ግብፅ የህዳሴው ግድብ ድርድሩ እንዲፋጠን ጠየቀች

ግብፅ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የሚደረገው ውይይት እንዲፋጠን እንደምትፈልግ ማስታወቋን አልሻረቅ አል አውሳት የተሰኘው የአገሪቱ ጋዜጣ ዘገበ፡፡ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሽኩሪ ለአፍሪካ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ አዲስ አበባ በተገኙበት ወቅት ይህን ማስታወቃቸውን ጋዜጣው አስረድቷል፡፡

ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያው አቻቸው አቶ ወርቅነህ ገበየሁ ጋር በአዲስ አበባ ተገናኝተው በግል ባደረጉት ውይይት የግብፅን አቋም እንደዳስረዱ የዘገበው ጋዜጣው ወደፊት ግድቡን በተመለከተ የሚደረገው ድርድር እንደከዚህ ቀደሙ የተንጓተተ ከመሆን ይልቅ እንዲፈጥን መጠየቃቸውን ገልጿል፡፡ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም ረቡእ እለት ባወጣው መግለጫ በአዲስ አበባ በተደረገው ውይይት ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች መታየታቸውን አስታውቋል፡፡ በግድቡ ውሃ አሞላል ዙሪያ የተነሳውን ውዝግብ ለመፍታት በግብፅ፣ በሱዳንና በኢትዮጵያ መሀከል ባለፈው ሚያዚያ ወር የሶስትዮሽ ድርድር መደረጉ ይታወሳል፡፡

ከድርድሩ በኋላ መከናወን ባለባቸው የድርድሩ አፈፃፀሞች ላይ መንጓተት እንደታየ በመመልከት ግብፅ ቅሬታ እንደተሰማት መናገሯ ነው የተዘገበው፡፡ የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አህመድ ሀፌዝ ለአልሻረቅ አል አውሳት ጋዜጣ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ጉዳዩን በጥቂት ቀናት ውስጥ እልባት እንደምትሰጠው ቃል ገብታለች፡፡ ሀፌዝ ሲናገሩም ‹‹የኢትዮጵያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሶስቱ አገራት መሀከል ያለው ድርድር እንዲቀጥል የሚያስፍል መፍትሄ በጥቂት ቀናት ውስጥ ይዛ ትመጣለች›› ማለታቸውን ጋዜጣው አስረድቷል፡፡

የግብፁ ፕሬዚደንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ባለፈው ወር በግድቡ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖረው ግንኙነት ለፖለቲካ ፍጆታ እንደማይውል ቃል መግባታቸውንም ጋዜጣው አውስቷል፡፡
https://www.youtube.com/watch?v=x9Np1L1BJWY

ተጨማሪ ያንብቡ:  የቫንኩቨር ኢትዮጵያዊያን ተደስተዋል - ቤተክርስቲያናቸው ቋሚ ቤተመቅደስ አግኝታለች
Share