በኢትዮጵያ መቃብር ላይ አዲስ አገር ለመፍጠር ምለውና ተገዝተው ህብረትን የፈጠሩት ትህነጋዊያን እና ኦነጋዊያን መንበረ ሥልጣኑን ከተቆጣጠሩ እነሆ ሶስት አስርተ ዓመታት አልፏል ነገር ግን ኢትዮጵያ በድቡሽት ላይ የተሰራች ጎጆ ካለመሆኗ የተነሳ በቀላሉ እንደማትፈርስ በመገንዘባቸው ከመሰረቱ መንግሎ ለመጣል ቋጥኝ መፈልፈል ከጀመሩ እነሆ 30 ዓመት ቢሆናቸውም አመርቂ ውጤት አልተገኘም ።
በዘመናዊ መሳሪያ ዘምተው በጦር በጎራዴ ድባቅ የተመቱት የውጭ ጠላቶቻችን እሾህን በእሾህ እንዲሉ ከጉያችን በፈጠሩት የባንዳ ስብስቦች አማካኝነት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ህዝቡን በጎሣ ከፋፍሎ መበታተን ፤ ኢትዮጵያዊነትን እንደ ማንነቱ የሚቆጠረውን አማራ አከርካሪውን መስበር ፤ ለኢትዮጵያ መሰረት የሆነችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነትን በመንግሥት ጣልቃ ገብነት ከሲኖዶሱ ድንጋጌ በተቃረነ መልኩ ለማፍረስ እንቅስቃሴ መጀመሩ ፤ ታሪካዊ ቅርሶቻችን ሙሉ በሙሉ ለማውደም ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑ ፤ የውጭ ጠላቶቻችን ዘወትር የሚሸማቀቁባቸው የድል መዘክሮቻችን የአድዋና የካራማራ የድል ቀኖች እንዳይከበሩ የሚያደርጉት ክልከላ ተጨባጭ ማረጋገጫ ነው።
እነኚህ ቡድኖች አንግበው የተነሱትን ፕሮጄክት ለመተግበር እንቅፋት ነው ብለው ያመኑትን አማራ ከተቻለ ለማጥፋት ካልሆነም ለማዳከም በከፈቱት ዘመቻ ከፍተኛ ህይወት አልፏል ፤ ሀብት ንብረት ወድሟል ፤ ከሞት የተረፉት ተፈናቃዮች ለረሀብ እና ለእንግልት ተዳርገዋል ።
በስውር ይካሄድ የነበረው የዘር ማጥፋት እና ማጽዳት ዘመቻ ከአራት ዓመት ወዲህ በገኃድ በጠቅላይ ሚንስቴር አብይ አህመድ መሪነት ፤ በአቶ ሽመልስ አብዲሳ አዝማችነት እና በስም የሚለያዩ በገቢር ግን አንድ በሆኑ በኦሮሞ ሕዝብ ስም የተቋቋሙ ድርጅቶችና ሚዲያዎች የተቀናጀ ጦርነት ተከፍቶበት እንዲያልቅ እየተደረገ ነው።
አብይ አህመድ ኦነግን ዘመናዊ መሳሪያ አስታጥቆ አማራን እያስፈጀ ከትህነግ ወረራ የታደገውን ፋኖ ለመምታት እና የአማራን መሬት አሳልፎ ለመስጠት በእርቅ ሰበብ ሴራ በመጎንጎን ላይ ይገኛል ።
ውድ የአማራ ሕዝብ ሆይ ሳይቃጠል በቅጠል ነውና አብይ አህመድ ከትህነግ ጋር በመሆን በኢትዮጵያ መቃብር ላይ ታላቋን ትግራይና ታላቋን ኦሮሚያ ለመመስረት እንቅፋታችን የሆነውን ነፍጠኛ ከመንገዳችን እናስወግድ ብለው የጋራ ግንባር ፈጥረዋል።
አማራ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እንቅፋት ከመሆን ውጭ በሌላው ላይ የፈጸመው በደል አለመኖሩን ጽንፈኞቹ የኦነግ መሪዎች ኦቦ ለማ መገርሳ „በኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ጭቆና አልነበርም የውሸት ዲርቶ ነው“ ሲሉ ፣ ኦቦ ሌንጮ ለታ “በብሄር የተደራጀነው የግድ የምንታገለው ጠላት ያስፈልገን ስለነበር ነው ብለዋል“ ፣ ኦቦ ሌንጮ ባቲ “የብሔር ፖለቲካን የተጠቀምነው ለማታገያነት ነው“ በማለት ሶስቱም የኦሮሞ ፖለቲከኞች የብሔር ጭቆና አለመኖሩን የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል ።
በአሁኑ ወቅት እነኚህ ፖለቲከኞች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሥልጣን ይዘዋል ተጺኖ ማሳደር የሚችሉ ሆነው በክልላቸው የዘር ማጥፋትና ማጽዳት ዘመቻ እየተካሄደ ለማስመሰል እንኳን ለማውገዝ አለመፈለጋቸው ማንኛውም የኦሮሞ አደረጃጀት የስልጣን የውስጥ ሽኩቻ ካልሆነ በቀር በኢትዮጵያ መቃብር ሌላ አገር በመመስረቱ ዶክተር አብይን ጨምሮ ልዩነት የላቸውም።
በቋንቋ እንጂ በስነልቦና አንድ ያልሆነውን የኦሮሞ ሕዝብ በጉልበት ጭምር አስገድዶ አንድ ላይ ለማድረግ የምጥረው የዶክተር አብይ የብልጽግና መንግሥት አማራን ከፋፍሎ ለማዳከም ጎጃሜ ፣ ጎንደሬ ወሎዬ እና ሸዌ ነኝ እንዲል ያም አልሆን ስል የእምነት እና የነገድ ልዩነት ለመፍጠር ያለ የለሌ ኃይሉን በመጠቀም ላይ ያለ መሆኑን ተገንዝቦ አማራ እንደ እጅና ጓነት ሆኖ አንድነቱን ማጠናከር ይኖርበታልት ።
በአማራነትህ እየተገደልክ ወደ መንደርና ሰፈር በመውረድ የሴረኞች መሳሪያ አትሁን ፣ ኢትዮጵያዊነትህም ቢሆን የምትገደልበት የማንነትህ ምክንያት እንጂ ማንም ሊቸርህና ሊቀማህ ስለማይችል መደበቂያ ምክንያት ማቅረብ ተቀባይነት የለውም ፤ እየሞትክ ያለሔው በአማራነትህ ነው እና የአምስት አመቷን ህጻን ተማጽኖ ላስታውስህ „ወላሂ ሁለተኛ አማራ አልሆንም„ ይህች ህጻን በማንነቷ ኮርታ ማደግ ሲገባት ፈልጋ ባልተወለደችበት ማንነት ከመሞት ለመሰንበት የማይሆን ተማጽኖ እንድታደርግ መገደዷ ሊያስቆጣንና ሊያስቆጨን ይገባል ። ስለሆነም በአማራነታችን ተደራጅተን ህልውናችንን በማስጠበቅ በኢትዮጵያዊነታችን እንኖራለን ።
ኅወኃትንና በአምሳሉ የፈጠራቸውን ድርጅቶችም ሆኑ ግለሰቦችን ማንነት ለማወቅ 30 ዓመት በጣም ብዙ ጊዜ በመሆኑ ከመናገራችው በፊት የሚያስቡትን ሁሉ መገመት ችለናል እና የአማራ ብልጽግናዎች የፈለጉትን ማውራት ይችላሉ ካሁን በኋላ ግን የአማራን ገዳዮች ካባ ከመደረብ መላቀቃቸውን በተግባር እስከሚያሳዩን ድረስ ማመን እና መዘናጋት አይኖርብንም ። ለመታመን ቢያንስ በክልሉ ህገ መንግሥት አማራን እንደ ጨቋኝ አድርገው የተቀበሉትን የሀሰት ትርክት ማረጋገጫ የህግ
አንቀጽ አስወግደው ያሳዩን፤ የታሰሩ የአማራ የቁርጥ ቀን ልጆችን በሙሉ ይፍቱ ፤ በእማራ አጽመ እርስት ላይ ያላቸውን ግልጽ አቋም በይፋ ለሕዝባችን እና ለሴረኞቹ ይግለጹ ፤ ለፋኖ እውቅናን ሰጥተው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ያድርጉ ፤ ካሁን በፊት በትህነግ በጉልበት ተይዘው የነበሩና የአማራ ሕዝብ ልጆቹን ገብሮ ያስመለሳቸው አካባቢዎች በፌደራሉ መንግሥት የተያዘው በጀት ተለቆ ሰላማዊ ኑሮአቸውን እንዲመሩ በማስደረግ ከሕዝብ ጎን መቆማቸውን በተግባር ማሳየት አለባቸው።
የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ዶክተር ይልቃል ከፋለ ሰሞኑን አማራ በመላው ኢትዮጵያ ተበተኖ ስለምኖር ችግሩ የሚፈታው በኢትዮጵያ ማእቀፍ ውስጥ ነው ብለዋል ። በመላው ኢትዮጵያ ተበትኖ ይሚኖረው አማራ ብቻ አይደለም ፤ በኢትዮጵያ ማእቀፍ ይፈታል ሲሉስ ምን ማለታቸው ነው ? ችግሮች በኢትዮጵያ ማዕቀፍ የሚፈቱት ከፋፋይ የሆነው ህገ መንግሥት ሲቀየርና የጎሣ ፌደሬሽኑ ሲቀር ነው ያ እንዳይሆን ዶክተር አብይ ለአንድ ክልል ተብሎ ሕገመንግሥት አይለወጥም ሲሉ አገር አፍራሾቹ ትህነጎችና ኦነጎች በመቃብራችን ላይ ካልሆነ አይቻልም ብለው ቁርጡን ነግረውናል ። ሌላው ያለው ህገመንግሥት እንኳን የሚፈቅደውን መብት ከልክለው ክልላቸውን ከሌሎች ዘውጌዎች የጸዳ ልሙጥ ማንነት እንዲሆን በመጣደፍ ላይ ናቸው። ሀቁ ይህ ሆኖ እያለ እርሳቸው ማስተላለፍ የፈለጉት የብልጽግና መንግሥት በአምሳሉ የፈጠረው የምክክር ኮሚቴ ስለሚፈታው ጠብቁ የሚል የማደንዘዣ መለዕክት ማስተላለፍ ነው ።
አብንን በተመለከተም ትልቅ ተስፋ የተጣለበትን ድርጅት ለስልጣንና ለጥቅም አሳልፈው ከሰጡ ጥቂት አመራሮች ጋር ተደረገ የተባለው እርቅ ካሁን ቀደም በሽምግልና ስም ከተፈጸሙ ክህደቶች ተምረን ነባሩን አመራር በምርጫ አስወግደው የተሟላ ሪፎርም እስከሚያደርጉ ድረስ ማመኑ የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ እንዳይሆን መጠንቀቅ ያሻል ።
አማራ የሚታወቀው በጀግንነቱ እንጂ አልቃሻ አይደለም ፤ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ሚኒስትር ዶከተር ለገሠ ቱሉ “አማራ ማለቃቀስ ይወዳል“ ሲል አቶ ሺመልስ አብዲሳ “ተው ያልቅስ መሀረብ አቀብሉት“ በማለት ተዘባብተውብናል ። ትዕግሥትም ልክ አለውና ልናመርና በቃ ልንል ይገባል ፤ ተቅለስላሽና ምክንያት ደርዳሪ አማራ ሚናወን መለየት አለበት ።
በአገሪቱ መዲና ፣ በዲፕሎማቶች መኖሪያ እና በገነባት ከተማ አዲስ አበባ መግባት አትችልም ተብሎ ከመከልከልና መኖርም አይፈቀድልህም ተብሎ ቤቱን እላዩ ላይ እያፈረሱ በጅብ ከማስበላትና እራሱን በራሱ እንዲያጠፋ ከማድረግ በላይ ምን እስከምንሆን ነው የምንጠብቀው ?
ካለው ነባራዊ ሁኔታ የምንረዳው የኦነግ ብልጽግና እና ትህነግ ውይይቱን የፈለጉት ሰላም ለማስፈን ሳይሆን ዓላማቸውን ከማሳካታቸው በፊት ሁለተኛው ሕዝባዊ ማእበል እንዳይነሳ ለማደናገርና እንቅፋት ይሆንብናል የሚሉትን አሁን በፋኖ ላይ እንደጀመሩት ለይተው በመምታት ለማዳከም ነው ። ግባቸው የሚሆነው ትህነግ የበላይ በነበረችበት ወቅት ከሌሎች ክልሎች የቀማቻቸውን መሬት መመለስና የትህነግን የታላቋን ትግራይ የመመስረት ቅዠት እውን ማድረግ ነው ። በዚህ ተግባር ላይ ከውጭ ጠላቶቻችን ጭምር ሁሉ አቀፍ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው ።
ኢትዮጵያን እንደ ዶሮ ብልት ለመገነጣጠል የሚፈቅድ ህገ መንግሥት ስላለ ቀሪውን ኦህዴድ ብልጽግና ይገባኛል የሚለውን መሬት ከክልሎችና ከከተማ መስተዳድሮች በመውሰድ የቀሩትን አናሳ ዘውጌዎች ከፈለጉ በገዳ ስርአት ደንብ ማንነታቸውን በውዴታ በመተው ገርባ ሆኖ በኦሮሙማ እንዲዋጡ ማድረግ ፣ ያልፈለገውን በህገ መንግሥቱ መሰረት የክልሎችን ቁጥር በመጨመር አቅመ ቢስ አድርጎ አሁን እንደጀመሩት እንዲገነጠሉ መፍቀድ ነው „በእትዮጵያ መቃበር ላይ ኦሮሙማን መገንባት ማለት ይህ ነው„። ዛሬ በአማራ ሕዝብ ላይ እየተካሄደ ያለው የኦሮሞ ብልጽግና መንግሥት መራሹ የዘር ማጥፋትና ማጽዳት ዘመቻ ነግ በሁሉም ላይ የሚቀጥል በመሆኑ የእያንዳንዱ ክልል ነዋሪ ከአማራ ሕዝብ ጎን ቆሞ ድምጹን ሊያሳማ ይገባል
የኦህዴድ ብልጽግና በዶክተር አብይ አህመድና በአቶ ሽመልስ አብዲስ መሪነት በቅድሚያ በአማራ ሕዝብ ላይ ቀጥሎ ሌላውን ዘውጌ ተራ በተራ በህግ መስከበር ሽፋን በኦሮሞ ልዩ ኃይልና ኮማንዶ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ህጻንና አዛውንት ሳይለይ ህገወጥ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን በመገንዘብ ያለ ኢትዮጵያ የሚኖር ዘውጌ (ብሔር ፣ ብሔረሰብ ወይንም ሕዝብ) ስለማይኖር ማንኛውም ግለሰብ ፣ ቡድንና ድርጅት የትህነግንና የኦሮሞ ድርጅቶችን ሀገር የማፍረስ ተግባር ለማስቆም አገር አቀፍ ሕዝባዊ እምቢተኝነት መደረግ አለበት ።
አገር አቀፍ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ለማደረግ አንድ የሚያረጉን የጋራ አጀንዳዎች አሉን ፦
የኢትዮጵያ ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት አደጋ ፤ በኦርቶዶክ ተዋህዶ እምነትና በእስልምና ላይ የሚደረግ የመንግሥት ጣልቃ ገብነትና ሴራ ፣ የአዲስ አበባ ከተማን የመዋጥ ተግባር ፣ ህገወጥ አፈናና ግዲያን ማስቆም ፤ መንግሥት ሰራሽ የኑሮ ውድነትን መቃወም ፤ የኦህዴድ ብልጽግናን አገር አቀፍ የመሬት ወረራና የኦሮሙማ ግንባታን መቃወም ፤ የኦህዴድ ብልጽግናን ተረኝነትን መቃወም የጋራ አጀንዳ በመሆኑ ጥቃቅን ልዩነቶችን ለጊዜው በመተው በአገራዊና ሕዝባዊ ጉዳዮች ላይ ትግሉን ከጀመሩት አዲስ አቤቤ ፣ የጉራጌ ፣ የአማራ የሲዳማ እና የወላይታ ሕዝብ ጋር አብሮ በመሆን የተጋረጠብንን ወቅታዊ አደጋ በጋራ ለመመከት ሕዝባዊ እምቢተኝነት የህልውና ጉዳይ እንጂ አማራጭ አይደለም።
ፈጣሪ ኢትዮፕያንና ሕዝቦቿን ይጠብቅልን
ንጉሤ አሊ