ከእስርቤት ወደ ፍርድቤት ከሄድኩባቸው ወደ አራት የሚጠጉ ቀናት በሶስቱ ቀናት ጋዜጠኛ ተመስገን ደስአለኝም እንደእኔው የፍርድቤት ቀጠሮ ኖሮት ኖሮ አግኝቼዋለሁ፡፡ በጨረሻ ባገኘሁት ቀን በመጀመሪያ ስሜ የተጠራው እኔ ነበርኩ፤ ችሎቱን ታድሜ ስመለስ ፍርዱ ለተጨማሪ ስምንት ቀናት መቀጠር ሆነ፡፡ ይህንኑ ሰምቼ ስመለስ እስረኞች መሃል ሆኖ ተራውን የሚጠባበቀው ተመስገን ደስአለኝ ልብሴን ጎተት አድርጎ በጉጉት “ምን ተባልሽ?” ሲል ጠየቀኝ፡፡ ነገርኩት፤ቅር ባለው ፊት ዝም አለ፤እኔም ወደቦታየ ተመለስኩ፡፡
የእሱ ስም ተጠራና ተነስቶ አራተኛ ፎቅ ላይ የሚያስችለውን ችሎት ለመድረስ የፎቁን አቀበት ተያያዘው፡፡ በዚህ ቀን እሱ እና ሰለሞን ሹምየ “በአስር ሽህ ብር ዋስ ውጡ” ብሎ ፍርድቤቱ ፈረደላቸው፡፡ ሲመለስ እኔም በተራየ ምን እንደተባለ ጠየቅኩት፡፡ “በብር ዋስ ተባለ” አለኝ፤”የስንት ብር ዋስ?” አልኩኝ ነገረኝ ፤”እንኳን ደስ አለህ አልኩኝ”፤”አይ! አብረን ቢሆን ነበር እንጅ” አለኝና ወደመቀመጫው አመራ፡፡
ተሜ ይህን የሚለው ፍርድቤት የሚለው ተከብሮ እሱ የተፈረደለት የአስር ሽህ ብር ዋስትና ተግባራዊ ከሆነ ከእኔ የስምንት ቀን ቀጠሮ ከተሰጠኝ የአራስ ልጅ እናት ቀድሞ መውጣቱ ከብዶት ነው፡፡ የሆነው ግን ሌላ ነው!
ፍርድቤት ለቆት እያለ የመንግስት ጉልበተኛ ጫማ ረግጦት እስር ቤት ስላስቀረው አንድ ሃገር ወዳድ ጋዜጠኛ ኢ-ፍትሃዊ እስር አዝናለሁ ! “አብረን ቢሆን ነበር እንጅ” ያላት ንግግሩ ጆሮየ ላይ ታስተጋባለች::ዛሬ በእሱ ቦታ ሆኜ “አብረን ቢሆን ነበር እንጅ” የምለው እኔ ሆኛለሁ፤አዝናለሁ! ተራ ዜጋ ከማዘን በቀር ምን ያደርጋል ???