April 27, 2023
27 mins read

“ጦርነት ይብቃ ሰላምን እናጽና” በሚል መሪ ቃል በወዳጅነት አደባባይ ስለተካሄደው ወለፈንዴ ተወኔት የግል ምልከታ (አንዳርጋቸው ጽጌ)

እሁድ መጋቢት 15 2015
አንዳርጋቸው ጽጌ
አንድ ከሀገርና ከህዝብ ክብር ጋር የተሳሰረች ነፍስ ያለው ሰው፣ የሃገሩን እና የህዝቡን ክብር ማስከበር ካቃተው የራሱን ክብር ያስከብራል። ምን ማድረግ ይቻላል በሚል ተልካሻ ምክንያት ራሱን ለውርደት አሳልፎ አይሰጥም። “ጊዜ እስኪያልፍ …….. “ የሚለውን የሆዳሞች ተረት እየተረተ ትወልድ የሚያፍርበትን ስራ ሲሰራ አይታይም። ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ አይነቱ ከግለሰቦች ሰብአዊ ክብር ጋር የተያያዘው የቆየው ባህላችን እየጠፋ ነው። ጥቅምንና ስልጣን እያሰላሉ የራስንና የህዝብን ክብር እየሸጡ፣ ነገር ግን የያዙትን እርባና ቢስ አቋም ከከፍተኛ የሞራል ማማ ላይ ተቁሞ እንደተያዛ አቋም አድርገው ራሳቸውን ሸንገለው ሌላውን ለመሸንገል የሚሞክሩ አሳዛኝ ፍጥረቶች የሃገራችን የፖለቲካ ምህዳር እንደ ተምች ሰፍረውበታል።

342906281 747849000383092 7198518306613029024 n 1 1
#image_title

በእንዲህ አይነቱ ሃገር፣ የፍትህ፣ የሞራልና የመብት ጥያቄዎች የሚያነሱ የስርአቱ የአፈናና የጥቃት ሰለባ እንደሚሆኑና እየሆኑ እንደሆነ ይታያል። ከጥቂት አመታት በፊት የፈነጠቀው የለውጥ ተስፋ የሰቆቃ እና የሲቃ፣ የዘረፋና የገፈፋ ዘመን እንዳበቃ የጠቆመን መስሎን ነበር። የተንጠለጠልነው በቀቢጸ ተስፋ ላይ እንጂ በእውነተኛ ተስፋ ላይ አለመሆኑ መረጃዎቹ እየተበራከቱ መጥተዋል። ይህ እያዩ እንዳላዩ ማለፍ ለእንደኔ አይነቱ ሰው ከነውርም በላይ ነውር ነው።

ሰላም የሁሉ ነገር መሰረት መሆኑን እኔም በግሌ በተደጋጋሚ ተናግሬያለሁ። ጽፌያለሁ። የሃገርና

የህዝብ ሰላም ከሚደፈርስ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እጅግ አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ፣ ይህችን የመቶ ሚሊዮኖች ድሆች ሃገራችንን በታሪኳ አይታ በማታወቀው ደረጃ የዘረፉ የወያኔ መሪዎች በወንጀሎቻቸው ሳይጠየቁ በነጻ ይሂዱ ብያለሁ። ከወያኔ ጋር አብረው ህዝብን ሲገደሉና ሲዘርፉ የነበሩትን የብአዴን፣ የኦህዴድ እና የድህዴን ወንጀለኛ ባለስልጣናትንማ ስማቸውንም አንስቼ አላውቅም።

እኔ ብቻ አይደለሁም አብዛኛው የሃገራችን ህዝብ ለሰላም ሲል መከፈል የሚገባውን ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ሆኖ ነበር። “በወያኔ የግፍ ዘመን የተገደለውን ሁሉ የኢትዮጵያ እናቶች ሰላም ካገኙ ወልደው ይተኩታል፤ ከህዝብ የተዘረፈውን ሃብት ህዝብ ሰላም ካገኘ ባጭር ጊዜ ውስጥ ሰርቶ ያገኘዋል” በማለት ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን ለሰላም በጽናት ቆሜያለሁ። “በይቅርታ እንሻገር በፍቅር እንደመር” ሲባልም ከፊተኞቹ ሰልፈኞች ፊት እንጂ ከኋላ አልነበርኩም። ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ የእንግሊዙ የቀደሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጀረሚ ኸንት “ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድን የኖቤል የሰላም ሽልማታቸው ሊቀሙ ይገባል” ብሎ በእንግሊዝ ፓርላማ ሲደሰኩር፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኖቤል ሽልማት ማግኘት የሚገባው በኤርትራና በኢትዮጵያ መሃል ሰላም በማውረዱ ሳይሆን፣ የመጣውን ሃገራዊ ለወጥ ከቂምና ከበቀል ነጻ በሆነ መንገድ ለማስተናገድ፣ ደም መፋሰስን ለማስቀረት ይዞት ለመጣው አዲስ፣ የሰላም፣ የፍቅር፣ የይቅርታ የፖለቲካ ባህል ነው፣ ለተፈጠርው ግጭት ጥፋተኛው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይሆን ጥብቅና የቆምክላቸው በእብሪት ተነሳስተው ጦርነት ያወጁት ወያኔዎች ናቸው” በማለት በሚገባው ቋንቋ ምላሽ ሰጥቻለሁ።

ስለሆነም ለእንደኔ አይነቶቹ ሰዎች ሰላም የሁሉ ነገር መሰረት መሆኑን ማንም ሊሰብከን አይችልም። ችግሩ የተፈጠረው በሆደሰፊነት ህዝብ ከወንጀል ተጠያቂነት ነጻ ያደረጋቸው የወያኔ መሪዎች፣ ለሰላም ሲል ምህረት ባደረገላቸው ህዝብ ላይ በእብሪት ተነሳስተው ጦርነት ማወጃቸው ነው። በ27 አመታታ የግፍ አገዛዛቸው ያመረቱበት ሰቃይና ሰቆቃ ላይ ተጨማሪ ስቃይና ሰቆቃ ሊፈጽሙ መነሳታቸው ነው።

ይህንን በወያኔ እብሪት የተለኮሰ ጦርነት ለማስቆም፣ ከክልል ክልል የተለያያየ ቢሆንም፣ ሁሉም የሃገሪቱ ህዝብ መከፈል የሚገባውን መስዋእትነት ከፍሏል። የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መሰረት የወያኔ የሰላም ፍላጎት ሳይሆን፣ የወያኔ እብሪት ህዝብ በከፈለው መስዋእትነት የተነሳ መተንፈሱ ነው። ጦርነቱ የቆመው የሰላም ሽልማት የተበረከተላቸው የወያኔ መሪዎች የጦርነትን አሰቃቂነት ተገንዝበው ሰላምን ስለመረጡ አይደለም። ከእንግዲህ በመንፈራገጥ መቀጠሉ መላላጡን የሚያብስ መሆኑን ስልተረዱ ብቻ እንጂ!

የሰላማችን መሰረት ከየቤቱ ነቅሎ ወጥቶ በየሜዳው፣ በየተራራው፣ በየሸለቆው፣ በወጉ አስከሬኑ አፈር ያልለበሰው፣ ህይወቱን ለሃገሩና ለሰላሙ የሰጠው የሃገሪቱ ህዝብ፣ በተለይ ደሃው ህዝብ ነው።

ባላፈው እሁድ መጋቢት 15ቀን 2015 “ጦርነት ይብቃ ሰላምን እናጽና “በሚል መፈክር ስር በመንግስት የተዘጋጀውን ትእይንት አጸያፊ አድርጌ እንዳይ ያደረገኝ ለሰላም ጥላቻ ስላለኝ አይደለም። ቂም በቀለኛ ስለሆንኩም አይደለም። ደሃው፣ ባተሌው ህዝብ ለሰላም የከፈለውን መስዋእትነት ሳይሆን ሰላሙን አደፍረሰው ለከፍተኛ እልቂት የዳረጉት ሹማምንቶች በሰላም ስም ሲሸነጋገሉና በሰላም ስም ሲሸላለሙ የሚያሳይ የኢሞራላዊ ድርጊት ሆኖ ስላገኘሁት ነው።

ገዥዎች ሁሌም ህሊና ቢሶችና የማስታወስ አቅማቸው ዝቅተኛ ስለሆነ በየጊዜው የሚያስታውሳቸው ያስፈልጋል። ዛሬ የሃገሪቱ መሪዎች ያሻቸውን የሚሰሩበት መንግስትና ስልጣን ጸንቶ እንዲቀጥል፣ የቀድሞ የወያኔ ጓደኞቻቸውን እያቀፉ በሰላም ስም ሽልማት ለመስጠት እንዲችሉ ህዝብ የከፈለው መስዋእትነት መሆኑን ደግመን ደጋግመን ልናስታውሳቸው ይገባል።

ሁላችንም እንዲሁ በደፈናው በመቶሽዎች በሚሊዩኖች የረገፉበት ጦርነት ሲባል ስምተናል። መቶ ሽዎችና ሚሊዮኖች ግን ስም የለሸና መልክ የለሽ በመሆናቸው ቁጥሩ ብቻውን የተከፈለውን መስዋእትነት ግዙፍነት የሚያሳይ መሆን አልቻለም። የተከፈለውን መስዋእትነት ተገቢ ትርጉም፣ ከጦርነቱ ቀጠና ርቆ የሚኖረው ህዝብ በውል እንዲረዳ በድፍን መቶሽዎችና ሚሊዮኖች ከሚለው የተለመደ አባባል ወጣ ብሎ ጥቂት የሚዘገንኑ ሃቆችን ማንሳት ያስፈልጋል። ጥቂት ሰማእታትን በስማቸው በመጥቀስ፣ እነዚህ ሰማእታት ቁጥር ብቻ ሳይሆኑ እንደኛው፣ እንደሃገሪቱ ባላስልጣናት ሰዎች መሆናቸውን ከሚያሳዩ የማንነታቸው መገለጫዎች ጋር ማቅረቡ ተገቢ ይሆናል።

ከዚህ ቀጥሎ የማቀረበው አንድ አነስተኛ መረጃ በወያኔ አቀጣጣይነት በተለኮሰው ጦርነት የረገፈው በመቶ ሽህዎች የሚቆጠር ዜጋ፣ ሰው እንጂ ዝንብ እንዳልሆነ ያሳየናል። ቦታው ጎጃም ውስጥ ሸበል በረንታ የሚባል ወረዳ ነው። ከዚህ ወረዳ ብቻ ከዘመቱ ሚሊሻዎች መሃል በአንድ እለት በአቀስታ ግንባር፣ ዶባ ተራራ ላይ በጀግንነት ተዋግተው ጥይት አልቆባቸው 19ኙ ተሰውተዋል። እነዚህ የሚሊሻ አባላት እነማን ናቸው። ከተራ ቁጥር የዘለለው ስማቸው፣ቤተሰባቸው፣ ህይወታቸው ምን ይመስላል? እኝሁላችሁ!

  1. ዘማች አቶ መብሬ ፈንታ አለሙ እድሜው በውል አላታወቀም። ከአባራ ቀበሌ የዘመተ፤ ባለቤቱ ባንቹ ፈንታ አበራ እደሜ 41፤ ልጆቻቸው በረከት መብሬ ፈንታ ወንድ እደሜ 23 የመጀመሪያ ድግሪ ኮምፒዩተር ሳይንስ፣ መለሰ መብሬ ፈንታ ወንድ እደሜ 21 10ኛ ክፍል፣ እመቤት መብሬ ፈንታ ሴት እድሜ 18 9ኛ ክፍል፣ አበበ መብሬ ፈንታ ወንድ እደሜ 15 8ኛ ፣ ሀብታሙ መብሬ ፈንታ ወንድ እደሜ 10 4ኛ ከፍል፤
  2. ዘማች አቶ ግዛቸዉ አንዳርጌ ደምሰዉ እድሜ 48 ከሰለልኩላ ቀበሌ የዘመተ፣ ባለቤቱ እታቱ ደረሰ እድሜ 36፣ ልጆች እማዋይሽ ግዛቸዉ አንዳርጌ ሴት እድሜ 23 10+2 Animal production፣ ደመቀ ግዛቸዉ አንዳርጌ ወንድ እድሜ 17 10ኛ ክፍል፣ ታለአምላክ ግዛቸዉ አንዳርጌ ወንድ እድሜ 7 3ኛ ክፍል፤
  3. ዘማች አቶ ዳምጤ ጫኔ ተሰማ እድሜ 46፣ ከሱሃ ቀበሌ የዘመተ፤ ባላቤቱ ደይቴ ገበየሑ አበበ እደሜ 37፣ ልጆች ገነት ዳምጤ ጫኔ ሴት እደሜ 20 ደረጃ 4 IT፣ ነጻነት ዳምጤ ጫኔ ሴት እደሜ 17 10ኛ ክፍል፣ መላኩ ዳምጤ ጫኔ ወንድ እድሜ 11 5ኛ ክፍል፣ ባንተግዜ ዳምጤ ጫኔ ወንድ እድሜ 2 ወር፤
  4. ዘማች አቶ ፍሬዉ ከፋለ ረዳ እድሜ 58 ከሱሃ ቀበሌ የዘመተ፣ የባላቤቱ ስም ዉዲት ንጉሴ አየለት እድሜ 55፣ ልጆች አሞኘሽ ፍሬዉ ከፋለ ሴት እደሜ 25፣ ላመስግን ፍሬዉ ከፋለ ሴት እደሜ 23 10ኛ ክፍል፣ ፍሬዉ ከፋለ ሴት እደሜ 10ኛ ክፍል፣ እንዳላማዉ ፍሬዉ ከፋለ ወንድ እደሜ 16፣ 8ኛ ክፍል፣ ካሴ ፍሬዉ ከፋለ ወንድ እድሜ 13፣ 5ኛ ክፍል፣ ጥሩሰዉ ፍሬዉ ከፋለ ወንድ እደሜ 10፣ 2ኛ ክፍል፤
  5. ዘማች አቶ ይበልጣል ተሰማ አቡየ 58 ከሱሃ ቀበሌ የዘመተ፣ የባላቤቱ ስም ንግስቴ ታደለ ጓዴ እድሜ 42፣ ልጅ፣ ጥሩሰዉ ይበልጣል ተሰማ ወንድ እድሜ 21 10ኛ ክፍል፤
  6. ዘማች አቶ ቢያዝን ማናየ ሁነኝ እድሜ 48 ከሱሃ ቀበሌ የዘመተ፣ የባለቤቱ ስም ዉዴ ሰዉነት አበበ እድሜ 42፣ ልጆቻቸው ዉባለ ቢያዝን ማናየ ወንደ እደውሜ 19 11ኛ ክፍል፣ አንችንአሉ ቢያዝን ማናየ ሴት እድሜ 15 9ኛ ክፍል፣ ሃይማኖት ቢያዝን ማናየ ሴት እድሜ 11 4ኛ ክፍል፣ አባትነህ ቢያዝን ማናየ ወንድ እድሜ 4፤
  7. ዘማች አቶ ተፈራ አባተ ዘለቀ እድሜ 58 ከሱሃ ቀበሌ የዘመተ፣ የባላቤቱ ስም ደጇ ሙሉ እንዳሌ እደሜ 48፤ ልጆቻቸው ልየዉ ተፈራ አባተ ወንድ እደሜ 25 10ኛ ክፍል፣ በላይ ተፈራ አባተ ወንድ እድሜ 20 ክፍል 5ኛ፣ ትርንጎ ተፈራ አባተ ሴት እድሜ 8፤
  8. ዘማች አቶ አሳቡ ወሰን የኔነዉ እደሜ 45 ከገዳያሱ ቀበሌ የዘመተ፣ ባላቤቱ ሀብታም አዳሙ አሰጌ እድሜ ?፣ ልጆች፣ ያደግድጉ አሳቡ ወሰን ሴት እድሜ 27፣ 10ኛ ክፍል፣ ወርቋ አሳቡ ወሰን ሴት እድሜ 25 10ኛ ክፍል፣ ሙሉ አሳቡ ወሰን ሴት እድሜ 22 10ኛ ክፍል፣ ዉዱ አሳቡ ወሰን ወንድ እደሜ 18፣ 7ኛ ክፍል፣ አዲስ አሳቡ ወሰን ሴት እድሜ 15 9ኛ ክፍል፤ ሁለተኛ ባላቤት ወርቅያጥፉ ባንቴ ተሰማ እደሜ 40 ልጆቻቸው ጥሩሰዉ አሳቡ ወሰን፣ ሴት እድሜ 3
  9. ዘማች አቶ አበባዉ ካሳ ጋሹ እደሜ 36 ከገዳያሱ ቀበሌ የዘመተ፣ ባላቤቱ ይለፉ አዳነ ደጓለ እድሜ 31፤ ልጆቻቸው ጌትነት አበባዉ ካሳ ወንድ እድሜ 12፣ 2ኛ ክፍል -በአባቱ ሞት ምክንያት ትምህርት ያቋረጠ፣ ሃይማኖት አበባዉ ካሳ ወንድ እድሜ 9፣ ጤናየ አበባዉ ካሳ ሴት እደሜ 4፤
  10. ዘማች አቶ እሽቱ አሻግሬ ዉዴ እድሜ 27 ከገብሲት ቀበሌ የዘመተ የት/ደረጃ 4ኛ፣ ባላቤቱ ዝግጁ አለ ጫኔ እደሜ 24፣ ባላቤቷ በተሰዋበት እለት ነፍሰ ጡር የነበረች፤
  11. ዘማች አቶ ተመስገን ዳኘ አማረ፣ እድሜ 28፣ ከገብሲት ቀበሌ የዘመተ፤ ባላቤቱ ያየሽ እንዳሌ አሸነፍ እደሜ 28፣ ልጆቻቸው ዉጭላይ ተመስገን ዳኘ ሴት፣ እድሜ 2፤
  12. ዘማች ወ/ር ሀብታሙ ሞስየ አለሙ እደሜ 30 ከፍንድቅበይ 01 ቀበሌ የዘመተ፣ 9ኛ ክፍል የት/ደረጃ ፣ ባላቤቱ ጎጃም አበጀ ፈንቴ እድሜ 25፣ ልጆቻቸው አለማየሁ ሀብታሙ ሞስየ ወንድ እድሜ 4፣ ታማኝ ሀብታሙ ሞስየ ወንድ እድሜ 3፣ ሁለተኛ ባላቤት ትጓደድ
  13. ዘማች አቶ ዘለቀ ተሾመ ዘሪሁን እድሜ 56 ከፍንድቅበይ01 ቀበሌ የዘመተ፣ የት/ደረጃ 8ኛ፤ ባላቤቱ ድታሽ በዛብሽ አየለ እድሜ 52፣ ልጆቻቸው አንማዉ ዘለቀ ተሾመ ወንድ እደሜ 22 9ኛ ክፍል፣ ትግስት ዘለቀ ተሾመ ሴት እድሜ 18 10ኛ ክፍል ፣ ምስጋና ዘለቀ ተሾመ ሴት እድሜ 14 8ኛ ክፍል፣ ሰማይነሽ ዘለቀ ተሾመ ሴት እድሜ 25፣ አረብ አገር ያለች
  14. ዘማች አቶ ወርቅነህ እሸቱ ፍቃዱ እድሜ 42 ከወይንየ ቀበሌ የዘመተ፣ ባለቤቱ በህይወት የሌለች፣ ልጆቹ፣ ዘበናይ ወርቅነህ እሸቱ ሴት እደሜ 16 3ኛ ክፍል፣ በላይ ወርቅነህ እሸቱ ሴት እድሜ 14 3ኛ ክፍል፣ አባትነህ ወርቅነህ እሸቱ ወንድ እድሜ 10 1ኛ ክፍል፣ ያየህ ወርቅነህ እሸቱ ወንድ እድሜ 7፣ ኬጅ የሚማር፣ አምላኩ ወርቅነህ እሸቱ ወንድ እድሜ 1፤
  15. ዘማች አቶ ጀንበሩ መንገሻ ደምሴ እድሜ 58 ከወይንየ ቀበሌ የዘመተ፣ ባላቤቱ በላይነሽ ባየ ታሪኩ እድሜ 46 የት/ደረጃ 7ኛ፣ ልጆቻቸው ዉቤ ጀንበሩ መንገሻ ሴት እድሜ 24፣ 10ኛ ክፍል፣ ዋለበላይ ጀንበሩ መንገሻ ወንድ እድሜ 22 8ኛ ክፍል፣ አለምነሽ ጀንበሩ መንገሻ ሴት እደሜ 20፣ 9ኛ ክፍል፣ መላኩ ጀንበሩ መንገሻ ወንድ እድሜ 18፣ 9ኛ ክፍል፣ መልካሙ ጀንበሩ መንገሻ ወንድ እደሜ 15 4ኛ ክፍል፣ አበረ ጀንበሩ መንገሻ ወንድ እድሜ13 2ኛ ክፍል፤
  16. ዘማች አቶ እንዳለዉ በላይ ምረቱ እድሜ 50፣ ከየዕድዉሃ ዙሪያ የዘመተ፣ ባለቤቱ ዉዳላት አንዳርጌ እድሜ 46፣ ልጆቻቸው ንጉስ እንዳለዉ በላይ ወንድ እድሜ 20 ከፍል 12ኛ፣ ያደግድግ እንዳለዉ በላይ ሴት እድሜ 22 9ኛ ክፍል፣ መለሰች እንዳለዉ በላይ ሴት እድሜ 14፣ ክፍል 6ኛ፣ ትጓደድ እንዳለዉ በላይ ሴት እድሜ 8፣ ክፍል 3ኛ፣ ጤናዉ እንዳለዉ በላይ ወንድ እደሜ 10 ክፍል 6ኛ፣ ብርቂት እንዳለዉ በላይ ሴት እድሜ 6፣ ክፍል 1ኛ፤
  17. አቶ ወርቁ ከበደ በለዉ እድሜ 50 ከአንሸብ ቀበሌ የዘመተ፣ ባላቤቱ አዳም አደራ ቸሬ እድሜ 40፤ ልጆቻቸው መልካ ወርቁ ከበደ ሴት እድሜ 24 10ኛ ክፍል፣ ደረጀ ወርቁ ከበደ ወንድ 20 እድሜ 8ኛ፤ አበበች ወርቁ ከበደ ሴት እድሜ 18፣ 11ኛ ክፍል፣ አንማዉ ወርቁ ከበደ ወንድ እድሜ 14 5ኛ ክፍል፣ ሀይለማርያም ወርቁ ከበደ ወንድ እድሜ 5 መዋለ ህጻናት፣ ወ/ሮ አዲሴ ስራዉ አጥናፉ እድሜ 39 2ኛ ባላቤት
  18. ዘማች አቶ ስንቱ መንግስቴ ከበደ እድሜ 58 ከወይንየ ቀበሌ የዘመተ፣ ባላቤቱ ሞሳ ሽፈራዉ አዳሙ እድሜ 40፣ ልጆቻቸው አዳምነሽ ስንቱ መንግስቴ ሴት እድሜ 30፣ 10ኛ ክፍል፣ ዉባለ ስንቱ መንግስቴ ወንድ እድሜ 28 9ኛ፣ ሀብታሙ ስንቱ መንግስቴ ወንድ እድሜ 26፣ ክፍል 6ኛ፣ አባይነህ ስንቱ መንግስቴ ወንድ እደሜ 24 9ኛ ክፍል፣ የሰዉልክ ስንቱ መንግስቴ ሴት እድሜ 22 10ኛ ክፍል፣ ብዙነሽ ስንቱ መንግስቴ ሴት እድሜ 20፣ 9ኛ ክፍል፣ 8 ላቀች ስንቱ መንግስቴ ሴት እድሜ 15፣ 5ኛ ክፍል፣ አለማየሁ ስንቱ መንግስቴ ወንድ 10፣ 1ኛ ክፍል፤
  19. ዘማች አቶ ሹሙ አባተ ባሴ እድሜ 60 ከየዕድዉሃ ዙሪያ ቀበሌ የዘመተ፣ ባላቤቱ ዉድየ መኮነን መሸሻ እድሜ 50፣ ልጆቻቸው ደህኔ ሹሙ አባተ ሴት እድሜ 22፣ 8ኛ ክፍል፣ አለልኝ ሹሙ አባተ ወንድ እድሜ 18 ክፍል 11ኛ፣ ብርቄ ሹሙ አባተ ሴት እድሜ 14 7ኛ ክፍል፣ ትጓደድ ሹሙ አባተ ሴት፣ እድሜ 10፣ 4ኛ ክፍል፣ ትግስት ሹሙ አባተ ሴት እድሜ 6፤

በአጠቃላይ 19 አባወራዎች 19 ሚስቶቻቸውን ባል አልባ፣ 77 ልጆቻቸውን አባት አልባ ያደረገ መስዋእትነት ከፍለዋል።

እንግዲህ በዚህ መረጃ መነጽርነት በመላው ሃገሪቱ (የወያኔ መሪዎች ጦርነቱን የጀመሩበትን ትግራይን ጨምሮ) ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ምን ያህል ህጻናት ያለአባት፣ ምን ያህል ሚስቶች ያለባል፣ ምን ያህል አረጋውያን የለጧሪ ቀባሪ፣ ምን ያህል እህቶች ያለወንድም እንደቀሩ ማሰብ ከባድ አይደለም። አካል ጉዳተኛ የሆኑንትን አንርሳ፤ ከሞቱት የባሰ እጣ ነውና የሚጠብቃቸው። ይህ በቀጥታ በጦር ሜዳ ተሳትፈው የተሰውትን ተዋጊዎች ብቻ የሚመለከት ነው። ከጦርነት ውጭ የጦርነቱ ሰለባ የሆኑትን ህጻናት፣ ጎልማሶች፣ እናቶች፣ አባቶች እናስታውሳቸው።

በየጎጇቸው ደጃፍ ተቀምጠው የማይመለሱ አባቶቻቸውን መምጣት የሚጠብቁ ስንት ሽህ ህጻናት እንደሚኖሩ፣ የስንቱ ቤት የሰንቱ ጓዳ የስንቷ እናት ልብ በሃዘን እንደጨለመ፣ የስንቱ ቤት እንደፈረሰ፣ የስንቱ ቤተሰብ እንደተበተነ እናስበው። ጦርነቱ ቀጥሎ ሌላ ተጨማሪ ወገኖቻችን ከሚያልቁ ችግሩ በሰላም እንዲቋጭ መደረጉ የጦርነቱን አስከፊነት እንዲህ አይነቱ መረጃ ይደረሰን ለነበረው ሰዎች ትልቅ የህሊና እረፍት የሰጠ ነበር።

ባለፈው እሁድ መጋቢት 15 2015 “ጦርነት ይብቃ ሰላምን እናጽና” በሚል መሪ ቃል ያየነው ሽርጉድ ግን ከላይ ከገለጽነው የህዝብ ሰቆቃ ጋር ምን ግንኙነት የሌለው በሰላም ስም የተድረገ ሽቀጣ ነው።

እኔም እደግመዋልሁ። ሰላም የሁሉ ነገር መሰረት ነው። ከፍተኛ መከራና አበሳ ያየውን ህዝብ ሰቆቃ የማያንጸባርቅ፣ የማያስታውስ፣ የማይዘክር፣ ህዝብ ለከፈለው መስዋእትነት የታሪክ ማስታወሻ የማይተው፤ በተሰበረ ልብ፤ ሃዘን የፈገግታ አቅማቸውን አሟጦ በወሰደባቸው ፊቶች፣ እንባ በቋጠሩ አይኖች፣ ቁጭት ነክሶ በያዛቸው ጥርሶች ሳይሆን፣ በፈንጠዝያ፣ በሳቅና በፈገግታ፣ በመሞጋገስና በመሸላላም በሰላም ስም የተካሄደ ትእይንት ሃገራችን የገባችበትን የጭካኔ፣ የግድየለሽነትና የሞራል ዝቅጠት የሚያሳይ ነው።

የመጋቢት 15ቱ የሰላም ወለፈንዴ ትወና ፣ ህዝብን ያገለለ፣ የሞራል መሰረት የሌለው በሰላም ስም ህዝብን ሰላም የነሳ ነው። ህዝብን በማፈን፣ በመዝረፍና መጨፍጨፍ ትራክ ሪኮርድ ያላቸው የቀድሞ ገዥዎች ከአዲሶቹ ገዥዎች ጋር ያልተቀደሰ ጋብቻ መፈጸማቸውን የሚያሳይ ትእይንት እንጂ ለህዝብ የተሻለ ዘመን መምጣቱን የሚያበስር አንዳች ነገር አልታየበትም። ህዝብ የሚናፍቀው ዘለቄታነት ያለው ሰላም ከእንዲህ አይነቱ ሞራልና መርህ አልባ ትርኢት አይመጣም። እንደሁሉም መርህና ሞራል አልባ ግንኙነቶች የመጋቢት 15ቱ ሽርክና መጨረሻው እንደማያምር ለመተንበይ ነብይ መሆንን አይጠይቅም። ቀደም ብሎ የተተነበየ መሆኑን ግን ሁሉም ልብ ይበል።

Latest from Blog

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
Go toTop