ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
የካቲት 26፣ 2023
አቶ ባይሳ ዋቅ-ወያ “የሽግግር ፍትህ፣ “የይቅርታ” ፖለቲካና የፍትህ ስርዓታችን” በሚል ርዕስ ስር የጻፈውን በዘሀበሻ ላይ የወጣውን ጽሁፍ አነበብኩት። በመጀመሪያ ደረጃ፣ የሽግግር ፍትህ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ አይደለም። ሽግግሩ ከየት ወደየትና ፍትህስ ለማን ነው የሚሰጠው? በሁለተኛ ደረጃ፣ ራሳቸውን ወንጀለኞችን፣ ማለትም ህውሃትንና የፈሺሽቱን የአቢይን አገዛዝ ወንጀል እንዳልፈጸሙ፣ ሌሎች ተጠያቂዎች እንደሆኑና፣ እንደነዚህ ዐይነት ወንጀሎች ለመፈጸማቸው አምኖ በአገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሙያዊ ልምድ ባለቸው እንዲመረመሩ አመቺ ሁኔታን መፍጠር የሚለው አቀራረብ በጣም አሳሳች ነው። በመሰረቱ ተጠያቂዎቹ ህወሃትና የአቢይ አገዛዝ ናቸው። እነሱ ደግሞ አመቺ ሁኔታን ሊፈጥሩ አይችሉም፤ ፍላጎታቸውም አይደለም። ምክንያቱም ራሳቸው የወንጀሉ ዋና አቀነባባሪዎች ስለሆኑ። በሶስተኛ ደረጃ፣ ከዚህ ጽሁፍ ውስጥ ያልተካተተው፣ አቢይ አህመድ ስልጣን ላይ ከወጣ ከአንድ ዓመት በኋላ ሆን ብሎ በአማራው ወገናችንና የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች በሆኑት ላይ ያደረሰውንና የሚያደርሰውን እልቂት በፍጹም በቁጥር ውስጥ አላስገባም። በአራተኛ ደረጃ፣ ከዚህም በተጨማሪ በሻሸመኔ የደረሰውን ውድመት፣ ከዚያ በኋላ በአጣዬና በሸዋ ሮቢት በራሱ በአገዛዙ በተቀነባበረ መልክ የደረሰውን የከተማዎችና የሀብት ውድመትንና የሰዎችንም መሞት በፍጹም አይጨመርም። በአምስተኛ ደረጃ፣ ከዚህ ባሻገር በምዕራብ ወለጋ በራሱ በአቢይና በሺመልስ አብዲሳ በተቀነባበረ መልክ እስካሁን ድረስ በአማራው ወገናችን ላይ የሚካሄደውን ጦርነት ወይም የዘር ማጥፋትና የሰዎችን ማፈናቀል በፍጹም አያካትትም። በስድስተኛ ደረጃ፤ በአዲስ አበባ አካባቢ አዲስ ዋና ከተማ ለመመስረት በሚል ሰበብ፣ በተለይም በስንት ልፋት ገንዘብ አጠራቅመው ቤት ሰርተው እፎይ ብለው መኖር በጀመሩ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን አሰቃቂ ድርጊት በጽሁፉ ውስጥ አልገባም። በተለይም አዳነች አበቤና ሺመልስ አብዲሳ በማንአለኝበት ቤቶች እንዲፈርሱ ትዕዛዝ እየሰጡ ሰዎች በተኙበት ቤታቸው እንዲፈርስ እየተደረገ፣ አንዳንዶች ራሳቸውን ሲገድሉ፣ ትናንሽ ልጆች ደግሞ በጅብ እንዲበሉ ተደርገዋል። በየሜዳው የተጣሉ ዜጎችም ቁጥራቸው ጥቂት እንዳልሆነ ይታወቃል። እነዚህ ሰዎችም መጠለያና ካሳ ሳይሰጣቸው ነው ቤታቸው እንዲፈርስ የተደረገው። በመሰረቱ ከህግ አንጻር ነገሮችን ነጣጥሎ ማየት ቢገባም፣ ቀደም ብሎ ወያኔ ስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜና፣ አቢይ አህመድ ደግሞ ስልጣን ከያዘ ከዛሬ አምስት ዓመት ጀምሮ የሚያካሂዱት ጦርነት ኢትዮጵያን እንዳለ እንደ አገርና እንደማህበረሰብ ለማፍረስ ነው። ሰሞኑን በኤርትራው ፕሬዚዳንት በቀረበው የቃለ-መጠይቅ ምልልስ የስሜን ዕዝን ጦር ወይም ወታደሮችን እንዲገደሉ አሜሪካ በቀጥታ የእልቂቱ አቀነባባሪ እንደሆነ ነው የሚነግሩን። ይህም ማለት፣ ወያኔ ራሱ ለወታደሩ ዕልቂትና ለጦርነቱ መንስዔ ብቻውን ተጠያቂ ሊሆን እንደማይችል ነው የሚነግሩን። ምክንያቱም ይሉናል፣ አሜሪካ አካባቢውን ለመቆጣጠር ስለሚፈልግ ሰላም እንዳይኖር እንደዚህ ዐይነት ጭንቅላታቸው የተበላሸ ወይም የተመረዘ አገዛዞችን እያስታጠቀ ጦርነት ማካሄድ ከደሙ ጋር የተዋሃደ በመሆኑ ነው። በሰባተኛ ደረጃ፣ የሰሞኑን የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ ባይሳ በደንብ ተከታትሎ እንደሆን አቢይ አህመድና ግብረ አበሮቹ ከወያኔ ጋር በመሰጣጠር ይፎካከረናል የሚሉትን አማራውንና የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ ድምጥማጣቸውን ለማጥፋት ቆርጠው እንደተነሱ ነው። ለዚህ አገርን የማጥፋት ድርጊታቸው ደግሞ የምዕራቡ ዓለም፣ በተለይም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም እንደሚተባበራቸውና እንደሚደግፋቸው ግልጽ እየሆነ በመምጣት ላይ ነው። ከሶስት ቀን በፊት በፕሬዚደንት ፑቲን የተደረገውን ሰፊ ሀተታ በደንብ የተከታተለ ሰው የሚረዳው የምዕራቡ የካፒታሊስት ዓለም የኦርቶዶክስን ሃይማኖት እንዳለ ለማጥፋትና ማንኛውንም የሰውን ልጅ እሴቶች በመደምሰስ የራሱን የተበላሽ የአኗኗር ሁኔታ ለማስፋፋት ጦርነት እንደከፈተ ነው የሚነግሩን። በዓለም አቀፍ ደረጃ በነፃ ንግድና በገበያ ኢኮኖሚ ስምም ተግባራዊ የሚሆኑት የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ ዋና ዓላማቸው የየአገሩን ኢኮኖሚዎች በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ በመመስረት ሰፋ ያለ የአገር ውስጥ ገበያ መገንባትና የአንድን አገር ህዝብ የሚያስተሳስሩ ባህላዊ ነገሮችን ማዳበር ሳይሆን፣ ለውጭው ዓለም በመክፈት መባለጊያ መድረክ ማዘጋጀት ነው። በስምንተኛ ድረጃ፣ ከባይሳ ዋቅ-ወያ አፃፃፍ እንደምረዳው ከሆነ ተራ የቴክኖክራቲክ አቀራረብና የችግሮችን ዋና ምንጭ በመረዳት ሳይንሳዊ መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችል አይደለም። ወያኔም ሆነ አቢይና የኦሮሞ ኤሊት ነን ባዮች የጠለቀ ዕውቀት ቢኖራቸው ኖሮና መንፈሳቸው የነቃ ቢሆን ኖሮ እንደዚህ ዐይነቱን አገርን የማጥፋት ድርጊት ባልፈጸሙ ነበር። ለማንኛውም እንደዚህ ዐይነቱ አገርን የማውደም ተግባርና ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ወንጀለኞች በህግ ፊት ቀርበው አስፈላጊው ቅጣት የሚሰጣቸው በኢትዮጵያ ምድር አገር ወዳድና የነቃ ኃይል ስልጣንን ሲጨብጥ ብቻ ነው።
ይህንን ካልኩኝ በኋላ ባይሳ ዋቅ-ወያን የምለምነው ባለፉት ሰላሳ ዓመታት በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ድምጹን ያላሰማና ሳይንሳዊ ጽሁፍም ያላቀረበ ነው። አሁን ጡረታ ከወጣ በኋላ ልክ ለአገርና ለህዝብ ተቆርቋሪ እንደሆነ እንደነዚህ ዐይነት ምንም ዐይነት ሳይንሳዊ ይዘት የሌላቸውንና ግንዛቤ የማይሰጥ፣ እንደዚሁም ከተጨባጭ ሁኔታዎችን የኣቁ ጽሁፎችን እያቀረበ የዋህ ኢትዮያውያንን ያሳስታል። ባይሳ ዋቅ-ወያ ገብቶት እንደሆን የዓለማችን ሁኔታ በጣም ግራ የሚያጋባ ቢሆንም፣ ጊዜው የሚጠይቀው ከዕወቀት ጋር የተያያዙና ለህዝባችን ሳይንሳዊ መፍትሄዎችን የሚሰጡ ጽሁፎችን ማቅረብና ማስተማር ነው አንገብጋቢው የጊዜው ጥያቄ። ፈላስፋዎች እንደሚያስተምሩን የአንድ አገርም ሆነ በዓለም ላይ የሚታዩት ችግሮች በሙሉ ከዕውቀት እጦትና የተፈጥሮን ህግ ካለመረዳት የተነሳ የሚከሰቱ ችግሮች እንደመሆናቸው መጠን፣ ጭንቅላታችንን ወደዚሁ ማዞሩ ችግሮችን በቅደም ተከተል እንድንፈታ ያስችሉናል። የአንድ አገር ህዝብ ችግር ከህግ አንጻር ብቻ የሚፈታ ስላይደለ ጭንቅላታችንን ክፍት በማድረግና በትችታዊ ቲዎሪ(Critical Theory) መነጽር በመመርመር የተወሳሰበውን የአገራችንን ችግሮች በመረዳት ህዝባችን በሰላም የሚኖርበትን አመቺ ሁኔታ መፍጠር ነው ዋናው ተግባራችን። ስለሆነም በአገራችን ምድር ፍትህ የሚረጋገጠውና የህግ የበላይነትም የሚከበረው በመጀመሪያ ደረጃ የነቃና ስልህግ ምንነት የተገነዘበ አገዛዝና የህብረተሰብ ኃይል ሲኖር ብቻ ነው። መልካም ግንዛቤ!