በመንግስት አካላት መካከል የሚታዩ መፋጠጦች እንዲረግቡ ካልተደረጉ ችግሩ ወደ ህዝቡ በመውረድ አጠቃላይ ሀገራዊ ቀውስ ውስጥ ሊከቱን ይችላሉ ሲል ያስጠነቀቀው ኢዜማ፤ ሃገር እየመራ ያለው የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች የእርስ በእርስ ንትርክና ፀብ ለሃገር ስጋት ሆኗል ብሏል፡፡
በብልጽግና ስር ተጠቃለው ክልሎችን ለመምራት በስልጣን ላይ የተቀመጡ የብልጽግና አመራሮች ተናበውና ተቀናጅተው ሃገሪቱን ከገጠማት ዘርፈ ብዙ ፈተና ለማውጣት በጋራ መስራትና ከህዝቡ አንድ እርምጃ ቀድመው የመፍትሔ ሃሳብ ከማቅረብ ይልቅ በየጊዜው እርስ በእርስ እየተናከሱ አለፍ ሲልም ለፀብ እየተጋበዙ፣ ከኑሮ ውድነቱ በላይ ራሳቸው አመራሮቹ የሃገር ስጋት ሆነዋል ሲል ጠቅሷል፡፡
“ብልጽግና ውስጥ የሚፈጠርን ችግር የማምለጫ መንገድ ተደርጎ እየተወሰደ ያለው ህዝብን ከህዝብ ማጋጨት ነው” ያለው ኢዜማ፤ የህዝብን አብሮ የመኖር እሴት በቋሚነት በመሸርሸር የመንደራቸው አውራ ለመሆን የሚታትሩ የብልጽግና አመራሮች ከዚህ አስነዋሪ ድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል” ሲል አሳስቧል – ፓርቲው።
በአሁን ወቅት በሃገሪቱ ላይ የተደቀኑ ኢኮኖሚያዊ፣ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ጥልቅና ዘርፈ ብዙ መሆናቸውን ያመለከተው ፓርቲው፤ እነዚህ ችግሮች ከግብታዊነትና ከእልህ በወጣ መልኩ በመነጋገርና በመግባባት ብቻ የሚቀረፉ መሆኑን በማመን ሁሉም አካላት ሃገራቸውን አስቀድመው በሰከነ መንገድ ወደ መነጋገሩ መድረክ እንዲመጡ ጥሪ አቅርቧል፡፡
አሁን በሃገሪቱ ባሉ ችግሮች ላይ ተጨማሪ ችግሮችን መፍጠር መጠፋፋትን እንደሚያስከትል የተቆመው ኢዜማ፤ በብሔር ዘውግ ጫፍና ጫፍ ሆነው መጓተት ውስጥ የገቡ አካለት ከእለት ወደ እለት ሃገሪቱን ብዙ ዋጋ እያስከፈሏት ነው ብሏል፡፡
እነዚህ በሃገሪቱ ላይ የተጋረጡ ስጋቶችንና የተደቀኑ አደጋዎችን አስመልክቶ መፍትሔ ለማበጅት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመነጋርና ለመወያየት ዝግጁነቱን የገለፀው ኢዜማ፤ ለሃገሪቱ ሠላምና ለህዝቦች አንድነት፣ የሃይማኖት መሪዎች የሃገር ሽማግሌዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ምሁራን የዚህ ሂደት ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪውን አቅርቧል፡፡