አገራችንን ከጥፋት፤ ሕዝባችንን ከመከራ ለመሰወር፤ በጌታ ፍቃድ – ከዶ/ር በቀለ ገሠሠ

መንደርደሪያ፤

ሁላችንም የወጣነዉ ከየእናቶቻችን ማህፀን ዉስጥ ነዉ፤ ለ9 ወራት በማህፀን ተሸከሙን፤ ወለዱን፤ አጠቡን፤ አበሉን፤ ሳሙን፤ አቅፈዉ አሳደጉን። በዚህም ምክንያት እናቶቻችንን ከማንም አስበልጠን እንወዳቸዋለን። እንደዚሁም አገር እናት ናት። ዕትብታችን የተቀበረዉ በርስዋ ዉስጥ ነዉ። ከመሬትዋ እህሎች በቀሉልን፤ በልተን አደግን። ከከርሰ ምድርዋ የሚወጣዉን ዉሃ ጠጥተን አደግን። ወተትና ምግብ የሚሰጡን ከብቶቻችን የሚግጡትና የሚጠጡት ዉሃ የሚገኘዉ ከዚያችዉ ምድር ነዉ። የምንተነፍሰዉ ጥሩ አየር የሚነፍሰዉ በርስዋ ላይ ነዉ። ስንሞት የምንቀበረዉ በርስዋ ዉስጥ ነዉ። ስለዚህ ዉድ አገራችንን የእናቶቻችን ያህል እንወዳታለን። አገር ደግሞ የጋራ ናት። ቸሩ አምላካችን ሲፈጥረን የዚያችን ፍሬ እኩል እንድንካፈል ነዉ። እንደፈለግን በነፃ ተዘዋዉረን ሠርተን እንድንኖርባት ነዉ። ይሄ ሁሉ በጣም ግልፅ ይመስለኛል። ከፋም ለማ፤ የብዙ ሺህ ዓመታት የጋራ ታሪክ ያለን ሕዝብ ነን። ዛሬ ግን በተግባር የምናየዉ ሌላ እየሆነ አስቸገረን፤ ብዙ የአፍሪቃ አገሮች ዲሞክራሲያዊ ሥርዓቶች እየገነቡ በሰላም ሲኖሩ እኛ ለምን ወደኋላ እንደምንቀር ስመለከት እጅጉን አዝናለሁ፤ መንፈሣዊ ቅናት ያድርብኛል። ሃሳብና ጭንቀት ዉስጥ ይከተናል። ተያይዘን ከምንጠፋ ተያይዘን ብንነሳ ይቀላል። ስለዚህ ዉድ አገራችንን ከጥፋትና ሕዝባችንን ከመከራ ለመሰወር እያንዳንዳችን የምንችለዉን ያህል አስተዋጽኦ እንድናደርግ በፈጣሪያችንና በልጆቻችን ስም አደራ እላለሁ፤ እግዜር ይታረቀን፤ የጌታችን በረከት አይለየን፤ አሜን።

 

፩ኛ/       ኢትዮጵያ የማን ናት?

መጠየቁስ? እንዳትሉኝ። ኢትዮጵያ የሁሉም ዜጎችዋ እኩል አገር ናት። እንኳን ለዜጎችዋና በፖሊቲካም ሆነ በሃይማኖት ምክንያት ከየአገሮቻቸዉ ተሰድደዉ የመጡትን በሙሉ እጇን ዘርግታ በመቀበልና በማስተናገድ የታወቀች ቅድስት አገር ናት። በመጽሐፍ ቅዱስ፤ በቅዱስ ቁራንና በታሪክ መዘክሮች በግልጽ የተቀመጠ ሃቅ ነዉ። ዛሬ ግን ፌደራላዊዉ ሥርዓት የተዘረጋዉ ጎሣንና ቋንቋን ብቻ መሠረት በማድረጉ ምክንያት ብዙ ግጭቶች እየተፈጠሩ ይገኛሉ። ከ80 በላይ ጎሣዎች በሚኖሩባት አገር ለሁሉም ዜጋ ተስማሚ የሆነ ሥርዓት መዘርጋት የግድ ይላል። ይሄን አስፈላጊና አንገብጋቢ ጉዳይ በተመለከተ እንደብዙዎቹ ግልፅ ስምምነት ላይ መድረስ እጅግ ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ።

 

፪ኛ/        ምን ዓይነት ኢትዮጵያን እንፈልጋለን?

 • ሰላም የሰፈነባትና ዜጎችዋ በነፃ እየተዘዋወሩ የሚኖሩባት፤ የሚነግዱባት፤ ወዘተ አገር
 • ፍትሕ ያልተዛባባት
 • ድህነትና በሺታ የማይፈራረቁባት
 • የሁሉንም ዜጋ እኩልነት የምታረጋግጥ ዲሞክራሲያዊት አገር።

 

፫ኛ/       ከመሪዎች ምን እንጠብቃለን?

በመጀመሪያ ከዬት ተነስተን ዬት እንዳለን አለመርሳት ያስፈልጋል። አምባገነናዊ አገዛዞችን አስወግዶ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ዜጎች ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈሉባት አገር ናት። አሁንም በዚያዉ ጉዞ ላይ ነን። አሁን ያለዉ መንግሥት ነፃ የሆነ አገራዊ ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ በተለይ በሚከተሉት ሀሳቦች ዙሪያ ከፍተኛ ትኩረት ቢያደረግ የሚጠቅም ይመስለኛል፤

 • የዜጎች ደህንነትና እኩል መብት መጠበቁን ማረጋገጥ፤
 • የሺማግሌዎችን፤ የኃይማኖት አባቶችንና የምሁራንን ምክር መስማት፤
 • አገርና ሕዝብ ማረጋጋት፤
 • አስፈላጊ ተቋማትን ማቋቋምና ማጠናከር፤
 • በአገሩ ያለዉን ከባድ የፖሊቲካ ቀዉስ በትኩረት ዉስጥ በማስገባት ሁሉን ያካተተ ጊዜያዊ ህዝባዊ መንግሥት ማቋቋም፤
 • ከዚያ በኋላ ርትዐዊና ፍትሐዊ የሆነ ነፃ አገራዊ ምርጫ ማመቻቸት ይቻላል።

 

፬ኛ/       ከሺማግሌዎችና ከመንፈስ አባቶች ምን እንጠብቃለን?

አገሪቷ ለስንት ሺህ ዓመታት በሰላምና በነፃነት የኖረችዉ በአረጋዉያንና በኃይማኖት አባቶች ምክርና ፀሎት ነዉ። ፅዉቀት፤ ፀጋና የሕይወት ልምድ ያለዉ በነርሱ ዘንድ ነዉና። አሁንም ዉድ ሺማግሌዎችንና የኃይማኖት አባቶችን አጥብቄ የምለምነዉ፤

 • የአገሪቷ ታሪክ እንዳይዛባ ሃቁን እንዲመሰክሩ፤
 • ‘ድር ቢያብር አንበሳ ያስር’ የሚለዉን መርህ እንዲያስታዉሱ፤
 • በጭቁን ሕዝባችን መሃል ምንም ዓይነት ጥል እንዳልነበረ እንዲመሰክሩ፤
 • በከንቱ ፖሊቲከኞች ቅስቀሳ በተጋጩ ወገኖች መሃል እርቀሰላም እንዲያወርዱ፤
 • ለአገራችን አንድነትና ለሕዝባችን ደህንነት ፀሎታቸዉ እንዳይለየን።

 

፭ኛ/       ከምሁራንና ባለሙያዎች ምን እንጠብቃለን?

ዕድሜ ለተፈራረቁት አምባገነን መንግሥታት፤ ኢትዮጵያ ያሳድጉኛል በማለት በሌላት ዐቅም ለፍታ ያስተማረቻቸዉ  ብርቅ ልጆችዋ በጥይቶች ረገፉ፤ ከተረፉት መሃል ደግሞ ብዙዎቹ እንደባህር አሸዋ በዓለም ተበትነዉ በስደት ላይ ይገኛሉ። አሁንም ተስፋ መቁረጥ አይኖርብንም። ከያለንበት ሆነን ለአገራችን ሰላምና ዕድገት የምንችለዉን ሁሉ አስተዋጽኦ ከማድረግ መቆጠብ አይኖርብንም።  ‘የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ’ ተብሎ የሌ?

በእህል ማምረቻ፤ በአካባቢዉ አየር ብክለት መከላከያና መቋቋሚያ አስፈላጊ ቴክኖሎጂዎች ማሳደግ፤ በወንዞቻችንና ሃይቆቻችን ጥበቃ፤ በሰዎችና እንስሳት ጤናዎች አጠባበቅ፤ ወዘተ ላይ በቶሎ ካልተባበርን አገራችን ምድረበዳና ሕዝባችን ጉዳተኞች ሆነዉ እንዳይቀሩ እጅግ በጣም ያሳስበኛል። የተማረ ሰዉ ቃልኪዳኑን መጠበቅ ይኖርበታል፤ አለመዋሸት፤ ሃቁን መመስከርና ሣይንሱን ማስተማር ይጠበቅበታል። በሙያዉ ሠርቶ ማደር ስለሚችል ሕዝባችንን መታደግ እንጂ በክፉ ነገር ላይ መጣል ከቶ አይጠበቅበትም። አገሪቷ ለፍታ ያስተማረቻቸዉ ልጆችዋን እንዲከፋፍሉና እንዲያናክሱ ሳይሆን በእዉነተኛዉ መንገድ እንዲሄዱና እንዲታደጓቸዉ ነዉ።

 

፮ኛ/        ከወጣቶችስ ምን እንጠብቃለን?

ከሁሉም በላይ የሚያሳስበኝ የአሁኑ ወጣቶችና የመጪዉ ትዉልድ ዕጣ ፈንታ ነዉ። ግጭቶች እየተበራከቱ ናቸዉ። በሰላም ወጥቶ መግባት አጠራጣሪ እየሆነ ነዉ። አየሩ እየተበከለ ነዉ። መሬቶቻችን ጠፍና ምድረበዳ እየሆኑ ናቸዉ። ስለዚህ ለወጣቱ ትዉልድ የሚከተሉትን ቅን ምክሮች ስለግስ ትህትና በተሞላበት መንፈስ ነዉ፤

 • ተስፋ አትቁረጡ፤
 • ራሳችሁን ጠብቁ፤
 • በባልንጀሮቻችሁ ላይ አትጨክኑ፤
 • ራስ ወዳድነት እንዳያሸንፋችሁ፤
 • የአገራችሁን ትክክለኛ ታሪክ ጠንቅቃችሁ ለማወቅ ሞክሩ። አገር መገንባት፤ አንድነት ማጠናከርና ድንበራችንን ከዉጪ ጠላቶች መከላከል ቀላል ትግል አልነበረም፤ አባቶቻችን፤ አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን አጥንታቸዉን ከስክሰዉና ደማቸዉን አፍስሰዉ ነዉ ነፃ አገር ያስረከቡን።
 • ለእኩልነት መታገል እጅግ ያስፈልጋል፤ ለዚህም ነበር እልፍ አእላፍ ወጣቶች ለመሬት ላራሹና ለመደብ እኩልነት ከፍተኛ የሕይወት መስዋእትነት የከፈሉት።
 • ዘርና ጎሣ አትለዩ። አምላካችን በአምሳሉ የፈጠረን አንድ ሕዝብ ነን። እኛ ልጆች በነበርንበት ወቅት ሆነ በትግሉ ውስጥ እያለን ዘርና ጎሣን ለይተን አናዉቅም ነበር። እያንዳንዱ ግለሰብ መታት ያለበት በማንነቱ ብቻ ነዉ።
 • ትግላችሁ ለሁሉም ዜጋ ዲሞክራሲና እኩልነት እንጂ ለጭቆናና ለመጠፋፊያ እንዳይሆን ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባችኋል።
 • በኢትዮጵያና ተመሳሳይ አገሮች ያለዉ ዋናዉ ችግር የመልካምና የዲሞክራሲያዊ አስተዳደር እጦት ነዉ። የሚታየዉም መፈናቀል፤ ረሀብና ችጋር ዋናዉ ምክንያት የዲሞክራሲና ሰላም እጦት ስለሆነ በዚህ ላይ መረባረብ ይኖርብናል።
 • የምትኖሩባትን ምድርና አየሯን ተንከባከቡ፤ ይህን ካደረግን ምድራችን እንኳን ለኛና ለሌሎችም ትተርፋለች።
 • ቸሩ አምላካችን ከመከራ ይሰዉራችሁ።

 

፰ኛ/       ከሁሉም በላይ ግን ሕዝባችንና አምላካችን አለ

ሕዝቤ ሆይ፤ ሁላችሁንም እጅግ አድርጌ እወዳችኋለሁ፤ አከብራችኋለሁ። በሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች ዞሬ ዐይቻለሁ፤ በሙያዬ ትንሽም አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ። ደግ ሕዝብ፤ እንግዳ ተቀባይ፤ ፈሪሃ እግዚአብሔር (በየአምልኮቱ) ያደረበት ነዉ። በየቦታዉ (ከሰሜን እስከደቡብ፤ ከምሥራቅ እስከምዕራብ) ያለዉም የሕዝባችን ችግር ተመሳሳይ ነዉ። ዋናዉ የዲሞክራሲ አስተዳደርና ሰላም መጥፋት ነዉ። ምድራችን በጠፍነት እየተጠቃ ከመሆኑ በስተቀር ሰፊ ነዉ፤ ለሁሉም የሚሆን፤ ከዚያም የሚተርፍ ነዉ። ሰላም ካለ የአየሩን ብክለትና የመሬቱንም ጠፍነት ልንከላከል እንችላለን።

ደጉ ሕዝቤ ሆይ፤ ለብዙ ሺህ ዓመታት የምትታወቀዉ በደግነትህና በአንድነትህ ነዉ። አሁንም በማንም በማንም እንዳትታለል፤ በዘር፤ በጎሣና በሃይማኖት እየተከፋፈልክ እርስ በርስ አትባላ። ባንድ ላይ ሆነህ ኑሮህን አሸንፍ። በህብረት ቆመህ ድንበርህን ከዉጪ ጠላት ተከላከል። ከክፍፍላችንና ከጥፋታችን የሚያተርፈዉ ሴይጣንና የዉጪ ወራሪ ጠላት ብቻ ነዉ። እስካሁን ድረስ በአንድነትህና በእግዚአብሔር ኃይል ነፃነትህን ጠብቀህ ቆይተሃል። አሁንም በዚያዉ ቀና መንፈሣዊ መንገድ ቀጥል። ለልጆችህና ለልጅ ልጆችህ ሰላም የሰፈነባት አገር አዉርስ።

የቸሩ ፈጣሪያችን በረከት ሳይለየን የዉድ አገራችንን አንድነትና የሕዝባችንን ደህንነት ይጠብቅለን።

 

2 Comments

 1. Well said. I totally agree to what you wrote, except to your suggestion regarding transitional govt.Do you think 135 Parties will agree to transit us to a democracy. I don’t think so. Don’t forget you said all inclusive. Of course no one should be excluded, but 135 parties could have been no more than 4 if they were to agree on anything.

 2. ኢትዮጵያ በዘር ፖለቲካ ተጠልፋ ለመውደቅ በቀናቾች የሚቆጠሩ ጊዜ የቀራት ይመስላል ፡፡ ይህን የዘር ፖለቲካና ጭፍን የሆነ አክራሪነት እያጦዙት ያሉት ደግሞ፡፡ በሀገር ውስጥ ያሉ ሙህራኖች እና ከሀገር ውጭ ያሉ የፖለቲካ አቀንቃኞች ናቸው፡፡
  በፖለቲካ አክቲቪስቶች የምትዘወር ሀገር የቀጣይ የለውጥ አቅጣጫዎችን አስቀምጦ ለመከዎን በሀገሪቱ መንግስት ላይ በራስ መታማመን እዳይኖረው ያደርጋል ይህንንም አስግጦ የሚነግረን መንግስት ለሶሻል ሚዲያ ትኩረት ሰጥቶ መልስ መስጠቱ ነው፡፡ ፡፡

Comments are closed.

Previous Story

የአገራችን የተወሳሰበ ችግር  አንድን መሪ በሌላ በመተካት ብቻ የሚፈታ አይደለም  !!  – ፈቃዱ በቀለ፣ ዶ/ር

96210
Next Story

የትነበርሽ ንጉሴ ዝምታውን ሰበረችው አክራሪ ኦሮሞ ሀገር ከማፍረስ ሰከን ቢሉ ይሻላል:: አለማየት ወንጀል አይደለም አለማስተዋል ግን ስህተት ነው

Latest from Blog

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ የውጪ ግንኙነት የቤተክርስቲያኒቱን የሺሕ ዘመናት ታሪክ እና እሤቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርባታል!!

በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) (ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደጻፈው) እንደመንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው ጽሑፌ መነሻ የሆነኝ- ባሳለፍነው ሳምንት በአፍሪካ ኅብረት ኔልሰን ማንዴላ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለአንድ ቀን የተካሄደው፤ ‹‹የአፍሪካ  መንፈሳዊ ቀን/The African Spiritual

የአበባው ታደሰ እና የአረጋ ከበደ ፍርጠጣ | ስለአማራ ክልል ከነዋሪዎች የተሰማው | አበባው ጉ’ድ ሆነ – “አበባውን ሳትይዙ እንዳትመጡ”|“በባህርዳር ተከበናል፣ ከፍተኛ አዛዦች ተመተዋል” | “ፋኖ መንግ’ስት ሆኗል” ጄ/ሉ |

የአበባው ታደሰ እና የአረጋ ከበደ ፍርጠጣ አበባው ጉ’ድ ሆነ – “አበባውን ሳትይዙ እንዳትመጡ”|“በባህርዳር ተከበናል፣ ከፍተኛ አዛዦች ተመተዋል”| “እጅ ከመስጠት ውጭ አማራጭ አይኖረንም” ፊ/ማ “ፋኖ መንግ’ስት ሆኗል” ጄ/ሉ |
Go toTop