ዶ/ር አብይ ከከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ጋር ተወያዩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዛሬው እለት ከክፍለ ጦር አዛዦች በላይ ካሉ ወታደራዊ አመራሮች ጋር በፅህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል። በዚሁ ውይይት ወቅት መከላከያ ሰራዊትን በሁሉም መስክ ብቁ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት በከፍተኛ ግለት እንደሚቀጥል አስታውቀው ይህም ከለውጡ ጊዜ ጀምሮ ሲካሄድ የነበረው ዘርፉን ዘመናዊ፣ ብቁ እና ውጤታማ ለማድረግ የሚከናወን ጥረት አካል መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በቅርቡ በተወሰኑ ወታደሮች የተከሰተው ከወታደራዊ ዲሲፕሊን ያፈነገጠ ድርጊትም እንደ መነሻ ተወድሷል ብለዋል።
በህገ መንግስቱ አንቀጽ 87/4 መሰረት ‹‹መከላከያ በማንኛውም ጊዜ ለህገ መንግስቱ ተገዢ ይሆናል›› በሚል በተለየ አፅንኦት መከላከያን ከህገ መንግስታዊ ስርዓት ጠባቂነትና ተገዢነት ጋር እንዳቆራኘው የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ላይ የሚፈሰው በጀትና የሚሰጠው ትኩረትም ይህንን ቃል ኪዳን መሰረት ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
በህገ መንግስቱ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ለግዳጅ ሲሰማራ በታጠቀው መሳሪያ ምክንያት ሀይል ቢኖረውም እርምጃው ቅቡልነትን በሚያረጋግጥ መልኩ በከፍተኛ ጥንቃቄ፣ የህግ ተገዥነትና የህዝብ ተቆርቋሪነት ስሜት ማከናወን እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአፅዕኖት ተናግረዋል።

ዶክተር አብይ ጨምረውም መከላከያ ሰራዊት ሀይል አለኝ ብሎ እርምጃ የማይወስድ ቢሆንም ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመጠበቅ ግን በተሰጠው ስልጣን በጥብቅ መመሪያ የተቃኘ፣ ሰላም ወዳድ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ይሁንታ የሚሰጡት ተግባራዊ መፍትሄ መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመዋል።

‹‹ባለፉት ሶስት ወራት መከላከያ በለውጥ ጎዳና ላይ ይገኛል›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ ለውጡም በህጋዊ ማዕቀፎች፣ በአደረጃጀት፣ በመፈፀም ብቃት እና በትጥቅ እንደሚገለፅ አመልክተዋል።

አዲሱ የመከላከያ ሰራዊት መቋቋሚያ አዋጅ የባህር ሀይል አደረጃጀትን አካቶ እንዲሁም ወደፊት የሳይበርና የህዋ/ስፔስ/ ምህዳሮችን ለማካተት በሚያስችል መልኩ መሻሻሉንም እንደጠቆሙ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅህፈት ቤት ካሰራጨው መረጃ ለመረዳት ችለናል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ፖሊስ የደብረማርቆስ ተማሪዎችን እያፈሰ እያሰረ ነው • ‹‹ኢህአዴግ አይገዛንም!›› ተማሪዎቹ

ዘመናዊው ዓውደ ውጊያ በሚጠይቃቸው አምስቱም ምህዳሮች ማለትም የምድር፣ ዓየር፣ ባህር፣ ሳይበርና ህዋ ዝግጁ የሆነ መከላከያ ሰራዊት ለመገንባት እንቅስቃሴ እንደተጀመረ ያወሱት ዶክተር አብይ የአሰራር መመሪያዎች እንዲዳብሩና ዘመናዊ ሰራዊት ሊኖረው በሚገባው ደረጃ እንዲሆኑ ከፍተኛ ጥረት መደረጉንም ነው ያነሱት።
በአደረጃጀት በኩል ከዚህ በፊት የነበረው አደረጃጀት በርካታ ማነቆዎች የነበሩት፣ የሲቪልና መከላከያ ቅንብርን በሚገባው ደረጃ ያላካተተ በመሆኑ ሰፊ ጥናት ተደርጎ አዲስ አደረጃጀት መፅደቁን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፋይናንስ አጠቃቀምና አወጣጥ ስርዓት ዘርፉ የሚጠይቀው ሚስጥራዊነት እንደተጠበቀ ሆኖ በግልፅ መመሪያዎች እንዲመራ የሚያስችል አሰራር ተዘርግቷልም ብለዋል።

መከላከያ በዘመናዊ ትጥቅ እንዲደራጅና ግዳጅ የመፈፀም ብቃቱ ከፍተኛ እንዲሆን የሚያስችሉ የተጠኑ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም በዛሬው ስብሰባ ገልፀዋል።
https://www.youtube.com/watch?v=nOka95WpYt4

Share