May 6, 2019
53 mins read

እነርሱ ምን ያድርጉ? – ጠገናው ጎሹ

May 6, 2019

ጠገናው ጎሹ

 

  1. የህወሃት/ኢህአዴግን እኩይ የፖለቲካ አስተሳሰብ፣ አደረጃጀትና አካሄድ ለማስወገድና እውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ለማድረግ የሚያስችል የጋራ አገራዊ ራዕይ ፣ መርህና የድርጊት ፕሮግራም ያለው የፖለቲካ ሃይል (ድርጅት) ተወልዶ እንዲጎለብት ለማድረግ ያለመቻላችን ጉዳይ የሁለት አስቀያሚ ምርጫዎች ጥያቄ  (dilemma )  ላይ ጥሎናል ።  እነዚህ ሁለት አስከፊ (አስቀያሚ) ምርጫዎች ፦ ሀ) መሠረታዊ  የሥርዓት ለውጥ እውን ለማድረግ በሚያስችል መንገድ ወደ ፊት ከመራመድ ይልቅ  የኢህአዴግ “የጥልቅ ተሃድሶ” ጨዋታ አጃቢ (አካል) በመሆን የፍርፋሪ “ትሩፋት” አነሰንና ዘገየብን ከሚል እጅግ የወረደና አዋራጅ የፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ  መዘፈቃችን  ለ) ከመጀመሪያውም  እውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ለማድረግ በሚያስችል ሂሳዊ አቀራረብ  (critical approach ) ሳይሆን   የለውጥ አራማጅ የምንላቸው የኢህአዴግ ፖለቲከኞችን በእንከን የለሽ (በማምለክ አይነት ) አቀባበል  እንደተቀበልን ሁሉ አሁንም በዚያው “ቃላችን ፀንተን” ሁሉን ነገር  ለእነርሱ ትተን አርፈን መቀመጥ ናቸው ።

የተሻለ ብለን እየሄድንበት ያለው ምርጫ  በአብዛኛው የሚያመዝነው ወደ  የመጀመሪያው (የኢህአዴ ጥልቅ ተሃድሶ ትሩፋት ምፅዕዋተኛ )  መሆኑ  በግልፅ የሚታይ ሃቅ ነው ። ግን  ጨርሶ  አይሻልም ። እንዲያውም እንዲህ አይነት የመፅዋችነትና የተመፅዋችነት የፖለቲካ አውድ (political arena) በአካሄዱ ሰብአዊና የዜግነት መብትን ወደ ታች የሚያወርድ ከመሆኑም በላይ ዘላቂነት ስለማይኖረው እየመላለሰ አስከፊ አዙሪት ውስጥ የሚዘፍቅ ነው  የሚሆነው   ።  ምክንያቱም በመጀመሪያ ደረጃ የህዝባዊ ትግሉ መነሻ ምክንያትና መዳረሻ ጨርሶ ይህ አልነበረም ። አሁንም አይደለም ። ነገም ሊሆን አይችልም ። በሁለተኛ ደረጃ በወሳኝነት ሳይሆን በአጃቢነት የሚገኝ ፍርፋሪ “በለጋሹ” ወገን ፈቃደኝነትና ወሳኝነት ላይ የተመሠረተ ስለሆነ በማነኛውም ምክንያትና ጊዜ ሊቆም (ሊቋረጥ) የሚችል በመሆኑ እራስን ከሰብአዊ ፍጡር በታች አዋራጅ (self-dehumanizing ) ነው  ።

ለዘመናት የተከፈለው ግዙፍና መሪር መስዋትነት ከንዲህ አይነቱ እጅግ የከፋና የከረፋ የፖለቲካ አዙሪት ለመውጣት ካልሆነ የተቀደሰ መስዋእትነቱ እንዴት ሊገለፅ ነው ?   ሁለቱም ምርጫዎች አስከፊዎች (እጅግ አስቀያሚዎች)  መሆናቸውን ሳይመሽና ነገር ይበልጥ ሳይበላሽ ተገንዝበን  ወደ የምንፈልገው (የምንመኘው) እውነተኛ ሥርዓተ ፖለቲካ የሚወስደንንና ጨርሶ አማራጭ የማይገኝለትን ምርጫ (ለመሠረታዊ የሥርዓት ለውጥ ትግልን )   ከጣልንበት አንስተን በፍጥነትና በጥራት መራመድ ይኖርብናል ።

ሩብ መቶ ክፍለ ዘመን የመከራና የውርደት ዋነኛ ምክንያት (ምንጭ) የሆነው ኢህአዴግ እንደ ሥርዓት ፈርሶ (ተወግዶ) ከወንጀለኛና ከአገር አጥፊ አክራሪነት ልክፍት አልላቀቅም ከሚል በስተቀር ያገባኛል የሚል ሁሉ ሰላማዊ በሆነና አግባብነት ባለው ተሳታፊነት በሚዘረጋ የመሸጋገሪያ መንግድ (transitional mechanism) አማካኝነት እውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆን አለበት ከሚለው መሠረታዊና ትክክለኛ ምርጫ (ጥያቄ) እየሸሸን ወይም እየተደበቅን ለምን እጅግ አስከፊ (አሳፋሪ) ከሆኑት ሁለቱ ምርጫዎች (dilemma) ውስጥ እንደተዘፈቅን ከባድ የፖለቲካ እንቆቅልሽ (serious political puzzle) ነው ።

በጋራ አገራዊ ራዕይና ስሜት በተገመደ ፣ ከቁጥጥር ውጭ በሆነ ብሶት ወለድ ስሜታዊነት ሳይሆን በማስተዋልና በምክንያታዊነት ላይ በተመሠረተ፣ በማይናወጥ የነፃነትና የፍትህ መርህ ላይ በቆመ፣ የጋራ መነሻውንና መድረሻውን   ጠንቅቆ በተረዳ እና የጋራ ስትራቴጅና የተግባር መርሃ ግብር ባለው የፖለቲካ አውድ (political arena) ያልተመራ ህዝባዊ እምቢተኝነት ምን ያህል የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ ሰለባ እንደሚሆን ለመረዳት ምንም አይነት የተለየ እውቀት ወይም የትንታኔ መድብል አይጠይቅም ። ዘመናትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ህዝብ የእለት ከእለት የሰቆቃና የውርደት ህይወት ሲነገርና ሲፃፍ ከኖረው በላይ ይናገራልና ።

እናም  ከሞት አፋፍ የተመለሰው ኢህአዴግ የበላይነቱን ከህወሃት ወደ ኦህዴድ/ኦዴፓ አዛውሮ ሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ሙሉ በፈፀመው እጅግ የከፋና የከረፉ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል (ኅጢአት) እንደተጨማለቀ ስሜትን የሚኮረኩሩ ዲስኩሮችን እየደሰኮረ (እየሰበከ) እና የለውጥ አዋላጅ የሚመስሉ እርምጃዎችን እዚያም እዚህም እያሳየ “በንስሃ የታጠብኩ የዴሞክራሲም ሆነ የአገር ህልውና ዋስትና እኔ ነኝና ተከተሉኝ” ቢል ከቶ ለምን ይገርመናል ? “አማላይ (ስሜት ኮርኳሪ) በሆነ አንደበት የምትሰብኩት ዴሞክራሲ፣ ሰላም ፣ፍቅርና ብልፅግና ሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ሙሉ የኖራችሁበትና በፖለቲካ ወለድ ወንጀል (ሃጢአት) የበከተው ሥርዓተ ኢህዴግ እንደ ሥርዓት (እንደ ገዥ ቡድንና እንደ መንግሥት) በሚዘውረው የፖለቲካ አውድ (political arena) ውስጥ ፈፅሞ እውን ሊሆን አይችልምና በአገራዊ ምክክር መላ እንፍጠርለት” የሚል የዴሞክራሲያዊ ሽግግር አርበኝነት በእጅጉ በተልፈሰፈሰበት ምሪር ሃቅ ውስጥ የኢህአዴ ፖለቲከኞች በተሃድሶ ስም ሌላ ሩብ መቶ ክፍለ ዘመን መንበረ ሥልጣን ላይ ለመቆየት ይጠቅማል የሚሉትን የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ ጨዋታ ከመጫወት ሌላ ምን እንዲያድርጉ ነው የምንጠብቀው?  

አውቆና አሳውቆ ፣ በማይናወጥ መርህ ላይ ቆሞና ለማስቆም አስችሎ ፣ መልካም የጋራ ራዕይን ሰንቆና አሰንቆ ፣   ተደራጅቶና አደራጅቶ ከመከራውና ከውርደቱ የሚገላግለው አማራጭ ሃይል (ድርጅት/ህብረት/ቅንጅት) ባልነበረበትና በሌለበት ሁኔታ ከየጎሳው/ከየመንደሩ ውጭ እንዳያስብ በሚያደርግ እጅግ የከፋ የፖለቲካ ድንቁርና  ( ህመም) ተሰቅዞ የተያዘው የዋህ የአገሬ ህዝብ  ኢህአዴግ እንደ ሥርዓት  ሳይወገድ  ከሚውሰዱ የጥገናዊ ለውጥ እርምጃዎች የምትገኘዋን  ምፅዋዕት  ደግፎና ተቀብሎ “ታሪካዊ ለውጥ  አመጣንልህ” ሲሉት “የነማቱሳላን እድሜ ይስጣችሁ” ቢል በእጅጉ ያሳዝን እንደሆነ እንጅ ከቶ ምን ይገርማል ? የለውጥ አራማጅ የምንላቸው የኢህአዴግ ፖለቲከኞችስ “አዎ!  እድሜ ይስጠን ፤ ምክንያቱም እንደ ሥርዓት ከፈረስን አገር ይፈርሳልና” በሚል የማስፈራሪያ (የማሸበሪያ) ፕሮፓጋንዳ እራሳቸውን ተሃድሶ (reform) በሚሉት ቆንጆ ማስመሰያ ነገር (cosmotic) ኳኩለው ለሌላ ሩብ መቶ ክፍለ ዘመን የመከራና የውርደት ህይወት ሊያመቻቹን ቢሞክሩ   ለምን ይገርመናል? “የምትሄዱበት መንገድ የነውረኞች ወይም የአፀያፊዎች መንግድ ነውና ወደ ህዝባዊ ትግሉ መነሻ ምክንያትና የታለመለት መዳረሻ  ተመለሱና በጋራ መክረን ወደ የጋራ ግብ የሚያደርሰንን መንገድ በጋራ ቀይሰን በጋራ ወደ ፊት የምንራመድበትን  መንገድ እናመቻች” የሚል ሃይል (ድርጅት/ህብረት/ቅንጅት) በሌለበት  በሸፍጥ የተለወሰ የተሃድሶ ትሩፋት ተመፅዋቾች በማድረግ ከዜግነት ብቻ ሳይሆን ከሰብአዊ ፍጡር በታች አድርገውን ለመቀጠል ቢሞክሩ ለምን ይገርመናል ? በዚህ አኳኋናችንስ እነርሱ ምን እንዲያደርጉ ነው የምንጠብቀው?

  1. የህዝባዊ ትግሉ ሂደት በኢህአዴግ ፖለቲከኞች የበላይነት እየተመራ የታለመለትን ግብ ጨርሶ ሊመታ እንደማይችል የኢትዮጵያን የፖለቲካ ታሪክና በተለይ ደግሞ በህገ መንግሥት ደረጃ ተደንግጎ ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በህዝብ ላይ የመከራና የውርደት ዶፍ ሲያወርድ የነበረውን የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ ሥርዓተ ፖለቲካ ከምር ለሚገነዘብ ዜጋ ከበቂ በላይ ግልፅና ግልፅ መሆን ነበረበት ። አሁንም ከስህተት ለሚማር አልመሸምና ግልፅ የነበረውን (የሆነውን) መሪር ስህተት ገንቢ በሆነ ፀፀት ተቀብሎ ወደ ትክክለኛው አስተሳሰብና አካሄድ የመመለሱ አስፈላጊነት ከቶ አማራጭ የለውም ።

“ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው” እንደሚባለው ከመቸውም ጊዜ የከፋ  የታሪክ ስህተት ውስጥ ተያይዘን ከመዘፈቃችን በፊት ጊዜን መሻማት ግድ ይለናል ።

እንደ ባለሥልጣን ፣ እንደ ግለሰብ ዜጋ ፣ በልዩ ልዩ ሙያና ፍላጎት እንደ ተደራጀ  ማህበረሰብ  እና በአጠቃላይ እንደ  የአንድ አገር ህዝብ በጊዜ (በወቅቱ) መሥራት ያለብንን ሳንሰራ በመቅረታችን አገርና ህዝብ ሲተራመስ “ምነው ምን ነካችሁ ? ስንባል ከደካማና  ሸፍጠኛ ፖለቲከኞቻቸን አንደበት እየነጠቅን “የለውጥ ሂደት የእዮብን ያህል ትእግሥትና  ረጅም ጊዜ ስለሚወስድ አዲስ ነገር አይደለም”  የሚል እጅግ አሰልችና አደንቋሪ ትርክት መተረኩ በብርቱ ተጠናውቶናል።

 

በልዩ ልዩ የውውይት መድረኮች ፣ በየነባሩ (traditional) እና በየማህበራዊ ሚዲያው (social media) አብዝቶ ሲስተጋባ የምንታዘበው ይህንኑ ከጠቅላላ እውነታ የሚነሳን ንድፈ ሃሳብ   ከድክመት ወይም ከአቅም በላይ ከሆነ ብቻ ሳይሆን ከሸፍጥና ከሴራ ፖለቲካ ጋር እያደበላለቁ   ለዘመናት በፖለቲካ ወለድ ወንጀል ተዘፍቀው ለኖሩ የኢህአዴግ ፖለቲከኞች ተልካሻ ምክንያት (clumsy excuse) የማቀበልን ክፉ ልማድ ነው ።  አያሌ ንፁሃን ዜጎች  ከገንዛ ቀያቸው ሲፈናቀሉና ለምድራአዊ ሲኦል ሲዳረጉ ብቻ ሳይሆን ኢህአዴግ ወለድ  የጎሳ/የዘር አጥነት  ፖለቲካ  ማንነትን  እየቆጠሩ እርስ በርሳቸው  ሲተራረዱ ቀድሞ መከላከሉ ቀርቶ  ከፖለቲከኞች ትእዛዝ አልደረሰኝም በሚል  የወገኑን ሰቆቃ በታዛቢነት ቆሞ   የሚመለከት የመከላከያና የፀጥታ ሃይል ነኝ ባይ ባለበት አገር ውስጥ “በለውጥ ሂደት የሚያጋጥምና ጊዜ የሚወስድ ነው” የሚል እጅግ የሚከረፋ ሰበብ መደርደር በንፁሃን ዜጎች መተኪያ የሌለው ህይወት ላይ መሳለቅ (መቀለድ) ነው ። ከዚህ የበለጠስ ፖለቲካ ወለድ ውርደትና ወንጀል የት አለ ?

 እንዲህ አይነቱ አገርን (ህዝብን) ለመግለፅ ወደ የሚያስቸግር የውርደት ቁልቁለት ይዞ እየወረደ ያለ የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ ይቆም ዘንድ በእውነተኛ የህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ አርበኝነት ከመታገል ይልቅ እንደ አሜባ እየተራባ በኢህአዴግ የተሃድሶ ተውኔት ውስጥ በረዳት ወይም በተባባሪ ተዋናይነት ተመድቦ ለመተወን የሚቋምጥ (የሚሽቀዳደም) የፖለቲካ ድርጅት/ፓርቲ ነኝ ባይ ባለበት የፖለቲካ አውድ (political arena) ውስጥ የኢህአዴግ ፖለቲከኞች ምን እንዲሆኑና ምን እንዲያደርጉ ነው የምንጠብቀው?

 

  1. በመላ አገሪቱ በርሃብ ጠኔ እየተመቱ ካሉ ሚሊዮኖች በተጨማሪ ኢህአዴግ የተከለው እጅግ እኩይ የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ ሥርዓተ ፖለቲካ ባስከተለው ጠንቅ ምክንያት ከመቸውም በባሰና እንደ ህዝብ በእጅጉ በሚያሸማቅቅ  ሁኔታ የሚሊዮኖች ንፁሃን ዜጎች ህይወት (ህልውና) ምስቅልቅሉ ከወጣና ብዙም ህይወት ከተቀጠፈ በኋላ እጅግ የሰለቸና በውሸት የተለወሰ የመግለጫ ድርሰት እየደረሱና እያስተጋቡ ፣ በየአዳራሹና በየአደባባዩ በእጅጉ የጠነዛ (እጅግ የሰለቸ) ዲስኩር እየደሰኮሩ ፣ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አዋልኩ የሚል ተውኔት መሰል (ውጤት የሌለው) የፖለቲካ ጨዋታ እየተጫወቱ “ችግሩ ከባድና የቆየ ስለሆነ በቀላሉ አይወገድም” በሚል ተልካሻ  ምክንያት  ( clumsy excuse) ለማሳመን መሞከር ህይወታቸው ምስቅልቅሉ በወጣ (እየወጣ ባለ)  ዜጎችና በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ህዝብ መከራና ውርደት ላይ መሳለቅ (መቀለድ) ነው ።

ከሩብ መቶ ክፍለ ዘመን የመከራና የውርደት አገዛዝ  በኋላ የእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጎህ ቀደደ ስንል  ተመልሰን እየተዘፈቅንበት ካለው ሸፍጠኛና ሴረኛ  የፖለቲካ  አዙሪት የሚያወጣንና ወደ  የጋራ ግብ የሚወስደን ትክክለኛው መንገድ    የእውነተኛ ዴሞክራሲ ፣ የሰላምና የጋራ ብልፅግና ጉዳይ ያገባናል የሚሉ የፖለቲካና የሲቭል ድርጅቶች  የሚመክሩበትና የጋራ የመፍትሄ ሃሳብ አምጠው  የሚወልዱበት  አገራዊ ጉባኤ  እንጅ በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የተጨማለቀው ኢህአዴግ በበላይነት የሚቆጣጠ ረው አካሄድ  አይደለም ።ሊሆንም አይችልም ።

 

ታዲያ ይህንን እጅግ መሠረታዊ ጥያቄ እርግፍ አርጎ ትቶ “መርታችሁ እንደምታሸጋግሩን መቶ በመቶ እናምናችኋለንና እናንተው እንደሚሆን አድርጉን” የሚልና እንደ አሜባ የተራባ ተፎካካሪ ተብየ የፖለቲካ ድርጅት ባለበት አገር በሸፍጥ ተወልደው በሸፍጥ ያጎለመሱ የኢህአዴግ ፖለቲከኞች ያንኑ የሸፍጥ ፖለቲካ በተሃድሶ ቀለም ቀባብተው ከማስኬድ በላይ ምን ያድርጉ ?

 

  1. አዎ! አያሌ ንፁሃን ዜጎች እጅግ ግዙፍና መሪር መስዋትነት የከፈሉት በጎሳ/በዘር ማንነት ላይ ተመሥርቶ መለያየትንና ጥላቻን እያጦዘ ህዝብን የመከራና የውርደት ቀንበር ተሸካሚ ያደረገው ህወሃት/ኢህአዴግ እንደ ሥርዓት መቀጠሉ አብቅቶለት እሱን እራሱን (ኢህአዴግ) ጨምሮ የአገር ጉዳይ ከምር ያገባናል የሚሉ የፖለቲካና የሲቭል ድርጅቶች ሁሉ በነፃነትና በእኩልነት የሚሳተፉበት  የሽግግር አግባብ እውን እንዲሆን እንጅ በፖለቲካ ወለድ ወንጀል ተዘፍቆ የኖረውን  ኢህአዴግን በተሃድሶ ስም ሸፋፍኖ እንደ ሥርዓት  ለማስቀጠል አልነበረም ።  መሆንም የለበትም !

ነገር ግን ያለመታደል ወይም የጧት እድል ሆኖብን ሳይሆን እንዲህ አይነቱን እጅግ የከፋና የከረፋ የፖለቲካ ጨዋታ አዙሪት ሰብሮ የሚወጣና አገርን (ህዝብን) ወደ እውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት ማሸጋገር የሚችል አማራጭ ሃይል ለመፍጠርና ለማጎልበት ባለመቻላችን የህወሃቱን ኢህአዴግ በተሃድሶ (reform) ቀለም   ቀባብቶ   በኦዴፓው ኢህአዴግ የማስኬድ አዙሪት ውስጥ   መግባታችንን በመሬት ላይ ካለው እውነታ በላይ የሚነግረን የለም።

ከዚህ መሪር ሃቅ ጋር በአግባቡና በዴሞክራሲያዊ አርበኝነት ተጋፍጦ እራሱን እየደጋገመ ከባድ ፈተና ውስጥ የሚዘፍቀንን የፖለቲካ አዙሪት ሰብሮ በመውጣት ታሪክ ከመሥራት ይልቅ እየተነሱ መውደቅን ልማድ ባደረገ የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ እውነተኛ ለውጥ እንዴት ከምኞት ሊያልፍ ይችላል ? የኢህአዴግ ፖለቲከኞችስ “ለውጥ ማለት በተአምራዊ   ፍጥነትና ጥራት እያስኬድነው ያለውነው ተሃድሷችን (reform) ነውና ሌላ የለውጥ ጥያቄ ማንሳት ፀረ-ለውጥነት ነው “በሚል አዋጅ ቢጤ ቢያውጁ ወይም ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ማስጠንቀቂያ አዘል ዲስኩር ቢደሰኩሩ ምን ይገርማል? ከዚህስ በላይ ምን እንዲያደርጉ ነው የምንጠብቀው  ? 

  1. ጠቅላይ ሚኒስትሩና ጓዶቻቸውም ጥራሳቸውን ነቅሎ ያሳደጋቸው ገዥ ቡድን (ኢህአዴግ) ሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ሙሉ በጥልቀት የተከለውንና በስፋት ያሠራጨውን የጎሳ/የዘር/የመንደር ፖለቲካ ማንነት መርዝ የመንፈሳዊውንና የገሃዱን ዓለም ታላላቅ መፃህፍት እያደባለቁ በመደስኮር (በመስበክ) ለማስወገድ ጨርሶ እንደ ማይቻል ከአንድ ዓመት በኋላም በቅጡ (ከምር) የተገነዘቡት አይመስልም ፤ ወይም ለመገንዘብ አልፈለጉም ።

ክርስቶስ የቁም ስቃይ ካደረሱበት በኋላም የሞትን ፅዋ በፀጋ የተቀበለው የነፃነት፣ የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የሰላምና የፍቅር እሴት (value) ከእንስሳት ሁሉ ተለይቶ ረቂቅ ማሰቢያ አእምሮና ብቁ አካል ለተሰጠው የሰው ልጅ ዋጋ የማይተመንለትን መስዋዕነት (priceless sacrifice) እስከመክፈል እንደሚያደርስ ሆኖና አድርጎ ሊያሳየን እንጅ መሰቀሉንና ስቃዩን እናምናለን በሚል ብቻ ከሞት በኋላ አለ ብለን የምናምነውን ህይወት እንድንወርስ አይመስለኝም ።

በእውነት ከተነጋገርን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ ሳይሆኑ የሃይማኖት መሪዎችና ሰባኪዎች ስቅለቱን ፣ ሞቱንና ትንሳኤውን አስመልክተው ያስተላለፉት መልእክት በመልእክትነቱ ትክክል ወይም ተገቢ ቢሆንም ከክርስቶስ የቃልና የተግባር ውህደት አንፃር ሲመዘን ግን ከባድ ፈተና ያለብን መሆኑን ነው የሚነግረን ።   ቃልና ተግባርን ትርጉም ባለው አኳኋን  የተዋሃዱበትን  የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ  እውን ለማድረግ  ያለብን ፈተና  በእጅጉ ከባድ ነው ። ይበልጥ የሚሳስበው ደግሞ ለውጥ መጣ በተባለ ቁጥር ፖለቲከኞች እና  የሃይማኖት መሪዎች ያልተገባ መተሻሸት ከሚያመጣው የተዛባ ግንኙነት ተምረው ያለመገኘታቸው ልክፍት ነው ። ልክፍቱም   የሚጀምረው ፖለቲከኛውም ሆነ የሃይማኖት መሪው (ሰባኪው) ህዝብን ከገባበት ሁለንተናዊ ቀውስ ነፃ ለማውጣት ቁልፍ በሆነው በእውነት ስለእውነትና በሞራል ልእልና አርአያነት ፀንቶ ካለመቆም  (ካለመገኘት) ደካማነት ወይም ውድቀት ነው ። ይህ ውድቀት በዚህ የነፃነትና የፍትህ ፍለጋ ወቅትም ግልፅና ግልፅ የሆነ እውነታ ነውና ለምን ተደፈርን በሚል ከማውገዝ ወይም ከመራገም ይልቅ  ተገቢውን እርምት ማድረጉ ነው የሚሻለው ።

በጎሳ/በዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ምክንያት የሚሊዮኖች ህይወት በገንዛ አገራቸውና ቀያቸው ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ምስቅልቅሉ ሲወጣ ሃላፊነቱን ለመወጣት የተሳነው ፖለቲከኛ  ስለስቅለቱና ስለ ትንሳኤው በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ አብዝቶ የመተረኩ (የመስበኩ) ጉዳይ ከእለታዊ የስሜት ማስተንፈሻነት  የሚያልፍ አይሆንም ።  ሚሊዮኖች ንፁሃን ዜጎች ታይቶ በማይታወቅ አኳኋን ከህፃናት ፣ አረጋውያንና አቅመ ደካማ ቤተሰቦቻቸው ጋር ለማያቋርጥ የቁም ሰቆቃ ሲዳረጉ በየሃይማኖቱ የስብሰባ አውድ ላይ እየተገኙ የሃይማኖት መሪዎችና ሰባኪዎች የሚያነበንቡትን ተግባር አልባ ስብከት  ለፖለቲካ ጨዋታ እንዲስማማ እያደረጉ መደስኮር በስሜታዊነት ወይም በልታይ ባይነት ከሚደረግ የአድናቆት ጭብጨባ የዘለለ ፋይዳ የለውም ።

ይህ አገላለፄ ብዙ አማኝ ወገኖቼን በእጅጉ እንደማይመቻቸው በሚገባ እረዳለሁ ። እንደ አጥባቂ ሳይሆን እንደ አንድ ተራ የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ባለኝ ግንዛቤ ግን ይህ ግልፅና ቀጥተኛ አስተያየቴ ሰዎችን እንጅ ፈጣሪን ያስቀይማል (ቅር ያሰኛል) የሚል እምነት የለኝም። እኛ የምናምነው ፈጣሪ እንዲህ አይነት እንደማይሆንም እምነቴ ነው። እናም በዚህ ረገድ ያለብንን የራሳችን ድክመት ከላይ ከገለፅኩበት አገላለፅ በተሻለ ለመግለፅ ብችል ደስ ባለኝ ። ነገር ግን እውነትን የመሸሺ ቦቅቧቃነት/ፍርሃት (cowardicliness) ስለሚሆን አላደረግሁትም ።

እጅግ የተሳከረና ሸፍጥ የተጠናወተው የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ ወደ እውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አያሸጋገረንምና  ሳይመሽ  (በጊዜ) መታረምና ወደ ትክክለኛው አስተሳሰብና አካሄድ መመለስ ያስፈልጋል  የሚለው ድምፅ እየሰለለ (እየኮሰመነ ) እና በአፃሩ ጠንካራ ወይም እስከመቃወም ሊሄድ የሚችል ሂስ መሰንዘር ለውጡን  ማደናቀፍ ነው የሚለው ድምፅ እያየለ  የመጣበትን  ሁኔታ በቅጡ አጢኖ ተገቢውን አቅጣጫ ማስያዝ ተገቢ ነው ።  ይህንን ሆኖና አድርጎ ለመገኘት ከተሳነን  የኢህአዴግ ፖለቲከኞች “ከእኛ ሌላ የአሸጋጋሪነት ዋስትና የለም “ ቢሉን ለምን ይገርመናል ? ከዚህ በላይስ ምን እዲያደርጉ ነበር የጠበቅነው የምንጠብቀውስ ?

  1. የሃይማኖት መሪዎች ቢሆኑም ክርስቶስ የቁም ስቃይ ከተቀበለበትና  የሞት ፅዋ ከተጎነጨበት አስተምህሮቱ አንፃር ሲታይ ውድቀታቸው ከፖለቲከኞች ቢከፋ እንጅ የተሻለ አልነበረም ። አይደለምም ።   እውነተኛውን የፈጣሪ (የክርስቶስ) ወይም የአላህ አስተምህሮትም አያሳይም ። ክርስቶስ በአብዛኛው  ያስተማረው በተመቻቸ አካባቢና የመሰብሰብሰቢያ ቦታ እየመረጠ ሳይሆን በወቅቱ በነበረው ፍፁማዊና ጨካኝ የአገዛዝ ሥርዓት (የነገሥታት ሥርዓት) መከራና ውርደት ወደ ተጎሳቆሉ ሰብአዊ ፍጡራን እየተጓዘ የአስተምህሮት ቃሉን ከድርጊት ጋር በማዋሃድ መሆኑን ለመረዳት የሃይማኖት ሊቅ መሆንን አይጠይቅም ።

ከሞት በኋላ ህይወት የመኖሩ ምስጢር ካልሆነ በስተቀር በምድር ላይ ያስተማረበት፣ በቁም ስቃይ የተቀበለበትና በመጨረሻም የሞት ፅዋ የተጎነጨበት ምስጢር ረቂቅ ሳይሆን የሚጨበጥና የሚዳሰስ የህይወት አካል ነው ። ሰብአዊ ክብር፧ ፍትህ ፣ሰላም፣ ፍቅር ፣ እውነት ፣ ታማኘነት ፣ ፅዕናት ፣ ቅንነትና  ሌሎችም ታላላቅ በጎ ሥራዎች የዓለም ገዥ ባህሪያትና እሴቶች ሆነው እንዲዘልቁ ከተፈለገ የሚጠይቁት መስዋእትነት በዋጋ ሊተመን የማይችል (priceless) እንደሆነ ነው ሆኖና አድርጎ ያሳየን ። ለዚህ ነው የዘመኑን እኛነታችን ወደ ውስጥ ስንመረምረው ባዶነት የሚሰማን ። ለዚህ ነው የሃይማኖት መሪዎቻችንና ሰባኪዎቻችን በቃል ብቻ አትንገሩን ፥ ሆናችሁና ሠርታችሁም አሳዩን (SHOW US , DO NOT JUST TELL US! ) ማለት በሰማይም ሆነ በምድር ትክክል የሚሆነው ።   እውነቱን ለመናገር ሃይማኖታዊ ተልእኮአችንን  ከሚመጣውና ከሚሄደው ፖለቲከኛ ጋር በምንፈጥረው የመተሻሸት ግንኙነት እየለካን የምናስኬደው  ከሆነ የህዝብን መከራና ውርደት እናራዝማለን እንጅ አናሳጥረውም ። እየመረረን መቀበል ቢቸግረንም አሁንም እያጋጠመን ያለው ክፉ ልክፍት የሚመነጨው ከዚሁ እጅግ የተሳሳተ ወይም ሚዛኑን ከሳተ ግንኙነት ነው ።

 

በክፉው የጎሳ/የዘር/የመንደር  ፖለቲካ ሥርዓት ምክንያት በመለያየትና በመወጋገዝ አባዜ ውስጥ ተዘፍቀውና ከእርቀ-ሰላም እርቀው የቆዩ የሃይማኖት መሪዎች  እንደነበሩ የትናንት አስቀያሚ ትዝታ ነው። ታዲያ ያ ለጥላቻ እንጅ ለእርቅ የማይመቸው  የህወሃት/ኢህአዴግ ሥርዓት ከራሱ በወጡና  የለውጥ አራማጅ  በምንላቸው ፖለቲከኞች በአንፃራዊነት አደብ እንዲገዛ ሲደረግ   “ከእንግዴህ በቂ ማመካኛ የለንምና ፖለቲከኛም ሆነ አሸማጋይ ሳያስፈልገን በክርስቶስ አቀራራቢነትና ዳኝነት እኛው እራሳችን እርቀ ሰላም አውርደን መንፈሳዊና ምድራዊ ተልእኮአችንን እንውጣ” የሚል  የሃይማኖታዊ አርበኝነት ወኔ  የከዳቸው የሃይማኖት መሪዎች  የፖለቲከኞችን ጣልቃ ገብነት (አስታራቂነት)  ከሰማየ ሰማያት እንደተላከ ተአምራዊ ተልእኮ አድርገው ተቀበሉ ።

ይህን የምለው ለምን በፖለቲከኞች ታረቁ የሚል የድንቁርና ጥያቄ  ለመጠየቅ  አይደለም ። የክርስቶስን ተልእኮና መንፈስ እንደ ተሸከመ የሃይማኖት መሪ በራስ አነሳሽነትና አድራጊነት ይቅር አለመባባሉ የሚፈጥረው የስሜት መንገጫገጭ እንደተጠበቀ ሆኖ በምንም ይሁን በማን እርቀ ሰላም ማውረዱ ተገቢ ነው ።

ጥያቄው እንዲህ አይነቱ አካሄድ ሊፈጥረው የሚችለው (እየፈጠረ ያለው)  አላስፈላጊ (አስቀያሚ) ይሉኝታ ወይም መተሻሸት የለም ወይ? የሚለው ነው ።

እንደማነኛውም ሰብአዊ ፍጡር  በፈጣሪ አምሳል የተፈጠሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ  ንፁሃን ዜጎች የሃይማኖት መሪዎችን ባስታረቁ ፖለቲከኞች እጅግ ልኩን ያለፈ ድክመት (ውድቀት)፣ በሚመሩት ድርጅትና መንግሥታዊ መዋቅር ውስጥ በተሠማሩ ሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞች እና  የለውጥ አራማጅ  ቡድኑ ባለሥልጣናት ከውጭ እጃቸውን ስመው ባስገቧቸው የጎሳ/የዘር ፖለቲካ ልክፍተኞች ህይወታቸው ምስቅልቅሉ ከወጣ በርካታ ወራት ተቆጠሩ ።

ይህን የመሰለ በቃል መግለፅ የሚያስቸግርና አገራዊ ውርደት የሚያከናንብ ፖለቲካ ወለድ እብደት በዚህ ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ ምድር ላይ ሲፈፀም ማየትና መስማት እንኳን የክርስቶስን አደራ ለተሸከመ (ተሸክሚያለሁ ለሚል) ለማነኛውም ጤነኛ አእምሮ ላለው ዜጋ ወይም ሰብአዊ ፍጡር ህመሙ በእጅጉ ከባድ ነው ። በእውነት ስለእውነት ከተነጋገርን የሃይማኖት መሪዎቻችንና አስተማሪዎችን (ሰባኪዎቻችን) በዚህ ረገድ ያጋጠማቸው ውድቀት በጭራሽ ሊስተባበል የሚችል አይደለም ።  ከክርስቶስ የተሰጣት የህዝብ እረኝነት አደራ አለባት የምትባልን የሃይማኖት ተቋም (ቤተ እምነት) እመራለሁና ስለእሷም አስተምራለሁ የሚል የሃይማኖት መሪ ወይም አስተማሪ ወይም ባለ ሌላ ማእረግ አገልጋይ የፈጣሪን የሰው እኩልነት አስተምህሮ ጨርሶ በደረመሰ የጎሳ/የዘር/የቋንቋ ፖለቲካ እብደት የሚሊዮኖች ንፁሃን ዜጎች ህይወት በከፍተኛ ሰቆቃ ውስጥ ሲወድቅ ከምር ካልተቆጣና በተለይ ሃላፊነት ያለባቸውን ፖለቲከኞች (ባለሥልጣኖች) ያለምንም ይሉኝታና ፍርሃት ካልገሰፀ ሌላ ምን አይነት ታላቅ ተልእኮ ሊወጣ ይችላል ? እየመረረን ለመቀበል ብንቸገርም የማያወላዳው መሪር ሃቅ ይኸው ነው ።

 

ታዲያ እነዚህ የለውጥ አራማጅ የምንላቸው የኢህአዴግ ፖለቲከኞች እየሄዱበት ያለው የሸፍጥ ፖለቲካ (“አሸጋጋሪዎቻችሁ እኛና  እኛ ብቻ  ነን ፥ የእናንተ ሥራ መከተል/ማጀብ ነው”) ብለው በግልፅና በቀጥታ  ሲነግሩን “አዎንና አሜን !” ብለን በእነሱ በጎ ፈቃድ ሥር ሰንወድቅላቸው እነርሱ ምን ያድርጉ ?  አስተሳሰባችሁና አካሄዳችሁ  ግዙፍና መሪር መስዋዕትነት ለተከፈለበት የነፃነትና የፍትህ ትግል መሸጋገሪያና መዳረሻ በፍፁም የማይመጥን ነውና ቆም ብላችሁ በማሰብ ለሁሉም ወደ የሚበጀው የፖለቲካ አካሄድ ተመለሱ ብሎ የሚገስፅ የሃይማኖት መሪ ወይም አስተማሪ ብርቅየ እያሆነ በመጣባት አገር ውስጥ እውነተኛ የነፃነት ፣ የፍትህ ፣የአብሮነት ፣ የመከባበር፣ የፍቅር ፣ የሰላምና የጋራ ብልፅግና የፖለቲካ መሪዎችን ማፍራት እንዴት ይቻላል ?

  1. አሁን የምንገኘው በስሜት የመጋለብ ፣ የችግሮች ሁሉ ምንጭ ከሆነው ኢህአዴጋዊ ሥርዓት ይልቅ እርሱው በሚያስከትላቸው ክስተቶች ዙሪያ የመሽከርከር ፣  በየስብሰባ አዳራሹና በየአደባባዩ በመሬት ላይ ያለውን እጅግ አስከፊ ፈተና በአግባቡ ለመወጣት የማያስችል የፖለቲካ ቅኔ የመቀኘት ፣ አጋጣሚውን ተጠቅሞ የጎሳ/የዘር ፖለቲካ ንግዱን የማጧጧፍ ፖለቲካዊ አውድ ውስጥ  ነው።

እውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በኢህአዴጋዊያን አሸጋጋሪነት በፍፁም እውን አይሆንም ። የዴሞክራሲ ተፈጥሮና ባህሪ የሌለው የጎሳ/የዘር/የብሄረሰብ ፖለቲካ ድርጅትን አዴፓ እና ኦዴፓ እያሉ በመሰየም ዴሞክራሲያዊ ለማስመሰል መሞከር  በዴሞክራሲና ዴሞክራሲን አጥብቆ በሚናፍቅ ህዝብ መሳለቅ ነው የሚሆነው።

የእውነት ለውጥ የምንፈልግ ከሆነ አይናችን ያየውንና እያየ ያለውን ፣ ጆሯችን የሰማውንና እየሰማ ያለውን ፣ ህሊናችን ያስጨነቀውንና እያስጨነቀ ያለውን  መሪር እውነታ ለባለሥልጣኖቹ እና እኩይ ዓላማቸውን በጎሳ/በዘር/በመንደር ፖለቲካ ማንነት ጡዘት ( አክራሪነት) ለማሳካት ለሚቃዡ ፖለቲከኞች ነን ባዮች  ልንተወው ከቶ አንችልም ።  በመሆኑም  እንደ መልካም ዜጋ ብቻ ሳይሆን እንደ  ነፃነትና ፍትህ ናፋቂ ሰብአዊ ፍጡር  ወቅታዊና ውጤታማ  የጋራ እርብርብ ማድረግ ይኖርበታል ።

ወደ የጋራ ነፃነትና ብልፅግና በሚወስደን መንገድና ተግባር ላይ መደማመጥና በጋራ መረባረብ እስከ አልቻልን ድረስ የኢህአዴግ ፖለቲከኞች በተሃድሶ ስም እራሳቸውን አሸናፊ አድርጎ በማውጣት መሠረታዊ የሥርዓት ለውጥ ጥያቄን በፖለቲካ ወለድ ወንጀል በተጨማለቀ ሥርዓታቸው ሥር በሚካሄድ ጥገናዊ ለውጥ (reform) አማካኝነት በሚገኝ የፍርፋሪ ምፅዋዕት ቢያዳፍኑት ምን ይገርማል?  ከዚህ ሌላስ ምን እንዲያደርጉ እንጠብቃለን ?     

  1. ኢህአዴግ መንበረ ሥልጣኑን ለማስጠበቅ  ይጠቀምበት በነበረው የአፈና እና የግፍ እርምጃ መቀጠል እንደማይችል ጠንቅቆ ሲያውቅ  ከገባበት ቅርቃር የሚያወጣውን የተሃድሶ ትርክት ከምር በሚመስሉ  እርምጃዎች አጅቦ  የሸፍጥ ንስሃ እየተናዘዘ በድል አድራጊነት ለመውጣት የሄደበት መንገድ  መሠረታዊ ለሆነው የህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ምሥረታ ጥያቄ  ጨርሶ የሚመጥን አልነበረም ። አሁንም አይደለም ።ኢህአዴግ ህልውናውን ብቻ ሳይሆን መንበረ ሥልጣኑን እንዴት ማስቀጠል እንደሚችል በር እየዘጋ ዱላ ቀረሽ ክርክር (ውዝግብ) አድርጓል። ተቀዋሚ ነኝ የሚለው ፖለቲከኛ ግን ስለኢህአዴግ ሃጢአት፣ ውዝግብና መፈረካከስ ሲተርክ በአቋራጭ ኢህአዴግ ከሞት አፋፍ ነፍስ ዘርቶ ይኸውና የትግሉ ማእከል ከሆነው  የሥርዓት ለውጥ ጥያቄ እያንሸራተተን  የእሱን አሻሸጋጋሪነትን በተስፈኝነት እንድንጠባበቅ እያደረገን ነው ።

 

የለውጥ አራማጅ የምንላቸው የኢህአዴግ ፖለቲከኞችም ተያይዞ ከመውደቅ ይሻላል ያሉትን መንገድ መርጠው አያሌ መስዋዕትነት የተከፈለበትን የነፃነትና የፍትህ ፍለጋ ትግል በመሪነት የተቀላቀሉት የህወሃትን የበላይነት አስወግዶ በኦሆዴድ/ኦዴፓ የበላይነት በመተካት ኢህአዴግ ፈተናውን አልፎ በአሸናፊነት መውጣት የሚችል (survival of the fittest) የፖለቲካ ሃይል እንዲሆን ለማሰቻል እንደነበርና አሁንም እንደሆነ ማስረጃ የሚያስጠይቅ አይደለም ።።

ለምንና እንዴት? ብሎ ሳይሞግት   “እስረኛ መፍታታችሁ፣ እኛን ለዚህ  ማብቃታችሁ ፣ የህዋሃትን የበላይነት አስወግዳችሁ የእራሳችሁን የበላይነት መጎናፀፋችሁ ፣ ፍኖተ ካርታ አልባ ቢሆንም ለዘመናት ያልሰማነውን ፖለቲካዊና ታሪካዊ ቃለ ህይወት ማሰማታችሁ ፣ በምንና እና እንዴት እንደሆነ ባትነግሩንም ከጎረቤት አገር ጋር  እንደገና ፍቅር በፍቅር ስለአደረጋችሁን ፣ ተቃዋሚ በሚለው ምትክ “ተፎካካሪ”  የሚል አኩሪ ስያሜ ስለሰጣችሁን  ፣ ወዘተ  አምነንና  ታማኝ ሆነን  አሻጋጋሪነታችሁን በተስፋ እንጠብቃለን” የሚል ከመቶ በላይ የፖለቲካ ክለብ (ፓርቲ ማለት ያሳፍራል) ባለበት የፖለቲካ አውድ ውስጥ እውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዴት እውን ሊሆን ይችላል ?

የኢህአዴግ ፖለቲከኞች በዚህ እጅግ የወረደ የፖለቲካ አውድ (political arena) ውስጥ አሸናፊ ሆነው ለመውጣት የሚያስችላቸውን እርካሽ የፖለቲካ ጨዋታ ከመጫወት ሌላ ምን እንዲያደርጉ ነው የምንጠብቀው?

  1. ለማጠቃለል

የሥርዓት ለውጥ እውን የማድረጉ ፈተና ከመቅለል ይልቅ ይበልጥ እየከበደና እየተወሳሰበ መምጣቱ የሚያጠያይቅ አይደለም ። ያከበድነውና ያወሳሰብነው ግን  እኛው እራሳችን ነን ። እንደ ቅን አሳቢ ዜጋ፣ በልዩ ልዩ ሙያና ፍላጎት እንደ ተደራጀ የማህበረሰብ ክፍል ፣ እንደተማረና በመማር ላይ እንደሚገኝ ዜጋ  ፣ሃላፊነት እንደሚሰማው ባለሥልጣን እና በአጠቃላይ እንደ ህዝብ በዴሞክራሲያዊትና ሉአላዊት አገር ለመኖር በሚያስችሉ ቁልፍ ጉዳዮቻችን  ዙሪያ በጋራ መምከር ፣ በትእግሥት መደማመጥና የጋራ መፍትሄ እውን ማድረግ አለመቻላችን ነው ከባድና አላስፈላጊ መስዋእትነት እያስከፈለን እዚህ የደረስነው ።

ከሽዎች ዓመታት በፊት የሚግባቡበት ቋንቋ ድብልቅልቁ ወጥቶባቸው   ስለተቸገሩት ባቢሎናዊያን እየተረክን እኛም በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዚያው አይነት የመደነቋቆር አዙሪት ውስጥ ነው የምንገኘው ። እናም ወደ ውስጠ ህሊናችን ተመልሰን በገንቢ የፀፀትና የቁጭት መንፈስ ያለፈው ይብቃ ብለን ወደ ፊት ለመገሥገሥ ጊዜውን እንሻማ ። ለውጥ መጣ በተባለ ቁጥር በስሜት ፈረስን እየጋለብን ፖለቲከኞቻችን ያባለግናቸውና የምናባልጋቸው እኛው ነንና ቶሎ ብለን ከዚህ ክፉ ልማድ እንውጣ ።

የኢህአዴግ  ሥርዓት እንደ ሥርዓት በቀጠለበት እና  “አሸጋጋሪው እኔ ነኝና ተከተሉኝ (አጅቡኝ) “ በሚልበት የፖለቲካ አውድ ውስጥ እየገቡ መንቦጫረቅና ማንቦጫረቅ  ከእራስ የፖለቲካ ተሞክሮ አለመማር ነውና አሁንም መሽቶ ሳይጨልም የሚበጀውን ማድረግ ትክክለኛ የዴሞክራሲ አርበኝነት ነው ።

ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ያገባኛል የሚል ሁሉ የሚሳተፍበት ብሄራዊ የምክክር ጉባኤ በሚስማማበት የመፍትሄ ሃሳብ አማካኝነት በሚፈጠር የአካሄድ ወይም የአፈፃፀም ዘዴ (mechhanism) እንጅ በኢህአዴግ የበሰበሰ አመለካከት ፣ በሸፍጥና በሴራ ተፅፎና ፀድቆ የግፍ ማስፈፀሚያ በሆነ ህገ መንግሥት  እና በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የተጨማለቀ ባለሥልጣንና ካድሬ የድርጅትና የመንሥት መዋቅርን በተቆጣጠረበት ሁኔታ ውስጥ ፈፅሞ እውን ሊሆን አይችልም ።  ይህን በግልፅና በቀጥታ ለመናገር ፣ ለማነጋገር እና ለተግባራዊነቱም በፅናት ለመቆም ወኔ ማጣት ውደቀትን አስቀድሞ መቀበል ካልሆነ በስተቀር ሌላ ትርጉም አይኖረውም ።

 

የኢህአዴግ ፖለቲከኞችም “እኛ ነን አሸጋጋሪዎች” የሚለውን የበከተ የፖለቲካ ቀልድ ወይም ጨዋታ ተውትና ሁሉንም በሚያሳትፍ የመሸጋገሪያ መንገድ ወደ እውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለመሸጋገር በሚያስችል አኳኋን እራሳችሁን አዘጋጁ።  ይህን በማድረግ ነው ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ተዘፍቃችሁበት ከነበረው እጅግ አስከፊ  ፖለቲካ ወለድ ወንጀል (ኅጢአት)  መገላገልና ለቀሪ ህይወታችሁ አንፃራዊ ሰላም ማስገኘት የምትችሉት  ።

 

Previous Story

የሕብር ሬዲዮ ሚያዚያ 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ፕሮግራም

Next Story

በሳይንስና በፍልስፍና መነፅር መታየት ያለባቸውና መልስ የሚያስፈልጋቸው የብሄረሰብ፣ የጭቆናና የማንነት ጥያቄዎች !!

Latest from Blog

blank

ትግሉ ይጥራ – ከጥሩነህ ግርማ

የህልውና ትግሉን ወደሚቀጥለው ምዕራፍ ለማሸጋገር የኦይዶሎጂ ብዥታን ማጥራትና በመሬት ላይ ያለውን ተንኮል መጋፈጥና ማፅዳት ያስፈልጋል የህልውና ትግሉ በአማራ ብሄርተኝነት ላይ ያጠነጠነ እንደመሆኑ የመኖር አለዚያም እንደ ህዝብ  የመጥፋት ትግል ነው: ሌላው ኢትዮዽያዊ ወገን
blank

የፋሽስቱ አብይ አህመድ አሊ ኢትዮጵያ ውስጥ በአማራ ላይ እየተካሄደ ስለሚገኘው ጦርነት ከመስከረም 13 እስከ 27/2017 ዓ.ም በተለያዩ ቦታዎች ላይ የደረሰ የጉዳት !!!መረጃ:

ሸዋ በሸዋ ጠቅላይ ግዛት መርሀቤቴ አውራጃ በደራ ወረዳ ልዩ ስሙ ኮሉ በተባለ አካባቢ ላይ በሚገኙ የአማራ ተወላጆች ላይ አሸባሪው የሸኔ ቡድን ከኦሆዴዱ ጥምር ጦር ጋር ቅንጅት በመፈጠር መስከረም 22 ቀን 2017ዒ.ም ከለሊቱ
Go toTop