እንዳለፉት ጊዜያት
ለረዥም ዘመናት
ሰው እንደኖረበት
ኖሮ እንዳለፈበት
ገድል አስመዝግቦ
ታሪክን አድልቦ
ደጉንም
ክፉንም
ጥላቻን
ፍቅርን
ማግኘትን
ማጣትን
መጥገብን
መራብን
ከአገር መሰደድን
ተዋርዶ መኖርን
መታመም መሞትን
ታሞ ማገገምን
ሁሉንም በቅጡ
እንድየ አመጣጡ
እንዳስተናገደው
በአግባቡ እንደሸኘው
ይህችም ቀን ታልፋለች
አክብረን ካልያዝናት ታስተዛዝባለች
ትዕግሥቷ ሲሟጠጥ
ስንገፋት ያለቅጥ
መገንዘብ አቅቶን
ስንጋብዝ መከራን
ለጠላት በማገዝ
አገርን ስናወግዝ
በዓይናችን እያየን
ሲያልቅብን ሕዝባችን
ዙሪያውን ተከበን
በጠላቶቻችን
ምጡ ጨክኖባት
የአገራችን ጩኸት
አዋላጅ በማጣት
ድረሱልኝ ብላ ስትጮኽ እያየን
ጆሮ ዳባ ልበስ አልሰማነም ብለን
ጦር አውርድ በማለት መከራ እንጠራለን
ይህችም ቀን ታልፋለች
አክብረን ካልያዝናት ታስተዘዝባለች
ትዕግሥቷ ሲሟጠጥ
ስንገፋት ያለቅጥ
ጨለማው ይበራል
ድፍርሱም ይጠራል
የአገር ጠላት ያፍራል
ጀግኖችን ያኮራል
በጊዜ ዳኝነት
ፍርዱን ቆሞ ማየት
የማይቀር ሐቅ ነው
በቅርብ የምናየው
ሕዝባችን እንደሆን
ለምዶታል መከራን
መፍትሄው አንድ ነው
አማራጭ የሌለው
እንደ አባቶቻችን
እንደ እናቶቻችን
በጋራ አብረው ቆመው
ጠላትን መክተው
መቁሰልን
መሞትን
የመጣውን ሁሉ
የኔ ነው ሳይሉ
እንደየ አመጣጡ ሁሉን አጣጥመው
ክፉ ቀንን ሳይቀር አብረው አሳልፈው
ለእኛ ሲሉ ሞተው
አገር አቆይተው
ትውልድን ተክተው
ለአስረከቡን ሀገር
ልንሆን ይገባናል ጨፈቃና ማገር
የጊዜው ግርግር የትም ላያደርሰን
በታሪክ ተወቃሽ ቆይቶ እንዳያደርገን
ማሰብ ይገባናል መልሰን መላልሰን
ማፈስ ስለሚከብድ የፈሰሰ ውሃን
የእግር እሣት ሆኖ እንዳያቃጥለን
እናስተውል ከልብ መልሰን መላልሰን
ይህችም ቀን ታልፋለች
አክብረን ካልያዝናት ታስተዛዝባለች
ትዕግሥቷ ሲሟጠጥ
ስንገፋት ያለቅጥ