ግራ የሚያጋባ ሁኔታ፣ ግራ የተጋባ መሪ፣ ግራ የገባው ህዝብና ምሁር፣ እንዲሁም የለውጥ ጉዳይ ! – ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)

ሰኔ 11፣ 2019

መግቢያ

ከጥቂት ወራት ጀምሮ ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረውን የዶ/ር አቢይን አገዛዝ በሚመለከት የተለያዩ አስተያየቶች፣ ትችቶች፣ ቀልዶችና የካባሬት ባህርይ ያላቸው ሂሶች ይሰነዘራሉ።  እንደዚሁም ደግሞ የዶ/ር አቢይን አገዛዝ ሙሉ በሙሉ ጭፍን በሆነ መልክ በሚደግፉና በዓለም አቀፍ ዘንድና በታወቁት ሚዲያዎች ተቀባይነትን ያገኙ ወጣት መሪ ናቸው በሚሉ አንዳንድ ምሁራንና፣ በሌላ ወገን ደግሞ የአገራችን መንግስትና አገዛዝ ያልተሳካለት ወይም የወደቀ መንግስት(Failed State) ነው በማለት ነገሮችን በሚገባ ሳያብራሩ ግራ የገባውን ወጣት የባሰውን ግራ በማጋባት ተስፋ እንዲቆርጥ የሚጥሩ ኃይሎች እዚህና እዚያ ድምጻቸውን በማሰማት ላይ ናቸው።

ዶ/ር አቢይ ስልጣን ከጨበጡ ጀምሮ ለውጥ የሚባል ነገር በአገራችን ምድር ሲካሄድ አይታይም፤ ሰፈውንም ህዝብ ተስፋ የሚሰጠው ነገር በጉልህ አይታይም፤ እንዲያውም አገዛዙ የሴሌብሪቲ ዐይነት ስራ ሲሰራና የውጭ ኃይሎችን ለማስደሰት ደፋ ቀና ሲል የሚታይ እንጂ፣ የሚዳሰስና የሚጨበጥ፣ እንዲሁም የሚታይና የሚማርክ ስራ ሲሰራ አይታይም የሚሉና ትችት የሚሰነዝሩ ብዙ ሰዎች አሉ። ስለሆነም ይላሉ እነዚህን የመሳሰሉ የአገር ተቆርቋሪዎች፣  የዶ/ር አቢይ አገዛዝ አገሪቱን ሊያስተዳደርና ወደ ዕድገት አቅጣጫ ሊያመራት የሚችል አጠቃላይ ዕቅድ(Master plan or Road Map) የሌለው አገዛዝ ነው ይሉናል። ሌሎች ደግሞ ከዚህ ቀደም ብለው በመሄድ አገዛዙ ከውጭ በአርቆ መቆጣጠሪያ መሳሪያ(Remote Controller) ክትትልና ቁጥጥር ይደረግበት ይመስል ይህንን ወይም ያንን አድርግ ሲባል የሚያስፈጽም እንጂ አገራችንን ካለችበት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ የባህልና የስነ-ልቦና ቀውስ በማውጣት ብሄራዊ ነፃነቷ የተከበረች፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የበለጸገች፣ የምትፈራና የምትከበር፣ እንዲሁም ህዝባችንም የሚመካበት አገር ለመገንባት የሚያስችለው የቲዎሪ፣ የሳይንስና የፍልስፍና እንዲሁም ልዩ ዐይነት ብሄራዊ አጀንዳ የለውም ብለው የሚከራከሩ አሉ።

በአንዳንድ በታወቁ ወጣትና ትንሽም በዕድሜያቸው ገፋ ባሉ የካባሬትና የጉራማይሌ ፈጣሪዎች የሚቀርበውን ትችት ጠጋ ብለን ስንመለከት አቀራረባቸው በጣም የሚያመረቃ ብቻ ሳይሆን፣ ትችታቸውም ትክክል ነው ብሎ መደምደም ይቻላል። „አዲስ ባሬስታ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ“ የሚለውን የወጣቱን የበኃይሉ ገብረ እግዚአብሄርን ግሩም ንባብ፣ „ፍራሽ አዳሽ“  በሚል በተስፋሁን ከበደ የተደረሰውን ግሩም የሆነ የፖለቲካ ጉራማይሌ አቀራረብ፣ „ግራ የገባው ህዝብና ግራ የገባው  መሪ„  በሚል በመምህርት እፅነት ከበደ የተደረሰውንና የተነበበውን ትችታዊ ጽሁፍ፣  እንዲሁም  „በእነ እትዬ በላይነሽ መንደር ውስጥ የጠቅላይ ሚኒስተሩ የአንድ ዓመት ግምገማ“  በሚል በታወቀው ገጣሚውና በስነ ፅሁፍ ጸሀፊው በፈቃዱ ከበደ የቀረበው ንባብ፣ በእርግጥም የአበደውን ሰውና ቡጭቅጫቂ ለብሶ የሚዘዋወረው እንደ ዕብድ የሚቆጠር ሳይሆን፣ ዋናው ዕብድ በሀብቱ በመመካት አርቆ-አሳቢነት በጎደለው መልክ የአገርን እሴት የሚያፈራርሰውና አገሪቱን የሚቸበችበውን የሚወነጅል፣ “አጭበርባሪ ሁላ ሰው ለመሆን በርቱ“ በሚል በሰላማዊት ደስታ የቀረበውን ግጥም አዘልና የህብረተሰብአዊ ትችት አቀራረብ.. ወዘተ. የቀረቡትንና የተነበቡትን አያሌ ስነ-ፅሁፎችንና ግጥሞችን፣ እንዲሁም በአንድ ግለሰብ ተዋንያን(one man show) የሚቀርቡትን ድራማ መሰልና የካባሬት አቀራረቦችን ጠጋ ብለን ስንመረምርና ስንመለከት አብዛኛው ህዝብ በዶ/ር አቢይ አገዛዝ እንዳልተደሰተ መገንዘብ ይቻላል። በተለይም በየቦታው ያለው የፀጥታ መደፍረስ፣ የፅንፈኛ አስተሳሰብ መስፋፋትና፣ አብዛኛው ህዝብ በፍርሃት እንዲዋጥ ማድረግ፣ በዘር እያሳበቡና መጤ ነህ በማለት ሰው ከተወለደበት፣ ከአደገበትና ሀብት ካፈራበት፣ እንዲሁም ቤተሰብ መስርቶ የልጅ ልጆች ካየበት መንደር ወይም ከተማ ማባረር፣ ማሰቃየትና ወደ ሜዳ ላይ እንዲጣል ማድረግ፣ አንዳንዱ የሰራውን ቤት፣ የተሰራው ቤት ከዕቅድ ውጭ ነው በማለት ቤቱ በቡል ዶዘር እንዲፈራርስና አባትና ሚስት ከነልጆቻቸው ካለመጠለያ ሜዳ ላይ እንዲወድቁ ማድረግ፣ ህግንና ስርዓትን በሚገባ አለማክበርና የሰውም መብት ምን ማለት እንደሆነ ባልገባው ፖሊስ የሚደበደበውና የሚገደለው፣ እንዲሁም በተደጋጋሚ በሚደረግ የገንዝብ ቅነሳ (Devaluation) የተነሳ የዋጋ ግሽበት እንዲናር ማድረግ፣ ለወጣቱ የስራ መስክ ለመክፍት የሚያስችል የአጭርና የረጅም ጊዜ ዕቅድ አለመኖሩ… ወዘተ. … ወዘተ.  እነዚህ ሁሉ ሰፊውን ህዝብ ተስፋ እንዳስቆረጡት የማይካድ ሀቅ ነው። ከዚህም ባሻገር በአገራችን ምድር አንድ መንግስት ብቻ ሳይሆን ሁለትና ሶስት መንግስታት ያሉ ይመስል አንዳንዱ እየተነሳ የሚደነፋበትና የሚዲያ የአሰራር ህግን፣ አገራዊ  አሴትን ያላገናዘበና፣ በአማዛኝ ጎኑ ከአንድ ብሄረሰብ የተውጣጡ ምሁራን ነን ባዮች ሳይንሳዊና የቴዎሪ መሰረት የሌለውና በኢምፔሪካል ደረጃ ሊረጋገጥ የማይችል ወሬ የሚያራግቡበት ሚዲያ በማቋቋም የሚደነፉበት አገር ሲታይ አብዛኛውን ህዝብ ማስደንገጡ የሚያስገርም ጉዳይ አይደለም። በዚህም የተነሳ ዶ/ር አቢይና አገዛዛቸው ከስምንት ወራት በፊት የነበራቸውን ተቀባይነትና የህዝብ አመኔታ በከፍተኛ ደረጃ እንደቀነሰ ያለው ሁኔታ በጉልህ የሚያረጋግጥ ነው። በመሆኑም ዶ/ር አቢይ በአሁኑ ወቅት በህዝቡ ዘንድ 25% ብቻ ተቀባይነት እንዳላቸው በግልጽ ያልወጡ እስታትስቲኮች ያረጋግጣሉ።

በሌላ በኩል የህዝባችን ምኞትና(Expectation) ደረጃ በደረጃ ተግባራዊ መሆን ያለባቸውን ነገሮች መፈለግ ትክክል የሆነውን ያህል፣ በዶ/ር አቢይ ላይ የተጣለውን አደራና በቀላሉ ተግባራዊ ሊሁኑ ያልቻሉና የማይችሉ ነገሮችንም ማየትም የሚያስፈልግ ይመስለኛል። በዶ/ር አቢይ ዘንድ „የለውጥ ፍላጎት“ ቢኖርም እንኳ ህዝባችንና አገራችን የሚፈልጉት አስተማማኝና በሂደት ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው ለውጥ የቱን ያህል በዶ/ር አቢይና „የለውጥ ኃይሎች“ ናቸው በሚባሉት ጭንቅላት ውስጥ መቀረጹን ማወቅ አስቸጋሪ ነው። ከዚህም በላይ ሰፊው ህዝብና በተለይም ደግሞ የለውጥ ያለህ እያለ የሚጮኸው ኃይል ስለለውጥ በሚያወራበት ጊዜ ምን ዐይነት ለውጥ ማየት እንደሚፈልግና፣ በተለይም ደግሞ ለውጡ አይታይም ወይም ደግሞ ለውጡ ላይ ላዩን ብቻ ነው በሚለው አክቲቪስት ዘንድ መምጣት ያለበት ለውጥ፣ የቲዎሪና ሳይንሳዊ መሰረቱ በግልጽ ሲቀመጥ አይታይም። ስለሆነም አማራጭ ሳያቀርቡ ወይም ደግሞ በሳይንስና በቲዎሪ ደረጃ ትንታኔ ሳይሰጡ ትችት መሰንዘሩ ውዥንብር ከመንዛት በስተቀር ምንም የሚያመጣው ነገር የለም። በተለይም ህብረተሰብአዊ ለውጥ(Social transformation) በሚለው መሰረታዊ ጉዳይ ላይ ግልጽ የሆነ አሰተሳሰብ እስከሌለን ድረስ ጩኸታችን የህዝባችንን መሰረታዊ ችግር በፍጹም ሊፈታው አይችልም። ከዚህ ስንነሳ እራሱ የዶ/ር አቢይ አገዛዝም „ህዝብንና ዓለምን ያስደመመ ለውጥ እየተካሄደ ነው“ እያለ በየጊዜው ለማረጋገጥ ቢሞክርም ሌላውን ትተን በምድር ላይ ያለውን ሁኔታ ስንመለከት አገዛዙ ስለለውጥ ያለው አስተሳሰበ እጅግ የተዛባ እንደሆነ እንመልከታለን።

ከዚህ ዐይነት ውዥንበር፣ ግራ መጋባትና ተስፋ መቁረጥ በመነሳት ይህ ዐይነቱ የተዛነፈ አስተሳሰብ እንዴት ሊስፋፋ እንደቻለ ለማሳየት እሞክራለሁ። በተለይም ቀድሞም ሆነ ዛሬ የውጭ ኃይሎች በአገራችን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ህይወት ውስጥ ጣልቃ በመግባት ያለፈውንም ሆነ የዛሬውን አገዛዝ በማታለልም ሆነ ጫና በማድረግ ለቀውሱ መባባስ የማይናቅ አስተዋፅዖ እንዳበረከቱ ለአብዛኛዎቻችን ይህን ያህልም ግልጽ አይደለም። በተለይም የውጭ ኃይሎች በተለያዩ ግልጽና ግልጽ ያልሆኑ ቀውሱንና ድህነትን ማራዘሚያ መንገዶች በመጠቀም ብሄራዊ ነፃነታችንን እንዴት እንደሚገረስሱ፣ እርስ በርሳችን እየተናቆርን እንድንኖር የሚያደርጉትን ተንኮል በግልጽና በድፍረት ለመወያየትም ሆነ ለመከራከር ፈቃደኛ ባለመሆናችን የአገራችንን ሁኔታ ከአንድ አቅጣጫ ብቻ እንድናየው ተገደናል። ይህም ቢሆን በጠለቀ መልክ ሳይሆን በስሜታዊነት ብቻ የሚካሄድ ነው።  ከዚህ በመነሳት አገራችንን ያለችበትን ሁኔታና የህዝባችንና የእራሳችንንም ግራ መጋባት በዚህች ጽሁፍ ለማሳየት እሞክራለሁ።

 

ግራ የሚያጋባ ሁኔታ ሲባል ምን ማለት ነው !

በመሰረቱ ከተፈጥሮ በስተቀርና በተፈጥሮ ውስጥ ከሚገኙ ነገሮች ውጭ በአንድ አገር ውስጥ የሚታዩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የስነ-ልቦና ሁኔታዎች ወይም ቀውሶች፣ የቤቶችና የመንገድ አሰራሮች፣ ወይም ልዩ ልዩ የአጭርና የረጅም ጊዜ የፍጆታ ዕቃዎች… ወዘተ. የሰው ልጅ የማሰብ ወይም ያለማሰብ ኃይል ውጤቶች ናቸው። በአንድ አገር ውስጥ አብዛኛው ነገር ካለዕቅድና ከአብዛኛው ህዝብ ፍላጎት ውጭ የሚሰራና ሁሉም ነገር ተዝረክርኮ የሚገኝ ከሆነና፣ አብዛኛውም ህዝብ ግራ የሚጋባ ከሆነ በመሰረቱ እነዚህ ነገሮች የሚያሳዩት በአንድ አገር ውስጥ የሰፈነው አገዛዝ የማሰብ ሁኔታ(The State of Mind) ውጤቶች ናቸው ማለት ይቻላል። በሌላ አነጋገር፣ ስለግራ የሚያጋባ ሁኔታ በምንናገርበት ጊዜ ስለአገዛዙ፣ ስለሚከተለውና ተግባራዊ ስለሚያደርገው ፖሊሲ ብቻ ነው ማውራት የምንችለው። ይህም ማለት እንደኛ በመሳሰሉ አገሮች በምድር ላይ የሚታዩ ሁኔታዎች፣ በአንዳንዶች የሚፈጸሙ ወንጀሎች፣ የፍትህ መጓደልና አስተሳሰብን ሊያበላሹ የሚችሉ ሁኔታዎች መፈጠር፣ ከፖለቲካ ውይይት ይልቅ ጉልበት የሚያመዝን ከሆነ፣ እያንዳንዱ ጠበንጃ ያዝኩኝ ብሎና ስልጣኑን ተገን አድርጎ ሌላውን ምስኪኑን የሚደበድበው ወይም የሚገድለው ከሆነ… ወዘተ. … ወዘተ. እነዚህ ነገሮች የሚያረጋግጡት የአንድ አገር ፖለቲካ በፍልስፍናና በሳይንስ ላይ ያልተመሰረተ ወይም በአቦ ሰጡኝ የሚካሄድ ነው ማለት ይቻላል። በተለይም አንድ አገዛዝ በራሱና በምሁራን ጥረት ሳይሆን በውጭ ኃይሎች እየተመራና እነሱን እየተለማመጠ ተግባራዊ የሚያደርጋቸው ፖሊሲዎች በሙሉ አገርን ከማረጋጋት፣ ህዝባዊ ሀብት ከመፍጠርና ውብ ውብ ነገሮችን ከመስራት ይልቅ ዝርክርክር ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ የሚደረግ ከሆነ ሰፊው ህዝብ ግራ መጋባቱ የማይቀር ጉዳይ ነው። አንድ መንግስት ወይም አገዛዝ ከውጭ ኃይሎች ጋር በማበርና ከእነሱ ትዕዛዝ በመቀበልና የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም አንድ ህዝብ ያለውን ተፈጥሮአዊ የመፍጠርና እራሱን የማሻሻል ኃይል ተግባራዊ እንዳያደርግ እንቅፋት የሚደረግበት ከሆነ አንድ አገር በጸና መሰረት ላይ ሊገነባ አይችልም። ይህ ዐይነቱ በውስጥና በውጭ ኃይሎች መሀከል ያለው ያልተቀደሰ ጋብቻ የግዴታ ህዝቡን ግራ ማጋባቱ የማይቀር ጉዳይ ነው። በዚህ ላይ ይህንን አስቸጋሪና ውስብስብ ሁኔታ ለማስተማር ዝግጁ ወይም ፈቃደኛ የሆነ ኃይል ከሌለ፣ ወይም ደግሞ የተማረው እራሱ የሚሰራው ደባ ግልጽ ካልሆነለት ሰፊው ህዝብ ለምን እንደሚኖርና ወዴትስ እንደሚጓዝ ለማወቅ የማይችልበት ሁኔታ መፈጠሩ የማይቀር ጉዳይ ነው።

ከዚህ ስንነሳ በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ህዝብ ግራ ሲጋባ በመሰረቱ ግራ እንዲጋባ ያደረገውን ዋና ምክንያት መመርመር ያለብን ይመሰለኛል። ላይቢኒዝ የሚባለው ካልኩለስ በመባል የሚታወቀው የሂሳብ ዘርፍ ፈጣሪና ሳይንቲስት „አንዳች ነገር ካለአንዳች በቂ ምክንያት ሊከሰት አይችልም ይላል።“  ስለሆነም በአገራችን ምድር፣ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው በአገሪቱ ውስጥ፣ በተለይም በትላልቅ ከተማዎችና መንደሮች ውስጥ ያሉትን ሁኔታዎችና እዚህና እዚያ ግራ በመጋባት የሚዘዋወረውን ወጣትም ሆነ በዕድሜ የገፋውን ስንመለከት፣ ይህ ዐይነቱ ግራ የሚያጋባ ሁኔታ የፖለቲካውና የመንግስቱ አወቃቀር ነፀብራቅ ነው ማለት ይቻላል። ከዚህም በሻገር ዝርክርኩ የአገራችን ሁኔታ የሚያረጋግጠው ተማርኩ የሚለውንም የአስተሳሰብ ወይም የዕይታ ሁኔታ ነው።  በአንድ አገር ውስጥ በምድር ላይ የሚታዩ ሁኔታዎች በአንድ ወቅት ወይም ከመቅጽበት የሚፈልቁ ሳይሆኑ በታሪክ ሂደት ውስጥ እየተከማቹና እየተወሳሰቡ የሚመጡ ናቸው። ስለሆነም በተለያየ የታሪክ ወቅት ስልጣንን የጨበጡ አገዛዞች ወይም ስልጣንን ለመጨበጥ ሲታገሉ የነበሩ ከመጀመሪያውኑ እንደነዚህ ዐይነት ነገሮች ለምን መፈጠር ቻሉ? ምክንያቶቻቸው ምንድናቸው? ብሎ በመጠየቅ የተዝረከረከውን ሁኔታ መልክ ለማሲያዝ የሚጥሩ፣ የሚያጠኑና ወይም እንዲጠና የሚያደርጉ ሳይሆኑ በእልክና በአወቅሁኝ ባይነት ባለው አስቀያሚ ሁኔታ ላይ ሌላ በመጨመር ችግሩ ውስብስብና እንዳይፈታ ለማድረግ ይበቃሉ።  ይህ ዐይነቱ ችግርን መደራረብና ውስብስብ ማድረግ በአገራችን ብቻ ሳይሆን፣ ልክ አንድ ዐይነት ባህርይ ያለን ይመስል በአብዛኛዎች የአፍሪካ አገሮችም፣ በተለይም በዋናና በሌሎች ትላልቅ ከተማዎች ውስጥ የሚታዩና ጭንቅላትን የሚዘገንኑና በጣምም የሚያስፈሩ ሁኔታዎች ናቸው።  ይህም የሚያሳየው አገዛዞችም ሆነ የተማረው አንድ ዐይነት የመንፈስ ችግር እንዳለባቸው ነው በምድር ላይ ያሉት ነገሮች የሚያረጋግጡት። በእንደዚህ ዐይነት ከተማዎች ደግሞ ደረቱን ገልብጦ በመንገድ ላይ ለመንቀሳቀስ የሚችለው ጉልበት ያለው ወይም በስልጣኑ የሚመካ፣ ካሊያም ደግሞ ጠበንጃ የያዘ ፖሊስና ወታደር ብቻ ነው።

በአገራችንም ሆነ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ውሰጥ የተፈጠሩትን ግራ የሚያጋቡ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ቀውሶችና እንዲሁም ካለዕቅድ የተሰሩ ከተማዎችን ስንመለከት፣ በአንድ በኩል የፖለቲካ አወቃቀርና የፖሊሲዎች ነፀብራቆች ሲሆኑ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ባለፉት 70 ዐመታት በተለይም ካፒታሊዝም ዓለም አቀፋዊ ባህርይ በመውሰድና እነዚህን አገሮች ወደ ተቀጥያነትና ወደ ታዛዥነት በመለወጡም ጭምር ነው። በየአገሩ የተተከሉትን የመንግስት መኪናዎች፣ ማለትም የሲቪሉን፣ የፖሊሱንና የፀጥታውን፣ የወታደሩንና ሌሎች ተቋማትን(Institutions) በምንመለከትበት ወይም በምንመረምርበት ጊዜ እነዚህ ሁሉ ተቋማት በከፍተኛ ዕውቀት በመደገፍ ከታች ወደ ላይ ቀስ በቀስ ከሀገር ፍላጎትና ሀብት ጋር በመነፃፀር አገርን ለማሳደግ ወይም ለማበልፀግ የተገነቡ ተቋማት ሳይሆኑ የውጭ ኃይሎችን ፍላጎት ለማሳካት ወይም ለማስፈጸም የተቋቋሙ ናቸው። ከመጨቆኛ መሳሪያነትም የማያልፉ ናቸው። በሌላ አነጋገር፣ አገዛዞቹ በሙሉ አንድ መንግስትና አገዛዝ አንድን አገር ሁለንተናዊ በሆነ መልክ የመገንባት ኃላፊነት እንዳለባቸው ያልተገነዘቡና ለህዝብና ለአገር ደንታ የሌላቸው፣ እንዲሁም በራሳቸው ዓለም ውስጥ ለራሳቸው ብቻ የሚኖሩ እንደሆኑ መገንዘቡ ከባድ አይደለም። ስለሆነም በተለያዩ የአፍሪካ አገሮችና በአገራችንም ጭምር በምድር ላይ ያለውን የተዝረከረከ ሁኔታና የተስፋፋውን ድህነት ስንመረምር፣ እነዚህ ነገሮች የተፈጠሩትና አገሮችን መቀመቅ ውስጥ የከተቱት ካፒታሊዝም ከውጭ ሲገባ በተጠና መልክ ባለመግባቱና አገዛዞችም የካፒታሊዝምን ውስጣዊ ሎጂክ ባለመረዳታቸው ነው።

ስለሆነም ቢያንስ ባለፉት ሰላሳና አርባ ዐመታት በአገራችንም ሆነ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ተግባራዊ የሆኑትን ፖሊሲዎች በመንመረምርበት ጊዜ ፖሊሶዎቹ በሙሉ ከዓለም አቀፍ ካፒታሊዝም ጋር የተያያዙ እንጂ የየአገሩን ህዝብ ፍላጎት ለማርካትና ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ መሰረት ለመጣልና፣ ሰላምና መረጋጋት የሰፈነበት አገር ለመመስረት አይደለም። የአገራችንም ሆነ የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች አገዛዞች፣ ሰው፣ አገር፣ ማህበረሰብና ህብረተሰብ ማለት ምን ማለት ናቸው? ብለው ስለማያወጡና ስለማያወርዱ፣ ከዚህም ባሻገር የህዝብ ተቆርቋሪ የሆኑ የሲቪል ማህበራት ስለሌሉ፣ ወይም ደግሞ ያሉት በደንብ ያልተደራጁ በመሆናቸውና ምሁራዊ መሰረታቸውም የሳሳ በመሆኑ በየአገሮቻቸው ውስጥ ተግባራዊ የሚሆኑትን ፖሊሲዎች ለመቀዋምና አማራጭ ወይም የተሻለ መፍትሄ ለማቅረብ በፍጹም አይችሉም። በዚህም ምክንያት የተነሳ ፖለቲካንና የመንግስትን መኪና እንደግል ሀብታቸው የሚቆጥሩ አገዛዞች ከውጭው ዓለም ጋር በመቆላለፍና ትዕዛዝ በመቀበልና በማስፈጸም አንድ ህዝብና አገር ሊወጡት የማይችሉትን ሁኔታዎች ይፈጥራሉ። እነዚህ ሁኔታዎች ደግሞ በተለይም ወጣቱን ትውልድ ግራ በማጋባት ወዳልባሌ ቦታ ይጥሉታል። የተማረና ኃላፊነት የሚሰማውና አገር ወዳድ ወጣት ትውልድ ማፍራት እንዳይቻል የየመንግስታቱና የዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው ፖሊሲዎች ከፍተኛ መሰናክል ሆነዋል ማለት ይቻላል።

ከዚህ አጭር ሁኔታ ስንነሳ መጠየቅ የሚኖርብን ጉዳይ ለምንድን ነው በየኤፖኩ የሚነሱ አገዛዞች ብዙም ሳያስቡ ይህንን ወይም ያኛውን ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ህብረተሰብአዊ መመሰቃቀልን የሚፈጥሩት? ለምንድን ነው ራሳቸውን የማይጠይቁት? ለምድን ነው በምድር ላይ የሚታዩት ነገሮች በሚገባ የማይታያቸውና መፍትሄ ለመፈለግ የማይጥሩት? ለምንድን ነው እየመላለሱ ተመሳሳይ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በማውጣት አንደኛውን የህብረተሰብ ክፍል በሀብት እንዲደልብ ሲያደርጉ፣ አብዛኛውን ደግሞ ወደድህነት ዓለም ውስጥ የሚጥሉት?  ለምንድ ነው በችግር ላይ ችግር እየፈጠሩና እያከማቹ የሰውን ህይወት የሚያከብዱት? የሚለውን ነው መጠየቅ ያለብን። ጥንትም ሆነ በ20ኛው ክፍለ-ዘመን ብቅ ያሉ ፈላስፋዎች ለእንደዚህ ዐይነት ጥያቄዎች የሚሰጡት መልስ እንደነዚህ ዐይነት ሰዎች ወደ ውስጥ ለማየት(Reflect)  የማይችሉና ገና ስሜትን ያላደበሩና ውስጣዊ ፍላጎትም የሌላቸው በመሆናቸው ነው የሚል መልስ ነው። ይህ ዐይነቱን አባባላቸውን ለማረጋገጥ የሚመረኮዙበት መሰረተ-ሃሳብ የሰው ልጅ የተጓዘበትን አስቸጋሪ ሁኔታ በመመርመርና የጭንቅላትን መዳበርም ሆነ አለመዳበር ሊያስከትል የሚችለውን ሁኔታ ካገናዘቡ በኋላ ነው። ስለሆነም ማንኛውም ሰው በአንድ የታሪክ ወቅት አዳዲስ ነገሮች ቢፈጥርም፣ በሌላ ወገን ደግሞ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በአንድ አገር ውስጥ የሚፈጠሩ ነገሮች እንደልማድ በመወሰድ የአንድን ሰው ወይም ህብረተሰብ አስተሳሰብ ይቀርጹታል። ይህም ማለት በአብዛኛው ጎኑ ህዝብም ሆነ መሪዎች የሁኔታዎች ተገዢ በመሆን በምድር ላይ የሚታዩ ነገሮችን እንዳያዩና መልስም እንዳይፈልጉ ይገደዳሉ። የግሪክ ፈላስፎች „ጭንቅላት ማየት ካልቻለ ዐይንም ማየት አይችልም“ የሚለው አባባል በአገራችንም ሆነ በተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ውስጥ እንደሰፈነና የአገዛዞችን የማየት ኃይል እንዳጨለመው መረዳት ይቻላል። ከዚህ ስንነሳ በአገራችን ምድር የሚታየውን የተወሳሰበ ሁኔታ ከአንድ አቅጣጫ ብቻ ሳይሆን ከሌላ አቅጣጫም ለመመርመር መሞከሩ ለችግራችን መፍትሄ የሚሆን የተጠጋጋ መልስ ለማግኘት እንችላለን ብዬ አምናለሁ።

 

ግራ የተጋባ መሪ!

በአንድ አገር ውስጥ ስልጣንን የሚጨብጥ መሪ ሂድና ይህንን ህዝብ ምራ፣ አቅጣጫውንም አሳየው ብሎ ከሰማይ እግዚአብሄር የሚወረውረው ወይም የሚልከው ሳይሆን የአንድ ህብረተሰብና በአንድ የታሪክ ወቅት የሚከሰት የኃይል አሰላለፍ ውጤት ነው። በአገራችን ምድር ስልጣንን የሚጨብጡ ኃይሎች በሙሉ ከታች ወደ ላይ በልምድና በተመክሮ አንድን አካባቢን በማልማትና በማሳደግ፣ ተቋማትን በመገንባት፣ በልዩ ልዩ የስራ-ክፍፍል የሰለጠኑ የማዕከለኛና የአነስተኛ ኢንዱስትሪዎችንና፣ ሌሎች በአንድ አካባቢ የሚኖርን ህዝብ እንደ አንድ ዜጋና የዚያው አካባቢ አካል መሆኑን እንዲሰማው የሰለጠነ ስራ በመስራት የተገነቡ ሳይሆን በአጋጣሚ ስልጣንን የሚይዙ ናቸው። ይህ ዐይነቱ ስልጣንን የመያዝ ሁኔታ በተለይም በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን ጎልቶ የሚታይና፣ አንድ ሰው የትልቅ ቤተሰብ ልጅ በመሆኑ ወይም የዘመድ አዝማድ በመሆኑ ልምዱና ተመክሮው ምን እንደሆነ ሳይታወቅ ዲግሪ ስለጨበጠ ብቻ ሚኒስተር የሚሆንበትን ሁኔታ ሳንከታተልን የቀረን አይመስለኝም። አሁን ባለንበት ክፍለ-ዘመን ደግሞ በተለይም እንደኛ ባሉ ወደ ኋላ በቀሩ አገሮች በተለይም ጠቅላይ ሚኒስተር ሆነው የሚሾሙት ለአገራቸው አስተዋፅዖ ሊያበርክቱ ይችላሉ፣ ዕድገትን የማምጣት ችሎታ አላቸው፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የበለፀገች አገር ሊገነቡ ይችላሉ፣ በዚያው መጠንም ስላምንና መረጋጋትን በማስፈን አንድ ህዝብ ተከብሮ እንዲኖር ለማድረግ ብቃት ያላቸው መሪ ናቸው ተብለው የሚመረጡ ሳይሆኑ፣ በተለይም የአሜሪካንንና የተቀረውን የዓለም ኮሙኒቲው በመባል የሚታወቀውን ፍላጎት የሚያሟሉና ትዕዛዝም ሊቀበሉ ይችላሉ ተብለው የሚገመቱና በደንብ ከተጠኑ በኋላ ስልጣን ላይ እንዲወጡ የሚደረጉ ናቸው። ይህንን ጉዳይ በተለይም የደርግ አገዛዝ ሊወድቅ ሲል ያየነው ሀቅና የመለስ ዜናዊ ስልጣን መያዝ ከውጭ ኃይሎች ጥቅምን ማስጠበቅና አገራችንን በዘለዓለማዊ ትርምስ ውስጥ ከማስገባት ጋር የተያያዘ ስሌት እንደነበር ይታወቃል። ለዚህ ነው መለስ ዜናዊ የምዕራብ አገሮች ጓደኛ ነው በመባል ሙገሳና ጥሩ አቀባበል ይደረግለት የነበረው።  መለሰ ዜናዊ ከሞተ በኋላ ስልጣንን የተረከበው ኃይለማርያም ደሳለኝ እንደዚሁ አገራዊ ባህርይ፣ የዕድገት ህልምና አጀንዳ ያለው መሪ ሳይሆን የምዕራቡን ፍላጎት ተግባራዊ የሚያደርግና የበለጠ አለመረጋጋትና ህዝብ እንዲዋከብ የማድረግ ብቃት አለው ተብሎ ስለታመነበት ብቻ ነው ስልጣንን ሊይዝ የቻለው። ይህ ዐይነቱ መሪ ደግሞ እንደሎሚ ተመጦ ተመጦ ካለቀና ተልዕኮውን ካስፈጸመ በኋላ አገር የመምራት ብቃት የለውም በመባል በሌላ ኃይል የመተካቱን ጉዳይ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ውስጥም የተመለከትነው ሀቅ ነው።

በአገራችን ምድር በተለይም ስልጣንን ለመያዝ በሚሯሯጡት ተቃዋሚ ነን በሚሉትና በምሁራን ዘንድ ያለው የፖለቲካ አመለካከት ወይም ትንታኔ የአገራችንን የመንግስት መኪና አውቃቀርና የገዢዎችን ስልጣን መቀዳጀትና አገርን ማሸት ንጹህ በንጹህ በጠባብ የፖለቲካ ስሌት ማየቱ ነው። በዚህም የተነሳ በውስጥ አገዛዙና በውጭ ኃይሎች መሀከል የሚኖረውን የእከክልኝ ልክከልህ መተሳሰርና በጥቅም መያያዝ በፖለቲካ ተንታኞች ዘንድ በፍጹም ግንዛቤ ውስጥ አይገባም። ቀድሞም ሆነ ዛሬ በአገራችን ምድር የተፈጠሩት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የስነ-ልቦና ቀውሶች፣ እንዲሁም እዚህና እዚያ አለመረጋጋት መታየት በንጹህ መልካቸው በአገር ውስጥ ባሉት ኃይሎች ወይም በመንግስት ብቻ የሚፈጠሩ ናቸው። አገራችንም ከውጭው ዓለም ጋር በተለያዩ ድሮች ያልተሳሰረችና እንደደሴትም ስለምትታይ  የውጭው ኃይል በአገራችን የፖለቲካ ህይወት ላይ ምንም ዐይነት ተፅዕኖ የለውም የሚል ግንዛቤ በፖለቲካ ተንታኞች ዘንድ ተቃባይነትን ያገኘ ይመስላል። ስለሆነም በአገራችን ምድር ቀድሞም ሆነ ዛሬ የተከሰቱትና የሚከሰቱት ቀውሶች አይ ካለማወቅ ወይም ግራ ከመጋባት፣ አሊያም ደግሞ አገዛዞች በባህርያቸው ፀረ-ዲሞክራት በመሆናቸው የሚመነጩ እንጂ ግሎባል ካፒታሊዝም በአገራችን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሁኔታ ላይ የሚጫወተው ሚና እዚህ ግባ የሚባል አይደለም የሚል ኢ-ፖለቲካዊና ኢ-ሳይንሳዊ ትንተናና ድምዳሜ ነው። መሪዎችም የውጭውን ኃይል ጥቅም አስጠባቂና አገልጋይ ሳይሆኑ የራሳቸውንና የጥቂቱን ኤሊት ጥቅም ብቻ የሚያስጠብቁ ናቸው የሚል ግንዛቤ አለ።

ይህንን ወደ ጎን ትተን ወደ ተጨባጩ ሁኔታ ስንመጣ በአንዳንዶች ግምት ወይም እነሱ ደረስንበት በሚሉት ማስረጃ የዶ/ር አቢይ ስልጣን መያዝ ዝምብሎ ከሰማይ ዱብ ያለ ሳይሆን በውጭ ኃይሎች ውስጥ ለውስጥ የተሰራ ስራና፣ በእነመለስ ዜናዊና በተቀሩት የህወሃት ታጋዮች የተጀመረውንና ያልተገባደደውን የቤት ስራ አሁን ደግሞ በሌላ ሽፋን ለማስቀጠልና እንዲገባደድ ለማድረግ በአገራችንና በህዝባችን ላይ የተጠነሰሰ ትልቁ ሴራ ነው የሚል ነው። ይህንን አባባል ተቀበልንም አልተቀበልንም፣ የኮንስፒራሲ ቲዎሪ አልነውም አላልነውም የአንድን አገዛዝና መሪውን ፖለቲካ መመርመር የምንችለው ከሚያካሄደውና ከሚከተለው ፖሊሲ በመነሳት ብቻ ነው። በሌላ ወገን ደግሞ አንድ መሪ የራሱ የሆነ ራዕይ ሊኖረው ቢችልም የተኮተኮተበት ዕውቀት፣ የተወሳሰቡ ነገሮችን የማየት ችሎታውና ለነዚህ ነገሮች መልስ ለመስጠት ያለው ብቃትና፣ እንዲሁም ደግሞ ቀደም ብለው የተፈጠሩና የተከማቹ በምድር ላይ የሚታዩ ሁኔታዎች ፖለቲካውን ሊወስኑ እንደሚችሉም ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። ይህ ዐይነቱ የተወሳሰበ ችግር ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴና የሲቪል ማህበረሰብ በሌለባቸው እንደኛ በመሳሰሉትና በተቀሩት የሶስተኛው ዓለም አገሮች መሪዎችንም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የከተተና በቀላሉ ሊቀረፍ የማይችል ነገር ነው።  በተጨማሪም በመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ በህዝብ ገንዘብ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራቶች ካለጉቦ ለመስራት አለመፈለግ፣ ወይም ደግሞ ሰውን ማንገላታትና ማበሳጨጥ እንደ አንድ ዐይነት የስራ ዘዴዎችና እንደባህልም በሚወሰዱበት አገር ውስጥ ስርዓት ያለው ነገር ለመስራትና ሁለ-ገብ የሆነ ዕድገት ለማምጣት በጣም ያስቸግራል። ስለሆነም አንዳንድ መሪዎች አንድ ነገር ለመስራት ቆርጠው ቢነሱም ወደፊት እንዳይገፉ የሚያግዷቸው ከፊታቸው የተደቀኑ እንቅፋቶች አሉ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጻድቃን ገብረትንሳዔ አዲሱ የወያኔ ፊት! ከቢቢሲው ጁሊያን ማርሻል ጋር (ኦሃድ ቤንዓሚ)

ከዚህ ባሻገር በአፍሪካ ውስጥ ብቅ ለሚሉ ወጣት መሪዎች አስቸጋሪው ሁኔታ በየአገሩ የሰፈነው እጅግ ደካማ የሆነ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ነው። እንደሚታወቀው ማንኛውም ዕውቀት የሚባለው ነገር በምዕራቡ ዓለም የተፈጠረና ለትምህርት መመሪያ ሆኖ የተዘጋጀውን ነው የምንማረውና ተግባራዊም ለማድረግ የምንጥረው። በተለይም እንደ ኢኮኖሚክስና ሌሎች የሶሻል ሳይንስ ትምህርቶች ተጣመውና በተቆጠበ መልክ ስለተዘጋጁ አብዛኛዎቻችን ዋናውንና አስፈላጊ የሆነውን የካፒታሊዝምን አነሳስና ምክንያቶች፣ አስተዳደግና ውስጣዊ ህግ፣ ከአገር ውስጥ መስፋፋት አልፎ ዓለም አቀፋዊ ባህርይ በመውሰድ የሰባት ቢሊዮንን ህዝብ ህይወት መደንገግ መቻል ደረጃ በደረጃ ስለማንማር፣ ይህ ዐይነቱ ሁኔታ በአስተሳሰባችን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ለማሳደር ችሏል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በአገራችንም ሆነ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ወደ ውጭ ወጣ ብሎ መከራከር ባለመለመዱና፣ በጣም ጥቂት የሆኑ ምሁራን መድረኩን ስለሚይዙ ዕውቀት የሚባለው ነገር በሰፊው እንዳይንሸራሸርና ሌሎች የራሳቸውን አስተያየት በመስጠት አድማሱ እንዳይሰፋ ይደረጋል። በዚህ ላይ ባህልና ዕውቀት የሚባሉት ነገሮች በዋና ከተማዎች ብቻ ጎልተው የሚታዩ ስለሆነ በሰፊው ህዝብና በከተማ ነዋሪው መሀከል ከፍተኛ የሆነ የባህል ልዩነት ይታያል። በዚህ ምክንያት የተነሳ ሰፋ ያለ አገራዊ ዕውቀት ማዳበርና በምድር ላይ የሚታዩ ነገሮችን፣ የፖለቲካ ሆኔታዎችንና የምርት ግኑኝነቶችን በሰፊው ማጥናትና የችግሮችን መነሻ በማወቅ መፍትሄ ለመፈለግ ሙከራ ማድረግ አይቻልም። ይህ ዐይነት ውስን የሆነ የዕውቀትና የማቴሪያል ዕድገት የግዴታ በመሪዎች ላይም የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ የማይቀር ጉዳይ ነው። በሌላ አነጋገር፣ የአንድን መሪ ወይም አገዛዝ አስተሳሰብ የሚወስኑ አያሌ ነገሮች አሉ ማለት ነው። ይህም ማለት በአንድ አገር ውስጥ ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴና የነቃ ምሁራዊ ኃይል እስከሌለ ድረስ የመሪዎችም አስተሳሰብ ውስን ይሆናል ማለት ነው።  በአንፃሩ የምዕራ አውሮፓን የፖለቲካና የኢኮኖሚ፣ እንዲሁም የባህል ዕድገት ስንመለከት ዕውቀት የሚባለው ነገር ሁሉ ከስልጣን ውጭ በነበሩና ባሉ ምሁራን የተፈጠረና የተስፋፋ፣ እንዲሁም መልክ እየያዘ የመጣ ነው። አገዛዞችም ቀስ ቀስ እያለ በመጣው ምሁራዊ እንቅስቃሴ በመገፋትና በመዋጥ ሳይወዱ በግድ የግዴታ ለካፒታሊዝም ዕድገት አመቺ ሁኔታዎችን መፍጠር ችለዋል። በተለይም ፍልስፍናና የተፈጥሮ ሳይንስ መፈጠርና መዳበር፣ እንዲሁም መስፋፋት ከጀመሩበት ከ14ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የገዢ መደቦች ሳይወዱ በግድ ሰፋ ያለና በሳይንሳዊ ጥናት ላይ የተመረኮዘ አገራዊ ፕሮጀክት ተግባራዊ በማድረግ ለህብረ-ብሄር የሚሆን መሰረት ለመጣል ችለዋል። ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ ዕውቀቶችም የተለያዩ ምሁራንን የሚያይዙ በመሆናቸው ግልጽና የጦፈ ክርክር በማድረግ ለህብረ-ብሄር ግንባታ የሚያመቹ ፍቱን ዘዴ መፈለግ የምሁራኑ ተግባር ነበር።  ይህ በራሱ አዳዲስ የህብረተሰብ ኃይሎችን በመፍጠርና እንዲተሳሰሩ በማድረግ፣  የኢኮኖሚም ሆነ የባህል እንቅስቃሴዎች ከአንድ ክልል በማለፍና ብሄራዊ ባህርይ በመውሰድ በአንድ አገር ውስጥ የሚኖረው ማንኛውም ግለሰብ እንደ እኩል ዜጋ ሆኖ መታየት የሚችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ችሏል።

ከዚህ ስንነሳ ዶ/ር አቢይን ብሩህ መሪ ናቸው፣ አገራችንንም ለማሳደግና በዓለም ማህበረሰብ እንድትከበር የማድረግ ብቃት አላቸው ብለን በመጀመሪያው ወቅት ብናስብም፣ በጊዜው ይህን ያህልም ያላሰላሰልናቸው ብዙ ነገሮች ነበሩ ማለት ይቻላል። የዛሬው የሳቸው ግራ መጋባት በራሳችንም ላይ የሚታይ ነው። ምክንያቱም ቢያንስ ባለፉት 28 ዓመታት በአገራችን ምድር የተፈጠሩትን ውስብስብ ሁኔታዎች ወይም ችግሮችና ምክንያቶቻቸውን በደንብ ለማገናዘብ አለመቻላችን ወይም ጥረት አለማድረጋችን ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩትና፣ በተለይም ደግሞ በአብዮቱ ወቅት የተፈጠረውን ምስቅልቅል ሁኔታና ከቁጥጥር ውጭ መውጣት፣ እንዲሁም ደግሞ የእነመለስ ዜናዊ ስልጣን ላይ መውጣት በምን መልክና በማን ዕርዳታ ነው? የሚለው በፖለቲካ ስሌታችን ውስጥ በፍጹም ገብቶ ስለማያውቅ በጭፍን ድጋፍ እንድንሰጥና እንድናመልክም ተገደናል ። በተለይም እነመለስ ዜናዊ ስልጣን ላይ ከወጡ ጀምሮ በአገራችን ምድር ተግባራዊ የሆኑትን እንደክልል የመሳሰሉ ፖሊሲዎች በሙሉ ወያኔ የጠነሰሰው ሴራ ብቻ እንጂ የውጭ ኃይል እጅ የለበትም የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰናል። በሁለተኛ ደረጃ፣  እነመለስ ዜናዊ ስልጣን ከያዙ ከአንድ ዓመት በኋላ ተግባራዊ ያደረጉትን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ በወያኔ በራሱ ብቻ የታቀደና ተግባራዊ የሆነ ነው ብለን በማመናችን በአገራችን ላይ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ወንጀል እንድንፈጽም ተገደናል። የኢኮኖሚ ፖሊሲው የዓለም ኮሙኒቲው እየተባለ በሚጠራው ያልተቀነባበረ እንደሆነ አድርጎ በመውሰድና፣ ፖሊሲውን ከሶሻሊስቱ የዕዝ ኢኮኖሚ ወይም የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ብለን ከምንጠራው ጋር በማመሳሰልና በማስተጋባት የጠራና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ትግል እንዳናካሄድ ተደርገናል። በውጭ ኃይሎች የተቀነባበሩት እነዚህን የመሳሰሉትና ሌሎች አያሌ አገርን የሚያዳክሙና ምስቅልቅልን የሚያመጡ ነገሮችን የፖለቲካ ትግል ስሌታችን ውስጥ ለማካተት ባለመቻላችን ከውስጥም ሆነ ከውጭ የነቃና የአገር ተቆርቋሪ የሆነ ምሁራዊ ኃይል ብቅ እንዳይል አግደናል።

ዶ/ር አቢይ ወይም የቲም ለማ የሚባለው ቡድን ስልጣን ሲይዝ ሁላችንም የማረከን የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የፖለቲካ ዕቅዳቸው፣ እንዲሁም ደግሞ አገራችንን ታላቅ አገር አድርገው የመገንባት ህልማቸው ሳይሆን፣ መልካቸውና „ኢትዮጵያ ሱስ ናት፣ ስንፈጠርም ኢትዮጵያኖች፣ ስንሞትም ኢትዮጵያኖች ነን“  የሚሉት አረፍተ-ነገሮች  ወይም አነጋገሮች ብቻ እንጂ የህይወት ታሪካቸውን፣ የሰሩትን ስራ፣ ርዕዮተ-ዓለማቸውን፣ ስለፖለቲካ፣ በተለይም ስለዓለም አቀፍ ፖለቲካ ያላቸውን ግንዛቤ በመመርመራችን አይደለም። እንደዚህ ዐይነቱ የአንድን ድረጅት ወይም ግለሰብ አቋም ከሳይንሱና ከፍልስፍና አንፃር ሳይመረምሩ በጭፍን አቋም መውሰድ በአገራችን የፖለቲካ ትግል ውስጥ የተለመደና ለደም መፋሰስም ያበቃን ጉዳይ ነው። አብዮቱ ከከሽፈ በኋላና፣ በተለይ ደግሞ ከግንቦት ሰባት ምርጫ መክሽፍ በኋላ ይህንን ዐይነቱን ጭፍን የፖለቲካ ስሌት በመከተላችንና፣ አንድን ደርጅት ወይም አንድን ግለሰብ አምላኪ ሆነን በመቅረታችን 15 ዓመት ያህል እንዳናስብ፣ እንዳናጠናና እንዳንመራመር ተደርገናል። በዚህም ምክንያት የተነሳ አንዳንዶቻቸን አለፍ አለፍ እያለን መሰረታዊና በተጨባጭ ማስረጃ የተደገፈ ትችት በምንጽፍበት ጊዜ ማስፈራሪያ ደርሶብናል፤ ተሰድበናልም። ስለሆነም ሰውን ላለማስቀየም በማለት አስፈላጊ የሆኑ ሳይንሳዊና ፖለቲካዊ ትችት እንዳንጽፍ ተገደን ነበር ብል ማጋነን አይሆንም። ይህም የሚያረጋግጠው ትግል ብለን እዚህና እዚያ የምንሯሯጠውና ኃይላችንን የምንጨርሰው በመሰረቱ ታላቅና የተከበረች፣ እንዲሁም ሰፊው ህዝብ በኑሮው ደስተኛ ሆኖ የሚኖርባት አገር ለመመስረት ሳይሆን ለግለሰቦችና በፓርቲ ደረጃ ተደራጅተናል ለሚሉ በመሰረቱ ፍልስፍናቸው ለማይታወቅና ቅርፅ ለሌላቸው ድርጅቶች ነን ባዮች ነው ድጋፋችንን ስንሰጥና ስናሞጋግሳቸው የከረምነው።

ዶ/ር አቢይ ስልጣን ለመያዝ የቻሉት ለሁለት ዓመታት ያህልና ከዚያም በላይ እየተጋጋለ በመጣው ህዝባዊ እንቅስቃሴ ምክንያት ነው። የህውሃት አገዛዝም ከመግደል፣ ከማስቃየት፣ ከማሰርና በጅምላ ከመጨፍጨፍ ውጭ ሌላ ሊሰጠው የሚችለው መልስ ስላልነበረውና ከእንግዲህ ወዲያ በድሮው መልኩ ተዝናንቶ ለመግዛትና ለመበዝበዝ ባለመቻሉ የኋላ ኋላ የህዝብ ግፊት ሲበዛበት ስልጣኑን እንዲለቅ ተግዷል። በሌላ አነጋገር፣ ወያኔ ስልጣኑን ሊለቅ የተገደደው በኢህአዴግ ውስጥ በተደረገ የእርስ በእርስ ሽኩቻና የርዕዮተ-ዓለም ትግልና ፖሊሲያችንን መለወጥ አለብን በሚለው ላይ የጦፈ ክርክር በመደረጉ ሳይሆን በአማዛኝ ጎኑ በህዝብ ግፊትና ተጋድሎ ምክንያት ነው። በዚህ ላይ የውጭው ኃይል፣ በተለይም የአሜሪካኖችና የሳውዲ አረቢያ እጅ እንዳለበት የሚናገሩና ትንተና የሚሰጡ አሉ። ከዚህ ስንነሳ የእነ ዶ/ር አቢይ ስልጣን ላይ መውጣት ጭንቅላታቸው ውስጥ የተቀረጸና ለረጅም ጊዜ ሲብላላ የቆየ፣ ከእንግዲህ ወዲያ ለዚች አገር ዲሞክራሲና ዘመናዊነት የግዴታ ያስፈልጋታል ከሚል ውስጣዊ ፍላጎት የተነሳ አይደለም ስልጣንን ሊጨብጡ የቻሉት። ስልጣን ላይ ሲወጡም በድሮው መልኩ ሊገዙ እንደማይችሉ የታወቀ ጉዳይ ነው። የህዝቡን፣ በተለይም የወጣቱን የጋለ ስሜት የሚያቀዘቅዝ እርምጃዎች መውሰዳቸው ግዴታ ነበር ማለት ይቻላል።

ያም ተባለ ይህ የዶ/ር አቢይን ፖለቲካ ስንመለከት ግራ የሚያጋቡ ብዙ ነገሮች አሉ።  ሌላውን ትተን በመሰረቱ የህወሃት አገዛዝ ይከተል ከነበረው በዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው ተረቆ ከመጣው አገርንና ባህልን አውዳሚ ከሆነው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ በፍጹም ሊላቀቁ አልቻሉም። አሁንም እንደትላንትናው የገንዘብ ቅነሳ ፖሊሲ እየተካሄደ ሲሆን፣ ይባስ ብሎ የገንዘብን የመግዛት ኃይል „በአቅራቢና በጠያቂ ህግ“ ለመወሰን የሚያስችል ጥናት እየተካሄደ ለመሆኑና ዋናው ተዋናይም የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት(IMF) ነው። በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ዕምነት የኢትዮጵያ ብር ከዶላር ጋር ሲወዳደር አሁንም ቢሆን 20% ከፍ ያለ ስለሆነ፣ 20% መቀነስ አለበት በማለት አገዛዙንና ፖሊሲ አውጭዎችን ግራ እያጋባ ነው። በቡሃ ላይ የጆሮ ደግፍ ተጨምሮበት እንዲሉ፣ የብር የመግዛት ኃይል 20% እንዲቀንስ ከተደረገ ወይም ደግሞ የመግዛት ኃይሉ በአቅራቢና በጠያቂ(Free Floating) የሚደነገግ ከሆነ በዋጋ ግዥበት ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ መገመቱ ከባድ አይሆንም። በእነ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቱና በዓለም ኮሙኒቲው ዕምነት መሰረት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከፍተኛ የሆነ የማክር ኢኮኖሚ መዛባት(Macroeconomics Imbalances) ስለሚታይበት እንደዚህ ዐይነቱን የገንዘብና የበጀት ቅነሳ ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረጉ ኢኮኖሚውን ወደ ሚዛናዊነት ያመጣል የሚል ነው። ይሁንና ግን ፖሊሲው ተግባራዊ መሆነ ከጀመረ ከ26 ዓመታት ጀምሮ የማክሮ ኢኮኖሚው ከፍተኛ መባዛት እየታየበት ነው። የውጭው ንግድ ሚዛን በከፍተኛ ደረጃ ወደ ታች ያሽቆለቆለ ሲሆን፣ አገሪቱ $17 ቢሊዮን የሚጠጋ የገንዘብ ጉድለት(deficit) አለባት። በተጨማሪም የውጭው ዕዳ ወደ $29 ቢሊዮን የሚጠጋ ሲሆን ሌሎች ዘርፎችም በከፍተኛ ደረጃ የተዛቡ ናቸው። ፖሊሲው አገሪቱን እንደዚህ ዐይነት መቀመቅ ውስጥ እየከተተ አገዛዙ አሁንም ቢሆን የሙጥኝ በማለት የሚከተለው ፖሊሲ የባሰውን ኢኮኖሚውን የሚያዛባና የስራ መስክም ሊከፍት የማይችል የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲን ነው። በተጨማሪም በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ የህዝብ ሀብቶችን፣ ማለትም ኩባንያዎችን ወይም ፋብሪካዎችን ወደ ግል ይዞታ ለመለወጥ መነሳሳት፣ ይህ ዐይነቱ ፖሊሲ የእነ አቶ መለሰ ዜናዊ የተቋም ፖሊሲ(Structural Adjustment Program) ተቀጥያ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም። በኒዎ-ሊበራል የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት አሁንም ቢሆን የአገራችን የተወሳሰበ ችግር እንዳይፈታና ዕውነተኛ የሆነ ብሄራዊና ህዝባዊ ሀብት እንዳይፈጠር እየተደረገ ነው። እንዲያውም ይህ ዐይነቱ አካሄድ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የካፒታሊስት ኢኮኖሚና፣ የተወሳሰበ የአገር ውስጥ ገበያ(Home Market) እንዳያድግ የሚያግድ ነው። ከዚህ የተምታታ ሁኔታ ስንነሳ የዶ/ር አቢይንና የአገዛዛቸውን የፖለቲካ ፍልስፍና ለማወቅ ይህን ያህልም የሚያስቸግር አይደለም። ተግባራዊ የሚያደርጉት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማንነታቸውን የሚገልጽ ነው። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ለመሪዎቻችን በሳይንስ ላይ በተመሰረት የኢኮኖሚ ፖሊሲና በኒዎ-ሊበራል ፖሊሲ መሀከል ያለው የሰማይና የምድር ያህል እርቀት ግልጽ የሆነ አይመስለኝም። ያም ሆነ ይህ ዶ/ር አብቢይ የዘመናዊነትን አርማ የያዙ ቢመስልም ምን ዐይነት ዘመናዊነትን ይከተሉ እንደሆን ለማወቅ ይከብዳል። ለማንኛውም ፖሊሲያቸውንና ርዕያቸውን ከርዕዮተ-ዓለም አንፃር ስንመረምረው እሳቸውና የትግል አጋሮቻቸው የሚከተሉት ርዕዮተ-ዓለም የግራ፣ የኮሙኒስት ወይም የሶሻሊስት፣ የቀኝ ወይም የቀኝ ፖፑሊስት፣ ሰብዓዊነት ባህርይ ያለውና የሁሉንም ህብረተሰብ ጥቅም የሚያካትትና ፍትሃዊ የሆነ ስርዓትን እንደንገነባ የሚያስችለን ርዕዮተ-ዓለም እንደሆነ ለማወቅ ያስቸግራል። አንድን አገርና ህብረተሰብ እመራለሁ የሚል አገዛዝና መሪ የሚያምንበትና ከደሙ ጋር የተዋሃደ አንዳች ዐይነት የፖለቲካ ፍልስፍና ወይም ቀለም እንዲኖረው ያስፈልጋል። ለመደገፍም ሆነ ለመቃወምም የሚያመቸውና አማራጭም ለማቅረብ የሚቻለው አገዛዙ የሚመራበትን ራዕይ የተረዳን እንደሆን ብቻ ነው። አይ ራዕይ የለንም፣ አገራችንና ህዝባችንም ምንም ዐይነት የፖለቲካ ፍልስፍና አያስፈልጋቸውም የሚባል ከሆነ ደግሞ ዝም ብለን ነው የምንደናበረው ማለት ነው። እንደዚህ ዐይነቱን አካሄድ በአብዛኛዎች የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የምንመለከተውና አገሮችንና ህዝቦችን መቀመቅ ውስጥ የከተተና ወደ ባሰ የድህነት ዓለም ውስጥ የወረወራቸው ነው።

ይህንን አልፈን በዋና ከተማችን ሊሰራ የታቀደውን የመገበያያ ቦታና(Mall)፣ የአረብ ባለቱጃሮች በአገራችን ምድር የሚጫወቱትን ሚና ስንመለከት፣ ለሳውዲዎችና ለቻይናዎች የእርሻ መሬት ቆርሶ በመስጠት ህዝባችንን ወደ ባርነት እንዲለወጥ ማድረግ፣ በህዝብ ተወካዮች ዘንድ ክርክር ሳይደረግበትና ህዝብ ሳያውቀው ከውጭ አገር ኩባንያዎች ጋር የሚደረገው ስምምነት… ወዘተ. እነዚህ ሁሉ የሚያረጋግጡት ዶ/ር አቢይና አገዛዛቸው በመሰረቱ ከህውሃቱ የውስጥ ለውስጥ ድርድር ያልተላቀቁ እንደሆነ ነው የምንመለከተው። ምናልባት በዚህ ዐይነቱ አካሄድና „የአገዛዝ ፍልስፍና“ ታላቅ አገርን እንገነባለን ብለው አስበው ይሆናል። ካሊያም በኢኮኖሚ ፖሊሲና በአገር ግንባታ ታሪክ ውስጥ ከዚህ ዐይነቱ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ በስተቀር ሌላ አማራጭ ያለ መስሎ አይታያቸውም ይሆናል። ለማንኛውም በአካባቢያቸው የተሰበሰቡትን ቀድሞ ለዓለም ባንክ ይሰሩ የነበሩ ኢኮኖሚስቶችን ስንመለከትና፣ የውጭ ኢንቬስተሮች በመባል የሚታወቁት ወደ አገራችን መግባትንና መውጣትን ስናይ፣ የአማካሪ ኩባንያዎች (Consulting Firms) መንጋጋትና አገዛዙን በቁጥጥር ስር ማድረጋቸውን ስንመለከት ግራ መጋባታችን አይቀርም። የድሮው የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስተርና አሁን ደግሞ ለአንድ የአሜሪካን ኢንቬስትሜንት ባንክ የሚሰሩትን የእነ ቶኒ ብሌርን መምጣትና የጠቅላይ ሚኒስተሩ አማካሪ መሆናቸው- ቶኔ ቢሌር ከቡሽ አስተዳደር ጋር በማበርና የኢራኩን ፕሬዚደንት ሳዳም ሁሴንን በውሽት በመወንጀል ለስድስት መቶ ሺህ ኢራካውያን መሞት፣ የታሪክ ቅርስ መውደምና ለእርስ በእርስ ጦርነምክንያትና ተጠያቂ የሚሆኑ ወንጀለኛ መሪ ናቸው- የሚያረጋግጠው አገዛዙ ከውጭ ኃይሎች ቁጥጥር ውጭ እንደማይንቀሳቀስ ነው። በተለይም በኢኮኖሚ ሚኒስተር ውስጥ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካሪ በመሆን የተቀመጡት የውጭ አገር ሰዎችና፣ በባንክ ውስጥ የተሰገሰጉትን የሞኒተሪ የገንዘብ ፖሊሲ አራማጅ ፈረንጆችን ስንመለከት አገዛዙ ከቀድሞው የተሻለ እንዳልሆነና፣ በራሱ መንቀሳቀስ እንደማይችል ነው የምንረዳው። የዶ/ር አቢይ አገዛዝ በዓለም አቀፍ ካፒታሊዝም ጉያ ስር መውደቁ የድህነታችንና የኋላ-ቀርነታችንን ዘመን የሚያራዝመው እንጂ በምንም ዐይነት ነፃ አገር እንድንገነባ የሚያስችለን አካሄድ አይደለም።

ወደ ፖለቲካው ሁኔታ ስንመጣ በመደመር ስም የተከተሉት አካሄድ ከፖለቲካ ጥራት ይልቅ የበለጠ ውዥንብርን ያመጣ ነው ማለት ይቻላል። ለጽንፈኞችና፣ እንዲሁም በውጭ ኃይሎች በመታገዝ ለሚንፈላሰሱና ሜዳውን ለያዙትና የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲመጣ ቅስቀሳ ለሚያደርጉት፣ የብሄረሰብን አርማ አንግበው የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲመጣ ለሚፈልጉ ኃይሎች የፖለቲካው ሜዳ ልቅ ሆኗ። እነዚህ የፀረ-ዕድገትና የፀረ-ዲሞክራሲ ኃይሎች እንደልባቸው ሲንቀሳቀሱና በውጭ ኃይሎች በሚደገፍ ሚዲያ በመጠቀም በታሪክና በሳይንስ ያልተደገፈ መላቅጥ የሌለው የተምታታ ነገር ሲያቀርቡ፣ አንዳንዶች ደግሞ ብሄራዊ ባህርይ ያላቸውና የህዝብ ተቆርቋሪ የሆኑ ፎቶግራፍ አንሺዎችና ጋዜጠኞች በፖሊሶች እየታደኑ ሲንገላቱና ሲታሰሩ ስናይ የዶ/ር አቢይን ፖለቲካ በትዝብትና በጥርጣሬ እየተመለከትነው ነው። ይህንና በየቦታው የሚካሄደውን የህዝብ መፈናቀልና፣ ከዕቅድ ውጭ የተሰሩ ቤቶች ናቸው እየተባለ የምስኪን ሰዎችን ቤት ማፍረስና መንገላታት ስንመለከት፣ አሁን ደግሞ ከመቶ ሰላሳ ስምንት ዓመት በላይ ያስቆጠረውን የአፄ ምኒልክን ትምህርት ቤት ለማፍረስ ሽር ጉድ ማለቱን ስናይ አገራችን ወዴት እንደምታመራ መገንዘቡ ከባድ አይሆንም። ይህንን ጉዳይ በሚመለከት የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪዎች ተጠይቀው ግልጽ የሆነ ገለጻና መልስ ሲሰጡ፣ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አቶ ታከለ ኦማ ውሸት እንደሆነ ለማስተባበል ሲሞክሩ ስናዳምጥ በአገራችን ምድር የቱን ያህል ሀቀኝነት የጎደለው ፖለቲካ እንደሚካሄድ ነው ተጨባጩ ሁኔታ የሚያረጋግጠው። አንዳንድ ፖለቲከኛ ባዮች የታሪክን ሂደትና የህብረተሰብን ውስብስብነትና የሚያመጣውን አሉታዊ ውጤት ስያገናዝቡ የሚወስዷቸው እርምጃዎች ህዝብን ግራ እያጋቡና፣ የአገዛዙንም ማንነት እያረጋገጡልን ነው። እነዚህና ሌሎች በደንብ ሳይጠኑ የሚወሰዱ አገር በታኝ ፖሊሲዎች የመጨረሻ መጨረሻ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ጠንቅ የሚሆኑ ናቸው። ለጊዜው አንዳንዶች የመጠቀም ዕድል ቢያጋጥማቸውም የመጨረሻ መጨረሻ ግን እንወክለዋለሁ የሚሉትን ብሄረሰብ ነው የሚጎዱት።

አጠቃላዩን የፖለቲካ ሁኔታ ስንመለከት ለሰላምና ለመረጋጋት የሚያመች አይደለም። ህዝባችን በረደፍ በረድፍ በመደራጀት መብቱን የሚያስከብርበት ሁኔታ ሲዘጋጅለት አይታይም። በተለይም ከ28 ዓመት የጭቆናና የዘረፋ አገዛዝ በኋላ ህዝባችን ዕውነተኛ ነፃነትን ይፈልጋል። ሰራተኛውና ገበሬው በሙያ ማህበር በነፃ መደራጀትና መብታቸውን ማስጠበቅ አለባቸው። እንደዚሁም ሴቶችና ወጣቶች የመደራጀት መብት ተስጥቶአቸው የፖለቲካ ትርጉምን እንዲረዱ ማድረግ የመንግስት ዋናውና ተቀዳሚው ተግባር ነው። ህዝቡ ሲደራጅ ብቻ ነው አንድን አገር መገንባት የሚቻለው። ስራ አላሰራ የሚለውንና በሙስና የተጠመደውን ቢሮክራሲ ለመቆጣጠር የሚቻለው ህዝቡ በነፃ ሲደራጅ ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ ስለለውጥና ስለዲሞክራሲ ማውራት በፍጹም አይቻልም። ከዚህም ባሻገር የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ-ገብነት መቀነሰ ያስፈልጋል። ለአገራችንና ለህዝባችን የሚስማማ ሳይንሳዊና የፍልስፍና መሰረት ያለው ሁለ-ገብ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሊነድፉሉን አይችሉም። የመደብና የርዕዮተ-ዓለም ባህርያቸው አገራዊና ብሄራዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዲነድፉ አያስችላቸውም። የእነሱ ምኞትና ስትራቴጂ አንድን ደካማ አገር የባሰውን ማቆርቆዝ ነው። ሀብቷ የሚዘረፍበትንና ህዝቡ ባይተዋር የሚሆንበትን አገር ማመቻቸት ብቻ ነው። ተልዕኮአቸው የዓለም አቀፍ ካፒታሊዝምን ፍላጎት ማሟላት ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ የሰላምና የብልጽግና ተልዕኮ የላቸውም።

 

ግራ የገባው ህዝብና ምሁር !

ባጠቃላይ ሲታይ የኢትዮጵያ ህዝብ ከዛሬው የተሻለ ሁኔታ ቢመጣለት በጣም ደስተኛ ነው። ቢያንስ በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባትን ይፈልጋል። ይሁንና ያለበትንና የሚኖርበትን ሁኔታ በደንብ ይረዳ አይረዳ፣ ምን ዐይነት ህብረተሰብ ይመኝ እንደሆነና፣ በጭንቅላቱ ውስጥ የሳለው አንዳች የህብረተሰብ ሞዴል ይኑረው አይኑረው ለማወቅ በጣም አስቸጋሪ ነው።

በህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ አንዳች ዐይነት ስርዓትን የሚፈጥሩ አብዛኛውን ጊዜ የፖለቲካ ስልጣንን የጨበጡ ናቸው። በአንድ አገር ውስጥ፣ በተለይም ደግሞ አምባገነናዊ አገዛዞች በሰፈኑባቸውና በጥልቀትና በስፋት የሚያስብ የነቃ  የህብረተሰብ ክፍል በሌለበት አገር አገዛዞች የሚያወጧቸውና ተግባራዊ የሚያደርጓቸው ፖሊሲዎች በአቦ ሰጡኝ ነው። በተለይም ደግሞ በዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው ግዳጅና ምክር ተግባራዊ እንዲሆኑ የሚደረጉ ፖሊሲዎች የተረጋጋና ለፈጠራ የሚያመች፣ እንዲሁም ደግሞ ግብረ-ገብነትንና ስነ-ምግባርን የሚያዳብሩ ማህበረሰብ እንዲመሰረት የሚያግዙ ሳይሆኑ የተቃራኒውን እንዲሆን የሚያደርጉ ናቸው። ካለፉት 28 ዓመታት ጀምሮ በአገራችን ምድር እየባሰበት የመጣና በተለይም ወጣት ሴቶችንና በዕድሜ ገፋ ያሉትን የሚያስፈራና የሚያስቆጣ ሁኔታ ከሰማይ ዱብ ያለ ሳይሆን ስልጣንን በጨበጡትና የህዝባችንን ዕድል በሚወሰኑትና በውጭ ኃይሎች የተቀነባበረ ሴራ ነው። በተለይም ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዋናው ዓላማውም ሳይንስና ቴክኖሎጂን በማዳበር የሰፊውን ህዝብ ኑሮ በማሻሻል ጥበባዊና የተከበረ አገር መገንባት ሳይሆን፣ ደሃና ለማኝ፣ እንዲሁም ፈሪና አጎብዳጅ ህብረተሰብ ለመፍጠር ነው። ከዚህ ስንነሳ ባለፉት 28 ዓመታት ከዚያ በፊት ታይተው የማይታወቁ የአገራችንን እሴቶች የበጣጠሱ ሁኔታዎች በመስፋፋት ህዝቡ እንደ ማህበረሰብና እንደ ህብረተሰብ እንዳይኖር አድርገውታል። የሙስና መስፋፋት፣ ጥቂት ደሞዝ እያለው በጥቂት ዓመታት የብዙ መቶ ሚሊዮኖች ዶላርና ቁጥራቸው የማይታወቁ ንብረቶች ሀብታም መሆን፣ የዕፅ ሱስና የሴተኛ አዳሪነት መስፋፋት፣ የማጅራች መቺዎችና የኪስ አውላቂዎች እንደ አሽን መፈልፈልና ለሰፊው ህዝብ ጠንቅ መሆን፣ ተፈጥሮአዊ ያልሆነ የወሲብ ተግባር መስፋፋትና አገሪቱም ለእንደዚህ ዐይነቱ አጸያፊ ተግባር ክፍት መሆኗ፣ ሰላዮች እንደፈለጋቸው መዋኘት መቻላቸውና በስልጣን ላይ ያሉትንና የተወሰነውን ኤሊት በማባላግ ሀብት እንዲዘረፍ ማድረግ…ወዘተ. እነዚህና ሌሎች የአገርን ክብር እንዲጣስ ያደረጉት ሁሉ ከሰማይ ዱብ ያሉ የእግዚአብሄር ቁጣዎች ሳይሆኑ በሰው የተሰሩ ናቸው። እነዚህ ነገሮች በሙሉ ማን እንደፈጠራቸው፣ ለምንስ እንደዚህ ዐይነት አፀያፊ ተግባሮች እየተለመዱና ተቀባይነትን እያገኙ መምጣት እንደቻሉ የሚያጠና ድርጅትም ሆነ ግለሰብ ባለመኖሩ በተለይም ሰፊው ህዝብ ግራ ተጋብቶ እንዲኖር ተደርጓል። ሳይወድ በግድ ይህ ዐይነቱ አፀያፊ ተግባር እንደ አንድ የኑሮ ፍልስፍና አድርጎ እንዲቀበለው ሊደረግ በቅቷል።

በዚህ ዐይነቱ የተዘበራረቀ ሁኔታ ደግሞ በተለይም ወጣቱን የሚያሳስቱና መንፈሱን የሚሰልቡ ሃይማኖት መሰል ነገሮች በመስፋፋት አቅመ-ቢስ አድርገውታል። የሰውን ጭንቅላት በማደንዘዝ እንፈውስሃለን በማለት ገንዘብ በመሰብሰብና ካዲላክ መስል መኪናዎችን በመግዛት የሚንደላቀቁ ፓስተሮች ነን ባዮች የተከፈተላቸውን በርና የተለቀቀላቸውን ሜዳ በመጠቀም ባለፉት 28 ዓመታት በቀላሉ መፍትሄ የማይገኝለት ወንጀል ሰርተዋል፤ እየሰሩም ነው። በዚህ ላይ ምሁር  ነን በማለት በየቴሌቪዥኑ እየወጡ ቃለ-መጠይቅ የሚደረግላቸውና መልስ የሚሰጡ በአገሪቱ ምድር ላይ የሚታየውን ሁኔታ ለምን እንደተፈጠረ ከማስረዳትና መፍትሄ ከመሻት ይልቅ፣ የሚሆን የማይሆነውን በመናገር በተለይም ወጣቱ ሀቁን ከውሸት እንዳይለይ ለማድረግ በቅተዋል፤ ዛሬም እያደረጉ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሀገር ውስጥ የስንዴ ገበያ ለችግር መጋለጡን ተጠቃሚዎች እየተናገሩ ነው

በመሰረቱ የምሁሮች ዋና ተግባር አንድ ህብረተሰብ ዝብርቅር በሆነና በተበላሸ ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ ከሆነ ዝም ብሎ ማየትና በችግሩ ላይ ሌላ ችግር መጨመር ሳይሆን ለእነዚህ ሁኔታዎች ምክንያት የሆኑትን ነገሮች ማጥናትና መፍትሄ መሻት ነው። በተለይም በመንግስትና በአገዛዙ፣ እንዲሁም በውጭ ኃይሎች ግፊት ተግባራዊ የሚደረጉትን ፖለቲካዊ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲዎች በመመርመርና የሚያስከትሉትን ህብረተሰብአዊና ባህላዊ ጠንቆች ለሰፊው ህዝብ በማሳየትና የተሻለ አማራጭ በማቅረብ የህዝባቸው አለኝታ መሆናቸውን ማረጋገጥ ነው። ይሁንና ግን ምሁሩ  ለህዝብና ለአገር ጠበቃ ከመሆን ይልቅ በዓለም ኮሙኒቲው አማካይነት ተግባራዊ የሚሆነውን የኢኮኖሚም ሆነ ሌላ ፖሊሲዎች ዝም ብሎ የሚመለከት ከሆነ ለሚፈጠረው ምስቅልቅል ሁኔታ መንግስት ብቻ ሳይሆን ተጠያቂው እሱም ጭምር ነው። ዝም ብሎ የሚመለከት ምሁር ደግሞ ራሱን ነፃ ያላወጣና በራሱ ፍላጎት የሚገዛ ሳይሆን በውጭ ኃይሎች የሚጠመዘዝና እነሱን የሚያመልክ ነው። ስለሆነም እንደዚህ ዐይነቱ ምሁራዊ ኃይል ታላቁ የጀርመን ፈላስፋ ኢማኑኤል ካንት እንደሚለው „በፍላጎቱና በማሰብ ኃይሉ የማይገዛ ነው፤  ሰው መሆኑንም የሰረዘ ነው።“   እንደዚህ ዐይነቱ ምሁር ህብረተሰብአዊ ጥቅምን  ካማምጣትና አገር ከማስከበር ይልቅ ብሄራዊ ውርደትን ነው የሚያስከትለው።

ከዚህ ስንነሳ በአለፉት ሃምሳና አርባ ዐመታት የደረሱት አሰቃቂ ድርጎቶች፣ እንዲሁም ድህነትና ረሃብ ተስፋፍተው የአገራችን መለያዎች መሆናቸው የሚያመለክተው የምሁሩንም ድክመት ነው። ሰፋ ባለና በተወሳሰበ ዕውቀት እንዲያስብ ሆኖ ያልተዘጋጀው ምሁራዊ ኃይል፣ በተለይም እንደ ኢኮኖሚክስ የመሳሰሉትን ትምህርቶች ከአንድ አንፃር ብቻ በማየትና የአገራችንን ችግር ወደ ጠያቂነትና አቅራቢነት ብቻ (Demand and Supply) በመቀነስና የገበያ ኢኮኖሚ የተወሳሰበውን የህብረተሰብአችንን ችግር መፍቻ አድርጎ በመመልከቱ ለተመሰቃቀለው የአገራችን ችግርና ለድህነትም መስፋፋት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጠያቂ ነው ማለት ይቻላል።  ይህ ብቻ ሳይሆን፣ አብዛኛው ምሁር ወይም ተማርኩ ነኝ የሚለው የሚያደላው ወደ ፖለቲካ ብቻ ነው። የፖለቲካ ጉዳይንም የሚመለከተው ስልጣንን ከመጨበጥ አንፃር ብቻ ስለሆነ ፖለቲካ የሚባለው ግዙፍ ጽንሰ-ሃሳብና ሳይንስ ከሌሎች የህብረተሰብ ጥያቄዎች፣ ከፍልስፍና፣ ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ እንዲሁም ከማህበራዊና ከኢኮኖሚ ጥያቄዎች ተነጥሎ በመታየቱ የህብረተሰብአችንን ችግር መፍቻ መሆኑ ቀርቶ መፋለሚያና ግራ አጋቢ መሳሪያ ሊሆን በቅቷል።

ከዚህም ባሻገር ህዝባችን ግራ የተጋባው በምሁራኑ ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚ ነን በሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶችም ጭምር ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ተቃዋሚ ነኝ የሚል መደራጀቱንና ከህዝብ ጋር ግኑኝነት እንዳለው ማረጋገጥ መቻል አለበት። በየቀበሌው፣ በየወረዳዎችና በክፍለ-ሀገር ከተማዎችና በመንደሮችም ጭምር ሰፋ ያለ የአደረጃጀት መዋቅር እንዲኖረው ያስፈልጋል። በሁለተኛ ደረጃ፣ ተቃዋሚ ነኝ የሚል ድርጅት በምን ዐይነት ራዕይ ወይም ርዕዮተ-ዓለም እንደሚመራ ማሳየት አለበት። በሶስተኛ ደረጃ፣ ስልጣን ላይ ካለው አገዛዝ በምን እንደሚለይ ለሰፊው ህዝብ ማሳየት አለበት። አራተኛ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊና የስነ-ልቦና ችግሮች ካሉና ጎልተው የሚታዩ ከሆነ ምክንያቶቻቸውንና እንዴትስ ደረጃ በደረጃ መፈታት እንደሚችሉ መመርመርና መፍትሄማ ማቅረብ አለበት። አምስተኛ፣ በተለይም ከውጭ የሚመጡ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን በማጥናት፣ ተግባራዊ በሚሆኑበት ጊዜ ሊያስከትሉ የሚችሉትን ህብረተሰብአዊ ጠንቆች ለሰፊው ህዝብ ማስተማርና የተሻለም መፍትሄ ማቅረብ አለበት። ስድስተኛ፣ እያንዳንዱ ድርጅት ወይም ፓርቲ የራሱ የሆነ  የአገርንና የዓለምን ሁኔታ የሚዳስሱ ሳምንታዊ ጋዜጣና በየወሩ የሚታተምና ሰፋፊ ሀተታዎችን የያዘ መጽሄት ያስፈልገዋል። የፖለቲካ ድርጅቶች ጋዜጣዎችና መጽሄቶች የየፓርቲዎችን ራዕይ ማሳያዎችና ማንነታቸውንም የሚገልጹ ናቸው። በዚህ መልክ ያልተደራጀና ራዕይ የሌለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ በመሰረቱ ህዝብን ግራ ከማጋባት በስተቀር ለአገራችን የተወሳሰቡ ችግሮች እንደ አማራጭ ሆኖ ሊቀርብ አይችልም። አገራችንም በጸና መሰረት ላይ እንድትገነባ የማድረግ ኃይልና ብቃትም ሊኖረው አይችልም።

ከዚህ ስንነሳ በአገራችን ምድር ከመቶ በላይ የሚሆኑ ተደራጀን የሚሉ „ፓርቲዎች“ አሉ። ሁኔታውን ለሚከታተለው እነዚህ ሁሉ ድርጅቶች ከረጅም ጊዜ ምሁራዊ እንቅስቃሴና ጥናት በኋላ ማህበራዊና የህብረተሰብ ጥያቄዎችን በማንሳትና በማጥናት የተወለዱና ታንፀው የወጡ አይደሉም። በፓርቲ ደረጃ ተደራጀን የሚሉ ሁሉ በተለይም ባለፉት 28 ዓመታት በአገራችን ምድር ተግባራዊ የሆነውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲና ጠንቁን በማጥናትና በመጻፍ ህዝቡን፣ በተለይም ወጣቱን ለማስተማር የሞከሩ አይደሉም። ስለሆነም በሀብታምና በደሃ መሀከል ሰፊ የገቢ ልዩነት ሲፈጠርና፣ አብዛኛው ህዝብ ወደ ድህነት ዓለም ሲወረወር ዝም ብለ የሚመለከቱ እንጂ ድምጻቸውን በማሰማትና በመጻፍ የህዝብና የአገራችን ጠበቃ መሆናቸው አላረጋገጡም። በተለይም አገራችን የአካባቢ ውድመት ሲደርስባት፣ ጫካዎች ሲመነጠሩ፣ ወጣቱን የሚያበላሹ ብልሹ ነገሮች ሲስፋፉ፣ የዕፅ ሱሰኛ እንዲሆን ሲደረግ፣ የተራድኦ ድርጅቶች የሚባሉት በመስፋፋት የአገራችንን እሴቶች ሲያፈራርሱ፣ ከተፈጥሮና ከህብረተሰብ ህግ ውጭ የሚሆኑ የህንፃ አሰራሮች ሲሰሩ ዝም ብሎ በመመልከት የአገራችንን ውድመት ማፋጠን ችለዋል ማለት ይቻላል። ስለሆነም ግራ የተጋባው ህዝብ አልፎ አልፎ የሚጠይቀው ጥያቄ እንደዚህ ዐይነቱ ተቃዋሚ ነኝ የሚል ኃይል ለምንድ ነው የሚያስፈልገው? ለምንድን ነው ግራ የሚያጋባን ? እያለ ነው። የተቃዋሚው ኃይል ችግር ልክ እንደ አጋዛዞቻችንም በውጭ ኃይሎች ላይ ያለው አመለካከት የተዛባና በጥናት ላይ የተመሰረተ አይደለም። አብዛኛው ተቃዋሚ ነኝ የሚለው ኃይል የውጭ ኃይሎች ለአገራችን ዕድገትና መረጋጋት ጠንቅ መሆናቸውን በፍጹም የተረዳ አይመስልም። በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የተዋቀረውን ዓለም አቀፋዊ የሚሊታሪ፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ኃይል አሰላለፍና፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲዎች አማካይነትም በደካማ አገሮች ውስጥ በመግባትና ተፅዕኖ በማድረግ የሚፈጠሩትን ህብረተሰብአዊና ማህበራዊ ውዝግቦች በደንብ ያላጠና ወይም ያልተረዳ በመሆኑ የካፒታሊስት አገሮችን እንደ ተፈጥሮአዊ አጋርና ዕርዳታ ሰጪ አድረጎ ነው የሚመለከታቸው። በሌላ አነጋገር፣ ተቃዋሚው ኃይል ዛሬ በዓለም ላይ የሚታዩት የኢኮሎጂ ቀውሶች፣ የፖለቲካ ውዝግቦች፣ የማሀበራዊ ሁኔታዎች መናጋትና፣ የአፍሪካ መንግስታትም ችግሮችን መፍታት አለመቻል… ወዘተ. ዋናው ምክንያት ካፒታሊዝም ልቅ በሆነ መልክ በዓለም አቀፍ ደረጃ መስፋፋቱን የሚቀበል አይደለም። ስለሆነም ተቃዋሚው ኃይል የዓለም ኮሙኒቲው የየአገሮችን ባህልና የተፈጥሮ ሁኔታ፣ እንዲሁም የመንግስታትን አወቃቀርና የሰፊውን ህዝብ ስነ-ልቦና ሳያገናዝብ ተግባራዊ እንዲሆኑ ግፊት የሚያደርጋቸው ፖሊሲዎች አገራችን ውስጥ ለተከሰቱትና በጉልህ ለሚታዩት ቀውሶች ዋናው ምክንያት መሆኑን በፍጹም አይቀበልም። ለማመንም በፍጹም አይፈልግም። በአብዛኛው ተቃዋሚ ኃይል ዕምነት የውጭው ኃይል ከበስተጀርባው የሚያውጠነጥነው ምንም ተንኮል የለውም።

አጠቃላዩን የአገራችንን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የባህልና የስነ-ልቦናዊ ቀውሶች ስንመለከት የህዝቡ ግራ መጋባት የሚያስደንቀን ሊሆን አይችልም። በአንድ በኩል አንድ አገዛዝ 28 ዐመታት ያህል ከውጭ ኃይሎች ጋር በመተባበርና ከእነሱ ዕርዳታ በማግኘት አገርን ሲያተራምስና የአንድ ትውልድ ዕድል ብቻ ሳይሆን፣ የሁለትና የሶስት ትውልድ ህይወት ሲያበላሽ ዝም ብሎ መመልከት የህዝባችንን የንቃተ-ህሊና ሁኔታ ያሳያል። በሌላው ወገን ደግሞ ምሁሩ ይህ ዐይነቱን የትውልድ ጠንቅ ዝም ብሎ መመልከቱና ለህዝብ ጠበቃ ሆኖ አለመነሳቱን ስንመለከት የሱንም የፖለቲካ ንቃተ-ህሊና ደረጃ መጠየቃችን የማይቀር ነው። መማር ማለት ዝም ብሎ ማየት ወይም መቀበል አይደለም ብለን የምናምን ከሆነ የትምህርቱንም ይዘትና በአጠቃላይ ሲታይ የአገራችንን የህብረተሰብ አወቃቀርና የስነ-ልቦና ሁኔታ የግዴታ መጠየቅ አለብን። እንደማህብረሰብና እንደህብረተሰብ መኖር አለብን የምንል ከሆነ ዛሬ ካለንበት ሁኔታ ባሽገር ማየት ያለብን ይመስለኛል። በምድር ላይ የሚታዩትን ምስቅልቅል ነገሮችና በየቦታው የሚካሄዱትን የእርስ በእርስ ጦርነቶች ትችታዊ በሆነ መልክ መመልከትና መመርመር መቻል አለብን። ምክንያቶችቻውን ለማወቅ የማቋርጥ ጥረት ማድረግ አለብን። አሁን ባለን አመለካከትና የማሰብ ኃይል ወደፊትም የምንገፋ ከሆነ በእርግጥም የአገራችንን ውድመት ማፈጠናችን የማይቀር ጉዳይ ነው። የግራ መጋባትና ዝም ብሎ የማየት ውጤት የመጨረሻ መጨረሻ  መጥፋት ነው። እንደ ህብረተሰብና እንደማህበረሰብ አለመኖር ነው። ከዚህ በመነሳት ነው ከአንድ ዐመት ጀምሮ  ይካሄዳል የሚባለውን „ለውጥ“  መመርመር የሚያስፈልገው። ይህ በአዲሱ የገዢ ኃይልና በብዙዎቻችንም ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘው ለውጥ የሚባለው ነገር በእርግጥስ እንደሚነገርለት ለውጥ ነው ወይ? ህብረተሰብአችን ከገባበት ማጥ ውስጥ ሊያወጣው ይችላል ወይ? በዚህ ዐይነቱ „የለውጥስ ሂደት“  የአገራችን መሰረታዊ ችግሮች ደረጃ በደረጃ ሊፈቱ ይችላሉ ወይ? የሚሉትን ጥያቄዎች ጠጋ ብለን እንመርምር።

ለመሆኑ በኢትዮጵያ ምድር ለውጥ እየተካሄደ ነው ወይ?

በመጀመሪያ ደረጃ ለውጥ ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንመልከት። ለውጥ ማለት አንድ ነገር ከነበረበት ሁኔታ ወደ ሌላ  ነገር ሲለወጥ ተለውጧል ወይም ተቀይሯል ማለት ይቻላል። አንድ የጥሬ-ሀብት ውስጣዊ ይዘቱ(Chemical Composition) ሳይቀየር፣ በኃይል(Energy)፣ በሰው የማሰብና የጉልበት ኃይል፣ እንዲሁም  በማሽን ድጋፍ ከነበረበት ሁኔታ ለሰው ልጅ ጥቅም ወደ ሚያገለግል ፍጆታ ከተለወጠ ይህንን ለውጥ ብለን እንጠራዋለን። በዚህ መልክ የምንመገባቸው፣ የምንለብሳቸው፣ የምንጠቀምባቸው የረጅምና የአጭር ጊዜ ዕድሜ ያላቸው ነገሮች በሙሉ የተለወጡና ወደ ቀድሞ ሁኔታቸውም ሊመለሱ የማይችሉ ናቸው። እራሳቸውም ዛፎችም ሆነ ሰዎች በተወሰነ የተፈጥሮ ህግ አማካይነትና በዲያሌክቲካል ሂደት ነው ከነበሩበት ሁኔታ በመለወጥ ዛሬ የምናየው ደረጃ ላይ ሊደርሱ የቻሉት።

ወደ ህብረተሰብም ስንመጣ ይህንን ዐይነቱን ክንውናዊ ሁኔታ እንመለከታለን። ልክ እንደጥሬ ሀብትም ህብረተሰብአዊ ክንዋኔና ለውጥ በሰው የማሰብ ኃይል ማኑፕሌት በመሆን ነው ከዝቅተኛ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ሊሸጋገርና ሊቀየር የሚችለው። አንድን ህብረተሰብ ሙሉ በሙሉ በዕቅድ አማካይነት መለወጥ ባይቻልም መልክና ስርዓት ማሲያዝ የሚቻለው በማሰበ ኃይል አማካይነት ብቻ ነው። እነዚህም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ሲሆኑ የለውጡም ዐይነትና ውስጠ-ኃይል(Dynamism) ማግኘት በአንድ አገር ውስጥ በሰፈነው ዕውቀትና ምሁራዊ ኃይል፣ እንዲሁም መንግስታዊ አወቃቀር ይወሰናል። መንግስትና በልዩ ልዩ ሙያ የሰለጠኑ ምሁራዊ ኃይሎች የተገለጸላቸው(Enlightened) ከሆኑ አንድ ህብረተሰብ ጥበባዊና ፍትሃዊ በመሆን ለተከታታዩ ትውልድ የሚተላለፍ ይሆናል። ቴክኖሎጂና ሳይንስ ዋናው የሀብት ማመንጫ ዘዴዎች መሆናቸውን በመረዳት አነሰም በዛም የተረጋጋና ሰላም የሰፈነበት አገር መመስረት ይቻላል።

ይሁንና ግን በህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ እንደታየው አንድን ህብረተሰብ መለወጥ ወይም ዘመናዊ ለማድረግ አንድን የጥሬ-ሀብት ወደ ፍጆታ ነገር እንደመለወጥ ቀላል አይደለም። የሰው ልጅ ጭንቅላት የተወሳሰበና አፈንጋጭ ስለሆነ ውስጡ ከተዋቀረውና ከለመደው አስተሳሰብ ቀይሮ አርቆ-አሳቢ ለማድረግ በጣም አስቸጋሪ ነው። በተለይም ደግሞ አንድ የተወሰነ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሚሊታሪያዊ አወቃቀር ከተዘረጋና፣ የተወሰኑ ሰዎች እሱን በመጠቀም ፍላጎታቸውን ተግባራዊ የሚያደርጉ ከሆነ የነበራቸውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታ(Economic and Social Status) ላለማጣት ሲሉ መሰናክል ይፈጥራሉ። በዚህ ላይ ደግሞ አንድ ዐይነት ርዕዮተ-ዓለም ጭንቅላታቸው ውስጥ ከከተቱ የበላይነታቸውን ለላማጣት ሲሉ ወደ ኃይል የሚያመዝኑበት ጊዜ አለ። ከዚህም በላይ በተለያዩ ድሮች ከውጭው ዓለም ጋር የተሳሰሩ ከሆነ አንድ ላይ በማበር ወደ ውስጥ ፍትሃዊ አስተዳደርና ጥበባዊ የሆነ የኢኮኖሚ ስርዓትና  ጠንካራ አገር እንዳይገነባ መሰናክል ይፈጥራሉ። የተለያዩ ምክንያቶችን በመፍጠርና በቡድን በመደራጀት የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል ከመሰረታዊ ጥያቄና ፍላጎት እንዲያፈነግጥ ያደርጋሉ። የሰው ጭንቅላት በማያስፈልግ ነገር እንዲጠመድ በማድረግ የራሳቸውን ጨዋታ ይጫወታሉ። የሚሆን የማይሆን ነገር በመፍጠር በአንድ ድርጅትም ሆነ በአንድ አገር ውስጥ በህዝብ መሀከል አለመተማመን እንዲፈጠር ያደርጋሉ። አንድ ህዝብ ኃይሉን ሰብሰብ አድርጎ ለአንድ ዓላማ እንዳይነሳ የማይሆን ነገር ይነዛሉ። በዚህም ምክንያት የተነሳ አንድ ህዝብና አዲስ የወጣት ትውልድ ለውጥ እያለ ከፍተኛ መስዋዕትነት ቢከፍልም የመጨረሻ መጨረሻ ስልጣን በሌላ ኃይል በመያዝ የለውጡ ፍላጎት ደብዛው ይጠፋል። ይህንን ጉዳይ የጥቢው አብዮት በመባል በሚታወቀው በቱኔዚያና በግብጽ፣ እንዲሁም በሊቢያ የተካሄደውንና ምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የምንመለከተው ሃቅ ነው። በተለይም ከመጀመሪያውኑ በሳይንስ፣ በቲዎሪና በፍልስፍና የማይመረኮዝና ዓላማውም የማይታወቅ ትግል የመጨረሻ መጨረሻ እንደሚከሽፍ የታወቀ ጉዳይ ነው። ለማንኛውም ከአንድ ዓመት ጀምሮ በአገራችን ምድር ይካሄዳል ስለሚባለው ለውጥ አንዳንድ መሰረታዊ ነገሮችን እንመልከት። ለውጥ ሲባል ታች በተዘረዘሩት መልክ የሚታይና የሚካሄድ መሆን አለበት።

ለውጥ ሲባል፣

  1. ከታች ወደ ላይ የሚያድግ(Organic Growth) ነው።
  2. ሁለ-ገብ(Holistic) መሆን አለበት። ፓለቲካዊ፣ መንግስታዊ፣ የተቋማት፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የከተማና የመንደሮች ግንባታንና ሌሎችንም አንድን አገር እንደ አገር የሚያስቆጥሯትን ነገሮች ሁሉ የሚያጠቃልል ነው።
  3. ተከታታይነት(Sustainable) ያለው መሆን አለበት።
  4. በመንፈሳዊ ተሃድሶና በዕውነተኛ ዕውቀት የሚደገፍና የሚመራ መሆን አለበት።
  5. ሰፊውን ህዝብ ያሳተፈና ለሰፊው ህዝብ ጥቅም የሚሆን መሆን አለበት።
  6. አገር አቀፍ በሆኑ ተቋማት(Institutions) የሚመረኮዝ መሆን አለበት። እነዚህም ዘመናዊና የተቀላጠፉ ተቋማት መሆን አለባቸው። በየጊዜው በአዳዲስ የስልጠና ዘዴዎች መሻሻል አለባቸው።
  7. የአገርን የሰውና የጥሬ-ሀብቶች የሚያንቀሳቅስና በራስ መተማመን(Self-reliance)የሚያዳብርና የሚደገፍ መሆን አለበት። ማንኛውም ህይወት ያለው ነገር፣ አትክልቶችንም ጨምሮ ውስጥ ባላቸው ኃይል የማደግ ችሎታ አላቸው። የውጭው ሁኔታ አጋዥ ነው። ለምሳል ዘር ሲዘራ ባለው ውስጣዊ ኃይል ስርን፣ ግንድንና ቅጠላ ቅጠሎችን ያበቅላል። ከዚያም በኋላ ፍሬ ይሰጣል። ፀሀይ፣ ዝናብና ሚኒራሎች አጋዦች ናቸው። ሲበዙ ግና አትክልቶች የማፍራት ኃይላቸው ይቀንሳል ወይም ይሞታሉ።
  8. ለውጥ ሲባል በመጀመሪያ ደረጃ የህዝብን መሰረታዊ ፍላጎቶች ማለትም፣ የተሟላ ምግብን፣ መጠለያን ወይም ቤትን፣ ህክምናን፣ ትምህርትና፣ ንጹህ ውሃን ማግኘትንና ሌሎች እንደልብስ የመሳሰሉትን የሚያካትትና የሚያሟላ መሆን አለበት። እነዚህን ማሟላት የማይችል ለውጥ አይባልም።
  9. ለውጥ ሲባል ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች በመቋቋምና በማኑፋክቸር በመደገፍ ህዝባዊ ወይም ብሄራዊ ሀብት የሚዳብርበት ሁኔታ ሲፈጠር ነው። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄድ መሆን አለበት።
  10. ዕውነተኛ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው በኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት አይደለም። ዐይነተኛ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው በመንግስት የተደገፈ ሁለ-ገብ ፖሊሲ ተግባራዊ ሲሆን ብቻ ነው። ስለሆነም ዕውነተኛ ለውጥ የውጭ ኃይሎችን ወይም የዓለም ኮሙኒቲውን ጣልቃ-ገብነት የሚፃረር ነው።
  11. የመንግስት መኪና ሙሉ በሙሉ ከመጨቆኛ መሳሪያነቱ ሲላቀቅና የህዝብ አለኝታ የሆነ መንግስታዊ መዋቅር ከተዘጋጀ ስለለውጥ ማውራት ይቻላል። ስለሆነም እንደዚህ ዐይነቱ መንግስት ከውጭ ኃይሎች ተፅዕኖ ሙሉ በሙሉ የጸዳ ሊሆን ይችላል።
  12. ይህ ዐይነቱ አገዛዝ ፍትሃዊነትን በአገር አቀፍ ደረጃ የሚያበስር መሆን አለበት።
  13. ዕውነተኛ ለውጥ በግለሰብአዊ ነፃነትና ተሳስቦ በመኖር የሚገለጽ ሲሆን፣ አርቲፊሻል የሆነ የብሄረሰብና የማንነት ጥያቄዎች ለመሰረታዊ ለውጥና ለስልጣኔ ጠንቆች ናቸው። አንድ አገር ሁለንታዊ በሆነ መልክ እንዳያድግ የሚያግዱ ናቸው። የነፃነትን ብርሃን የሚያጨልሙ ናቸው።

ከነዚህ መሰረታዊ ሃሳቦች ስንነሳ ነው አንድ ዐመት ያህል በአገራችን ምድር ለውጥ እየተካሄደ ነው የሚባለውን አነጋገር መመርመር ያለብን። በእርግጥ ዶ/ር አቢይ ስልጣን ከጨበጡ ጀምሮ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች ለመፈታት ችለዋል። የእነዚህ ሰዎች መፈታት በህዝብ ግፊትና ትግል፣ እንዲሁም በብዙ መስዋዕትነት የተገኘ ድል ነው። የአገዛዙ ቡራኬ አይደለም። አገዛዙም በድሮው መልኩ ሊቀጥል እንደማይችል የታወቀ ጉዳይ ነው። ስለሆነም ይህንን የመሳሰለውን የእስረኞችን መልቀቅና ሃሳብን የመግለጽ ነፃነት መፈቀዱ በህዝብ ተጋድሎ የተገኙ ውጤቶች ናቸው። ይሁንና አጠቃላዩን የፖለቲካ ሁኔታ ስንመለከት በተለይም 28 ዐመታት ያህል ህዝብን ሲገድሉ፣ አገርን ሲያተራምሱ፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት፣ ብሄረሰብን ከብሄረሰብ ጋር ሲያጋጩና የአገርን እሴት ባፈራረሱት ላይ ምንም ዐይነት ህጋዊ ዕርምጃ አልተወሰደም። በተጨማሪም የመንግስቱ መኪና ለጊዜው ገብ እንዲል የተደረገ እንጂ ከመጨቆኛ ባህርይው በመላቀቅ ዲሞክራሲያዊ ባህርይ ሲላበስና የህዝብ አለኝታ እንዲሆን ሲዋቀር አይታይም። ህዝብን ሲገድሉና ሲያሰቃዩ የነበሩ አንዳንዶቹ ከነበሩበት ቦታ ወደ ሌላ በመቀየር በሌላ መልክ ስራቸውን እየሰሩ እንደሆነም የምንገነዘበው ሃቅ ነው።

በብዙ አገሮች ውስጥ፣ ከአርጀንቲና፣ እስከቺሌና ብራዚል ድረስ እነዚህ አገሮች ከወታደራዊ አገዛዞች ወደሲቪል አገዛዝ ቢሸጋገሩም እስካሁን ድረስ በትርምስ ዓለም ውስጥ የሚገኙትበት ዋናው ምክንያት በመንግስት መኪናውና በፖለቲካው አወቃቀር ላይ መሰረታዊ የሆነ መሻሻል ባለመታየቱ ነው። በህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ መንግስታዊ አወቃቀር ስር-ነቀል በሆነ መልክ ባልተሻሻለበት፣ ወይም ለውጥ ባልተደረገበትና ባልተካሄደበት አገር ሰፋ ያለ ብሄራዊ ኢኮኖሚ መገንባትና የባህልም ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል የታወቀ ጉዳይ ነው። አሳ መጠንባት የሚጀምረው ከእራሱ ላይ ነው እንደሚባለው አነጋገር የፖለቲካና የመንግስት ጥያቄ መሰረታዊ በሆነ መልክ እስካልተፈታ ድረስ የተወሳሰቡት የአገራችን ችግሮች በፍጹም ሊፈቱ አይችሉም። በሌላ ወገን ደግሞ የአገራችንን የመንግስት መኪና አወቃቀር ስንመለከት በተለይም ከ1940ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ የተዋቀረው መንግስታዊ መኪና ኢቮሊሽናዊ በሆነ መልክ ከታች ወደ ላይ ከአገር ግንባታና ከህዝብ ፍላጎት አንፃር በመታየት በተገለጸላቸው ሰዎች የተገነባ ሳይሆን በከፍተኛ ደረጃ የውጭ ኃይሎች ተፅዕኖ ነበረበት። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ መንግስታዊ አውቃቀር ከፊዩዳላዊ ስርዓቱ ጋር በመቀናጀት ለዕድገትና ለነፃነት እንቅፋት እንደሆነ ይታወቃል። ከዚህም ባሻገር ኢኮኖሚው ውስጠ-ኃይሉ ደካማ ስለነበር አዳዲስና የተገለጸላቸው ኃይሎችንና ምሁራንን በማፍራት በመንግስቱ መኪና ላይ ግፊት ማድረግ አይቻልም ነበር። በዚህም ምክንያት የተነሳ ነው የየካቲቱ አብዮት ሊከሽፍ የቻለው። በአንፃሩ ራሳቸውን ችለው ወደ ስልጣን ላይ የመጡ ኃይሎች፣ እንደ ሶቭየት ህብረትና ቻይና የመሳሰሉ አገሮች ውስጥ አብዮቱ ከሞላ ጎደል ሊሳካና እነዚህም አገሮች ወደ ኃያል መንግስትነት ሊለወጡ የቻሉት የመንግስቶቻቸውን መኪናዎች ደረጀ በደረጃ ዘመናዊ በማድረግ ወይም በመለወጣቸው ነው። በተጨማሪም የእነዚህ አገሮች የመንግስት ተቋማት በውጭ የስለላ ኃይሎች አልተተበተበም። ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚደረገበትና አንድ ሰው ለውጭ ኃይሎች ሰላይ በመሆን አገርንና መንግስትን የሚበድል ስራ ከሰራና ከተያዘ በሞት ይቀጣል። እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ ደግሞ በልዩ ዘዴ ትክክል ተደርጎበት ይገደላል።

ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ የዶ/ር አቢይ አገዛዝ የመንግስቱን መኪና ራዲካል በሆነ መንገድ ሊለውጥ የማይችልበት ሁኔታ አለ። በመጀመሪያ ደረጃ የውጭው ኃይል ግፊት አለ። የውጭው ኃይል በእንደዚህ ዐይነቱ ለዕድገት ጠንቅ በሆነ የመንግስት መኪና አማካይነት ነው ድህነቱና የሰላም እጦቱ እንዲራዘም የሚያደርገው። በሁለተኛ ደረጃ፣ ምሁሩና ተቃዋሚው ኃይል ስለመንግስት መኪናና ዲሞክራሲያዊ ባህርይ ስለመላበሱ ጉዳይ ይህንንም ያህል የተገለጸላቸው አይደሉም። የመንግስት መኪና እንደታቦት የማይነካና የማይሻሻል ተደርጎ ነው የሚቆጠረው።

ይህንን ትተን ወደ ኢኮኖሚ ጥያቄዎች ስንመጣ የዶ/ር አቢይ አገዛዝ አሁንም ቢሆን ህዝባችንን ካደኸየውና አገራችንን ካተራመሰው የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ ለመላቀቅ አልቻለም። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ዕውነተኛ ብሄራዊ ሀብትን ሊፈጥር በሚችል የፖለቲካ ኢኮኖሚ ፖሊሲና ድህነትን በሚፈለፍል የኢኮኖሚ መሀከል ያለውን ልዩነት አገዛዙም ሆነ የፖሊሲ አውጭዎች የተረዱ አይመስለኝም። በሌላ ወገን ደግሞ የኢኮኖሚ ቲዎሪንና ፖሊሲን አስመልክቶ በአገራችን ምሁራን ዘንድ ምንም ዐይነት ውይይት አይካሄድም። የኢኮኖሚ ችግሮች በገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ብቻ ነው ሊፈቱ የሚችለው የሚለው አስተሳሰብ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘ ይመስላል። ስለሆነም የሚወራው ስለጂዲፒ ማደግና አለማደግ ነው እንጂ፣ ድህነትን ስለመቅረፍና በምንስ ፖሊሲ አማካይነት ነው? ብሄራዊ ኢኮኖሚ መገንባት የሚቻለው በሚለው መሰረታዊ ጥያቄ ላይ ውይይት ሲካሄድ አይታይም። ምሁሩም ሆነ መንግስት ህዝቡ በማይገባው ቋንቋ ነው የሚያወሩት። ህዝባችን ስለጂዲፒ ማደግና ስለዶር መጥፋትና አለመጥፋት ሳይሆን የሚያስበው እንዴት አድርጌ ነው? ከድህነት ልወጣ እችላለሁ እያለ ነው ሌት ተቀን የሚያስበው። ልጆቼንና እራሴን ምን ነገር ነገር ነው የምመግበው? እያለ ነው የሚጨነቀው። የትስ አድራለው? ከቤቴስ ነገ እፈናቀላለሁ ወይ? በማለት ነው የሚያወጣውና የሚያወርደው። ስለሆነም የመንግስት ዋና ተግባር ለህዝብ በማይገባው ቋንቋ መናገርና በማይሆን ነገር ላይ መረባረብ ሳይሆን በቀላሉ ሊገባውና ችግሩን በሚያቃልልለት ጉዳይ ላይ ነው መረባረብ ያለበት።

ከዚህ ስንነሳ የአገዛዙ ግራ መጋባት ይህንን ያህልም የሚያስገርመን አይደለም። አገዛዙ በውጭ ኃይሎች ወይም ኤክስፐርቶች እየተመከረ የሚያካሂደው ፖሊሲና የመንግስትን ሀብት ወደ ግል ማዘዋወር በመሰረቱ የሰፊውን ህዝብ የድህነት ዘመኑን የሚያራዝም እንጂ የህዝባችንን መሰረታዊ ችግሮች ሊፈታ የሚችል አይደለም።

አብዮት ያካሄዱ አገሮችንና በመንግስት ጣልቃ ገብነት አማካይነት መሰረታዊ ለውጥ የታየባቸውን አገሮች ሁኔታን ስንመለከት እነዚህ አገሮች በሙሉ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አላካሄዱም። እንደ ቻይና የመሳሰሉት አገሮች ከኋላ መያዝ የሚለውን ስትራቴጂና በራስ መተማመን የሚለውን ፖሊሲ በመከተል ነው የኋላ ኋላ ለገበያ ኢኮኖሚ ለውጥ የሚሆኑ መሰረቶችን ሊይዘጋጁ የቻሉት። ታውቆም ይሁን ሳይታወቅ በዚህ ዐይነቱ ሰፊውን ህዝብ በማንቀሳቀስ ስትራቴጂና የኢንዱስትሪ ተከላ አማካይነት ነው ቻይና ከድህነትና ከረሃብ ልትላቀቅና ዛሬ ደግሞ ወደ ኃያል መንግስትነት ለመሸጋገር የምታመራው። ቻይና እዚህ ዐይነት ደረጃ ልትደርስ የቻለቸው ሌሎች አገሮችን በመለመንና በዕዳ በመተብተብ ሳይሆን በራስ በመተማመን ብቻ ነው። የሰሜን ኮርያም ዛሬ ባልስቲክ ሚሳይል መስራት የቻለችው በቁጭትና በራስ በመተማመን ነው። አሜሪካኖች በከፈተቱ ጦርነት ወደ አራት ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ አልቋል። አገሪቱ እንዳለ ወድማ ነበር። ከዚህ አሳዛኝ ሁኔታ በመነሳት ነው የተወሳሰቡ ቴክኖሎጂዎችን መስራት የቻለችው። በአብዮቱ ጊዜ የተሟላ የማሽን ኢንዱስትሪና የመሳሪያ ፋብሪካ ለኢትዮጵያችን ለግሳለች።  ጃፓንም ሆነ ጀርመን ቀደም ብለውም ሆነ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ወደ ሁለ-ገብ የአገር ግንባታና የቴክኖሎጂ ዕድገት መሸጋገር የቻሉት በተጠና የመንግስት ጣልቃ-ገብ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ነው እንጂ በእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና(IMF) በዓለም ባንክ በመመከርና በውጭ መዋዕለ-ነዋይ አማካይነት አይደለም። በአውሮፓ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ዕድገት ታሪክ ውስጥ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ አሜሪካና ጀርመን በሌላ የውጭ ከረንሲ በመመካትና በመበደር አይደለም  ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊጎናጸፉና ዓለምን ለመቆጣጠር የቻሉት። በዘመኑ ዶላርና ኦይሮ የሌሎች አገሮችን ዕድገት አጨናጋፊ መሳሪያዎች ናቸው። ማታለያ መሳሪያዎች ናቸው። ውስጣዊ ዋጋ(Intrinsic Value)የላቸውም። በታሪክና በአገር ግንባታ ውስጥ በዕዳና በዕርዳታ ተመክቶ ያደገ አገር የለም። ታላላቅ ስልጣኔዎች በሙሉ ዶላርና ኦይሮ ከመፈጠራቸውና የዓለም ንግድ መገበያያ መሳሪያዎች ከመሆናቸው በፊት ተመስርተዋል። ከተማዎችና ካቴድራሎችና መስጊዶች፣ እንዲሁም ቤተ-መንግስቶች ተገንብተዋል። የዕደ-ጥበብ ስራዎችና ንግድ በየአገሩ አብበዋል። እነዚህ ሁሉ የተገነቡትና ማደግ የቻሉት ቀስ በቀስ ማደግ ከጀመረው የውስጥ የስራ-ክፍፍል ጋር ተያይዞ ካደገው የአገር ውስጥ ገንዘብ ጋር በመተሳሰር ነው። ስለሆነም ዶላርና ኦይሮ የተዘበራረቀ ሁኔታ ከመፍጠርና ድህነትን ከማራዘም በስተቀር ስርዓት ወዳለው ጥበባዊ ወደ ሆነ የአገር ግንባታ ሊሸጋገሩን በፍጹም አይችሉም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  "ከውስጥ ኾነው የተላላኪነት ሥራ በሚሠሩ የሕዝብ ጠላቶች ላይ ሕጋዊና ፖለቲካዊ እርምጃ እየተወሰደ ነው" የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ያለዓለም ፈንታሁን

የምዕራብ አውሮፓን፣ የጃፓንን፣ የደቡብ ኮርያን፣ የሶቭየት ህብረትን፣ ዛሬ ደግሞ የራሽያን፣ የሲንጋፖርንና የአንዳንድ አገሮችን የተስተካከለና የተሟላ የኢኮኖሚ ዕድገት ፖሊሲ ስንመለከት ከታች ወደ ላይና ከላይ ወደታች በጣልቃ-ገብ ፖሊስ አማካይነት ነው እዚህ ዐይነቱ ደረጃ ላይ ሊደርሱ የቻሉት። የጀርመንን ሁኔታ ስንመለከት ጀርመን ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ስኬታማ ውጤት ልታመጣ የቻለችው፣ በመጀመሪያ ደረጃ መሰረታዊ የህዝብ ፍላጎቶች ከተመለሱ በኋላ ነው። ሰፊውን ህዝብ መንገድ ላይ እንዲጣል በማድረግና በጎጆ ቤት ውስጥ እንዲኖር በማድረግ አይደለም የአንድን አገር ኢኮኖሚ በጠንካራ መሰረት ላይ ሊገነባ የሚችለው። በአገራችንና በብዙ አፍሪካ አገሮች ውስጥ ያለው  የአስተሳሰብ ግድፈት የኢኮኖሚ ጉዳይ ከህዝብ ፍላጎት ጋር ለመያያዝ ባለመቻሉ ነው። የሚተከሉት ኢንዱስትሪዎችም ሆኑ ተግባራዊ የሚሆነውም የእርሻ ፖሊሲ የውጭ አገሮችን ፍላጎት ለማርካት እንጂ በተቀዳሚ የህዝባቸውን ፍላጎት ለማርካት አይደለም። በዚህም ምክንያት የተነሳ አገዛዞች የፕላንቴሽን ኢኮኖሚ በማካሄድ ድህነቱና መዘበራረቁ እንዲራዘሙና ህዝብም እንዲናቅ በማድረግ ላይ ናቸው። በተጨማሪም ሆቴል ቤቶችን በመስራት ከፍተኛ ሀብት ይወድማል። አንድ አገር ወድ አስረሽ ምችነት እንድትለወጥ ትደረጋለች። ይህ ማለት ግን ጊዜውን ጠብቆ እንደ አስፈላጊነቱ ሆቴል ቤቶች አይሰሩ ማለት አይደለም። ህዝብን ሜዳና ቆሽሻ ላይ ውስጥ እየጣሉ ሆቴል ቤቶችን መስራት ከፍተኛ ወንጀል ነው። የስልጣኔና የዕድገት ምልክት ሳይሆን የኋላ-ቀርነት ምልክት ነው።

የዚህ ሁሉ ዋናው ችግር የአገራችን አገዛዞች ስልጣን ሲይዙ በመጀመሪያ ደረጃ ዋናው ዓላማቸው ምን እንደሆነ አለመታወቁ ነው። በሁለተኛ ደረጃ፣ ለተወሳሰቡት ችግሮች መነሻዎቻቸው ምንድናቸው? በሚሉት ጉዳዮች ላይ ጥናት ስለማይካሄድ ነው። ስለሆነም የዶ/ር አቢይ አገዛዝ ከተሳሳተ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት(Macroeconomic imbalances) በመነሳት ነው የአገራችንን የተወሳሰበ ችግር ለመፍታት የሚቃጣው። እንደሚታወቀው ይህ ዐይነቱ መዛባት የመሰረታዊ ኢኮኖሚው አወቃቀር (Strucctural Crises) ነፀብራቅ (Manisfestation) ነው እንጂ፣ በራሱ ለቀውሱ ዋና ምክንያት አይደለም። የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ኮሙኒቲው የአንድን አገር የኢኮኖሚ አወቃቀር በተሳሳተ መልክ ነው የሚረዱትና የሚያነቡት። በአስተሳሰባቸው ውስጥ ህብረተሰብአዊ አወቃቀርና የፖለቲካ ኃይል አሰላለፍ(Social formations and political power relationships) የሚባል ነገር የለም። እነዚህ ነገሮች ድህነትን በመፈልፈልና ኋላ-ቀርነትን በማፈርጠም የሚኖራቸውን ሚና በፍጹም አይገነዘቡም።  ስለዚህም ድህነትና ኋላ-ቀርነት ጉዳያቸው አይደለም። ስለሆነም የዓለም የገንዘብ ድርጅት የሚባለውና የዓለም ኮሙኒቲው አዳዲስ አገዛዞችን በማሳሳትና ጫና በማድረግ ቀውሱ ጥልቀት እንዲያገኝና የመፍቻ ዘዴም እንዳይገኝለት ያደርጋሉ። ይህን ዐይነቱን ፖሊሲ ከ60 ዐመታት በላይ ተግባራዊ ሲያደርጉ የቆዩበትና የበላይነታቸውም መግለጫ ስለሆነ የግዴታ ድህነትና አጠቃላይ የሆነ የኢኮኖሚ ቀውስ እንዲፈጠር ያደርጋሉ። ስለሆነም አገዛዙ ከዚህ ዐይነቱ ድህነትን ፈልፋይ ከሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እስካልተላቀቀ ድረስ የኢትዮጵያ ህዝብ ዕውነተኛ ነፃነቱን ሊቀዳጅ በፍጹም አይችልም።

በአጭሩ የዶ/ር አቢይ አገዛዝ ከላይ የዘረዘርኳቸውን 13 መሰረተ-ሃሳቦች ሊያሟላ የሚችል አገዛዝ አይደለም። ስለለውጥ ያለውም አስተሳሰብ የተዛነፈና ኢ-ሳይንሳዊ ነው። የአገራችንን ብሄራዊ ነፃነት የሚያስከብርና ህዝባችንም ዕውነተኛ ነፃነትን የማግኘት ኃይሉ እየመነመነ ይሄዳል ማለት ነው። ስለሆነም ነው የዶ/ር አቢይ አገዛዝ በዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘውና ተስፋ የሚጣልበት አገዛዝ እየተባለ የሚወደሰው።  መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ደፍ ደፍ በማለቱና ድህነትን ለመጨረሻ ጊዜ ከአገራችን ምድር ለማስወገድ ባለው የተወሳሰበ ስትራቴጂ አይደለም የሚመሰገነው። መሰረታዊ ለውጥ የማምጣት ፍላጎት ያለው ኃይል ቢሆን ኖሮና ፍንጭም ቢያሳይ እንደ ታንዛኒያው ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ ዘመቻና ዛቻ ይካሄድበት ነበር።

ለማንኛውም በአገራችን ምድር መሰረታዊ ለውጥን ማምጣትና አለማምጣት መቻል በዶ/ር አቢይ አገዛዝ ላይ ብቻ የሚሳበብ አይደለም። የዶ/ር አቢይ አገዛዝ ከድሮዎች አገዛዞች፣ በተለይም ከወያኔ አገዛዝ የወረሳቸው የተወሳሰቡ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ቀውሶች አሉ። እነዚህ ቀውሶች ከአገዛዙ አቅም በላይ የሆኑ ብቻ ሳይሆኑ ሁላችንም ለዚህ ዐይነቱ አስቸጋሪ ሁኔታ የተዘጋጀን አይደለንም። ከመጮህና ከመተቸት በስተቀር አማራጭ የሆነ ሁለ-ገብ ፖሊሲ አዘጋጅተን ማቅረብ አልቻልንም። አንዳንዶቻችን ከመንግስቱ ጋር ተለጥፈን ዝም ብለን መጓዝን የመረጥን አለን። ሌሎች ደግሞ ከመተቸትና የማይሆን ጥያቄ ከማቅረበ በስተቀር ያለውን ችግርና ምንጩን በመረዳት መሰረታዊ የሆነ መፍትሄ ሲያቀርቡ አይታይም። ይህም ማለት ያለው ድክመት በሁላችንም ዘንድ ነው። ስለዚህ ችግሩ ሁላችንን የሚመለከትና አዲስ አስተሳሰብ እንድናፈልቅና እንድናዳብር የሚጋብዘን ነው ማለት ነው። ከዚህ በመነሳት ሰሞኑን የተወረወሩ አንዳንድ ሃሳቦችን በመዳሰስ ጽሁፌን ለመደምደም እፈልጋለሁ።

ተስፋ የሚጣልበት ወይም ያልተሳካለት መንግስት(Failed State)! 

ሰሞኑን በሁለት ግዙፍ ምሁራንና የአገራችን ተቆርቋሪ ነን በሚሉ ሁለት ጽሁፎች ለንባብ ቀርበው በተለይም በውጭው ዓለም የምንኖረውን ኢትዮጵያዊያኖች ግራ „አጋብተውናል።“ ሁለቱም ዶ/ር አቢይ ስልጣን ላይ ከወጡ በኋላ አገር ቤት በመግባት አንዳንድ ቦታዎችን ያዩና በውይይትም ሆነ በጥናት የተሳተፉ ናቸው።

አንደኛው የዶ/ር አቢይን አገዛዝ ያልተሳካለት ነው ሲል፣ ሌላው ደግሞ ተስፋ የተጣለበትና በዓለም አቀፍ ኮሙኒቲውም ሆነ በታወቁ ጋዜጦች ተቀባይነትን ያገኘና የሚወደስ ወጣት መሪ ነው በማለት የጦፈ ክርክር ተካሂዷል። ሁለቱም አቅራቢዎች አስተያየታቸውን በቲዎሪም ሆነ በኢምፔሪካል ደረጃ ሳያረጋግጡና መቋጠሪያ ሳይስጡ  ነገሩን ዘግተውታል። ሁለቱም ተቃራኒዎች የአሜሪካን ቲፎዞዎችና በአሜሪካን የበላይነት የሚያምኑ ናቸው። በመሰረቱ የሚያጣላቸው ነገር አልነበረም። ሻለቃ ዳዊት ኃይለጊዮርጊስና ፕሮፌሰር ኃይለማርያም በመባል የሚታወቁና ብዙ መጣጥፎችንም ለንባብ ያቀረቡና የሚያቀርቡም ናቸው።

ከሻለቃ ዳዊት እንነሳ። ሻለቃ ዳዊት ጥቂት ሳምንታት ኢትዮጵያ ውስጥ ከቆየ በኋላ ያየውንና ለማንበብ የቻለውን አሜሪካ ከተመለሰ በኋላ የዶ/ር አቢይን አገዛዝ ያልተሳካለትና ጸጥታንም ማስጠበቅ ያልቻለ መንግስት ወይንም አገዛዝ ነው በማለት ይከሰዋል። የላይ ላዩን ሲታይ ይህ ውንጀላ ትክክል ነው ብሎ መቀበል ይቻላል። ይሁንና ሻለቃ ዳዊት የዶ/ር አቢይ አገዛዝ ያልተሳካለት ነው ሲል ያላየቸውና ለማየትም ያልቻላቸው አያሌ ጉዳዮች አሉ። አንድ መንግስትና አገዛዝ ምን ምን ነገሮች ሲጎድሉት ነው ያልተሳካለት አገዛዝ የሚባለው?  ምን ምን ነገሮች ሲሟሉ ነው የተሳካለት አገዛዝስ ተብሎ ሊወደስ የሚችለው? በተጨማሪም ይህ ሁኔታ እንዴት ሊከሰት ቻለ? ከመቅጽበት ወይስ እየተክማቸ የመጣ? በአገዛዙ ብቻ የተፈጠረ ወይስ የውጭ ተፅዕኖ ያለበት? የሚሉትን መሰረታዊ ጥያቄዎች በማንሳት አላስተማረንም፤ እንድንወያይም አላደረገንም። ለማንኛውም የሻለቃ ዳዊትን ጽሁፍ ላነበበ ሰውየው ንጹህ በንጹህ መልክ የሚሊታሪ ሰው እንደሆነና፣ ከሚሊታሪ ሎጂክ አንፃር እንደተመለከተው መረዳት ይቻላል። ይህም ማለት አጻጻፉና አመለካከቱ፣ እንዲሁም ግንዛቤው ለአንድ ህብረተሰብ እንደማህበረሰብ ለመያያዝና ለመጠንከር የሚያስፈልጉትን ሰፋ ያለና፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም በማኑፋክቸር ላይ የተመሰረተን አገር እንደመነሻ ወይም እንደመነጻጸሪያ አድርጎ በመውሰድ አይደለም ሊያስተምረን የተነሳው። በዚህም ምክንያት የተነሳ የሰውን ልጅ ምንነትና በተሟላ የነፃነት ዓለም ውስጥ መኖርን እንደ አስፈላጊና፣ ይህም ጉዳይ የአንድ አገር መንግስት መሰረታዊ ተግባር  መሆኑን በመገንዘብ  አይደለም የአገዛዙን ደካማነት የሚነግረን። ከዚህም በላይ ስለተቋማት(Institutions) አስፈላጊነት በፍጹም አላነሳም። በተቋማትና በብቃትነታቸው አማካይነት ብቻ ነው በአንድ አገር ውስጥ ሰፋ ያለ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሊመጣ የሚችለውና መረጋጋትም የሚኖረው።

እንደሚታወቀው ወይም ደግሞ ምናልባት አንዳንዶቻችን ጥናት አድርገን እንደሆን፣ የዛሬው አስቸጋሪ ሁኔታ ወይም የውድቀት ጉዳይ ዛሬውኑ በዶ/ር አቢይ የአንድ ዐመት አገዛዝ ዘመን ከመቅጽበት የተፈጠረ አይደለም። ጉዳዩ የብዙ መቶ ዐመታት ታሪክ ያለው ሲሆን፣ የአገራችን አስቸጋሪ የህብረተሰብ አወቃቀር ታሪክ ነፀብራቅ ነው ማለት ይቻላል።  በተለይም የዛሬው ያልተሳካለት መንግስት ጉዳይ መሰረቱ የተጣለው አፄ ኃይለስላሴ ከስደት ከተመለሱና ስልጣንን ከጨበጡ በኋላ ነው ማለት ይቻላል። በጊዜው የኢትዮጵያ መንግስት መኪና ዘመናዊና ፊዩዳላዊ በሆኑ የአሰራር ዘዴዎች የሚገለጽ ነበር። ዘመናዊ የሚባለው በአዲስ አበባ ብቻ ላይ የተስፋፋ ሲሆን፣ በአብዛኛው ክፍለ-ሀገሮች ውስጥ ዘመናዊ ተቋማት ያልነበሩና ሰፊው ህዝብም ካለምንም አጋር የሚኖር ነበር ማለት ይቻላል። በአፄው የአገዛዝ ዘመን የነበረውን የአዲስ አበባንም ሁኔታ ስንመረምርም የተዘበራረቀና ተቋማትም ያልተሟሉ ነበሩ። የከተማው ዕቅድና የተቋማቱ ጉዳይ የተዘበራረቀው የእኮኖሚ ነፅብራቆች ናቸው ማለት ይቻላል። ይህም ማለት፣ የአፄው አገዛዝ በ20ኛው ክፍለ-ዘመን አንድ መንግስት ለአገሩ ማድረግ የሚገባውን የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የባህላዊ፣ የስነ-ልቦናና ሌሎች ለአንድ ህብረተሰብ የሚያስፈልጉ ተቋማትን መዘርጋት ያልቻለና ምንም ያልታየው ነበር። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ አንዳንድ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላቸው የአሺያ አገሮች ካለፉት ስርዓቶች በመማርና ሰፋ ያለ ተቋማትን በመዘርጋትና በየጊዜው የመሻሻልን አስፈላጊነት በመረዳት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ፣ በዚያው ዘመን የአፄው አገዛዝ ይመካ የነበረው ንጹህ በንጹህ በወታደሩና በጸጥታ ኃይሉ ብቻ ነበር። ወደ ገጠርና ወደ ክፍለ-ሀገር ከተማዎችም ስንሄድ የተዘበራረቁና ሁኔታዎችና ፊዩዳላዊ ስርዓቶች እንደነበሩ እንረዳለን። በዚህም ምክንያት የተነሳ የአፄው አገዛዝ የሰፊው ህዝብ ጉዳይ የማያገባውና የአንድን መንግስት መሰረታዊ ተግባሮች ያልተረዳ ነበር ማለት ይቻላል። በየጊዜው በተደጋጋሚ የተከሰተውን ረሃብና በገጠሮችና በአንዳንድ ከተማዎች የተስፋፋውን ድህነትና የሴተኛ አዳሪነት እንደ አሸን መፍለቅ ስንመለከት በጊዜው የአፄው መንግስትም ያልተሳካለት መንግስት(Failed State) ነው ብሎ መደምደም ይቻላል። በጊዜው የአፄው አገዛዝ ከፍተኛ የሆነ የርዕዮተ-ዓለም ተቀባይነት ቢኖረውምና የሚመለክም አገዛዝ ቢሆንም፣ አገዛዙና ሚኒስተሮቹ ከህዝብ እርቀው የሚኖሩ ነበሩ። ሌላውን ትተን የኢኮኖሚና የእርሻ ሚኒስተሮች በተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር የህዝቡን አኗኗርና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን የሚያጠኑና ምን ምን ነገሮች መደረግ እንዳለባቸው ጥናት እንዲደረግ ትዕዛዝ የሚሰጡና የሚከታተሉ አልነበሩም። ከዚህ አጭር ሀተታ ስንነሳ የኢትዮያ ህዝብ የራሱ የሆነ መንግስትና አገዛዝ አልነበረውም። ዝም ብሎ ብቻ አንገቱን ደፍቶ የሚኖርና አምላክ ሆይ ደህና ቀን አምጣልኝ ብሎ የሚጸልይና የሚለምን ህዝብ ነበር። እንደዚህ ዐይነቱን አገርና ህዝብ ነው አፄውና አገዛዛቸው ጥለውልን የሄዱት።

ይህንን ጉዳይ አብዮቱ ከፈነዳ በኋላ ከሞላ ጎደል ለማረም አንዳንድ የጥገና ለውጦች በመወሰድ ተፎካካሪ የመንግስት መዋቅሮች ተተክለው ነበር። ገበሬውና ሰራተኛው በሙያ ማህበሩ መደራጀት፣ የቀበሌ ማህበራት መቋቋምና፣ የሴቶችና ወጣቶች መደራጀትና ሃሳባቸውን መግልጽ፣ ሰፊውን የገጠር ኗሪ ህዝብ ለማስተማር የተደረገው ዘመቻና በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች በገጠር ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሰመራትና ቀስ በቀስ የፊዩዳሉ ስርዓት መንኮታኮት የሚያረጋግጡት በጊዜው አገራችን ወደ ተሻለ ዘመናዊነት በመሽጋገር ላይ እንደነበረች ነው። ይህ ዐይነቱ ለውጥ በውስጥና በውጭ ኃይሎች የተቀነባበረ ሴራ ሊከሽፍና አገራችንም የጦር አውድማ ለመሆን በቅታለች። በዚህ ዐይነቱ አገርን የማፈራርስ ሴራ ውስጥ በጊዜው አንዳንድ ለአሜሪካን ያደሩ ወጣት መኮንኖችም ተሳትፈውበታል። ወያኔም እንዲገባ ሁኔታውን አመቻችተውለታል።

ከዚህ ስንነሳና እነወያኔ ስልጣን ከያዙ በኋላ ተግባራዊ የሆነው የክልል አስተዳደር ለዘመናዊና ለተቀለጣፈ ተቋማት መቋቋም አመቺ ሁኔታ እንዳይፈጠር አግዷል። በየክልሉ ዋና ከተማዎች ምሁራዊ እንቅስቃሴ መዳበር አልቻለም። የየክልሉ አስተዳዳሪዎች እራሳቸውን ከማደለብና ሀብት ከመዝረፍ በስተቀር የስራ-ክፍፍል እንዲዳብር ለማድረግ አልቻሉም። በአንፃሩ በተለይም በኦሮምያ ክልል የተስፋፋው የአበባ ተከላ አካባቢውን ሊያደቀው ችሏል። ድህነትና ውድቀት ስር ሊሰዱ ችለዋል። በአጭሩ ያልተገለጸላቸው የየክልሉ አስተዳዳሪዎች አካባቢዎቻቸውን ዘመናዊና የሰለጠነ ማድረግ አልቻሉም። ሰፋ ያለ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲዳብር ማድረግ አልቻሉም። የባህል ማዕከሎችም በማቋቋምና፣ በተለይም ወጣቱን በማስተማር የህዝቡ የማሰብ አድማስ እንዲሰፋና እንዲዳብር ለማድረግ አልቻሉም። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ በሌለበት ደግሞ ተቋማትን መመስረት አይቻልም። ተቋማት በሌሉበት ቦታ ደግሞ ህዝቡ የሚመካበት  ነገር ስለማይኖረው በቀላሉ ለአደጋ መጋለጡ የማይቀር ግዴታ ነው። ወጣቱም በሙያ ስልጠናና በስራ እስካልተወጠረ ድረስ በቀላሉ የልዩ ልዩ ነገሮች ሰለባ መሆኑ የማይቀር ጉዳይ ነው። ይህ በራሱ ደግሞ ለጽንፈኛ ኃይሎች አመቺ ሁኔታን ይፈጥርላቸዋል። በአጭሩ የዶ/ር አቢይ አገዛዝ ያልተሳካለት ነው ወይም ማስተዳደር አልቻለም ስንል፣ ይህ ሁኔታ እንዴት እንደተፈጠረ ደረጃ በደራጃ ማጥናትና የተሻለ ሃሳብም መሰንዘር አለብን። ሻለቃ ዳዊት ኃይለጊዮርጊሲ ነገሩን ከብዙ ሁኔታዎች አንፃር ሳይመለከትና ሳይመረምር የሰነዘረው አስተያየት ሳይንሳዊ ግንዛቤ የሚጎድለው ነው። አቀራረቡ አሳሳች ነው። ለአገር ተቆርቋሪ ነኝ ብሎ ለማስመሰል የተጻፈና በሰፊው እንዳናስብና ስሜታዊ እንድንሆን የሚጋብዘን ነው።

የፕሮፌሰር ኃይለማርያምን አቀራረብ ደግሞ እንመልከት። ፕሮፌሰር ኃይለማርያምም እንደ ሻለቃ ዳዊት አንዳንድ ቦታዎችን ተመልክቷል። ከሻለቃ ዳዊት ይልቅ ፕሮፌሰር ኃይለማርያም ከዶ/ር አቢይ ጋር የጠበቀ ግኑኝነት አለው። በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከሻለቃው ለየት ባለ ሁኔታ እንዲመለከተው ተገዷል። በእሱ ዕምነትም የዶ/ር አቢይ አገዛዝ ያልተሳካለት አገዛዝ ሊባል የሚችል አይደለም። ኢትዮጵያ በታሪኳ ውስጥ መልካም ራዕይ ባለውና በዓለም ኮሙኒቲው ዘንድ ተቀባይነትን ባገኘ ወጣት መሪ የምትመራ አገር ነች ብሎ የተቀበለና የሚያምን ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ በዓለም ላይ አሉ የሚባሉ ጋዜጦች ሁሉ ዶ/ር አቢይን ያደንቁታል በማለት ለማረጋገጥ ሞክሯል። ለተቀሩትም የአፍሪካ አገዛዞች ምሳሌ ለመሆን የበቃና ተፅዕኖም ሊያሳድር የሚችል ነው የሚል ዕምነት አለው።

በመሰረቱ እንደዚህ ዐይነቱ አባባል ከአንድ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር የሚጠበቅ አጻጻፍ አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ አንድ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና ብዙ መጽሀፎችን ያነበበ በሌሎች የሚመራና እነሱን እንደምስክርነት መውሰድ ያለበት ሳይሆን፣ በራሱ ህሊና የሚገዛ መሆን አለበት። በሁለተኛ ደረጃ፣ በምድር ላይ የሚታዩትን ነገሮችና አገዛዙ ተግባራዊ ሊያደርጋቸው የሚፈልጋቸውን ፖሊሲዎች መመርመር አለበት። በሶስተኛ ደረጃ፣ የአገዛዙን ርዕየተ-ዓለም መመርመር አለበት። ከዚህም በመነሳት የሚታዩትን ችግሮች በምን ዐይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለመቅረፍ እንደተነሳ ማጥናት አለበት። በአራተኛ ደረጃ፣ በአጠቃላይ ሲታይ ብሄራዊ አጀንዳውንና ራዕዩን ማጥናት አለበት። ከዚያ በኋላ የራሱን ግምገማ መስጠት ይችላል። ይህንን ሳያደርግ የዝምባላችሁ ተቀበሉ አጻጻፍ የአምባገነንነትን ባህርይ ያሳያል። እኔ ምሁር ስለሆንኩ ከእኔ በላይ ማንም የሚያውቅና ፍርድም የሚሰጥ ስለሌለ ሁላችሁም አፋችሁን ዝጉ የሚል አጻጻፍ ነው ፕሮፌሰሩ ያስነበበን። ያም ተባለ ይህ፣ የፕሮፌሰሩ ዋና ድክመት አንድን መሪ እንደ ሙሴ ማየቱ ነው። እሱ ብቻ ነው ችግሩን መፍታት የሚችለው ብሎ ማመኑ ነው። በሌላ ወገን ግን ፕሮፌሰሩ የአገራችንን ሁኔታ ወረድ ብሎ በየቆሻሻ ቦታዎች ያሉትን ሁኔታዎች እየተዘዋወረ ቢያጠናና እዚያው አንድ ሁለት ቀን ቢያድር ኖሮ ምናልባት የችግሩን ውስብስብነት ሊገነዘበው በቻለ ነበር። ቤተ-መንግስት ገብቶና አድሮ ሲወጡ የሚኖር አስተያየት ሁል ጊዜ ሚዛናዊ ፍርድ ለመስጠት ያስቸግራል። የወያኔ አፍቃሪ ፈረንጆችም አዲስ አበባ ሄደው አገዛዙ ሼራተንና ሌሎች ዘመናዊ ሆቴል ቤቶች ውስጥ ጋብዟቸው ሲመለሱና የኢትዮጵያን ሁኔታ ሲጠየቁ ይሰጡን የነበረው መልስ አገሪቱ በጣም ተለውጣለች፤ ድህነትም በጣም ቀንሷል በማለት ነበር።  በዚህ መልክ አብዛኛው ህዝብ በድህነት ዓለም ቢኖርም አንዳንድ ሰዎች ከራሳቸው ምቹ ሁኔታና አቀባበል በመነሳት ሌላውም ሰው እንደ እነሱ ተመችቶትና ተደስቶ የሚኖር ይመስላቸዋል።

ባጭሩ የሁለቱን ምሁሮች አቀራረብ ስንመለከት አጻጻፋቸው ሶፊስቲያዊ ነው። ኃይል ያለው ትክክል(Might is right) ነው የሚለውን የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምን የአመጽ ፖለቲካ የሚያንፀባርቁ ናቸው። አስተሳሰባቸው በእሱ ሎጂክ ውስጥ የተዋቀረ ነው።  ወደ ውስጥ በመግባት በአገራችን ውስጥ የተፈጠረውን አስቸጋሪ ሁኔታ በመቃኘት አይደለም ሁለቱም ምሁሮች ብሶታቸውንና ደስታቸውን የሚጽፉልን። ሁለቱም የአገራችንን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የባህል ዕድገትና አወቃቀር በዲያሌክቲካዊ መነጽር በማየት የዛሬው ሁኔታ እንዴት ሊፈጠር እንደቻለ ሊይስረዱን በፍጹም አልቻሉም። እንደሌሎች አብዛኛዎች የአፍሪካ አገሮችም ኢትዮጵያም የግሎባል ካሊታሊዝም መስዋዕት መሆኗን የተገነዘቡ አይደሉም። ስለ ዓለም አቀፍ የፖለቲካ፣ የሚሊታሪና የኢኮኖሚ አወቃቀር ያላቸው አስተያየት ግልጽ አይደለም። በተለያየ ጊዜ ስልጣንን የተቀዳጁ አገዛዞች በኢምፔሪያሊዝምንና በግሎባል ካፒታሊዝም ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሚሊታሪያዊ አወቃቀር ውስጥ በመካተት እንደሚታሹና ህዝቦቻቸውም የድህነት ሰለባ እንደሆኑ በፍጹም የተገነዘቡ አይመስልም። ይህንንና የአገራችንን አስቸጋሪ የህብረተሰብ ታሪክ ሂደት ነው ሻለቃ ዳዊትም ሆነ ፕሮፌሰር ኃይለማርይም ሊመለከቱና ሊገነዘቡ ያልቻሉት። የአንድን አገር ተጨባጭና የፖለቲካ ሁኔታ በሳይንስና በንድፈ-ሃሳብ በመደገፍ መተንተን ካልቻልን የግዴታ የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ነው የምንደርሰው።

 

መደምደሚያ!

የአገራችን ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ነው። ድክመቱ የሁላችንም ነው። ዛሬ የምናየው የተወሳሰበ ችግር እየተደራረበ የመጣ ነው። በተለያዩ ጊዜያት አገራችንን ይገዙ የነበሩ ኃይሎች ተግባራዊ ያደረጓቸው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ ህዝባችንን የሚያስተሳስሩ አልነበሩም። የሳይንስንና የቴክኖሎጂን፣ የተቋማትን መገንባት፣ የከተማዎችን ጥበባዊ በሆነ መልክ መሰራት፣ የስራ-ክፍፍል መዳበርና በተለያዩ የኢኮኖሚ መስኮች መሀከል መተሳሰር ያለባቸው መሆናቸውን ለመገንዘብ ባለመቻላቸው አገራችንና ህዝባችንን አዝረክርከውና አድክመው ሄደዋል። የብሄራዊ ውርደት አከናንበውናል። ሰፋ ያለና በራሱ የሚተማመን ምሁራዊ ኃይል እንዳይዳብርና የህዝባችንና የአገራችን አለኝታ እንዳይሆን ለማድረግ በቅተዋል። አገዛዞቻችን በራሳቸው ዓለምና ለራሳቸው የሚኖሩ እንጂ ከህዝባቸው ጋር የሚያስተሳስራቸው አንዳችም ነግር አልነበረም። ስለሆነም ህዝባችንን አደንቁረውና በውስጥ ኃይሎች እንድንቦረቦርና እንድንዳከም አድርገውን ሄደዋል። ይህ በራሱ ደግሞ ለዚህኛውና ወይም ለዚያኛው የውስጥ ኃይል የመንቀሳቀሻ መድረክ በመፍጠር ከውስጥ ጦርነት አውጀውብናል። ብሄራዊ ስሜት እንዳይዳብርና በአንድነት ተነስተን ጠንካራ አገር እንዳንመሰርት ተደርገናል። ከዚህ ስንነሳ ሁኔታውን በሌላ የምሁራዊ መነፅር መመልከትና መመርመር ያለብን ይመስለኛል። አገር ልትፈርስ ነው እያሉ መጮኽ በራሱ የሚያመጣው ጥቅም ምንም ነገር የለም። ጭንቅላታችንን በአዲስ ምሁራዊ አስተሳሰብ እስካላነፅንና እስካላደስን ድረስ የአገራችን ሁኔታ ከመቶ ዓመት በኋላም በዚህ መልክ መቀጠሉ የማይቀር የታሪክ ግዴታ ነው። አሁን ባለን አመለካከትና ጩኸት ለህዝባችንና ለአገራችን ፋይዳ ያለው ነገር ልንሰራ አንችልም። የጨለማውንና የድኽነቱን ዘመን ከማራዘም በስተቀር አዲስ ኢትዮጵያን ልንገነባና ለመጭው ትውልድ ማስተላለፍ አንችልም።

ዋናው አስቸጋሪ ነገር በሁላችንም ዘንድ ያለው እጅግ ወደ  ኋላ-ቀር አስተሳሰብ  ነው። ጭንቅላታችንን በኋላ-ቀር አስተሳሰብ በመወጠሩ የተነሳ የነገሮችን ዕድገትና ውስብስብነት እንዳናይ ተገደናል። በዚህ ላይ ያልተገለጸላቸውና ፊዩዳላዊ የሆኑ ኃይሎችና አክቲቪስቶች የፖለቲካውን መድረክ በመያዛቸው በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠርን ህዝብንና ወጣትን እያታለሉ ነው። የፖለቲካው ሜዳ ሁሉም እንደፈለገው የሚዋኝበት ሆኗል። ሁሉም ለአገር ተቆርቋሪ ነኝ ባይ ነው። እዚያው በዚያው ደግሞ የውጭ ኃይሎችን የሚማጽን ነው። የርዕዮተ-ዓለም ጥራት የሌለውና አገራችን በምን ምን መሳሪያዎች መገንባት እንዳለባት የተገለጸለት አይደለም። በዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ ግልጽ አስተዋፅዖ ማበርከት በፍጹም አይቻልም። ደቀ-መዝሙሮችን ማፍራትም አይቻልም። በተለይም በውጭ ኃይሎች የሚደገፉትንና የሚንቀሳቅሱትን መቋቋም በፍጹም አይቻልም። እነዚህ ኃይሎች ህልማቸው የውጭ ኃይሎችን ጥቅም ማስጠበቅ ስለሆነ በአገራችን ምድር ዕውነተኛ ነፃነትና ብልጽግና እንዳይመጣ አጥብቀው የሚታገሉ ናቸው። በዚህ ዐይነት ያልተስተካከለ ትግል ውስጥና፣ አብዛኛው ደግሞ ከዕውቀት ይልቅ የላይ ላዩን የሚጋልብ ከሆነ ስለ አገርና አንድነት መጠበቅ ማውራት በፍጹም አይቻልም። ጥያቄው ይህንን ሁኔታ እንዴት መስበር ይቻላል? ነው። ስለህነም ለዚህ መልስ መፈለግ ያለብን ይመስለኛል። መልካም ግንዛቤ !!

 

 

fekadubekele@gmx.de    

 

Share