ይህንን የዛሬውን ጽሁፌን ከመጻፍ ይልቅ ምን ርእስ ልስጠው እሚለው ነበር ቀናቶችን የፈጀብኝ። ብዙ ሰዎች በዚች አጭር አርባ ምናምን አመትህ እንዴት ይህንን ሁሉ ሰው አገኘህ? ብለው ይጠይቁኛል። ሀሜተኞቹም በደካማ አእምሮአቸው ስም ያወጡልኛል። ሳገኛቸው እጅግ ስሜቴን መቆጣጠር ካቃተኝ ውስጥ አንዱ ዶ/ር አረጋዊ በርሄን ነበር። በርግጥ የቦብ ማርሌን እናት፣ የሱፍ ያሲንን፣ ልኡል ዶ/ር አስፋው ወሰንን፣ የጋናውን የዲሞክራሲ አባት ጀሪ ሮቢንሰንን፣ በ1977 we are the world በሚል ያቀነቀነውን ቦብ ጊልዶፍን ( አቶ ገ/መድህን ስለ ገንዘቡ የት ገባ ያጋለጠውን) በህይወት አጋጣሚ ሳገኛቸው ተመሳሳይ ስሜት ተሰምቶኛል።
በ2016 እኤአ ጀኔቫ ከተማ ከዋናው ለገሀር ፊት ለፊት ካለች ላብራሴር የምትል ቢራ ቤት ከሶስት ሀበሾች ጋር ቁጭ ብየ እነሱ ቢራ ይጋብዙኛል። እውነት ለመናገር በወቅቱ ት/ት ቤቴ የሚሰጠኝን አበል ጀኔቫ ላይ እንኳን ቢራ ሊያስጠጣ የትራንስፖርት ትኬት ለመግዛት እቸገር ነበር።
የተለመደውን የፖለቲካ ክርክር ከእነዛ ውድ ኢትዮጵያውያን ጋር እያደረግን ድንገት አንድ ቁመተ መለሎ፣ አፍንጫው ስልክክ ያለ ድምጹ ጎርናና ሰው ሰላምታ ሰጥቶን ቁጭ አለ።
ዶ/ር አረጋዊ ነው ተዋወቀው አሉኝ። እኔ ይህንን ድምጽ የት ነው እማውቀው፣ ፊቱም አዲስ አልሆነብኝ እያልኩ አእምሮየን በማስጨነቅ ላይ ነበርኩ።
በአእምሮየ ከልጅነቴ ጀምሮ በዶቼቨሌ፣ በቪኢኤ፣ በጦቢያ መጽሄት ዘወትር የምከታተለው ሰው ነው። በተጨማሪ ስለ ህወሓት ታሪክ የመመረቂያ ጽሁፉን ልቅም አድርጌ አንብቤው ነበር። ዝም ብየ ፊቱን እያየሁ የጀመሩትን ውይይት አዳምጥ ጀመር። ተጫዎት እንጅ? ይሉኛል እነ ውሂበ። ለአርባ አመት ሀገሩ ገብቶ የማያውቅ ሌላው አስደናቂ ታሪክ ያለው ሰው።
ይቅርታ ዶ/ር ዛሬ አንተን በዚህ አጋጣሚ ስላገኘሁህ የተሰማኝን ደስታ ልገልጽህ አልችልም። መጽሀፍን አንብቤዋለሁ። በአእምሮየ የሚመላለሱብኝ ሶስት መሰረታዊ ጥያቄዎች አሉኝ ፈቃደኛ ነህ ትመልስልኛለኝ? አልኩት።
ስሜቱ ቅጭም ብሎ እሽ እሞክርራለሁ ብሎ ጎንበስ አለ። ሌሎቹ ጠይቀው፣ ጠይቀው አሉኝ።
ጥያቄ አንድ፣
“””””””””””””””’
እናንተ ሶስት ሽህ ዘመን በፊት ከተሰራ የአክሱም ሀውልት ስር፣ ከየሀ ቤተ መቅደስ አጠገብ፣ ኢዛና በድንጋይ ላይ ቀርጾ ከጻፈው ጥንታዊ ቅርስ አጠገብ አፈር እየፈጫችሁ አድጋችሁ ስለምን የኢትዮጵያ ታሪክ 100 አመት ነው ብላችሁ ለመነሳት ደፈራችሁ?
ጥያቄ ሁለት፣
“”””””””””””””””
የትግራይ ህዝብ ከዘጠኙ ቅዱሳን፣ እስከ ቅዱስ ያሬድ ዜማ፣ ከአብርሀ አጽብሀ እስከ ጽዮን ቤተክርስትያን ድረስ ታሪኩን እየሰማችሁ፣ በእጃችሁ እየዳሰሳችሁ፣ በአይናችሁ እያያችሁ አድጋችሁ ” ኦርቶዶክስ ጠላታችን ነው” አላችሁ? ለማፍረስስ በሽዎች የሚቆጠሩ ወጣት ካድሬዎችን አሰልጥናችሁ ሰገሰጋችሁ?
በተጨማሪም የትግራይና የአማራ ህዝብ በቋንቋ፣ በባህል፣ በታሪክ፣ በሀይማኖት፣ በጋብቻ፣ በኩታ ገጠም አሰፋፈር፣ በስነ ልቦና አንድ ሁኖ ” አማራ ጠላታችን ነው” ብላችሁ ተነሳችሁ? ምን ነበር ዋና ምክንያታችሁ?
ጥያቄ ሶስት፣
**””””””””””””
በ1967 /ዓም ወደ ጫካ ስትወርዱና ያንን ማኒፌስቶ ስታወጡ ለመጀመሪያ ግዜ ድጋፍ ያደረገላችሁ ግለሰብ፣ ድርጅት ወይም አገር ማን ነበር?
ብየ ዶ/ር ኤልያስ ጨቡድ ስለ ጥናታዊ ጽሁፍ አወጣጥ ያስተማረኝን እጅግ አጭር ግን መጽሀፍ የሚወጣቸው የተጨመቁ ጥያቄዎችን አቀረብኩለት።
ለተወሰነ ደቂቃ ዝም አለ። ይገርምሀል እስከ አሁን የዚህ አይነት ጥያቄ ጠይቆኝ የሚያውቅ ሰው የለም። እስኪ እምችለውን ልሞክር አለኝ።
እኛ በወቅቱ ወጣቶች ነን። እውቀታችን ውስን ነው ። ሁሉን ከእኛ በፊት ያለውን ነገር ሁሉ ፊውዳሊዝም የሰራው በመሆኑ መወገድ አለበት ብለን እናምን ነበር። እኔ ትግሉን አቁሜ ወደ ኖርዌይ ሂጄ ኦስሎ ዩንቨርሲቲ ላይብረሪ ውስጥ እጅግ ግዙፍ መጽሀፍ ከሁለት ሽህ አመት በፊት አንድ ማኒ እሚባል የፋርስ ፈላስፋ የጻፈውን አክሱም የሚል መጽሀፍ ካነበብኩ በኋላ ደነገጥኩኝ። እኛ ምንም እንደማናውቅ ገባኝ።
አማራን በተመለከተ እኛ ህዝቡን ሳይሆን የአማራን ፊውዳልን ነበር ጥላት ያልነው። ኦርቶዶክስንም እንዲሁ ከፊውዳሊዝም ጋር አገናኝተነው ነው። እርዳታ የሰጣችሁ ማነው ላልከኝ ያው ትግል ስትጀምር መጀመሪያ በራስህ ሀብት ትጀምራለህ፣ ምርኮ ትማርካለህ ጉልበት እያወጣህ ስትመጣ ሁሉን ወደ አንተ ይመጣል። ብሎ መለሰልኝ። መልሱ አላረካኝም። ግን ቀጥየ መከራከር አልፈለኩም።
እነሆ ዛሬ ሁሉም ፍንትው ብሎ ለሁላችንም ግልጽ ሁኖ መጣ። በማኒፌስቶው ላይ አማራ ጠላታችን ነው፣ ኦርቶዶክስን እናፈርሳለን ብለው ገና ከጧቱ ወጣቶችን መልምለው ግማሾቹ ወደ ቤተ ክህነት ፣ግማሾቹ ወደ ቤተ መንግስት አንድ አይነት የፖለቲካ ርእዮት ጠጥተው ተሰማርተው እነሆ ፖለቲካውን እነ ደብረ ጽዮን ፣ ቤተ ክህነቱን እነ አቡነ መርሀ ክርስቶስ ተቆጥጥረው አንድ ወንበር ላይ በጋራ ቁጭ ብለዋል።
ከሀምሳ አመት ጉዞ በኋላ ለዚህ ደረጃ በቅተዋል። ኢትዮጵያን እናፍርስ ብለው በመቶ ሽህ ወጣት አስበልተዋል፣ ህዝቡን ቅጠል እስኪበላ ድረስ አድርሰውታል። እነሆ አሁን ቤተክርስቲያኑን አፍርሰው የሚመጣውን በጋራ እናያለን።
መልካም የመገንጠል ዘመን። የወደዳችሁትን አድርጋችኋል። ሽፍንፍኑ ሁሉ ግሀድ ወጥቷል። ተጨማሪ ጥያቄም መልስም አያስፈልገንም።
ይቆየን
–