በመቀሌ የዳቦና የስንዴ እጥረት ተከስቷል

በአዲስ አበባ ዛሬ ለንባብ የበቃው አዲስ ማለዳ ጋዜጣ በመቀሌ የተከሰተውን የዳቦና የስንዴ እጥረት በተመለከተ ዝርዝር መረጃ አስነብቧል፡፡

 እንደጋዜጣው ከሆነ በትግራይ ዋና ከተማ መቀሌ የዳቦ እጥረት የተከሰተው ከስንዴ አቅርቦት ችግር ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ላለፉት ዘጠኝ አመታት በድጎማ መልክ ወደክልሉ ይገባ የነበረው ስንዴ በመቋረጡ ችግሩ መፈጠሩን የትግራይ ክልል የከተማ ልማትና ንግድ ቢሮ ማስታወቁን ጋዜጣው አስረድቷል፡፡ የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ዳንኤል መኮንን ለአዲስ ማለዳ ጋዜጣ እንደተናገሩት በመቀሌ አንድ ብር ከሰላሳ ሳንቲም ሲሸጥ የነበረው መቶ ግራም ዳቦ ሁለት ብር ከሃምሳ ገብቷል፡፡ 

ይህም በእጥፍ መጨመሩን ያሳያል፡፡ እንደ አቶ ዳንኤል ገለፃ የከተማው ህዝብ በከፍተኛ የዳቦ እጥረት ችግር ውስጥ ሲሆን ስንዴም በኩንታል እስከ ሁለት ሺህ ሶስት መቶ ብር እየተሸጠ ነው፡፡ የቢሮው ምክትል ሃላፊ እንዳስረዱት ከፌዴራል መንግስት በድጎማ ይላክ የነበረው ስንዴ ለመቆሙ የተሰጠው ምክንያት ነቀዝ የበላው ስንዴ በመርከብ ስለገባና የግዢ ሂደቱ በመዘግየቱ ነው የሚል ቢሆንም ይህ ምላሽ እንዳላሳመናቸው ገልፀዋል፡፡

 ችግሩ ከሚያዚያ 2010 ጀምሮ ለተከታታይ ወራት መዝለቁን የተናገሩት አቶ ዳንኤል በኢትዮጵያና ኤርትራ በኩል ያለው ድንበር መከፈቱና ከተለያዩ አካባቢዎች የሚፈናቀሉ የክልሉ ተወላጆች መብዛት  የስንዴ አቅርቦቱን ማዳረስ አስቸጋሪ እንዳደረገውም አስረድተዋል፡፡ በመቀሌ በዱቄት አቅራቢነት የሚሰሩት አቶ ሃዱሽ ሃይሉ ለጋዜጣው ሲናገሩ ከጊዜ ወደጊዜ የሚቀርበው የስንዴ ምርት በማነሱ ምክንያት ለኪሳራ መዳረጋቸውን ገልፀዋል፡፡ 

ችግሩን ለመፍታት መንግስት በድጎማ የሚገባውን ስንዴ በአግባቡ ማከፋፈል እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ምርቱን ወደክልሉ ለማስገባት የትራንስፖርት ችግር መፈጠሩም እንደምክንያት ይነሳል፡፡ 

ተጨማሪ ያንብቡ:  “ኦነግ ሸኔ” ከተራ አባል አንስቶ እስከ ከፍተኛ መንግስት ባለስልጣን ድረስ “የሰርጎ ገብ አደረጃጀት አለው” ኢዜማ

በተያያዘ በመቀሌ አጋጥሞ የነበረው የጤፍ እጥረት መቃለሉን የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ቢገልፅም አንድ እንጀራ እስከ ሰባት ብር በከተማው እየተሸጠ መሆኑን ጋዜጣው አስረድቷል፡፡

2 Comments

  1. ችግር የለም ሱዳን ጤፍ በሽ ነው:: እድሜ ለሱዳን ስንዴም ይመጣል:: ቡናም ሽግር አይኖርም ብለውናል::
    ዳቦ ሞቶ ቢሸጥም ችግር አይኖርም:: ብቻ ህገመንግስቲ ይከበርልን:: ህጋዊ ገዳዮቻችንና ዘራፊዎቻችንን ህገ መንግስታችን ለፍርድ
    ማቅረብ የለበትም:: ሀጎስ ነኝ ከመቕለ

  2. ትግራይ ለዘላለም በመንግስት ሰንዴ በድጎማ እንድንኖር ህገ መንግስት አዝዋል:: ህገ መንግስቱ ይከበር!!!

Comments are closed.

Share