ከማንነትና ከክልል አስተዳደር ጋር የሚነሱ ጥያቄዎችና በኃይል ለመፍታት መሞከር የተጀመረውን የለውጥ ሒደት ብቻ ሳይሆን፣ አገሪቱንም ጭምር አደጋ ላይ እንደሚጥል ተገለጸ

ከማንነትና ከክልል አስተዳደር ጋር የሚነሱ ጥያቄዎችና በኃይል ለመፍታት መሞከር የተጀመረውን የለውጥ ሒደት ብቻ ሳይሆን፣ አገሪቱንም ጭምር አደጋ ላይ እንደሚጥል የቀድሞው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ኢታማዦር ሹም ጻድቃን ገብረትንሳኤ ገለጹ:: ጀነራሉ ይህን ያሉት በ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) በሳምንቱ መጨረሻ ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት አጠቃላይ ፖለቲከዊ ሁኔታ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ምን መደረግ አለበት በሚል አጀንዳ ላይ በተደረገ የምክክር መደረክ ላይ ነው::

በመድረኩ ላይ ንግግር ያቀረቡት ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ በሦስት ዋነኛ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡

እሳቸው የተጀመረው የለውጥ ሒደት የታለመለትን ግብ ያሳካ ዘንድ፣ ‹‹በዋነኛነት ከየት ተነስተን የት እንደርሳለን?›› እንዴት እንደርሳለን የሚል ግልጽ የሆነ የፖለቲካ ፍኖተ ካርታ ለውጡን ተፈጻሚ ለማድረግ የመጀመርያው ቅድመ ሁኔታ መሆን እንደሚኖርበት ነው፡፡

የተጀመረውን የለውጥ ሒደት በቅጡ ለመምራት ይቻል ዘንድ ግልጽ የሆነ፣ እንዲሁም ትዕግሥት የተላበሰ የለውጥ አስተዳደር (Reform Management) ሊኖር እንደሚገባ፣ የዚህም መኖር ለውጡን በአግባቡ ለማስተዳደር ዓይነተኛ ሚና የሚጫወት መሆኑን፣ ይህም የፖለቲካው ፍኖተ ካርታ አካል በመሆን ለውጡ የታለመለትን የሕዝቦችን ተጠቃሚነትና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታን ማፋጠን፣ እንዲሁም ለውጡን ዘለቄታዊ ለማድረግ ይረዳል የሚል አተያይ እንዳላቸው አመላክተዋል፡፡

ጄኔራሉ በሁለተኛነት ያነሱት ሐሳብ ደግሞ በቅርቡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እያቆጠቆጡ የሚገኙና የዜጎችን ሕይወትና ንብረት እየነጠቁ ያሉ የማንት ጥያቄዎችን እንዴት መፍታት ይቻላል? የሚለው ነጥብ ላይ በማተኮር፣ ለውጡን ወደ ታለመለት ግብ ማድረስ እንደሚቻል እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ አንፃር ከማንነትና ከክልል አስተዳደር ጋር የሚነሱ ጥያቄዎችን በኃይል ለመመለስ መሞከር? ወይስ ሕገ መንግሥቱን መሠረት ባደረገ መንገድ በሰላማዊ መንገድ መፍታት? የሚለው አጽንኦት ተሰጥቶት ሊታይ እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡ ለውጡ የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ የማንነትና የክልል ጥያቄዎች በሕገ መንግሥቱ መሠረት መፍታት ከምንም በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  (ሰበር ዜና) የሚኒሶታው ደብረሰላም መድሃኔዓለም ቤ/ክ በገለልተኛነቱ እንዲቀጥል የሚፈልገው ወገን አሸነፈ

በማከልም፣ ‹‹ከማንነትና ከክልል አስተዳደር ጋር የሚነሱ ጥያቄዎችና በኃይል ለመፍታት መሞከር የተጀመረውን የለውጥ ሒደት ብቻ ሳይሆን፣ አገሪቱንም ጭምር አደጋ ላይ ይጥላል፡፡ በኃይል የሚደረግ አማራጭ አደገኛ ነው፤›› በማለት፣ ጉዳዩን በሕገ መንግሥቱ መሠረትና በሰከነ መንገድ በሰላማዊ የውይይት መድረኮች ለመፍታት መሞከር፣ ለአገሪቱም ለተጀመረው ለውጥም ቀጣይነት አስፈላጊ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡

በሦስተኛነት ለውጡን ተፈጻሚ ለማድረግ አስፈላጊው ነጥብ ደግሞ የሽግግር ፍትሕ (Transitional Justice) ጉዳይ ሲሆን፣ ለውጡን ተከትለው በመጡት ሥራዎችና አካሄዶች እየተወሰዱ ያሉ ዕርምጃዎች የተመረጡ (Selective) እንዳይሆኑ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በዚህም መሠረት የሚወሰዱ የፍትሕ ዕርምጃዎች በግልጽነት የሚከናወኑ ሊሆኑ እንደሚገባ በማስገንዘብ፣ ተመርጬ ጥቃት ደርሶብኛል የሚል ነገር እንዳይፈጠር ውሳኔዎቹን ማጤን እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ይህንን ያሉበትን ምክንያትም ሲገልጹ ጉዳቱ መስመር ከሳተ የሚያዛባው የለውጡን ሒደት ብቻ ሳይሆን፣ የአገሪቱንም ህልውና አደጋ ውስጥ ሊከት የሚችል ነው ብለዋል፡፡
https://www.youtube.com/watch?v=_Ed6iA2v558&t=91s

1 Comment

Comments are closed.

Share