስጥ ተሰሚነት ባላቸው ሰዎች ጭምር በመናበብና በተቀናጀ መልኩ ስለሚፈጸም “የገዳ ስርዓታችን እንኳን ለኢትዮጵያ ለዓለም ጭምር የሚተረፍ አብሮ የመኖርና የፍቅር ምሳሌ ስለሆነ በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ሊካተት ይገባል” በማለት ሲደሰኩሩ የሚኖሩት “አባ ገዳ” ተብዬዎች እንኳ በይፋ ወጥተው ጭፍጨፋውን ሲያወግዙ አልታዩም አልተደመጡም፤ ከነሱም አይጠበቅም፡፡ ምክንያቱም ልጅ የሚመስለው አሳዳጊውን ነው፤ ይህንን ጭካኔና ኢሰብዓዊ ድርጊት ለመፈጸም ያበቃቸውን የሐሰት ትርክትና ስነ-ልቦና አስታጥቀው ያሳደጓቸውም እነሱ ናቸው፡፡ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችም አልፎ አልፎ በዘገባቸው ለይምሰል ያህል ከማውገዝ ያለፈ በተግባር ምንም ሲያደርጉ አይታዩም፡፡ ድርጊቱ የተፈጸመው በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኙ ሌሎች ዘሮች ላይ በአማራ ቢሆን ኖሮ ግን ምን ሊሉና ሊያደርጉ እንደሚችሉ መገመት አይከብድም፡፡ ይህ ሁሉ ዝምታቸው በአማራ ላይ ያላቸውን ጥላቻና የቆፈሩለትን የጥፋት ጉድጓድ ጥልቀት የሚያሳይ ነው፡፡
- እንደገና ወደ ንጽጽራችን ስንመለስ፤ ሰርቦችን ሌላው ዘር እንዲነሳባቸው በማድረግና በአገሪቱ ጦርነት በማስነሳት በመጨረሻም የዩጎዝላቪያን መፈራረስ ያሳኩት ምዕራባውያን የአማራን ሕዝብ ሌሎች እንደ ጠላት እንዲያዩት፤ ሁኔታው አሁን ካለው ሲከፋም አማራ እራሱን ለመከለከል በሚያደርገው እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ ውስጥ የለየለት የእርስ በርስ ጦርነት ማስነሳት ነው፡፡ አማራ ለነጻነቱና ለህልውናው ሲዋጋም ብዙ ቀውስ ይከተላል ግን ጦርነቱ በቀላሉ አሸናፊ ስለማይኖረው ለረጅም ጊዜ የሚቆየውን ቀውስ ለማስቆም “ሰላም አስከባሪ” በመላክ ልክ ቦስኒያ፣ ኮሶቮ እና ሌሎች ክልሎችም ገብተው ግዛቶቹን እንደገነጠሏቸው የኢትዮጵያንም ክልሎች ወደ ትንንሽ አገርነት በመቀየር ኢትዮጵያን እንደ ዩጎዝላቪያ ለመበታተንና ደካማ የእነሱ ፈቃድ ፈጻሚ የሆኑ አገራትን ለመፍጠር እየሞከሩ ነው፡፡
- ምንም እንኳ ምዕራባውያን ኢትዮጵያን ለመበታተን እየሄዱበት ያለው መንገድ ዩጎዝላቪያን ለማፍረስ ከተጠቀሙበት ስልት ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም ነገር ግን ውጤቱ እስካሁን ተመሳሳይ አልሆነላቸውም፤አይሆንላቸውም፡፡ ምክንያቱም ዩጎዝላቪያ እና ኢትዮጵያ ከአመሠራረታቸው ጀምሮ በርካታ ልዩነቶች ስላሏቸው ነው፡፡ ሆኖም ግን የአማራ ህዝብ ሲደረግበት የኖረውንና እየተደረገበት ያለውን እንዲሁም ሊደረግበት የታቀደውን ከውጭ አገር እስከ አገር ውስጥ የተሳሰረውን አደገኛ የጥፋት ሴራ በሚገባ በመገንዘብ እራሱን በተለያዩ በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ በሚመሠረቱ የተቀናጁ አደረጃጀቶች በማጠናከር በማንኛውም ጊዜ የሚሰነዘርበትን ጥቃት ለመመከት እንዲሁም ለማጥቃት በሚያስችለው ልክ ዝግጁ መሆን አለበት፡፡
- በዩጎዝላቪያ ውስጥ በሰርቦች ላይ ይፈጸም የነበረውን ሴራና ወንጀል የተቃወመ ሌላ ዘር እንደሌለ ሁሉ በኢትዮጵያ ውስጥም በአማራ ላይ ከላይ የተጠቀሱትና እስካሁንም ተጠናክረው የቀጠሉ ወንጀሎች ለብዙ ዓመታት ሲፈጸሙበት በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ሌሎች ዘሮች “በአማራው ላይ የሚደረገው ጥቃት ይቁም ፍትሕም ይሰጠው” ብሎ የጮኸለት የለም፤ ወደ ፊትም ላይኖር ይችላል፡፡ አማራዎች ተፈናቅለው ባሉበትም የት ወደቁ ብሎ ሊጠይቃቸው የፈቀደ የለም፡፡ ምክንያቱም የተሠራበት የሐሰት ትርክት ሌላው ዘር ሁሉ በአማራው ሞት እንዲሳለቅና ምንም እንዳይመስለው የሚያደርግ፤ አማራ በየቦታው ሲገደል ሌላው ዘር “ይበላቸው” እንዲል የሚያደርግ ነው፡፡ አማራን ጨምሮ የአገሪቱን ህዝብ ሁሉ እመራለሁ ብሎ ስልጣን ላይ የተቀመጠው የ”ብልጽግና” ድርጅት አማራን እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ የመጠበቅ ግዴታ ቢኖርበትም ግዴታውን ለመወጣት ፍቃደኛ እንዳልሆነ ለዓመታት አሳይቷል፡፡ አሁን እንደሚታየውም አማራ ላይ በተፈጸሙና እየተፈጸሙ ባሉት ወንጀሎች መንግስት እጁ እንዳለበት ግልጽ ሆኗል፤ ብልጽግና (በተለይም የኦሮሚያ) እና ኦነግ (ኦነግ ሸኔ) የአንድ ሣንቲም ግልባጭ እንደሆኑ ግልጽ ሆኗል፡፡ በአዲስ አበባ እና በሌሎችም የኦሮሚያ ክልል ውስጥ ባሉ ከተሞች “ለልማት” እና ለሌሎችም ሰበቦች በተለይ የአማራ ቤቶች እየተመረጡ እየፈረሱና እየተዘረፉ ነው፡፡ በዚህም የብልጽግና መንግስት አማራን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት እየሠራ ያለ ጠላት እንደሆነ ግልጽ ሆኗል፡፡ አማራ በግፍ ሲጨፈጨፍ የአገሪቱ መሪዎች ለይመሰል እንኳ ሲያዝኑ አይታዩም፡፡ ይልቁንም ጥላ እንዲሆናቸው በሞቱት ላይ ዛፍ እንተክላለን፣ የራባቸው ሰዎች ምግብ ቢያጡ እንኳ ጥላ ስር ተቀምጠው እንዲራቡ ዛፍ እንትከልላቸው እያሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሳለቁ ተደምጠዋል፡፡ መንግስት የተፈናቀሉትን ለጊዜው የመርዳት፣ በዘላቂነት ደግሞ የማቋቋም ግዴታ ቢኖርበትም ነገር ግን ባለስልጣኖች እንኳን ሊያቋቁሙት ቤቱን አፍርሰው ያፈናቀሉት አማራ በአዲስ አበባና በአካባቢው ቤት ተከራይቶ እንኳ እንዳይኖር በማድረግ ግልጽ የሆነ የዘር ማጽዳት እየፈጸሙበት ነው፡፡
አማራ ለአገሩ ብዙ የሠራ ቢሆንም አመድ አፋሽ ሆኖ ኖሯል፡፡ ለአገሩ በከፈለው መስዋዕትነት ልክ ሊያከብሩት ፍቃደኛ ባይሆኑ እንኳ ሌሎች ኢትዮጵያውያን እንደ ጠላት ሊያዩት ባልተገባ፣ ሊያጠፉትም ባልተነሱ ነበር፡፡ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ተነስቶ በነበረው ጦርነትም መስዋዕትነት ከፍሎ አገርን እና መንግስትን ከውድቀት ቢያድንም ነገር ግን ያዳናቸው ባለ ሥልጣኖች መልሰው ጠላት አድርገውት ያጎረሰ እጁን እየነከሱት ነው፡፡ አሁን ደሞ ይባስ ብለው ኢትዮጵያን ሊያፈርስ ሞክሮ ካልተሳካለት የሕወሓት ቡድን ጋር ወዳጅነት በመፍጠር በአማራ ህዝብ ላይ የጋራ የጥፋት ዘመቻ ከፍተዋል፡፡
- አሁን በአማራው ላይ የሚፈጸመው ግፍ ጽዋው ሞልቶ ስለፈሰሰ ለህልውናው ለመታገል ቆርጧል፡፡ አማራ ለህልውናው እራሱ ካልታገለ ከፈጣሪው ሌላ ማንም ሊረዳው እንደማይችል ቁርጡን አውቆ ጠላቱን ተዋግቶ በማሸነፍ በደምና በአጥንቱ በገነባት ሙሉ ኢትዮጵያ በእኩልነትና በነጻነት የመኖር መብቱን ለማስከበር ተነስቷል፡፡ የተጀመረው ትግልም ከዳር ሳይደርስና አማራ ህልውናውን በማያጠራጥር ሁኔታ እስከሚያረጋግጥ የማይቆም መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም ትግሉ ጫፍ ሳይደርስ በምንምና በማንም ምክንያት ከተቋረጠ ወይም ከተጨናገፈ አማራን ጠላቶቹ ሊያዳክሙት ሳይሆን ከምድረ ገጽ ሊያጠፉት ወይም አገር አልባ ሊያደርጉት ስለተነሱ የማይታረም ስህተት ይሆናል፡፡ በትግሉ ሂደት ምንም ወይም የጎላ ስህተት ላለመሥራትም ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡ እርቅና ድርድር በሚባሉ ማዘናጊያዎች መታለልንም በአማራው ላይ የተጋረጠው ግልጽና ቅርብ የህልውና አደጋ አይፈቅድም፡፡ የተጀመረው የትግል ቅንጅት ቀጥሎ ሠራዊቱን ወጥ በሆነና በተናበበ መልኩ በስነ-ምግባር አንጾ በመምራት ለድል እንዲበቃ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ማድረግ ሲቻል ለራሱና ለአገሩ ህልውና የሚያስብ ሌላው ኢትዮጵያዊም ከአማራ ጎን እንዲሰለፍ በማድረግ ትግሉን ባነሰ ጊዜና መስዋዕትነት ከግቡ ማድረስ ይቻላል፡፡
በመጨረሻም፤ ይህ ሁሉ በአማራ ላይ በመንግስትና መንግስታዊ ባልሆኑ፣ በውጪና በአገር ውስጥ አካላት የሚፈጸም ግፍና ወንጀል በአጋጣሚ የሆነ ሳይሆን በአማራ ላይ የተጠነሰሰ የረጅም ጊዜ የምዕራባውያን ሴራ ውጤት ነው፤ መዳረሻ ዓላማውም ኢትዮጵያን ማፍረስ ወይም ደካማ ማድረግ ነው፡፡ ወደ ፊትም አማራ እጅ የሰጠና የተንበረከከ እስከሚመስላቸው ድረስ መቀጠሉ አይቀሬ ነው፡፡ ነገር ግን አማራ እንደ አባቶቹ ለጠላቶቹ እጅ አይሰጥም አይንበረከክም፤ ጠላቶቹ እንደተመኙለትም አገር አልባ አይሆንም፡፡ ይልቁንም ለሺህ ዓመታት ከውስጥና ከውጪ ጠላቶቹ ጋራ ተዋግቶ ነጻነቱን በክንዱ እምዳስከበረ አሁንም ህልውናውንና ነጻነቱን በጀግንነቱ ያስከብራል፤ በጠላቶቹ መቃብር ላይም የራሱንና የኢትዮጵያን ሕልውና ያጸናል፡፡
ድል ለአማራና ለኢትዮጵያ! ሽንፈትና ሞት ለአማራና ለኢትዮጵያ ጠላቶች!
ዳግማዊ ፍሠሓ፡ dagmawi.fisseha443@gmail.com