ሰማያዊ ፓርቲ “የዜጎችን ሰቆቃ እና በደል ችላ ማለት ከግፈኞች ጋር እንደመተባበበር ይቆጠራል” አለ

“የላንቻ ፖሊስ ጣቢያ ሃላፊዎች ሳዑዲ ኤምባሲ በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የተሳተፉና ታስረው በዋስ የተለቀቁ ዜጎችን በስልክ እየደወሉ በመጥራት ማስፈራሪያና ድብደባ እያደረሱ ነው፡፡ሃላፊዎቹ ከ3 ቀናት በፊት ወጣት ዮናስ ከድርን በስልክ በመጥራት በ2 ደህንነቶች የስደበደቡት መሆኑ የሚታወስ ሲሆን በትናንትናው እለትም በእለቱ ታስረው ለነበሩት በሙሉ ስልክ ደውለው የጠሯቸው ሲሆን በጉዳዩ ላይ በመነጋገር ህጋዊ መጥሪያ ካልተሰጠን አንሄድም የሚል ምላሽ ሰጥተው ሳይሄዱ ቀርተዋል፡፡” ሲል በፌስ ቡክ ገጹ የዘገበው ሰማያዊ ፓርቲ ለዘ-ሐበሻ በላከው መግለጫ “የዜጎችን ሰቆቃ እና በደል ችላ ማለት ከግፈኞች ጋር እንደመተባበበር ይቆጠራል” አለ። ሙሉ መግለጫው የሚከተለው ነው፦

ሰማያዊ ፓርቲ በሳውዲ አረቢያ የሚገኙ ዜጎቻችን ላይ የሳውዲ መንግስት እያደረሰ ያለውን እስራት፣ ስቃይ እና ግድያ በመቃወም እና ህይወታቸው ላለፈ፣ ለተደበደቡ እንዲሁም የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ህዝቡ ሃዘኑን እንዲገልጽ በመጪው እሁድ በሚደረገው ታላቁ ሩጫ ላይ የሚሮጡ ተሳታፊዎች ጥቁር ሪቫን አድርገው እንዲሮጡ ጥሪ ማስተላለፉ የሚታወቅ ነው፡፡
ይሁን እንጂ የታላቁ ሩጫ አስተባባሪዎች ይህንን ጥሪ እንደሚቃወሙት እና በፕሮግራሙም ላይ ጥቁር ሪቫን ያሰረ ተሳታፊን እንደተሳታፊ እንደማይቆጥሩ መናገራቸው ፓርቲያችንን እጅግ አሳዝኖታል፡፡ ፓርቲያችን ይህንን ጥሪ ሲያስተላልፍ አላማው ፍጹም ፖለቲካዊ አንድምታ የሌለው ሲሆን ጥያቄውም በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እና ግድያ እንዲቆም እና ፍትሃዊ እርምጃም እንዲወሰድ ለመጠየቅ ብቻ እና ብቻ እንጂ ሌላ አላማ እንደሌለው እየታወቀ የታላቁ ሩጫ አስተባባሪዎች ግን ጉዳዩ ከፖለቲካ ጋር ለማያያዝ መሞከራቸው የሚያስተዛዝብ እና ህዝባዊ ወገንተኝነታቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው፡፡
ስፖርት ሰላማዊ ነገር የሚሰበክበት እንዲሁም እኩይ ተግባራት የሚወገዙበት መድረክ ነው፡፡ በአለማችን ላይ በተለያዩ ጊዜያት በተከሰቱ አሰቃቂ ሰው ሰራሽ አደጋዎች በተለያዩ ስፖርታዊ ዝግጅቶች ላይ ሲወገዙ እንዲሁም ለሰለባዎች ሃዘን የመግለጽ ስነ ስርዓትና የህሊና ጸሎት ሲደረግ መመልከት የተለመደ ነው፡፡ ታዲያ በጠራራ ፀሀይ በአደባባይ እናት ልጆችዋ ፊት እንዲሁም ሴት ልጅ ቤተሰቦችዋ ፊት ስትደፈር ከማየት የዘለለ ምን እኩይ ተግባርስ ሊኖር ነው? ታዲያ ስፖርት ይህንን ካላወገዘ ምንን ሊያወግዝ ነው?
በመጨረሻም የታላቁ ሩጫ አስተባባሪዎች የፓርቲውን ጥሪ መቃወማቸው ፓርቲያችንን ያሳዘነ እና ያስቆጣ መሆኑን እየገለጽን አሁንም ፓርቲያችን በድጋሜ በዝግጅቱ ላይ ተሳታፊዎች ጥቁር ሪቫን አድርገው እንዲሮጡ እየጠየቀ ጥቁር ሪቫኖችን ማግኘት ለማትችሉ በሰማያዊ ፓርቲ ጽህፈት ቤት ተገኝታችሁ መውሰድ የምትችሉ መሆኑን እናስታውቃለን፡፡
ክብር ለዜጎቻችን ይሁን!!

ተጨማሪ ያንብቡ:  በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ከተማዋ ሊገባ የነበረ 49 ሺህ 300 ዶላር በቁጥጥር ስር ዋለ

1 Comment

  1. Boycott The Great Run or Show your solidarity with Ethiopian in Saudi Arabia, who has been killed and gang-raped by The Arab maniac Security Forces and vigilante Youth Groups, embossing Black Mourning badge at one arm. Go to Blue Party for The Black Mourning Badge for free.
    Show your compassion to your people. You are we and we are the People.

Comments are closed.

Share