አድዋ ሶስተኛውን ፍልስፍናዊ አብዮት ትወክላለች፡፡ በጥቂቱ ርእሰነገሩን ለማስረዳት ያህል፣ በአለም ላይ ሶስት ፍልስፍናዊ አብዮቶች አሉ፡፡
ስለመልካም ግብ ግህደት (እውንነት) የነበረውን ሁሉ እንዳልነበረ ያደረጉ፣ በእግሩ የቆመውን በሙሉ በጭንቅላቱ የተከሉ፣ የውስጡን ወደውጪ የገለበጡ፣ተደብቆ የነበረውን ሁለንተና ሀቅ ነጻ ያወጡ እሳቤያዊ አብዮቶች ናቸው፡፡
‹‹የመጀመሪያው አብዮት ኮፐርኒከን ሬቮሉሽን፣ ሁለተኛው አብዮት ካንሺየን ሬቮሉሽን እና ሶስተኛው አብዮት ምኒሊከን ሬቮሉሽን በመባል ይታወቃሉ፡፡
ኮፐርኒከስ በቶለሚ ተነጽሮ የነበረውንና ምድርን ማእከሉ (ጂኦሴንትሪክ ቪው) ያደረገውን ፍልስፍና ዘ ሳይንስ ወስነፈለክ ከውስጥ ወደውጪ በመገልበጥ ጸሀያዊው ስርአት (ሶላር ሲስተም) በምድር ዙሪያ የሚሽከረከር ሳይሆን ምድር ራሷ ናት በጸሀይ ዙሪያ የምትሽከረከረው፤ በማለት አዲስና ፋና ወጊ የሂልዮሴንትሪክ (ጸሀይን ያማከለ) አብዮትን በስነፈለክ አወጀ፡፡
ካንት በበኩሉ በስነእወቀት የፍልስፍና መስክ አዲስ አብዮትን ነፍስ ዘራበት፡፡ ነገሩ፣ ቀለል ባለ አገላለጽ እንዲህ ነው፡፡ በህሊናችን ውስጥ ያለውን ይዘት ልምድ አይወስነውም፡፡ ይልቅዬ ልምድን እራሱን የሚወስነው ህሊናችን ነው፡፡ እናም የምንዳስሰው አለም በራሱ ሆኖ የሚገኝ ሳይሆን የአእምሮአችን የተለያዩ ፈርጆች በወቀሩት፣ በሰሩት፣ ባበጃጁት፣ ፈር ባስያዙት፣ ልክ ባገቡት እና በጫኑበት ቅርጽና በለገሱት ስርአት መሰረት የሆነ ነው፡፡ እናም እውነታ ለእኛ ህሊናችን አቡክቶ በጋገረው መሰረት የሚታየው፣ የሚለበበው እና የሚቀርበው ሲሆን፣ እውነታ በራሱ ግን ምን እንደሆነ አይታወቅም፤ በማለት አዲስ የእሳቦት ፈር በስነእውቀት ቀደደ፡፡
ሶስተኛው አብዮት በፖለቲካዊ ፍለስፍና ዘርፍ በምኒሊክ መሪነት አድዋ ላይ እውን የሆነው አብዮት ነው፡፡
እስከአድዋ ድል ድረስ ከኢትዮጵያ በስተቀር አለም በሙሉ በነጮች ገዢነት፣ በነጮች ፍጹም የበላይነት፣ በነጮች ወሮ ድልአድራጊነት፣ በነጮች ሉላዊ መሪነት፣ በነጮች ብቸኛ ተሰሚነት፣ ፍጹማዊ ፈላጭ ቆራጭነት ስር ስትፍገመገም ኖረች፡፡ ከአድዋ ድል በሁዋላ ግን ይህ ታሪክ በጭንቅላቱ ተተከለ፣ ከፍጹምነት አምድ ወደአንጻራዊነት ወታቦ ተሸኳለለ፤ ከአለማቀፋዊ ገዢ እውነታነት ወደወራዳ ፖለቲካዊ ድስትፊያነት ተንደባለለ፡፡
ይህ የነጮችን የበላይነት በፍትህ የበላይነት፣ የዘርና የቀለም ልዩነትን መራሄነት በሰው ልጆች ሁሉ ልእልና ገዢ አስተምህሮነት፣ የጥቁሮችን መናቅና ውርደት በሰው ልጆች ሁሉ እኩልነት የተካ ሁለንተናዊ ፖለቲካዊ አብዮት ምንሊከን ሬቮሉሽን ወይም ሶስተኛው ፍልስፍናዊ አብዮት ተብሎ ይጠራል፡፡
ነጮች ከእግዚአብሄርም፣ ከሰውም ሆነ ከህግ በፊት ለቀለምና ለዘር ቅድሚያ ሲሰጡ፣ከነሱ ቀለምና ዘር ውጪ ያለውን ከተራራ አናት ቄጤማ ከበረሀ ብብት በረዶ አምጡ ብለው እንዳላላገጡ አድዋ ላይ በጉዳቸው ወጡ፡፡ ነጮች ለዘመናት የሰው ልጆችን በህግ ፊት ቀርቶ በአምላክ ፊት እንኩዋን እኩል መሆንን ዘንግተው ኑረው፣ በአድዋ የጀግንነት ውሎ ፊት የሰው ልጆች ሁሉ እኩል መሆናቸውን ሳይወዱ በግድ እንዲያውቁ ያደረገ ሁለንተናዊ አብዮት ሚኒሊከን ሬቮሉሽን ወይም ሶስተኛው አብዮት ይሰኛል፡፡
ይህ ከላይ የገለጽኩት ምኒሊከን ሬቮሉሽን ኢትዮጵያውያን በጥልያን ፋሺስቶች ላይ በተቀዳጁት አንጸባራቂ፣ ልዩና ወደር ነቅናቂ ድል ላይ የተመሰረተ የዘመናችንን የአለም ታሪክ አቅጣጫ የቀየረ አብዮት ነው፡፡
ከኢትዮጵያ ወገን አንድም ሰው አልተማረከም፡፡ ሆኖም ከሮማን ኢምፓየር የልጅ ልጅ… ልጆች በኩል፣ ማለትም ከጥልያን በኩል ከሰባት ሺህ ወታደር በላይ ከአንድ ጀነራል ጭምር (ጀነራል አልበርቶኒ) የተማረከበት መላ አለምን ያስደመመ ጀግንነትን ከክብር ከፍታ የከተመ፣ ክብርንም በድል ምንገድ ያተመመ ገድለኛ አብዮት ነው፡፡
በሺዎች የሚቆጠሩት ምርኮኛ ጥልያኖች በወቅቱ ከአድዋ መጥተው አዲስ አበባ ላይ የሰፈሩበት አካባቢ እስካሁንም ድረስ … ጣሊያን ሰፈር … በመባል ይታወቃል፡፡ እነኚህን ምርኮኞች እጃቸውን ለጀግናው የአጼ ሚኒሊክ ጦር ከሰጡበት ደቂቃ አንስቶ አንበሶቹ ኢትዮጵያውያን የተሟላ ሰብአዊ ክብርና እንክብካቤ እያደረጉላቸው ከአድዋ አዲስአበባ አመጧቸው፡፡ የምርኮኞቹ አያያዝ እጅግ የሰለጠነ ሀገርና ጀግና ህዝብ ያደረገው ሁለንተናዊ ክብካቤ ነበርና መላው አለም ለኢትዮጵያ የነበረውን እውቅና እንደገና አድሶ ኤምባሲውን በመዲናችን ባዲሳባ ለመክፈት ይሻማ ጀመር፡፡
በሽሚያው ጥልያንን የቀደመ አልተገኘም፡፡ ፈረንሳይ ተጋግጣ ሁለተኛ፣ እንግሊዝ ተሟሙታ ሶስተኛ፣ አሜሪካን ተፍጨርጭራ አራተኛ ደረጃን በኤምበሲ ከፈታው ውድድር ለመያዝ በቁ፡፡ ኢትዮጵያም ወደጥልያን መመለስ እንሻለን ያሉትን ምርኮኞች ሁሉ በተሟላ ክብር ለሀገራቸው መሬት እንዲበቁ አድርጋለች፡፡
ይህንን ሶስተኛውን ፍልስፍናዊ አብዮት አጼ ሀይለስላሴ አርባአራት አመት በቆየው የንጉሰነገስትነት ዘመናቸው ሰላሳ አራት ጊዜ አራዳ ጆርጊስ በመገኘት በምኒሊክ አደባባይ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በይፋ አክብረዋል፡፡ ኮለኔል መንግስቱ ሀይለማርያም ደግሞ አስራሰባት አመታት በዘለቀው አስተዳደራቸው ወቅት አስር ጊዜ በአራዳ ጂርጊስ ተገኝተው በምኒሊክ አደባባይ ከመላ ኢትጵያውያን ጋር በኦፊሴል አክብረዋል፡፡ መለስ ዜናዊ ሀያአንድ አመት በዘለቀው አገዛዙ አንድ ጊዜ ስንኩዋን አድዋን በምኒሊክ አደባባይ መገኘትና ማክበር ቀርቶ በቲቪ መስኮት ስንኩዋን በኮሚባፈታ/ የግብር ይውጣ ንግግር ሳያከብር በመቅረቱ የምር የባንዳ ልጅነቱን አረጋግጧል፡፡ ሀይለማሪያም ደሳለኝ አምስት አመት በቆየው የስልጣ ዘመኑ አንዴም የአድዋን ድል በአል አራዳ ጆርጊስ ካለው ምኒሊክ አደባባይ ተገኝቶ ሳያከብር ቀርቷል፡፡ ዶ/ር አብይ አህመድ በበኩሉ ይህ መጽሀፍ እስከተጻፈበት ጊዜ ድረስ ለሶስት አመት በቆየው የስልጣን ዘመኑ አንዴም ጆርጊስ ካለው የምኒሊክ አደባባይ ተገኝቶ የአድዋን ድል በአል አላከበረም፡፡
ከሰውን ናስው መጽሀፍ ምእራፍ 1 የተወሰደ