በምዕራብ ወለጋ የተለያዩ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎች ተካሄዱ

በቤኒሻንጉል ጉምዝና በኦሮሚያ አዋሳኝ ወረዳዎች ሰሞኑን በታጣቂዎች የተገደሉ የኦሮሚያ ፖሊስ አባላትን የሚዘክሩ ሰልፎች ጊንቢንና ነጆን ጨምሮ በተለያዩ የምዕራብ ወለጋ ከተሞች ተደረጉ።

በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በተሳተፉበት በዚህ ሰልፍ ላይ ፖሊሶች እና ወታደሮችም ከነዩኒፍርማቸው ተሳትፈውበታል::

በኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አዋሳኝ ወረዳዎች በተደጋጋሚ ከሚፈጸመው ጥቃት ውጭ ሰሞኑን ብቻ ከ34 የማያንሱ የኦሮሚያ ፖሊስ እና ጥብቃዎች መገደላቸው ይታወሳል:: ይህን ተከትሎም ትናንት በአምቦ በነቀምትና በሌሎች ከተሞችም የሻማ ማብራትና ሟቾችን የሚዘክሩ ሰልፎች መካሄዳቸውን የዘገብን ሲሆን ዛሬ በጊምቢ; በነጆ እና በተለያዩ የም ዕራብ ወለጋ ከተሞች ሕዝቡ ሃዘኑን እና ቁጣውን በሰላማዊ መንገድ ለመግለጽ አደባባይ ወጥቷል:: ገዳዮች በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ ያሳሰበው ሰልፈኛው; በአካባቢው ያለውን ተደጋጋሚ ጥቃት እልባት ለመስጠት መንግስት የሚወስደውን ማናቸውንም እርምጃዎች እንደግፋለን ብለዋል::

በዶ/ር አብይ እና አቶ ለማ መገርሳ የሚመራው ኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ በአስቸኳይ ተሰብስቦ ባወጣው ቆጣ ያለ መግለጫ “ከመራራ እና እልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ አሁን በሀገሪቱ መታየት የጀመረውን የተስፋ ብርሃን ስልጣን ያለአግባብ ሲጠቀሙ የነበሩ እንዲሁም የኢኮኖሚ ዝርፊያ ሲያካሂዱ የነበሩና ይህ ጥቅማቸው ከእጃቸው የወጣ አካላት ትግሉን ወደ ኋላ ለመመለስ በሁሉም ስፍራዎች ግጭቶች እንዲከሰቱ በማድረግ በሰው ልጅ ላይ መፈፀም የሌለባቸው አሰቃቂ ወንጀሎች እንዲፈፀሙ በማድረግ እና ዜጎች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ በማድረግ የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ እየሰሩ ነው:: ይህ የመቃብር አፋፍ ላይ የደረሰው ህልማቸው ወደ መቃብር ይወርዳል እንጂ መቼም ቢሆን የኦሮሚያ ክልልን የብጥብጥ እና የጦርነት አውድማ አያደርጋትም” ብሏል::

“የዚህ የተደራጀ ወንጀል አላማም በጥቅሉ ሲታይ የኦሮሞ ልጆችን ደም በማፍሰስ ኦሮሚያን የጦር አውድማ በማድረግ አንድነታችንን በማፍረስ፤ በህዝብ እና በመንግስት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሻክር አድርገው ህዝብን ሀብት ለመዝረፍ እንዲሁም ህዝቡ ወደ ነፃነት የሚያደርገው ጉዞ እንዲደናቀፍ በማድረግ ለሌብነት፣ ለዝርፊያ እና የባርነት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ነው” ያለው ማዕከላዊ ኮሚቴው የገቡበት ገብተን ለፍርድ እናቀርባቸዋለን ሲል አስጠንቅቋቋል::

ተጨማሪ ያንብቡ:  በዜጎች ላይ የተፈጸሙ በደሎችን የሚያክም የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ

https://www.youtube.com/watch?v=cKOwRaexXZ4&t=4s

Share