March 16, 2023
26 mins read

ከታሪክ ማህደር – ጋዜጠኛ ብዙ ወንድማገኘሁ (ከማጀት እስከ አደባባይ)

በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ ጉልህ አሻራ ካኖሩት መካከል አንዷ ናት፡፡ በተለይ ከ 1962 -1983 ለ 21 አመት በሚድያው ዘርፍ ናኝታበታለች፡፡ መነን መጽሄት ላይ ሰርታለች፡፡ አዲስ ዘመንም ቤቷ ነበር፡፡ ብዙ ወንድም አገኘሁ አለሙ ለአመታት መኖርያዋን በካናዳ ያደረገች ሲሆን ከ 3 ወር በፊት ሀገር ቤት መጥታለች፡፡ ወዳጃችን ሮማን ተገኝ ስለብዙ መጻፍ እንዳለበት ነግራን ብዙን ለማግኘት ጉዞ ወደካዛንቺስ ሆነ፡፡ እናም ብዙ አወጋን፡፡ አማረ ደገፋውና እዝራ እጅጉ ብዙን እንደሚከተለው ያስነብባሉ፡፡

336669780 737091404492193 1375882874806800233 n 1 1

➢ ዘጠኝ ጊዜ ዳዊትን ደግማለች

በ 1948 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ ሰንጋ ተራ በተባለ ሰፈር ባለ የቀኝ አዝማች ወንድምአገኘሁ ዓለሙ እና የወ/ሮ አረጋሽ ደስታ ቤት 3ኛ ልጅ ሁና ተከሰተች፦ ብዙ ወንድምአገኘሁ ዓለሙ። ወግ አጥባቂ የነበሩት አባቷ ለጸሎት ያህል ዳዊትን ከደገምሽ በቂ ነው ብለው ለዘመናዊ ትምህርት ሳይሆን ለትዳር ሊያጯት ሲሰናዱ ታዝባቸዋለች። ትዝብቷን በልጅ አእምሮዋ ቀምራ ከዳዊት በኋላ የሚጠብቃትን ትዳር ፍራቻ ዘጠኝ ጊዜ ዳዊትን ደጋግማ ተምራለች።

ከትምህርት ማዕቀብ የተጣለባት ብዙ ወንድማገኘሁ በሰፈሯ የሚያልፉ ተማሪዎችን ማየት እያንገበገባት ወድቀው የምታገኛቸውን ጋዜጦችና ወንድሟ የሚያቀብላትን መጽሐፍት ማንበብ ተያያዘች። በዚሁ መጽሐፍ አቀባይ ወንድሟ ትግል አባቷ ተሸንፈው በማየት ብቻ ስትቀናባቸው የነበሩ ተማሪዎችን ተቀላቅላ በየነ መርዕድ ትምህርት ቤት ተገኘች።

➢ ጽሁፏ እንዲወጣ ብር ይዛ ሄደች

እስከ 8ኛ ክፍል በዚያ ከቆየች በኋላ አባሀና ጅማና (በኋላ ጆንኦፍ ኬኔዲ የተባለው) ት/ቤት ለ 9ኛ ክፍል ትምህርቷ አቀናች። በዚያ በሳምንት 1 ቀን ከሰንደቅ ዓላማ ስነስርዓት ቀጥሎ “ሰዎች ምን ይሉናል?” በሚል ርዕስ ተማሪዎች ፊት ዝግጅት በማቅረብ የጋዜጠኝነት ጉዞዋን ሀ ብላ ጀመረች። ቀጥላ የጋዜጠኝነት ፍቅሯ እየገፋት የራሷን ጽሑፍ አዘጋጅታ ወደ ‹‹ድምፅ›› ጋዜጣ አቀናች። የልጅነት የዋህ ልቧ ጋዜጠኛ ለመሆን ክፍያ ያስፈልገዋል ብሎ ነግሯት ከጽሑፏ ጋር ከወንድሟ ያስላከችውን ገንዘብ ይዛ ከአቶ ከበደ አኒሳ ፊት ቆመች። የወቅቱ የድምፅ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ከበደ አኒሳ የልጅነት የዋህ ልቧንና ይዛ የመጣችውን ጽሑፍ በአባታዊ ፍቅር ተቀበሏት። በማግስቱ ጽሑፏን ጋዜጣው ላይ አወጡላትና በራሳቸው ክፍያ በየዕለቱ የጋዜጣዋን አንድ ኮፒ ትምህርት ቤት ድረስ እንዲደርሳት አደረጉ።

በጽሑፏ በርትታ በበዓሉ ግርማ ጠያቂነት ለ”መነን” መጽሔትም መፃፍ ጀምረች። ጽሑፎቿ ጠንከር ያሉ ሀሳቦችን ስለሚያነሱ ብዙዎች ማን እንደሆነች ለማወቅ ጓጉተው እንደነበር ታስታውሳለች። 11ኛ ክፍል ስትሆን በድምፅ ጋዜጣ የሴቶች አምድ አዘጋጅ ሁና ከጽሑፍ አበርካችነት ወደ ቋሚ ተቀጣሪነት አደገች። ወዲያው ድምፅ ጋዜጣ ስትዘጋ ብዙ ወንድማገኘሁ በ 182 ብር ወደ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ተዛወረች። የአስራዎቹ እድሜዋን እንኳ ሳትጨርስ ለአራት ዓመታት አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ አገለገለች።

እዚያው አዲስ ዘመን እያለች ለፖሊስና እርምጃው ጋዜጣም ትፅፍ ነበር። ይህ የአፍላነት እድሜዋ ድፍረትን ሰጥቷት ብዙ ጽፋለች፤ ጉምቱዎቹ ጋር ትከሻ ለትከሻ ተገፋፍታለች። ገና በለጋነቷ የወደቁ ጋዜጦችን ስታነብ ደጋግማ እንደሱ በሆንኩ ያለችው ጳውሎስ ኞኞን “አዳር በንፋስ ስልክ ሲነጋ ላምበረት” ብሎ በመፃፉ ሞግታ “አንድ ለሊት በመሸታ ቤት” ብላ ፅፋለች፤ በጽሑፏ በሽቀው ሊደበድቧት የመጡ ባለዱላዎችን በብርሃኑ ዘሪሁን ትከሻ ተከልላ አልፋለች፤ ለጋሽ ፀጋዬ ገብረመድህን ትችት አይኗን ሳትሰብር አይበገሬ መሆኗን አሳይታለች፡፡

336654601 765377591607159 5089974219363523903 n 1 1

➢ የመነኗ ብዙ

ብዙ ወንድምአገኘሁ በመነን መጽሄት ትሰራ በነበረበት ጊዜ ምናልባት 20 አመት ቢሞላት ነው፡፡ በጊዜው ማለትም በመጋቢት 1965 የዚህ መጽሄት ተጠባባቂ አዘጋጅ አዛርያ ኪሮስ ነበር፡፡ ስራ አስኪያጅ ደግሞ ስብሀት ገብረእግዚአብሄር ነበር፡፡ ያኔ ብዙ ወንድምአገኘሁ በመዝገብ ስሟ እና በብእር ስሟ በርካታ ጽሁፎችን ታበረከት ነበር፡፡ በጊዜው ብዙ ከጻፈችው ፊቸር ጽሁፍ ውስጥ ‹‹የከርታታዋ ኑሮ›› የሚለው ይገኝበታል፡፡ የሴተኛ አዳሪዎችን ህይወት የዳሰሰችበት ሲሆን ጽሁፉን እንዳየነው ቀለል ባለ መንገድ የተጻፈ እና ጠንካራ ማህበራዊ ጉዳይን በወጉ ያቀረበ ነው፡፡ ብዙ ጽሁፏን ስትጀምር ‹‹ከከርታታ ልጃገረዶች ጋር ለመተዋወቅ በጣም አስቸግሮኝ ነበር ስትል መጣጥፏን አንድ ብላ ጀመረች፡፡ ገና አንደኛ ደረጃ ሳለች የጋዜጠኝነት ፍቅር የጀማመራት ብዙ ወንድምአገኘሁ በመነን መጽሄት እድሉ ሲሰጣት ያን ውስጣዊ ፍቅር ትወጣ ነበር፡፡ ታዲያ የመነን አዘጋጆች በተለይ አቶ አዛርያ በልዩ ክህሎቷ ምንጊዜም ይደመሙ ነበር፡፡ በሌሎች ጋዜጣዎች ላይም ብእሯን አንስታ እንድትጽፍ ያበረታቷት ነበር፡፡

ብዙ ወንድምአገኘሁ ብእሯ የሰላ ነው፡፡ የምትጽፈው ሲነበብ የመሳብ ሀይል አለው፡፡ በ 5 ገጾች የቀረበው የከርታታዋ ኑሮ የተሰኘ ጽሁፍ አንባቢን ሰቅዞ የመያዝ ጉልበት አለው፡፡ ብዙ የከርታታዋ ኑሮ የተሰኘውን ጽሁፍ አንድ ባለችበት 2ኛ አንቀጽ ላይ ይህን ተጠቅማለት፡፡ በጨረፍታ እስቲ እናንብበው፡፡

‹‹…..በጣም ደስ ትይኛለሽ፡፡ በተለይ ደግሞ የማውቅሽ ይመስለኛል፡፡ እባክሽ እንተዋወቅ ትዝታሽ እባላለሁ›› አልኳት እውነተነኛ ስሜን ደብቄ፡፡ አዎ ሌላ ምንም ማግባቢያ ዘዴ አልነበረኝም፡፡አስቴርም ደስ ብሏት ተዋወቀቺኝ፡፡›› ብላ ትቀጥላለች ብዙ፡፡ የዛሬ 48 አመት በዚህ መልክ ብእር ከወረቀት አዋህዳ ወደ ጋዜጠኝነቱ እየዘለቀች የመጣችው ብዙ ትዝብቲቱ እና ሙያዬ ምስክር በተሰኙ የብእር ስሞች የበርካታ አንባቢያንን ጥም አርክታለች፡፡ የብዙን የብዕር አጣጣል ለማየት በመነን መጽሄት ላይ የወጣውን ጽሁፍ መጽሄቱን በምስል አንስተን ከዚህ ጽሁፍ ጋር አብረን አውጥተነዋል፡፡

ብዙ በመነን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ድምጽ ጋዜጣ ላይ የሴቶች አምድን በጥንቃቄ ታዘጋጅ ነበር፡፡ በ 1962 አ.ም ከእነ አቶ ከበደ አኒሳ ጋር ገና በአስራዎቹ የእድሜ ክልል ሳለች ሰርታለች፡፡ በተጨማሪም በኢትዮጵያ የሴት ጋዜጠኞች ታሪክ ውስጥ ሁለተኛዋ አንጋፋ ጋዜጠኛ ወ/ሮ እሌኒ ፈጠነ ጋር የመስራት እድል ገጥሟታል፡፡ ብዙ ከሰሞኑ እንዳጫወተችን ወይዘሮ እሌኑ ሙያቸውን የሚወዱ ጠንካራ ሴት ነበሩ፡፡ ከእርሳቸው ቆራጥ መሆንን ተምሬአለሁ ስትል ብዙ ምስክርነት ሰጥታለች፡፡

➢ ብዙ እና የ 1964ቱ አውቶግራፍ

ይህን መጣጥፍ ለማጠናከር ስንል የብዙን አውቶግራፍ ማየት ነበረብን፡፡ ሰውን ለመረዳት ፣የዘመኑን እውነተኛ ስሜት በወጉ እና በልኩ ለመገንዘብ ዳየሪ እና አውቶግራፍ መመልከት ልዩ ዋጋ እንደሚኖረው ይታመናል፡፡ የዛሬ 50 አመት በሰኔ እና በመስከረም ወሮች ብዙ አውቶግራፍ ላይ የሰፈሩ ቁምነገሮች ብዙ የመናገር አቅም ነበራቸው፡፡ ብዙ አውቶግራፍ ላይ ያስፈረቻቸው ሰዎችም ስለ ብዙ ያሰፈሩት ሀሳብ ከ 50 አመት በኋላም ሲነበብ ልዩ ጣእም ነበረው፡፡ ሀሳባቸውን ያሰፈሩት ደግሞ የዛን ጊዜዎቹ ዝነኞች ዻውሎስ ኞኞ ፤ ጥላሁን ገሰሰ ፤ እና አበበ ቢቂላ ይጠቀሳሉ፡፡ ብዙ የዛሬ 50 አመት እነዚህ ስመ-ጥሮች ስለ እርሷ በብእራቸው የጻፉትን ስታስብ እውነትም በወርቃማው ዘመን እንኳን አሳለፍኩ ያሰኛታል፡፡ የእነዚያን ብርቅ ሰዎች የብእር አጣጣል እያየች ደግሞ ትደመም ነበር፡፡

➢ የዻውሎስ ኞኞ አጣጣል

ብዙን እንደማውቃት ጎበዝ ልጅ ነች፡፡ በተለይ በጋዜጣ ስራ በሌላ ሀገር ቢሆን በጣም ተፈላጊ ጋዜጠኛ ነበረች፡፡ ደፋር በመሆኗ ማስታወቂያ ለመሰብሰብ የተደበቀ ወሬ ለማግኘት በቂ ችሎታ የሚኖራት ነበረች፡፡ አሁንም ቢሆን የሚያደፋፍራትና እንድትሰራ የሚገፋፋት ብታገኝ ያገራችንን ጋዜጠኞች ሁሉ ማስከንዳት የምትችል ናት፡፡ ለምን እንዲህ እንደማያደርጓት አይገባኝም፡፡ አሁንም በምታደርገው መፍጨርጨር አደንቃታለሁ፡፡ ከእርሷ እኩል የማይሰሩ ግን ስራዋን ሲያንቋሽሹ አዝናለሁ፡፡ ከወንዶቹ የተሻለች ጥሩ ጋዜጠኛ ነች፡፡

➢ መስከረም 22 1965 ዻውሎስ ኞኞ

ሌሎቹም ባልደረቦቿ ወርቁ ሳህሌ፣ አቢይ መኩርያ እና ሀዲስ እንግዳ ለብዙ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡ ወርቅ ሳህሌ ብዙ አውቶግራፍ ላይ ሰኔ 16 1964 ይህን መጻፉ አልቀረም፡፡

የወርቁ ሳህሌ አጣጣል

ወ/ት ብዙ፣ በጋዜጣ አለም ተሰማርተሸ ባሳየሽው አገልግሎት ህብረተሰቡ ብዙ ሊማር ችሏል፡፡ ጥረት፤ ግረት ፤ ትጋት ገንዘቦችሽ እንደሆኑ በግልጽ እረዳለሁ፡፡ ባንቺ እድሜ ከእድሜሽ የበለጠ የጋዜጣ ስራ አበርክተሻል፡፡የማያቋርጥ ጥረት ስላለሽ አሁንም ከዚህ የበለጠ እንደምትሰሪ አምናለሁ፡፡ በርቺ ወርቁ ሳህሌ

ብዙ እነዚህን መሰል አስተያየቶች ስታስተናግድ በጋዜጠኝነት ሙያ ገና 3 አመት አልሰራችም ነበር፡፡ ጉምቱዎቹ የጽሁፍ ሰዎች ታሳየው የነበረውን ጥረትና ውስጣዊ ክህሎቷን ስለተረዱ ወደፊት በሙያው በትጋት እንድትቀጥል የሚያደርጋትን አስተያየት ይለግሷት ነበር፡፡ ዛሬ ብዙ እነዚህን አስተያየቶች ስታነብ በሙያው ሞራል አግኝቶ ለማለፍ ትልቅ እገዛ አድርጎላታል፡፡ ብዙ እነዚህ አንጋፋ ሰዎች የዘመኑ ወርቆች ናቸው ስትል ለእነርሱ ያላትን አክብሮት ትገልጻለች፡፡ በነገራችን ላይ ስድስቱ ሰዎች ብዙ አውቶግራፍ ላይ ከእነእጅ ጽሁፋቸው የጻፉትን ሀሳብ ከዚህ ጽሁፍ ጋር ፎቶ አንስተን ያወጣነው ስለሆነ የዝነኞቻችን ጽሁፍ እንደምን እንደሆነ መመልከት ይችላሉ፡፡

➢ ብዙ ወንድም አገኘሁ በኢቲቪ

ብዙ በ 1968 ዓ.ም ወደ ቴሌቪዥን ተሻገረችና የረዘመውን የጋዜጠኝነት ህይወቷን በዚያው አሳለፈች። “ከማጀት እስከ አደባባይ” በሚል ርዕስ በበርካታ የሀገራችን ክፍሎች እየዞረች ብዙ ዝግጅቶችን ሰራች። ወደ አርሲ ዘልቃ በርካታ ሚስቶች ስለሚያገቡት አባወራ የሰራችው ፕሮግራም ከተማን አስትቶ ወደ ክፍለ ሀገር ልቧን እንዳሸፈተው ትናገራለች። ስለሱርማ ብሔር የሰራችው ዝግጅትን ዛሬም ድረስ ታስታውሰዋለች፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በቦታው ስትደርስ ለአካባቢው ባህል ተገዝታ ልብሶቿን ጥላ አብራቸው ጨፍራለች።

ከትራንስፖርትና ከካሜራ እጥረት ጋር እየታገለች ኢትዮጵያን አካላለች፤ እግሯ በርካታ የሀገራችንን ክፍሎች መርገጡን ለማስረዳት “አፄ ምኒልክ በሁለት ግዛቶች ብቻ ነው የሚበልጡኝ” ትላለች። ከአፍላ እድሜዋ አራት አስርታትን ብትርቅም ዛሬም በወኔ “ባህሪዬ ነው መሰል ማንንም አልፈራም” ትላለች። ይሄ ድፍረቷ አይነኬ የተባሉ ርዕሶችን እያነሳች ከሚኒስተሮች ጋር ጭምር አጋጭቷታል። ለዚህ ማሳያ ሲስተር እማዋይሽ ገሪማን ቃለ-መጠይቅ አድርጋ በሰራችው ስራ የወቅቱ የጤና ሚኒስቴርን አበሳጭቶ በወታደር ተከባ እንደነበር ታስታውሳለች።

ከዚህ ሁሉ ትጋትና ድፍረት ጋር በቴሌቭዥን መስኮት በርካታ ዝግጅቶችን ለተመልካቾቿ አድርሳ ኢትዮጵያን ካስተዋወቀች በኋላ በ1983 አ.ም መንግስት ሲለወጥ እንቅፋት ገጠማት። ደህንነት ነሽ ተብላ ታገደች፤ ጉዳዩዋ ሲጣራ ከሳሾቿ ማስረጃ ማቅረብ ቢያቅታቸውም፤ ደህንነት አለመሆኗን ለማስረዳት ብትጥርም ያለፍርድ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከምትወደው ሙያዋ ተገለለች። በኋላ ላይ እንድትመለስ ብትጠየቅም አሻፈረኝ አለች።

ጥቂት ጊዜአትን ኢትዮጵያ ከቆየች በኋላ ወደ እስራኤል በኋላም ወደ ካናዳ አቅንታ በስደት ኑሮዋን ተያያዘች።

ከነጳውሎስ ኞኞ ጋር ትከሳ ለትከሻ የተካከለች፤ በድፍረትና በአፍላነት ሀገሯን ስታገለግል የኖረች፤ ከማጀት እስከ ከተማ እየተጓዘች በቴሌቭዥን መስኮት ሀገሯን ለባለሀገሩ ያስተዋወቀች፤ ጋዜጠኛ ልሁን ስትል ሴትነቷን አጣቅሰው በዝናብ መስራት እንደሚከብዳት ቢነግሯት ‘ጋዜጠኛ እንኳን በዝናብ በጦርነትም ይዘግባል’ ብላ የተከራከረች፤ ለጋዜጠኝነት ራሷን የሰጠች ብዙ ወንድማገኘሁ ዛሬ ለእርሷ ባልተገባ ህይወት ውስጥ ትገኛለች። ጋዜጠኝነት ታላቅ ሙያ ቢሆንም አንዳንዴ ግን በስጨት ያደርጋታል፡፡ የቀደሟትን እያነሳች፣ አሟሟታቸውን እያወሳች “ይህች ሀገር እንደሸንኮራ መጣ ትጥላለች እንጂ ባለውለታዎቿን አታከብርም” ብትልም በእርሷም የደረሰው ተመሳሳይ ነበር። እንዲህ ብትሆንም ዛሬም ሀገሯን ትወዳለች፤ አንገቷ ላይ የኢትዮጵያ ካርታ ያለበትን ሀብል አንጠልጥላ “ጣቴን ብትቆርጠው ደሜ ኢትዮጵያ ይላል” ትላለች።

የአንድ ወቅት አለቃዋ የነበሩት ተክሉ ታቦር ስለ ብዙ ሲናገሩ “ታታሪ ነበረች” ይላሉ። ወደ ሰሜን ሸዋ ተጉዛ ሰርታው የነበረን ፕሮግራም አንስተው ዛሬም ድረስ እንደሚገርማቸውና የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጭምር ቢሯቸው ድረስ አስጠርተው እንዳመሰገኗት ያስታውሳሉ። የካሜራ ባለሙያና የስራ ባልደረባዋ የነበሩት አቶ ኤልያስ ብሩም ስለብዙ ሲመሰክሩ “በሄደችበት ቦታ ሁሉ በስራዋ አንቱ ትባል ነበር፤ እንደእርሷ ያለች ሴት በቴሌቭዥን አላየሁም” ይላሉ። ራሷም እንዳለችው ኢትዮጵያ እንደሸንኮራ መጣ ከጣለቻቸው ውስጥ መሆኗ ቢያሳዝነንም ተወዳጅ ሚዲያ ያለችበትን አፈላልጎ ታሪኳን በዚህ መልኩ ሲሰንድ ይህች ባለውለታ እውቅና እንዲሰጣት ይፈልጋል፡፡ እውቅና ሲባል ከ 30 አመት በላይ በሚድያ አለም ዘልቃለችና እናመሰግንሻለን መባል አለባት፡፡ ሌሎች እንዲያስታውሷት ደግሞ ይህን አጭር የሕይወት ታሪክ አውጥተናል፡፡

336659425 895539034887994 3802904373191379076 n 1 1

መዝጊያ፣ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የመዝገበ-አዕምሮ የመማክርት ቡድን አባላት አቋምን የሚያንጸባርቅ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የጠፉ ልጆቿን መፈለጊያዋ ጊዜ አሁን እንደሆነ እናምናለን፡፡ መረዳዳት ፤ መጠያየቅ በህይወት ሳሉ ነው፡፡ ብዙ ወንድምአገኘሁ በተራራ በገደሉ በየጥሻው እየዞረች ስትታገል ለሙያው ታላቅ ከበሬታ ሰጥታ ነው፡፡ በበቅሎ እየተጓዘች ካሜራ ማን ይዛ መስክ ስትሄድ ለተከበሩ ተመልካቾች አንድ ነገር ይዤ መቅረብ አለብኝ በሚል እሳቤ ነው፡፡ ይህን ግቧንም አሳክታለች፡፡ ብዙ የሚያውቋት እንደሚናገሩት ለአለቃ ማጎብደድ የሚሉት ነገር ፍጹም አይገባትም፡፡ የተሰማትን ፊት ለፊት ትናገራለች-በዚህ አጋጣሚም ልትጋጭ ትችላለች፡፡ ብዙ ምንም ቢሆን ግን ለስራ ቅድሚያ ትሰጣለች፡፡ አብረዋት የሰሩ ሁሉ ልዩ ትጋቷን በሙሉ አንደበት ይመሰክራሉ፡፡ ብዙ ሰርታ ሰርታ ልክ 35ኛ አመቷን እንዳከበረች ኢህአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር አትፈለጊም ተብላ ተወረወረች፡፡ የ 5 አመት ልጇን ይዛ ይህ ውሳኔ መምጣቱ ለጊዜው አስደንጋጭ ቢሆንም ብዙ ግን መንፈሰ-ጠንካራ ለመሆን ጥርስ ነከሰች፡፡ ኢትዮጵያ ልጆቿን የማትይዘው ለምንድነው ብለን ብንጠይቅ ብዙ መልስ እናገኛለን፡፡ በ 16 አመት እድሜዋ መነን ላይ ድምጽ ላይ ብእሯን ያሟሸችው ከ 35 አመት እድሜዋ አንስቶ ግን ከወረቀትና ከብእር ጋር ተለያየች፡፡ ኑሮን ለማሸነፍ የሚደረገው ትግል ቅድሚያ ተሰጠው፡፡ የአንድ ወንድ ልጅ እናት የሆነችው ብዙ በካናዳ እንደማንኛውም ስደተኛ በብዙ የህይወት ውጣ ውረድ አልፋለች፡፡ የድሮ ትዝታዋ እንዳለ ነው፡፡ የቆዩ ወጎችን ታውቃለች፡፡ ከሙያው ብትርቅም ኢትዮጵያ ልቧ ውስጥ ተከትባለችና ጋዜጠኝነትም አብሯት ነው፡፡ ብዙ የመጀመሪያዋ የቱሪዝም ጋዜጠኛ ልትባል ይገባል፡፡ መሸለም መወደስ ይገባታል፡፡ መሰረታዊ ፍልጎቶቿ ሁሉ ተቀርፈው የሀገሯን አየር እየማገች ትኖር ዘንድ የብዙዎች ምኞት ነው፡፡ በአሁኑ ሰአት ሙሉ ለሙሉ በእናት ሀገሯ ላይ ለመኖር ጠቅልላ እንደመጣች አጫውታናለች፡፡ እኛም እንደ ተወዳጅ ሚድያ ብዙ ወንድም አገኘሁን ‹‹የዘመኑ ጀግና ሴት ጋዜጠኛ›› ስንል የክብር ስም ሰጥተናታል፡፡ ብዙን ለማመስገን የሚደረጉ መሰናዶዎችና በጎ ስራዎች ላይ አብረን ለመስራት በራችንን ክፍት አድርገናል፡፡ ኢትዮጵያ በሯን ለእነዚህ ካልከፈተች ለማን ልትከፍት ኖሯል? ብዙ እናከብርሻለን፡፡

#ታሪክን_ወደኋላ

Tewedaje media

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop