ድኀረ-1983 በተራዛሚው የኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ማግስት “የሀገር መከላከያ ሠራዊት” ከመቋቋሙ በፊት በትጥቅ ትግሉ ወቅት የኢትዮጵያዊነት የሀገር ፍቅር ስሜት የነበራቸውን፤ ለወያኔ ጠባብ የዘረኝነት ፍላጎት ማስፈፀሚያ የማይመቹ የኢሕዴን ነባር ታጋዮችን የማጥፋት ሥራ ተሰርቷል።
ሂደቱም 1983 ክረምት ወር ላይ የጀመረው የሰራዊት ግምገማ በነ አዲሱ ለገሰ፣ ተፈራ ዋልዋና፣ በረከት ስምዖን የሚመራ ነበር።
በሠራዊቱ ላይ የሚደረገው ግምገማ ዋና ግቡም ነባሩን ተዋጊ ኃይል ጠራርጎ ማስወጣት ነበር፡፡ በዚህ ግምገማ የ”ቴዎድሮስ”፣ “ዋለልኝ”፣ “አዋሽ”፣ “ሰንገዴ” የተሰኙ የኢህዴን ክፍለ ጦሮችን እንደጨው የማሟሟት ያህል ታጋዮን የመበተን ሴራ ተሸርቦ፣ አሳክተውታል፡፡
በወቅቱ የ”ቴዎድሮስ” ክፍለ ጦር መሪ ብ/ጀኔራል ተፈራ ማሞ ነበር። “ሰንገዴ” የተሰኘችውን ክፍለ ጦር ይመራ የነበረው ደግሞ ሜጀር ጀኔራል መለሰ (የአሁኑ የአማራ ልዩ ዋና አዛዥ) ነበር።
በትግሉ ጊዜ ስምና ዝና የነበራቸው እንደ አዋሽ ክፍለ ጦር ያሉ ክፍለጦሮች ጨርሰው እንዲፈርሱ ተደርጓል፡፡ ይህ ሂደት ነበር የአማራ ነባር ታጋዮች እንዲበተኑ፣ የቤተሰብ ጥገኛና ጎዳና ላይ እንዲወጡ ያደረጋቸው፡፡
(ያኔ የሆነውን ነገር ዛሬም ለመድገም ነው የታሰበው።)
ያኔ ትህነግ በኢህአዴግ ስም የሰራዊት ቅነሳ አስፈላጊ መሆኑን አወጀ፡፡ ልክ ዛሬ ኦህዴድ፣ በብልጽግና ሥራ አስፈፃሚ ስም ውሳኔ አሳለፍኩ እንዳለው መሆኑ ነው።
ያኔ የኢህዴን ክፍለ ጦሮች ተቅሊጥ (ብወዛ) ይደረግ ተብሎ ከ3,500 በላይ ታጋዮች ያለምንም ወደጎሚያ (መሰናበቻ ካሳ) እንዲሰናበቱ ሲደርግ ትሕነግ ከሰራዊቱ ለቀነሳቸው የራሱ ታጋዮች ከጎንደር በኃይል ከወሰደው የወልቃይት ጠገዴ መሬት (ዲቪዥን ከመንደር አንድ እስከ ስድስት፤ እንዲሁም ‹ሽግልል› በተባለ የሰፈራ መንደሮች) ላይ ከነትጥቃቸው ለመደበኛ ህይወት አስፍሯቸዋል፡፡
እነዚህ ተቀናሽ የቀድሞ ታጋዮች በማህበር ተደራጅተው ከአማራ በተነጠቀ መሬት በሜካናይዝድ እርሻ ስራ መተዳደር እንዲጀምሩ አድርጓል፡፡
(ይህን ግፍ ነው ከ30 ዓመት በኋላ ሊደግሙት ያሰቡ)
በአንፃሩ ኢህዴን ከነበሩት ታጋዮች በርካቶችን ሲያሰናብት ቅያሬ ልብስ እንኳ አልሰጣቸውም ነበር፡፡ አብዛኞቹ (ተሰናባች) ታጋዮች ከተማን የማያውቁ ለዛውም የደሃ አርሶ አደር ልጆች በመሆናቸው ለመሀል ሀገር ፍጹም አንግዳ ነበሩ፡፡ ወደ አገር ቤት ለመመለስ የአዲስ አበባን ህዝብ ምጽዋት መጠየቅ ነበረባቸው፡፡ በዓላማ ልዩነት ከተዋጉት የቀድሞ ጦር ሰራዊት ጋር እኩል ፎጣ አንጥፈው የለመኑበት አሳዛኝ ሁኔታ የትህነግን ሴረኝነት የኢሕዴን/ብአዴን አድርባዮችን ድርጅታዊ ሃጢያት የከፋ ያደርገዋል፡፡
በመከላከያ ተቋም ውስጥ ይታይ የነበረውና ዛሬም ተረኛው ኃይል እያስቀጠለው ያለ ተቋማዊ ዘረኝነት አመጣጡ ይህን የሚመስል ነው።
ነባሩን ብቻ ሳይሆን አርበኛውንና ተገዳዳሪውን ኃይል በማጥፋት ለአንድ ብሔር የፖለቲካ ዓላማ ማስፈፀሚያ መሳሪያ ማድረግ ወያኔ ጀምሮት ኦህዴድ እያስቀጠለው ያለ የተቋማዊ ዘረኝነት (institutional racism) ውርስ ነው።
(ይህን ውርስ ዛሬ በአዲሱ ተረኛ ኃይል ለማስቀጠል ነው የልዩ ኃይል ፍርሰት የተቀመረው።)
ከሰላሳ ዓመት በኋላ ካለፈ ስህተቱ የማይማረው በዋናነት በብአዴን/ብልጽግና ውስጥ የሲኒየርነት ሚና ይዘው የተሰለፉ አመራሮች የቀድሞ አለቆቻቸው አማራን አሳልፈው በሸጡበት መንገድ ላይ ናቸው።
ከመነሻው ከመጋቢት 2010 ወዲህ ተሰራ የተባለው የመከላከያ ሪፎርም ወደ ፈረቃ መቀየሩ እየታወቀ እርምት ሳይሰጥ፤ ከመምሪያ ኃላፊዎች እስከ ዕዝ አመራር፤ ከሚሊተሪ ካውንስል እስከ ወታደራዊ አታሼ ድረስ በአንድ ወገን ኃይል ሲጠቀለል ማስቆም ያልቻለ አመራር፣ ያለፈ ጥፋቱን ሳያርም በመላ ኢትዮጵያ የኃይል ቁጥጥርን ለአንድ አውራ-ብሔር ለማስረከብ የተረገመውን ዘመን ሊደግም አጨብጮቦ መጥቷል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ቀዳሚ ተጠያቂዎቹ አማራን ወክለው የብልጽግና ሥራ አስፈፃሚ ውስጥ ያሉ ስምንቱም አመራሮች ናቸው።
ለታላቋ ኦሮሚያ ግንባታ ‘State Formation’ ላይ ያለው ኃይል፣ ያውም የሀገሪቱን የፀጥታ ኃይል 90% ለመወከል አልሞ እየሰራ ባለበት ሁኔታ ሁሉንም ክልሎች አስተባብሮ ውሳኔውን እስከ ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ ማቆየት ያልቻለ የአማራ አመራር ከታሪክ ተጠያቂነት አያመልጥም!! በሰላም መኖርም የማይታሰብ ነው!!!
ብዙ ልፋፌ የተሰማበት የፕሪቶሪያው ስምምነት ወረቅት ላይ ቀርቶ፣ ትሕነግ “ለልዩ ተልዕኮ” በሚል ተጨማሪ ኃይል እያሰለጠነ፣ የትጥቅ አቅሙንም እያሳደገ ባለበት ሁኔታ የክልሎች ልዩ ኃይል ይፍረስ የሚል ውሳኔ መቀበል/አብሮ መወሰን የሀገር አፍራሾቹን ታሪክ መጋራት ነው።
የኦህዴድ/ብልጽግና ውሳኔው ላይ፦
“የክልል ልዩ ኃይል አባላት የሚሸፍኑትን ስራዎች የመከላከያና የፌዴራል ፖሊስ ይወጡታል/ይሸፍኑታል”
የሚለው ሀሳብ፦
ወልቃይት-ጠገዴ፣ ጠለምት፣ ራያ፣ ዛታ፣ ኦፍላ አካባቢዎች ወገኖቹን እየጠበቀ ያለው የአማራ ልዩ ኃይል እንዲወጣ/እንዲበተን ያለመ የአማተሮች ሴራ ስለመሆኑ ግልፅ ነው።
መታወቅ ያለበት ነገር ዛሬ እውነታው ስለመቀየሩ ነው።
እንደ 1984/85 ታጋይን በትኖ አልያም በመዋቅራዊ ጥቅለላ ማሟሟት የሚቻልበት ነባራዊ ሁኔታ አሁን ላይ የለም፤ ሊኖርም አይችልም።
ከምንም በላይ በኢትዮጵያ ህልውና አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ ከመዳከር ሌሎች አማራጮችን እስከማለም የሚደርስ የብሔርተኝነት ስሜት እያደገ በመጣበት ሁኔታ ይህን የአማተሮች ሴራ ማሳካት የሚቻል አይደለም።
እርማችሁን አውጡ!!
ልዩ ኃይል ድንገገት ከእንቀልፍህ ተነስተህ በጥላቻ እንደምታፈርሰው የምስኪኖች መኖሪያ ቤት አይደለም።
እንደአማራ ካየነው፣ በሺዎች የሚቆጠሩ አናብስቶች አጥንታቸውን ከስክሰው የዘመናት የማንነት ጥያቄን የመለሱበት የደም ተቋም ነው።
እንደአገር ካየነው፣ በኢትዮጵያ በዘር ላይ የተመሰረተው የክልሎች አወቃቀር ሳይፈርስ የሚፈርስ የልዩ ኃይል አደረጃጀት የለም!! ሊኖርም አይገባም!!
ሶማሌ፣ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ሲዳማ፣ አማራ፣ … በልዩ ሁኔታ ከፍተኛ የውስጥና የውጭ ስጋት ያለባቸው ለወሰንና ድንበር ተሻጋሪ ጥቃቶች ተጋላጭ የሆኑ ክልሎች ናቸው።
እነዚህ ክልሎች ለአብነት ተጠቀሱ እንጅ የደቡብ ብሄረሰቦች ሁሉም የማንነት ቡድኖች፣ ሐረሪ፣ ድሬዳዋ፣ … ቤኒሻንጉል፣ የመዋጥ አደጋ ውስጥ በወደቁበት በዚህ ጊዜ፤ ያውም የሀገር መከላከያና የፌዴራል ፖሊስ የአመራር ስምሪት ጤናማ ባልሆነበትና የሴራ ፖለቲካ ሚስፈፀሚያ በሆኑበት ሁኔታ ልዩ ኃይል ይፍረስ ብሎ መፍቀድ መታነቂያ ገመድን በገዛ እጅ እንደማጥለቅ ይቆጠራል።
በአጭሩ ልዩ ኃይላችን የሺዎች ሰማዕታት አደራ ያለበት የደም ተቋም ነው!!
ይህ ተቋም የክብር ስንብት ሊያደርግ የሚችለው የዜጎች የሞት መዝገብ የሆነው ሰነድ (ሕገ-አራዊቱ) በአዲስና መላ ኢትዮጵያዊያንን ባሳተፈ መልኩ ሲሻሻል፣ በአዲሱ ማኀበራዊ ውል መሰረት የዜጎች ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ፣ ሀብት ንብረት የማፍራት መብታቸው ያለገደብ ሲተገበር ብቻ ነው።
በተረፈ ይህ የሞት መዝገብ ተቀዶ ሳይጣል፤ በዘር ላይ የተመሰረተው የክልል አወቃቀር ሳይፈርስ የሚፈርስ ልዩ ኃይል የለም!!!
(እንደአማራ ይህን የፈተና ጊዜ በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ ፈተናው የመውጫ ዕድል ይሆናል። እንግዲህ የትግል ጠረጴዛው ላይ ያለው ምርጫ ሁለት ነው፦ የኩርድ ወይም የእስራዔልን ዕጣ ከሚሸልመው የትግል መንገድ አንዱን መምረጥ ነው!!)