እንደ ተከበሩና እንደ ኮሩ መሞት  – ጠገናው ጎሹ

September 29, 2019

ጠገናው ጎሹ

እንደ መግቢያ

ከራስ በላይ ወዶሽ ሊጋባው በየነ
እንደ ኮራ ሞተ እንደ ተጀነነ
ጠጅ ጠጣ ሲሉት ውሃ እየለመነ ።
ኧረ ምነው ፣ኧረ ምነው ምነው
ከሞተልሽ በላይ የወደደሽ ማነው?
ኧረ ምነ ፣ ኧረ ምነ ምነ
እንሞታለን እንጅ
እንደ ጀግናው ሊጋባው በየነ።
ኧረ ምነ ፣ኧረ ምነ ምነ
እንሞታለን  እንደ ተዋደድነ
እንሞታለን  እንዳማረብነ።

በድንቅ የውዝወዜና ድራማዊ አቀራብ ታጅቦ በአርቲስት ግዛቸው ተክለማርያም እጅግ ውብ የድምፅ ቅላፄና የማሲንቆ አጨዋወት ከቀረበው ቪዲዮ  ላይ ለጉዳዬ መነሻ እንዲሆነኝ የወሰድኩት ነው (ከአክብሮትና ከአድናቆት ጋር) ።

ኩራትና ከበሬታ (pride and digity) የህብረተሰብ መሠረት ከሆነው የቤተሰብ ማህፀን ተወልዶና አድጎ መልሶ ለተወለዱበትና ለአደጉበት ማህበረሰብ (አገር) በጎ ሥራን በማከናወን የሚገኙ የታላቅ ሰብእና መገለጫ ፅንሰ ሃሳቦች ናቸው።   ከአገራችን ሁኔታ አንፃር   በጥሞና ለሚያጤናቸው ደግሞ   ግዙፍና ጥልቅ የሆነውን የአገራዊ (የብሔራዊ) ማንነትን፣ ምንነትን፣ እንዴትነትንና ወዴትነትን የዋጋ ተመን በማይገኝለት የህይውት መስዋእትነት ለትውልደ ትውልድ ከማስተላለፍ የሚገኘውን የኩራትና የከበሬታ ልዕለ ኅያልነትን የመግለፅ አቅምን የተሸከሙ ቃላት ናቸው።

ቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን  የእናት ምድርን  (የኢትዮጵያን )  የዳር  ድንበርና  የሉአላዊነት  አይደፈሬነትን ከሚደርስባቸው የገዥዎች  (የነግሥታት)   በደልና ግፍ ጋር ሳያቀላቅሉ የውጭ ወራሪና ተስፋፊ ሃይል መጣ ሲባል የቀረበላቸውን የባንዳነትና የአድር ባይነት ጥያቄ ውድቅ በማድረግ  በየፍልሚያው አውድ ቀድሞ በመገኘት ከቶ ሊተካ የማይችል ህይወታቸውን  አሳልፈው የሰጡበት ወርቃማ ታሪክ  የአገራዊ ኩራትና ክብር መሠረት  ነው።  አገር ከሌለ ሌላው ነገር ሁሉ አይኖርምና።

ይህ ግዙፍና ጥልቅ የታሪክ እውነታ በለየለት ቅዠት (total illusion) ውስጥ ለሚቃዡ ፅንፈኛ የጎሳ/የዘር/የቋንቋ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ልክፍተኞች ከቶውንም የሚዋጥላቸው አይደለም። አይሆንምም።   መሪሩን እውነት መቀበል እያቃታቸው ሲያስመልሳቸው ይኖራሉ እንጅ በጋራ ደምና አጥንት የተመሠረቱት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት እነርሱ በቃዡ ቁጥር እንደ እንቧይ ካብ የሚናዱ ማንነቶችና ምንነቶች አይደሉም ። አይሆኑምም። በእርግጥ ይህ እንዳይሆን ሥራ ይጠይቃል

መግቢያዬ ላይ የጠቀስኩት የሙዚቃ ሥራ በታሪኩ ባለቤት (በሊጋባው በየነ) አማካኝነት የሚነግረንም ዘመን በማይሽረው ወርቃማ የተጋድሎ ታሪክ የተረከብናትን  ነፃና ሉአላዊት  አገር ለዜጎቿ ሁሉ የሚመች ሥርዓት ባለቤት እንድትሆን አስችሎ መሞት ምን ያህል  የኩራትና የክብር ሞት እንደሆነ ነው።

ይህ ትውልድ በቀደምት አባቶቹና እናቶቹ የህይወት መስዋእትነት የተረከባትን እናት ምድር  ነፃነቱና መብቱ የተከበረባት ዴሞክራሲያዊት አገር አድርጎ በአብሮነትና በጋራ ብልፅግና ለመኖር እንዴት እንደተሳነው እራሱን ከምር ጠይቆ የሚበጀውን ለማድረግ ፈቃደኛና ዝግጁ መሆን ይኖርበታል። ያለዚያ የሸፍጠኛ እና ፅንፈኛ የጎሳ/የዘውግ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ልክፍተኞች (እብዶች) በሚያዘጋጁለት ልክ የሌለው የስሜታዊነት ፈረስ እየጋለበና ከእራሱ የወደፊት እጣ ፈንታ ጋር እየተላተመ የመከራና የውርደት ህይወት (ህይወት ከተባለ) አዙሪት ውስጥ ሲጎጉጥ (ሲዳክር)  ይኖራል ።

የሙዚቃ (የኪነ ጥበብ)  ሥራዎች  በውስጣቸው  የተሸከሙትን ቁም ነገር  በጊዜያዊ የስሜታዊነት ፈረስ ከመጋለብ  ወጥቶ ከምር ለመረዳት ለሚሞክር ቅንና ብልህ የአገሬ ሰው  ከብዙ ንግግር (ዲስኩር) በላይ ሰፊና ጥልቅ ሃይል አላቸው።  ተራራዎችን ፣ኮረብታዎችንና  ሸንተረሮችን ከሸፈነው ደመና በታች እያንሳፈፈ “ይኸውልህ/ይኸውልሽ የአንተ/የአንች ቀደምት አባቶችና እናቶች  አጥንት ተነባብሮ  የተከሰከሰባትና  ደማቸውም ተቀላቅሎ  የፈሰሰባት ነገር ግን ዛሬ አንተ/አንች በየጎጡ /በየጎሳው /በየቋንቋው ተወሽቀህ/ተወሽቀሽ ካላጠፋኋት በሚል ያዙኝና ልቀቁኝ የምትልባት/የምትይባት   ቅድስ ምድርህ/ሺ ይህች ናት ” እያለ ውስጠ ነፍስን የሚሞግት ብርቱ ሃይል ።

የሊጋባው በየነ ድራማዊ ሙዚቃም ይዞን የሚነጉደው ለአገር ነፃነትና ሉአላዊነት ሲባል ደም ተቀላቅሎ ወደ ፈሰሰባቸውና አጥንት ተነባብሮ ወደ ተከሰከሰባቸው የእናት አገር ተራራዎች፣ ሸንተረሮች፣ ሸለቆዎችና ወንዞች ነው ። አዎ! ለአገርና ለወገን የሚተርፍ ታሪክ ሠርቶ እንደ ተከበሩ፣ እንደኮሩና እንዳማሩ የማለፍን (በሥጋ የመለየትን ) ጥልቅ ሚስጥርን ነው የሚነግረን ።  የተወዛዋዦች እንቅስቃሴ፣ የፈረሱ መቁነጥነጥና በሊጋባው በየነ ልብ ውስጥ የሚቀጣጠለው ጥልቅ የአርበኝነት ስሜት የሚነግረን ዛሬ ደንቆሮ የጎሳ/የዘውግ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ልክፍተኞች ርካሽ የግልና የቡድን ፍላጎታቸው ካልተሳካ እናፈራርሳታለን በሚል ያዙንና ልቀቁን የሚሉባት አገር የተመሠረተችበትን  የማይናወጥ መሠረት ነው።

የዚህ ትውልድ ውደቀት የሚጀምረው ሸፍጠኛ የኢህአዴግ ፖለቲከኞችንና ፅንፈኛ የጎሳ/የዘውግ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ነን ባዮችን እውቀትን፣ ምክንያታዊነትን ፣ ገንቢነትን፣ ግልፅነትን እና ቀጥተኝነትን  በተላበሰ የአርበኝነት መንፈስና ቁመና ከመሞገትና አደብ ከማስገዛት ይልቅ አሳፋሪ ለሆነ  የመሽኮርመም አባዜ ወይም “የባሰ ይመጣል” ለሚል የተሸናፊነት ስሜት ሰለባነት እራሱን አሳልፎ የሰጠ እለት ነው።

እናም  እኔስ/እኛስ እውን ተከብረን፣ ኮርተንና አምሮብን ለማለፍ (በሥጋ ለመሞት) እንድንችል የሚያስችለንን የነፃነት፣ የፍትህ፣  የእኩልነት ፣ የአብሮነት፣ የሰላምና የጋራ ብልፅግና ሥርዓተ ማህበረሰብን እውን ለማድረግ  ለምን ተሳነኝ/ተሳነን ? ብሎ መጠየቅና ትክክለኛውን ምክንያት ከነመልሱ  ማግኘት ያለብን ነገ ሳይሆን ዛሬ ነው።

በእውነት ከተነጋገርን  የጋራ ታሪካችንን ጥንካሬና ድክመት ከምር ተረድተንና ለይተን አሉታዊውን እንዳይደገም ፣ አዎንታዊውን ደግሞ ለምናደርገው ሁለንተናዊ ግሥጋሴ እንደ የተሞክሮ ግብአት እየተጠቀምን የመሄድን ታላቅ እሴት ለማጎልበት የምናደርገው ሙከራ እዚህ ግባ የሚባል አልሆነም።  በአሳዛኝ መልኩ ከማጥፋትና ከመጠፋፋት አስከፊ አባዜ ለመውጣት ያለመቻላችንን እንቆቅልሽ  ይበልጥ እያወሳሰብነው ሄደናል።  የጋራ አገራዊ ኩራትና ክብር ምን እንደሆነ ትክክለኛው ትርጉም ጠፍቶብናል።  የአንዳችን መከራና ውርደት የሌሎቻችን ኩራትና ከበሬታ መስሎ እየታየን በእጅጉ ተቸግረናል ወይም ታመናል።

ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን የመጣንበትና አሁንም በተሃድሶ ስም የቀጠለው የኢህአዴግ የፖለቲካ ጨዋታ የሚነግረንም የዚህኑ ፈተና ከባድነትና ውስብስብነት ነው።   ከአገራችን ረጅም ታሪክና በእጅጉ የተሳሰረ ባህላዊና ማህበራዊ መስተጋብር አንፃር ሲታይ በዚህ ዘመን እየሆንና እያደረግን ያለነው ነገራችን ሁሉ የሚያኮራና የሚያስከብር ሳይሆን ተቃራኒው እየሆነብን በእጅጉ ተቸግረናልና  በግልፅና በቀጥታ እየተነጋገርን በጋራ ጥረት ከተዘፈቅንበት ክፉ የፖለቲካ አዙሪት ሳይመሽብን ለመውጣት መረባረብ ይኖርብናል ።

ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በአስከፊ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል የተበከለውን ሥርዓተ ኢህአዴግ ከቃላት ባልዘለለ  ይቅር በሉኝ /በሉን ባይነት ፣ በሸፍጥ በተለወሰ  የተሃድሶ ተውኔት ፣ በደምሳሳና ተራ የመደመር ትርክት ለማስቀጠል መሞከር ጨርሶ መወገድ ያለበትን በሽታ አስወግዶ ሙሉ ጤናማ በሆነ አካልና አእምሮ መኖር ሲቻል በሽታው የሚያስከትለውን ክፉ ህመም ጊዜያዊ ማስታገሻ እየወሰዱና በሽታውን ለትውልድ እያስተላለፉ ሞትን መጠባበቅ እንደ ማለት ነው። ከዚህ የከፋ የአገራዊ ኩራትና ክብር ውድቀት ከቶ የለም። “አለ እንጅ !” የምንል ካለንም ሊኖር የሚችለው እንደ አገር መኖር አቅቶን የየጎሳችንና የየመንደራችን መንግሥታትን ፈጥረን እርስ በርስ የመጠፋፋት አዋጅን ይፋ የማድረጉ ጉዳይ ብቻ ነው።

ለሩብ  ምዕተ ዓመት የዘለቅንበትን እጅግ እኩይ ኢህአዴጋዊ የፖለቲካ ሥርዓትን በቅጡ አጢኖ የሚበጀውን ከማድረግ ይልቅ ለማመን በሚያስቸግር የግልብነትና የስሜታዊነት አስተሳሰብና አካሄድ የለውጥ ሐዋርያት ብለን የተቀበልናቸው የኢህአዴግ ፖለቲከኞች ቀናትን (ጳጉሜንን ልብ ይሏል) ባልነበረና በሌለ እፁብ ድንቅ የነፃነት፣ የፍትህ፣ የፍቅር፣ የኩራት፣ የመደመርና የማባዛት ፣ የብልፅግና ፣ የሰላምና እርቅ ፣ ወዘተ ስያሜ እየሰየሙ በየአደባባዩና በየአዳራሹ እልልልልል! በሉ ሲሉን ለምንና እንዴት? ሳንል እንደ በቀቀን ተቀብለን  እናስተጋባለን ። እንዲህ አይነት በእጅጉ  የወረደ የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ  የነፃነትና የፍትህ ፈላጊ ትውልድ ባህሪ ሊሆን አይችልም።

በአሁኑ ወቅት የምንገኝበት ሁኔታ ማንነትን፣ ምንነትን ፣እንዴትነትን እና ከየት ወደ የትነትን ከፖለቲከኞች ሳይሆን ከእኛው ከየራሳችን ውስጠ ህሊና ፈልገን ማግኘትንና የሚበጀውን ለማድረግ ፈቃደኞችና ዝግጁዎች መሆነን መገኘትን  ይጠይቃል። ይህን ሆነንና አድርገን እስከ አልተገኘን ድረስ  እንደ ዜጋ እና እንደ ሰው መብትን አስከብሮ ፣ ተከብሮ ፣ተከባብሮ፣ በአገራዊ ኩራት ተጀንኖ ፣ በጋራ ብልፅግና የጋራ ደስታን ፈጥሮ እና  ለትውልደ ትውልድ የሚበጅ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሠረትን  አውርሶ ለማለፍ  ከቶ የሚቻለን አይሆንም ። ይህን እንቆቅልሽ ለመፍታት የምናደርገው ጥረት (ትግል) መጀመር ያለበት ደግሞ ለዘመናት በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የተዘፈቀውን  ኢህአዴግን በሸፍጥ በተለወሰ ንስሃና ተሃድሶ  እንደ ሥርዓት በማስቀጠል እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ማድረግ ይቻላል ከሚለው የለየለት  የፖለቲካ አስተሳሰብ ቅዠት (political illusion and dellusion) ከመውጣት ነው።  ህዝብን ከዚህ የቅዠት አባዜ መንጥቆ ለማውጣት ይቻል ዘንድ ደግሞ  ለዜጎቿ ሁሉ የምትመች ዴሞክራሲያዊት አገር የመፍጠሩ ትግል  የሰመረ እንዲሆን እንታገላለንና እናታግላለን የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች በቅድሚያ እራሳቸውን ከዚህ ቅዠት ነፃ ማውጣት ይኖርባቸዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:     ህወሃት የመከላከያ ሠራዊቱን  የገቢ ምንጭ በማድረግ ይጠቀምበታል፦

በአጠቃላይ በአንድ ወይም በሌላ መልክ የዚህ ቅዠት ሰለባ የሆኑ የፖለቲካ ሃይሎችና ግለሰቦች ከሃላፊነትና ተጠያቂነት ለመሸሽ የሚደረድሩት ሰንካላ ሰብብ (clumsy execuse) ለማንምና ለምንም እንደማይበጅ አውቀው ተገቢውን ታሪካዊ ተልእኮ መወጣት እንደሚኖርባቸው በግልፅና በቀጥታ መነጋጋር የግድ ነው።

 ይበልጥ ግልፅ  ለመሆን ልቀጥል

ሀ)  አሁን ለምንገኝበት የአገራዊ ኩራትና ክብር ቀውስ  የመጀመሪያዎቹ  ተጠያቂዎች  ሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የተጨማለቀውና በተሀድሶ ስም እንደ ሥርዓት የቀጠለው ኢህአዴግ የበላይ አለቃነቱ በሌሎች ተወሰደብኝ በሚል ያዙኝና ልቀቁኝ የሚለው ህወሃት የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ልክፍተኞች (እብዶች) እና የምር ለውጥ ከመጣ የኑሮዬ እጣ ፈንታ አለቀለት ብሎ የሚሰጋው የኢህአዴግ የካድሬ ሠራዊት ናቸው።

እነዚህ ሃይሎች ናቸው እነሱው በፈጠሩት ምስቅልቅል የፖለቲካና የማህበራዊ ሁኔታ ውስጥ በሚካሄድ ምርጫ አሸንፈው ኢትዮጵያዊነትን በዴሞክራሲ በማድመቅ አገራዊ ኩራትና ክብር እንደሚጎናፀፉና እንደሚያጎናፅፉን ሌት ተቀን የሚሰብኩን እና  ሲያሻቸውም ማፍረስ ክፉ የፖለቲካ ባህሪያቸው ያልሆነ ይመስል ይህ ካልሆነ አገር እንደሚያፈርሱ ያለ ሃፍረት የሚነግሩን (የሚያስጠነቅቁን)  ።

ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን የኩራት ሳይሆን የሃፍረት ፣ የክብር ሳይሆን የውርደት ፣ የአብሮነት ሳይሆን የመለያየት፣ አብሮ የመዳን ሳይሆን ተነጣጥሎ የመጠፋፋት፣ ወዘተ ሃይል ሆኖ በዘለቀውና አሁንም በተሃድሶ ስም በቀጠለው ሥርዓተ ኢህአዴግ መሪነት አገራዊ ኩራትንና ክብርን የሚያረጋግጥ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እውን ይሆናል ማለት ወይ የየዋህ ፖለቲከኛ እሳቤ ነው ፤ ወይም የፍርፋሪ ለቃሚነት ክፉ አድርባይነት ነው፤ ወይም ደግሞ አስከፊ የተሸናፊነት/የቦቅቧቃነት (cowardliness) ልክፍት ነው።

 

 ህወሃት/ኢህአዴግን የተካው ኦዴፓ/ኢህአዴግ የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ወዜማን (ጳጉሜን) እያንዳንዱን ቀን ትልልቅ ፅንሰ ሃሳቦችን በያዙ ስያሚዎች በድምቀት እንዲከበሩ አደረግሁ  ካላቸው ቀኖች መካከል አንዱ “የኩራት ቀን” መሆኑን ዓመት እንኳ ሳይዘልቅ ተመልሶ በገዥው ቡድንና በሚቆጣጠረው መንግሥት የፕሮፓጋንዳ መሣሪያነት አዙሪት ውስጥ በገባው ሜዲያ  አማካኝነት ነግሮናል ።

በሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበሰበሰውንና የከረፋውን ሥርዓተ ኢህአዴግ በተሃድሶ ስም ያስቀጠሉት ፖለቲከኞች አደንቁረውና አደንዝዘው ሲገዙት የኖሩትንና አሁንም በባሰ ምስቅልቅል ውስጥ ያስገቡትን መከረኛ ህዝብ “የኩራትህና የክብርህ ቀን ይኸው ተከብሮልሃልና ዛሬ ደስ ይበልህ!” በሚል ሲሳለቁበት ከማየት የከፋ ህሊናን የሚያቆስል ፈተና የለም ። ለአገር (ለወገን) ከምር የሚጨነቅና ጤናማ ህሊና ላለው ትውልድ።

የሰላም የሚል ታሪካዊ የማታለያ ስያሜ በተሰጠው ሜኒስቴር መ/ቤት ሥር እንዲሆኑ የተደረጉት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንና የደህንነት መሥሪያ ቤት መሠረታዊ  የአገር (የህዝብ) ደህንነትንና ሰላምን ማስጠበቅ  ባልቻለበት (ባልፈለገበት) ሁኔታ ውስጥ  “የኩራትና የሰላም ቀን በድምቀት ተከበረ” የሚለውን እጅግ ርካሽ  የፖለቲካ  ፕሮፓጋንዳ በአድናቆት ተቀበሉኝ ማለት መከረኛውን ህዝብ ማሰብና ማገናዘብ እንደማይችል እንስሳ መቁጠር ( dehumanization) ነው።  ይህ ለዘመናት የዘለቅንበት እጅግ አስቀያሚና መሪር የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ እስከ መቼና እስከ የትኛው የመከራና የውርደት ጠርዝ ነው መቀጠል ያለበት?  የሚለው ጥያቄ ነገ ሳይሆን ዛሬውኑ ትክክለኛውን አረዳድና መልስ የሚሻ  ነውና ከምር ልብ ሊባል ይገባዋል ።

ለሩበ መቶ ክፍለ ዘመን የተከበረው እየተባለ የውርደትና የመከራ ህጎችንና ድንጋጌዎችን እጅ እያወጣ የማረጋገጫ ማህተም ሲረግጥ   የኖረው የኢህአዴግ ፓርላማ አሁንም ለማስመሰል ካልሆነ በስተቀር አንዳችም ትርጉም ያለው ለውጥ ባላሳየበት ሁኔታ “የኩራት ቀን በማክበር ታሪክ ሠራን” ማለት የለየለት ርካሽ የፖለቲካ ጨዋታ (ተውኔት) ነው። 

እውነተኛው የኩራትና የክብር ቀን የሚከበረው የውርደትና የሃፍረት ፖለቲካ ተውኔት አካል የሆነው ፓርላማ ተወግዶ  ከህዝብ ፣ በህዝብና ለህዝብ የሆነ ፓርላማ እውን ሲሆን ብቻ ነው።ይህ ደግሞ በፖለቲካ ወለድ ወንጀል ተዘፍቆ በኖረው የገዥ ቡድን (በቀድሞው ህወሃት/ኢህአዴግ በአሁኑ ኦዴፓ/ኢህአዴግ) እውን ይሆናል ብሎ እንኳን መጠበቅ ማሰብም ወይ የለየለት ድንቁርና ነው፣ ወይም አስቀያሚ የአድርባይነት (የአሽቃባጭነት) ልክፍት ነው ፣ ወይም ደግሞ “ከኦዴፓ/ኢህአዴግ ፖለቲከኞች የሚገኘው የተሃድሶ ፍርፋሪ ለኢትዮጵያ ህዝብ ምን አነሰው” የሚል እጅግ የሚዘገንን የፖለቲካ ደደብነት ነው።

 የህግ የበላይነት (rule of law ) በሌለበት የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ  እንኳን የዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብትን ለማስከበር በገንዛ አገር ውስጥ ተዘዋውሮና የሚችሉትንና የተገኘውን የህይወት ማቆያ ሥራ ሠርቶ ለመኖርም በእጅጉ  ይቸግራል። ባለፈው ሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሥራ ላይ የዋለው የጎሳ/የዘውግ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ሥርዓት ካስከተላቸው እጅግ አስከፊ ሁኔታዎች አንዱ  የህግ  ተርጓሚው/የፍርድ ቤቱ ሥርዓት  (the judiciary branch of government) የእኩይ የፖለቲካ  አጀንዳ ማስፈፀሚያ መሆኑ ነው።

ይኸውና ዛሬም የጉልቻ ለውጥ እንጅ የእውነት ለውጥ ባለመኖሩ ይህ እጅግ ወሳኝ የሆነው የመንግሥት ክፍል ከተመሳሳይ አገልጋይነት አልተላቀቀም። ዛሬም በበላይነት  (በጠቅላይ አቃቤ ህግነት/Attorney General) የሚመሩት በዘመነ ህወሃት/ኢህአዴግ የተፈበረከ የፖለቲካ ክስ በማቀነባበር ፣ በማዘጋጀትና የጥፋተኝነት ፍርድ በመወሰን ንፁሃን ዜጎችን ለኢ-ሰብአዊ ሰቆቃ እያሳለፉ ሲሰጡ የነበሩ ህሊና ቢሶች ናቸው በአያሌ ንፁሃን ዜጎች ላይ የፖለቲካ ወለድ ፍርድ እየወሰኑ ያጉሩበትና  ያሰቃዩበት የነበረውን ማዕከላዊ ወደ ሙዚምነት ቀየርን ብለውና በውስጡ የነበሩትን የስቃይ መፈፀሚያ ነገሮችን (መሣሪያዎችን) አፅድተው እና ክፍሎችን ሳይቀር በቀለም ቡርሽ ቦርሸው የሚያስጎበኙንም እነዚሁ የህሊና እና የሞራል ሰብእና ጨርሶ  የሌላቸው ወገኖች ናቸው።

ከኢህአዴግ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የላቸውም ተብለው ለዚሁ የመንግሥት ክፍል (የከፍተኛ ፍርድ ቤት ) የተሰየሙት ሹማምንትም  በአድርባይነት ክፉ ባህሪ የተለከፉ መሆናቸውን ለመረዳት ሚዛናዊና ነፃ አስተሳሰብ እንጅ የተለየ እውቀት አይጠይቅም። ታዲያ  ፖለቲከኞቻችን የኩራትና የፍትህ ቀን በማክበር ከራሳችን አልፎ ዓለምንም አስደመምነው በሚል ሃፍረተ ቢስ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ጋጋታ ሊያሳምኑን ቢሞክሩ ለምን ይገርመናል ?   

ይህን አይነት እጅግ የቆሸሸ የፖለቲካ ጨዋታ በምክንያታዊነትና በማይናወጥ የእውነት መርህ ተከታይነት ተዋግቶ (ታግሎ) የሚበጀውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ማድረግና እንደ ሰውና እንደ ዜጋ ተከብሮና ተከባብሮ ለመኖር ከመቻል ይልቅ የለውጥ ብልጭታ ታየ በተባለ ቁጥር ሸፍጠኛ ፖለቲከኞችና የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ልክፍተኞች እንደ ጋሪ ፈረስ እንዲጋልቡት የሚፈቅድ ትውልድ የጠፋበትን የአገራዊ ኩራትና ክብር ትክክለኛ ትርጉም ፈልጎ ማግኘት አለበት። ለተወሰነ ጊዜ በሸፍጠኛ ፖለቲከኞች እንደ ጋሪ ፈረስ የመነዳት ቸግር ሊያጋጥም ይችላል ። ለአያሌ ዓመታትና በተደጋጋሚ የጋሪ ፈረስ  መሆን ግን ጨርሶ የነፃነትና የፍትህ ፈላጊ ሰብአዊ ፍጡር ባህሪ አይደለምና ቆም ብሎ በማሰብ የሚበጀውን ማድረግ የግድ ነው።

ከላይ የጠቀስኳቸው  ሃይሎች ከገቡበት  “ሁሉንም በበላይነት ካልተቆጣጠርን ሁሉም ነገር  ድራሹ ይጥፋ” ከሚል  አደገኛ ቅዠት ወጥተው ወደ ትክክለኛው የዴሞክራሲዊ ሥርዓት ሽግግርና ምሥረታ መንገድ እንዲገቡ ማስቻል (ማድረግ) የአገራዊ ኩራትና ከበሬታ ታሪክ ባለቤትነት መሆን  ነውና በዚሁ ላይ መረባረቡ የነገ ሳይሆን የዛሬ ሥራ መሆን አለበት የሚል ፅዕኑ እምነት አለኝ  ።

ሁሉንም  እየሄደበት ካለው ክፉ መንገድ እመልሳለሁ ማለት የገሃዱ ዓለም እውነታ አይደለምና አንመለስም የሚሉትን ከምር በመቆጣት “በእናንተ ምክንያት በአብሮነት ፣በእኩልነት ፣ በነፃነትና በጋራ ብልፅግና መኖር የምንችልባትን የጋራ ምድር (አገር) የእርስ በእርስ መናቆሪያና መጠፋፊያ እያደርገንና ትርጉም የሌለው ሞት እየሞትን መኖር ከአሁን ጀምሮ  ጨርሶ  አንፈቅድምና በቃችሁ” ማለት የግድ ነው ።

የአገራዊ ኩራትና ክብር ዋስትና ሥርዓተ ዴሞክራሲ ብቻ ነው። ይህን እውን ለማድረግ የኢህአዴግ ፖለቲከኞች “እኛ ነን አሸጋጋሪዎች” ከሚል ቅዠታቸው ወጥተው በብሔራዊ (አገር አቀፍ)  የምክክር መድረክ ሁሉን አቀፍ  የሽግግር ወይም ጊዜያዊ መንግሥት እስከ መመሥረት የሚደርስ መርህና ሥልት በጋራ ለመንደፍ ፈቃደኞችና ዝግጁዎች መሆን ይኖርባቸዋል። ሁሉም ዜጎቿ ነፃነትና እኩልነት የተረጋገጠባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን መሆን ከምር የምንፈልግና የምንናፍቅ ከሆነ ትክክለኛውና  ዘላቂው የመፍትሄ መንገድ ይኸው ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ታምራት ላይኔና አማረ (ክፍል-2) - (ከኢየሩሳሌም አ.)

አዎ! እንደ ግለሰብ ዜጋም ሆነ እንደ ህዝብ  ተከበርንና ተከባብረን ፣ በጋራ ኩራት ደምቀንና  አምሮብን እና ይህንኑ ታላቅ የማንነትና የምንነት እሴት ለትውልድ አስተላልፈን ማለፍ  ካለብን ትክክለኛው መውጫ መንገድ ይኸው ነው ።

 

ለ) ከዚህ በላይ የጠቀስኳቸው ሃይሎች (ወገኖች) ብቸኛ ሃላፊዎችና ተጠያቂዎች  ናቸው ብሎ መከራከር ለትክክለኛ መፍትሄ ፍለጋ ጨርሶ የሚጠቅም አይሆንም።

መሠረታዊ የህግና የፖለቲካ መዋቅር ለውጥ በሌለበት እና ዜጎች በገንዛ አገራቸው በነፃነትና በሙሉ አገራዊ ስሜት ተዘዋውረው መሥራትና  መኖር በማይችሉበት እጅግ አስከፊና አሳፋሪ ሁኔታ ውስጥ የኢህአዴግ ተሃድሶ ፖለቲከኞች  ነፃና ትክክለኛ ምርጫ በማካሄድ  ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን የማድረጉን ሂደት ወደ ላቀ ደረጃ እናሸጋግረዋለን የሚለውን ፕሮፓጋንዳቸውን ሊያለማምዱን እየሞከሩ መሆናቸውን እየታዘብን ነው።   ከሞት አፋፍ የተመለሰው ኢህአዴግ በግንባርነትም ይሁን በውህደት  (በቅርፅ ለውጥ ሽፋን) “ታሪካዊ የአሸናፊነት ድል” ሊጎናፀፍ እንደሚችል ከአሁኑ አምነን እንድንጠባበቅ “የሚያነቃቃ” ፕሮፓጋንዳ ነው እየሰማን ያለነው ።  ።

በህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ዘመን የተቋቋሙት የምርጫ ቦርድየሰብአዊ መብት ኮሚሽንና እንዲሁም ከአስተዳደራዊ በደል የሚመነጨውን የመንግሥት ሠራተኞችን እንባ ጠባቂ (ombudsman) ተብየ ምን ያህል በመከረና በውርደት ሥርዓት ሽፋን ሰጭነት ሲያገለግሉ እንደነበር በአደባባይ ምሥጢርነት የሚታወቅ ነው።  ለበርካታ ዓመታት ከደሃው ግብር ከፋይ ህዝብ ላይ በሚነጠቅ ገንዘብና ህወሃት/ኢህአዴግን አቅፈውና ደግፈው ቤተ መንግሥት ካስገቡና ለጋሽ ከሚባሉ መንግሥታት በሚገኝ እርዳታ የዴሞክራሲ ተቋማትን ማጠናከር  በሚል ሽፋን ሲፈፀም የኖረውን አስከፊ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ለምንና እንዴት? በሎ ከምር ለሚጠይቅ የአገሬ ሰው የሚሰማው  የህሊና ህመም እጅግ ከባድ ነው።

በዴሞክራሲያዊ ሽግግር ወደ መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሥረታ የሚወስደንን መንገድ ከኢህአዴግ የእኩይ ፖለቲካ መሃንዲሶች አስለቅቆ ዜጎች ሁሉ በነፃነትና በኩራት የሚመላለሱበት ለማድረግ የሚያስችል የፖለቲካ ሃይል በመፍጠር ረገድ አይወድቁ ውድቀት መውደቃችን ያስከተለው አሉታዊ ውጤት በእጅጉ አስከፊ ነው ።

ሸፍጠኛ የኢህአዴግ ፖለቲከኞች በተሃድሶ ስም ለውጥ የተደረገ የሚያስመስሉ እርምጃዎችን በማሳየት መከረኛውን ህዝብ የማደንዝዝ የፖለቲካ ጨዋታውን ተያይዘውታል ። መሠረታዊ የሥርዓት ለውጥን እውን ማድረግ የሚያስችሉ ሁኔታዎች (እርምጃዎች) ጨርሶ በሌሉበት ለሩብ ምዕተ ዓመት ዴሞክራሲን ለማጠናከር በሚል ስም የእኩይ ፖለቲካ ዓላማ ማስፈፀሚያ ሆነው የዘለቁት ተቋማት ወደ እውነተኛ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ አገልጋይነት ይለወጣሉ ብሎ ማሰብ (መጠበቅ) ውድቀትን በአሳዛኝ መልኩ መደጋገም ነው።

የምርጫ ቦርድና የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ተብየዎች እጣ ፈንታም ከዚሁ አስቀያሚ (አስከፊ) የፖለቲካ ጨዋታ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። እነዚህ ተቋማት ዛሬም በተሃድሶ ስም በቀጠለው ኦዴፓ/ኢህአዴግ  ሥር መሠረታዊ ለውጥ ሳይደረግባቸው ያንኑ የርካሽ ፖለቲካ ጨዋታ ሽፋን ሰጭነት አገልግሎታቸውን ቀጥለዋል ። የወለዳቸውና የሸፍጥ ፖለቲካ ጨዋታ ተዋንያን ያደረጋቸው ሥርዓተ ኢህአዴግ ለመሠረታዊ ለውጥ ቦታውን እንዲለቅ ለማድረግ የሚያስችል አማራጭ ዴሞክራሲያዊ ሃይል (አካል) በሌለበት ሁኔታ  እነዚህ ተቋማት በራሳቸው  ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ለማድረግ ያስችላሉ  ብሎ ማሰብ  ወይ የለየለት የፖለቲካ ቂልነት ነው ፤ ወይም የለየለት አድርባይነት ነው፤ ወይም ደግሞ “ለኢትዮጵያ ህዝብ ይህ ምን አነሰው” የሚል አሳዛኝ የፖለቲካ ሰብእና ውድቀት ነው።

ዛሬም በአገራችን ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ቢያንስ አንፃራዊ ምቹ ሁኔታ ጨርሶ አለመኖሩ በራሱ ግልፅና ግልፅ በመሆኑ አሳማኝ ምክንያት ካላመጣችሁልኝ አላምንም የሚያሰኝ አይደለም ። እናም የምርጫ ቦርድ ተብየው  የፈጣሪውን (የኢህአዴግን) ህገ መንግሥትና የፖለቲካ አጀንዳን ከማስፈፀም አዙሪት አልተላቀቀም ። ሊላቀቅም አይችልም። በየትኛው የፀና መርህ ፣ የማይታጠፍ ተልእኮና ዓላማ ባለው አማራጭ ሃይል  ?

ከአፈጣጠራቸውና ከተሰጣታቸው ተልእኮ የሚመነጭ እጅግ አስቀያሚ ምንነት (ይዘት) ለአላቸው ተቋማት ከገዥው ቡድን ጋር ንክኪ ያልነበራቸውንና በነበራቸው (በአላቸው) የታዋቂነት ሰብእና የሚታወቁትን ግለሰቦች ( የምርጫ ቦርዷን ወ/ት ብርቱካን ሜዴቅሳንና የሰብአዊ ኮሚሽኑን ዶ/ር ዳንኤል ተፈራ ልብ ይሏል) በበላይ ሃላፊነት ሾሞ የዴሞክራሲ ቆንጆዎች የማስመሰል የፖለቲካ ጨዋታ መጫዎት ነፃነትነቱና መብቱ የሚረጋገጥበትን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሚናፍቀው መከረኛ ህዝብ ላይ መሳለቅ ነው የሚሆነው።

 በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የተዘፈቀውን የኢህአዴግ ሥርዓትን በአገራዊ ራዕይና ተግባራዊ እርምጃ  አስወግዶ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ያደርጋል በሚል ተስፋና አንፃራዊ አመኔታ ተጥሎበት የነበረው ተቃዋሚ ነኝ ባይ ፖለቲከኛ ሁሉ በአሳፋሪ አኳኋን  የተሃድሶ ኢህአዴጋዊያን አፈ ቀላጤ በሆነበት መሪር እውነታ ውስጥ የምርጫ ቦርድና የሰብዊ መብት ኮሚሽን የመሰሉ ተቋማት ነፃና ትክክለኛ ሚናቸውን ይጫወታሉ ብሎ መጠበቅ  የኮሰመነ የፖለቲካ እሳቤ ነው ።

በእጅጉ የሚያሳዝነው ደግሞ እንደ ወ/ት ብርቱካን ሜዴቅሳ የመሰሉ በህግ ባለሙያነታቸውና እስከ ተቀዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሪነት በመድረስ በከፈሉት መስዋዕትነት ከአገር ቤት አልፎ ዓለም አቀፍ እውቅና እና አድናቆት የተቸራቸው ሰዎች የለውጥ አራማጅ ነን ከሚሉ ኢህአዴጋዊያን የቀረበላቸውን ሹመት ሳያቅማሙ የተቀበሉበት አስተሳሰብና አካሄድ ነው ። ህወሃትን በመጥላት ላይ የተመሠረተ ፖለቲካዊ አቋም በሚመስል ሁኔታ የለውጥ አራማጅ የሚባሉትን የኢህአዴግ ፖልቲከኞች እርምጃ በቅጡ  ለመገንዘብ የሚያስችል ጊዜና ትእግሥት ሳይወስዱ የኦዴፓ/ኢህአዴግ የሸፍጥ ፖለቲካ ሽፋን ሰጭ የመሆናቸው ጉዳይ ሰው ከመሆን ባህሪ አንፃር ባይገርምም የኢትዮጵያን ህዝብ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለቤት ከማድረግ ወይም ካለማድረግ አንፃር ግን በምንም አይነት ይበል የሚያሰኝ አይደለም ።

ለዓመታት ከተዘፈቀበት እጅግ አስከፊ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ለመውጣት መሠረታዊ የአስተሳሰብ ፣ የአወቃቀር እና የአሠራር ለውጥ ሳያደርግ እዚሀ ግባ በማይባልና በሸፍጥና በሴራ ፖለቲካ በተለወሰ የተሃድሶ ፍርፋሪ አከፋፋይነት የቀጠለውን ሥርዓተ አዴፓ/ኢህአዴግን የሹመት ግብዣ ተቀብሎ የዴሞክራሲ ተቋማት ተብየዎችን የመምራቱ ውሳኔ የግለሰቦች ነው ።  የየራሳችን  ኩራትና ክብር አክብረንና ጠብቀን ለመራመድ አቅሙ ሲያንሰን   በተበላሸ ሥርዓት ውስጥ የተዘፈቁ ተቋማትን እንመራለን ማለት ግን የአገርን (የህዝብን) ኩራትና ክብር ጨምሮ ዝቅ ስለሚያደርግ የግለሰቦች መብት ነው በሚል ሊታለፍ የሚገባው አይመስለኝም።

አሁን ባለው የአገራችን  የፖለቲካ እውነታ  የምርጫ ቦርድና ሌሎችም የዴሞክራሲ ተቋማት የምንላቸው አካላት ከሸፍጥ  የፖለቲካ መጫዎቻ ካርድነት  (ሰለባነት) ሊያመልጡ የሚችሉበት ሁኔታ  ጨርሶ የለም።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ተብየውን በሁለተኛ ምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። ከአንድ ዓመት በላይ አልፎ አልፎ ሳይሆን ተከታታይነት ባለው ሁኔታ ሚሊዮኖች ንፁሃን ዜጎች መግለፅ በሚያስቸግር ሁኔታ ለምድራዊ ሲኦል ሲጋለጡ  ከተለመደው የይታሰብበት አቤቱታ በዘለለ የዜጎችን መከራና ውርደት በግልፅና በቀጥታ  ለማሳወቅ የፖለቲከኞችን የስሜት ትኩሳት እየለካ የሚንቀሳቀስ  የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ተቋም ተብየ ባለበት የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ሰብአዊ ክብርንና  አገራዊ ኩራትን  እንኳን መጠበቅ ማሰብስ እንዴት ይቻላል?

በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚገኘውን መከረኛ ህዝብ ነው የለውጥ አራማጅ የምንላቸው የኦዴፓ/ኢህአዴግ ፖለቲከኞች ባለፈው ዓመት መገባደጃ የኩራትና የፍትህ ቀን በድምቀት አክብሮ ዋለ የሚል ርካሽ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ የሠሩበት።

እንደ እኔ አስተያየት ከተሃድሶ ፍርፋሪ አከፋፉይነት የፖለቲካ ጨዋታ ያልዘለሉትን ተቋማት “ቆንጆ ገፅታ” ለማላበስ ሲባል በመሪነት ላይ የሚገኙት ሁለቱ  ግለሰቦች (ወ/ት ብርቱካንና ዶ/ር ዳንኤል) ከነበራቸው በጎ የኋላ ማንነት ታሪክ  ለመነጨ ኩራትና ክብር ሲሉ ብቻ ሳይሆን ለአገር ኩራትና ክብር ሲሉ እራሳቸውን ከምር በመጠየቅና በመመርመር  በክብር በመሰናበት  የህዝቡን የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ምሥረታ ትግል ቢያግዙ መልካም ነው የሚል እምነት አለኝ ።

ሐ) በየጊዜው በተፈራረቁ  ኢ-ዴሞክራሲያዊ  ገዥዎችና በተለይም ባለፈው ሩብ መቶ ክፍለ ዘመን የግልና የቡድን ልክ የሌለው ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲሉ ለማመን በሚያስቸግር ሁኔታ  የአገር ሃብት ዘረፋ ላይ ተሠማርተው በነበሩ የኢህአዴግ ባለሥልጣናትና ግብረ በላዎቻቸው ምክንያት ከደሃዎችም ደሃ በሆነች  አገር ውስጥ  ከመቶ በላይ “የፖለቲካ ድርጅት” እንደ አሸን  ፈልፍሎ  የተዋጣለት ዴሞክራሲ እውን አደርጋለሁ ከማለት የባሰ የፖለቲካና የሞራል ውድቀት የለም ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ይድረስ ለነጻነት ናፋቂ ኢትዮጵያዊያን - ከያህያ ይልማ

አዎ! ዛሬም በህዝብ ላይ የተጫነውን የኢህአዴግ የመከራና የውርደት  ሥርዓት በተባበረ የአንድ አገር ልጅነት መንፈስና የተግባር ውሎ አስወግዶ ዴሞክራሲያዊት አገርን እውን ከማድረግ ይልቅ የኦዴፓ/ኢህአዴግ የተሃድሶ ፍርፋሪ ድርሻ አነሰኝ ወይም ሊያንሰኝ ይችላል በሚል እጅግ በዘቀጠ የፖለቲካ ጨዋታ የተጠመደ ተቀዋሚ ነኝ ባይ በሚተራመስበት ሁኔታ ውስጥ የፍትህ ፣የዴሞክራሲ ፣ የኩራት ፣ ወዘተ ቀን በደመቀ ሁኔታ ተከበረ የሚል ርካሽ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ማናፈስ የህዝብን የመገንዘብ አቅም መሳድብ ነው የሚሆነው።  ከዚህ የከፋም የአገራዊ ኩራትና ክብር ውድቀትም የለም።

ዛሬም ይህ አይነቱ   ካለመኖር የማይሻል የፖለቲካ ተውኔት መከረኛውን ህዝብ ግራ ማጋባት ብቻ ሳይሆን በባሰ ሁኔታ የሁለንተናዊ ቀውስ  ሰለባ አድርጎት ቀጥሏል። ከአዳራሽ ስብሰባ፣ ከሚዲያ ወግና በቤተመንግሥት ዙሪያ ደጅ ከመጥናት አልፎ የሚታይና ቢያንስ ሁለት   እርምጃ ወደ ፊትና አንድ እርምጃ ወደ ኋላ  መራመድ የቻለ ተቀዋሚ የፖለቲካ ድርጅት በሌለበት ስለ ምን አይነት ኩራትና ክብር እንደምናወራ ጨርሶ ስሜት የሚሰጥ ነገር አይደለም።

ታዲያ  የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ልክፍተኞች የተሃድሶውን ኦዴፓ/ኢህአዴግ በቀጥታና በተዘዋዋሪ በመቆጣጠር ያሻቸውን ቢያደርጉ ለምን ይገርመናል?    ቀደምት አባቶችና እናቶች በመስዋዕትነት ያስረከቡትን አገር ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ  መብቶቹ የተረጋገጡባት በማድረግ በኩራትና በከበሬታ አምሮበት ያልፍ ዘንድ   የራሱን ታሪክ መሥራት ሲገባው በውርደትና በሃፍረት ሥርዓት ውስጥ እየዛቀጠ ስለጎሳው/ስለ ዘውጉ/ስለመንደሩ  ኩራትና ክብር ወግ የሚጠርቅ ትውልድ ባለበት ሁኔታ ውስጥ የአገራዊ (የብሔራዊ) ማንነት ኩራትና ክብር ለምን ፈተና ላይ አይውደቅ ?

ቀድሞውንም እርባና የሌላቸው የፖለቲካ ፓርቲ ተብየዎችን አሁን ለምን እርባና አይኖራቸውም በሚል ክርክርና ትንታኔ ጊዜንና አቅምን ማባከን አስፈላጊ አይደለም  ።  ለገዥው ቡድን እርካሽ የፖለቲካ ጨዋታ መጫወቻ ካርዶች የሆኑ ተቀዋሚ  ፖለቲካ ፓርቲዎች ተብየዎችን ወይ ልብ ግዙና ወደ አንድነት ወይም ትርጉምና ዘላቂነት ወደ አለው የፓለቲካ ሃይልነት እደጉ ፤ ያለዚያ ግን በመከረኛው ህዝብ ላይ አትጫወቱ ብሎ በግልፅና በቀጥታ መንገር ግን አስፈላጊ ነው።  

መ) “በማይናወጥ መርህ ላይ ቆመን፣ ግልፅ ዓላማና ግብ አስቀምጠን ፣ ለተጨባጭ ሥራ የሚመጥኑ ፖሊሲዎችን ነድፈን ፣  ጠንካራ የማስፈፀሚያ ፕሮግራሞችን  አዘጋጅተን ፣ በራስ መተማመንን ተማምነን፣  ወዘተ  ዴሞክራሲያዊ አገር አቀፍ (የዜግነት) የፖለቲካ ሥርዓት እውን ይሆን ዘንድ  እስከ መስዋዕትነት እንሄዳለን”  ይሉን የነበሩ የተቀዋሚ ፓርቲ መሪዎች አሁን እየሆኑና እያደረጉ ያሉት ነገር  የኩራትንና የክብርን እውነተኛ ትርጉም አይናገርም።  

ሥርዓት ማለት አንድና ሁለት እያልን በስም የምንጠቅሳቸው ኢህአዴግን አዳሽ ኢህአዴጎች ማለት እስኪመስል ድረስ ደምሳሳ  የመደመር ፖለቲካን (አብይዝምን) ከምር ተቀብለው እንደበቀቀን መልሰው ሲያስተጋቡ መስማትና ማየት በምንም አይነት የኩራትና የከበሬታ ፖለቲካ ሰብእና ሊሆን አይችልም።

ለምን? ቢባል ለዘመናት በፖለቲካ ወለድ ወንጀልና የሞራል ውድቀት ክፉኛ የተበከለው ሥርዓተ ኢህአዴግ ዋና ዋና ምሰሶዎቹ ባልተነኩበት ሁኔታ እንኳን አንድና ሁለት ብለን የምንቆጥራቸውና በእራሱ በኢህአዴግ ሥር   ጥርሳቸውን ነቅለው ያደጉ “የተሃድሶ ፖለቲከኞች” የፖለቲካ መልአክት ነን የሚሉ ፖለቲከኞች (ከተገኙ) ቤተመንግሥት ቢገቡም የሚለወጥ መሠረታዊ ለውጥ ከቶ አይኖርም።

ሲያስተጋቡት በነበረው የአገራዊ ፖለቲካ አጀንዳና ባሳዩት መስዋእትነት እስከ መክፈል ባደረጉት እንቅስቃሴ አንፃራዊ ተቀባይነትና ተአማኒነት ተችሯቸው የነበሩ የተቃውሞው ጎራ ፖለቲከኞች በኦዴፓ/ኢህአዴግ ፖለቲከኞች መቶ መቶ በመቶ እንተማመናለን በማለት የለየለት ልጣፍነታቸውን (ተለጣፊነታቸውን) “በኩራት” እየነገሩን ነው ።

የእውቀትና የተሞክሮ ማጣፊያ የሚያጥረው የየትኛውም ተቀዋሚ የፖለቲካ ድርጅት ተብየ የአመራር ወይም ተራ አባል የለውጥ አራማጅ የሚባሉትን ፖለቲከኞች በጠንካራ ሂሳዊ አቀራረብ ለመደገፍ ወይም ለመቃወም ቢቸገር ከቶ የሚገርም አይሆንም ። በእውቀትና በተሞክሮ (ከእሥር እስከ የትግል ሜዳ) በከፈሉት መስዋእትነት አድናቆትና ከበሬታ የተቸራቸው የአመራር አባሎች የበሰበሰውንና የከረፋውን ሥርዓተ ኢህአዴግ አስወግዶ መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ለማድረግ በሚያስችል ፅዕኑ የእራስ መርህና የዓላማ ፅዕናት  ላይ ቆሞ መዝለቅ ሲሳናቸው መታዘብ ግን ባያስገርምም ያሳስባል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩንና የቅርብ የፖለቲካ ጓዶቻቸውን መቶ በመቶ እናምናቸዋለን ፤ በመላ አገሪቱ ስለሆነውና እየሆነ ስላለው አስከፊ ሁኔታ የሚያሳስበን መሆኑን መወሰድ አለበት ከምንለው እርምጃ ጋር በማስታወሻ ለቤተ መንግሥት እናቀርባለን እንጅ እዚህም እዚያም ጬኸት በተሰማ ቁጥር መግለጫ አናወጣም ፤ ከምርጫው በፊት አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎች መወሰድ እንዳለባቸው ብናምንም እነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግር የለም ካሉን የማናምንበት ምክንያት የለም  ፤ የህግ መንግሥት ይለወጥ ጥያቄ መነሳት ያለበት ከምርጫ በኋላ ነው ( በምርጫው አሸናፊ ሆኖ የሚወጣው ከተዘፈቀበት አስከፊ ፖለቲካ ወለድ  ወንጀል ጋር የቀጠለው ኢህአዴግ መሆኑን ልብ ይሏል) እና ሌሎች በመሬት ላይ ላለው መሪር እውነት የማይመጥኑ ልፍስፍስ መከራከሪያዎችን መስማት በምንም አይነት በራስ መተማመንና ኩራትን አያሳይም።

በእውነት ከተነጋገርን አማራጭ ሃይል አምጦ መውለድና ለቁምነገር ማብቃት ያልተሳካለትን መከረኛ ህዝብ በእንዲህ አይነት የፖለቲካ ጨዋታ ማደንቆር (ማደናቆር) ቢያንስ የሞራል ውድቀት ነው። ከፍ ሲል ደግሞ የኢህአዴግን የመከራና የውርደት ሥርዓት በገፅታ ማሳመሪያ (artificial make up) ማራዘም ነው ።

ኢህአዴግ እንደ ሥርዓት በሚቀጥልበት የፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ ለመንቦጫረቅ  የማይሞክሩት መሆኑን ቃል በምድርና በሰማይ በሚል አይነት ሃይለ ቃል በየስብሰባ አዳራሹና በየመገናኛ ብዙሃን አውታሩ ሲያስደምጡን “እውነትም አርበኞች!” እያልን መወድሱን ስናዥጎደጉድላቸውና ጭብጨባውን ስናቀልጠላቸው የነበሩ ወገኖች የህወሃት/ኢህአዴግ ከቤተ መንግሥት (ከአዛዥነት) ስለተወገደ  ዓላማቸው ግቡን እንደ መታ አይነት ቆጥረው  “የለውጥ ሐዋርያትን ገድል” አሳማኝ ለማድረግ የሚያቀርቡት ገለፃና ትንተና  ሁሉ እየተንሸዋረረባቸው ሲቸገሩ ማየት ባያስገርምም በእጅጉ ያሳዝናል (ያሳስባል)።

እናም በዘመኑ መሥራት የነበረባቸውን ታሪክ ሠርተው እንደኮሩና እንዳማረባቸው እንዳለፉት አባቶቻችንና እናቶቻችን ሁሉ እኛም የዘመናችንን ታሪካዊ ተልኮ ተወጥተን እንደኮራንና እንዳማረብን ለማለፍ እንችል ዘንድ  የየራሳችን ውስጠ ህሊና በጥብቅ መፈተሽ ይኖርብናል።

ለማጠቃለል

ቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን የነበሩበት ዘመን ይጠይቅ የነበረውን አገርን በደምና በአጥንት መስዋእትነት ተከላክሎና አስከብሮ ለትውልድ የማስተላለፍ እጅግ ወርቃማ ታሪክ ሠርተው አልፈዋል ።አዎ! እንደ ኮሩ ፣ እንደ ተከበሩና እንደአማሩ መሞት ማለት ይኸው ነው!

የዚህ ትውልድ ታሪካዊ ተልእኮ ደግሞ ግዙፍና መሪር መስዋእትነት ተከፍሎባት የተረከባትን አገር ከዘመን ጋር አብሮ የሚዘምን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለቤት እንድትሆን በማድረግ ለዘመናት ከኖረበት የመከራና የውርደት ሥርዓተ ፖለቲካ ለአንዴና ለመጨረሻ መገላገል ነው። ይህ እውን የሚሆነው ግን ለዘመናት በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የተዘፈቀው ኢህአዴግ እንደ ሥርዓት በሚቀጥልበት አካሄድ ሳይሆን ያገባኛል የሚለው ወገን ሁሉ በጋራ መክሮ በጋራ በሚስማማበት የሽግግር መንገድ (mechanism) አግባብ ነው።  ኢህአዴግ በግንባርነትም ይቀጥል ወይም የቅርፅ (የውህደት) ውል ይፈፅም እውነተኛ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አሸጋጋሪ ለመሆን የሚያስችል የፖለቲካም ሆነ የሞራል እርሾ (ስንቅ) ጨርሶ የለውም ።

ይህን መሪር ሃቅ ተቀብሎ በአገራዊ የምክክር መድረክ (ጉባኤ) በሚደረስበት የጋራ መግባባትና ስምምነት መሠረት  ኢህአዴግም እንደ ፓርቲ የሚሳተፍበት እና ዘላቂ የዴሞክራሲ ሥርዓት ምሥረታን የሚያመቻች   የሽግግር ወይም ጊዜያዊ መንግሥት ይቋቋም ብሎ ለመጠየቅ የሚሽኮረመም ወይም የሚልፈሰፈስ የፖለቲካ አስተሳሰብና ቁመና  ጨርሶ የትም አያደርስም ። በዚህ አይነት የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ የጋራ አገራዊ ኩራትንና ክብርን የሚያጎናፅፈውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ማድረግ የሚቻል አይሆንም ። ምርጫው ሁለት ነው ። የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሥረታን ከሂደቱ ጀምሮ የአገር ጉዳይ ያገባኛል የሚል ሁሉ በሚያሳትፍ የፖለቲካ አካል (የሽግግር መንግሥት) አማካኝነት የነፃነት፣ የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የሰላም፣ የፍቅርና የጋራ ብልፅግና አገርን እውን ማድረግ  ፤ ወይም ኩራትና ክብርን  ለኦዴፓ/ኢህአዴግ የተሃድሶ ፍርፋሪ (እሱም ከተገኘ ነው) መስዋዕት ማድረግ ።

የአብዛኛው ነፃነትና ፍትህ ናፋቂ (ፈላጊ) የአገሬ ሰው ምርጫ የመጀመሪያው እንደሚሆን እምነቴ መሆኑን እየገለፅሁ አበቃሁ!

 

 

1 Comment

Comments are closed.

Share