ተናገር ማህደር
ተናገር ዝክሩ
በዚያች በኛ ሀገር
ከቀየ እስክ ደብሩ
ተናገሪ ቋራ አንች ትንሽ ሰፈር
ማነን አንደወለድሽ ያስከበረ ሀገር
ተናገሪ ደግመሽ ማን እንደገደለው የት ላይ እንደሞተ
ለምንስ ሽጉጡን ወደ አፉ ከተተ
ተናገር መተማ አንት ጨካኝ በረሃ
ጀግናችን ያስቀላህ ሳታጠጣ ውኃ
አንተ አውሊያም በረሃ ለድርቡሽ ያደላህ
የቅዱሱን ንጉሥ አንገት ቆርጠህ በላህ
የታሪክን መድበል በእሣት አስለበለብህ
ተናገር አድዋ ሣልሳዊ ግፉን
በምድር በሰማይ ወገን መደብደቡን
ለሦስቱ ቀለማት ለኢትዮጵያ ባንዲራ
ጀግና እንደ ጧፍ ሲቀልጥ ለሞቱ ሳይፈራ
ጠላት አፍሮ ሲሄድ በምኒልክ ተራ
ተናገር አድዋ ስንቱ ጀግና ሞቶ ስንቱ ተረፈልህ
ባትናገር አንኳን መመዝገብ አለብህ
ስማቸውን ዘርዝር በማዕረግ ለይተህ
ተናገር ሳትደብቅ የሆነውን ሁሉ
ምስክሮች የሉም አልቀዋል በሙሉ
ተናገር መጣጥፍ ተናገር ብዕሩ
የመዘገብከውን ገድል በየዱሩ
ተናገር አትፍራ ያን መጥፎ ወረራ
የጅግኖችን እልቂት በጥሊያን አሞራ (አውሮፕላን)
በአርበኞች ጧፍነት ነፃነት ሲበራ
ወጨፎና መውዜር በምድር ሲያጉራራ
የአድዋ ተራራ መልሶ ሲጣራ
ሲሽመደመድ ሹምባሽ
ልቡ ጥላው ስትሸሽ
የኢትዮጵያ አርበኛ ደርሶ ምሽግ ሲያፈርስ
ደብቁኝ ሲል ጠላት መግቢያ ፈልጉልኝ
ዳግም አይለምደኝም የዛሬውን አውጡኝ
እምዬ ምኒልክ ታላቁ ንጉሥ
ከእንጦጦ ተነስቶ አድዋ ሲደርስ
መግቢያው ጠፍቷት ነበር የጠላቱ ነፍስ
ጦሩን ለጉበና እንዲመራው ሹሞ
ለኢትዮጵያ አርበኞች ካባውን ሸልሞ
ጥሊያንን ጉድ ሰራው አድዋ አምባ ቁሞ
ዓለምም ተደንቆ ብዕሩን አነሳ
ታሪክን በመክተብ አድዋን አወሳ
እንዲህ ነበር ያሉት ሀቁን ሳይደብቁ
እነሱ ያዩትን ሌሎችም እንዲያውቁ
አነዚህ ሐበሶች አሣቻ ፍጡሮች
ፍቅራቸውን እንጅ ጠባቸው አይመች
ተጠንቀቅ አውሮፓ ደግመህ አንዳትሞክር
ቁስሉ ተሎ አይሽርም ያሳረፉት በትር
አኛ ስንቃቸው ንቀውን ተገኙ
ጥሊያንን ገረፉት የሉሄ እያሰኙ
ተናገር አድዋ ይህን ሁሉ ጉድ
ትምህርት ነውና ለአሁኑ ትውልድ
ታላቁ ተራራ ሐውልት ይሰራልህ
የጀግኖችን አፅም እንድትይዝ ሰብስበህ
ብርድ አንዳይመታቸው ዕቅፍ ድግፍ አርገህ
ተናገር አሁንም የትናንቱን ዘመን
የታጨደብተን ወጣት እንደ ጎመን
ስንቱ ወጣት ሞቶ ስንቱ ተሰወረ
ስንቱ የሀገር ተስፋ በጥይት አረረ
የስንት እናት ማህፀን እርር ብሎ ቀረ
ተናገር መጣጥፍ ተናገር ብዕሩ
አስረዳ ለትውልድ ዙረህ በየደብሩ
*ተናገር ድጋሜ የትናንትናውን
ሃያ ሰባት ዓመት የተፈፀመውን
ሴቷን ልጅ አምክኖ ወንድ ያኮላሸውን
በልጇ አስከሬን ላይ ቁጭ በይ ያሰኘውን
አሬሣ ለመውሰድ ገንዘብ አስከፍሏል
አለቀስሽ በማለት ለእንግልት አብቅቷል
ወጣቱ ተሰዶ ዱካው አልተገኘም
ወይ ሙቷል ወይ አለ የሚል አይሰማም
የተፈፀመው ግፍ ተዘርዝሮ አያልቅም
መዘከር አለበት ለታሪክ ቢጠቅም
ተናገር መጣጥፍ ተናገር ዝክሩ
አስረዳ ለትውልድ ዙረህ በየደብሩ
መነገር አለበት
መመዝገብ አለበት
አሁንም ቀጥሏል
ሰቆቃው ጨምሯል
ወገን በወገኑ ክፉኛ ጨክኗል
ይመከር ትውልዱ
ሳይገለጥ ጉዱ
ከተጠያቂነት ማምለጥ አይቻልም
በጊዜ ዳኝነት ማንም አይማርም
ተናገር ሳትደብቅ
መዛግብትን ጠብቅ
ይሁነው ትሩፋት ለዚህ ትውልድ ስንቅ
ትውልዱስ በተራው ምን ነው እሚጠብቀው
በአጥንትና በደም ክዘር የወረሰው
የአባት ጋሻ ለልጅ መሆኑን በማወቅ
ለእናት ሀገሩ ክብር አለበት መዋደቅ
ተናገር ሳትደብቅ የሆነውን ሁሉ
ምስክሮች የሉም አልቀዋል በሙሉ