March 23, 2013
37 mins read

ሰላማዊ ትግል እና ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች – የማይረሳ ታሪክ በኢትዮጵያ ተሰራ! ከግርማ ሞገስ

  ከግርማ ሞገስ

ቅዳሜ መጋቢት 14 ቀን 2005 ዓመተ ምህረት (Saturday, March 23, 2013)

ሙስሊም ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን

ድምጻችን ይሰማየሚል አቤቱታ የማሰማት ሰላማዊ ትግል ከጀመሩ ከአመት በላይ ሆኗቸዋል። ከአንድ አመት በፊትም ሆነ ዛሬ ጥያቂያቸው አልተለወጠም። ከሞላ ጎደል ጥያቄዎቹ ባጭሩ እንደሚከተለው ሊቀርቡ ይችላሉ፥

1) የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት

(መጅሊስ) በሙስሊሙ ህበረተሰብ ቀጥተኛ ተሳትፎ በተመረጡ መሪዎች ይመራ፣

2) አወሊያ ትምህርት ቤት በቦርድ ይተዳደር፣

3) የአህባሽ ስልጠና እንዲቆም የሚሉ ናቸው።

የኢትዮጵያ ህገመንግስት እንደሚልው ከሆነ መንግስት እና ሃይማኖት የተነጣጠሉ ናቸው። ሁለቱ የተነጣጠሉ ናቸው ማለት መንግስት በሃይማኖታዊ (መንፈሳዊ) ጉዳይ እንዲሁም ሃይማኖት በመንግስት ፖለቲካዊ አስተዳደር ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ አይገቡም ማለት ነው። መንግስት ስራው ፖለቲካ ስለሆነ ምድራዊ ነው። ሃይማኖት ደግሞ ስራዋ መንፈሳዊ በመሆኑ ስራዋ ከፈጣሪ አምላክ ጋር የተሳሰረ እንጂ አገር ከማስተዳደር፣ ባጀት ከማጽደቅ፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከመንደፍ እና ከመሳሰሉት ምድራዊ ጉዳዮች ጋር ግንኙነት አይኖራትም። ሁለቱ ፍጹም በገናኘት አይኖርባቸውም። ስለዚህ መንግስት እራሱ የጻፈውን ህገመንግስት ማክበር ነበረበት። ሙስሊሙ ህብረተሰብ የመጅሊስ መሪዎቹን ካለምንም መንግስታዊ ጣልቃ ገብነት መምረጥ መቻል ነበረበት። ዋሃቢ (Wahhabi) እና አህባሽ (Ahbash) የተባሉት የእስልምና እምነት መንፈሳዊ ፍልስፍናዎች ካለ መንግስት ጣልቃ ገብነት በራሳቸው በነጻነት መፎካከር መቻል ነበረባቸው። የትኛው ይሻላል የሚለው ጥያቄ ለሙስሊሙ ህብረተሰብ ምርጫ እና ለስኮላሮች ክርክር መለቀቅ ነበረበት። በነገራችን ላይ ዋሃቢ የተባለው እምነት የመጀመሪያ አቀንቃኝ አብዱል ዋሃብ የሚባሉ በ17ኛው ክፍለ ዘመን ግድም በሳውዲ የነበሩ መንፈሳዊ ስኮላር ናቻው። የአህባሽ እምነት የመጀመሪያው አቀንቃኝ ደግሞ አብዱላሂ የሚባሉ በ20ኛው ክፍለ ዘመን (በዐፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት) በሐረር ኢትዮጵያ የነበሩ እና በዚያው ዘመነ መንግስት የተሰደዱ መንፈሳዊ ስኮላር ናቸው። ስለሆነም የአህባሽ እምነት ምንጩ ሐርረ ሲሆን ፍልስፍናው ጎልምሶ መንፈሳዊ ኃይል እንቅስቃሴ የሆነው በቤይሩት (ሊባነን) ይመስላል። ከዚህ ባሻገር ስለሁለቱ እምነቶች ፍልስፍና ምንነት እና ልዩነት መተረክ የዚህ ጽሑፍ ተልዕኮ አይደለም።

ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ያነሱዋቸው ሶስት ጥያቄዎች የመብት ጥያቄዎች መሆናቸውን ለማወቅ መጽሐፍ መግለጽ አያስፈልግም። ህገ

መንግስታዊ ጥያቄዎች ናቸው። የዲሞክራሲ ጥያቄዎች ናቸው። ይሁን እንጂ አምባገነን መንግስቶች ከፖሊስ፣ ከደህንነት፣ ከጦር ኃይል፣ ከእስር ቤት እና ከመሳሰሉት ተቋሞቻቸው በተጨማሪ ህዝብን ለመሰለል፣ ለመጨቆን እና ለመግዛት የሃይማኖት ተቋሞችን ይጠቀማሉ። የእነዚህ ተቋሞች ተግባሮች በመንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ መወሰን ሲገባው አምባገነኖች ተጨማሪ የፖለቲካ ስልጣን ምሶሶዎቻቸው ያደርጓቸዋል። ስለዚህ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን መጅሊሳችን የመንግስት የፖለቲካ ምሶሶ እንዳይሆን በራሳችን ቀጥተኛ ተሳትፎ በተመረጡ ሰዎች ይመራ የሚል ጥያቄ በ2004 ዓመተ ምህረት ባነሱበት ጊዜ ሟቹ አምባገነን አቶ መለስ የሰጣቸው ምላሽ አፈና እና ሽብር ነበር። የመጅሊሱ አባላት የህውሃት/ኢህአዴግ አባሎች ወይንም በጥቅም የተያዙ ሰዎች ነበሩ:: ስለዚህ አቶ መለስ ነባሩን መጅሊስ የሚፈልገው በምርጫ 97 ጨምሮ የስልጣን ምሶሶ በመሆን

እንዳገለገለው ወደፊትም ስልጣን ላይ ለመቆየት ድጋፍ የሚሰጥ ምሶሶ

(Support Pillar) እንዲሆነው ነበር። እንደሚታወቀው ሙስሊሙ ህብረተሰብ ድምጻችን ይከበርየሚል ሰላማዊ ትግል ሲጀምር የህውሃት/ኢህአዴግ መሪ አምባገነኑ አቶ መለስ በህይወት ነበር። ብሄራዊ ደህንነት በሚል ሽፋንጦር ሰራዊት፣ ፖሊስ እና ደህንነት በሙስሊም ህብረተሰብ ላይ የሚፈጸመውን የአፈና እና የሽብር ፖሊሲ ከነደፈ እና የነደፈውን ፖሊሲ አፈጻጸም ከ6 ወሮች በላይ ከመራ በኋላ ነበር ስለመታመሙ የተሰማው። ይሁንና የአፈናው እና የሽብሩ ፖሊሲ ግብ (አላማ) በፍራቻ ሙስሊሙ ህብረተሰብ መጅሊሱን አሜን ብሎ እንዲያስረክብ ለማድረግ ነበር። ዛሬም የሟቹ አምባገነን (የወንበሩ ሳይቀር) አምላኪ የሆኑት የኢትዮጵያ ገዢዎች በሙስሊሙ ህብረተሰብ ላይ እየፈጸሙ ያሉት ፖሊሲ ያንኑ በአቶ መለስ የተነደፈውን ፖሊሲ ነው። ሙስሊሙ ህብረተሰብ ግን ፍራቻን ሰብሮ ሰላማዊ ትግሉን ቀጠለ። ህውሃት/ኢህአዴግ የኦርቶዶክስ እምነት ተቋምንም የስልጣን ምሶሶው ለማድረግ ላለፉት 20 አመቶች ያህል በተቋሙ ውስጥ ሲፈጥር የነበረው ክፍፍል ዛሬም ቀጥሏል። የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ከመናደድ እና ከመሳደብ ወይንም ጠረጴዛ ከመምታት ያለፈ የፈጸሙት በአይን የሚታይ ተግባር የለም። የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች እንደ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ቀጣይነት ያለው ህዝብን ያሳተፈ ተመሳሳይ እርምጃ ሲወስዱ አላየንም። ሙስሊሙ ህብረተሰብ ከዐርብ ጸሎት በኋላ በየሳምንቱ ከአንድ አመት በላይ የሚፈጸምባቸው አፈና እና ሽብር ሳይበግራቸው ድምጻችን ይሰማየሚለውን አቤቱታቸውን በአደባባይ ለአገር እና ለውጭው አለም አሰምተዋል። የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችም እጅህን ከቤተ ክርስቲያናችን ላይ አንሳወይንም የሙስሊም ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ድምጽ ይሰማበሚል እሁድ ከጸሎት በኋላ ተመሳሳይ ሰላማዊ ትግል አድርገው ቢሆን ኖሮስ? የሆነው ሆኖ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች መብታቸውን ለማስከበር ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ተደርጎ የማይታወቅ በድስፕሊን የታነጸና ቀጣይነት ያለው ሰላማዊ ትግል በማድረግ ኢትዮጵያ የማትረሳው ታሪክ ሰርተዋል!!!

የኢትዮጵያ መንግስት በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ላይ እየፈጸመ ያለው አምባገነናዊ ወከባ፣ ጫና፣ አፈና እና ሽብር ብዙ ጉዳቶች አሉት። ጥቂቶቹን እንጥቀስ፥

1) ለአክራሪዎች መመልመያ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ችግሩ እንዲባባስ ያደርጋል፣

2)ህዝብ ለመንግስት ትብብሩን እንዲነፍግና በህዝብ መዋጮ የተጀመሩ ልማቶች ከፍጻሜ እንዳይደርሱ ያደርጋል፣

3)ለገበያ የሚቀርብ ምርት እንዲያቆለቁል እና የአገርበቀል ኢኮኖሚ እድገትን ያግዳል፣

4)የሃይማኖት ዘመዶቹን ጥያቄ ፍትሃዊነት ያጤነ ባለስልጣን ለመንግስት ትብብሩን እንዲነፍግ ያደርጋል፣

5) የሌሎች አገሮች ዜጎች የሆኑ የሃይማኖት ዘመዶቻቸውን ድጋፍ እና ምክር ለማግኘት ወደ ግብጽ እና ወደ መሳሰሉት አገሮች እንዲሄዱ በማድረግ አገራዊ ጸጥታ እና መረጋጋት የሚዳከሙበትን በር ይከፍታል፣

ስለዚህ ዛሬ በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ላይ እየተፈጸመ ያለው አምባገነናዊ ጫና፣ አፈና እና ሽብር ካልቆመ መዘዙ ብዙ ሊሆን ይችላል። አምባገነነኑ ህውሃት

/ኢህአዴግ በሙስሊሙ ህብረተሰብ ላይ እንደፈጸመው ኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክሶችን የፕሮቴስታንት ሃይማኖትን እንዲቀበሉ ቢያስገድድ ኖሮ ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ታሪክ አለን። በ17ኛው ምዕተ አመት መጀመሪያ ግድም (1633 ዓመተ ምህረት) የጎንደሩ ፋሲል (ፋሲለደስ) አባት ዓጼ ሱስንዮስ (Emperor Susenyos) እያረጀ በመሄድ ላይ የነበረውን ዘውዳዊ አገዛዙን ለማደስ እና ቴክኖሎጂ (ዘመናዊ ትምህርት) ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት ኋላቀር ኢትዮጵያን ለመለወጥ እና ወደ ቀድሞ ታላቅነቷ ለመመለስ ተመኘ። ይህን ግቡን ተፈጻሚ ለማድረግ በዚያን ዘመን የአለም ኃያል አገር ከነበረችው ስፔይን መንግስት ጋር ተወዳጀ። የወዳጅነት መገለጫው ከሮሙ ጳጳስ የካቶሊክ ሃይማኖትን መቀበል እና

መለስ ይህን ታሪክ ያውቃል። የዚህ ታሪክ ጸሐፊ የሆኑት ተክለ ጻዲቅ መኩሪያ በውንጌት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ አስተምረውታል። ከዚህ ታሪክ መማርን ያልመረጠው የፈለገው ትርምስ እስር እና ሞት ቢከተልም የእስልምና ህምነት ተቋም የሆነው ነባሩ መጅሊስ እንደቀድሞ የስልጣን ምሶሶው ሆኖ እንዲቀጥል በመምረጡ ነው። ለተጀመረው ሰላማዊ ትግል ህገ

መንግስታዊ ምላሽ በመስጠት ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ እንዲባሉ ከማድረግ መቆጠብ ነበረበት። የአቶ መለስ የአገር ደህንነት ምክር ቤት የአቶ መለስ ስልጣን ደህንነት መጠበቂያ ምክር ቤት ማለት ነው። በየስብሰባው የዚህን ምክር ቤት ውይይት ትልቁን ቦታ ሲይዝ የነበረው አጀንዳ በአካባቢና አገራዊ ምርጫ ላይ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ድጋፉን ይነፍገናል ወይንስ አይነፍገንም የሚለው ነበር። ለእነ አቶ መለስ ስጋታቸው ስልጣን ነው። በዚህ በያዝነው በመጋቢት ወር (2013) “ከአቶ መልስ ቢሮ የወጣ ሚስጥራዊ ሰነድበኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ የካቶሊክ እምነትን በሃይል መጫን ነበር። ይህን ማድረግ ቀላል አለመሆኑ ለንጉሰ ነገስቱ ስውር ባይሆንም የኢትዮጵያን ታላቅነት መልሶ የማምጣት ምኞቱ ስለበለጠበት የኢትዮጵያ ዋንኛ እምነት የካቶሊክ ሃይማኖት ነው ሲል አወጀ። የኦርቶዶክስ ካህናት ህዝቡ እንዲቃወም አስተባበሩ። በሰሜን ኢትዮጵያ ህዝብ በመንግስት ላይ አመጸ። ኦርቶዶክስ በመንግስት ላይ መንግስት ደግሞ በኦርቶዶክስ እምነት አማጺያን ላይ ጦርነት አወጁ። ምድረ ካህናት ለዕምነትህ በመሞት ሰማዕትነት እንዳያመልጥህ እያለ በጎንደር፣ በመረብ ምላሽ (ዛሬ ኤርትራ)፣ ትግራይ፣ ጎጃም፣ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ አጥብቆ ተዋጋ። ብዙ ደም ፈሰሰ። ነጉሰ ነገስቱ እራሱ የመራቸው በርካታ ጦርነቶች ተደረጉ። በመጨረሻ ሊያሸንፍ እንደማይችል አመነ። በከንቱ በፈሰሰው ደም እና ባለቀው ህዝብ መጠን አዘነ። ስልጣኑን በገዛ ፍቃዱ ልልጁ ለፋሲል (ፋሲለደስ) ለቀቀ። ስለዚህ ከዚህ ታሪክ የንጉሰ ነገስቱ ምኞት ጥሩ ቢሆንም በኃይል እምነት ለማስቀየር ስህተት ነበር። አምባገነኑ አቶ የሚል በየ ድህረ ገጹ የሚገኝ ሰነድም የሚያረጋግጠው ይህንኑ ነው።

እርግጥ ነው የተወሰኑ ሙስሊም ወንድሞቻችን አክራሪ ሊሆኑ ይችላሉ። ግን ጥቂት ናቸው። ኢትዮጵያ የክርስቲያን አገር መሆን አለባት የሚሉ ጥቂት አክራሪ ክርስቲያን ወንድሞች እንዳሉንም መዘንጋት የለብንም። አብዛኛው ሙስሊም እና ክርስቲያን እትዮጵያዊ ህግ አክባሪ፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው ግብር ከፍሎ የሚያድር ሰላማዊ ህዝብ በመሆኑ ጥቂት አክራሪዎች የፈለጉትን ቢሉ የመጅሊሱን ቁጥጥር ለሙስሊሙ ህዝብ መልቀቅ መንግስትን ሊያሰጋ አይገባም ነበር። ስጋቱ የመነጨው መጅሊሱ ነፃ ከሆነ አንድ የስልጣን ምሶሶ ማጣትን ስለሚያስከትል ነበር። ሽብርተኛው በሽብር ተወልዶ፣ በሽብር አድጎ፣ በሽብር ለስልጣን በቅቶ፣ ዛሬም በሽብር ኢትዮጵያን በመግዛት ላይ የሚገኘው የህውሃት

/ኢህአዴግ ድርጅት ባለስልጣኖች እና ካድሬዎች ናቸው እንጂ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች አይደሉም። በኢትዮጵያ ጥቂት አክራሪ ሙስሊሞች እና ጥቂት አክራሪ ክርስቲያኖች የፈለጉትን ቢሉ ብዙሃኑ ሙስሊም እና ክርስቲያን ህዝብ አይተባበርም።

በታሪካችን ከነብዩ መሐመድ ስብከት በኋላ የእስልምና እና የክርስትና እምነቶች ጎን ለጎን እስከዛሬ አብረው ኖረዋል። እስልምና ኢትዮጵያ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ እስከ

13ኛው ምዕተ አመት ድረስ በሁለቱ ሃይማኖቶች መካከል ግጭት ስለመኖሩ የተጻፈ ታሪክ አላየሁም። ከ13ኛው እስከ 16ኛ ምዕተ አመት ድረስ በነበረው መካከለኛ ክፍለ ዘመን ግን ማለትም ከይኩኖ አምላክ መንግስት መነሳት (13ኛው) ምዕተ አመት ጀምሮ እስከ ይማም አህመድ (ግራኝ በሚል የሚታወቁት ኢትዮጵያዊ) ታላቅ ወታደራዊ ስትራተጂስት መነሳት (16ኛው) ምዕተ አመት ድረስ ሁለቱ እምነቶች በሰላምም በግጭትም አብረው ኖረዋል። በዚህ መካከለኛው ክፍለ ዘመን ከሁለቱም ወገኖች እነ

ሰዓዲን እና አምደ ጽዮን

(ንጉሰ ነገስት) የመሳሰሉ ብዙ ታላላቅ ወታደራዊ ጀግኖች ተነስተዋል። ግጭታቸው በአብዛኛው የኢኮኖሚ ሲሆን በዚያን ዘመን የነበሩት አባቶቻችን ግን የሃይማኖት ትርጉም እየሰጡት ብዙ ደም ተፋሰዋል። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች ክርስቲያን ገዢዎቻቸውን ከድተው ሙስሊም መሪዎችን እየተቀላቀሉ ክርስቲያን ገዢዎችን ይወጉ ነበር። ሙስሊሞቹም ተመሳሳይ ነገር ይፈጽሙ ነበር። ያም ሆነ ይህ በዚህ ዘመን ትልቁ ጦርነት በልብነ ድንግል እና በይማም አህመድ መካከል የተደረገው ነበር። በዚያ ዘመን ሲካሄድ የነበረውን ጦርነት በቦታው ተገኝቶ የጦርነቱን ሁኔታ በጽሑፍ ያሰፈረው ሰው ዓረብ ፋቂህ እንደሚባል እና ዓረብ ፋቂህ የጦር አለቆች በሙሉ ብረት ለበስ የሆነ ነገር ለብሰው ከአይናቸው በቀር የቀረው ሰውነታቸው እንደማይታይ እና በሁለቱም ተዋጊዎች ዘንድ ከተፈጸሙት ጽኑ የጨበጣ ውጊያዎች ውስጥ አንዱን ውጊያ እንደሚከተለው እንደሚያትት ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ ያመለክታል፥ ልጓም ከልጓም፣ ስይፍና ጦር፣ ጎራዴና ጋሻ፣ እርስ በርሱ እየተጋጨ፣ የፈረሶቹ ማስካካት ከወታደሩ ጩኸት ጋር እያስተጋባ አየሩ በአቧራ እስኪሸፈን ድረስ ወታደር እርስ በርሱ ተራኮተይላል። ዓረብ ፋቂህ ያ ዘመን ምን ይመስል እንደነበር በአጭሩ እንድንመለከት ስላደረገን ሊሚሰገን ይገባል። በዚያ በመካከለኛው ክፍለ ዘመን ሁለቱ እምነቶች በሰላምም በግጭትም አብረው ኖረዋል። ከዚያም በኋላም ግጭቶች ነበሩ። በሰላም አብሮ መኖርም እንደዚሁ። ይሁን እንጂ ሙስሊም ወገኖቻችን በገዛ አገራቸው እስከ ደርግ ዘመን ድረስ ሃይማኖታቸው ይጨቆን ነበር። ስለዚህ የቀድሞ ታሪካችንን ስናስታውስ እና የዛሬው ሙስሊም ህብረተሰብ መብቱን ለማስከበር የመረጠውን የትግል ዘዴ ስናገናዝብ ካለ ምንም ማወላወል የኢትዮጵያ ሙስሊሞች በኢትዮጵያ የማይረሳ ታሪክ ሰርተዋል እንላለን። ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የማይረሳ ታሪክ ሰርተዋል!!!

ሰላማዊ ትግሎችን በደቡብ አፍሪካ፣ በኬኒያ፣ በናጄሪያ አይተናል። ኃይል የተቀላቀላቸው፣ ጭፈራ እና ግርግር የበዛባቸው ናቸው። በቀላሉ ከቁጥጥር ሊወጡ እና ለመንግስት ጥቃት በር ሊከፍቱ ይችላሉ። በአንጻሩ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ከአንድ አመት በላይ ያካሄዱት ሰላማዊ ትግል ግን በአቅሙም ሆነ በሰላማዊነቱ የሰለጠነውን አለም መንግስታት፣ ምሁራን እና ስኮላሮች ሳይቀር ያስደነቀ እና ያስቀና ነው። የስልጣን ምሶሶ

(መጅሊስ) ማጣት ሆኖባቸው ነው እንጂ የህውሃት/ኢህአዴግ አባላት ሳይቀሩ ተደንቀዋል። ሽንፈታቸውን ከተቀበሉ ለሌላው ተቃዋሚ ትምህርት ይሆናል በሚል ስጋት ነው እንጂ ከገቡበት ማጥ ለመውጣት ማሰብ ከጀመሩ ከርመዋል። አዎ! ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የማይረሳ ታሪክ ሰርተዋል!!!

ሰላማዊ ትግልን አስመልክቶ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ከአንድ አመት በላይ ሳይታክቱ ከሞላ ጎደል የሚከተሉትን በተግባር ግልጽ አድርገውልናል፥

1) ህዝብ የሚያምንበት ግብ፣ ድርጅት እና አመራር ከተገኘ ቀጣይነት ያለው ሰላማዊ ትግል ማድረግ ይቻላል።

2) በሚሊዮን የሚቆጠር የሰላም ትግል ሰራዊት የሚሳተፍበት ሰላማዊ ትግል ማደራጀት ከቻልን የመሪዎች መታሰር ሰላማዊ ትግሉን አያቆመውም።

3) በአንድ ጊዜ በተለያዩ ከተሞች እና ክፍለ ከተሞች ብዙ ሺዎች የሚሳተፉበት ሰላማዊ ትግል የአምባገነኖችን አቅም ይበታትናል። ትግሉ ከሳምንት በላይ ቀጣይነት ካለው የስልጣን እድሜውም ሊያጥር ይችላል።

4) ሚሊዎኖች (ብዙ ሺ) ሰዎችን ባሳተፈ ሰላማዊ ሰልፍ ውስጥ የሚገኙ ተሳታፊዎችን መንግስት የሚያስርበት እሰር ቤት የለውም። ሚሊዮኖች ፖሊሶችም የሉትም። ሚሊዮኖችን አስሮ መቀለብም አይችልም።

5) ሰላማዊ ትግል ሙስሊም እና ክርስቲያን ኢትዮጵያውያንን እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የማቀራረብ አቅም አለው። ለምሳሌ ያህል በኢትዮጵያ ሙስሊሞች እና ክርስቲያኖች ቢቃቃሩ መንግስት ይፈልግ ነበር። ሰላማዊ ትግል ግን እንዲቀራረቡ አደረገ። የመንግስት ምኞት ከሸፈ።

6) ሰላማዊ ትግሉ ቀጣይነት ያለው፣ በድስፒልን የታነጸ እና ሚሊዮኖችን (ብዙ ሺዎችን) ያሳተፈ ከሆነ የአለም አቀፍ ህብረተሰብን ትብብር በቀላሉ እና በፍጥነት ያገኛል። በአንጻሩ አምባገነናዊ መንግስትን ከአለም አቀፍ ህብረተሰብ በፍጥነት እንዲገለል ያደርጋል። የኢትዮጵያ መንግስት ከውጭ መንግስታት እየደረሰበት ያለው ወቀሳ ይህንን ሃቅ የሚያረጋግጥ ነው። በተለይ በለጋሽ አገሮች የሚተዳደር መንግስት ለረጅም ጊዜ መወቀስን መሸከም አይችልም። ለፖሊስ፣ ለጦር ኃይል፣ ለደህንነትና ቁጥር ስፍር ለሌለው ካድሬ የሚከፍለው ደሞዝ ሊያጣ ይችላል።

7) ሰላማዊ ትግል በመንግስት ውስጥ ክፍፍል ይፈጥራል።

8)ሰላማዊ ትግል ለአክራሪዎች እና ለሽብርተኞች (መንግስትን ጨምሮ) እድል አይሰጥም። ለምሳሌ በአረቡ አለም አልቃይዳን ያዳከመው የአረብ አምባ ገነን መንግስታት ጦር ኃይሎች፣ ተዋጊ ጀቶች፣ የባህር ኃይሎች፣ ፖሊሶች፣ የስለላ እና ደህንነት ኃይሎች ሳይሆኑ በቱንሲያ፣ በግብጽ፣ በየመን የነጻነት አደባባዮች የተደረጉት ሰላማዊ ትግሎች እንደሆኑ መርሳት የለብንም።

9)በድስፕሊን የታነጸ ሰላማዊ ትግል ለመንግስት ከፍተኛ ጥቃት ቀዳዳ አይከፍተም።

10)በሰላማዊ ትግል ላይ የመንግስት አፈና፣ ወከባ፣ ጫና እና ሽብር እየጨመረ በሄደ መጠን የሰላማዊ ትግል ሰራዊት ከአገር ውስጥ እና ከውጭው አለም የሚያገኘው ድጋፍ በፍጥነት ያድጋል። በአንጻሩ መንግስት በዚያው ፍጥነት ወደ ቀብሩ ይሄዳል።

11)የመብት ጥያቄ የዲሞክራሲ ጥያቄ መሆኑን እና የዲሞክራሲ ጥያቄ ደግሞ የመላው ህብረተሰብ ጥያቄ መሆኑን የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሰላማዊ ትግል እንድንገነዘብ ረድቶናል።

በተጨማሪ ይህ በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ያለው ሰላማዊ ትግል በሶማሊያ፣ በሱዳን እና በኤርትራ አዎንታዊ አስተዋጽዎ እንደሚኖረው እና ሰላማዊ ትግልን የወደፊቱ የምስራቅ አፍሪካ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ፍትህ ማምጫ ተመራጭ የትግል ዘዴ ሊያደርገው እንደሚችል እና በአንጻሩ የትጥቅ ትግል

(እርሰ በርስ ጦርነት) ባህልን ወደ ሙዚየም እንደሚሸኘው መገመት አያዳግትም። እንደ እኔ ከሆነ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር በኢትዮጵያውያን ሙስሊም ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የተሰራው የማይረሳ ታሪክ በኢትዮጵያ ተውስኖ የሚቀር ሳይሆን በመላው ምስራቅ አፍሪካ አገሮች እንደሚሰራጭ ምንም ጥርጥር የለኝም። የማይረሳ ታሪክ ተሰርቷል!!!

ይሁንና በአሁኑ ጊዜ ይህ በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለው ሰላማዊ ትግል በአብዛኛው መንግስትን በመቃወም እና በማግባባት ላይ ያተኮረ አቤቱታ ሲሆን አንዳንድ የህውሃት

/ኢህአዴግ ካድርዎች በሞሉት መጅሊስ የሚመሩ መስኪዶችን ደግሞ ባዶዋቸውን በማስቀረቱ ደግሞ ሁለተኛውን ትብብር መንፈግ የተባለውን የሰላማዊ ትግል መሳሪያም በተወሰነ ደረጃ መጠቀሙን እናስተውላለን። ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ ተቃውሞና ማግባባት (Protest and Persuasion) የተባለውን አንደኛውን የሰላም ትግል መሳሪያ በስፋት በመጠቀም ላይ ያለ ይመስላል። ለማንኛውም የሰላም ትግል መሳሪያዎች በቁጥራቸው 200 ያህል ሲሆኑ ለጥናት እንዲያመች በሶስት አብይ ክፍሎች ተከፍለዋል። እነሱም (1) ተቃውሞና ማግባባት (Protest and Persuasion) (2) ትብብር መንፈግ (non-cooperation) እና (3) ጣልቃ መግባት (intervention) ይባላሉ። እነዚህ የሰላም ትግል መሳሪያዎችን ከዚህ በፊት በኢትዮሚዲያ፣ በኢትዮጵያ ይታተም በነበረው በፍኖተነፃነት ጋዜጣ እና በቪኦኤ አማረኛው ስርጭት ፕሮግራም ላይ በተደረጉ ውይይቶች በሰፌው ቀርበዋል። አሁንም የፍኖተነፃነት ጋዜጣ የቀድሞ እትሞች በአንድነት ፓርቲ ድህረ ገጽ ላይ ስለሚገኙ ከቁጥር 4 እስከ ቁጥር 34 (ከነሃሴ ወር 2003 እስከ የካቲት ወር 2004 ዐመተ ምህረት) በታተሙት ጋዜጣዎች ላይ ማግኘት ይቻላል። እንዲሁም ከአምባገነን ወደ ዲሞክራሲ በሚለው በጂን ሻርፕ መጽሐፍ ውስጥ በሰፊው ተተንትነዋል። ይኼን መጽሐፍ በተለያዩ ቋንቋዎች ከአልበርት አነስታይን የሰላም ትግል ምርምር ድረ ገጽ (http://www.aeinstein.org) በነጻ ማግኘት ይቻላል።

በመጨረሻ ማንሳት የምፈልገው ጉዳይ ህውሃት

/ኢህአዴግ ሰላማዊ ታጋዮችን መፍትሄ ፍለጋ ጫካ እንዲገቡ እንዳደረገው ጥቂት የሙስሊም እምነት ተከታዮችንም ወደ ግብጽ እንዲጓዙ ማድረጉን በሚመለከት ነው። ከግብጽ ኢማም የተሰጠንን ምክር በፊዲዮ ስርጭት ድረ ገጾች (You Tubes) አይተናል። የኢማሙን ምክር ይዘት ለመረዳት የኮሌጅ ትምህርት አንሻም። የምክሩን ይዘት ስንመረምረው እንደ እነ ጂን ሻርፕ ከአምባገነን ወደ ዲሞክራሲ የምንጓዝበትን መንገድ የሚመክር ሳይሆን የግብጽን ጥንታዊ ስውር የውሃ ፖለቲካ ዋስትና ፖለቲካ (ጥንታዊውን የአባይ ውሃ ባለቤትነት ምኞት) ማስፈጸሚያ የሚሆን ኢትዮጵያን የምናዳክምበትን ምክር ነው የለገሰን። ትግሉ የመብት ትግል ሳይሆን በክርስቲያን መንግስት እና በሙስሊሞች መካከል የሚደረግ ትግል አድርጎ ነው ያቀረበልን። ደካማ ምክር ነው። ለዲሞክራሲያ የሚያታግል ዜጋ ከግብጹ ይማም ስብከት የሚፈልግ ከሆነ ላም ባልዋለበት ኩበት ፍለጋ አይነት ነው። መፍትሄው ዲሞክራሲ ነው። አምባገነኖች ዲሞክራሲ የላቸውም። ህውሃት/ኢህአዴግ ሽብር እንጂ ዲሞክራሲ ባህሉ አይደለም። ነፃ አውጪ ነኝ የሚል ከማንኛውም የኢትዮጵያ ጫካም ሆነ ከኤርትራ የሚመጣው አምባገነን ነው። ከግብጽም የሚመጣው አምባገነን ነው። ዲሞክራሲ የሚመጣው ከራሷ ከኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ህዝቡ ነው ለራሱ ዲሞክራሲን ሊሰጥ የሚችለው። ሙባረክ ለግብጽ ህዝብ ዲሚክራሲን ሳይሰጥ ነበር እሰር ቤት የገባው። ለግብጽ ህዝብ ዲሞክራሲን የሰጠው እራሱ ህዝቡ ነው። በተለያዩ ከተሞች፣ በሚሊዮኖች በመውጣት በድስፕሊን የታነጸ ያልተቋረጠ ሰላማዊ ትግል ማድረግ ነው መፍትሄው። በታሪክም የሚያኮራ ሚና አይደለም። በደህንነት ሽፋን መንግስት የስልጣን ምሶሶውን (መጅሊሱን) ለማቆየት ሲል በሙስሊም ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ሰላማዊ ትግል ላይ የሚፈጽመውን ሃሰት ፕሮፖጋንዳ በአንድነት ልንታገለው ይገባል። መጅሊሱን ያስረክብ። ኦርቶዶክስ በተክርስቲያንንም ይልቀቅ። ሙስሊሙ ህብረተሰብ ታሪክ ሲሰራ የክርስቲያኑ ህብረተሰብ ክፍል ቆሞ ተመልካች እና ምስክር መሆን በቂ አይደለም።

አሁንም በድጋሚ መፍትሄው ዲሞክራሲ ነው። የተወሰነ ህብረተሰብ ክፍል ብቻውን ታግሎ ዲሞክራሲን ለመላው ህብረተሰብ ሊያመጣ አይችልም። አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል በሰላማዊ ትግሉ ውስጥ ድርሻ ሊኖረው ይገባል። የሰላማዊ ትግሉን ኃላፊነት መከፋፈል ያስፈልጋል። ስለዚህ ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ እውን ለማድረግ ሰላማዊ ትግሉ ከአንድ ህብረተሰብ ክፍል ተሳትፎ ወደ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ መሸጋገር አለበት። ዲሞክራሲ አደባባይ (የዛሬው መስቀል አደባባይ) መገናኘትን ይጠይቃል!!!

Latest from Blog

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

Go toTop