ሐሙስ፣ ሐምሌ ፳ ፻ ቀን ፳ ፻ ፲ ፭ ዓ. ም. (7/27/2023)
የጎሳ ፖለቲካ በኢትዮጵያ ሕልውና የተሰነቀረ ስለት ነው።
የአንድ አገር የፖለቲካ ተሳትፎ መደረግ ያለበት፤ በዜግነት በተመሠረተ የአመለካከት ተመሳሳይነት ስብስብ ነው። ይሄ መሠረታዊ እውነታነት ያለው የተለመደ ሂደት ነው። በትውልድ ትሥሥር የተመረኮዘ ድርጅት፤ የፖለቲካ ርዕዩተ ዓለም የለውም። ይሄም ሀቅ ነው። አማራ ብሎ ርዕዩተ ዓለም የለም። የአማራ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ብሎ በርዕዩተ ዓለም የታገዘ የፖለቲካ ግንዛቤም የለም። ይሄ ሁሉ ትክክል ነው። በትክክል፤ የጎሳ ፖለቲካ በኢትዮጵያ ሕልውና የተሰነቀረ ስለት ነው። ወደፊት ለመሄድ፤ መጀመሪያ ይሄ ስለት ተነቅሎ መውጣትና መጣል አለበት። በሌላ በኩል ደግሞ፤ የፖለቲካ ትግል የሚካሄደው፤ በፅንፈ ሃሳብ ወይንም በአዕምሮ በመነጨ ትርክት ሳይሆን፤ በተጨባጩ የአገር የፖለቲካ እውነታ ነው። አሁን ባለንበት የፖለቲካ እውነታ፤ አማራው የግድ መደራጀት ያለበት መሆኑን የሚያስረዳ ትንታኔ አለኝ። እናም ንባብዎን ይቀጥሉ።
መጀመሪያ ይሄን ጽሑፍ እንዳዘጋጅ ያደረገኝን ላስረዳ። አገር ወዳድ ለሆን ኢትዮጵያዊያን በሙሉ፤ አገራችን ወደ መፍረስ መንገድ እንዳትጓዝ ምን መደረግ አለበት? የሚለው በጣም አሳስቦናል። ለዚህም ዋና መፍትሔ ብለን ሁላችንም የምናራምደው፤ በጎሳ የተመሠረተን የፖለቲካ ስርዓት ማስወገድ ነው። ይሄ ጥሩ ምኞት ነው። በርግጥ ሁሉም ነገር ከምኞት ይነሳል። ነገር ግን፤ የአንድ አገር የፖለቲካ ሂደት በተግባር የሚከናወነው፤ በአገሪቱ ካለው ተጨባጭ የፖለቲካ እውነታ ተነስቶ እንጂ፤ የግል ፍላጎታችንን ተመርኩዞ አይደለም። የአገራችን የፖለቲካ ክንውን፤ በተለይም ያለው ተጨባጭ እውነታ፤ ያለንበትን ፖለቲካ አሽከርካሪ ነው። አሁን አገራችን ላለችበት የፖለቲካ ሀቅ የዳረገን፤ በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር የተተከለው የጎሳ ፖለቲካ ሲሆን፤ በመቀጠልም የኦሮሞዎች ነፃነት ግንባር ይሄንኑ በከፋ ሁኔታ እንዲቀጥል ማድረጉ ነው።
አሁን በአገራችን ውስጥ፤ የጎሳ ፖለቲካን መሳሪያ አድርገው በሥልጣን ላይ የተቀመጡ የኦነግ መሪዎች፤ ተረኛ ነን ብለው፤ ይሄንኑ የጎሳ ፖለቲካ ተጠምጥመውበት እየገዙ ነው። ይህ ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ግዛት የቀጠለው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር የጎሳ ፖለቲካ ስርዓት፤ በትኩረት “ኢትዮጵያን አፍርሼ የራሴ አድርጌ ጠፍጥፌ ለመመሥረት፤ አማራው ፅኑ ኢትዮጵያዊ ሆኖ አስቸግሮኛልና፤ ላጥፋው!” ብሎ ዘመቻ ከፍቷል። የአማራው ጥፋት፤ “ኢትዮጵያዊ ነኝ!” ብሎ መጋተሩ ነው። በአማራዎች ላይ እየደረሰ ያለው በደል፤ ስለ አማራዎች እንዲህ ወይንም እንዲያ መሆን ሳይሆን፤ ስለ ፀረ–አማራዎች እውቀት ማነስ፣ ግትርነትና አረመኔነት ነው የሚነግረን። አማራዎች የማንንም ሀብት አልዘረፉም፣ የማንንም መሬት አልወሰዱም፣ የማንንም ባህል አልደፈሩም፤ ይልቁንም ማንነታቸው ወንጀል ሆኖ እየተበደሉ ናቸው። ይሄ ሀቅ ነው።
ይሄ ያለንበት ሀቅ ሆኖ፤ አሁን አማራዎች፤ “አማራነታችን ወንጀል አይደለም!” “በአማራነታችን የትም የአገራችን የኢትዮጵያ መሬት ሰፍረን መኖር እንችላለን!” “በአገራችን በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት እኩል ከሌሎች ጋር መሳተፍ መብታችን ነው!” ብለን ተነስተናል። ለኔ ይህ የያንዳንዱ ኢትዮጵያዊና ኢትዮጵያዊት ጉዳይ ነው። ይህ የአማራዎች ብቻ ጉዳይ አይደለም። እናም ሁሉም ኢትዮጵያዊያን አብረውን ሊቆሙ ይገባቸዋል። አዎ! አማራዎች አምፀናል። አዎ! አማራዎች በአማራነታችን ተደራጅተናል። የተደራጀንበት ያንተም፣ ያንቺም፣ የርስዎም ጉዳይ ነው። በአማራነታችን ልንደራጅ ያስገደደን፤ የአማራ መንግሥት ለማቋቋም ስለፈለግብ አይደለም። በአማራነታችን እንድንደራጅ ያደረገን፤ አማራነታችንን በሌሎች ላይ ለመጫን አይደለም። በአማራነታችን የተደራጀነው፤ “አማራ መሆን ወንጀል ነው!” ብለው ስለተነሱብን፤ ይሄን ለመቋቋም ነው። ይሄ ደግሞ የእያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ ነው። በትክክል ይሄን ለመቋቋም፤ አማራ መሆን ወይንም በአማራነት ብቻ መደራጀትና መታገል ግድ አይደለም። ነገር ግን፤ በተጨባጩ ነባራዊ ሀቅ፤ አማራ ናችሁና ልግደላችሁ ስንባል፤ አዎ! አማራዎች ነን! በአማራነታችን ደግሞ አንገደልም! አማራነታችንን ማስከበር እንችላለን! ብለናል። አገራችን ኢትዮጵያ ናት! ከዚህ የሚያነቃንቀን ማንም የለም! ብለናል። አማራዎች “እኛ!” “እናንተ!” የሚል አጥር የለንም። እናም ይሄን በጎሳ የተመረኮዘ ጥቃት፤ እያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያን መቃወም አለብን። የአማራዎች መደራጀት፤ ኢትዮጵያዊነትን ለመጠበቅ ነው። በአማራነት ላይ የተነሳው የአክራሪ ኦሮሞዎች ዘመቻ፤ ነገ በሌሎች ላይ የሚጫን ፍዳ ነው! ዛሬ ከአማራዎች ጎን መቆም፤ ነገ የራስን ሕልውና መጠበቅ ነው። አማራዎች ከኢትዮጵያ መሬት ቆርሰን፣ ከኢትዮጵያ ነፃ ልንወጣ፣ ሌሎችን አማራዎች ለማድረግ አልተነሳንም።
ለሕዝባዊ አመጽ መነሻ የሚሆነው፤ በአገሪቱ ያለው የፖለቲካ እውነታ ነው። ለአመጽ የሚገፋውን ሂደት የሚወስነው፤ የአገሪቱ የአገዛዝ ስልት እየሄደበት ያለው መንገድ ነው። ዛሬ ከሰላሳ ዓመታት በላይ በጎሳ ፖለቲካ ተተብትቦ የተያዘውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት ለማፍረስና ትክክለኛ አገራዊ የፖለቲካ ስርዓት የማንገሥ መንገዱ፤ ስርዓቱ ደካማ በሆነበት ቦታ ሲበጠስ ነው። ደካማ ጎኑ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለው አማራ መደራጀቱና ሌሎቹን በጎኑ እንዲሰለፉ ማድረጉ ነው። በአእምሯችን ብቻ በሳልነው እውነታ፤ ኢትዮጵያዊያን ተሰባስበው የሚታገሉበት የፖለቲካ መድረክ መፍጠር፤ ከምኞት አያልፍም። “አይሁን!” የሚል የለም። ነገር ግን፤ ባሁኑ ሰዓት ይሄ ይሆናል ብሎ ማሰቡ፤ ከተጨባጩ ሀቅ ጋር አይዛመድም። እናም ቀዳዳው፤ ከአማራው ጎን ተሰልፎ፤ ማንም በማንነቱ መጠቃት የለበትም፣ የትውልድ ማንነት በአገራችን የፖለቲካ ምሕዳር መሳተፊያ መሆን የለበትም! መጠቂያም መሆንም የለበትም! ብሎ መነሳት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ፤ “ኢትዮጵያ!” “ኢትዮጵያ!” ማለታቸው ብቻ ሳይሆን፤ “ሚሊዮን ዛፎችን ተከልኩ!” “በተቀበሩበት ጥላ እንዲያገኙ አደረግሁ!” “ሕጋዊ ደሃ አደረግኋቸው!” እያሉ በተግባር ምን እያደረጉ እንደሆነ ሁላችን እያየን ነው። ቅን የሚሏቸው አሉ። ግለሰቦችን ቅን ወይንም ሀቀኛ የሚያደርጋቸው፤ ሰዎች የሚፈልጉትን ተናጋሪነታቸው ሳይሆን፤ ከሰዎች ፍላጎት ውጪ እውነታውን ተናጋሪነታቸው ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ለኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ተግባራዊ ያልሆነ፤ “ኢትዮጵያ በደሜ!” ይላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ለኦሮሞ ፅንፈኞች፤ እነሱ የሚፈልጉትን መናገር ብቻ ሳይሆን፤ የሚፈልጉትንም እያደረጉላቸው ነው። በያዝነው ሂደት፤ የአክራሪ ኦሮሞዎች የበላይነት እንጂ፤ የአዲሲቱ ኢትዮጵያ በትክክለኛ የዴሞክራሲያዊ መንገድ ተጓዥነት ይመጣል ብሎ መመኘት፤ የዋህነት ነው።
ለማጠቃለል፤ ጥቂቶቹ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን፤ በዛ ያሉት አማራዎች ናቸው፤ “ኢትዮጵያ የምትድነው የጎሳ ፖለቲካ ሲወገድ ነው!” እናም “በአገር አቀፍ ደረጃ ስንሰባሰብ ብቻ ነው ትክክል የሚሆነው!” ይሄ ካልሆነ፤ “ኢትዮጵያ ትበታተናለች!” ብለው ቆመዋል። ይህ አቋም ግን ሊሠራ የሚችለው፤ ሁሉም ነገር ትክክለኛ መስመር ሲይዝ ነው። አሁን ያለንበት የተመሰቃቀለው የፖለቲካ ሀቅ፤ በትክክለኛ መንገድ የሚያስኬድ ሳይሆን፤ ማረሚያ የሚፈልግ እውነታ ነው። ለማረም ደግሞ፤ የጎበጠውን ወደ ተቃራኒው ማጉበጥ ያስፈልጋል። በትክክል ከተያዘና መንገድ ካልሳተ፤ በአማራነት ተደራጅቶ መታገል ትክክለኛ መፍትሔ ነው። ለዚህ ማስተማመኛው፤ አማራዎች መላ ኢትዮጵያን አገራችን ያልን መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፤ አማራነትን የፖለቲካ ስርዓት ሳናደርግ፤ ራስን ከጥቃት ለመከላከያ መታገያ ማድረጋችን ነው። አማራዎች፤ ይሄ የኔ! ያ የኢትዮጵያ! የምንለው የለንም። ሁሉንም ነገር ለኢትዮጵያ አስረክበናል። እናም ከኢትዮጵያ ተለይተን የምንቆምበት መሬት የለንም። የአማራዎችን ኢትዮጵያዊነት ለማወቅ ቆዳችንን መፋቅ አያስፈልግም። ራሱ ቁመናችን ከቅርብም ከሩቅም ኢትዮጵያዊነት ነው።