“ትህነግ”: በሞተ ርዕዮተ-ዓለም የሚመራ፣ ለውጥን የሚፈራ ድርጅት – ስዩም ተሾመ

ድሮ ድሮ ቆሞ ቀሩ ትህነግ የሁኔታ ግምገማና ትንተና አፈፃፀሙን የሚስተካከለው የሌለ ይመስለኝ ነበር። እነሆ በዚህ ሰሞን የማዕከላዊ ኮሚቴ ውይይቱ ደረስኩበት ያለው ድምዳሜ፣ ራሱን፣ የትግራይ ህዝብን፣ ሌሎች የአገራችን ህዝቦችና ተፎካካሪ ፓርቲዎችን እንዲሁም ጎረቤት አገር ኤርትራን የተመለከተበትና ለመልዕክተ ድምዳሜ የደረሰበት የሁኔታ ትንተና በዓለምና አገራችን ፖለቲካ የሌለ ያህል እንዲሰማኝ አድርጎኛል። ባለፉት 27 ዓመታት የተከላቸው የልዩነትና ጥላቻ መርዞችና ሞት አፋፍ ላይ ሆኖ ያደራጃቸው ሴራዎች እለት በእለት ከሽፈው እርቃኑን መቅረቱን ዘንግቶ፣ እርሙን በስሙ እየነገደበት ባለው የትግራይ ህዝብ ውስጥ ተሸጉጦ ከሰማይ የወረድኩ መሲህ ነኝ የምላችሁን ተቀበሉኝ ማለት ዳድቶታል።

ውስጣዊ ተፈጥሮው ባልሆነው የዴሞክራሲ ቃላዊ ሰበካ “ልማትና ዴሞክራሲን” በስም እየሰበከ፣ የአገራችን ህዝብ በለውጡ ያየውን አዲስ ተስፋ ለመቀልበስ ከሞት አፋፍ እየተንደፋደፈ ይገኛል። ከቆሞቀርነት ወጥቼ ወደ ለውጥ ካልገባሁ አበቃላኝ ከማለት ይልቅ፣ በፖለቲካ ቋንቋ ለውጡ አገራችንን ሊያጠፋት ነው፣ መጨረሻ ላይ ደርሰናል፣ እግዚኦ ማለቱን ተያይዞታል።

እድሜ ለለውጡ ትሩፋት ይሁንና ትህነግ ሲገዛትና ሞግዚት ሆኖ ሲቦጠቡጣት በነበረች አገራችን፣ ይህን መሰሉን የትህነግ የመፈንቅለ መንግስት ጥሪ ለሰራዊት ማድረግ ይቅርና፣ በመንግስት ላይ ያለ ቅቡልነት እንዲነሳ በግላጭ ማነሳሳት ይቅርና የተለየ ሀሳብ ማራመድ ጥፍር ያስነቅል፣ ብልት ያኮላሽ ነበር። በአሸባሪነት አስከስሶ እድሜ ልክ ግዞት ያስገባ ነበር።

ዛሬ ጨቋኟና ቆሞ ቀሯ ትህነግ እንዲቀለበስና መፈንቅል እንዲካሄድበት አቋም የያዘችበት የለውጥ መንግስት የዴሞክራሲ ሀሁን በተግባር አስተማራት። ቢያንስ የህዝብ ተቀባይነትና ተከታይ ወይም ገዥ በሌለው አብዮታዊ ዴሞክራሲ ፕሮግራሟ ላይ ቆማ ውህደትን መኮነን፣ መራገም ችላለች። በለመደችው አፈቀላጤነቷ በትግራይ ህዝብ ስር ተሸጉጣና በበሬ ወለደ ተረት “የትግራይ ህዝብ ጠላት ነህ” ተብለሃል በሚል አዲስ ትርክት በአማራና ሌሎች ህዝቦች ላይ ለዘመናት ስታራምድ የነበረውን የሀሰት ትርክት በአዲስ ነጠላ ዜማ ይዛ ብቅ ብላለች፣ ቆሞ ቀሯ ትህነግ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሽብርተኛው የኦህዴድ መንግሥት ፋኖን “ሽብርተኛ” ብሎ ሲከስ መላው ዓለም ታዝቦታል፤ንቆታል

ህገመንግስታዊ በሆነው ስርዓት በጋራ ለመኖር ፈቅደን ተስማምተናል ብላ ስትሰብክ እንዳልቆየች ሁሉ፣ ህገወጥነቷና ሴራዋ መክሸፉን በተደራች ጊዜ የመጨረሻ ዒላማዋን ለመምታት ባሰበችበት የመነጠልና የመገንጠል አባዜ “ የትግራይ ህዝብ ሆይ ከትግልህና ጥረትህ ውጪ መብትህንና ጥቅምህን ለማስጠበቅ ፈቃድ የሚሰጥህ ሌላ አካል የለም” በማለት የትግራይ ህዝብና የአገራችን ህዝቦች ጠላት ድህነት ነው ስትል የቆየችውን የዋሾ ፖለቲካ በቅቤ ምላሷ ህዝቡን ለማደናገርና በተለመደ እብሪቷ አብረን እንጥፋ የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ሞክራለች። እንግዲህ ትህነግን ቆሞ ቀር የሚያሰኛት ይህም ህልሟ ነው። ልክ የዛሬ 30 ዓመትና ከዚያ በፊት እንደነበረው ነፍጥ ነፍጥ ሸቶኛል ማለቷ፣ በስሙ የምትነግድበት ህዝብ ስልጣኔ፣ አገራዊና ዓለማዊ ሁኔታ መለወጡን ባለመረዳቷም ነው።

የትግራይን ህዝብ ምሽጓ አድርጋ ለመሟሟት የወሰነችው ትህነግ፣ ቢያንስ ለውጡ ለህዝቦች የሰጠው ዴሞክራሲ የትግራይ ህዝብ እንዳያጣጥመው ለማድረግ በተለመደ የአፈና ታክቲኳ የህዝቡን የተደበቀ ብሶት ሊያሰሙ የሚሞክሩ ፓርቲዎችን “ባንዳ” የሚል ስም እየሰጠች ከማሳደዷም በተጨማሪ በዚህ ተግባሯ እያፈረባት ያለውን የትግራይ ህዝብ “ገድል ፈፅመሃል፣ ገድል መስራትህን ቀጥል” በማለት ራሷ እየሰራች ያለውን ያለመለወጥና የሞት አፋፍ ሴራ ህጋዊና ቅቡል፣ የህዝብ ትግል ለማድረግም ትዳዳለች።

ከጫፍ ጫፍ ወደ መሻገርና ለውጥ የሚደረገውን የሰላም፣ የዴሞክራሲና የብልፅግና ሩጫ ለመቀላቀል ቆሞቀር ባህሪዋ የማይፈቅደው ትህነግ፣ አንድም ሩጫውን ለማስቆም ማምታታት፣ አለያም በዘራችው ልዩነትና ጥርጣሬ ጥፍጣፊ ወደ አንድ እየተሰባሰበና አገሩን ለማዳን እየተደመረ ያለውን ብሄር ብሄረሰብ በአሃዳዊነት ልትጨፈለቅ ነው በሚል የተለመደ ትርክቷ ልታደናግር ትሞክራለች፤ ይህን ብላ አቅም ያነሳት ሲመስላት ደግሞ “የተከበርከው መከላከያ ሰራዊት ህወሓት ከጎንህ ነው” በሚል የተባበረኝ አይነት ተማጥኖዋን ታቀርባለች።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አወይ ሶሪያ....የኢትዮጵያ ጠላት!

ትህነግ በዚህ ሳታበቃም በከፋፋይ አጀንዳዋ ያለያየችውን ህዝብና ለ20 ዓመታት ያጠፋችውን ወንድማማችነት ዘንግታ፣ በለውጡ ማግስት በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ በአገራችና በኤርትራ ህዝቦችና መንግስት መካከል ትህነግ አስተዋፅኦ ባላደረገችበት በለውጥ አመራሩ የተፈጠረውን የተስፋ ጭላንጭል እናጠናክረው ስትል የቀበሮ ባህታዊነቷን አጋልጣለች። በቋንቋና በባህል ተዛምዶ ለኤርትራውያን የቀረብነው እኛ ነን ስትል በህዝቡ ስም እጅ ስትነሳም፣ መሬት ስትስም ትታያለች።
ቆሞ ቀሯ ትህነግ የትግራይን ህዝብ ምሽግ አድርጋ ለውጡን ለመቀልበስም ሆነ ውህደቱን ለማክሸፍ የምታደርገው መንፈራገጥ የትም የሚያደርሳት አይደለም። በለውጡ ማግስት በተፈጠሩ የሰላም እጦቶች፣ ሞትና መፈናቀል፣ ረብሻና ስጋት ውስጥ ትህነግ እጇ አለበት ብቻ ሳይሆን የችግሩ ፈጣሪም ናት። ይህ ተግባርና ጥፋት የትህነግ የዛሬዋ ባህሪ አይደለም።

የያዘችውን አቋም ያሳካል ብላ እስካመነች ጊዜ ድረስ በራስዋ ህዝብ ላይ የዘረፈችውን ገንዘብ ረጭታም ጭምር በስሙ በምትነግድበት ህዝብ ላይ ጭምር አርማጌዶን ከማወጅ የምትመለስ አይደለችም። በትግራይ ምድር በህዝቡ ላይ በጨቋኞች የተካሄዱ በርካቶቹ ጥቃቶች ህዝቡን ለማሰባሰብና ለመያዝ በሚል በዘየደችው አረመኔያዊ ሴራ የተፈፀሙ ስለመሆናቸው፣ አብረዋት ተሰልፈው የነበሩት ሳይቀር የመሰከሩት ሀቅ ነው።
ለውጡ በመጣም ማግስት ትህነግ ያበቃላት መሆኗን ስትረዳ፣ በነበራት ኔትወርክና የተዘረፈ ገንዘብ በየክልሉና ዞኑ እንዲሁም ወረዳ በትግራይ ህዝብና በሌሎች መካከል ግጭትና መሳደድ እንዲፈጠር በማድረግ፣ ህዝቡ ሲሰደድም ተቀባይ በመሆን ኢሰብዓዊ የፖለቲካ ታክቲክ የተጫወተች አረመኔ ድርጅት ነች።

ትህነግ ለጊዜው ህዝቡን በማደናገርና የጠላትነት ስሜት እንዲፈጠርበት በመስራት ተሳክቶልኛል ብላ ብታስብም፣ ይህ አካሄዷ ረጅም ርቀት የማይወስዳት ለመለወጥ እስካልተዘጋጀች ድረስ ወደመቃብር የሚያወርዳትና የትግራይ ህዝብም በራሱ ትግል ከጭቆናና አፈፃ ቀንበር ነፃ እንዲወጣ የሚያስችለው እድል የሚያገኝበት ሁኔታ ነው የሚኖረው።
ስለ ውህደቱ ቅንጣት ግንዛቤ የሌላትና ይህን ለመተቸት የሞራል ሰብዕና ያልተላበሰችው ትህነግ፣ በውህደትና በአሃዳዊነት መካከል ያለው ልዩነት ግራ ገብቷት ሳይሆን፣ የጭቆና መረቧ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስላሳሰባት ፌዴራሊዝም ሊጠፋና ብሄሮች ሊጨቆኑ ነው ብላ ብሄረሰቦችን ቅራኔ ውስጥ ለመክተት ትጣጣራለች። ኢህአዴግን በስም ፈጥራ ስትዘውረው እንዳልነበረች፣ በዚህ አስተሳሰባዊ መዋቅሯም ጭቆናን እንዳላሰፈነች ሁሉ ህዝቡን “ኑ ከተፈጠረበት ዓላማ ውጪ ለጭቆና ስጠቀምበት የነበረውን ኢህአዴግ አድኑልኝ” ትላለች።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አማራ ኦሮማይ!!! ኦሮማይ ህገ-አራዊት!!! ፌዴራል መከላከያ የኦነግ ሠራዊት በአስቸኳይ ከአማራ ክልል ይውጣ!!!

የትህነግ ይህ ገለፃ የአየለ ጫሚሶን ቅንጅት ያስታውሰኛል። በ97 ምርጫ የኢህአዴግ የእግር እሳት የነበረውን ቅንጅት በተለያየ ሴራ ካፈረሰች በኋላ የአየለ ጫሚሶን ቅንጅት የፈጠረችው ትህነግ፣ ቅንጅት እንዲጠላ አየለ ጫሚሶ የተባለ አሪፍ ካራክተር አመጣችልን። ቅንጅት እኔ ነኝ ብሎ የወጣውን አየለ ጫሚሶን ያየው ህዝብ ቅንጅት የተባለውን ስም እርግፍ አድርጎ ጠላው። እናም ቅንጅት የሚል ቃል እንኳን በፓርቲ ስም በንግግርም የተጠላ ሆነ። ኢህአዴግም በትህነግ እስከወዲያኛው ተጠልቷል። እስካሁንም የቆየው ከዚህ ግንባር የወጡ ለውጥ አመራሮች “ህዝቡን በድለናል፣ ሰብዓዊመብት ረግጠናል፣ እናርማለን፣ እናሻግራለን” ስላሉ ብቻ ነው።

ውህደትና መደመር የዚህ ሽግግርና ማሻገር ማሳያ ነው። አለያማ ኢህአዴግ ካበቃለት ቆይቷል። የዚሁ ድርጅት መስራች የነበረችው ትህነግም ቢያንስ ይህን መረዳት በተቻላት ነበር። በአካል እንጂ በነፍስ ከሞተች የቆየች መሆኗን። እንግዲህ ትህነግ ለኢትዮዽያ ህዝቦች ጥሪ እያቀረበች ያለችው “ኢህአዴግን አድኑ” በሚል ነው። ለነገሩ ውህደት ይጠቅመናል፣ አጋሮች ሊዋሃዱ ይገባል ስትል የቆየችው ትህነግ እሷ የሌለችበት ስለሆነ ብቻ አጋሮች ይቅርባችሁ ማለቷ ለትዝብት የሚዳርግ ነው። ዳሩ ትህነግ ውስጥ ሼም የት አለና? እንደ ትህነግ ያለ ለውጥ ባመጣው ዴሞክራሲ ውስጥ ሆኖ መፈንቅል የሚጠራ ፀረዴሞክራሲያዊ ቆሞ ቀር ድርጅትስ ከወዴት ይገኛል? መጥኔ ለታጋሹ የትግራይ ህዝብ!!

ስዩም ተሾመ

1 Comment

  1. “Social Ethics” of TPLF:
    “ብዛዕባ ካሊእ እንታይ ኣእተወካ፣ ብዛዕባኻ ጥራሕ ሕሰብ!” “Principle” ተጠላሊምካ ሕደር ብፍላይ ኣብ ምድሪ ትግራይ ብሓፈሽኡ’ውን ኣብ መላ ኢትዮጵያ ንዝሓለፈ 40 ዓመታት!

Comments are closed.

Share