ጠቅላይ አቃቤ ህግ ‹‹በሁለት ቀናት ግርግር ከ412 ሚሊየን ብር በላይ ከባንኮች እና ከህዝቡ ላይ ተዘርፏል፡፡›› አለ
ጠቅላይ አቃቤ ህግ በቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ ኢሌ ላይ እና አብረዋቸው በእስር ላይ በሚገኙ 6 ሰዎች እና ባልተያዙ 46 ሰዎች ላይ በቀጣዩ ሳምንት ክስ እንደሚመሰርት ገለፀ፡፡
https://www.youtube.com/watch?v=RvScL9Cy1vM&t=1064s
በአቃቤ ህግ የተመራው ቡድን ከፌደራል ፖሊስና ብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት የተውጣጣ ባለሙያዎችን አካቶ ምርመራውን ሲያካሂድ የቆየ ሲሆን በክልሉ ከሃምሌ 28 አስከ 30 ባለው ቀን ብቻ ከባድ አመፅ ከተማ ውስጥ በማስነሳት የእምነት ቦታዎች እንዲቃጠሉ ተደርጓል፤ ዘርን መሰረት ባደረገ ሁኔታ አስገድዶ መድፈር ፤ አንገት መቅላት፤ እስከነ ነፍስ መቅበር፣ በጅምላ መቅበር፤ በእሳት ማቃጠል እና የመሳሰሉት አስከፊ ድርጊቶች መፈጸማቸውን መገንዘቡን አቃቤ ህግ አስረድቷል፡፡ ‹‹በዚህም የ58 ሰዎች ህይወት የጠፋ ሲሆን፥ 50 ሰዎች በጅምላ ተቀብረው ተገኝተዋል›› ያሉት የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ የሆኑት አቶ ዝናቡ ቱኑ ‹‹አርባ ሁለቱ አንድ ላይ፥ ስምንቱ ደግሞ ሌላ ቦታ አንድ ላይ ተቀብረው ተገኝተዋል። ሌሎች 200 ሰዎች በጅምላ ተቀብረው ቢገኙም የእርሱ ምርመራ ገና አልተጠናቀቀም›› ያሉ ሲሆን በግርግሩ ወቅትም ከ412 ሚሊየን ብር በላይ ከባንኮች እና ከህዝቡ ላይ መዘረፉንም ተናግረዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በዚህ ወንጀል ከተጠረጠሩት 46 ግለሰቦች ውስጥ የተያዙት ስድስት ብቻ መሆናቸውንና የተወሰኑት ከሀገር እንደወጡ፣ ሌሎቹ ደግሞ ያለመከሰስ መብት ያላቸው እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡ አቶ ዝናቡ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ወደ ጎረቤት ሀገራት የተሰደዱትን ለማስመጣት እና ተጠያቂ ለማድረግ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመው ያለ መከሰስ መብት ያቸውን ደግሞ ከክልሉ መንግስት ጋር በመነጋጋር ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡
ከጋዜጠኞች የቀድሞው የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋን በተመለከተ ለተጠየቁት ሲመልሱም ‹‹ካልተያዙ ሰዎች መካከል ያለመከሰስ መብት ያላቸው ናቸው፤ በመሆኑም ይህንን በተመለከተ ከክልሉ መንግስት ጋር እየሰራን ነው›› ብለዋል፡፡
ጌታቸው አሰፋ የትግራይ ክልልም ሆነ የፌዴራል ፓርላማ አባል አለመሆናቸውና በህግ የተሰጣቸው ያለመከሰስ መብት እንደሌላቸው ይታወቃል::