ከሰሞኑ የአብን ስራ አስፈጻሚ አብሮ ለመስራት ተስማማ የሚል ዜና ከአስፈጻሚወች ውብ ፎቶ ጋር ተለቆ ተመልክተናል፡፡በምን ተጣልተው፤በምንስ ተስማሙ ? ማነስ አስማማቸው? ብዙ ጥያቄ ግን መልስ የሌለበት ዘመን፡፡አብን አትርሱኝ፤አስታውሱኝ በሚመስል መልኩ ከለቀቀው ማስታወቂያ ቀጥሎ የ127ኛውን የአድዋ ድል በዓል አከባበር አስመልክቶ ባንዳ የሚል ቃል ያካተተ መግለጫም አውጥቷል፡፡ይህንን ባንዳ የሚል ቃል ህወሃትም፤ማርያምን ትጣላኛለህ ብለው አዋጅ ነግረው፤በግምባር ጦር መርተው የማይደገም ታሪክ የጻፋትን ታላቁን ንጉስ አጼ ምኒልክን መጀመሪያ ለማደብዘዝ ከዚያም ለመሰረዝ በማሴር ለበዓል የወጣውን ህዝብ በእውነተኛ ማንነቱ በጥይት ግንባሩን እያስመታ በሃሳዊ ማንነቱ ደግሞ በመግለጫ የሚያምታታው አብይም ባንዳ የሚለውን ቃል ሲጠቀመው ሰምተናል፤፤አሁን ደግሞ አብን፡፡እውነት ግራጫ አይደለችም ቢባልም እንዲህ ስትንገላታ እናያለን፡፡የመጀመሪያውን የአብን ፕሬዘዳንት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔን ፎቶው ላይ አልተመለከትንም፡፡ምናልባት ከውጭ አልተመለሰ ይሆን? ለምን ይህ ስብስብ ከሰሞኑ ይህንን ማወጅ አስፈለገው? በህይወታችን ወስጥ ሰይፍ ሲያልፍ አብን የት ነበር? በአብይ ዘመነ መንግስት ከየትኛውም ፓርቲ ይልቅ የኪነ ጥበብ ሰወች ከአንዴ ሁለቴ ከህዝብ ጎን በድፍረት ሲቆሙ አስተውለናል፡፡ በወለጋ ህዝብ ሲያነባ አብረው አንብተዋል፤መላው ኢትዮጵያ ማቅ ሲለብስም አብረው በመሪነት ማቅ ለብሰዋል፡፡በቁርጥ ቀን ከህዝብ ጎን ስለቆማችሁ ምስጋና ይድረሳችሁ እንላለን! አሁን ጠላትን ጠላት ወዳጅን ወዳጅ ፤ባንዳን ባንዳ፤ሆዳምን ሆዳም፤ነጩን ነጭ፡ጥቁሩን ጥቁር ማለት ያለብን ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ወይ ከጠላት ወይም ከወገን መሰለፍ ግድ ነው፡፡በሁለት ቢላ እየበሉ መቀጠል ሊፈቀድ አይገባም፡፡
ርዕሴ ወደ ሆነው ወደ አብን ልመለስ፡፡ወደ ዋናው የጽሁፌ መልዕክት ከመግባቴ በፊት ጥቂት ነገሮችን ላስታውስ፡፡ አብን እንደተመሰረተ ለያዥ ለገራዥ አስቸግሮ ነበር፡፡ለምሳሌ እንደ ፖለቲካ ድርጅት ሲመሰረት በመሪው በኩል ባደረገው የምስረታ ንግግር አስከቀራኒወ ድረስ አንደሚታመን ቃል መግባቱን በመጀመሪያ እናስታውስ፡፡ከዚያም የአማራን ብሔርተኝነት ያደበዘዘው ኢትዮጵያ የሚለው ካምፕ ስለሆነ ይህን ሃይል መታገል አለብን በሚል መነሻ ለታማኝ በየነ ለውጡን ተከትሎ ወደ አገር ቤት ከረጅም አመት የውጭ ሃገር ቆይታ በኋላ ወደ አማራ ክልል ሲዘልቅ ስለሚያደርጋቸው ንግግሮች ማሳሰቢየ አስከ መስጠት የዘለቀ አስተያየትም አንብበናል፡፡የአማራ ህዝብ ትግል የህልውና ትግል ስለሆነ አማራ ራሱን የመከላከል ህጋዊ መብት አለው የሚለው አቋሙ መንግስትንም ግራ አጋብቶ ነበር፡፡ከብ/ጀኔራል አሳምነው ጽጌም ጋር ግንኙነት አለው ተብሎ በኦነግ ይጠረጠር ስለነበር በኦነግ ካምፕ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮ ነበር፡፡አንዳንዶቻችንም እንደ ኦነግና ህወሃት የዘረኝነትና የጥላቻ ፖለቲካ ውስጥ እንዳይዘፈቅ መማጸናችንም አልቀረም፡፡የወልቃይትንና የራያን ጉዳይ ከፍ አድርጎ መዘመሩም አይዘነጋም፡፡ኦፌኮ ከምርጫው ራሱን ሲያገል አብን ግን በምርጫው መሳተፍ ብቻ ሳይሆን በኮቪድ ምክንያት ምርጫው መራዘሙን ደግፎ ቆሞ፡፡ከምርጫ በኋላ ግን አብን የተወሰኑ ወንበሮችን ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን በድርጅት ደረጃ የተወሰነ ባይሆንም አመራሮቹ የአብይ አህመድ መንግስትን ተቀላቀሉ፡፡ከዚህ በኋላ አብን ቢጠሩት የማይሰማ ቢቀሰቅሱት የማይነቃ ሆነ፡፡ከህዝብ ዕይታ ለመሰወሩ አልፎ አልፎ አገሪቱ ጦርነት ላይ ስለሆነች ነው የሚል ማስተባበያ ሲሰጥም ሰምተናል፡፡ይሁን እንጂ ጦርነቱ ጋብ ካለም በኋላ የድሮው የአብን ቶን ሊመለስ አልቻለም፡፡ጠቅላላ ጉባኤ በስርዐት አካሂዶ አመራር መምረጥም ተቸገረ፡፡ለምርጫ ቦርድም የጠቅላላ ጉባኤ ተወካዮች ክስ እንዳቀረቡ የሚታወስ ሲሆን ምን እንደተወሰነላቸው ግን አላውቅም፡፡
እናም በህዝቡ ዘንድ ወደ መረሳት የተጠጋው አብን ከሞት እንደ መነሳት አይነት ሰሞኑን በስራ አስፈጻሚወቹ ስምምነት ዜና ብቅ አለ፡፡ይህንን ጽሁፍ ስጽፍ በእጅጉ አስቤበታለሁ፡፡አንደኛ እንኳን የፖለቲካ አመራር ይቅርና ወቅቱ ኢትዮጵያ አገሬ የሚል እያንዳንዱ ዜጋ በጋራ መቆምን የሚጠይቅ በመሆኑ፤ ሁለተኛ ደግሞ እንዲህ ያሉ ከፍተቶችን ጠላት እንዳይጠቀምባቸው ማሰብ ስለሚገባ ነው፡፡በድምሩ የህዝብን ትግል እንዳይከፍልና እንዳይጎዳ ለመጠንቀቅ ነው፡፡ግን ደግሞ የህዝብ ትግል የሚጠለፈው መሪወችን በመጥለፍ ነው፡፡የህዝብ ትግል የሚበተነው መሪወችን በመበተን ነው፡፡እናም የህዝብን ትግል ከግራ ከቀኝ፤ከውስጥ ከውጭ መጠበቅ ግድ ይላል፡፡በተለይ ከለውጡ በኋላ ህዝብ ያለ መሪ ድርጅት እና መሪ ግለሰብ መቆየቱ አከራካሪ አይመስለኝም፡፡ ህዝብ የጠበቀው ሌላ የሆነው ሌላ ነው፡፡ገዥው ፓርቲ፤ተቃዋሚወችስ የሚለኝ ካለ እኔ የማወራው በተፈናቃይ ካምፕ ውስጥ ለመሆኑ መንግስት አለ ወይ? አገራችን የት ነው? እያሉ ስለሚጠይቁ ወገኖች ነው፡፡ የትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ውሥጥ ስላይደለሁ በምንም መልኩ ግርዶሽ የለብኝም፡፡እያስጨነቀኝ ያለው ሁሉንም እያሳሰበ ያለው የአገራችን ህልውና ነው፡፡ እናም በቅናትም ይሁን በሌላ መንፈስ ተነሳስቼ ሰውን ባጠቁር በነፍሴም እጠይቅበታለሁ፡፡ነገር ግን ሰወች ለስጋ ፍላጎታቸው ተሸንፈው አገርን የሚያሳጣ አሰላለፍ ውስጥ ሲገኙ ወላጅም ቢሆን ሊቃወማቸው ይገባል፡፡
እንግዴህ በሂህ መሰረታዊ ዕምነት ሆኜ በአብን መሪወች ላይ ያለኝን የጥንቃቄ መልዕክት ላካፍል፡፡ህወሃትና አብይ ተቃዋሚወችንና ጋዜጠኖችን እንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦችን ያኮላሹበት መንገድ የተለያየ ነው፡፡ህወሃት ደህንነት የሚከፍላቸው ተከፋይ አባላትን አስርጎ ያስገባል፡፡አጀንዳ ይሰጣል፡፡ከዚያም ክፍፍል እንዲፈጠር በማድረግ ወደ ምርጫ ቦርድ እንዲያመሩ ያደርጋል፡፡ምርጫ ቦርድም ያው ህወሃት ስለሆነ ሰርጎ ለገባው ቡድን ህጋዊ ወራሽ እንዲሆን ይደረጋል፡፡በዚህ ሂደትም ታዋቂ ሰወችን ስማቸው እንዲጠፋ በማድረግ እንዲበተኑ ያደርጋል፡፡ለአብነት እናንሳ ከተባለ ቅንጅትን ያህል ስብስብ አቶ አየለ ጫሚሶ እንዲረከቡት እንደተደረገ እናስታውሳለን፡፡ቀስተ ደመና የዚህ ሰለባ ነበር፡፡ትዝ ከሚለኝ ፕ/ር መራራ አሜሪካ የተቃዋሚ ህብረት ምስረታ ተሳትፈው ሲመለሱ የፓርቲው ቢሮ ታሽጎ ጠበቃቸው፡፡በኋላም አሁን ስሙን በትክክል ለማላስታውሰው ሰርጎ ገብ አወረሱት፡፡ፕ/ር መራራ ግን በሁለት እግራቸው የቆሙ ስለነበሩ ይሄው እስከ አሁን በቦታቸው አሉ፡፡ያው ካምፑ አሁን ተጠቃሎ ኦነግ ሆኗል፡፡አብይ ግን የመረጠው አካሄድ ምትሃት የሚመስል ለሰወች ያልጠበቁትን ነገር በማድረግ ነው፡፡በኢትዮጵያ ታሪክ መንግስት ከተቃዋሚ ፓርቲ ጋር አብሮ መስራት ቀርቶ አብሮ መሰብሰብ እንኳን በመሃል ፈረንጅ ከሌለ ችግር ነው፡፡በአሜሪካ እንኳን ብዙ የተለመደ አይደልም፡፡በኦባማ ጊዜ መከላካያ ሚ/ሩ ሪፓብሊካን እንደነበሩ አስታውሳለሁ፡፡አብይ ሰርፕራይ ይወዳልና ሰርፕራይዝ አደረጋቸው፡፡ከዚያም በኋላ ጣታቸውን አፋቸው ላይ ጭነው ቀሩ፡፡የሚያውቁት እንደማያውቁ፤የተማሩት እንዳልተማሩ ሆነው ተመለከትን፡፡በአማካሪነት ያሉትን ትተን እንኳን ሶስት ሚኒስትሮችን አስታውሳለሁ፡፡በዋና ጄኔራል ዳይክተርነት ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ፤ ደ/ር አረጋዊ በርሄን ማንሳት እንችላለን፡፡ታዋቂ ግለሰቦችን ደግሞ በከንቱ ውዳሴና በጥቅማጥቅም ዘረራቸው፡፡አለምጸሃይ ወዳጆ ከሰሞኑ አድዋን ከብልጽግና ጋር አሜሪካ ኤምባሲ አከበረች ሲሉ ሰምቼ አልፈረድሁባትም ፤ግን መጨረሻየን አሳምረው የሚለው ጸሎት ትዝ አለኝ፡፡ሌላውስ ይቅር የጊዮርጊሱን ስትሰማ ምን ተሰምቷት ይሆን? የአብይ ጠልፎ የመጣል አካሄድ ላይ ላዩን ሲታይ በጎ ይመስላል፡፡እውነቱ ግን ከህወሃት ጋር አንድና ያው ነው፡፡የኦነግ ፖሊሲ ተግባራዊ ይሁን እናንተ መግለጫ አንድትሰጡ ከፈቀድሁላችሁ፤አልፎ አልፎም በሚዲያ እየወጣችሁ ትችት ከሰጣችሁ ይበቃል ነው፡፡ዶ/ር አረጋዊ ህወሃት ተወግዶ ምናልባትም ትግራይ ውስጥ ትልቅ ሹመት ሲጠብቅ ህወሃትን አራት ኪሎ ይዞለት መጣ፡፡ዳንኤል ክብረትን ስለ ህወሃት ያንን ያህል ካስወራ በኋላ አራት ኪሎ ይዞለት መጣ፡፡በነገራችን ላይ ዳንኤል በትግራይ ህዝብ ጋር በዚህ ንግግሩ ያተረፈው ጥላቻ ይሄ ነው ተብሎ አይነገርም፡፡፤ፓትርያርኩ ላይም ዳንኤል ብዙ ብሏል፡፡ግን የጠፋትን በጎች አብይ መንበረ ፓትርያርክ ይዞ ሲሄድ አብሮ እጅ ሲነሳ ነበር፡፡ለብዙ ስንመኛቸው የነበሩ ምሁራን፤የነጻነት ጎህ ሲቀድ እያሉ መጽሀፍ የጻፋ ፤ስለ ነጻነት አብዝተው ሲሰብኩ የምናውቃቸው በሹመት ነጻነታቸውን አጥተው ተሸብበው ቁጭ ብለዋል፡፡እንግዲህ ወደ ሰሞኑ ወደ ተጋጋለው የህዝቡ ቁጣ ትግል ለመምራት መግለጫ በመስጠት የጀመሩትን የአብን ተሿሚወችስን በምን እንመናቸው? እርግጥ ነው እነ የሱፍ ኢብራሂም ወጣ እያሉ ሃሳባቸውን ሲያካፍሉ አይተናል፡፡ሁሉንም በአንድ ቅርጫት መክተት አይቻልም፡፡አብይ በቅርብ ጊዜ ከኦነግ ፕሮጄክቶች ውስጥ ሁለቱን መፈጸም ጀምሯል፡፡የቤተ-ክርስቲያኒቱ ነገር በርታ ስላለበት ስትራቴጂክ ዓላማውን ባይተውም በታክቲክ ነገሩን በይደር ይዞታል፡፡አድዋን ግን ሙሉ በሙሉ ከልክሏል፡፡ጀግናው የአዲስ አበባ ህዝብ ግን እንዳሰበው አልተሸማቀቀለትም፡፡ይልቁንም ተጋፈጠው፡፡ቤተ-ክርስቲያንም ቆፍጠን ያለ መግለጫ ሰጥታለች፡፡ይህን ተከትሎ የህዝቡ ስሜት በየቤቱ እሳት እየነደደ ነው፡፡አማራ ክልል ደግሞ ከዚህም ከፍ ያለ ያረገዘ ነገር አለ፡፡አብይ ይህንን የህዝብ እንቅስቃሴ ሪሞት ኮንትሮል እጁ ማስገባት እንደሚፈልግ እሙን ነው፡፡ሪሞቱ በእሱ ቁጥጥር ከሆነ ሲፈልግ አዝምቶ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ይመታል፡፡ካልሆነ ደግሞ ህዝብ እያለቀ ሰላም ነው ሰላም ነው እንዲል ያደርገዋል፤፤የአብንን መሪ/አመራሮች ከሰሞኑ ብቅ ማለት ሪሞቱን ሊቀበሉ ቢሆንስ በምን እናምናለን? የአብን አመራር ከፍተኛ የአመኔታ መሳሳት(Trust deficit) ያለበት ነው፡፡በተሾመ ማግስት ሙልጭ አድርጎ የሰደበውን ህዝብ ልመራ ብሎ ሲመጣ በራሱ ገራሚ ነው፡፡መጀመሪያ በይፋ ይቅርታ መጠየቅ እንኳን ትንሹ ነው፡፡እኔ በግሌ ለእናት ለአባቱ ያልሆነ መሪ ለማንም አይሆንም፡፡ስለሆነም አብን ወደ ህዝብ ትግል ከመመለሱ በፊት የሰራቸውን ጉልህ ስህተቶች አርሞ፤ በዴሞክረሲያዊ መንገድ፤በምስጢር ድምጽ አሰጣጥ አመራር መርጦ መመለስ ይኖርበታል፡፡ካልሆነ ግን የአማራን ህዝብ ለቀቅ ቢያደርግ መልካም ነው፡፡
ይህንን አቋም ወደ ፊት ማምጣት አስፈላጊ የሚሆነው በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምኑ ኢትዮጵያውያንና የአማራ ህዝብ ከእንግዲህ ወዲህ አውነተኛ አታጋይ ድርጅትና በእያንዳንዱ እርምጃው የተፈተነ መሪ ለማግኘት ከራሱ ከትግሉ በላይ ትግሉን በሚጠልፋ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ትኩረት መስጠት አስፈላጊ ስለሚሆን ነው፡፡ወርቅ በዕሳት እንደሚፈተን ሁሉ ዘመኑ ሁሉም የሲዖል በሮች የተከፈቱ እስኪመስል ድረስ በአማራ ህዝብ እና በኢትዮጵውያን ላይ የመከራ ዶፍ ሲዘንብ ህዝቡን ማታገል እኳን ቢቀር ማንም ሊያደርገው የሚችለውን ማጽናናት እንኳን ሲያደርጉ አሩትልታዩም፡፡በጦርነቱ ወቅት ከብልጽግና ጎን ሆነው ማስተባበር የሰሩትን ማንሳት ይገባል፡፡ይሁንና የመላላክ እንጂ ተጽኖ ፈጥረዋል ብየ አላስብም፡፡አማራ ከአብይ ጋር የሚደራደረው በዚህ ወቅት ነበር፡፡አጋጣሚውን አልተጠቀሙበትም፡፡ የአብኑ መሪና ስሙን መጥቀስ የማልፈልገው ሌላ አመራር በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት የምኒልክ ቴሌቭዥን ጋዜጠኛ ከአባላትና ከህዝብ የቀረበ ጥያቄ ሲያቀርብላቸው ዘመናዊና የሠለጠነ ፖለቲካ የሚጠይቀውን ተግቧቦት በመተው እናታግለዋለን የሚሉትን ህዝብ የሚመጥን ጨዋነትን፤ቁጥብነትን፤ህግና ስርዐት አክባሪነትን በተጻረረ መልኩ በይፋ የንቅናቄው መሪ ህዝብን ሲሳደብ ሰምተነዋል፡፡ይህም በሪከርድ የሚገኝ እና የማይክዱት አሳፋሪ ድርጊት ነው፡፡ከሰደበኝ ስድቡን የነገረኝ እንዲሉ የቀድሞው የብአዴን ጽ/ቤት ሃላፊ የነበሩት አቶ አለምነው መኮንን የተሳደቡትን ስድብ እኔም እደግመዋለሁ በማለት በአደባባይ፤አለም እየሰማ እያየ በፍጹም የህዝብ ንቀት የአማራን ህዝብ የተሳደቡ መሪ አይናቸውን በጨው አጥበው ልምራህ ብለው ተመልሰው ሲመጡ ሌላ የህዝብ ንቀት ነው፡፡ በነገራችን ላይ እኒህ በስም የገለጽኋቸው የቀድሞ የብአዴን ጽ/ቤት ሃላፊ ባልተገራ ና ባልታረመ ባለጌ አንደበታቸው ህዝብን ዘልፈው ምንም ተግሳጽ ሳያገኛቸው ፤ ለህግ ሳይቀርቡ መቅረታቸው ደቀ መዝሙራቸው የአሁኑ የአብን መሪ ያንኑ ስድብ እንዲደግሙት ምክንያት ሆኗል፡፡ላጠፋት ጥፋት ተገቢው ቅጣት ሳይሰጣቸው ቀርቷል፡፡ተመጣጣኝ ባይሆን እንኳን አቶ በረከት ማረሚያ ቤት ቆይተዋል፡፡ደብረ ማርቆስ ላይ ወጣቶች የፈጸሙት ቁጣ አቶ በረከት ህወሃትን ለማዳንና ሌሎች ሴራወችን/ቦንብ ቀበራቸውን(ሌላ ቅማንት) እንዲያቆሙ እንዳስገደዳቸው እና ቤተሰቦቻቸውም ቆም ብለው እንዲያስቡ ያስቻለ ኩነት ነበር፡፡አሁንም እንደዚህ ህዝብን ለጠላት አሳልፈው የሚሰጡ ከልክ በላይ የሆኑ ሆዳሞችን አባላቱና ህዝቡ አምርሮ መታገል ይኖርበታል፡፡ አቶ አለምነው መኮንን የሰራኸው ወንጀል የተረሳ መስሎህ ከሆነ ተሳስተሃል፡፡በይፋ ይቅርታ መጠየቅ እንኳን በጣም ትንሿ ነገር ነች፡፡ በነገራችን ላይ እኒህን ግለሰብ እና ተከታዮቻቸውን ገዥወቻቸው ከጠየቋቸው በላይ አብዝተው በመስራት ምን ያህል ራሳቸውንም ወገናቸውንም ለመሸጥ የወሰኑ ስለሆኑ በወቅቱ በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት የነበሩት ሌላው ከፍተኛ አመራር ጋዜጠኛውን ለመደብደብ ሲጋበዙ አስተውለናል፡፡ይህም ወንጀል ነው፡፡አንድ ሌላ አመራርም እናሸማግላለን በሚል ሽፋን ወጣቱን ከወራሪ ጋር እንዲፋለም ሲቀሰቅሱና ሲያነቁ የነበሩ የቁርጥ ቀን የህዘብ ልጆችን አሳልፎ እንደሰጠ ይታማል፡፡በተለይ በዚህ የሚታሙት ግለሰብ ከጦርነቱ በፊት በማህበራዊ ገጽ ድንፋታቸው ብናውቃቸውም ጦርነቱ ሲጀመር የት እንደገቡ ደብዛቸው የጠፋ ግለሰብ ናቸው፡፡
ስለሆነም ይህ አመራር ሸሚዙን እኳን ሳይቀይር ለኢትጵያ አንድነት ምሰሶ የሆነውን የአማራ ህዝብ እመራለሁ ቢለን ልናምነው አንችልም፡፡ስለሆነም ራሱን ያርም መጀመሪያ እላለሁ!
ሳላስበው ረዘም ያለ ጽሁፍ ሆነ!
ይቅርታ አንባብያን!
በሚቀጥለው ስለ ጀግናው የደጀን ህዝብ፤ ስለ ባ/ዳር ህዝብ፤ስለ አዲስ አበባ ህዝብ፤ስለ ወልቂጤ/ጉራጌ ህዝብ፤ስለ ወላይታ ህዝብ ተጋድሎና ተምሳሌትነት የተሰማኝን አጋራለሁ!
አግዜአብሔር በክፋ የተነሱብንን ልቡና ይስጥልን!