May 15, 2023
54 mins read

 በኢትዮጵያውያን ምሁራን ፎረም ላይ ስሜን በመጥቀስና ካለአግባብ በመክሰስ ለዶ/ር ኤሌኒ ገብረመድህን ጠበቃ በመሆን ለወነጀለኝ ለዶ/ር ብርሃኑ አበጋዝ የተሰጠ መልስ!

ፈቃዱ በቀለ (/)

ግንቦት 15 2023

ዶ/ር ብርሃኑ አበጋዝ ቀደም ብዬ ባወጣሁት በአገራችን ምድር “በገበያ ኢኮኖሚ ስም ሰለሚሰራው ወንጀል” ያወጣሁትን ጽሁፌን አስመልክቶ የዶ/ር ኤሌኒ ገብረመድህን ስም ስለተጠራና ስለተወነጀለችም፣ ይህ ዐይነቱ ክስ በሳይንስና በተጨባጭ ማስረጃዎች የተረጋገጠ አይደለም በማለት ስድብ አዘል ጽሁፍ በመጻፍ ምሁራን ነን በሚሉ በኢትዮጵያውያን ፎረም ላይ እንዲነበብ ለማድረግ በቅቷል። አስተሳሰቤንም የጨቅላ አስተሳሰብ ነው በማለት አንድ ምሁር ነኝ ከሚል የማይጠበቅ ስድብ ሰንዝሯል።

በመሰረቱ አንድ ሰው ሲተች ያ የተተቸው ሰው ነው የሰነዘርከው ትችት ትክክል አይደለም ብሎ መልስ መስጠት የሚገባው። ይህ ከመሆኑ ፈንታ ግን ብርሃኑ አበጋዝ የኤሌኒ ገብረመደህን ጠበቃ፣ ወይም የሷ ቃል-አቀባይ ይመስል “በጨቅላ አስተሳሰብህ በመነሳት ነው በዓለም ላይ ተወዳዳሪነት የሌላትን ኢኮኖሚስትና፣ አብረን የምንሰራ ጓደኛችንን የሰደብክብን” በማለት ያላግባብ ዘልፎኛል። እንደምረዳው ከሆነ ጽሁፌን በደንብ የተመለከተ፣ ወይም ያነበበ አይመስለኝም። ያነበበው ከሆነ ደግሞ ሀተታዬንና የተመረኮዝኩበትን የቲዎሪና የሳይንስ መሰረት በፍጹም አልገባውም ማለት ነው። በኢኮኖሚክስ ቲዎሪና ፖሊሲ ውስጥ የተለያዩ አተናተኖችና የአሰራር ስልቶች ስላሉ ኢኮኖሚስት ነን የሚሉ ሁሉ አንድን ተጨባጭ ሁኔታ በማንበብና በመረዳት ተመሳሳይ ዘዴን አይከተሉም። ይህ ዐይነቱ አመለካከትም በፍልስፍና ውስጥ ያለ ሲሆን፣  በአንድ በኩል ሁኔታዎችን በጥልቀት የማየትና የአተናተን ዘዴ ሲኖር፣ በሌላ ወገን ደግሞ የተወሰኑ ያሸበረቁ ነገሮችን መሰረት በማድረግ ለመጻፍና መፍትሄም ለመፈለግ ይሞከራል። በጥልቀት የሚያስቡ ፈላስፋዎች ራሽናል አስተሳሰብ ያላቸው ሲሆኑ፣ ለአንድ ነገር መከሰት ምክንያት እንዳለው በማስቀመጥ በተለያዩ ነገሮች መሀከልም መተሳሰር እንዳለ፣ አንደኛው በሌላኛው ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ያመለክታሉ። በዚህ የአመለካከትና የአተናተን ዘዴም የችግሮችን ምንጭ ወይም ሀቀኛውን መንገድ በማግኘት ትክክለኛውን መፍትሄም ይጠቁማሉ። በአገራችን ያለው ትልቁ ችግር በተለይም እንደ ኢኮኖሚክስ የመሳሰሉ በ20ኛው ክፍለ-ዘመንና አሁንም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰጠው ትምህርት መቼ እንደፈለቀና ከምንስ አንፃርና ማንስ እንደጻፈው ስለማይታወቅ ዝም ብሎ አሜን ብሎ በመቀበል እሱን እየደጋገሙ መማር ዋናው የትምህርት ዘዴ ሆኗል። በሌላ ወገን ደግሞ ይህ ዓለም አቀፋዊ የሆነው የኢኮኖሚክስ ትምህርት በአንድ አገር ውስጥ የሚኖሩ ወይም የሚታዩ ተጨባጭ ሁኔታዎችን ለማንበብ ያስችል ወይም አያስችል እንደሆነ ማንም አይጠይቅም። በዚህ መልክ የተዋቀረውና ዓለም አቀፋዊ ባህርይ እንዲወስድ የተደረገው የኢኮኖሚክስ ትምህርት ንፁህ በንፁህ ቀኖናዊ በመሆን በተለይም በእኛ አገር ኢኮኖሚክስን የሚማር እማሪ እንደ ቀኖና በመውሰድ ጥያቄ በሚጠየቅበት ወይም ትችት በሚቀርብበት ጊዜ ወደ ኩርፍያ አልያም ወደ ስድብ ማምራት የተለመደ ሆኗል ማለት ይቻላል። ሌላው በአብዛኛዎቻችን ዘንድ የማይታወቀው በኢኮኖሚክስ በአስተሳሰብ የዕድገት ታሪክ ውስጥ የዛሬው ዓለም አቀፋዊ የሆነ የመማሪያ ዘዴ፣ በተለይም ኒዎ-ክላሲካል ወይም ኒዎ-ሊበራል የሚባለው አስተሳሰብ ከመፍለቁ በፊት ሌሎች የኢኮኖሚክስ አስተሳሰቦች እንደነበሩ ለአብዛኛዎቻችን ግልጽ አይደለም። እነዚህም ፊዚዮክራቲ፣ መርከንታሊዝም፣ ጥንታዊ የኢኮኖሚክስ ትምህርት(Classical Economic Theory)፣ የማርክሲስት ኢኮኖሚክስ ቲዎሪ፣ ከታሪክ አንፃር የሚታይ የኢኖሚክስ ትምህርት(Historical Schools)፣ የተቋማት ግንባታ የኢኮኖሚስ ትምህርትና(Institutional Economics) የኬይኔሲያን የኢኮኖሚክስ አስተሳሰብ በመባል ይታወቃሉ። በዛሬው ዘመን ያለው ትልቁ ችግር እነዚህ ሁሉ እንዳልነበሩ ሁሉም አሜን ብሎ እንዲቀበለው በማድረግ ኢኮኖሚክስን የሚማሩ ሁሉ፣ በተለይም የሶስተኛው ዓለም አገር ተማሪዎች አዕምሮአቸው በአንድ አስተሳሰብ ብቻ እንዲቀረጽ ለመደረግ በቅቷል። በዚህም ምክንያት የተነሳ አንድን ተጨባጭ ሁኔታ ከተለያየ አንፃር ማየትና መገምገም የማይቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር ቻለ። ስለሆነም አንድን አገር እንደ መገበያያ መድረክ በመቁጠር ሁሉም አገር በዓለም አቀፍ ተዋንያን የተጻፈውንና የተደነገገውን የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ አለበት። ይህም ፖሊሲ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክስ ፖሊሲ በመባል ሲታወቅ፣ የአገራችንም ምሁራን ይህንን ብቻ ስለሚያውቁና ይህንን እንደትክክል አድርገው ስለሚቆጥሩ ለየት ያለ የአሰራር ዘዴን የሚከተልና ሌላ አስተሳሰብ ያለው ሰው ለየት ባለ መልክ በሚጽፍበት ጊዜ ሰውየውን አይ እንደ ዕብድ ያዩታል፤ አሊያም ያንቋሽሹታል። ይህ ዐይነቱ አካሄድ በአውሮፓ ምድር ውስጥ በተለይም በማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን የሚታወቅና፣ ሳይንቲስቶችንና ፈላስፋዎችን እንደወንጀለኛ ያስቆጠረና፣ አንዳንዶችም እንዲቃጠሉ በመደረግ ትምህርታቸው ደብዛው እንዲጠፋ ሙከራ የተደረገበት ዘመንን ያስታውሰኛል። በጊዜው የካቶሊክ ሃይማኖት እንደቀኖና ይታይ ስለነበር ይህንን አስተሳሰብ የሚቃወም አይ እንዲታሰር ይደረጋል፤ ካሊያም ደግሞ ከእነ ነፍሱ ይቃጠል እንደነበር ይታወቃል። የተቀረው ደግሞ ከአገሩ ይሰደድ ነበር። ስለሆነም በዘመናችን የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክስ አስተሳሰብ በመራባቱ ይህንን አስተሳሰብ የተቃወመ ሁሉ እንደሰይጣን ይቆጠራል። በተለይም በአገራችን ኢኮኖሚስቶች ዘንድ የተለመደ ነው። ወደ ካፒታሊስት አገሮች ስንመጣ ግን በየዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የተለያዩ የኢኮኖሚክስ ቲዎሪዎችና ፖሊሲዎች ይሰጣሉ። ከእነዚህም ውስጥ የኢንስቲቱሽናልና የማርክሲስት የኢኮኖሚክስ ቲዎሪዎችም ይገኙበታል።

ወደ ዋናው ቁም ነገር ስንመጣ በብርሃኑ አበጋዝ ዕምነት በአቢይ አህመድ የተመረጠው የኢኮኖሚክስ አማካሪ ቡድን በሳይንስ የተረጋገጠ ስራ ሰርቷል በማለት የእኔን ትችት ውድቅ ለማድረግ ሞክሯል። ይሁንና ግን ያልገባው ነገር የአንድ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማረጋገጫው በወረቀት ላይ የሰፈረ ስታትስቲክስ ወይም አሃዝ ሳይሆን፣ በአብዛኛው ህዝብ ላይ በሚኖረው አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ነው። ይኸውም አንድ ህዝብ ከድህነት ሲላቀቅ፣ ከድህነት የሚያላቅቀው ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ መስክ ሲዘረጋለትና፣ በተለያዩ የኢኮኖሚ መስኮች ተቀጥሮ ሲሰራና፣ በሚያገኘው ደሞዝ የመግዛት ኃይል ሲኖረውና፣ ለኑሮው አስፈላጊ የሚሆኑ ነገሮችን ገዝቶ ሲጠቀም በእርግጥም የኢኮኖሚ ፖሊሲው አመርቂ ውጤት አሳይቷል ማለት ይቻላል።  ይህ ብቻ ሳይሆን፣ የአንድ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊነት የሚታወቀው በአንድ አገር ውስጥ የውስጥ ገበያ(Home Market) በመባል የሚታወቀው እያደገና እየተስፋፋ ሲመጣ በእርግጥም የኢኮኖሚ ፖሊሲው ሳይንሳዊ ነው ሊያስብለው ይችላል። የአንድ አገር ጥንካሬም የሚመዘነው ሰፋ ባለ በሳይንስና በቴክኖሎጂ በሚደገፍ ኢኮኖሚያዊ መሰረት ተመርኩዞ ሲንቀሳቀስ እንደመሆኑ መጠን የሳይንስና የቴክኖሎጂ መሰረት የሌለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ የግዴታ ድህነትን ነው የሚያስፋፋው። ወደ ውጭ ደግሞ በዕዳ መተብተብንና የንግድ ሚዛንን መዛባት ነው የሚያስከትለው።

በአብዛኛዎች የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች አስተሳሰብ ኢኮኖሚ ከሌሎች መሰረታዊ ነገሮች ተነጥሎ የሚታይ ነው። ይህም ማለት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴና ዕድገት ካለማኑፋክቸሪንግ፣ ካለሳይንስና ካለቴክኖሎጂ በራሱ ብቻ ተግባራዊ ሆኖ እንደሚንቀሳቀስ ነው የሚታመነው። ከዚህም በላይ በኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች አስተሳሰብ የጥሬ-ሀብትንና የሰውን ጉልበት የሚያንቀሳቅስ ሰፋ ያለ ተቋማትና(Institution)፣  እንዲሁም ደግሞ ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካና የመንግስት አወቃቀርን አስፈላጊነት መኖርን እንደመሰረታዊ ጉዳዮች አያዩዋቸውም፤ አሊያም ቀድሞውኑ እንዳሉ ወይም እንደ ተዘጋጁ አድርገው ነው የሚቆጥሯቸው። ይህንን በሚመለከት ቬበሊን የሚባለው አሜሪካዊው ታላቅ ኢኮኖሚስት የኒዎ-ክላሲካል ኢኮኖሚስቶችን አስተሳሰብ በመቃወም በሰፊው አብራርቷል። ከዚህ ስንነሳ አንድ የጥሬ-ሀብት ወደ መጠቀሚያነት ከመለወጡ በፊት በኃይል(Energy)፣ በሰው ጉልበትና በማሽን አማካይነት የተለያዩ ሂደቶችን በማለፍ ነው ወደ መጨራሻ ምርትነት(End Product) በመለወጥ ወደ ገበያ ላይ ወጥቶ የሚሸጠው። ስለሆነም ኢኮኖሚክስ የሚባለው ነገር ካለፊዚክስ፣ ካለኬሚስትሪና ካለልዩ ልዩ መሰረታዊ ነገሮች በራሱ ብቻውን ትርጉም ሊሰጠን በፍጹም አይችልም

ሌላው ስለኢኮኖሚ ፖሊሲም ሆነ ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት በሚወራበት ጊዜ ግንዛቤ ውስጥ መግባት ያለበት ጉዳይ፣ በተለያዩ የኢኮኖሚ መስኮችና ንዑስ መስኮች ስላለው ትስስር ወይም የንግድ ልውውጥ ነው። ይህንን Linkages ወይም Value-added chain ብለን እንጠራዋለን። ለዚህ ዐይነቱ የValue-added Chain መሰረት የሚሆነው በምርምርና በፈጠራ ላይ የሚመረኮዝ የማሺን ኢንዱስትሪ መኖር ነው። በማሺን ኢንዱስትሪ አማካይነት ነው የተለያዩ ልዩ ልዩ ምርቶችን የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች የሚመረቱትና ተገጣጥመው ለአምራች ኃይሉ በሽያጭ መልክ የሚቀርቡት። ስለሆነም በአንድ በኩል ለአጭር ጊዜ መጠቀሚያ የሚሆኑ ምርቶችን የሚያመርት ኢንዱስትሪ ይተከላል፤ በሌላው ወገን ደግሞ የረጅም ዕድሜ ያላቸው እንደ ማቀዝቀዣ ወይም ልዩ ልዩ የቤት ዩቲንሲሎችንና መኪናዎችም ጭምር ይመረታሉ። ይህ ዐይነቱ የሀብት ክምችት መፍጠሪያ ዘዴ በካርል ማርክስ ክፍል አንድና ክፍል ሁለት በመባል ይታወቃል። ክፍል አንድ ለአጭር ጊዜ የሚሆኑ፣ ለምሳሌ እንደምግብና መጠጥ፣ በክፍል ሁለት ደግሞ እንደማቀዝቀዣና ልዩ ልዩ የኤሊክትሮኒክስ ዕቃዎች በመመረት በዚህ አማካይነት የአገር ውስጥ ገበያ በስፋትም ሆነ በጥልቀት እየዳበረ ይመጣል። ከዚህ ዐይነቱ ጠቅላላውን የህበረተስብ ክፍል ከሚያሳትፍና ከሚጠቅም የኢኮኖሚ ክንዋኔ ስንነሳ ነው የአንድን ኢኮኖሚ ፖሊሲ ፍቱንነትና ሳይንሳዊነት ለመረዳት የሚቻለው። በአንፃሩ አንድ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከብልጽግና ወይም ሰፋ ካለ የኢኮኖሚ ዕድገት ይልቅ ድህነትንና መዝረክረክን የሚያስከትል ከሆነ ይህ ዐይነቱ ፖሊሲ ሳይንሳዊ አይደለም። ለጥቂት ሰዎች ብቻ ታስቦ የሚታቀድ በመሆኑ በአንድ አገር ውስጥ በሁሉም መስክ መዛባትን ያስከትላል። ለዚህ ነው ህወሃት ወይም ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ በዓለም የገንዘብ ድርጅትና(IMF) በዓለም ባንክ(World Bank) በመመከርና በመደገፍ ተግባራዊ ያደረገው ፖሊሲ አገራችንን መቀመቅ ውስጥ የከተታት። የውጭው ዕዳ መጠንም ሊቆለልና፣ የውጭው ንግድ ሚዛንም በከፍተኛ ደረጃ ሊዛባ የቻለው ሳይንሳዊ መሰረት የሌለውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን ተግባራዊ በማድረጉ ነው።

ከዚህ አጠር መጠን ያለ ሀተታ ስንነሳ በአብዛኛዎች የኢትዮጵያ ኢኮኖሚስቶች ዘንድ ግንዛቤ ያላገኘውና የማይታወቀው ነገር የዛሬው የአብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች ኢኮኖሚዎች እዚህ ዐይነቱ የተወሳሰበ ደረጃ ላይ እንዴት ለመድረስ ቻለ የሚለውን ነገር ነው። አብዛኛዎቹም ጥያቄ በፍጹም አያነሱም። ዝም ብለው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ብቻ የተማሩትን እየመላለሱ በማስተማርና እሱን እንደ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መመሪያ በማድረግ ነው አገራቸውን መቀመቅ ውስጥ የሚከቱት።  ለምሳሌ አፄ ኃይለስላሴ ከስደት ተመልሰው አገዛዛቸው ተግባራዊ ያደረገውን የኢኮኖሚ ፖሊሲና ውጤቱን መመርመሩ  ለምን አገራችን የዛሬው ዐይነት ውዝግብና አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ለመውደቅ እንደቻለች ከፍተኛ ግንዛቤ ሊሰጠን ይችላል። ይህ ዐይነቱ ፖሊሲ Modernization ተብሎ ሲጠራ፣ መሰረቱም Import-substitution Industrialization በመባል ይታወቃል። ይህም ማለት ከውጭ የሚመጡ የፍጆታ ዕቃዎች፣ እንደኮካኮላ፣ ስኳር፣ የምግብ ዐይነቶችና ሲጋራ፣ የኋላ ኋላ ደግሞ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች ከውጭ መምጣታቸው ቀርቶ አገር ውስጥ እንዲመረቱ ማድረግ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ያሳድጋል የሚል ዕምነት ነበር። ይሁንና ግን ይህ ዐይነቱ ፖሊሲ  በአገራችን ምድር ያልተስተካከለ ዕድገት እንዲፈጠርና የመጨረሻ መጨረሻም አፄ ኃይለስላሴን ለውድቀት ሊዳርጋቸው በቃ። ምክንያቱም በጊዜው ለአንድ አገር ዋናው የዕድገት መሰረት የሆኑትና የመባዛት ኃይል ያላቸው የማኑፋክቸሪንግ፣ የማሽን፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ጉዳዮች አትኩሮ ስላልተሰጣቸው ነው። በአንፃሩ እነ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያና ዛሬ ደግሞ ቻይና በማሽን ኢንዱስትሪ ወይም በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ በመገንባታቸው ነው ከውስጥ ሰፋ ያለ ኢኮኖሚ ገንብተው፣ በዓለም ገበያ ላይ ደግሞ ተወዳዳሪ ለመሆን የበቁት።

በመሰረቱ የካፒታሊዝምን ዕድገት ለተመለከተ ከኢኮኖሚ አንፃር ብቻ የታየ ጉዳይ ሳይሆን፣ የመጀመሪያው መሰረት የባህል አብዮት ማካሄድ ነበር። የባህል አብዮቱ ሶስት ደረጃዎችን በማለፍ ነው የኋላ ኋላ የተፈጥሮ ሳይንስ ሲስፋፋ፣ በዚህ ላይ የተመሰረተ ቴክኖሎጂዎችን መፍጠርና ማዳበር የተቻለው። ይህም ማለት፣ ካለመንፈሳዊ አብዮትና ካለተፈጥሮ ሳይንስ ግኝት ውጭ ካፒታሊዝም እዚህ ዐይነቱ ደረጃ ላይ ለመድረስና ዓለምን ለመቆጣጠር በፍጹም ባልቻለ ነበር። የካፒታሊዝምን ዕድገትና ውስጣዊ እንቅስቃሴ በተለይም ካርል ማርክስ በሶስት ቅፅ ጽሁፎቹ፣ ዳስ ካፒታል በሚባለው መጽሀፎቹ ውስጥ በሚገባ አብራርቷል። የእሱን ጽሁፍና ምርም በመመርኮዝ የተለያዩ ምሁሮችም የካፒታሊዝምን ዕድገትና ዓለም አቀፋዊ ባህርይ መውሰድ በሚገባ ለማብራራት ሞክረዋል። ከማርክስ ቀደም ብሎ አዳም ስሚዝ ሰለገበያ ኢኮኖሚ በተለይም ስለረቀቀው እጅ(Invisible Hand) The Wealth of Nations  በሚለው መጽሀፉ ውስጥ ለማሳየት ሞክሯል። አዳም ስሚዝን ተመርኩዘው የሚጽፉ ኢኮኖሚስቶች የውጭ ንግድን አስፈላጊነት ብቻ በማሳየት ብዙ የሶስተኛው ዓለም ኢኮኖሚስቶችን ለማሳሳት ችለዋል። በመጀመሪያ ደረጃ አዳም ስሚዝ የኢኮኖሚ አስተሳሰቡን ከማዳበሩ በፊት በአውሮፓ ምድር ውስጥ በጊዜው የተለያዩ አገሮችን የሚገዙ ፍጹም ሞናርኪዎች የሚባሉ ነገስታት ለውስጥ ገበያ መዳበር ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክተዋል። ቀደም ብሎና በእነሱ ዘመን ነው ቆንጆ ቆንጆ ከተማዎች ሊገነቡና የንግድ እንቅስቃሴም ሊዳብር የቻለው። በፍጹም ሞናርኪዎች የአገዛዝ ዘመን የአንድ አገር ጥንካሬ የሚለካው በውስጥ ገበያ ማደግ አማካይነት መሆኑን በመረዳታቸው፣ በተለይም የነቁ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመደጎም የውስጥ ገበያን ለማዳበር ችለዋል።  የውስጥ ገበያዎቻቸውን ለማዳበር ደግሞ በተለይም ኋላ ላይ የተነሱ እንደ ፈረንሳይና ጀርመን የመሳሰሉ አገሮች በማደግ ላይ የነበሩ ኢንዱስትሪዎችን(Infant Industries) በታሪፍ መልክ ይከላከሉ ነበር። ከውጭ የሚመጡ ተመሳሳይ ምርቶችን መጠናቸውን በመቀነስ፣ አሊያም ደግሞ የሚከፈለውን ቀረጥ በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር በማድረግ ኢንዱስትሪዎቻቸውን ይከላከሉና እንዲያድጉ ያደርጉ ነበር። ይህንን የተመለከተው አዳም ስሚዝ በኢንዱስትሪ ዕድገት ቀድማ የሄደቸውን እንግሊዝን ፍላጎት በማስቀደም የነፃ ገበያን አስፈላጊነትና የታሪፍን ዕገዳ በመቃወም አስተሳሰቡን ማሰራጨት ጀመረ። ይህንን የተመለከቱ የጀርመን ምሁራንና ኢኮኖሚስቶች የአዳም ስሚዝንና የዴቢድ ሬካርዶን ሃሳብ በመቃወም መንግስታቸው የግዴታ የውጭ ገበያውን ክፍት እንዳያደርግ ግፊት አደረጉ። የራሳቸውንም የኢኮኖሚ ቲዎሪ በማዳበር ኢኮኖሚ ከሌሎች ነገሮች ተነጥሎ ሊታይና አመርቂ ውጤትም ለማምጣት እንደማይቻል አረጋገጡ። በተለይም ፍሬድሪሽ ሊስት የሚባለው ታላቅ ፈላስፋና የኢኮኖሚ ምሁር የማኑፋክቸሪንግን አስፈላጊነትና ማዕከላዊ ቦታን በማሳየት ጀርመን ባቡርንና የባቡር ሃዲድን በመስራት የተለያዩ ግዛቶቿን ማያያዝ ቀዳሚው ተግባር መሆኑን አመለከተ። ይሁንና የአዳም ስሚዝን መጽሀፍ በደንብ ላገላበጠ ስለ አንድ አገር ሀብት ዕድገት ወይም መጨመር ሲያወራ፣ 1ኛ) የስራ-ክፍፍል(Division of Labor) መኖር አለበት። ይህም ማለት የተለያዩ ፋብሪካዎች የተለያዩ ምርቶችን በማምረት ወይም ደግሞ በአንድ ፋብሪካ ውስጥ አንድን ምርት ለማምረት የሚያገለግሉ ልዩ ልዩ አካሎች በሚመረቱበትና በሚገጣጠሙበት ጊዜ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሊኖር ይችላል። 2ኛ) የማኑፋክቸሪንግ መኖር፤ ይህንን በሚመለከት ሁሉም የእንግሊዝ የጥንት ኢኮኖሚስቶች ይስማማሉ። 3ኛ) የገበያው መጠን(Market Size) በጣም ወሳኝ ነው። አዳም ስሚዝ ይህንን መጽሀፉን ሲጽፍ በጊዜው ከተማዎች የተገነቡና ልዩ ልዩ ተቋማትም ነበሩ። ዝም ብሎ በጭፍን የጻፈው ነገር አይደለም። ስለሆነም አብዛኛዎቹ የአገራችን ኢኮኖሚስቶች ይህንን ከግንዛቤ ውስጥ ባለማስገባት የኢኮኖሚን ምንነት ወደተራ ሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ በመለወጥ ድህነት እንዲስፋፋ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ለማበርከት ችለዋል ብል እንደተራ ውንጀላ አይቆጠርብኝም።

በአጠቃላይ ከኢኮኖሚ ፖሊሲ አንፃር የአብዛዎቹን የካፒታሊስት አገሮችን የኢኮኖሚ ዕድገት ስንመረምር አገዛዞች በሙሉ ንቁ የሆነ ተሳትፎ አድርገዋል። በመጀመሪያ ደረጃ እንግሊዝ ኢንዱስትሪዎችን በመከላከልና የሌሎችን አገሮች ኢንዱስትሪዎች በማጨናገፍና ሀብት በመዝረፍ ነው ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ የቻለችው። አሜሪካ በአብርሃም ሊንከንና በእነ ሃሚልተን ዘመን የማኑፋክቸሪንግን ትርጉም በመረዳት ነው እዚህ ላይ ርብርቦሽ በማድረግ አሜሪካ ቀስ በቀስ ከእንግሊዝ ማነቆ ለመላቀቅ የቻለችው። በተለይም በጊዜው የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስተር የነበረው ሃሚልተን የክሬዲት ሲይስተም እንዲፈጠር በማድረግ ነው ኢንዱስትሪዎች በርካሽ ብድር ሊያድጉና ሊዳብሩ የሚችሉበት ሁኔታ የተፈጠረው። ሃሚልተን በጥብቅ የእንግሊዝን የነፃ ንግድ ዶክትሪን የሚቃወም ታላቅ አሜሪካዊ ነበር። እነ ጀርመንም የራሳቸውን የባንኪንግ ሲይስተም በመፍጠርና በማኑፋክቸሪንግ ላይ በማትኮር ነው በአንድ ትውልድ ጊዜ ውስጥ እንግሊዝን ቀድማ ለመሄድ የቻለችው። በተለይም ዊሊሄልም ሁሞቦልድት የሚባለው ታላቅ ምሁርና የትምህርት ሚኒስተር የነበረው የትምህርት ስርዓቱን በማሻሻልና የደሃውም ቤተሰብ ልጅ የመማር ዕድል እንዲያገኝ በማድረግ ነው ጀርመን በአጭር ጊዜ ውስጥ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ሰዎችን ማፍለቅ የቻለችው። እነ ጋውስና ሪማን የሚባሉት ታላላቅ የማቲማቲክስ ሰዎች ሊፈጠሩ የቻሉት ሁምቦልድት የጥገና ለውጥ ባደረገው ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ገብተው በመማራቸው ነው፤ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገትም የሚጠቅም የማቲማቲክስ ግኝት ማዳበር የቻሉት ሰፋ ያለና የጠለቀ ዕውቀት በመቅሰማቸው ነው። የኋላ ኋላ ደግሞ ጀርመን በ20ኛው ክፍለ-ዘመን ሁለት ሶስተኛው የሚሆነውን የኖብል ፕራይዝ ተሸላሚዎች ለማፍራት የቻለችው ዊሊሄልም ሁምቦልድት ባሻሻለውና በዘረጋው የትምህርት ስርዓት አማካይነት ነው። በተለይም የቴክኖሎጂ ምርምር ጣቢያዎችና ኮሌጆች፣ እንዲሁም የሙያ ማስልጠኛ ተቋማት በመግንባታቸው ነው በስራ ላይ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ሙያተኞች ለመሰልጠን የቻሉት። በዚህ አማካይነት ነው በየአንዳንዱ ቤተሰብ ውስጥ ቀስ በቀስ ንፁህ ውሃ ሊዳረስ የቻለውና የመብራት መስመርም ሊዘረጋ የተቻለው። ይህ ስይስተም ከብዙ ነገሮች ጋር የተያያዘ በመሆኑ ጠቅላላውን ስርዓት ያንቀሳቅሳል። ስለሆነም ስለኢኮኖሚ ዕድገት በሚወራበት ጊዜ ኢኮኖሚ መሰረት አድርጎ የሚንቀሳቀባቸውን ነገሮችንም ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። በተለይም የሰለጠኑ ተቋማት፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ማዕከሎችና፣ በየጊዜው አዳዲስ ማሽኖችን መፍጠር ምርታማነትን የማሳደጉ ጉዳይ ይህ ሁሉ ስሌት ውስጥ መግባት አለበት።

ከዚህ ወጣ ብለን ወደ ሌሎች ጉዳዮች ጋ ስንመጣ፣ በተለይም እነ ዓለም የገንዘብ ድርጅት የመሳሰሉት አብዛዎችን የሶስተኛውን ዓለም አገሮች መንግስታት የሚያሳስቱት፣ መንግስት ከኢኮኖሚው ይውጣ በማለት ነው። ይህ ሊሆን እንደማይችል ኬይንስ የተባለው ታላቁ የእንግሊዝ ኢኮኖሚስትና በ1944 ዓ.ም በብሬተን ውድስ ላይ ከአሜሪካኑ መልዕክተኛ፣ ኋዋይትስ ከሚባለው ጋር የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ የዓለም ኢኮኖሚ በምን ዐይነት መልክ መዋቀር እንዳለበት የተነጋገረው በሚገባ አሳይቷል። በኬይንስም ዕምነት የካፒታሊስት ኢኮኖሚ የኒዎ-ክላሲካል ኢኮኖሚስቶች እንደሚሉት ራሱን በራሱ በማረም ወደሚዛናዊነት የሚመጣ ሳይሆን፣ መንግስት የግዴታ በፊስካል ፖሊሲ አማካይነት ጣልቃ መግባት እንዳለበትና የስራ-መስክም ሊከፈት የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንዳለበት ለማሳየት ሞክሯል። በኬይንስ ዕምነት በዴፊሲት ፖሊሲ አማካይነት ኢኮኖሚው የማደግ ኃይል ሲያገኝ፣ ኢንዱስትሪዎች ውስጥና ሌሎች የኢኮኖሚ መስኮች ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች ከሚያገኙት ገቢ ቀረጥ ስለሚከፍሉ ቀስ በቀስም የመንግስት ዕዳ ሊቀንስ ይችላል የሚል ነው፤ ትክክልም ነው። ኬይንስ የካፒታሊስትን ኢኮኖሚ ከንጹህ ኢኮኖሚያዊ ስሌት ብቻ የተመለከተ ሳይሆን፣ ማህበራዊ ጎኑንም በመመልከት ነው። ምክንያቱም መንግስት ኢኮኖሚያዊ ቀወስ በሚፈጠርበት ጊዜ ዝም ብሎ የሚመለከት ከሆነ የስራ-አጥ ቁጥር ይጨምራል። የግዴታ ይህ ሁኔታ ማህበራዊ ቀውስ ሊያከትልና፣ ከዚያም በላይ ፖለቲካዊ ግጭትን እንዲከሰት ያደርጋል የሚል ዕምነት ነበረው፤ ትክክልም ነው። ይህም የሚያረጋግጠው ኬይንስ ከፍተኛው የሆነ ማህበራዊ ኃላፊነት እንደሚሰማው ነው። ስለሆነም በኬይንስ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲና በኒዎ-ሊበራል የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መሀከል ከፍተኛ ልዩነት አለ ማለት ነው። ኬይንስ የመንግስትን ጣልቃ ገብነት ሲደግፍ፣ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች ደግሞ የመንግስትን ጣልቃ ገብነት አጥበቀው ይቃወማሉ። ሁሉም ነገረ ለገበያው ተዋንያን መለቀቅ አለበት ይላሉ። ሌላው የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች ስህተት ወይም ለመረዳት አለመቻል በገበያ ውስጥ የሚሳተፍ ሁሉ ተመጣጣኝ የሆነ የመግዛት ኃይል እንደሌለው ነው። የሀብት ክፍፍልን ልዩነት መኖርና፣ በተለይም የሀብትን ቁጥጥር ከስሌት ውስጥ አይስገቡም። በገበያ ውስጥ የሚሳተፈው ሁሉ በእኩል ደረጃ ነው የሚታየው። ይህንን ችግርና ከላይ የተቀመጠውን በኬይንስና በኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች መሀከል ያለውን ልዩነት ያልተረዱ ወይም ለመረዳት የማይፈልጉ የአገራችን ኢኮኖሚስቶች ከእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅት(IMF) ጎን በመቆምና የእነሱን ምክር በመቀበልና ጠበቃ በመሆን ደሃውን የአገራችንን ህዝብ የባሰ ደሃ ያደርጉታል; የአገራችንም ኢኮኖሚ በአፍ ጢሙ እንዲደፋ ያደርጋሉ።  በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመረኮዘ ጠንካራ ኢኮኖሚም እንዳይገነባ እንቅፋት ለመሆን በቅተዋል።

ከኬይንስ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አንፃር ስንነሳ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ምክንያት የተነሳ እንደ ጀርመን የመሳሰሉት በከፍተኛ ደረጃ ከተማዎቻቸውና እንፍራስትራክቸሮቻቸው የፈራሱባቸው፣ ኢንዱስትሪዎቻቸው የወላለቁባቸው፣ የመብራት ኃይልና የውሃ ቧንቧዎች የወደሙባቸው አገሮች በመንግስት ጣልቃ-ገብነት የተነሳ ነው በ15 ዓመት ዕድሜ ውስጥ ኢኮኖሚያቸው እንዲያንሰራራና ተወዳዳሪ ለመሆን የበቃው። በዚህም አማካይነት ነው ጀርመን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት በመሆን እነ አሜሪካን የመሳሰሉትን ለመወዳደር የቻለችው። በዚህ ምክንያት ነው 16 የሚሁኑት የጀርመን ክፍለ-ሀገሮች ሁሉም በተሰተካከለ መልክ ሊገነቡ የቻሉት። በፌዴራል አወቃቀር አማካይነትም አንደኛው ክፍለ-ሀገር ሌላውን በመደገፍ ነው በሁሉም ክፍለ-ሀገሮች ውስጥ ሚዛናዊነት ያለው ዕድገት የሚታየው። በአንዳቸውም የጀርመን ከተማ እንደኒዎርክና ሎስ ኤንጀለስ የመሳሰሉ ከተማዎች ውስጥ እንደሚታየው ደሃው ህዝብ ሜዳ ላይ ተኝቶ በፍጹም አይታይም። መንግስትም ደሃውን የመርዳት ግዴታ ስላለበት ቤቶች ለሁሉም በተመጣጣኝ መልክ በመሰራት እንዲከራዩ ይደረጋሉ። መንግስትም ጣልቃ በመግባቱ የተነሳ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ወይም ደግሞ በአብዛኛዎቻችን የሚታወቀው የገበያ ኢኮኖሚ በፍጹም አልተጎዳም።

ወደ ዶ/ር ብርሃኑ አበጋዝ ስድብና ውንጀላ ስመጣ በኤሌኒ ገብረመድህን ላይ የሰነዘርኩትን ትችት በሚገባ ያጤነው አልመሰለኝም። በመጀመሪያ ደረጃ ኤሌኒ ገብረመድህን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሳደግና የኢትዮጵያን ህዝብም ከድህነት ለማላቀቅ የተላከች ሳይሆን፣ የዎል-ስትሪት ጥቅምን ተግባራዊ ለማድረግ ነው። በዚህም ዐይነቱ አገሮችን አቆርቁዞ በሚያስኬድ ፖሊሲ ብለው በሚጠሩት ነገር የሰለጠነች በመሆኗም አገር ወዳድ ልትሆን በፍጹም አትችልም፤ ሰፋ ያለ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ እንዲገነባ የማድረግ ብቃትነትም የላትም። አስተሳሰቧም ኢሳይንሳዊ በመሆኑ የዓለም አቀፍ ኩባንያዎች፣ በተለይም የአሜሪካን የጥሬ-ሀብት ተቀራማቾች(Multi-National Companies) አገር ውስጥ በመግባት ጥሬ-ሀብትን እያወጡ ወደ አገራቸው እንዲልኩ ነው አመቺ ሁኔታዎችን የምትፈጥረው። ስለሆነም የኮሞዲቲ ገበያ የሚባለውን በመክፈትና ቡና በሚመረትበት በደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍላተ-ግዛት ገበሬው በቡና ምርት ላይ ብቻ እንዲሰማራ በማድረግ ነው ሌሎች ሰብሎችን እንዳያመርት ለማሳሳት የበቃችው። በዚህ ምክሯና አካሄዷ በአንድ በኩል የወያኔ ካድሬዎችን ስትጠቅም፣ በሌላው ወገን ደግሞ ድህነትን ለማስፋፋት ችላለች። ለ Ernst and Young የሚሰራው የዘመዴነህ ንጋቱ ዋና ተግባርም የአንድን አገር ኢኮኖሚ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ እንዲመረኮዝ በማድረግ ሰፋ ያለ የውስጥ ገበያ እንዲዳብርና አንደ አገር እንድትጠነክር ማድረግ ሳይሆን፣ ለአሜሪካ የጥሬ-ሀብት አውጭና ተቀራማች ኩባንያዎች ተቀጥሮ በመሰራት የአፍሪካ የጥሬ ሀብት እንዲዘረፍ ማድረግ ነው ዋና ተግባሩ። በዚህ ዐይነቱ አካሄዱና ስማርት ሆኖ በመታየቱ ብዙ ወጣቶችንና የአገራችንን ባለሀብታሞች እያሳሳተ ነው። እንደነዚህ ዐይነቶቹ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ አራማጆች ናቸው የእነ መለሰ ዜናዊና፣ ኋላ ላይ ደግሞ የአቢይ አህመድ አማካሪ በመሆን ሀብት እንዲቸበቸብ ለማድረግ የበቁትና ህዝባችንን ያደኸዩት።

ከዚህ መሰረታዊ ሀቅ ስነሳ በአቢይ የተቋቋመው፣ ዶ/ር ኤሌኒ ገብረ-መድህን፣ ዶ/ር ዮናስ ብሩ፣ ፕሮፈሰር መሀመድና ዶ/ር ብርሃኑ አበጋዝ የተካተቱበት የኢኮኖሚ ካውንስል ስታትስቲኮችን ከማገላበጥ ይልቅ በመጀመሪያ ደረጃ ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ለምን በድህነት ዓለም ውስጥ እንደሚገኝ ዋና ምክንያቱን መመርመር ነበረባቸው። ከዚህም በላይ በተለይም በወያኔ ዘመን እንደ እንጉዳይ የተፈለፈሉትን የቆሻሻ መኖሪያ ቦታዎችን እየተዘዋወሩ ማየት ነበረባቸው። ከዚህም በተጨማሪ የአገራችንን ኢኮኖሚ ለመረዳት የግዴታ በየቦታው በመዘዋወር የከተማዎችን ዕድገት፣ በየከተማዎችና በትናንሽ መንደሮች ውስጥ ማዕከለኛና ትናንሽ ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውንና አለመኖራቸውን መመርመር ነበረባቸው። ይህን ሁሉ ካደረጉ በኋላ ወያኔ በዓለም የገንዘብ ድርጅትና በዓለም ባንክ አማካይነት ተገዶና ተመክሮ ተግባራዊ ያደረገው የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ በመሰረቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ያልሆነውን መመርመርና፣ ለምንስ ለውጭ ዕዳ ዕድገትና ለውጭው ንግድ ሚዛን መዛባት እንደዳረግን በሚገባ መመርመር ነበረባቸው። ከዚህም በመነሳት የአንድ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ዋና ዓላማ ምን እንደሆነ በቅጡ በማገናዘብ አገዛዙ ይህንን ዐይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዳያደርግ ምክር መስጠትና ጫና ማድረግ ነበረባቸው። ይሁንና ግን አዲሱ የአቢይ አህመድ አገዛዝ የኢኮኖሚ ካውንስል የሚባለው በዚያው የእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅት የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ  እንዲቀጥልበት ነው ምክር የሰጡት። ስለሆነም በአሁኑ ወቅት በአገራችን ምድር ከፍተኛ የዋጋ ግሽበትና ድህነት የሚታዩትና አብዛኛዎችም ከተማዎች በተዝረከረከ መልክ “ሊገነቡ” የቻሉት በዚህ ዐይነቱ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ አስተሳሰብ አማካይነት ነው።  በአገራችን ምድር በተለይም የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል የሚያባልጉና የጥሬ-ሀብትን በከፍተኛ ደረጃ የሚጋሩ የአምስትና የሰባት ኮከብ ሆቴል ቤቶች ከመሰራታቸው በስተቀር ህዝባችንን ከድሀነት የሚያላቅቁት ማዕከለኛና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች እዚህና እዚያ አልተተከሉም። ስለሆነም ዶ/ር ብርሃኑ አበጋዝ “በጨቅላህ ጭንቅላትህ” በመነሳት ነው ይህችን የመሰለችውን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትታወቀውንና የረቀቀ አስተሳሰብ ያላትን ኢኮኖሚስት ኤሌኒ ገብረመድህንን የወነጀልከው ያለው ምንም ዐይነት ሳይንሳዊ መሰረት የለውም። ማንኛውም ህሊና ያለው ሰው የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ በማየት ፍርዱን መስጠት ይችላል። ለዚህ ደግሞ የግዴታ አንድ ሰው ኢኮኖሚስት መሆን አያስፈልግውም። ከአንድ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስት ይልቅ በችጋርና በዋጋ ግሽበት የሚሰቃየው፣ ከቆሻሻ ቦታዎች ምግብ እየፈለገ የሚበላውና፣ ቤቱ በላዩ ላይ የሚፈርስበትና በየቦታው የሚጣለው ሰው ነው ሳይንሳዊና ሚዛናዊ ፍርድ ሊሰጥ የሚችለው። ስለሆነም የዶ/ር ብርሃኑ አበጋዝ ስድብና ወቀሳ የራሱን ማንነት ነው የሚያረጋግጠው። “ጓደኛህን ንገረኝና ማንነትህን ልነግርህ እችላለሁ” እንደሚባለው አነጋገር ኤሌኒ ገብረመድህንን ማወደሱ የሚደንቅ አይደለም። ለህዝባችንና ለአገራችን ሳይሆን ለዎል-ስትሪት ተዋንያን ለሆኑትና፣ የአገርን ሀብት እንዲቸበቸብ በማድረግ አንድን አገር መቀመቅ ውስጥ የሚከቱትን ነው ያወደሰውና ጠበቃቸውም የሆነላቸው። ከዚህም በላይ ኤሌኒ ገብረ መድህን ሁለት ፋሺሽታዊ አገዛዞችን፣ ማለትም የህወሃትን የከፋፋይና የዘራፊ አገዛዝ፣ እንዲሁም ደግሞ የአቢይ አሀመድ አማካሪ ስትሆን፣ ዶ/ር ብርሃኑ አበጋዝ ደግሞ አቢይ አህመድ ስልጣን ላይ ከወጣ ጀምሮ በህዝባችን ላይ፣ በተለይም በአማራው ወገናችንና በኦርቶዶክስ ሃይማኖት መሪዎችና በተቋማቱ ላይ ጦርነት በማወጅና በመክፈት አገራችንን ወደከፍተኛ ትርምስ ውስጥ የከተተውን ፋሺሽታዊ አገዛዝ ነው እንዲያማክር የተመረጠው። በፖለቲካና በኢኮኖሚክስ መሀከል ያለውን ዲያሌክቲካዊ ግኑኝነት ለመረዳት ባለመቻሉ የማይገባ ክስና ስድብ ለመሰንዘር ተገዷል።መልካም ግንዛቤ!!

 

[email protected]

www.fekadubekele.com

ማሳሰቢያ፤ እንደዚህ ዐይነቱን የጥናት ጽሁፍ ለመጻፍ የራስን ጊዜ መሰዋት በጣም አስፈላጊ ነው፤

ብዙ ምርምርና ጥናትም ያስፈልጋል። ይህን ዐይነቱን ጥናታዊ ጽሁፍ ለማገዝ

መጽሀፌን በመግዛትና ድረ-ገጼን በመደገፍ መተባበር በጣም አስፈላጊ ነው። ድረ-ገጼ

ውስጥ በመግባት አስፈላጊውን መመሪያ ማግኘት ይቻላል። አንድ አገር በዕውቀት

አማካይነት ብቻ ስለሚገነባ በዕውቀት ላይ ኢንቬስት ማድረግ የጊዜው አንገብጋቢ

ጥያቄ ነው።

           የመጽሀፉ ስም፤ “African Predicaments and the Method of Solving

them Effectively” ይባላል።

ሁለተኛው መጽሀፍ “ ካፒታሊዝም” በመባል የሚጣወቅ ሲሆን

የፖለቲካ ኢኮኖሚክስን የቲዎሪ አፀናነስ የሚያትት ነው።

 

Literature

David S. Landes; The Wealth and Poverty of Nations: Why some are so rich and some so

poor, New York, 1999

David S. Landes; The Unbound Prometheus: Technological Change and Industrial

Development in Western Europe from 1750 to the present, UK, 2003

David Orrell; ECONO Myths: Ten Ways that Economics Gets it Wrong, UK, 2010

Eric Dorn Brose; The Politics of Technological Change in Prussia: Out of the Shadow of

Antiquity, New Jersey, 1993

Erik S. Reinert; How Rich Countries Got Rich… and Why Poor Countries Stay Poor,

London, 2007

Frederick Soddy; Wealth, Virtual Wealth and Debt: The Solution of the Economic Paradox,

London, 1921

Frederick G.Lawrence, Patric H, Bayrne(eds.) Macroeconomic Dynamics: An Essay in the

Circulation Analysis, Toronto, 1999

Gary Herrigel; Industrial Construction: The sources of German industrial power,

Cambridge, 1996

James Angresano; The Political Economy of Gunnar Myrdal, US, 1997

Jacob Soll; Free Market: The History of an Idea, New York, 2022

John Maynard Keynes; The General Theory of Employment, Interest and Money,

London, 1967

Kate Raworth; Doughunt Economics: Seven Ways to think like a 21st Century Economist,

London, 2017

Naomi Klein; The Shock Doctrine, London, 2008

Paul Mason; Post Capitalism: A Guide to our future, UK, 2015

Per Molander; The Anatomy of Inequality: Where does it come and how we control it,

Frankfurt/Main, 2014

Richard A. Goldthwaite, The Economy of Renaissance Florence, Baltimore, 2009

Robert Kuttner; Can Democracy Survive Global Capitalism?, US, 2019

Stephan Schulmeister, The Way to Prosperity, München, 2018

Steve Keen; Debunking Economics: The Naked Emperor Dethroned? New York, 2011

Thomas Piketty; Capital in the Twenty-first Century, US, 2014

TomአSedláček; The Economy of Good and Evil, New York, 2011

Vivian Walsh &Harvey Gram, Classical and Neoclassical Theories of General Equilibrium:

Historical Origins and Mathematical Structures, New York, 19

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
Go toTop