በአንድ ሀገር፣መንግሥት ዜጎች በህግ የሰጡትን ሥልጣን (ጉልበት ወይም ተመጣጣኝ ኃይል ) በአግባቡ ካልተጠቀመ አናርኪዚም እየተንሰራፋ ይሄዳል

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ
 መንግሥት ጉልበት አልባ የመሆን ዕጣ ፈንታ የለውም።መንግሥት የሀገርን ሠላምና ፀጥታ ለማስፈንና ለማስከበር ሲል ተመጣጣኝ የኃይል እርምጃ መጠቀም ይንሮበታል።
    ይህንን መንግስታዊ  ግዴታውን ሲወጣ እግረ መንገዱን ወንጀል በመስራት ተጠቃሚ ለመሆን ያኮበኮቡትን በሙሉ ወንጀል መስራት የሚያስከፍላቸውን ዋጋ በተጨባጭ በማሳየት የወንጀል ድርጊት እንዳይስፋፋ ያደርጋል ።
 የአንድ ሀገር ህዝብም ፣ፍትህ ለሁሉም እኩል መሆኗን፣ህጉ አድርግና አታድርግ ብሎ ያስቀመጠው፣የደነገገውና ያወጀው፣በእያንዳንዱ ዜጋ የሚተገበር፣የተፃፈና ያልተፃፈ ህግ ና  እስከ ህልፈተ ህይወት የሚዘልቅ የዘወትር በህብረተሰቡ የታወቀ የሞራል መመሪያ social norm እንዳለ ፣ማወቅ የሚችለውም፣ መንግስት ህዝብ የሰጠውን  ህልፍና በአግባቡ ተወጥቶት ሲመለከት ነው።
 (ህዝብ የምለው ፣ በተወሰኑ ግለሰቦች ቅስቀሳ ለሆዱ ተገዝቶ የማይጮኸውን ኩሩውን፣ በሚሊዮን የሚቆጠረውን ኢትዮጵያዊ ዜጋ በሙሉ እንደሆነ ይሰመርልኝ።)
      መንግሥት አንድ ዜጋ ወይም ሰው፣አብረውት፣የተፈጠሩና ከባህሪው የማይነጠሉ፣ወይም ሊነጠሉ የማይችሉ፣መብቶች እንዳሉት አሳምሮ ያውቃል።ከነዚህም መካከል ደስታን እና የደስታን ምንጭ እሥከህልፈተ ህይወቱ መሻት ነው።ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ከዚህ መብቱ በተጎዳኝ የሌላን ዜጋ መብት ፣በቡድን ተደራጅቶም ሆነ በግለሰብ ደረጃ የማደፍረስ ይቅርና “ጫፉን የመንካት”መብት እንደሌለበትም ለዜጎች ማሳወቅ የሚችሉው በህግ አግባብ ነው።
      ሰው፣በህይወት ሲኖር ፣ህይወቱን በደስታ የማኖር ተፈጥሯዊ መብት አለው ሥንል በመላው ኢትዮጵያ በጨረቃ ቤት እና በጎዳና ላይ የሚኖሩትንም ጭምር ሣንዘነጋ መሆኑን አሰምርበታለሁ።
      አለመታደል ሆኖ  በእኛ ሀገር ህይወትን በደስታ ለማኖር ያልቻልንበት ቀናቶች፣ወሮችና፣ዓመታት ይበዛሉ።የሰቋቃ ኑሯችንን ያባሰብን ዓመት ደግሞ የ27 ዓመቱ የኢሕአዴግ አገዛዝ ነው። (አሁን ያለው መንግሥት አብይ መራሽ የሽግግር መንግሥት እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ።)
    ሰውን የምናይበት ፍልሥፍና ቋንቋዊ ከሆነበት ከግንቦት 20/1983 ዓ/ም ጀምሮ
(ግንቦት 20 ታስቦ መዋል አለበት እንጂ ተከብሮ ሥራ የማይሰራበት ቀን መሆን የለበትም።ባለማወቅ ሰበብ በአዋቂዎቹ ምዕራባዊያንኑ ና በአሜሪካኖች  ሥውር እገዛ እንዲሁም፣ በተለያዩ ግላዊ ምክንያቶች የወቅቱን የኢትዮጵያ መንግሥት ከሥልጣን መወገድ የሚፈልጉ የወቅቱ የጎረቤትና አንዳንድ የአረብ መንግሥታት መሪዎች ድጋፍ፣ወንድም ወንድሙን ገድሎ ሥልጣን ሥለያዘ ወይም ቀኝ እጅ ግራ እጅን በመቁረጡ እንዴት ልናከብረው እንችላለን? የሚል ግላዊ አስተያየት አለኝ።ደሞስ መስከረም ሁለትን ሕወሀት ሰርዞት የለ?
       አንድ ለአምስት በመጠርነፍ ፣ግለሰባዊ ነፃነታችን ተደምስሶ በቡድን ነፃነት ተተክቶ፣ እንደእንሥሣ በጠመንጃቸው እያስፈራሩ ሲነዱን ኖረዋል።
    ጥቂቶቻችን፣ ሰው ለሆነው፣ለራሳችን የተለየ ምናልባትም የመለአክት መልክ ና ትርጉም እየሰጠን፣ቆዳችንን በማዋደድ ወደር በሌለው ግብዝነት እየተመፃደቅን ፣ እንድንኖር በፍርፋሪ እንደገዙን ጥቂት፣በጥቂት እየተገነዘብን መጥተናል።(ወያኔ ማረኝ።ደርግ ይግደለኝ የምንልም አለን።
     እንደትናትናዎቹ በዘመነ መሳፍንት ፣ባለማወቅ አረንቋ ውስጥ እንደነበሩ ፊውዳሎች፣” ጠጅ የመጠጣት መብት የእኛ ሆኖ ሳለ እንዴት ጠጅ እቤትህ ተገኘ ?” በማለትም ነፍሳችንን አስጨንቀዋታል።
   በእርግጥ ዛሬ ያ_አስጨናቂው ሕወሀት/ኢሕአዴግ በመንግሥት ከፍተኛው ሥልጣን ላይ የለም። በየክልሎቹ ግን በግለሰብ ጭንቅላት ወሰጥ አለ።
   በበኩሌ ዶ/ር አብይ የከፈቱት ቤት “27 ዓመት ሙሉ ተዘግቶ የቆየ ቢሆንም” (እሳቸው እዳሉት) ዛሬም ያ ቤት የሚከረፋው በሐጢያት የተጨማለቁ፣ሰዎችና ሰው፣ሰው የማይሸት አስተሳሰብ ያላቸው፣ ግለሰቦች፣በተከፈተው ቤት ፣ማለትም በዛሬዋ ኢትዮጵያ በየክልሉ ሁሉ ሥላሉ ይመሥለኛል።
   እነዚህ ሰዎች፣ዛሬም፣ በሥውር ( የኢትዮጵያን እድገት ብልጽግናዋን የማይፈልጉ ናቸውና) ፣ አንድ ወንድም በሌላው ወንድሙ ላይ ድንጋይ አንስቶ   “ቼበለው!”  እንዲል እየቀሰቀሱት ነው።
    ይህ ሀገር አናርኪዝም እያቆጠቆጠበት ነው።የነባኩኒን አስተሳሰብ፣ከሂትለር አመለካከት ጋር ፣በአደባባይ ሲራገብም፣እያስተዋልን ነው።
   እኔ በበኩሌ በኢትዮጵያ የሚስተዋለው ፣ፖለቲካዊ ግርግርና፣ውል አልባ ገመድ ጉተታ በእጅግ አስግቶኛል።
         እንሆ በማስተዋል መነፅር አተኩሬ ሥቃኝ፣በድፍን ሀገሬ፣ጥላቻ፣በጥላቻ፣ጎሠኝነት፣በጎሠኝነት፣ትምክህተኝነት፣በትምክህተኝነት፣ጠባብነት በጠባብነት፣ዘረኝነት በዘረኝነት…ሆዳምነት በባሰ ሆዳምነት፣የጎሣ ነጋዴነት፣በባሰ ጎሣ ነጋዴነት፣ሥሥታምነት በባሠ ሥሥታምነት፣በሥልጣን መባለግ፣በባሠ የሥልጣን መባለግ …አውሬነት፣በባሠ አውሬነት፣ሰው መሆንን መርሳት፣ በባሠ ሰው መሆንን መርሳት…ቀስ፣በቀስ እየተተካ ሲሄድ ይታየኛል።
     እውነት፣እውነት እላችኋለሁ፣የጠ/ሚር አብይ ፣በፍቅር፣ሥለፍቅር፣ሰው መሆንን ብቻ በማመን፣ የመደመር እና በአንድ ልብ የማሳብ  ፍልስፍና በብዙዎቻችን ልብ ውስጥ በቅጡ አልሰረፀም።ምክንያቱም ጠፍሮ ከያዘን የወያኔ ዘራዊ እና ቋንቋዊ አስተሳሰብ ገና አልተላቀቅንምና ሉሲ ወይም ድንቅነሽ ፣ የሚሊዮን ዓመታት የሰውን ጥንታዊ አፈጣጠር ማሳወቂያ አፅሞን በየክልሉ በማዞር፣ ይቅርና፣ ሉሲ ራሷ በአፀደ ነፍስ፣ ከነ ልጅ ልጆ በአካል ብትከሰት እንኳ  የዘረኝነት፣ ቆዳችን አንድ ሆኖ ሣለ ቆዳችንን የማዋደድ አስተሳሰብና የተንሸዋረረ አመለካከት በቀላሉ የሚለቀን አይመስለኝም።
     በዚህ ሥር የሰደደ ቆዳን የማዋደድ ፍልሥፍና፣ጦስ እና ጥንቡሳስ ሰውየው፣እንደሙሴ  ክፉኛ እየተቸገሩ ነው።ለአፍታ ዞር ሲሉ፣ከምታዩት የበለጠ ተአምር አሳያችኋለሁ  ባዩ(ልክ እንደምን ልታዘዝ ድራማ) ሺ ሆኖ ይጠብቃቸዋል።
     እውነት፣እውነት እላችኋለሁ፣ጠ/ሚ አብይ አህመድ (ዶ/ር) እንደ  መንግሥት ጠንካራ  በትረ ሥልጣን ” ሊኖራቸው ይገባል። በተዘጋ ቤት ውስጥ ያሉትን የበሰበሱ እና በሙስና በሽታ የተያዙትን ፣ጠራርገው፣የማሶገድ ብቃት እንዳላቸው ለጠላትም ለወዳጅም ማሳየት መንግሥታዊ ኃላፊነታቸው ነው።
   በዘላቂነት የህዙብን ሰላም ለማስከበር ና  የሀገር ደህንነትን ለማረጋገጥ የህግ የበላይነት በተጨባጭ እንዲኖር የሚያሥችል አዲስ የአደረጃጀት ለውጥ በክልል ፖሊሶች ላይ ሊፈጥሩ ካልቻሉ ና እስካልፈጠሩ ጊዜ፣ ድረስ፣እንቅልፍን እንደገደሏት ይወቁ።
     ከ65 አመት በላይ ፣የሆናቸውና ዛሬም ከመቶ ሃምሳ ዓመት በፊት በነበሩ መጥፎ ትዝታዎች ወጣቶን ሙሾ አውራጅ በመሆን የሚያስለቅሱትን ና ትውልዱ ባልሰራው ሐጥያት ተጠያቂ እንዲሆን በብሉይ ህግ ለመዳኘት እየቃጡ ያሉትን ከድርጊታቸው ማስቆም ታሪክ የጣለብዋ መንግሥታዊ ሥራ  ነው። ዜጋ ሁሉ፣ በጎውን የኢትዮጵያ ታሪክ ፣በየደረጃው እንዲማር   ማደረግም ፣ለነገ የማያሳድሩት የቤት ሥራዎት ይመስለኛል። …..
   ከቆዳ ማዋደድ ያልዘለለ አስተሳሰብ ያላቸውን ተማሪዎች የሰው ልጅ፣ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ አመጣጡን ፣ከእምነት፣ከሣይንሥ እና ከፍልስፍና አንፃር ማሳወቅ ተገቢ ነው።ለምን ቢባል ፣ ስልቻ እና ቀንቀሎ ልዩነት እንደሌለው ካላወቀ ፣ሥለዜግነት በውል ሥለማይገነዘብ ፣አሁን በእኛ ሀገር ከሚታየው ኋላቀር እና የሆዳሞች ፖለቲካ ከቶም አይላቀቅምና።
         ሙሴ  ህዝቡን ከዚህ የፈጣሪ ሃይል እና ከሰው ሰራሹ ጣኦት አንዱን ምረጡ ብሎ፣ህዝቡን ከለየ  በኋላ የወረወረው የእግዛብሔርን ቃል የያዘው ፅላት፣ በጣኦቱእና በተከታዮቹ ላይ ያደረሰውን ታላቅ መቅሰፍት ህዝቡ አይቶ፣ ባለማወቅ የተነሰ ለጣኦቱ ይሰግድ የነበረው ሥህተቱን ከመቅሥፈት ተገነዘበ። በክስተቱ ወደ ልቦናው ተመለሰ።ጥፋቱንም በውል ተረዳ።…የኢትዮጵያ መንግሥትም ፣እውነትን በዚህ ዓይነት መንገድ ለማሳወቅ መቻል ይኖርበታል። በዚህ ዓይነት የመንግሥትን የህዝብና የሀገር አሌንታነት ማረጋገጥ ካልቻለ፣በኢትዮጵያ ላይ ያንዣንበበውን በሆዳዊነት፣በድሎታዊነት እና በስስታማዊነት እጅግ የተደራጀ አሥፈሪውን ሞት ያረገዘ  የዕልቂት ደመና ማስቆም ከቶም እንደማይችል ከወዲሁ  መገመት ነብይ አያሰኝም።
        ደግሞም ማኬቬሊ እንዳለው፣” ጉልበተኝነትን እና ሕጋዊነትን በውል ዳር ድንበራቸውን መገንዘብ እንጂ፣ጉልበት አልባ መሆን አያዋጣም።”
በምንድነው፣አሜሪካ ኃያል የተባለችው? መልሱ ከባድ አይደለም።በአሜሪካ በህግ ቀልድ የለም።ህግን ለማስከበር የሚችሉ፣ፖሊሶች፣አቃቢ ህጎች፣ፍርድ ቤቶች እንዲሁም፣በብር አፋቸውን መዝጋት የማይፈልጉ ጋዜጠኞች ሥላሉ ነው።
    በዚህ በቴክኖሎጂ እጅግ በዘመነ ዓለም ውስጥ ፣ህግን ለማስከበር ከመቼውም ጊዜ ይልቅ የዘመነ ፣የመከላከያ እና የፖሊሥ ኃይል ያስፈልገናል።ጉልበት አልባ መሆን ብዙ ርቀት አያዝጉዘንም።………………….……….
በአንድ ሉአላዊ ሀገር፣መንግሥት ዜጎች በህግ የሰጡትን ሥልጣን(ጉልበት ወይም ተመጣጣኝ ኃይል ) በአግባቡ ካልተጠቀመ አናርኪዚም እየተንሰራፋ ይሄዳል።”
ተጨማሪ ያንብቡ:  ቀኛዝማች አባ ናዳ፤ (ቀኛዝማች ድልነሣሁ ጠንፉ) የኢትዮጵያ ጀግናና ዲፕሎማት - ኪዳኔ ዓለማየሁ
Share