በአማራው ሕዝብ ላይ ላለፋት አመታት ሲካሄድ የቆየው ሕልውናውን የመናድ ዘመቻ የአዋጁን በጆሮ እንዲሉ ከማንም የተሰወረ አይደለም:: በዚህ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ባለታሪክ ሕዝብ ላይ በቅንብር የተከፈተው ዘመቻ በእግዚአብሄር ቸርነት ተጠብቆ ነው እንጂ እረኛ እንደሌለው መንጋ በየአቅጣጫው ተበትኖ ወጥቶ በቀረ ነበር:: ልጅ እያለው እንደ መሀን ወገን እያለው እንደባዳ ለመከራው ቀን የሚደርስ ለሃዘኑ አጽናኝ ዘመድ አጥቶ እንባውን እያበሰ ብዙ የጭለማ አመታትን አሳልፋል::
ለአማራው ሕዝብ መዋረድ መረገጥና መከራ ላይ መውደቅ ምንም ምክንያቶቹ ጠላቶቹ ቢሆኑም ሳይማር ያስተማረው ሳይጠግብ ያጎረሰው ተራቁቶ ለክብር ባበቃቸው ልጆቹ ተክዶ በመቆየቱ ለመሆኑ ለክርክር የማይቀርብ ሃቅ ነው:: እርግጥ ነው ቁጥሩ አነሰ እንጂ የወገን ስቃይና መከራን አይተው ማለፍ ያልሆነላቸው ልጆቹ እስከ ሞት ታምነው አልፈዋል:: በእስር ተንገላተው በስደትም ባክነው ቀርተዋል:: ፕሮፌሰር አስራትን መቼም እንዘነጋም:: የነጎቤ መስዋዕትነት የነኮሎኔል ደመቀን ጀግንነት : የነማሙሸት አማረን ጽናት ታሪክ በክብር የሚያኖረው የቅርብ ግዜታሪካችን ነው:: በሃገር ውስጥ አቅምና ደጋፊ አጥቶ እንጂ ሕዝባችን በሚችለውና ባለው አቅም ብዙ ደክሟል::
በሃገር ውስጥ ከጸናው አፈና አንጻር አንጻራዊ ነጻነት ባለበት በውጪ ሃገር ተሰዶ የሚኖረውን የአማራ ማሕበረሰብ ለማሰባሰብ ላለፋት እረጅም አመታት ብዙ ሙከራ ሲደረግ ቆይቷል:: ነገር ግን ወገናችን የሚደርስበትን የተደራጀ ጥቃት እንደ ሕዝብ ተደራጅቶ ለመታገል በማያስችል አስቸጋሪ ዘርፈብዙ ሁኔታ ውስጥእንዲያልፍ ተገዶ ቆይቷል ::
የአማራ ሕዝብ ላለፉት 30 አመታት በሕወሃት አራቱን አመታት በኦነጋውያን የመከራ መዐበል ሲንጠው ሰቆቃ ስደትና ሞት ሲፈራረቁበት ቆሞ ከማየት ውጭ የሚታደገው አላገኘም:: አማራ የገጠመውን የሕልውና ፈተና በሚመጥን ደረጃ ለመቋቋም የሚያስችል ቁመና ላይ ዛሬም መድረስ አለመቻሉ መጭውን ግዜ አስፈሪ አድርጎታ::
የአማራ ፖለቲካ ዛሬም ግራ ከተጋባና ከተሳከረ ወጀብ አልወጣም:: የአቅጣጫ መዋዠቅ እና የእስትራቴጂ ብዥታውን ማጥራት ተስኖታል:: ግብና አላማውን ስቷል :: የጠላቶቹን አሰላለፍ የጥላቻቸውን ጥልቀትና ሊያጠፉት ሲዖል ድረስ ለመጏዝ ያላቸውን እቅድና ቁርጠኝነት በሚገባ የሚረዳ ተቋም አርጦበታል:: ያንጃበበትን ከበባ የታቀደለትን የቅርብና የእሩቅ የመጨፍለቅ እቅድ መረዳቱም ያጠርጥራል:: የጋራ ራዕይና የትግል አቅጣጫ ቀርጾ የሚመራው ጠንካራና የተማከለ የፖለቲካ ሃይል ማዋለድ አልቻለም:: ወንዘኝነትና ጎጠኝነት ጥቅምና ግለኝነት የተጫነው ኤሊት በመብዛቱ የእዝ ሰንሰለት የሌለው ብትን አድርጎታል:: ተቋማዊ አለመሆን የፈጠረው ክፍተት ሃገር ጠባቂው ለዘመናት ጽኑና ብርቱ ሆኖ የኖረው ሕዝብ ዛሬ ክፍተቶቹን በቅጡ መሸፈን አቅቶት ለእርድና እልቂት ተጋልጧል::
ደካማ ሕብረተሰብ የደካማ ልሂቅ ውጤት ነው:: የምሁራኑ ድብታ ማህበረሰቡን ለሽብር ዳርጎታል:: ለመልቲዎች ስብከት ለጮሌዎች ግርግር አመቻችቶታል ::አማራ ብቁና ተደማጭ አሰባሳቢ ተቋም ባለመገንባቱ የማንም ቦዘኔ የሚታደምበት አንባ: የዩቱብ ሸቃዮች ; ትኩረት ያጡ አክቲቪስቶች የሚነግዱበት ገበያ ሆኗል:: ደብተራውም ቁራሌውም አልፎ ሄያጁም ሱቅ በደረቴውም አጀንዳ ሰጭ የሆነበት አሳፉሪ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ ወድቋል:: ጋለሞታ አጫዋቹን አርበኛ ; የከተማውን አውደልዳይ ታጋይ ; ቀባጣሪውን አዋቂ እነሆድ አምላኩን አሰባሳቢ ; ያደረገ ትግል ውድቀትን እንጂ ድልን አያቀዳጅም::
አማራን በማደራጀት ስም የሕዝብን ኪስ ያጠቡና የህዝቡን መከራ የጡረታ ዘመናቸው ማገገሚያ ያደረጉ ጎረምሶችና ሽማግሌዎችን በዝርዝር ማቅረብ ይቻላል:: እንደነዚህ አይነት የእንብላውና እንማው የአሮጌው ዘመን የፖለቲካ ቅሪቶችን አራግፎ ሕዝባዊ ወገንተኝነት ያላቸውን ምግባረ ቀናና ለትግሉ ታማኝ የሆኑ ግለሰቦችን ማሰባሰብ ይገባል:: አማራን ያሉ ተቋሞች አስቀድሞ የእጅና የአፍ አመል ያላቸውን በአሞራና አራዊት ስም ድርጅት ፈጠርን የሚሉ የፖለቲካ አሳሞችን በመጀመሪያ ለይቶ በማራገፍ ከጥቅመኞችና አሉባልተኞች የጸዳ በንድፈ ሃሳብ የሚመራ ስትራቴጂያዊ ጥቅሞቹን በሃይል አሰላለፉ ውስጥ ያነጠረ ; ወዳጅ ማብዛትና ጠላትን መቀነስ የሚያስችል ስልትና ዘዴን የሚከተል ብቁ መሪዎች ማውጣት ይጠበቅበታል::
አማራው በተዛባ ትርክትና ባለፈ ዘመን የታሪክ እዳ ተጠያቂ ተደርጎ በገፍ የሚጨፈጨፈው የፈለገ የሚረግጠው ያይንህ ቀለም አላማረኝም በሚል ከየቦታው የሚፈናቀለው ለምንድን ነው:: በእርግጥ የሰራው በደል ኖሮ ነው:: አሳፉሪና ሃገር የጎዳ የታሪክ ነውር ፈጽሞ ነው:: ወይስ የሱ ያልሆነን ሃገርና ክልል በወረራ ይዞ በግፍ ተስፉፍቶና ሕዝቦችን በባርነት ገዝቶ ሳይሆን ጠላቶቹ ሞራሉን አጠልሽተው ሕልውናውን ሊረግጡ ያነበሩትን ሱኽት ትርክትእየመከተ ሊያመክን የሚችል ሃይል ባለማደራጀቱ ነው::
አማርኛ ቋንቋ እንዲስፉፉ የልሳንና የጽሁፍ ቋንቋ አድርጎ ለጥቁር ሕዝብ ኩራት ለኢትዮጵያውያን መማሪያነትማካፈሉ ወንጀል ነውን? ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት እንዲከበር ለሺ ዘመናት ተፉልሞ ማቆየቱ ስህተት ይሆን:: ይህንን አዲሱ የአማራ ትውልድ በቅጡ ተረድቶ አኪያሄዱን ሊያርም ይገባል:: አባቶቹ ያወረሱት ታላቅ ሃገር ብዝሃነትን ያወቀች ሁሉንም እንደየ ወግና ልማዱ ያቀፈች በክብር ደምቃ በነጻነት ያበራች የጥቁር ሕዝብ ሁሉ ኮከብ ነች:: ያንን ክብሯንና ማዕረጏን መመለስ እንጂ መንበርከክ ለዚህ ትውልድ ዘላለማዊ ውድቀት ነው::
ዛሬ የማንም ወፍ ዘራሽና የበታችነት ስነ ልቦና ያዳሸቀው የነጻነትን ክብር የማያውቅ የባርነት ጥማት ያናወዘው ተረኛ መንጋ ብሄሬና ቋንቋዬ ባህሌ የሚለው እሴቱ የተጠበቀው በነፍጠኛው አማራ እንጂ አጏትና ፈርሱን ከሚምግ ሗላ ቀር የመንደር ወፈፌ አይደለም:: ኢትዮጵያ በአውሮፓውያን ተገዝታ ቢሆን ኖሮ እንኳን ባህልና ትውፊታችን ስማችንም ስሜታችንም ሌላ በሆነ ነበር:: ትውልዱ ይህን መሪር ሃቅ በማስረጃ እያጣቀሰ የጠላቶቹሴራ ሊያከሽፍ ይገባል::
አማራው ይህ ሁሉ ግፍና ስቃይ የሚፈራረቅበት አቅም አጥቶና ወኔው ነጥፎ ሳይሆን ልሂቁ ዘመኑን የሚዋጅአደረጃጀት ፈጥሮ ሊያነቃንቀው ባለመቻሉ ነው:: አማራው በአዋጅ ማርከህ ታጠቅ በተባለው መሰረት በአሁኑወቅት በተገቢው ሁኔታ እራሱን አስታጥቆ ይገኛል:: አማራው ትጥቁም ስነልቦናዊ ዝግጅቱም ወኔና ገፊ የሆነው የበደል ማዕበል አንደ ጎርፍ ጠላቶቹን ጠራርጎ ከእራሱ ላይ እንዳያራግፍ ሳንካ የሆነበት የመሪ ድርጅት አሰላሳይ ልሂቅና ስትራቴጂ ነዳፊ ፖለቲከኛና ትቋም ማግኘት ባለምቻሉ ነው::
ሰሞኑን በውጭ የሚኖሩ የአማራ ድርጅቶች ተሰባስበው ለመምከር ቀጠሮ መያዛቸው ሰምተናል:: ሃገር በተቸገረበት የአማራው ሕዝብ ከመቼውም ግዜ በላይ የሕልውና አጣብቂኝ ላይ በደረሰበት በዚህ ወቅት ተሰባስቦ መምከሩ ከሃገርና ወገን ወዳድ ዜጎች የሚጠበቅ ነው:: ብዙዎች በተስፉና በጉጉት የሚጠብቁት ወሳኝ ስብሰባ ነው:: ይህ ስብስብ ያለፉ ተሞክሮዎችን የባከኑ እድሎችንና መጪ ሁኔታዎችን በጥልቀት ፈትሾ ትግሉን አቅጣጫ የማሲያዝ ታሪካዊ አደራም ይጠብቀዋል::
በተለይም በምዕራቡ አለም በየግዛቱ ተንጠባጥበው በአማራ ስም የተፈጠሩ ከዘኬ ማህበር ብዙም ያልራቁ ላዕላይ አመራርና ወጥ የሆነ ፖሊሲ የሌላቸው ከ50 በላይ ድርጅቶች እንዳሉ ይነገራል:: በዚህ አይነት ብትንና ጥቃቅን ድርጅቶች ፈጽሞ ምንም መስራት አይቻልም:: ለአንድ አማራ ጥያቄ ሃምሳ ጎራ እንደ አሜባ ማራባቱ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ከፍተኛ ነው::
የአማራው ተሰብሳቢዎች ከሁሉ አስቀድሞ እነዚህን ጥቃቅን የአካባቢ ድርጅቶች ባግባባ ሁኔታ አንድና ወጥነትያለው መዐከላዊ አመራር ፈጥሮ ትግሉን አንድ እርምጃ ወደፊት ለማሻገር ውሳኔ ካልሰጡበት የመሰባሰቡ ፉይዳ ትርጉምም ትርፍም የማያስገኝ ግዜያዊና የጥቂት ቡድኖች ስሜት ማርኪያ ከመሆን አያልፍም::
አማራ አንገቱ አንድ ነው የሚል መፈክር ይደመጣል:: ጥያቄውም አንድና አንድ ነው:: እራሱን ከጥቃት ተከላክሎ በሰላምና በጉርብትና ከወገኖቹ ጋር እራሱን አስከብሮ ሌሎችን አክብሮ በሰላም መኖር: : የትግሉን መጠናክር የሚፈልግ ማንኛውም አካል ጠንክሮ ለመውጣት ሽቅብ የሚለውን ኢጎ ተቆጣጥሮ ከቡድን ጥገኝነትና ከተቸካይ አስተሳሰብ ተላቆ ትልቁን ስዕል ሃገር የማዳኑን እና ሕዝብ የመታደጉን ታሪካዊ አደራ ለመወጣት ካልቻለ ምናልባትም አማራውን በውጭ አጠናክሮ የማደራጀቱ ሂደት እስከ ወዲያኛው እንዳይቀለበስ ሊታሰብበት ይገባል::
ሌላው የሃገራችን ፖለቲካ ከንቱ ልማድ በተለይ አማራው ጋር ጎልቶ የሚታየው ለባለ ቅጥያ ሙሁራን ያለው ጨለምተኛ አተያይ ሊስተካከል ይገባል:: በምሁር ስም የሃገሪቱን አካሄድ: የፖለቲካውን የሃይል አሰላለፍ የመረዳት አቅም ተሞክሮና ልምድ የሌለውን በምሁር ስም እንደተለመደው መሪ ማድረግ ተገቢ አይደለም:: ዶክተር ፕሮፌሰር ሃርቫርድ ኦክስፎርድ የተማረ ወይም የሚስተምር ምሁር ያለ ፖለቲካ ተሞክሮው በአካዳሚክ ብቃቱ ብቻ መምረጥ ትግሉን እንደሚያበላሽ ተደጋግሞ ታይቷል::
የምሁራን ተሳትፎና ምሁራዊ አቅም ያለው መሪ ወደፊት ማቅረብ አስፈላጊም ተገቢም ነው:: ነገር ግን ፖለቲካዊ ንባብና በቂ መረዳት የሌለውን ማግበስበሱ ጠቃሚ አለመሆኑም ሊታስብበት ይገባል:: ታግሎ የሚያታግል ግዜውን ለትግሉ የሚሰጥ ብቃትና ችሎታ ያለውን መሪ መሰየሙ ግዜው የሚጠይቀው አጣዳፊ ጉዳይ ነው::
ድል ለሕዝባችን
እግዚያብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!!!