ጠዋት ከእንቅልፌ ስነቃ ጆሮዬ ላይ “ጀዌው ጠ/ ሚንስተር” የሚል ቃላት አስተጋባብኝና ወዴት ዞሬ እንደነቃው ለማስተዋል ሞከርኩ፡፡ በቀኝ በኩሌ ነበር የነቃሁት፡፡ ከዚያም ማታ ምን አስቤ ባድር ይሁን በእንዲ ያለ ቃል የነቃሁት ስል እራሴን ጠየቅሁ፡፡ ለካስ ማታ ከመተኛቴ በፊት ስለ ጁንታና ጃዊሳ ሳስብ ነበርኩ፡፡
ጁንታ የሚለው ቃል ብልጽግና ወያኔን፣ በአጠቃላይ ትግራይን ለማውደም የፈጠረው ቃል ነው፡፡ ቃሉ እንግሊዘኛ ሲሆን ትርጉሙም የጥቂት ወታደራዊ መሪዎችና አመራሮች የኃይል ስብስብ ማለት ነው፡፡ ጆሯችን እስኪደነቁር ድረስ የሰማንው ይህ ቃል ትግራይን አውድሞ፣ የአማራና አፋር ክልል ከጥቅም ውጭ አውጥቶ፣ የኢኮኖሚና ኢንዱስትሪ አውታሮችን ደሴና ኮመበልቻ ላይ አጥፍቶ የመጀመሪያ ዙሩን አጠናቀቀ፡፡
አሁን ደግሞ በጦርነት እምቢልታ ነፊው ዲ/ን ዳንኤል ክብረት በኩል ጃዊሳ የሚል ቃል ተፈጥሮ ሌላ ዙር ውድመት እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ጃዊሳ ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን ትርጉም ለማየት ሞክሬ ነበር፡፡ ቀያዊ የሆነ የተለያየ ትርጉም ቢኖረውም የመዝገበ ቃላቱ ፍቺ እንዲህ ይለዋል፡፡ ጃዊሳ ማለት አካሉ ግዙፍ የሆነ፣ ጉለበታም ሰው፣ ሆዳም፣ ቀማኛ፣ ወንበዴ፡፡ ይህ እንግዴህ ለፋኖው ከፍ ሲልም ለአማራው የተሰጠው የማስወገጃ ብያኔ መሆኑ ነው፡፡
የጃዊሳ ትርጉም በግዜ ወደ ኋላ ወሰደኝና አንድ ገጠመኜን አስታወሰኝ፡፡ ከ1985 ዓ.ም. ጀምሮ ለሶስት አመት ያህል በደቡብ ኦሞ ጂንካ፣ የሃይ ስኩል ሂሳብ መምህር ሆኜ ሃገሬን አገልግዬለሁ፡፡ አስታውሳለሁ በዚያን ግዜ ህወሀት/ኢህዲግ ፀረ አማራ ትግሉን መአህድ መጣላችሁ፣ ጃስ… እያለ ያካሂድ ነበር፡፡
የቡሜና ፀማይ ህዝቦችን እዛው ደቡብ ኦሞ ቀይ አፈር የሚባል ከተማ ላይ ሰብስቦ በትልቅ ካርቶን ቦርጫምና ግዙፍ የሆነ ምስል ስርቶ ይህ የአማራ ገዢ መደብ በመሆኑ በእሳት አቀጥሉ አላቸው፡፡ አንድ የቡሜ ጎሳ መሪ ተነስተው የአማራ ትልቁ ሰው አፄ ኃይለስላሴ ናቸው፡፡ በህይወት ዘመናቸው እዚህ መጥተው አይተናቸዋል፡፡ አጭርና ቀጭን ሰው ነበሩ፡፡ ይህን የሚያክል አማራ የለም፣አናቃጥልም አሉ፡፡ ከዚያም ያን የካርቶን ጃዊሳ አንድ እወደድ ባይ ቄስ ተነስቶ በእሳት ለኮሰው፡፡
ይገርማል የጥበብና እውቀት ምንጭ የሆነችው ኦርቶዶክስ እንዲህ ያሉ ሰዎችንም ስታፈራ አያያን ኖረናል፡ ደርግ(ኮሚቴ) የሚለውን ቃል የፈጠሩት የኛው ጠማሞች ከቤ/ክህነት አይደሉምን? ዝከረ ዳንኤል ክብረት ተብሎ እይታዎቹን የሚያካፍልበት አንድ መርሐግብር በአክሱም ሆቴል አድርጎ ታድሜ አንደነበር አስታውሳለሁ፡፡
ዲያቆኑ በትልልቅ ሰዎች ጥላ ስር ማደር የሚፈልግ ልክስክስ መሆኑን የተረዳሁት የዚያን ግዜ ነው፡፡ በአዳራሹ ውስጥ ሞስሊሞችን ጨምሮ ወደ ሺህ የሚጠጋ ሰው ነበር፡፡ ምን ቢል ጥሩ ነው? መጽሐፍቶቼን በዱቤ ስል በዱቤ፣ በግማሽ ክፍያ ስል እንዲሁ በባዶ ጭምር የምታሳትምልኝ ቀዳማዊ እመቤት አዜብ መስፍንን አመስግኑልኝ፡፡ ይሀ ጃዊስ(ሆዳም) ከመጀመሪያው ጀምሮ የተተከለብን ኢምፕላንት ሰው ነው፡፡
እንግዲህ ነገሩ በጀ ጀምሮ በጀ ይለቅ ካልን ጃዌ ማለት ምን ማለት እንደሆ እንተርጉም፡፡ ጃዌ ማለት ከወገቡ በላይ ቀጥ ብሎ የሚሄድ፣ በፊቱ ያገኘውን ሰውም ሆነ ከብት የሚነድፍ፣ መልኩ ቡላ፣ ቁመቱ አራት ክንድ ያኽል ተሰቢ እንስሳ ነው ሲል መዝገበ ቃላቱ ይተረጉመዋል፡፡ በምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢ የሚገኝ የኮብራ እባብ ዝርያ ነው፡፡ ከቡለጋ አሳግርት፣ ከሰምን ወንዝ ይዞ እሰከ ምንጃር ጃዌ ወይንም ጎቢጥ ገና በመባል ይታወቃል፡፡
እባብ በፖለቲካ ትእምርት ውስጥ ተገልጦ ካነበብኳቸው መጽሐፎች ውስጥ አንዱ የሼክ ሁሴን ጅብሪል ትንቢታዊ ግጥሞች ናቸው፡፡ እንዲህ ይላል
አስመራና ትግሬ ትትል ሺህ ገዳይ
እባብ ከተፍ ይላል መምጫው ሳይታይ
ሸዋ የዚያን ግዜ ይላል ዋይ ዋይ
ጀርባውን መጅ መታው ወደትግሬ ቲይ፡፡
እኔ ጋር የሳቸው ግጥሞች ተበለው የታተሙት መጽሐፍቶች አሉኝ፡፡ ለግዜው ግን ዶ/ር ጌቴ ገላዬ፣ ሐምቡርግ ዩንቨርሰቲ 1996 ዓ.ም. ያሳተሙትን እየጠቀስኩ ነው የምናገረው፡፡ የሱፍያው ሼክ ትንቢት ሁሉ ካለፈ በኋላ የተጻፈ ስለሆነ ቅቡልነቱ ያጠራጥራል የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ ከላይ የጸሰፍኳት ግጥም ግን የአሁን ግዜን አመላካች ስለሆነችብኝ ዝም ብሎ ማለፍ አልተቻለኝም፡፡
በወያኔ የተሳሳተ ስሌት(miscalculation) ሰሜን እዝን በመምታት የተጀመረው፣ እነ አብይም አድፍጠው ሲጠብቁት የነበረው የጥቅምት 26 ጦርነት ከዛሬ ሁለት በፊት ከተጀመረ በኃላ አስመራም ትግሬም ሺህ ገዳይ ሺህ ገዳይ በከበሯቸው ዘፍነዋል፡፡ሸዋም የመአከላዊው ኢትዮጵያ ፖለቲካ ተወከልት፣ ፊቱን አዙሮ ትግሬን ሲመለከት ነበር፡፡ በጦርነቱ መሃልም ሆነ ከዚያን በኃላ በፋኖ ምክነያትም ይሁን በያዘው የፖለቲካ አቋም ጀርባው በመጅ ተመቷል፡፡ ይህ ደግሞ ሼክ እንዳሉት፣ በእባቡ(ጃዌው) አብይ አህመድ ዘመን ነው የሆነው፡፡
አብይን ማን ያለደገፈው ነበር፣ ከኤርትራ ጀምሮ በትግራይ በመላው ኢትዮጵያ? በሼኩ አንድ ግጥም ውስጥ እንዲህ የሚል ስንኝ አለ፡፡ ሲተክሏቸው ጥሩ፣ ሲበቅሉ ጠማማ…እንዲህ ነው ነገሩ፡፡ ደርግ “ኢትዮጵያ ትቅደም ያለምንም ደም!” ብሎ ጀመረ፡፡ ህልቁ መሳፍረቱን ጨርሶ አበቃ፡፡ ወያኔም በአቡነ ጳውሎስ በኩል 1986 ዓ.ም. ላይ በኢትዮጵያ ምድር ሴይጣን ታሰረ አሉ፡፡ ውለው አላደሩም ከኤርትራ ጋር ቀጥሎ ከሁሉም ጋር ወዲያ ወዲህ ሲሉ ቆይተው ትግራይን ባድማ አደረጓት፡፡ የአብይ ግዜ ደግሞ ባሰ፣ ኢትዮጵያውያን ሃገር አልባ ሆኑ፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ አለቀ፡፡ በለፉት አምስት አመታት የህዝቦች መፈናቀል፣ሞት፣ሰው ሰራሽ ረሃብ የምድሪቱ እጣ ፋንታ ሆኗል፡፡
ጸረ ሴማውያን የሆነው ኦሮሙማ ትግራይን በልቶ፣ አማራ ክልል ውስጥ ህዝብ እየጨፈጨፈ ይገኛል፡፡ ለኤርትራ ደግም በወደብ ስም የጦርነት ከበሮ ነጋሪቱን መምታት ጀምሯል ፡፡ በሶስተ ጎንዮሽ የጥፋት ድግስ ሴማዊ ቋንቋ የሚናገሩትን ህዝቦች ከኤርተራ ጀምሮ ያሉ ትግሬ፣ አማሮች፣ጉራጌ፣አርጎባ፣ አደሬና የጋፋት ቋንቋ ተናጋሪ ወራሾች የሆኑትን የሸዋ ኦሮሞዎችን እጅግ አዳክሞ አቅመ ቢስ በማድረግ ከሌሎች ኩሻውያን ተብለው ከሚጠሩ የሃገሪቱ ህዝቦች ጋር ለቁጦ ለመዋጥ በሂደት ላይ ነው፡፡ ለዚህ ምስክሬ ደግሞ የኦቦ ሽመልስ ኮንፊውዝና ኮንቪንስ ንግግር ተቀዳሚ ምስክር አደርጋለሁ፡፡
ጃዌው(እባቡ) ጠ/ሚ ገና ስልጣን ላይ ሲወጡ ጀምሮ ነው የእባብ መንገድ የሚባለውን ድምጥ አጥፍቶ ጠላትን መንደፍ የጀመሩት፡፡ መስቀል አደባባይ ላይ ቦንብ ተወረወረብኝ ያሉ ግዜ፣ የትግራይ ህዝብ ድገፋ የነበራቸው ግዜ ነበርና የወያኔ ባለስልጣናትን ከጎናቸው የኮለኮሉበት ፐሮግራም ነበር የተካሄደው፡፡ የወያኔው ደህንነት የት ሄዶ ነው ያሁሉ የተፈጠረው?
ስለጥቃቱ ምርመራ ለማድረግ የአሜሪካው ኤፍ.ቢ.አይ. ኢትዮጵያ መጥቶ ነበር፡፡ በመጨረሻ ባቀረበው ሪፖርት ያለተቀናጀ፣ ሱሉልታ ላይ የተመከረ ተራ ጥቃት እንጂ የኦነግ እጅ እነደሌለበት ነው መደምደሚያ ላይ የደረሰው፡፡ ታዲያ ጥያቄው ይህን ስሞክሰክሪን ድራማ ማን አቀናበረው ለምንስ አላማ?
ቤተ መንግስት ሄዱ የተባሉትም ወታደሮች አያልቅበት ጠ/ሚ ፑሽአፕ አሰርተው ሲመልሷቸው በቅድሚያ ተገኝተው የነበሩት (በወታደሮቹ እንግልት የደረሰባቸው) ምክትል ጠ/ሚ ደመቀ መኮንን እንጂ ጠ/ሚ አልነበሩም፡፡ ጠ/ሚሩ ከሌሎቹ ባለስልጣናት የሚለዩት በወታደርነቱ ሞያ ላይ ያን ያክል በይሆኑም በስለላ ሞያ ላይ ግን የአቡጀዴዋን ግርግር(film) መፍጠር ላይ የተካኑ መሆናቸው ነው፡፡
እርካብ እና መንበር የሚለው መጽሐፋቸውን ላነበበ ሰው ስእላዊ በሆነ መልኩ ጠ/ሚ እንዴት ከማካቤሌ ጀምሮ ሃሳዊ ሙሴ ሆኖ መተወን እንደሚቻሉ ግልጥ ብሎ ይታየዋል፡፡ ፈገግታቸው፣ ለቅሷቸው፣ ሳቃቸው፣ መኪና ሲነዱ የሚታዩት፣ ሲተክሉ…የአልባሳቶቻቸው ማማር ሁሉም የማነሁለያ ቀመር ግብአቶች ናቸው፡፡
መቼም የማንቼ ማሊያ ለብሰው በቀኝ በኩል በሰባት ቁጥር ቦታ ተጫውተው ያገቡት ግቦች ሰሞኑን የኤምሬትስ ሰዎችን ሃገር ድረስ አሰመጥቶላቸዋል፡፡ መቼም ያገቡት ግብ ዘዲክታቶር የሚለው ፊልም ላይ ብቸውን ሮጦ እንደሚያሸንፈው አይነት ግብ ብትሆንም፡፡
አንዳንዴ ሳስባቸው እንደ ፑቲን ለመሆን የሚዳደቸው ይመስለኛል፡፡ ፑቲን ሰላይ ነበሯ! እሳቸውስ፣ ከማን ያንሳሉ? ፑቲን በጁዶ ጥቁር ቀበቶ አላቸው፣ የኛም ጠ/ሚ ቀዩአን ቦኔት ያደርጋሉ፣ የድድ ዳዳ… መገናኛ ኩማንዶ ይሉሃል ይሄ ነው፡፡
ፑቲነ በማደንዘዣ ታይገር መተው ጥለዋል፣ ፈረሰኛ ናቸው፣ሆኪ ይጫወታሉ፣ በአየር ላይ ግላይድ ያደርጋሉ፣ ፒያኖም መጫወት ይችላሉ፡፡ ታዲያ የኛው ሰው እሰከዛሬ ድረስ ሄሊኮፕተር አብርረው ባያሳዩንም እንደ ህልመኛ ወያላ መኪና ላይ መንጠላጠል ይወዳሉ፡፡ ይህ በመኪና ባለስልጣነትን ይዞ መዞር የፖለቲካ ሲመቦል ይሆን ወይ እሳቸው እንደነገሩን እናታቸው በልጅነታቸው ስኳር ግዛ ብላ ወደ ሱቅ ስትልካቸው በአፋቸው አስነስተው ብርም፣ ብርም… አድረጋው በእግራቸው ይነዱት የነበረውን መኪና አድገውም አለቅ ብሎቸው እንደሆነ፣ አሁንም ባለስልጣናቱን በውሽት ፖለቲካዊ ፍኖት ብርም ብርም ሲያደረጉቸው ይሰተዋላል፡፡ አንድ ቀን ግን በፓራሹት ሳይወርዱ ወይም በአውቶ ፓይለት የሆነ የሚበር ነገር ሳይነዱ አይቀሩም ባይ ነኝ፡፡
የዚህን ጽሑፍ ርዕስ ጃዌው ብልጽግና ልለው አሰብኩና ብልጽግና ያለ ጠ/ሚ ምንም ስለማይሆን፣ እሳቸው እስካሉ ድረስ ብቻ የሚኖር በመሆኑ ርዕሱን ቀየርኩት፡፡ ከመጀመሪያው ጀምሮ ጠ/ሚሩ እነደተናገሩት የእሳቸው ወደ ስልጣን መምጣት የታሰበበትና የተሰራበት ነው፡፡
ገና ከጅምሩ ጠ/ሚ በትንቢት የመጡ አድርጎ መናገር፡፡ በፐሮቴሰታነቱ አለም የራሳቸውን መሲሃዊ አምልኮ(cult) መፍጠር፣ መደመር የሚል ፍልስፍና ፈጥሮ ከእሳቸው ጋር የተጣበቀ እሳቸውን ከፖለቲካ መሪ በላይ መንፈሳዊነትን በማላበስ የሙሴያዊነት አሻጋሪ ተልኮ መስጠት፣ ሁሉም ተቀምሮ የተሰራ ነው፡፡ እዚህ ላይ እርካብና መንበርን ላነበበ፣ ሙሴ ሙሴ ሲላቸው የነበረው ሰው ሁሉ እሳቸው በከፈቱለት ፍኖት መፍሰሱን ያሰተውላል፡፡ የኦርቶዶክስ ቤ/ክ አስታራቂና የፕሮቴሰታንት ቤ/ክ ጠባቂ ሆነውም ተቆጠሩ፡፡
ይህ እሳቸው አስልተው አቅደው የሰሩት ስራ ነበር፡፡ በስልጣናቸው የመጀመሪያ ሰሞን አሜሪካ በመጡበት ግዜ አንድ እሰላማዊ ድርጅት ስብሰባ ላይ ተገኝተው ሰይድና(ጌታዬ) አንቶኔ እንዳሉት በማለት የሱፊ እስልምና እምነት ተከታይም ለመምሰል ሲሞክሩም ታይተዋል፡፡ ለምን አክሱም ላይ መስጊድ አይሰራም በማለትም የሞስሊሞችን ልብ ለመያዝ ሞከሩ፡፡ ዱባይም ሄደው ቁራንን ፈትፍተው የሚሰተምሩ ኢትዮጵያውያን ኡለማዎች እንዳሉ አስታወቁ፡፡ እንዴት አንድ ሰው የሁሉም እምነት መሪ መሆን ይችላል?
ከጥቂት ግዜ በኋላ ግን የሆነው መስቀል አደባባይን ለኦርቶዶክስ፣ ፕሮትሰታንትና ሞስሊሞች ሻሞ ማለት ነበር፡፡ ቀጥሎም መጅሊሱን ከአማራ ሞስሊሞች በማጽዳት ለኦሮሞዎቹ መደላድል ተፈጠረ፡፡ የኦርቶዶክስ ሲኖዶስ ሶስት ቦታ ተከፈለ፡፡ ብዙ ደም በሃይማኖት ጎራው ፈሰሰ፡፡ ነቄ የሆኑ ፕሮቴሰታነቶችም ግን አፈንግጠው እየወጡ ነው፡፡ ነገሩ እግሩን የኦሮሞ ብሔር ውስጥ ተክሎ መቀመጫውን መካከለኛው ምስራቅ ውስጥ የሚወዘውዘው የስልጣን ጥማት እንጂ የእምነት ጉዳይ እንዳልሆነ ሲውል ሲያድር እየገባቸው ይገኛል፡፡ለዚህ ደግሞ ብዙ ግብአቶች አሉት፡፡
ኮሚኒዝም ለቀደሙት ስርአቶች ኒሂሊሰተ ነው የነበረውን የሚንድ፣ የማይረባ አድርጎ የሚገልጽና የመደብ ትግሉን አንዱ በሌላው መቃብር ላይ አድረጎ የሚስቀምጥ ርዕዮት አለም ነው፡፡ በ1950ዎቹ የነበሩ አብዮተኞች አብዛኞቹ የኮሚኒዝም ቅባትን የተቀቡ ነበር፣ ከግርማሜ ነዋይ ጀምሮ ማለት ነው፡፡ አሁን ያሉ ብዙ የኦነግ ጉምቱ ፖለቲከኞች የመኢሶንና የኢጫት አባላት ነበሩ፡፡ በአማራው እሴት ላይ ሲደረገ የነበረውና ያለው ትርክት ሁሉ የዚያ ተረፈ ኮሚኒዚም ውጤት ነው፡፡
የብሔር ፖለቲካስ ቢሆን የስታሊን ፍሬ አይደለምን? ኦሮሙማው ግን ታሪክን ላጠናው በፋሺስት ኢጣልያን አስተምሮ ተጀምሮ በናዚዝም ጸረ ሴማዊ አካሄድ የተቀኘ ነው፣ በተረፈ ኮሚኒዝም ሜክአፖ እራሱን ከማስጌጡ ውጭ፡፡ ስለዚህ ከሁለት አመት በፊት ደጋግሜ በዘሐበሻ ላይ የጻፍኩት ስለሆነ አሁን አልደግመውም፡፡
ልክ ናዚዝም ክርስቶስን ማርያም ከሮማ ወታደር የወለደቸው የአርያን ዝርያ አድርጎ ዲኮንስትራክት እንደሚያደርገውና የነኦዲንን ሚት አጉልቶ እንደሚያወጣው፣ ኦሮሙማ ዋቅ ጉራቻን ከክርስትና እምነት አላባውያን ጋር አዋህዶ ብልጽግና ውስጥ ይገልጣል፡፡ ለዚህም የብልጽግናን አርማን ማየት በቂ ነው፡፡
የብልጽግና አርማን ፊትለፊት ላየው አርማው የወንጌላውያን አርማ ጋር መመሳሰል ቢኖረውም የተለየ ነው፡፡ ሁለት ወደ ላይ የተዘረጉ ጥቁር መዳፎች ውስጥ ያሉ በሰማያዊ፣ቢጫና ቀይ ቀለሙ ሰዎች እናያለን፡፡ ከበላያቸውም የፈነጠቀ ቢጫ ጨረር ይታያል፡፡ እዛው ላይ ግን ሁለቱ መዳፎች የሰጎኗ ቀኝና ግራ የፊት ገጽተዋን ይመስላሉ፡፡ ከላይ ያለው ፍንጣቂ ጨረር ደግሞ ከሰጎኗ ኋላ የተዘረዘሩ ላባዎቿን ይመስላል፡፡ በወንጌላውያን አርማ ላይ የሚታየው እጅ፣ እጅ መሆኑ ይለያል በብልጽግናው ላይ ግን ሁን ተብሎ በመሾሉ እጅም የፊት ገጽታንም እንዲወክል ተደርጓል፡፡
ይህን አርማ ገልብጠን ስናየው ደግሞ ሰማያዊና ቀይ ክብ አይኖች ያሉት አፍንጫው ደግሞ በቢጫ ክብ የተሰራ የሰው ምስል እናያለን፡፡ ከፊቱ ቢጫ ጨረሮች ይፈነጥቃሉ፡፡ ሰውዬው በደፋው ዘውድ ላይ በግንባሩ አኳያ ባለ ሶስት ጫፍ መንሽ(Trident) ይታያል፡፡ ይህ ምልክት የሂንዱ የጥፋት አምላክ የሺቫ ምልክት ነው፡፡ ትርጉሙም በግዜ ውስጥ የሚደረግ ውድመትን፣ ጥበቃንና ፈጠራን ያመለክታል፡፡ እንግዲህ ጠ/ሚ ምንን አጥፍተው ምንን እየፈጠሩ እንዳሉ መመርመር ነው የሚጠበቅብን፡፡
ህንድ ውስጥ ይህን ሶስት መንሽ በፊታቸው ላይ በመሳል በየአመቱ ነሃሴ ወር ውስጥ የእባብ(ጃዌ) ፌስቲቫል ይከበራል፡፡ ናጋ ፓንቻሚ ብለውም ይጠሩታል፡፡ ናጋ ግማሽ ሰው ግማሽ እባብ የሆኑ ቅርጻቸውን መቀያየር የሚችሉ ፍጡራን ናቸው፡፡ እንግዲህ ጠ/ሚሩ ሰውም አውሬም ሲሆኑ ተመልክተናቸዋል ቀጥሎ ምን እንደሚሆኑ የሚያውቀው አንድዬ ብቻ ነው፡፡
የቫይኪነግ የሚመስለው ዘውድ እንደቫይኪነጎቹ ሁሉ በቀኝና በግራ ሁለት ቀንድ ያለው ዘውድ ከመንሹ ወዲያነ ወዲህ ይታያል፡፡ ከዚህ ንጉስ በላይ ሁለት ባራኪ ጥቁር እጆችን እናያለን፡፡ እንግዲህ የዋቅ ጉራቻ እጆች መሆናቸው ነው፡፡ በኦሮሞ ዋቄፍና እምነት አምላክ ዋቅ ጥቁር ነውና፡፡
መደዳውን በግንባሩ ላይ ያለውን ሶስት ሹል ጫፎችና ሁለቱ ቀንዶቹን ስንቆጥራቸው አምስት ይሆናሉ፡፡ ዱሮ፣ ዱሮ ልጅ ሳለን አያ ሰባት ቀንዶ ስለሚባል አስፈሪ አውሬ ተረት እየነገሩን ፍርሃትን ያለማምዱን ነበር፡፡ ይኸውላችሁ በራሱ ግዜ ገና በልጅነቴ ትንቢት የተነገረልኝ ነኝ የሚል በምስሉ ላይ የሚታየውን “አያ አምስት ቀንዶ” አርማውን ስሎላችሁ መጣ፡፡
ታዲያ እንዲህ ያለው ክርስትናን ከነባር እምነት ትእምርቶች ጋር አደባልቆ የሚያተራጉም የናዚ አርማና አስተሳሰብ በብልጽግና ውስጥ ማሳየት ለምን ተፈለገ፡፡ ናዚዝም የራሱ ክርስቶስ አለው፣ ግን የአንድ የአርያን ዘር የሆነ የሮማ ወታደር ልጅ ነው፡፡ የኖርስና የቫይኪነገ ነባር እምነቶችንም ቦታ ሰጥቶ በማዳቀል አዲስ የእምነት ፍልስፍናን ይዞ የሚጓዝ ነበር፡፡
ነገሩ ሂትለር ሲወገድ ናዚዝም እንደጠፋ ሁሉ ብልጽግናም ከጠ/ሚ አብይ በኋላ አይኖርም፡፡ ጠ/ሚሩ ከፍተኛ የአንበሳ ጥላቻ እንዳላቸው መጽሐፋቸው እርካብ እና መንበር ውስጥ ጽፈውታል፡፡ አንበሳውንም በፒኮክ ቀይረዋል፡፡ ከዋቅ ጥቁር እጆች ጋር በብልጽግና አርማ ውስጥ የተሳለችው ፒኮክ፣ በቤተ መንግስት በር ላይ እንደ ኪሩቤል ወዲያና ወዲህ የቆመችው ፒኮክ፣ ከላይ እንዳየንው መለኮታዊነት ስትላበስ ለአዳም አልሰግድም ብሎ ያለውን በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ያዚዲ በመባል የሚታወቁ የእምነት ጎራዎች የሚያመለኩት መላከ ጣዎስ ነው የሚሆነው፡፡ ይህም በእስልምናና በኦርቶዶክስ እምነት መጽሐፎች ላይ እንደሚነበበው ሴይጣንን አመላካች ነው፡፡ ፈጣሪ ለአዳም ስገድ ሲለው እንቢ ያለው መላክ በእስልምና ኤብሊስ በኦርቶዶክስ እምነት ደግሞ ሴይጣን ነው፡፡
ይህን ሁሉ ትርጉም ሊሰጠው በሚችል ሁኔታ ፖለቲካን ከእምነት ጋር አደባለቆ በመመሰል ጣጣ ውስጥ መግባት ከምን የሚመነጭ ነው? የእራስን ድብቅ እምነትና አመለካከት በሌሎች እምነቶች ውስጥ ቀስ ብሎ የማስረጽ አካሄድ ካልሆነ በቀር? ለምንስ ይህ ያሰፈልጋል? ሴኩላሪዝም ማንን ገደለና?
በነገራችን ላይ ያዚዲ ቤተመቅደሶች በር ላይ የእመነቱ ተከታዮች ተሳልመው የሚገቡት እባብ አለ፡፡ አሁን ወደ ጃዌው(እባቡ) እንመለስ፡፡ እባብ የራሱን ዝርያ የሚሰለቅጥ፣ የሚውጥ እንሰሳ ነው፡፡ ጠ/ሚሩስ ቢሆኑ ስንቱን ሰለቀጡት፡፡ እነ ቲም ለማ፣ ገዱ፣ እነ ጀዋር.. አጋራቸው የነበረውን ፋኖን ደግሞ አሁን ጀምረውታል፡፡ የሚሳካላቸው ግን አይደለም፡፡ጃዌ እባብ በመንደፍ ብቻ ሳይሆን መርዙን ሌሎች አይን ላይ በመርጨት አይን ማሳወር ይችላል፡፡ በጠ./ሚ አይናቸው ታውሮ ገደል አፋፍ ላይ የደረሱትን መቁጠሩን ለአንባቢዎች ትቼለሁ፡፡
ሃገሪቱ በአራቱም አቅጣጫ ጦርነት ላይ ሆና፣ ርሃብ(ፖለቲካ ሰራሹን ጨምሮ) ህዝቡን እየቆላው፣ ህዝቦች ለመበጣጠስ በመቀነስ ላይ እያሉ፣ የመደመር ቱሪናፍ አሁንም ይለፈለፋል፡፡ መለኮታዊ መሪ አለን እያሉ የሚናገሩ ሰዎች ቁጥር ትንሽ አይደለም፡፡ ሰው ነቅሎ ዛፍ መትከል የመሪው መርሆ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡
አምባገነኖች ከፊታቸው ያለውን ጥፋታቸውን ማየት ሲሳናቸው ታሪክ ደጋግሞ አሳይቶናል፡፡ ከእውነትም ከህዝብም ተነጥለው ሲሄዱ አይታወቃቸውም፡፡ጃዌ አንዳንድ ግዜ የራሱ ጭራ ሊያጠቃው የመጣ ሌላ የሚበላ እንስሳ ይመስለውና እራሱን ከጭራው ጀምሮ መዋጥ ይጀምራል፡፡ ብልጽግናም በጠ/ሚ አመራር ይሆንኑ እያደረገ ነው ያለው፡፡ ጃዌ(እባብ) በተፈጥሮው አንገቱ ከተቆረጠ በኋላ ወዲያው አይሞትም ለሰአታት በህይወት ሊቀጥል ይችላል፡፡ የተቆረጠው አንገቱ ብቻ ይናደፋል፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የጃዌው ጭንቅላት ከአካሉ ጋር ያልተለያየ ይምስላችኋል? ሂዱና አማራ ክልል ፈልጉት፡፡ ኦሮሚያ ውስጥ …ሌሎቹ ክልሎችም ይቀጥላሉ…
አስቻለው ከበደ አበበ
ሜትሮ ቫንኩቨር ካናዳ