November 8, 2018
6 mins read

ኦነግ እና መንግሥትን ለማግባባት ወደ ምዕራብ ኦሮሚያ ያቀኑት የሃገር ሽማግሌዎች ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ

(BBC) በምዕራብ ኦሮሚያ ያጋጠመውን የጸጥታ መደፍረስ በሽምግልና ለመፍታት ወደ ስፍራው አቅንተው የነበሩ የሃገር ሽማግሌዎች ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን ቢቢሲ ዘገበ::

ወደ ምዕራብ ኦሮሚያ ካቀኑት የሃገር ሽማግሌዎች መካከል አንዱ የሆኑት ኢንጂነር መስፍን አበበ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ነጋዴዎች፣ አባ ገዳዎች እና የሃይማኖት አባቶች ከልዑኩ ቡድን አባላት መካከል ይገኙበታል።
“አስቀድመን ከነቀምት፣ ጊምቢ እና ደምቢ ዶሎ ከተሞች ነዋሪዎች ጋር ውይይት አድርገናል” የሚሉት ኢንጂነር መስፍን የሃገር ሽማግሌዎቹ ከነዋሪዎች የተነሱላቸውን ጥያቄዎች እና አስተያየቶች አድምጠዋል።
ከዚያም ጊዳሚ ከሚገኝ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አመራሮች ጋር ውይይት መደረጉን ይናገራሉ። ”የውይይቱን ውጤት መንግሥት እና ኦነግ መግለጫ የሚሰጡበት ጉዳይ ስለሆነ እኔ በዚህ ላይ ሃሳቤን አልሰጥም” ብለዋል።
ኢንጅነር መስፍን ጨምረው እንደሚሉት ”ውይይቱ በአንድ ጊዜ የሚጠናቀቅ ሳይሆን በቀጣይነት ብዙ ወይይት ሊያስፈልግ ይችላል” ብለዋል።
”በጉዟችንም ሆነ በቆይታችን ምንም አይነት ችግር ሳይገጥመን በሰላም ደርሰን ተመልሰናል” ይላሉ ኢንጂነር መስፍን።
ሌለው የልዑኩ ቡድን አባል የሆኑት የታሪክ መሁሩ ሼክ ሃጂ ኢብራሚም ይገኙበታል። ሼክ ሐጂ እንዳሉት ከተለያዩ የከተማ ነዋሪዎች ጋር በተደረጉት ውይይቶች ላይ በርካታ የመብት ጥያቄዎች ተነስተዋል ብለዋል።
”መሰረተ ልማቶች እንዲገነቡ፣ የኦሮሞ ህዝብ መብት እንዲከበር፣ ኦሮሚያ ውስጥ የሚኖሩ የሌሎች ብሔሮች ተወላጆች መብቶች እንዲከበሩ ለመንግሥት መልዕክት አስተላልፉልን ሲሉ ጠይቀውናል” ሲሉ ሼክ ሐጂ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በምዕራብ ኦሮሚያ ከሚገኙ የኦነግ ወታደሮች እና አመራሮች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን የሚያስታውሱት ሼክ ሐጂ፤ ”ከፍተኛ አመራሮቻችን አዲስ አበባ ነው ያሉት፤ ከእነሱ ጋር መወያየት ይኖርባችኋል” የሚል ምላሽ ከኦነግ ወታደሮች እና አመራሮች እንደተሰጣቸው ይናገራሉ።
በተጨማሪም ‘የኦሮሞ ህዝብ መብት ለረዥም ዓመታት ሳይከበር ቆይቷል። የኦሮሞ መብት እንዲከበር እንሻለን። ይህንንም መናገር ያለበት እላይ ያሉት ከፍተኛ አመራሮቻችን ናቸው። ከእነሱ ጋር ተወያይታችሁ ከስምምነት መድረስ ትችላላችሁ” እንደተባሉ ሼክ ሐጂ ኢብራሂምም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
”ወደ ሃገር ውስጥ ሳንገባ በመሪዎቻችን እና በክልሉ ፕሬዚዳንት መካከል የተደረሰው ስምምነት ለምን ተግባራዊ አልተደረገም?” የሚል ጥያቄ በኦነግ ወታሮች መነሳቱን ሽማግሌዎቹ ገልፀዋል።
በሌላ በኩል የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ አድማሱ ዳምጠው ለክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሲናገሩ ወደ ምዕራብ ኦሮሚያ የሄዱት የሃገር ሽማግሌዎች ተደብድበው እና ተዘርፈው የሄዱበትም ዓላማ ሳይሳካ መመለሳቸውን ተናግረዋል።
በቄለም ወለጋ ዞን ከሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎች ፖሊስ ጣቢያዎች ውስጥ የጦር መሳሪያ ተዘርፏል የሚሉት አቶ አድማሱ፤ ከአንድ ሺህ በላይ ቀበሌዎች ውስጥ የመንግሥት አስተዳደር እንዲፈርስ ተደርጎ በሌላ ሥርዓት እየተደራጀ ነው ብለዋል።
ሼክ ሐጂ ኢብራሂም ግን ”የተደበደበም ሆነ የተዘረፈ ሰው አላየንም። በሰላም ሄደን በክብር ነው የተሸኘነው” ይላሉ።
”ከውይይታችን መረዳት እንደቻልነው ሁለቱም ወገኖች የሚፈልጉት ሰላም እንዲሰፍን ነው” የሚሉት ሼክ ሐጂ፤ ከጥቂት ቀናት በኋላም የኦነግ እና የመንግሥት ባለስልጣናትን አንድ ላይ በማምጣት እንደሚያወያዩ ተናግረዋል።

3 Comments

  1. ሽማግሌዎች ሆይ
    ስለ ሰላም አስባችሁ ላደረጋችሁት ሁሉ ምስጋና ይድረሳችሁ
    ኦነግ አዲስ አበባ ሲገባ ባያው የህዝብ ድጋፍ ሰክሯል፡፡ እረሱን በመቆለል ከህግ በላይ፣ በመንግስት ላይ መንግስት አድርጓል፡፡ ማንም ከህግ በላይ እንዳልሆነ መነገር ነበረበት፡፡ ለመሆኑ ስለትጥቅ መፍታት ለምን አልነገራችሁንም፣ ኦነግ እንደታጠቀ ነው ወይስ ትጥቅ ፈቶ የሰላም መስመርን መርቷል፡፡ መንግስት ዛሬ አገር እየመራ፣ ትጥቅ አልፈታም ብሎ ከነመሳሪያው ካለ አንድ ድርጅት ጋር ከተደራደረ መሞቱን አስመሰከረ፡፡
    የኦሮሞ ህዝብ መብት አልተከበረም ማለት ምን ማለት ነው፤ የየትኛው የኢትዮጵያ ህዝብ መብት አልተከበረም፡፡ እስከ ዛሬ ዜጋው በኦሮሚያ ክልል ሲሳደድ ሽማግሌ ተብዬዎች ለህዝቡ ሳይሆን ለአንድ የፖለቲካ ፓርቲ በማሰብ ሽምግልና የመጣችሁበት ምክንያት ያሳዝናል፡፡ እስከዛሬ ሰው ሲሞትና ሲፈናቀል የት ነበራችሁ ፡፡ ይህ አመጸኛ፣ ለህግ አልገዛም፣ አሰከመሳሪያዬ እቀጥላለሁ፤ ፓርቲ ሳልሆን መንግስት ነኝ የሚል ደንባራ ድርጅት ልኩን በህግ አግባብ ማግኘት አለበት፡፡ መንግስት ከዚህ በህግ አግባብ ልኩን ማሳየት አለበት፡፡ በኦኤንን ምን እየሰራ እንዳለ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እየታዘብ ነው፡፡ የ1984ቱን ቅሌት ዛሬም መድገም የፈለገ ይመስላል፡፡

  2. የሚያዋጣው መወያየት ነው:: ከግጭት የሚገኝ ትርፍ የለም:: ለህዝብ ስላምና ድህንነት
    እንዲሁም ልማት የፈለገውን ጊዜ ወስዶ የዶክተር ዐቢይ መንግስት በውይይት መፍትሄ እንዲያመጣ እመኛለሁ::
    ሽማግሌዎቹ በኦሮሚያ ያሉ ሌሎች ህዝቦችም መብት እንዲከበር ከአካባቢው ህዝብ ይህ ጥያቄ መምጣቱ የሚደነቅም ነው::
    አንድነት ሀይል ነው

  3. These shimagiles should know the real cause of this seemingly never ending fight.If anything this elderly people should tell Oromos that Meles Zenawi is evil and his words are void.Inly 1990’s Meles Zenawi told OLF that Oromos can ask for referendum if only OLF fights warfare for 30 years same as Shabiya fought warfare for 30 years before getting referendum. Ever since OLF has been counting the years since then,in early 2020’s OLF is expecting to hold referendum for Oromos.That is when Oromos expect to get what they patiently had been waiting for, according to word from Nekemt in early 2020’s referendum will be held otherwise Oromos will mobilize in full force and take over everywhere by forceOLF is making sure the fight continues for 30 years as the anti-Ethiopia Meles Zenawi encouraged OLF to do so.

Comments are closed.

92426
Previous Story

ዶ/ር አብይ ከከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ጋር ተወያዩ

92431
Next Story

ኢትዮጵያ ስለምታቋቁመው የባህር ሃይል ማብራሪያ ተሰጠ | ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ቤተመንግስት የሄዱት ወታደሮች ጉዳይም ተናገሩ

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop