ዶ/ር በቀለ ገሠሠ (drbekeleg@gmail.com)
ሀ) መንደርደሪያ፣
ዛሬ የአማራ ህዝብ በታላቅ እንግልትና መከራ ውስጥ ይገኛል። የኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት ፈተና ውስጥ ገብቷል። አፍሪቃ በኢሣት ላይ ይገኛል። ምክንያቶቹ የውስጥና የውጪ ጠላቶች ናቸው። የውጪ ኃይሎች ለህዝብ መቆርቆር ሳይሆን ማፍረስ፣ ማዳከም፣ አፍሪቃን ወደባርነት መመለስና መበዝበዝ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ አንዱ ጎሣ ጠፍቶ ሌላው በሰላም ይኖራል ብሎ መገመት ትልቅ ሞኝነትና እብደት ነው። የውጪ ኃይሎችም በዚህ ከቀጠሉ ለእነርሱም እጅግ ሊያሰጋ እንደሚችል ሊነገራቸው ይገባል። ስለዚህ ሁሉም መተባበርና ሰላም ማውረድ ይኖርበታል። ካለዚያ ተያይዞ መጥፋትንና ባርነትን ያስከትላል። ነገሮች ከመባባሳቸው በፊት ወደሕሊናችን ተመልሰን አብረን በሰላም ብንኖር ይመረጣል፣ እግዚአብሔር የሚወደውም ይህንን ነውና።
ለ) ኢትዮጵያን የመበተን ሤራ፣
በጣሊያኖች፣ በእንግሊዞች፣ በቱርኮች፣ በግብፆች ስንወረር አቸነፍናቸው፣ አሳፈርናቸው። በዚያ ቂም ያዙብን። ሸዓቢያን የረዱት ለኤርትራ ህዝብ አስበው አይደለም። ወያኔንና ኦነግን የረዱት ለትግራይና ለኦሮሞ ህዝብ ተቆርቁረው አይደለም።
ዓላማቸው አማራን ካዳከሙ በኋላ ኢትዮጵያን ለመበተን ነው። ከዚያ በመቀጠል የአፍሪቃን አንድነት ለመበተንና ወደባርነት ለመመለስ ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ሊግ ኦፍ ኔሽን በ1923 ዓ/ም የተቀላቀለች አንዷ ብቻ የአፍሪቃ አገር ናት። በዚያ መድረክ ላይ ቆማ የጣሊያንንም ወረራ ለዓለም አቀፍ ህብረተሰቦች ያጋለጠች ናት። በ1945 ዓ/ም የዓለም መንግሥታትን ከመሠረቱ አገራት አንዷ ነበረች። በ1963
ዓ/ም በአፍሪቃ ህብረት ምስረታ ላይ ቁልፍ ሚና ተጫውታለች። በቅኝ ለተያዙት የአፍሪቃ አገራት ከፍተኛ ድጋፍ ሰጥታለች።
ስለዚህ የአፍሪቃ ህብረትን ለማፍረስ ያመቻቸው ዘንድ መጀመሪያ አማራን ማዳከም፣ ቀጥለውም ኢትዮጵያን ማፍረስ ይፈልጋሉ። ከዚያ የሚያተርፍ አንድም የኢትዮጵያ ጎሣ ሊኖር እንደማይችል አውቀን ብንጠነቀቅ መልካም ነው።
ብዙ ምሣሌዎች መጥቀስ እንችላለን። ኢራቅን፣ አፍጋኑስታንን፣ ሊብያን፣ ወዘተ የወረሩት ለኢራቅ፣ ለአፍጋኒስታን፣ ለሊብያ፣ ወዘተ ህዝብ ብለው አልነበረም።
ዛሬ ደግሞ ኒጄርን፣ ማሊን፣ ቡርኪና ፋሶን፣ ወዘተ እያወኩ የሚገኙት ለህዝብ ጥቅም ሳይሆን ማዕድኖችንና ነዳጆችን ለመዝረፍ ብቻ ነው።
ስለዚህ እነዚህን ከባድ ሤራዎች ተገንዝበን አንድነት ፈጥረን በሰላም የምንኖርበትን መንገድ ማመቻቸት ብቻ ነው የሚበጀን። ሰው በሰላም ገብቶ ምፕውጣት አለበት። ገበሬው በሰላም ወጥቶ ማረስ አለበት። ነጋዴው በሰላም ተዟዙሮ መነገድ አለበት። ወጣቶችን ወደ ትምህርት ቤት እንጂ ለጦርነት ወይም ለስደት መማገድ ትልቅ ኃጢአት ነው። እጅግ ካልተጠነቀቅን ተያይዞ መጥፋትን ያስከትላል። ከቅርብና ከሩቅ ታሪኮች መማር ይኖርብናል።
የእግዚአብሔር በረከት ይጨመርበት።