መግቢያ
በ13 ማርች 2023 “ወደ ሰላም ወይም ወደ ቀውስ፤ የትግራይ – ኢትዮጵያ ጉዳይ” በሚል ርእስ አንድ ጽሁፍ አቅርቤ ነበር። የዛሬውን ጽሁፌን ርእስ ደግሞ “ኢትዮጵያ ወደ ቀውስ” ብዬዋለሁ። ይህን ያልኩት በጣም በሚያስገርም ፍጥነት የሰላምና የቀውስ አማራጩ በውል ስለለየለት ነው። ኢትዮጵያ ወደ ቀውስ በተጠናከረ መንገድ የምትሄድበት አማራጭ ግልጽ ሆኗል። የዛሬው ጽሁፌ በዋንኛነት የሚያተኩረው የሰላም አማራጩ እንዴትና ለምን እንደተዘጋ በሚያሳዩና ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ ነው።
- ህወሃት ከሽብርተኛነት መዝገብ መፋቁ፣ የጌታቸው ረዳ ርእሰ መሰተዳደር ሹመት፣ የቀጠለው የወያኔ ቡድኖች ሽኩቻ፣
በ13 ማርች 2023 “ወደ ሰላም ወይም ወደ ቀውስ፤ የትግራይ – ኢትዮጵያ ጉዳይ” በሚል ርእስ በፌስ ቡክ ገጼ ላይ አንድ ዘለግ ያለ ጽሁፍ አቀረብኩ። እንደገና በ 18 ማርች 2023፣ በዚሁ የፌስቡክ ገጼ ላይ፣ በትግራይ ውስጥ የሚሆነው ሁሉ ለምን ሊያሳስበን እንደሚገባ ለመጠቆም የሚከተለውን ማስታወሻ ጻፍኩ።
“ትግራይን በተመለከተ ለምን ትኩረት እንደማደርግ በቅርቡ በበቂ ምክንያቶች የተደገፈ ጽሁፍ አቀርባለሁ። በጥቅሉ አሁን ትግራይ ውስጥ የሚሆነው በመላው ኢትዮጵያ ወደፊት ሊሆን ከሚችለው ነገር ጋር በቀጥታ ይያዛል የሚል እምነት አለኝ። የትግራይ ህዝብ አሁን የተፈጠረለትን አጋጣሚ ተጠቅሞ መብቱን ፣ ጥቅሙን፣ ንብረቱን እና ሰላሙን ከተደራጁና ከነቀዙ የፖለቲካ አካላት ፈልቅቆ ማውጣት ከቻለ ለተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ፋና ወጊ ይሆናል። የትግራይ ህዝብ ተሸነፎ መብቱን እና ጥቅሙን መልሶ የዘረፋና የግፍ ሬኮርድ ላላቸው የተደራጁ የፖለቲካ አካላት አሳልፎ ከሰጠ የተቀረውን የኢትዮጵያ ህዝብ ሃብት በመዝረፍ፣ መብቱን በመርገጥ በባርነት ለሚገዙትና ሊገዙት ላሰፈሰፉ የተደራጁ የፖለቲካ አካላት የልብ ልብ የሚሰጥ ሁኔታ በሃገራችን ይቀጥላል። በትግራይ የሚቋቋመው ጊዜያዊ መንግስት የአመሰራረት ሂደት ምን ይመስላል? ማን ይቆጣጠረዋል? የሚሉት ጥያቄዎች ወሳኝ የሚሆኑት ለዚህ ነው። በድርጅቶች ሳይሆን በህዝብ ውሳኔ የሚመሰረትና በህዝብ ቁጥጥር ስር የሚወድቅ ከሆነ ብሩህ ተስፋ ለትግራይ ለተቀረውም ኢትዮጵያም ይጭራል።”ብያለሁ
ከላይ የጠቀስኩትን ማስታወሻ በጻፍኩኝ በአራት ቀናት ውስጥ የትግራይ የሽግግር መንግስት ምስረታ ተጠናቋል። በኢትዮጵያ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ በህወሃት ላይ ተጭኖ የነበረው የሽብርተኛነት ታርጋ ተነስቷል። ጌታቸው ረዳ የህወሃት ድርጀት ብቻ ሳይሆን የትግራይ የሸግግር መንግስት ፕሬዚደንት መሆኑ በኢትዮጵያ መንግስት ተቀባይነት አግኝቷል። ትልቁ ቁም ነገር ህወሃት ለምን ከሽብርተኛነት ፍረጃ ተነሳ አልተነሳም አይደለም። ለኔ ትልቁ ቁምነገር ከላይ እንደገለጽኩት የሽግግር መንግስቱ አመሰራረት ከትግራይ ህዝብ እጅ ወጥቶ በወያኔና በሌሎች ድርጅቶች እጅ መውደቁ ነው። የዛሬው ጽሁፌ በዚህ ቁምነገር ላይ የሚያተኩር ቢሆንም ወያኔ ከሽብረተኛነት ነጻ በተደረገበት ሂደት ላይ የተወሰኑ ነገሮችን ሳላነሳ ማለፉ ነውረኛ ያደርገኛል።
አንድ ድርጅት ህዝብና ሃገርን ለማሸበር አቅም እስከሌለው ድረስ ሽብርተኛ ተባለ አልተባለ ለህዝብ ትርጉም አይኖረውም። የቴክኒካሊቲ ጉዳይ የህዝብ ችግር አይደለም። ወይም አንድ ድርጅት ከሽብርተኛነት ጋር በተያያዘ ሲያስተጋባቸው የነበሩ አመለካከቶችና ራእዮች ሰርዣለሁ ማለቱ፣ በተለይ ከወያኔ ጋር በተያያዘ አቶ ሬድዋን ሊነግረን እንደሞከረው፤” በሃገር ውስጥ አንድ የመከላከያ ሰራዊት ብቻ እንደሚኖር፣ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት እንደሚያከብር” ወያኔ በቃልና በጽሁፍ መስማማቱ ትልቁ ከሽብርተኛነት ፍረጃ ነጻ ሊያደርጉት የሚችሉ መሰረታዊ ነጥቦች አይደሉም። አቅም እስከሌለው ድረስ ጠዋትና ማታ ሃገር አፈርሳልሁ፣ የትግራይ መከላከያ ሰራዊት እገነባልሁ፣ የኢትዮጵያ አንድነት አናጋለሁ በማለት በድምጽ ማጉሊያ ሲያንባርቅ ቢውል የህዝብ ችግር አይሆንም። ይህ በማድረጉ ወያኔን መንግስት አሸባሪ አለው ወይም አላለው ህዝብን የሚገደው አይሆንም።
የወያኔን ከሽብርተኛነት መዝገብ መፋቅ አሳሳቢ የሚያደርገው በ13 ማርች 2023 በማስረጃ አስደግፌ ለማቅረብ እንደሞከርኩት ህወሃት ቁልፍና እና ወሳኝ የሆኑትን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነቶች ፈጽሞ አለመፈጸሙ ነው። ከባድና ቀላል መሳሪያዎቹን አላስረከበም። ወታደሮቹ ትጥቅ አውርደው የፌደራል መንግስቱ በሚቆጣጠራቸው ካምፖች ውስጥ ለተሃድሶና ለዲሞብላይዜሽን በሚመች መንገድ አልተሰባስቡም። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እንኳን መቀሌ ቀርቶ በሁሉም የትግራይ ወረዳዎች መግባት አልቻለም። መከላከያ መቀሌ እንዳልገባ እየታወቀ በአቶ ሬድዋን አማካይነት፣ ለምን ምክር ቤቱን ለመዋሸት እንደተፈገ ግን አልገባኝም። ከዚህ የሃሰት መረጃ ውጭ ሌላውን ሃቅ እኔ ሳልሆን ወያኔ ከሽብርተኛነት ነጻ ለማድረግ የቀረበውን ሃሳብ ቅዱስነት ሲያብራራና የሚቃውሙትን ሲሞግት የነበረው የነጌታቸው ረዳ የቅርብ ጓደኛ የሆነው የኢትዮጵያ መንግስት ተወካይ አቶ ሬድዋን ሁሴን ያመነው ሃቅ ነው።
የኔ አላማ ወያኔን ከሽብረተኝነት ፍረጃ ነጻ ለማድረግ አቶ ሬድዋን ሁሴን እና ሌሎች የመንግስት ተወካዮች ያንን ያህል ለምን መቀላመድ እንዳስፈለጋቸው ለመመርመር አይደለም። ይህን ማድረግ የሚፈልግ ሰው በጣም በቀላሉ አቶ ሬድዋን ያቀረበውን በምክንያት ላይ ያልተመሰረተ ለወያኔ ጥብቅና የቆመበትን የ12 ደቂቃዎች ንግግር ባዶነት በማሳየት እርቃኑን ማቆም ይችላል። በምክር ቤቱ ስብሰባ በተሰጠቻቸው ጥቂት ደቂቃዎች “ንጉሱ እራቃኑን መቅረቱን” ለማሳየት የአብን የኢዜማና ሌሎችም ለህሊናቸው ያደሩ ብልጽግናን ወክለው ፓርላማ የገቡ የምክር ቤቱ አባላት የተቻላቸውን አድርገዋል። እነዚህ የሬድዋን ንግግር የያዙ 12 ደቂቃዎች፣ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የምክር ቤቱን ውሎ ዘገባ ባቀረበበት የሚከተለው ሊንክ ላይ ( https://www.youtube.com/live/V1IZGGOTo-I?feature=share ) ከ1 ሰአት ከ2 ደቂቃ ጀምሮ፣ እስከ 1 ሰአት 14 ደቂቃ መሃል የሚገኙት ደቂቃዎች ናቸው።
የእነዚህ 12 ደቂቃዎች ንግግር ከአድዋ ጦርነት በፊት የ1889ኙን (እአአ) የውጫሌን ውል ትክክለኛነት በሸፍጥ፣ የምኒሊክ መንግስትን ለማሳመን የጣሊያንን መንግስት ወክሎ በምኒልክ እልፍኝ በእብሪት እንደተከራከረው እንደ ካዎንት ፒየትሮ አንቶኔሊ (Count Pietro Antonelli) ንግግር በታሪክ ሲታወስ የሚኖር ይሆናል። ከታሪክም መታወሻነት አልፎ እንደ ውጫሌ ውል ወይም ከዛም የከፋ መዘዝ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ሊያስከትል ይችላል። ምኞቴ ግን እንዳያስከትል ነው። የሰውነት ቋንቋ (body language) ማንበብ የሚችሉ ሰዎች አቶ ሬድዋን ራሱ የሚናገረው ነገር ምቾት ያልሰጠው መሆኑ በንግግሩ መሃል ራሱን በእስክሪፕቶው ለማከክ ያደረግውን ሙከራ እንደማመላከቻ ማቅረብ ይችላሉ።
ቀደም ብዬ ቃል በገባሁት መሰረት የሬድዋንን ንግግር ቃል በቃል በማቅረብ ምን ያህል ከሃቅና ከአመክኖ የተጣላ መሆኑን ለማሳየት አልደክምም። ሆኖም ግን አንዱንና አሳፋሪ የሆነውንና ወያኔ ለምን ትጥቅ ማውረድ እንደሌለበት በሬድዋን የተሰጠውን ምክንያት ሳላነሳ ባልፍ እኔም በገዛ ሂሊናዬ ተወቃሽ እሆናለሁ።
ሬድዋን “ወያኔ ትጥቅ መፍታት አለበት የሚል ክርክር የሚያቀርቡ ሰዎች በሁሉም የሃገሪቱ ክፍል ከመንግስት መደበኛ ሃይሎች ውጭ መሳሪያ የታጠቁ በሙሉ መሳሪያቸውን ማስረከብ አለባቸው ብለው ሊከራከሩ ይገባል” በማለት ተከራክሯል።
ይህ ክርክሩ፣ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል ድረስ እንወርዳለን (ጌታቸው ረዳ ቃል በቃል የተናገረው) የሚል አላማ አንግቦ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ያበረውን፣ በኢትዮጵያ መከላከያና በንጹሃን የአማራና የአፋር ወገኖቻችን ላይ አሰቃቂ ግፍ የፈጸመውን፣ እነዚህን ክልሎች በማውደምና በመዝረፍ ባድማ ያደረገውን የወያኔ ታጣቂና እና ይህን ጸረ ሃገርና ጸረ ህዝብ የሆነን ቡድን በመታገል የአካባቢውን፣ የቤተሰቡን ደህነነትና የሃገሩን ህልውና ለማስከበር፣ ከተጠቃውና ከተዋረደው የመከላከያ ሰራዊታችን ጎን ለመቆም፣ ወዶ ሳይሆን በወያኔ ሰራዊት ወረራ የተነሳ መሳሪያ ያነሳውን፣ በአስር ሽዎች ወይም በመቶ ሽዎች በአማራና በአፋር ክልል፣ ወንድምና እህቶቹን በመስዋእተነት የገበረውን ሃገራዊ አርበኛ በእኩልነት ለንጽጽር ያቀረበ አሳፋሪ ክርክር ነበር። ይህ ጉዳይ ከፖለቲካ በላይ ተሻግሮ የሞራል ጉዳይ ስለሆነ ብቻ ነው እዚህ ላይ ለመጥቀስ የተገደድኩት። በሬድዋን ንግግር ውስጥ ከዚህ ነጥብ ውጭም ማንንም ሃገሩን የሚወድና ለኢትዮጵያ ህዝብ ሰላምና ደህንነት የሚመኝ ዜጋ ሊያሳስበው የሚገቡ በርካታ ጉዶች እንደታጨቁበት መናገር ያስፈልጋል።
ይህ እንዳለ ሆኖም የኢትዮጵያ መንግስት በአቶ ሬድዋን በኩል ለምን እንዲህ አይነት የቃላት ጂምናስቲክ መስራት እንዳስፈለገው ሁሉም የየራሱን ጥያቄ ማንሳት ይገባዋል። መንግስት በአደባባይ ወጥቶ በግልጽ የፕሪቶሪያ ስምምነት ዋና ቁም ነገሮች ሳይፈጸሙ ለምን ተጣድፎ ወደ እንደዚህ አይነት ውሳኔ እንደገባ፣ ለምንስ ህዝብን ጉድ ያሰኘ፣ ለወሰደው እርምጃ ማሳመኛ ይሆናሉ ብሎ ያሰባቸውን ውሃ የማይቋጥሩ ምክንያቶችን በመደርደር በቀቢጸ ተስፋ እንደባዘነ እውነቱን ለህዝብ እስካላቀረበ ድረስ ስማርት ስልክ ያለው ሁሉ በጥንቆላ ላይ የተመሰረተ የየራሱን ትነተናዎች እያቀረበ ከውዥንብር መጥራት ባልቻለው ፖለቲካችን ላይ ተጨማሪ ውዥንብር ቢጨመርበት ማንም የመንግስት አካል ሊያማርር አይችልም። እኔ ከዚህ ቀጥሎ ከጥንቆላና ከሴራ ነጻ ወደሆነው በትግራይ ከተመሰረተው የሽግግር መንግስት የአመሰራረት ሂደትና ውጤቱ ጋር ተያያዥነት ባላቸው፣ የሃገሪቱን የወደፊት እጣ በበጎም ሆነ በጥሩ ይወስናሉ ባልኳቸው መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ አተኩራለሁ።
ከዛ በፊት ግን በትግራይ ውስጥ የጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልል ርእሰ መስተዳደር ሆኖ መውጣት ያለቀለት ጉዳይ ተደርጎ መታየት እንደሌበት ማሳወቅ እፈልጋለሁ። በጌታቸውና ረዳና በጌታቸው አሰፋ ቡድኖች መሃል የተጀመረው የስልጣን ሽኩቻ እንዲህ በቀላሉ የሚቋጭ አይደለም። የጌታቸው አሰፋ ቡድን ብሩ፣ ዶላሩ፣ ወርቁና ሳፋየሩ በጁ ነው። ከባድ እና ቀላል መሳሪያ የታጠቀው የትግራይ ሰራዊት ውስጥ ከፍተኛ ድጋፍ አለው። በውጭ ሃገር ለትግሉ በሚል የተሰበሰባውን ዶላር ከዚህ ቡድን የወሰበት አካል የለም። የጌታቸው ረዳ ቡድን የፈልገውን ቢፏችር የትግራይ ዳያስፖራን ድጋፍ ማግኘት አይችልም። የጌታቸው አሰፋ ቡድን ይቃወሙኛል የሚላቸውን ወጣት ፖለቲከኞች ቀደም ብሎ መግደልና ማስገደል ጀመሮ ነበር። መረጃዎች የሚያሳዩት ይህን አይነቱ ድርጊት ተጠናክሮ የሚቀጥልበት ሁኔታ እንደሚኖር ነው። የሽብር ስራውን ከትግራይ ውጭ ለማካሄድ አሁንም ስራ መስራቱን አላቆምም።
ባለፈው እሁድ 09 07 2015 አለም ገብረዋህድ፣ ሞንጀሪኖ፣ ጌታቸው አሰፋ፣ የቀድሞ የአዲስ አበባ ፖሊስ አዛዥ የነበረው ይህደጎ ሰዩምና ሌሎች የቀድሞ ታጋዮችና ካድሬዎች በጋራ በመሰብሰብ፤
1ኛ እነጌታቸውን የመረጡ የህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ ኣባላት ከድርጅት ኣባልነታቸው እንዲወገዱ ኣሰቸካይ ድርጅታዊ ጉባኤ መጠራት ኣለበት፣
2ኛ የጌታቸው ቡድን በህዝቡ ይሁን በወታደሩ ውስጥ ተቀባይነት እንዳይኖረው የተለያዩ ሰራዎች መስራት አለብን በሚሉ አጀንዳዎች ላይ ውይይት አድርገው እቅድ አውጥተው ተለያይተዋል። አንባቢን ላለማድከም ብለን ነው እንጂ የተወያዩባቸው አጀንዳዎች ብዙ ናቸው።
- እንዴት የትግራይ ህዝብ መሸነፍ ከተቀረው ኢትዮጵያ ህዝብ መከራ መራዘም ጋር ይገናኛል፣
በዚህ ርእስ ስር የማቀርባቸውን ሃሳቦች በሚገባ ለመረዳት የሚፈልግ ማንኛውም አንባቢ፣ ህዳር 2011 ቀን “በሃገር ህልውና እና በዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ላይ ያሰፈሰፉ አደጋዎችና መውጫ መንገዶቹ” በሚል ርእስ የጻፍኩትንና ለመጀመሪያ ጊዜ በእነዚህሊንኮች https://m.facebook.com/story.php?
ለሁለት ከፍዬ ፖስት ያደርግሁትን ጽሁፍ እንዲያነብ እጋብዛለሁ።
ይህን ከተጻፈ አምስት አመት ሊሞላው ትንሽ ወራት የቀረው ሰነድ በርካታ መሰረታዊ ጉዳዮችን የሚመለከት በመሆኑ መርዘሙ የግድ ነበር። ይህን ጽሁፍ ህዝብ እንዲያነበው በማድረግ ከዚህ ቀደም እንደገለጽኩት አንድ ሰው የእይታ ግርዶሽ የሚፈጥሩበት ምክንያቶች እስከሌሉ ድረስ ሃገራችን ወዴት ልታመራ እንደምትችል መተንበዩ እንዴት ቀላል እንደሆነ መረጃ የሚሰጥ በመሆኑ ይፋ አድርጌዋለሁ። በመሆኑም የሃገራቸው ጉዳይ ከምር የሚያስጨንቃቸውና የማንበብ ብቃትና ትእግስቱ ያላቸው በሙሉ እንዲያነቡት ፌስ ቡክ ላይ ጭኜዋለሁ። በዚህ አጋጣሚ ሁሉም ሚድያዎች ይህን ጽሁፍና ሌሎችንም የኔን ጽሁፎች በሚፈልጉት መንገድ፣ በህትመት ሆነ በድምጽ ወይም በተለያዩ ፎርማቶች፣ ሁሉንም ይሁን ከፊሉን ቆራርጠው የማሰራጨት መብት ያላቸው መሆኑን፣ ይህን ለማድረግ የኔን ፈቃድ መጠየቅ እንደሌለባቸው ማሳወቅ እወዳለሁ።
ይህን ጽሁፍ ከመንግስት ባለስልጣናት መሃከል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀመሮ በርካታ የፌደራልና የክልል መንግስታት ባለስልጣናት እንዲደርሳቸው አድርጌያለሁ። ከተወሰኑትም ጋር ውይይት አድርጌበታለሁ። ለበርካታ የተፎካካሪ ፓርቲዎች መሪዎች አሰራጭቻለሁ። በወቅቱ የግንቦት 7 ንቅናቄ እንደ ድርጅት ያልከሰመበት ወቅት በመሆኑ ለድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ አቅርቤ ኢትዮጵያ በ2011 የምትገኝበትን ወቃታዊ ሁኔታ በሚገባ የሚገመግም ሰንድ ሆኖ በመገኘቱ ስራ አስፈጻሚው የራሱ የድርጅቱ የወቅታዊ ሁኔት የግምገማ ሰነድ አድርጎ ተቀብሎት ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ይህንን ሰንድ ለተለያዩ የሃገር ጉዳይ ለሚያሳስባቸው፣ ሁነኛ የሆነ የፖለቲካ ተሳትፎ ላላቸው ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና ቡድኖች እንዲደርሳቸው አድርጌያለሁ። ከሚድያዎችም ሰንዱ በኢሳት ጋዜጠኞች እጅ ቢገባ እነሱ ከርቀት የሚመለከቱት ሃገር የገጠመውን ተጨባጭ ችግሮች እንዲረዱ በማድረግ በሚድያ ስራቸው የተለየ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩባቸው የሚገቡ ነጥቦች ያመላክታቸዋል በሚል እምነት እንዲደርሳቸው አድርጌያለሁ። በተለያዩ አጋጣሚዎች ኤርምያስ ለገሰ አንድ አንዳርጋቸው የላከው ሰንድ በሚል የሚጠቅሰው ይህን ሰንድ ነው። አይቶት ይሁን አይሁን የማውቀው ነገር የለም። ለማንኛውም ይህን ጽሁፍ የሚያነብ ሰው ጽሁፉ የተጻፈበትን በዛን ጊዜ በኢትዮጵያ የነበረውን ሁኔታ ግምት ውስጥ አስገብቶ ሊያነበው ይገባል። ከዛ በኋላ የተቀያየሩ ብዙ ጉዳዮች አሉ። በተለይ ከኢህአዴግ ውስጥ ወጥቷል ብለን ስናስበው ከነበረው “የለውጥ ሃይል” ጋር የተሳሰስሩ፤
ይህ ረጅም ጽሁፍ፣ ህዝብ ከፍተኛ መስዋእትነት ከፍሎ ያመጣው ለውጥ የሚደናቀፈው ከማንም በላይ በኢህአዴግ አማካይነት ነው ብሎ ይሞግታል። ይህ መጨናገፍ ሁለት መሰረታው ከሆኑ የኢህአዴግ የባህርይ ችግሮች ጋር በተያያዘ መሆኑን ያትታል። የኢህአዴግ መሰረታዊ ባህርይ ጸረ ዴሞክራሲና ጸረ ኢትዮጵያ ነው ይላል። አያይዞም፤
“ኢህአዴግን አሁን ባለው ቁመናውና ድርጅታዊ እምነቱ አትርፎ የሃገር ህልውናን መጠበቅ፤ ኢህአዴግን አትርፎ ዴሞክራሲያዊ ስርአት መዘርጋት በአንድ ላይ ሊሄዱ የማይችሉ ተቃራኒ ነገሮች መሆናቸው እየታየ ነው። በለውጥ ሃይሉ ውስጥ ያለው አመለካካት ግን ፈረንጆች እንደሚሉት ኬኩን መብላትም ማስቀመጥም የመፈለግ ቅርቃር ውስጥ የተሰነቀረ ይመስላል።
ኢህአዴግን ከዘር ፖለቲካ ውጭ ማሰብ አይቻልም። የለውጡ ኃይል ለውጡን ለማካሄድ የሚያስችለውን መዋቅራዊ የሥልጣን መሰረቱን ያገኘውና የሚጠብቀው ባብዛኛው በዚሁ ድርጅት መዋቅር ውስጥ ሆኖ ነው። አሁንም ለሃገሪቱ ህልውና እና ዴሞክራሲያዊ ስርአት በሃገሪቱ መፈጠር አደጋ የሆነው የኢህአዴግ መሰረታዊ ባህሪ በዘር ፖለቲካ ላይ የተገነባ ድርጅትነቱ ነው። ይህ የድርጅቱ ባህሪ በሃገሪቱ መምጣት ለሚገባው ለውጥ እንቅፋት ብቻ ሳይሆን ለውጥ ፈላጊውንም የኢህአዴግ ሃይል ጭምር ሊበላ የሚችል ነው።” ይላል
ከላይ ለታየኝ ስጋት የሰጠሁት መልስ “የለወጥ ሃይሉ” በወቅቱ እከተለዋለሁ ይል ከነበረው የለውጥ አይነትና፣ ነበረው ብዬ የያሰብኩትን የማድረግ አቅም ውስኑነትና የገባበትን አጣብቂኝ ግምት ውስጥ ያስገባ ነበር። “የለውጥ ሃይሉ” የምናካሂደው አዝጋሚ ለወጥ እንጂ አብዮት አይደለም በማለቱ፣ ስርነቀል ለውጥ አደርጋለሁ ብሎ ቢነሳም አቅሙ የሌለው መሆኑን፣ እኔም “አብዮታዊ ለውጦች ሃገራዊ ቀውስ በማምጣት የቂምና የበቀልን አዙሪት በማስቀጠል ሃገራችንን ማለቂያ ለሌለው ቀውስ ያጋልጣሉ የሚል” እምነት ስለነበረኝ፣ የለወጥ ሃይሉ ግዙፍ ከሆነው የኢህአዴግ ሃገራዊ መዋቅር ጋር ተጋጭቶ የትም እንደማይደርስ በመረዳት፣ ከራሱ መዋቅር ጋር እንዲላተም ጥሪ አላቀረብኩም።
ኢህአዴግ እንደ ድርጅት “በለውጥ ሃይሉ” ላይ ሊፈጥር የሚችላቸውን ችግሮች መገዳደሪያ ሊሆነው የሚችል አስተዳደሩን፣ ሰላምና ጸጥታ አስከባሪውን፣ የፍትህ አካላትን በዛ አስቸጋሪ ወቅት የሚያግዝ ተጨማሪ ሃይል ያስፈልገዋል በሚል አሳማኝ ሰበብ ከፓርቲ ውግንና ውጭ ሁሉም ኗሪዎች በኗሪነታቸው የተደራጁበት ድርጅታዊ መዋቅር ከቀበሌ አንስቶ እስከ ሃገር አቀፍ ደረጃ እንዲዋቀር ሃሳብ አቅርቤ ነበር። የለውጥ ሃይሉ ከመቀሌ እስከ ሞያሌ ከጋምቤላ እስከ ሰመራ ድጋፉን ከሰጠው በሚሊዮኖች ከሚቆጠር ህዝብ ጋር በእንዲህ አይነቱ አደረጃጀት ከተሳሰረ፣ የኢህአዴግ የበሰበበሰ መዋቅር የሚፈጥርበትን ጫና መቋቋም የሚችል ህዝባዊ ጉልበት ይኖረዋል። ህዝብን በፈለገው ጊዜ በማስነሳት ኢህአዴግ በሃገሪቱ ያስፋፋውን ሌብነት፣ ሙስና፣ መጥፎ አስተዳደር፣ ህዝብን ከህዝብ የሚነጣጥልን ዘረኝነትና ጉልበተኛነት አስቀጥላለሁ ብሎ ቢያስችግር በዚህ ትይዪ አደረጃጃት አማካኝነት “የለውጥ ሃይሉ” ህዝብን ተጠቅሞ አደብ ሊያስገዛው ይችላል የሚል ስትራተጂ ነበር። ከዚህ እምነት በመነሳት ጽሁፉ
“የተጨባጭ የመፍትሄ እርምጃዎች የመሰረት ድንጋዮች የሚከተሉት ናቸው” በማለት ይዘረዝራል። ከያዝነው ጉዳይ ጋር ብቻ ተያያዥነት ያላቸውን ነጥቦች ልጠቀስ፤
- የኢህአዴግ ድርጅታዊ መዋቅር ይሁን በዚህ ድርጅት አባላት የተያዙት መንግስታዊ አስተዳደራዊ መዋቅሮችና አባላት ራሳቸው የችግሩ አካል እንጂ የመፍትሄው አካል እንደማይሆኑ መረዳት፣
- የለውጥ ሃይሉ፣ ሰላምና የተረጋጋ ህይወት መኖር በሚፈልገው ህይወቱ እንዲሻሻል በሚሻው፣ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ባለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ እጅግ ከፍተኛ ድጋፍ እንዳለው መረዳት ያስፈልጋል።
- የለውጥ ሃይሉና ለውጡን የሚደግፈው ህዝብ በቀጥታ የሚገናኙበት መዋቅራዊ ሰንሰለት በፍጥነት መፍጠር ለውጡን ከአደጋ መጠበቂያ ብቸኛ መሳሪያ ህዝብ ብቻ መሆኑን መገንዘብ ያሻል። ህዝቡ እንጂ የኢህአዴግ የድርጅት መዋቅር የለውጥ አስፈጻሚው ዋንኛ ኤጀንት አለመሆኑን መቀበል ያስፈልጋል። ህዝቡ የለውጡ ኤጀንት መሆን የሚችልበት ሁኔታ ሲፈጠር ብቻ እንደሆነ ለውጡ መቀጠል፣ የለውጥ ሃይሎቹም ከአደጋ መትረፍ የሚችሉት መሆኑን ማመን ይጠያቃል፣
በትግራይ ጉዳይ ላይ ትኩረት ያደረግሁት ከዚህ ጽሁፍ ማእቀፍ በመነሳት ነው። የትግራይ ህዝብ ከራሳቸው ስልጣን እና በዚህ ስልጣን አማካይነት ከሚገኝ የዘረፋ እድል ውጭ ምንም ቅንጣት ታክል ከህዝቡ ደህንነትና ጥቅም ጋር ግንኙነት በሌላቸው ጥቂት የነቀዙ ግለሰቦች አማካይነት ከረጅም ዘመናት ጀምሮና አሁንም በቅርቡ የከፈለው መስዋእትነት ግዙፍ ነው።
ይህንንም ግዙፍ መከራ ተቀብሎም ቢሆንም የትግራይ ህዝብ ባሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ ለውጡ በመጣበት ወቅት ያላገኘውን፣ በዘረፋ እና ባፈና የተካኑ የኢህአዴግን ሹማምንትን ከጫናቃው ላይ አሽቀንጥሮ በመጣል ራሱን ነጻ የማውጣት፣ ሁለንተናዊ ደህንነቱን በገዛ እጁ የሚያስገባበት እድል ተፈጥሮታል የሚል እምነት ይዤ ነበር። ይህ ይሆናል ብዬ ያሰብኩት ጊዚያዊ የሽግግር መንግስቱን የማቆም ስልጣን ከነቀዙ የፖለቲካ ድርጅቶች እጅ ወጥቶ በቀጥታ በህዝብ እጅ ይገባል ከሚል ጽኑ እምነት በመነሳት ነበር። ይህ እምነት መያዝ የቻልኩት ዝም ብዬ በምኞት ብቻ ሳይሆን የፌደራል መንግስቱ ፍላጎትም የሽግግሩን ሂደት ህዝብ በዋንኛነት እንዲቆጣጠረው የመፈለግ አዝማሚያ እንዳለው በመገንዝቤ ነበር። አሁን እንደተረዳሁት ያ አዝማሚያ የማስመሰል አዝማሚያ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
የፕሪቶሪያው ስምምነትም በአንድ በኩል የኢትዮጵያን የብሄራዊ ደህንነት አደጋ የሚቀንሱ ነጥቦች ያካተተ ብቻ ሳይሆን ሳይታሰብ ለትግራይ ህዝብ በታሪኩ አግኝቶት የማያውቀውን ራሱን በስሙ ከሚነግዱ ዘራፊዎችና ጨቋኞች ነጻ ማውጣት የሚችልበት እድል ይዞለት መጥቶ ነበር። ለትግራይ ህዝብ በረከት ለኢትዮጵያ ህዝብም ቱሩፋት ይሆናሉ ያልኳቸው የሰላም ስምምነቱ ነጥቦችን ትርጉማቸው ይህን ይመስላል የሚል እሳቤ ነበረኝ።
1) ህወሃት በስምምነቱ መሰረት ከባድ እና ቀላል መሳሪያዎቹን እንዲያስረከብ በማለቱ ጥቂት ግለሰቦች የትግራይን ህዝብ ለዘመናት የሚያስፈራሩበትን ወታደራዊ አቅም ማምከን የሚችል መሆኑ፣
2) የሽግግር መንግስቱን የመመስረት ሂደት የማስጀመርና የመቆጣጠር ስልጣን ለፌደራል መንግስቱ በመሰጠቱ፣ መንግስት ይህን ስልጣን ተጠቅሞ የዚህን የሽግግር መንግስት ምስረታ ሂደት በትግራይ ህዝብ እንጂ በተደራጁ የፖለቲካ አካላት እጅ እንዳይወድቅ በማድረግ ወያኔ የትግራይን ህዝብ ሁለንተናዊ ህይወት ተቆጣጥሮ የኖረበትን መንግስታዊ፣ አስተዳደራዊና ድርጅታዊ ስልጣኑን የሚያጣበትን ሁኔታ መፍጠር የሚችል መሆኑ፣ ይህን የመንግስት ጥረት የትግራይ ህዝብ እና ከአባራኩ የወጡ በወያኔ ውስጥና ውጭ ያሉ ወጣት የተማሩ ልጆቹ ከልባቸው የሚፈልጉትና የሚደግፉት መሆኑ፣ ይህ ፍላጎት በወያኔ ውስጥ ሲካሄድ ከነበረው የውስጥ ትግል አንስቶ ህዝቡ ወያኔን በቃኝ ማለቱን የሚያመላክቱ ማሳያዎች እየተበራከቱ መምጣታቸው፤ በራሱ በወያኔ ውስጥ ህዝብን የዘረፉና ለከፍተኛ ጥፋት የዳረጉ የቀድሞ የወያኔ ቱባ ባላስልጣናትን ለማስወገድ የመረረ ትግል በድርጅቱ ውስጥ መካሄድ የጀመረ መሆኑ፣
3) የህዝብን ሰላምና መረጋጋት የማረጋገጥ የህግ የበላይነትን ማስከበር ስራ ህዝብ የመረጣችው አስተዳዳሪዎች በሚያዙት ህዝብ በመረጣቸው ታጣቂዎችና የታጣቂዎች መሪዎች የሚሰራ መሆኑ፣ ታጣቂዎች ከህዝብ ቁጥጥር ውጭ መውጣት የማይችሉበት የተጠያቂነት ስርአት በስራ ላይ ማዋል የሚቻልበት እድል መገኘቱ፤
4) ህዝብ ከራሱና ከቀረው ከኢትዮጵያ ህዝብ፣ ጥቂት የወያኔ ባለስልጣናት ዘርፈው ትግራይ ውስጥ በየዋሻውና በየሰው ቤት ያከማቹትን ጥሬ ብር፣ ዶላር፣ ወርቅና ሳፋየር ለህዝብ ጥቅም እንዲውል የማድረግ፣ እንዲሁም ኤፈርት የሚባላውን በትግራይ ህዝብ ስም ተቋቁሞ በሂደት የጥቂት ሌቦች የግል ሃብት ወደመሆን የተሸጋገረውን ድርጅት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የትግራይ ህዝብ ሃብት እንዲሆን ማድርግ የሚችልበት ውሳኔ መወሰን የሚችልበትን፣ የኢትዮጵያን ህዝብ በመዝረፍ በውጭ ሃገራት ባንኮች ገንዘብ ያከማቹትን፣ የሁሉንም ሌቦች ገንዘብ ማስመለስ ባይቻል፣ ትግራይ ውስጥ በአካል የሚገኙ ከፍተኛ የዶላር ክምችት በውጭ ሃገር እንዳላቸው የሚታወቁትን የወያኔ መሪዎች አስገድዶ ገንዝቡን ወደ ኢትዮጵያ የሚመልሱበትን ሁኔታ መፍጠር የሚያስችል እድል ማገኘቱ፣
5) ውሎ አድሮም በሽግግር ሂደቱ፣ የትግራይ ህዝብ የተመቻቸ ሁኔታ ላይ ደርሻለሁ በሚልበት ወቅት የፖለቲካ ድርጅቶች ህዝብን በጉልበትን እና በኢኮኖሚ ተጽእኖ ሳያስፈራሩ፣ በእኩልነት በፍትሃዊነት የህዝቡን ነጻነትና መብት አክብረው የምረጡኝ ዘመቻ ማድረግ የሚችሉበት፣ በትግራይ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በነጻና ገለልተኛ አካል አስተናባሪነት ምርጫ ማድረግ የሚቻልበት የፖለቲካ ድባባ መፍጠር የሚችልበት እድል መገኘቱ፣
ከዚህ በላይ የጠቀስኳቸው፣ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት እውን ሊያደርጋቸው ይችሉ የነበሩ እድሎች እውን ባለመሆናቸው የትግራይ ህዝብ ለስልጣን እና ለጥቅማቸው ሲሉ በመቶ ሺዎች እንዲያልቅ ባደረጉት፣ በዘረፋ ለተካኑና፣ ነጻነቱን እና መብቱን ረግጠው አፍነው ለዘመናት ሲረግጡት ለነበሩት አካላት እንደገና በገጸ በረከትነት ቀርቧል። የዚህ ውሳኔ ውጤት የኢትዮጵያን ህዝብ መከራ የሚያራዝም ይሆናል። ለምን?
1) በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ወያኔ የከባድና የቀላል መሳሪያዎች ሙሉ ትጥቁን አውረዶ የትግራይ ህዝብ ብቻ በየመኖሪያ ክልሉ በመረጣቸው ሰላም አስከባሪዎች አማካይነት የሰላምና የህግ ማስከበር ስራ የሚሰራበት ሁኔታ ተፈጥሮ ቢሆን፣ ይህ ሁኔታ የማእከላዊ መንግስትን መውጋት የሚያስችል ቁመና ተላብሶ፣ የሁለት አመት ውጊያ ማካሄድ የቻለው የክልሉ ልዩ ሃይል ያበቃለት ይሆን ነበር። ይህ ሂደት በቀላሉ በሌሎች ክልሎች ውስጥ የተደራጁትን፣ እንደ ትግራይ ልዩ ሃይል ማእከላዊ መንግስትን ለመውጋት የሚያስችል ቁመና የተላበሱትን ወይም ክልሎች እርስ በርስ ለመዋጋት የሚያስችል አቅም እንዲኖራቸው ያደረገውን፣ የኢትዮጵያ የህልውና ዋናው አደጋ የሆኑትን ልዩ ሃይሎች እድሜ የሚያሳጥር ይሆን ነበር። ትግራይ ልዩ ሃይል ሳይኖረው ሌሎች ክልሎች ልዩ ሃይል ይዘው መቀጠል የሚችሉበት የተቃርኖ አሰራር ሊኖር ሰለማይችል የግድ የሌሎችን ክልሎች ልዩ ሃይሎች ወደማፍረስና ከፌደራል ሰራዊቱና ፖሊሱ ውጭ ሌሎች ክልሎች የነፍስ ወከፍ መሳሪያ ብቻ በታጠቁ የሰላም አስከባሪዎች የአካባቢያቸውን ሰላምን ህግ የሚያስከብሩበት ሁኔታ ይፈጠር ነበር። አሁን በሌሎች ክልሎች የተደራጁ ልዩ ሃይሎች ማፍረሰ ቀርቶ በትግራይ ልዩ ሃይል መልሶ የሚደራጅበት ሁኔታ እውን ሆኗል።
2) ከትግራይ ውጭ፣ የትግራይን ህዝብና የኢትዮጵያን ህዝብ የዘረፉ፣ እንደ ትግራይ ዘራፊዎች ዶ/ር አብይ “የቀን ጅብ” የሚል ስም ያልሰጣቸውን እኛም “ከይቅርታ ጋር” መንግስትን ተከትለን የረሳናቸውን አሁን በመንግስት ወስጥና ውጭ እንደልባቸው ህዝብን የሚዘርፉ “የቀን ጅቦችን” የተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ስልጣናቸውን መከታ አድረገው የዘረፉትን ሃብት ማስመለስ፣ ከዛም አልፎ ከወያኔ ዘመን በላይ እንደካንሰር የተስፋፋውን፣ እንደ ክልሎች ልዩ ሃይል የሃገር ህልወና ማናጋት ደረጃ የደረሰውን ሙስና ማስቆም የሚችልበትን እድል የነፈገው ሆኗል። የትግራይ ህዝብ ስልጣን፣ መሳሪያን ብቻ ሳይሆን ሃብትና ንብረቱን ከቀን ጅቦች መልሶ መረከብ ባላመቻሉ፣ በኢትዮጵያ ምድር ህዝብ በሃገር አቀፍ ደረጃ ግንባር በፈጠሩ “የቀን ጅቦች” አስከአጥንቱ የሚጋጥበትን ሁኔታ ተጠናክሮ የሚቀጥልበት ሁኔታ ተመቻችቷል።
3) የትግራይ ህዝብ የአካባቢውን የፖለቲካ አየር ከጉልበተኞችና ከዘራፊዎች ነጻ በማድረግ ሁሉም የፖለቲካ አመለካከቶች በነጻነት ማድመጥ፣ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች በነጻነትና በእኩልነት የሚንቀሳቅሱበት ሁኔታ መፍጠር ችሎ ቢሆን፣ የዚህ ትርጉሙ የተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብም በተራ ቁጥር 1 እና 2 የጠቀስኳቸውን ሁኔታዎች በመላው ሃገሪቱ እንዲፈጠሩ ባማድረግ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በነጻነት ያሻውን መሪዎች መምረጥ የሚችልበት እድል ያገኝ ነበር።
4) የታጠቁ የክልሎች ሃይሎች የሃገር ህልውናን ፈተና ውስጥ ከመጣል አልፈው፣ ባላፈው ሁለት አመት እንዳየነው የቀጠናም ስጋት መሆን እንደሚችሉ ነው። ወያኔ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ከባድና ቀላል መሳሪያውን ባለማውረድ የቀጠናው የደህንነት ስጋት ሆኖ እንዲቀጥል የተፈቀደለት ይመስላል። ቀደም ባለው ሰንድ እዳስቀመጥኩት ወያኔዎች ዛሬም ጠላታችን ነው የሚሉትን የኤርትራ መንግስት ለመውጋትና ለመጣል ፍላጎቱ እንዳላቸው በየስብሰባቸው የሚያነሱት ጉዳይ ነው። ይህ ፍላጎታቸው ደግሞ በቀይ ባህር ስትራተጂካዊ አካባቢ ላይ የበላይነት ለመቀዳጀት ፍላጎት ያለው የአሜሪካ መንግስት ፍላጎት ነው። ወያኔዎች ኤርትራን የሚወጉት በራሳቸው አቅም ብቻ ሳይሆን የፕሪቶሪያን የሰላም ስምምነት ለማስከበር ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ሆነው እንደሚያደርጉት በየስብሰባቸው እንደሚናገሩት ባላፈው ጽሁፌ አቅርቤ ነበር። አዲሱ የትግራይ ክልል ርእሰ መስተዳደር ጌታቸው ረዳ ገና ከመድረሱ በሰላም ስምምነቱ መሰረት የኤርትራን እና የአማራን ሃይሎች አደብ ማስገዛት የፌደራል መንግስቱ ሃላፊነት ነው እያለ እየነገረን ነው። ወያኔ የሰላም ስምምነቱ ደጋፊ ነኝ በማለት ከፌደራል መንግስቱ ጎን ቆሞ ምን ለማድረግ እያሰበ እንደሆነ ፍንጭ እየሰጠን ነው።
በአንድ ሳምንት ውስጥ ከትግራይ ተያይዞ የተከናወነው ነገር በሙሉ የኢትዮጵያን ህዝብ ከሰላም ይልቅ ወደ ቀውስ፣ ከነጻነት ይልቅ ወደ ባርነት፣ ከብልጽግና ይልቅ ወደ ድህነት፣ ካለመዘረፍ ወደ ከፋ መዘረፍ የሚውስድ ነው እንድል ያደረጉኝ ምክንያቶች ከላይ =ያቀረብኳቸው ናቸው። በዚህ ተቃራኒ ልንሄድ ነው ብለው የሚያስቡ ምክንያታቸውን ያቅርቡ።
http://amharic-zehabesha.com/archives/180658