የኦሮሞ አባገዳዎች በምእራብ ኦሮሚያ የሚታየውን አለመረጋጋት ለመፍታት ወደ ስፍራው ሊያቀኑ መሆኑን ገለፁ፡፡ አባገዳዎቹ በመጪው ሳምንት ከኦዲፒና ከኦነግ አመራሮች እንዲሁም ከአካባቢው ህዝብና ከኦነግ ሰራዊት ጋር በመምከር እርቅ እናወርዳለን ብለው ዛሬ ቃል ገብተዋል። ሀዩ ወይም መካሪ እየተባሉት የሚጠሩት ነባር አባገዳዎችም ሆኑ አዳዲስ ተተኪ አባገዳዎች በክልሉ የሚታየው ግጭት ‹‹በዚህ ወቅት ሊኖር የማይገባ ነው›› ካሉ በኋላ ‹‹አሁን ላይ እንደ ክልልና ሀገር ተያይዘን የምናድግበት እንጂ የምንጋጭበት መሆን የለበትም።›› ሲሉ ድርጊቱን ኮንነውታል::
በአለም እውቅና የተሰጠው የአባገዳ ስርአት ተጸንሶ የተወለደባት ኦሮሚያ ክልል በዚህ ሁኔታ ውስጥ መገኘቷ የሀገር ሽማግሌዎችንም ሆነ አባገዳውን አሳዝኗል። ‹‹አለመግባባቶች ካሉ እንኳን ገዳን የሚያክል መታላቅ ስርአት ይዘን መፍታት እየቻልን ጠብ መንጃን ምርጫ አድርገን መጓዝ ይብቃን›› በማለት አባገዳዎቹ ተናግረዋል፡፡ የገዳ ስርአት ዴሞክራሲያዊ ስርአት ሲሆን በሀገሪቱ ላይ አሁን የሚታየው ጭላንጭል ዴሞክራሲ ስርአቱ በመንግስት በኩልም መተርጎም መቻሉን የሚያሳይ ነው።
ተተኪ አባ ገዳዎች በበኩላቸው ‹‹በኛ ወቅት ይህ መሆኑ ከመንግስት ጋር በጋራ ለመስራት የበለጠ እድል የሚፈጥር ነው›› ብለዋል፡፡ ሀዩ ወይም መካሪ አባገዳዎች ግጭቱ በፍጥነት እንዲቆምና በሰላማዊ መንገድ ችግሮችን መፍታት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል። ይህ እንዲሆን መንግስት ብቻውን የሚወጣው አይደለምና የሀገር ሽማግሌዎች አባገዳና የሀይማኖት አባቶችም ማገዝ አለብን የሚል መልእክትን አስተላልፈዋል፡፡ ጨምረውም ‹‹ህዝቡም ሆነ የፖለቲካ ሰዎች ይህን ታሳቢ እንዲያደርጉ የሚያስችል ውይይትና አርቀ ሰላምን ለማውረድ ወደ ስፍራው እናቀናለን›› ብለዋል፡፡ በምእራብ ኦሮሚያ በሚኖራቸው ቆይታ ሰላም ሳናወረድ አንመለስም ያሉት አባገዳዎቹ፤ ለዚህ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የኦሮሞ ህዝብ አባገዳንም ሆነ ስርአቱን ሲያከብር ለየኖረና ወደ ፊትም የሚያከብረው በመሆኑ ችግሮቹን ተፈተው ሰላም ወርዶ እንደሚመለሱም እምነታቸውን ገልጸዋል።
https://www.youtube.com/watch?v=KcPKUXGZAys&t=28s