ከጥፋት ውሀና ከገሞራም ከፍተን፣
ጵጵስና ቅብጠት ቅንጦት ሲሆን አየን፡፡
ምንኩስና እርዛት እራብ ነው ቢባሉ፣
እንደ ፈረንጅ ቀበጥ ኬክ ሲገምጡ ዋሉ፡፡
ብፁእ ቅዱስ ነን ብለው የጰጰሱ፣
ተገደን አጳጰስን እየወሸከቱ፤
ተእግዜር እጅ አምልጠው ሰይጣን ጉያ ገቡ፡፡
የሰማዩን ንጉሥ ታዘዙ ቢባሉ፣
ለምድር ገዥ ሎሌ ሆነው ይኖራሉ፡፡
በጋችሁን ጠብቁ ታደጉ ቢላቸው፣
ድሎት ይበላሉ ቀበሮ አሳርደው፡
ሰማእትነት ቢያሳይ ፍሪዳ አድርጎ እራሱን
እነሱ አሳረዱ በግ አርገው ምዕመን፡፡
ፍሪዳው አርጎ ቁጭ ሲል ተእግዜር ቀኝ፣
በግ አሳራጆቹ ሄሮድስ ማረን ማረን፡፡
ከተራራ አውጥቶ ጌታን የፈተነው፣
በአውላላው ሜዳ ላይ አንበረከካቸው፡፡
የክርስቶስን ደም መስቀል አንጠልጥለው፣
ለሄሮድስ ሲሰግዱ አይሰገጥጣቸው፡፡
መጣፈ መነኮሳት መንኑ ቢላቸው፣
ይተም ይፈሳሉ ከተማ ውስጥ ቀልጠው፡፡
አትዩ፣ አታሽቱ አትስሙ ቢባሉ፣
ቀንበጥን ሲመርጡ ሲያሸቱ ያድራሉ፡፡
ተገንዘብ እራቁ ብሎ ቢያዝዛቸው፣
ደሞዝና ዝርፊያ ሆኗል ዝማሬአቸው፡፡
ለቀኖኗ ዶግማ ምዕመናን ታርደው፣
ሲኖሩ አይከብዳቸው እርምን ቅርጥፍ አርገው፡፡
ከሰዶም የከፋ እንዲህ ዓይነት ዘመን፣
ጳጳስ የዓለም ወዳጅ ሰማእታት ምዕመን፡፡
በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
ሐምሌ ሁለት ሺ አስራ አምስት ዓ.ም.