የአቶ በረከት ስም ዖን ኔትወርክ ፈረሰ

በአቶ በረከት ስምኦን የተመሰረተው ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሙሉ በሙሉ ፈረሰ፡፡  የፅ/ቤቱ ሰራተኞች ባለፈው ህዳር 12 ቀን 2011 የንብረት ርክክብ አከናውነዋል፡፡ አዲስ ዘይቤ ጋዜጣ ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው አቶ በረከት ስምኦን በሚኒስትር ማእረግ ይመሩት የነበረው ይህ መስሪያ ቤት እስከክልል የተዘረጋ መዋቅር ነበረው፡፡ 

እንዲሁም በየመንግስት መስሪያ ቤቱና ድርጅቶች ያሉ ኮሙኒኬሽን መዋቅሮችን በዳይሬክቶሬት ደረጃ የሚሾምና ፖለቲካዊ አቅጣጫ በመስጠት ለፕሮፓጋንዳ የሚያሰማራ ተቋም እንደነበር ጋዜጣው አስረድቷል፡፡ 

በዚህ መስሪያ ቤት አማካኝነት አቶ በረከት በ24 ሰአት ውስጥ በመላው ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ቀበሌዎች መፈክር አስፅፈው፣ ባነር አሳትመው፣ መሪ ቃል ሰይመው ትልቅ የድጋፍ ሰልፍ ማድረግ ይችሉ እንደነበር ታውቋል፡፡ 

በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ማለትም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣን፣ ኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣን፣ አል አለም የአረብኛ ጋዜጣን፣ በሪሳ አፋን ኦሮሞ ጋዜጣንና የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን በሙሉ አቶ በረከት በዚህ መስሪያ ቤት አማካኝነት አቅጣጫ ከመስጠትም አልፈው ይመሯቸው እንደነበር ተዘግቧል፡፡  

የ97ቱን ምርጫ ውጤት ተከትሎ በአቶ መለስ ትእዛዝ የአገሪቱን መረጃ አፍኖ ለመቆጣጠር የተቋቋመው ይህ መስሪያ ቤት እቅዱ አገሪቱን በሙሉ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፕሮፖጋንዳ ማጥለቅለቅ ነበር፡፡ 

አቶ በረከት ከለቀቁ በኋላም በተለያዩ ከፍተኛ ባለስልጣናት ሲመራ ቆይቶ ባሳለፍነው ሳምንት መስሪያ ቤቱ ግብአተ መሬቱ እንደተፈፀመ ከዘገባው ለመረዳት ችለናል፡፡ በፅ/ቤቱ ይሰሩ የነበሩት 247 ሰራተኞች ወደተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ይበተናሉ ተብሏል፡፡

https://www.youtube.com/watch?v=Qd-gjrRllUA&t=385s

ተጨማሪ ያንብቡ:  "ሰሞኑን በጎንደር ማክሰኝት ከተማ በመንግስት ታጣቂዎች በንፁሃን ላይ የተወሰደው የከባድ መሳሪያ እርምጃ ለእኔ መንግስታዊ ሽብር ነው” ሲሉ የአማራ ፋኖ አንድነት በጎንደር ሰብሳቢ ሻለቃ ሰፈር መለስ

1 Comment

Comments are closed.

Share