አቶ አብዱልራህማን መሀዲ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) መስራችና ዋና ጸሃፊ የሆኑት አቶ አብዱልራህማን መሀዲ ለመጀመሪያ ጊዜ ቃለምልልስ ሰጥተዋል፡፡
https://www.youtube.com/watch?v=ncwpPfdrV3E&t=991s
ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት በዚህ ቃለምልልስ ሲናገሩ ‹‹ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የፖለቲካ ምህዳሩን ከፍቶታል፡፡ አቋሙ እጅግ በጣም ቀና ነው፡፡ ለዚህም ነው አርበኞች ግንቦት ሰባትን፣ ኦነግን፣ ኦብነግን ሌሎችንም የተለያዩ ነጻ አውጪ ግንባሮችን እንዲገቡ ያደረገው፡፡›› ብለዋል፡፡ ጨምረውም ‹‹በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብና እያንዳንዳችንም እውነተኛ ዴሞክራሲን ለማምጣት ብዙ መስራት አለብን፡፡ ለውጥ ያመጡ እርምጃዎች መውሰዳቸውን እናምናለን፡፡ ይሄንን እንዲቀጥልበት እናበረታታለን፡፡›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ከአመታት በፊት በኦጋዴን የተገደሉትን ቻይናዊያን በተመለከተ በወቅቱ ኦብነግ ሀላፊነቱን እንደሚወስድ ይፋ አድርጎ የነበረ ሲሆን ይህን በተመለከተ የተጠየቁት አቶ አብዱልራህማን ሲመልሱ ‹‹እኛ ኃላፊነት የወሰድነው በአካባቢው ከኢትዮጵያ ሰራዊት ጋር ውጊያ ያደረግን መሆናችንን ነው፡፡ ቻይናዎቹን የገደልነው እኛ ነን ብለን ኃላፊነት አልወሰድንም፡፡ ስምንት ያህሉን ማርከናቸው ነበር፡፡ ውጊያው እንዳለቀ ለቀይ መስቀል አስረክበናቸዋል፡፡ በስፍራው የሁለቱ ሰራዊቶች ግጭት ነበር፡፡ በሁለቱም ወገን ጉዳት ደርሷል፡፡ በግጭት ወቅት ሲቪሎች የበለጠ ችግር ላይ ይወድቃሉ፡፡›› በማለት ተናግረዋል፡፡ ለግድያው ማን ሃላፊነት መውሰድ እንዳለበት ተጠይቀውም ‹‹በጦርነት ወቅት ሁልጊዜም ጉዳት ይደርሳል፡፡›› ካሉ በኋላ <<ብዙ ሲቪሎች ከአውሮፓ፤ ከአሜሪካ፤ ከቻይና በመንገድ ላይ የሚሰሩ አሉ፡፡ አጥቅተናቸው አናውቅም፡፡ ቻይናዎቹን ግን ማን እንደገደላቸው አናውቅም፡፡ ውጊያው ግን በሁለቱም ሰራዊት መካከል ነበር፡፡›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አቶ አብዱራህማን መሃዲ በዚሁ ቃለ ምልልስ <<የሱማሌ ሕዝብ አሁንም የተገለለ ነው፤ ሕገ መንግሥቱ ከተከበረ ግን መነጠል አያስፈልገንም›› በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በኦጋዴን ስላለው የነዳጅ ሃብት ክፍፍል ተጠይቀው <<እያንዳንዱ ክልል የራሱ ተፈጥሮ ሃብት ስላለው በአካባቢው የሚኖሩ ሕዝቦች በእነዚህ ሃብቶች ላይ መብት አላቸው፡፡ ሃብቱን ለመካፈል ግን በፌደራሉና ክልሉ መንግሥት መካከል ድርድር ያስፈልጋል፤ እኩል ድርሻም መኖር አለበት›› ሲሉ መልሰዋል፡፡ ኦብነግ አሁን ሠራዊት አለው ወይ ተብለው ለተጠየቁትም “አዎ፣ ሠራዊታችን በክልሉ ጸጥታ ሃይል ይካተታል” ብለዋል፡፡