ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
መስከረም 4፣ 2023
መጥፎም ሆነ ጥሩ ስርዓትን የሚፈጥሩ ሰዎች ናቸው። ስርዓት ከላይ ዱብ የሚል ነገር ሳይሆን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ አንድ ህዝብ ወይም ደግሞ የፖለቲካ ስልጣንን የያዙ የገዢ መደቦች የሚፈጥሩት ወይም የሚመሰርቱት ነው። በአጠቃላይ ሲታይ, ህብረተሰብአዊ ስርዓት፣ ማለትም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊና አንድን ህብረተሰብ በሚያያዙት የረቀቁ ነገሮች የሚገለጽ ስርዓት የብዙ መቶ ዓመታት የሂደት ውጤት ነው። እንደ አገሮችና እንደዕውቀት ማደግና መዳበር አንዳንድ ስርዓቶችና፣ ስርዓቶችን የሚገልጹ የከተማ አገነባቦች፣ የቤተክርስቲያን አሰራሮች፣ የገበያ አዳረሾችና ሌሎችም በረቀቀና ባልረቀቀ መልክ የሚታዩና የማይታዩ ነገሮች ሌፈጠሩ የሚችሉት የሰው የማሰብ ኃይል ሲዳብርና አዳዲስ ዕውቀቶችን ሲያፈልቅ ብቻ ነው። ሰለሆነም በህብረተሰብ ግንባታ ሂደት ውስጥ ማንኛውም ስርዓት በየጊዜው መታደስ አለበት። ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፉ የአኗኗር ስልቶች፣ የአመራረት ዘዴዎች፣ የአረጁ ተቋሟትና ሌሎችም ከጊዜው ሁኔታና እየጨመረ ከሚመጣ የህዝብ ቁጥር ጋር ሊሄዱ የማይችሉ ወይም እየጨመረ የመጣ የህዝብ ቁጥርን ማስተናገድ የማይችሉ ከሆነ በአዲስና ውስጠ-ኃይል ባላቸው ተቋማት መተካት አለባቸው። አብዛኛውን ጊዜ ህብረተሰብአዊ ለውጥ ሊመጣና የተወሰነውም የህብረተሰብ ክፍል አስተሳሰብ ሊለወጥ ወይም ሊሻሻል የሚችለው ስልጣንን በጨበጡ የገዢ መደቦች አማካይነት ሳይሆን፣ ከስልጣን ውጭ ባሉና በተገለጸላቸው ኃይሎች አማካይነት ብቻ ነው። ከስልጣን ውጭ ያሉ ኃይሎች ለህብረተሰብአዊና ለፖለቲካ ግጭት ምክንያቶች የሆኑትን ነገሮች ጠጋ ብለው በመመርመር አንድ ህብረተሰብ በእንደዚህ ዐይነት ስርዓት ውስጥ መኖር እንደሌለበት በመገንዘብ በአገዛዙ ላይ ጫና ያደርጋሉ። አንድን አገዛዝ ሰፋ ባለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ በመወጠር መፈናፈኛ ያሳጡታል።
ከምዕራብ አውሮፓ የህብረተሰብ ለውጥና መሻሻል ታሪክ ስንነሳ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ብቻውን በራሱ በቂ አይደለም። በሌላ ወገን ግን የነቁና የተገለጸላቸው ኃይሎች መፈጠር በህዝቡ ውስጥ በሚካሄዱ የዕደ-ጥበብ ማደግ፣ የንግድ እንቅስቃሴ መስፋፋት፣ የከተማዎች በዕቅድ መሰራትና በዚያውም መጠንም ተፍ ተፍ የሚል የህብረሰብ ኃይል መፈጠር ብቅ ለሚሉ አዳዲስ ምሁራን አድማሳቸውን ያሰፋላቻወል። የሚካሄደውንም ለውጥ ጠጋ ብለው በመመርመር የሰው ልጅ ውስጣዊ ኃይል እንዳለውና ከዚያም በላይ ርቆ እንደሚሄድ ይገነዘባሉ። ይህ ዐይነቱ የማቴሪያላዊ እንቅስቃሴ ለውጥ፣ በዕደ ጥበብ ዕድገትና በንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚሳተፉ ኃይሎች ብቅ ማለት በህብረተሰብ ውስጥም የፍጆታ አጠቃቀምን ባህርይ ይለውጣል። ይሁንና ግን የገዢ መደቦችም በአመራረት ስልት መለወጥ፣ በከተማዎች ዕድገትና በንግድ እንቅስቃሴ ራሳቸውም ተጠቃሚ ቢሆኑም ካሉበት ወይም ከጨበጡት የፖለቲካ ስርዓት ባሻገር ማየት ይሳናቸዋል። በስልጣናቸው እየተዝናኑና እየተደሰቱ ህብረተስባቸውን ወይም ህዝባቸውን በኑሮው እንዲስሻሻል ከማገዝና ይልቅ ዕንቅፋት ይሆናሉ። አብዛኛዎችም በአዳዲስ መልክ ከሚፈልቁና ከሚዳብሩ ዕውቀቶች ርቀው ስለሚኖሩ ጭንቅላታቸውን ለማደስና ጥያቄም ለመጠየቅ ይሳናቸዋል። ለዚህም ነው በአውሮፓ ምድር ከአስራሶስተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የዕደ-ጥበብና የንግድ እንቅስቃሴ ቢታይም፣ ከዚያም በኋላ የተፈጥሮ ሳይንስና የፍልስፍና ዕውቀት ቢስፋፉም፣ ከሬናሳንስ በኋላ ደግሞ ሬፍሮሜሽን የሚባለው የሃይማኖት ተሃድሶ ከሞላ ጎደል ተግባራዊ ቢሆንም ዲስፖቲያዊ አገዛዞች ብቅ በማለት ህብረሰተብአዊ ለውጥ እንዳይመጣ እንቅፋት ለመሆን የበቁት። ለዚህም ነው በአውሮፓ ምድር ውስጥ ተደጋጋሚ ጦርነቶች ይከሰቱ የነበረው። ለዚህም ነው ሰላሳ ዓመት የፈጀ ጦርነት በፕሮቴስታንና በካቶሊክ የሃይማኖት ዕምነት ተከታዮችና ቄሶች መሀከል ጦርነት የተካሄደው።
በታሪክ ውስጥ እንደታየው አብዛኛውን ጊዜ ወይም ሙሉ በሙሉ ስልጣን ላይ የሚወጡ ወንዶች በመሆናቸው ከፓትሪያሪካላዊ ወይም ከበላይነት ስሜት ለመላቀቅ ይሳናቸዋል፤ ሌላውንም በእኩል ደረጃ ለማየት አይፈልጉም። በአገርም ውስጥ ሆነ በዓለምአቀፍ ደረጃ ለሚቀሰቀሱት ጦርነቶች መቶ በመቶ ዋናው ምክንያቶች ወንዶች ናቸው። ወንዶች ከፓትሪያሪካል አስተሳሰብ ለመላቀቅ ችግር ስላለባቸው ሴቶችንም ሆነ ሌላውን ኮሳሳ መስሎ የሚታየውን ሰው በዝቅተኛ ስሜት ነው የሚያዩት። ለምሳሌ በአንዳንድ የአውሮፓ አገሮች ሴቶች የመምረጥ መብት የተፈቀደላቸው በ1970ዎች መጀመሪያ ላይ በ20ኛው ክፍለ-ዘመን ነው። እንደ ጀርመን በመሳሰሉት አገሮች ደግሞ አንድ ሴት ስራ ለመስራት ከፈለገች ባለቤቷን ማስፈቀድ ነበረባት። እንደዚህ ዐይነቱ ኋላ-ቀር አስተሳሰብ ተግባራዊ ይደረግ የነበረው አብዛኛው የምዕራብ አውሮፓ አገሮች የኢንዱስትሪ አብዮትን ካካሄዱ በኋላ፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት በመሆን የራሳቸውን ህብረተሰብ ብቻ ሳይሆን የዓለምንም ህዝብ ዕድል በሚደነግጉበት በ20ኛውና በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ነው። አሁንም ቢሆን በሴቶች ላይ ያለው ጾታዊና ሌሎች ጥቃቶችም በተለያዩ የካፒታሊስት አገሮች የተለመደ ነው። ይህንን ሀቅ ስንመለከት አንዳንድ ወንዶች የአዕምሮ ወይም የአስተሳሰብ ለውጥ ችግር እንዳለባቸው፣ ወይም ደግሞ የጭንቅላታቸው መዳበር (The Evolution of the Mind) ሂደቱን ወይም ዕድገቱን እንዳላጠናቀቀ መገንዘብ እንችላለን። ይህ የጌታና የሎሌ አስተሳሰብ ባህርይ አሁንም ቢሆን ያለና በተለይም በአብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ለሚካሄደው የውክልና ጦርነትና፣ በተለያዩ የማዕከለኛውና የደቡብ አሜሪካ አገሮች ለሚታየው በልዩ ልዩ መልኮች ለሚገለጸው ህብረተሰብአዊ ቀውስ ዋናው ምንያት ነው። በተለያዩ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ባሉ የፖለቲካ፣ የሚሊተሪ፣ የስለላ፣ የኢኮኖሚ ኤሊቶችና በካፒታሊስት አገሮች ኤሊቶች መሀከል የጥቅም ትስስር ምክንያት የተነሳ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉና በተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ የተቋምና የኢኮኖሚ መሻሻል እንዳይመጣ ዕንቅፋት ይሆናሉ። እንደኛ ባለው አገር ስልጣንን የጨበጠውን የፖለቲካ ኤሊት፣ የሚሊተሪ፣ የስለላና የኢኮኖሚ ኤሊት በጥቅም በማባለግ ጠቅላላው ህብረተሰብ በማህበራዊ፣ በባህላዊ፣ በስነ-ልቦናዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በኢኮሎጂ ቀውስ እንዲናጋ በማድረግ ከ90% በላይ የሚሆነው ህዝብ እንደ እንስሳ፣ ወይም ከእንስሳ በታች እንዲኖር ያስገድዱታል። ከቆሻሻ ኑሮ ጋር እንዲለማመድና ኑሮውም እንዲጨልም ያስገድዱታል። ስልጣንም ላይ የሚወጡ ኃሎች ይህንንም ያህል በዕውቀት ያልገፉ በመሆናቸውና በአንዳንድ ብልጭልጭ ነገሮችም ስለሚታለሉ እነዚህን ነገሮች የኢኮኖሚያዊ ዕድገት ምልክቶች ናቸው ብለው በማመን አብዛኛውን ህዝብ፣ በተለይም ደግሞ ተማርኩ ነኝ የሚለውን ያባልጉታል። በብልጭልጭ ነገሮች አዕምሮው እንዲጋረድ በማድረግ ካለበት ኑሮ ባሻገር እንዳያይ ይሆናል፤ ጥያቄ እንዳያነሳ ይገደዳል፤ በዚያው መጠንም አንዳንዱ የተበላሸ ባህርይ ወይም የአኗኗር ስልት በማዳበር ቆሸሽ ብሎ የሚታየውን የህብረተሰብ ክፍል መናቅ ይጀምራል፤ በዚያውም መጠን ለታዳጊው ትውልድ መጥፎ ምሳሌ ይሆናል። በተለይም ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣ ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ተግባራዊ ያደረገውን አገርንና ባህልን አውዳሚ የሆነውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲንና አሉታዊ ጎኑን ጠጋ ብሎ መመርመር ያስፈልጋል።
ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ የመሳስሉ በብዙ ነገሮች ኋላ ቀር የሆኑ አገሮች የስርዓታቸው ሁኔታ በተለይም ከ19ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ እስካሁኑ 21ኛው ከፍለ-ዘመን ድረስ በግሎባል ካፒታሊዝም የተደነገገና የሚደነገግ በመሆኑ በተለያየ መልክ ከውጭው የገባው የኢኮኖሚ መሻሻል(Economic Modernization)፣ የባህልና የመንግስቱ መኪና በካፒታሊስት የጭቆናና የብዝበዛ ስርዓት ውስጥ መካተት የነገሮችን ውስብስብነት እንዳናይ አግዶናል። የሚብለጨለጭና የሚስቅ ሁሉ እያታለለን ይህንን ዐይነቱ ባህልን የሚያበላሽ፣ ኑሮን የሚያዝረከርክና ግልጽነት የሌለውን የገበያ ተቋምና የተበላሸ የአሰራር ሁኔታና ሙስናን አሜን ወይም ትክክል እንደሆነ አምነን ለመቀበል ተገደናል። ስለሆነም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ፖለቲካዊ ውዝግብ፣ የአገዛዙን ማጭበርበርና ውንብድና፣ ባለስልጣናት የሚባሉትን የመንፈስ ድክመትና ለውጭ ኃይሎች ታዛዢነት፣ የአገር ወዳድነት ስሜት ተሟሾ መጥፋት፣ የብሄራዊ ነፃነት መደፈር፣ …ወዘተ. እነዚህ ሁሉ ሊያያዙ የሚችሉት ከካፒታሊስቱ ዓለም፣ ወይም ደግሞ ከአሜሪካን ሰተት ብሎ የገባውን አገር አፍራሽ ባህል ከቁጥር ውስጥ ያገባንና የመረመርን እንደሆን ብቻ ነው። ስለሆነም የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ስርዓት በቅሪትነት እስካሁንም ድረስ እየተጓተተ ባለው አዕምሮን ከሸፈነው፣ ወይም ደግሞ የነገሮችን አመጣጥና ውስብስበነት ከተለያዩ ሁኔታዎች አንፃር በጥልቅ ለማየትና(perceive) ለመመርመር አለመቻል የሁለቱ ስርዓቶች፣ ማለትም የፊዩዳሊዝምና በቁንጽል መልክ የገባውና መንፈስን ለማደስ ያልቻለው የፔሪፈሪ ካፒታሊዝም ውጤት ነው ማለት ይቻላል። ስለሆነም ስለስርዓት በሚወራበት ጊዜ ጠቅላላውን የህብረተሰብ አወቃቀር መመልከት ወይም መመርመር ያስፈልጋል። ፖለቲካዊና መንግስታዊ አወቃቀሮች ከጠቅላላው የህብረተሰብ አወቃቀር ተነጥለው በፍጹም ሊታዩ አይችሉም። አብዛኛውን ጊዜ ነገሮችን እየነጣጠሉ የሚያዩ ተማርን የሚሉ ሰዎች ኤምፕሪሲዝም በሚባል ነገሮችን በጥልቀት አንድ ሰው እንዳያይ ተደርጎ በቀረበ ትምህርት የሰለጠኑ ከሆነ ነው። በተለይም ካፒታሊዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲስፋፋ የሰውን አስተሳሰብ ወደ ኢኮኖሚያዊ፣ እንዲያም ሲል ወደ ፍጆታዊ አጠቃቀም ስለቀነሰው ፖለቲካና መንግስታዊ አወቃቀር ከሌላው የህብረተሰብ አወቃቀር ጋር ምንም ግኑኝነት እንደሌላቸው ተደርጎ መታየት ጀመረ። ስለሆነም በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የመስፋፋት ርዕዮተ-ዓለም የሰለጠኑ ምሁራን ነን የሚሉ የመንግስትን መኪና በመቆጣጠር በአገሮች ውስጥ ሰላም እንዳይኖር፣ ህዝቦች ያላቸውን ሪሶርሶችን በስነ-ስርዓት እያወጡ እንዳይጠቀሙ፣ ከተማዎችንና መንደሮችን ለራሳቸው እንዲስማማ አድርገው እንዳይገነቡ፣ ራሳቸውን ለመመገብ የሚያስችሏቸውን ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎችን እንዳይገነቡ ታገዱ። በተለይም የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ በአባዛኛዎች የሶስተኛው ዓለም አገሮች በሚባሉ ውስጥ ተግባራዊ መሆን ከጀምረ ጀምሮ ልዩ የህብረተሰብ ኃይል ስለተፈጠረ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የባህል፣ የስነ-ልቦናና የኢኮሎጂ ቀውሶች ሊፈጠሩ ያሉ። በዚህ ላይ የጠለቀ ዕውቀት የሌላቸውና ህብረተሰብና ሰው ማለት ምን ማለት እንደሆኑ የማይረዱ፣ እንዲያም ሲል የዛሬው ሁኔታ ካላቀድሞ ሊታስብ እንደማይችል የማይገባቸውና የታሪክን ሂደት በተጣመመ መልክ ለማቅረብ በሚፈልጉ የመንግስትን መኪናን በመጨበጥ የባሰ ጨቋኝና አፋኝ ስርዓት መገንባት ቻሉ። በዚህም አማካይነት ሁኔታዎች መባባስ ቻሉ። ስርዓቱ እንዳለ እንዲግማማ ለማድረግ በቁ። ዛሬ በልዩ ልዩ መልክ የሚገለጸው የባህልና የጠቅላላው ስርዓት ውድመት በቀጥታ ከጭንቅላት አለመዳበር ጋር የሚያያዝ ነው። በአዕምሮ አማካይነት ብቻ ነው ነገሮችን በግልጽ ለማየት፣ ለመገንዘብና መልስም ለመስጠት፣ ወይም ደግሞ ለማየትና ለመገንዝብ አለመቻል፣ እንዲሁም መልስ ለመስጠት አለመቻል የሚወሰነው። ከዚህ ውጭ ለማሰብ መሞከር በጣም አደገኛ ብቻ ሳይሆን ስርዓት ያለውና የጠቅላላውን ህዝብ ኑሮም እንዳይሻሻል እንቅፋት መሆን ነው።
በአገራችን ውስጥ የማሰብ ኃይል ድክመት፣ የችኮነት ባህርይ፣ የግብዝነትና የበላይነት፣ እንዲሁም የበታችነት ስሜት መሰማት፣ እንዲያም ሲል ለውጭ ኃይሎች በማጎበደድ አገራችንን ወደ ጦር አውድማነት ለመለወጥ መጣደፍ በሁሉም ብሄረሰቦች ወይም በጠቅላላው ህዝብ መንፈስ የሚስተጋቡ አይደሉም። የአገራችንን የህብረተሰብ አወቃቀር ለተመለከተና በተለያዩ ብሄረሰቦች ዘንድ፣ በተለይም ኤሊት ነኝ በሚለው ዘንድ ያለውን የባህርይ አቀራረጽ ለተመለከተ ከፍተኛ ልዩነት እንዳለ መገንዘብ እንችላለን። ወደ ሰሜኑ ክፍል፣ በተለይም ወደ ትግሬና ኤርትራ ስንመጣ በከፍተኛ ደረጃ ፓትሪያሪካል አስተሳሰብ የተስፋፋበት ስለሆነም፣ ሌሎችን የመናቅ ወይም በበላይነት ስሜት ለመታየት ይሞከራል። በተለይም የትግሬ ኤሊቶች ጭንቅላታቸው አንዳች ነገር የጎደለው ይመስል የነገሮችን ሂደት ለመመልከትና ለመገንዘብ የማይችል ነው። እዚያው በዚያው በበላይነት ስሜትና በዝቅተኝነት ስሜት የሚሰቃይ፣ ለተቀረው ህዝባችን እንደማህበረሰብ ለመኖርና ለማደግ ከፍተኛ እንቅፋት የሆነ ነው። አንድ ድርጅት ከአርባ ዐመት በላይ ጦርነትን አካሂዶና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆተሩ ሰዎችን ካስጨረሰና ሀብትን ካወደመ በኋላ አሁንም ለጦርነት የሚዘጋጅ ከሆነ ከፍተኛ የማሰብ ኃይል ጉድለት አለው ማለት ይቻላል። እንደ ሌሲትን(Lecithin) የመሳሰሉ የማሰብ ኃይልን የሚያዳብሩ የፕሮቲን ንጥረ-ነገሮች ጎድሏቸው ሊሆን ይችላል። ያም ´ሆነ ይህ አንድ አገር እንዲያግ ከተፈለገና እንደ ስርዓተ-ማህበር እንዲዋቀርና ለተከታታዩ ትውልድ እንዲተላለፍ ከተፈለገ መንፈሳቸው ከማንኛውም ዕቡይ ባህርይ የጸዱ ሰዎች ያስፈልጋሉ። ሀቀኝነትንና ታማኘነትን ከመንፈሳቸው ጋር ያዋሀዱ ሰዎች በጣም አስፈላጊዎች ናቸው። አንድ ቡድን ወይም ሰው ተንኮል፣ የከፍፋይነት ባህል፣ አለመተማመን እንዲፈጠር በዚህም በዚያም አሻጥር የሚሰራ ከሆነ አንድ አገር በፍጹም እንደማህበረሰብ ለማደግ አይችልም። እንደማህበረሰብ ለማደግና ለመጠንከር የሚያስፈልጉትን ሳይንስና ቴክኖሎጂዎችንም ለመፍጠርና ለማዳበር በፍጹም አይችልም። ከዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ስንነሳ በተለይም የትግሬ ኤሊት የዘራፊነት(Predatory)፣ የበላይነት ስሜት፣ የከፋፋይነትና፣ እንዲያም ሲል ለውጭ ኃይሎች በማጎብደድ ባህልን ማውደምና የተበላሸ ዜጋ መፍጠር ዋናው መለዮአቸው ሆኗል ማለት ይቻላል። ስለሆነም አንድ ማህበረሰብ ወይም ስርዓት ለመፍጠር ህብረተሰብአዊ ኃላፊነትን ለመውሰድ የሚችልና ካለምንም አድልዎና አሻጥር ስራ የተቆጠበና መንፈሱም የፀዳ መሆን ያስፈልጋል። በሌላ አነጋገር፣ የፖለቲካው መድረክና የመንግስት መኪናዎች አገርን ወደ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ለመጣል ለሚጣደፉ ኃይሎች በምንም ዐይነት ክፍት መሆን የለበትም። ወደ መንግስት መኪና ውስጥ የሚገቡና በፖለቲካ እንቅስቃሴ ለመሳተፍ የሚፈልጉ ሰዎች በሙሉ የህይወት ታሪካቸውን በሚገባ መመርመር ብቻ ሳይሆን ጭንቅላታቸውን በልዩ መሳሪያ መመርመር ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን ብቻ ነው ከሞላ ጎደል ህዝባችን የሚፈልገውን ስርዓት መገንባት የሚቻለው። ይህ ዐይነቱ በትግሬና በኤርትራ ኤሊቶች የሚታየው የበላይነት ስሜት፣ የአንድን ነገር አመጣጥ አለመገንዘብና በረቀቀ መልክ አለማሰብ፣ ጥያቄ አለመጠየቅና መልስም ለመፈለግ አለመቻል በአንዳንድ የአማራ ኤሊቶችም ዘንድ በግልጽ የሚታይ ነው። ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ በአገራችን ምድር ከ1950ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ ሰተት ብሎ የገባው ትምህርት በሰብአዊነት መርሆች ላይ የተመረኮዘ ባለመሆኑ አንድን ነገር በጥልቅ እንዳንመረምር ለማድረግ በቅቷል፣ ጥያቄ እንዳንጠይቅ ተገደናል፤ ትችታዊ አስተሳሰብን ለማዳበር በፍጹም አልቻልንም። ሰለሆነም ይህ ዐይነቱ የተበላሸ የመንፈስ አቀራረጽ ለተወሳሰበ ችግራችን ዋናው ምክንያት ሆኗል ማለት ይቻላል።
ያም ተባለ ይህ ወደ አገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመጣ ነገሮችን ለያይቶ ማየት ያስፈልጋል። በፊዩዳሊዝምና በቢሮክራቲክ ካፒታሊዝም ስርዓት ያደጉና አብዛኛውን ጊዜ አመለካከታቸው ታራማጅ ባህርይ የሌለው፣ ወይም ደግሞ ሁለ-ገብ ዕድገት ማለት ምን ማለት እንደሆነ የማይገባቸው፣ አሁንም ቢሆን ፖለቲከኞች ነን፣ ስለፖለቲካም ያገባናል፣ የአገራችንም ሁኔታ ያንገበግበናል የሚሉ ዕድሜያቸው በሰባና በስማኒያዎቹ ውስጥ የሚገኙ አሉ። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ፣ ለአገራችን እናስባለን ቢሉም የአሜሪካንን የበላይነት የሚያራምዱ ናቸው። አብዛኛዎች የዓለምን ፖለቲካና የኢኮኖሚ አወቃቀር የመረዳት አቅም የላቸውም። ክሪቲካል አሰተሳሰብ በፍጹም የላቸውም፤ አስተሳሰባቸውም በጣም ቁንጽል ከመሆኑ የተነሳ ገፍተው በመሄድ የነገሮችን አመጣጥ በጥልቀት ከሁሉም አኳያ ለመመልከት በፍጹም አይችሉም። የእነዚህ ሰዎች ጭንቅላት የተዘጋ ስለሆነ ጭንቅላታቸውን ለማደስ በፍጹም አይቻልም። የግሪክ ፈላስፋዎች እንደሚያስተምሩን ጭንቅላት ማየት ካልቻለ ዐይንም ማየት አይችልም እንደሚሉት የእነዚህም ሰዎች ጭንቅላት የሚታዩ፣ የሚዳሰሱ፣ የሚሰሙና አብዛኛውን ህዝብ መቀመጫ መነሻ ያሳጧቸውን ነገሮች ለማየት በፍጹም አይችሉም። ይህ ጉዳይ በማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን በአውሮፓ ምድር ውስጥ የሰፈነ ስለነበር በከፍተኛ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ነው ከሞላ ጎደል ሊወገድ የቻለውና ካፒታሊዝም ቀስ በቀስ ሊያድግ የቻለው። ይህም ማለት ያለው ችግር ምሁራን ነን ከሚሉ የሚመነጭና፣ በዚህም በዚያም ብለው በአቋራጭ ስልጣንን በመጨበጥ በሚያወናብዱ የሚፈጠርና፣ ከስልጣንም ውጭ ሆነው በምሁራዊነትና በፖለቲካ ተንቀሳቃሽነት ሰም ሰፊውንና የዋሁን ህዝብ በሚያወናብዱ የዘመኑ ብልጣብልጦች ምክንይት ነው።
ይህንን እንደገና በምሳሌ ላስረዳ። የሰውን ልጅ ስልጣኔ ታሪክ፣ ወይም የሳይንስንና የቴክኖሎጂን ዕድገት ስንመረምር መሰረቱ የተጣለው በግሪክ ፈላስፋዎች ነው። በጊዜው የፍልስፍናን ዕውቀት፣ የተፈጥሮ ሳይንስን ምርምር፣ ማቲማቲክስን የፈጠሩ ታላላቅ ምሁራን፣ እንደ ፕሌቶ የመሳሰሉት ከአሪስቶክራሲው ቤተሰብ የተወለዱ ናቸው። የፕሌቶ አስተማሪ ሶክራተስ በአባቱ ከዕብነ-በረድና ከዲንጋይ ትላልቅ ቅርፃቅርፆችን የሚሰራ ሲሆን፣ እናቱ ደግሞ አዋላጅ ነበረች። እነዚህና ተከታታዩ ትውልድ በሰብአዊነት ትምህርት(Humanistic Education) ማለትም በግሪክ ቋንቋ፣ በጄኦሜትሪና በጂይምናስቲክ እንዲሁም በፍልስፍና ትምህርት ጭንቅላታቸው የተኮተኮተ ነበር። እነዚህና ተከታዮቻቸው በሙሉ የራሳቸውን ህይወት ወይም ኑሮ በመሰዋት አብዛኛውን ጊዜያቸውን በምርምር ላይ በማዋል ነው የግሪክን ህዝብ ከጨለማ ስርዓት ማውጣትና ብርሃንን እንዲያይ ያደረጉት። በአጠቃላይ ሲታይ የግሪክን ፋላስፋዎች ፈለግ የተከተሉ፣ እንደነ ዳንቴ፣ ጋሊሊዬ፣ ኮፐርኒከስ፣ ኩዛኑስ፣ ኬፕለር፣ ዴካ፣ ስፒኖዛ፣ ኒውተን፣ ላይብኒዝ፣ ካንት፣ ሄገል፣ ኒቸና ሌሎችም በሰብአዊነት የትምህርት ዘዴ የሰለጠኑ በመሆናቸው ለዕውቀትና ለመንፈስ የበላይነት ግምት በመስጠት ነው ለሰው ልጅ ዕድገት የሆነውን የሳይንስና የቴክኖሎጂን መስመር የቀደዱት። እንደነዚህ ዐይነት ሰዎች ባይፈጠሩና አብዛኛውን ጊዜያቸውን በምርምር ላይ ባያውሉ ኖሮ የሰው ልጅ በሙሉ በጨለማ ዓለም ውስጥ በኖረ ነበር። እነዚህ ተመራማሪዎች በዚያ አስቸጋሪ ወቅት ወረቀትና ማተሚያ እንደልብ ባልተስፋፋበት ዘመን መጽሀፎችን በመጻፍ ዕውቀትን በአውሮፓ ምድር ለማስፋፋት ችለዋል። እንደነላይብኒዝ የመሳሳሉት የፍልስፍና ተመራማሪና የካልኩልስ አፍላቂዎች ደግሞ– ኒውተንና ላይብኒዝ ሳይተያዩና ሳይተዋወቈ ነው ሁለቱም አንዱ ከሌላው ሳይኮርጅ ካልኩለስን ያገኙት፣ የቴክኖሎጂ ዕድገትና አጠቃቀም በፍጹም ካለካልኩለስ ሊታሰብ አይችልም- ከተወለደበትና ካደገበት ከጀርመን ውጭ ወደ ለንደን፣ ፓሪስና ሞስኮ በዚያን ጊዜ የነበረው አስቸጋሪ ሁኔታ፣ በረዶ ክረምት ሳይገድበው በጋሪ በመሄድ ነው ከመሰሉ ተመራማሪዎች ጋር በመገናኘት ስለሳይንስና ስለቴክኖሎጂ ዕድገት ይወያይ የነበረው። ላይብኒዝ በህይወቱ ዘመን በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ የደብዳቤ ልውውጥ አድርጓል። አያሌ የፍልስፍናና የሳይንስ መጽሀፎችን ጽፏል። እነዚህን የመሳሰሉ ተመራማሪዎች በወቅቱ ትዳር ልመስርት ብለው የሚጨነቁ ሳይሆን፣ እንዴት ለሰው ልጅ የሚጠቅም አንድ ነገር ማግኘትና ጥዬ ማለፍ አለብኝ በማለት ነበር ጭንቅላታቸውን ያስጨንቁ የነበረው። እያንዳንዳቸውም ወደ እግዚአብሄር የሚጠጉና፣ አምላክም የሰውን ልጅ ከጥፋት አድነው ተብለው የተላኩ ይመስል ለራሳቸው ሳይሆን ለሌላው ሰው ነው የኖሩት ማለት ይቻላል። በዕውቀታቸውና ባገኙት፣ እንዲሁም ለሰው ልጅ ላበረከቱት አስተዋጽዖ የሚመፃደቁ ወይም ትዕቢተኞች አልነበሩም። ጭንቅላታቸው በሙሉ ከማንኛውም ዕቡይ ፀባይ የጸዳ ነበር ማለት ይቻላል። ምክንያቱም ፍልስፍና፣ የተፈጥሮ ሳይንስ፣ ማቲማቲክስ፣ ለጥቅም የሚውለው ቴክኖሎጂ ሊፈጠሩና ሊዳብሩ የሚችሉት የሰው ልጅ ጭንቅላት ከማንኛውም ዕቡይ ነገሮችና ተንኮሎች የፀዳ ከሆነ ብቻ ነው። ሰው መሆኑን ሲገነዘብ ብቻ ነው። ሰው መሆኑንም ሲገነዘብ ከእንስሳ የተለየ መሆኑን ይረዳል። ይህንን ሲረዳ ብቻ ነው ሌላውን ከሚጎዳ ነገር ሁሉ ሊቆጠብ የሚችለው። ሰውን ለመግደል አያስብም። ማንኛውንም ሰው እንደ ጠላቱ አይመለከተውም። ሰውን እንደ ሰው ነው የሚያየው። ሌላው አስቸጋሪ ከሆነ የሚረዳው ጭንቅላቱ በደንብ ያልተኮተኮተ መሆኑን በመገንዘብ ብቻ ነው። ሌላውን አምሳያውን የሚገድል፣ የሚያሰቃይ፣ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚል፣ አገር ማፍረስ አለብኝ ብሎ ሌላውን መግቢያና መውጫ የሚያሳጣ፣ ራሱን ለውጭ ኃይል የሚሸጥና ለሌላው ታዛዥ ለመሆን የሚቃጣው፣ ለዚሁ ሁሉ ዋናው ምክንያት ጭንቅላት በደንብ በትክክለኛ ዕውቀት ያልተገነባ ከሆነና በአስተዳደጉም የተበላሽ ከሆነ ብቻ ነው። ይህ ጉዳይ በአገራችን ምድር ካለፉት ሃምሳ ዓመታት ጀምሮ በጉልህ የሚታይ ጉዳይ ነው። የአሁኑ የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ወይም ስርዓት የሚያረጋግጠው የእኛን የኢትዮጵያኖችን የጭንቅላት መቀጨጭ ነው። መልካችንና ቁመናችን ያምራል። ባህሪያችን ግን አስቸጋሪና አገርን አውዳሚ ነው። ይህ ጉዳይ በተለይም ተማርኩ በሚለው ላይ የሚያይል ነው። አገርንም የሚያወድምና ለውጭው ኃይል ተገዢ የሆነው የኢትዮጵያ ገበሬና ወዝአደር፣ ባጭሩ ዘጠና በመቶ የሚሆነው ሰፊው ህዝብ ሳይሆን፣ ተማርኩኝ የሚለው በጥራዝ-ነጠቅ ዕውቀት ራሱ ተሰቃይቶ ሌላውን በሚያሰቃየው ነው። የዚህን ተማርኩኝ ነኝ ባይ አዕምሮ በፍጹም ማደስ አይቻልም። የኖይሮ ባይሎጂ ተራማሪዎች እንደሚሉት የሰው ልጅ የማሰብም ሆነ ያለማሰብ ኃይል እስከ አስራ-ሁለት ዓመት ባለ ዕድሜ ውስጥ የሚጠናቀቅ ነው። አንድ ልጅ እስከ አስራሁለት ዓመቱ ድረስ ጭንቅላቱ በጥሩ ዕውቀት ከተኮተኮተ የማሰብ ኃይሉ ከፍ ስለሚል የመፍጠር ኃይሉ ከፍ ይላል። ሌላውንም አያጠቃም። ስለዚህም ነው በአውሮፓ ምድር ብቅ ያሉ ፈላስፋዎች፣ ሳይንቲስቶች በሙሉ ከልጅነታቸው ጀምሮ በትክክለኛው ዕውቀት መንፈሳቸው የተቀረጸ ስለሆነ ሳይንስን፣ ማቲማቲክስንና ሌሎች ለዕድገት የሚሆኑ ነገሮችን ለመፍጠር የቻሉት። ስለሆነም ነው እነ ጋሊሊዮና፣ ኬፕለር፣ ዴካና ኒውተን፣ ላይብኒዝና ካንት፣ ሄገልና ሌሎችም ፈላስፋዎች ገዳይ ያልሆኑት። እነሱ ባነጠፉት የሳይንስ መሰረት የተሰሩ የሰውን ልጅ ማጥፊያ መሳሪዎችና የአቶም፣ የባይሎጂና የኬሚካል መርዞች በእነዚህ ታላላቅ ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች ስም የሚሳበቡ አይደለም። የስውን ልጅ ማጥፊያ፣ ለጦርነት የሚውሉ ውስብስብ መሳሪያዎች በሙሉ የሚሰሩትና ትዕዛዝም የሚሰጠው ሰይጣናዊ መንፈስ ባላቸው የፖለቲካ ስልጣንን በጨበጡ፣ የሚሊታሪ- ኢንዱስትሪ ውስብስብ ባለቤቶችና፣ የዓለምን ሀብት ለመቆጣጠር በሚሯሯጡ የፖለቲካና የኢኮኖሚ፣ እንዲሁም የስለላና የሚሊተሪ ኤሊቶች አማካይነት ነው።
ነገሩን ለማሳጠር በልዩ ልዩ መልክ የሚገለጸውን የአገራችንን ችግር ለመረዳት የሚቻለው በስርዓቱ በማሳበብ ሳይሆን የራሳችንን ጭንቅላት በመመርመር ነው። እነዚህ ዐይነት ምስቅልቅልና ዘግናኝ ሁኔታዎች የተፈጠሩት ጭንቅላታችን በጥልቀት ለማሰብ ባለመቻሉና፣ ራሳችንንም ለመጠየቅ የሚያስችል ኃይል ስለሌን ነው። ከተፈጥሮ በስተቀር፣ ሌሎች ነገሮች በሙሉ፣ ማለትም የመንግስት መኪና፣ የፖለቲካ ሁኔታ፣ የኢኮኖሚና የማሀበራዊ ሁኔታዎች፣ የከተማዎችና የመንደሮች አገነባብ፣ በአጠቃላይ ሲታይ የነገሮች ተዝረክርኮ መገኘት፣ ግልጽነት ያለው የገበያ ዕድገትና እንቅስቃሴ አለመኖር፣ የጭንቅላታችን መቀጨጭ ውጤቶች ናቸው። ጭንቅላታቻን በሰብአዊነት ዕውቀት(Humanistic School of Thought) ያልተዋቀረና ያልዳበረ በመሆኑ አገራችንን ጥበባዊ በሆነ መልክ ለመገንባትና፣ ህዝባችንን በሰለጠነ መልክ ሊያስተዳደር የሚችል መንግስታዊና ፖለቲካዊ፣ እንዲሁም የተቋማት ስርዓት መፍጠር የማንችልበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን። ለሰላም እጦትም ጠንቅ የሆነው እኛ ተማርን የምንለው ጥቂት ሰዎች ነን። ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝባችን ሰላምን ይፈልጋል። ሰርቶ መብላትንም ይመኛል፤ በአገሩም ተከብሮ መኖርን ይሻል። መልካም ግንዛቤ!!
Francisco Valera & Evan Thopson; The Embodied Mind: Cognitive Science and Human Experience, USA., 1993
Julin Jaynes; The Origin of Consciousness in the Breakdown of the Bicameral Mind, Princeton, 1976
Rutger Bregman; Humankind: A Hopeful History, Hamburg 2023