May 3, 2018
39 mins read

ከታሪክ ማህደር – አገሬ አዲስ

ተቀምጠው የሰቀሉት ቆመው ለማውረድ ያዳግታል!

ሚያዝያ 24 ቀን 2010ዓም(02-05-2018)

በቀላሉ ተመልክተውና ገምተው፣ማንነቱንና ፍላጎቱን ሳያጤኑ በአንዳንድ ንክኪና መመሳሰል ምክንያት መሪ እንዲሆን ፈቅደው የተቀበሉት ግለሰብ ወይም ቡድን እያደር ሲያዩት ይሆናል ብለው ከጠበቁት ግምትና ተስፋ ሊያፈገፍግ ፣ብሎም አምኖ የተከተለውን ህዝብ ከማይጠበቅ አደጋ ውስጥ ሊከት እንደሚችል በተለያዩ አገሮች የታሪክ ጉዞ ታይቷል።

በጎሳና በነገድ ተከፋፍሎ በእርስ በርስ እልቂት መከራ ውስጥ ማለፍ ለዓለም ሕዝብ እንግዳ አይደለም።በተለያዩ አገሮች ተመሳሳይ ችግር ተከስቶ ለአገር መፈራረስና ለሕዝብ እልቂት ምክንያት ሆኗል።የጀርመንን መሪ የሂትለርን አነሳስና ያደረሰውን ጉዳት ወደ ጎን ትተን በቅርቡ እኛው በህይወት ዘመናችን የታዘብናቸውን አገሮች ታሪክ ብንመለከት በሶማሊያ፣በሩዋንዳ፣በብሩንዲ፣በዩጎዝላቪያ…ወዘተ የደረሰው ቀውስና የሕዝብ እልቂት ብሎም አገር የመፈራረስ ሂደት ጎሰኞች ያመጡት መዘዝ ውጤት መሆኑን አንዘነጋውም።

አገራችን ኢትዮጵያም በተመሳሳይ የታሪክ ጉዞ ውስጥ አልፋለች።በመሪዎች የስልጣን ሽኩቻ ምክንያት የደረሰውን ጥፋትና ስብራት ብንመለከት እንዳይደገም ከበቂ በላይ ትምህርትና ምክር የሚሰጡ ታሪኮች አሉን።በዘመነ መሳፍንት ጊዜ በተከሰተው የስልጣን ሽኩቻና ውድድር የአገር ቅርስ ወድሟል፣ቁጥሩ ይህ ነው የማይባል ሕዝብ አልቋል፣ተሰዷል፣ተፈናቅሏል፣አካለስንኩል ሆኗል፣ለውጭ ሃይል ሰርጎ ገቦች በር ከፍቷል።ከሃያ ሰባት ዓመት ወዲህ የተፈጠረውም የጎሰኞች ስርዓት ኢትዮጵያ አገራችን ብዙ የህይወት ዋጋ ተከፍሎበት የተገነባ አንድነቷን በመቦርቦር ለወደፊቱ ለመበታተን መንደርደሪያ ለሚሆነው አሁን ላለችበት ደረጃ እንድትበቃ አድርጓታል።

አገራችን ባለፉት አርባ አምስት ዓመታት በሁለት የአምባ ገነን ስርዓቶች ስትደቅ ኖራለች፤አሁንም እየኖረች ነው።

አምባ ገነን መሪዎች ስልጣን ላይ ለመውጣት ከሚጠቀሙበት መንገዶች ዋናዎቹ

1 በባዶ ዲስኩር፣የተስፋ መና እየመገቡ፣ስሜቱን እየቀሰቀሱ ሕዝብን ማማለልና ተከታይ ማድረግ፣

2 በጦር ሃይል በማንበርከክ ወይም ግልበጣ(ኩዴታ)በማካሄድ፣በጎሳ እየሸነሸኑ እርስ በራሱ እያጋጩ ሃይሉን በማዳከም የስልጣኑ ባለቤት መሆንና፣የስለላ መረብ ዘርግቶ ሕዝብን በፍርሃት ድባብ መቆጣጠር።

ባለፉት አርባ አምስት ዓመታት ያሳለፍነው፣የደርግና የወያኔ ስርዓት አመጣጥና የታሪክ ጉዞ በነዚህ በሁለቱ ሂደቶች ውስጥ የተጠናቀቀ ነው።የደርግን ስርዓት ብንመለከት፣መብቱ ባለመከበሩ፣ ኑሮው ከድጡ ወደማጡ እያሽቆለቆለ በመሄዱ ለውጥ እንዲመጣ የጠየቀው ሕዝብ ከዳር እስከዳር በአንድነት በተነሳበት ወቅት ጩኸቱንና ትግሉን በመንጠቅ አስመሳይ ዲስኩር በማሰማት በወታደሩ ስም ስልጣን ላይ የወጣው ቡድን ለአስራ ሰባት ዓመት የሰቆቃ ኑሮ እንደዳረገው ሁሉም ያውቀዋል። በኢትዮጵያ ትቅደም ባዶ ድንፋታ አገሪቱ የደም ገንዳ ሆና መተኪያ የሌላቸው ብዙ ምሁራንና ተስፋ የሰነቁ ወጣቶች ማለቃቸውን የሚክድ የለም። አንድ በበታችነት ስሜት ቂምና ምቀኝነት ያደረበትን፣ ከስምንተኛ ክፍል በላይ የትምህርት ደረጃ የሌለውን፣ ጨካኝ ሰው በባዶ ፉከራውና የመለፍለፍ ችሎታው ያለክብሩ ክብር፣ያለችሎታው ችሎታ ተሰጥቶት ያሻውን እንዲያደርግና በሃያ ሰባት ሚሊዮን ሕዝብ እጣ ፈንታ ላይ ብቸኛ ወሳኝ እንዲሆን መደረጉ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። የተማረ ሰው ከመጥላቱ የተነሳ በወታደራዊው መስክም ሳይቀር ከሱ በላይ እውቀትና ትምህርት የነበራቸውን የሐረር አካዳሚ ምሩቃን ከማሶገድ አልፎ ተቋሙንም እንደዘጋው ሁሉም ያውቀዋል። ከአፍሪካ የመጀመሪያና ለሌሎች አገሮችም ወታደራዊ ስልጠና ይሰጥ የነበረው ተቋም በቅናት መንፈስ እንዳልነበረ ሆነ።በአገሪቱም ላይ በመሰል ጨካኝ የሽብር ተባባሪዎቹ ድጋፍ ለአስራ ሰባት ዓመት የመከራ ዘመን ለማስፈን በቃ።በጣልያን ወረራ ከግራዚያኒ ወዲህ ኢትዮጵያዊ በአዋጅ(በቀይ ሽብር) የተጨፈጨፈበት ጊዜ ቢኖር የደርግ ዘመን የመጀመሪያው ጊዜ ነው። በዚያን ጊዜም በደርግ ውስጥ ሁለት የግራና የቀኝ ክንፍ አለው፣የግራውን እያጠናከሩ የቀኙን ማዳከም ይቻላል በሚል ፈሊጥ የአመለካከት ስህተት ነበር።ያም ለዘገናኙና ላሳፋሪው ታሪካችን ትልቅ ድርሻ ነበረው።አሁን ከአርባ ዓመት በዃላ መደገሙ ግን ያሳዝናል።

ከሃያ ሰባት ዓመት በፊትም ስልጣኑን በሃይል የነጠቀው ጎሰኛ ቡድን ጭቁንና ጨቋኝ በሚል ሽፋን የጎሳ ፖለቲካ በመርጨት የሕዝቡን ትስስር በመበጣጠስ፣ እርስ በርሱ እያጋጬ የአገር አንድነትን የማፈራረስ ተልእኮውን የሚያራምደው ለሕዝቡ ችግር መፍትሔ አመጣለሁ በሚል የተስፋ ስብከት በመንዛት ነው።እምቢ ያለውን ደግሞ ከመግደል ወደዃላ አላለም።በሚሊዮን የሚቆጠር ዜጋ ህይወቱን አጥቷል፣ተፈናቅሏል፣አካለጎደሎ ሆኗል፣በየእስር ቤቱ መከራውን አይቷል።አሁንም እያዬ ነው።እየተገደለና እየቆሰለ፣ እየተፈናቀለም ነው።ካለፈው ስህተትና መከራ ያልተማረው ወገን አሁንም በሚረጨው ፕሮፓጋንዳ ተማርኮ ሲያጨበጭብ ማዬት ከማስገረም አልፎ ያሳዝናል።የንቃተ ህሊና ደረጃውንም ያስገምታል።

ደርግ የተባለው የጨካኞች ቡድን በቀውስና በሕዝቡ ጥላቻና ተቃውሞ ሲወጠር፣ ሕዝቡን ለማታለል የወታደር ቆቡን በከረባት ቀይሮ ፣ከወታደራዊ አገዛዝ ወደ ኢሰፓነት(የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ) ለውጦ የስልጣን ዘመኑን ለማራዘም እንደሞከረው ሁሉ፣ ወያኔ የመሰረተው ስርዓት ለመንኮታኮት ሲዳዳው ፣ሕዝቡን የሚያማልልና ትጥቅ የሚያስፈታ ዘዴ ለመቀመር ተገደደ።ያም ዘዴ ለተሠራው ወንጀል ተጠያቂና ተካፋይ የሆነውን ግለሰብ አሽሞንሙኖ ወደፊት ማምጣትና በጠ/ምኒስትርነት መሾም ነው።

በጠቅላይ ሚኒስቴርነት ደረጃ አሁን በወሬና ለጆሮ በሚጥሙ ዲስኩሮች የተጠመደው ዶር/ኮሎኔል አብይ አህመድ በየቦታው እየሄደ የሕዝቡን ስሜት በሚነካ መልኩ ንግግር በማድረግ እንኳንስ ተራውን ሕዝብ ተማርኩ ፣የፖለቲካ ንቃት አለኝ፣ ተቃዋሚ ነኝ የሚለውን ወገን አቋሙን እያሽመደመደው መጥቷል። በዚህ መረብ ውስጥ የተጠመደው ወገን ዘወር ብሎ ከሃያ ሰባት ዓመት በፊት ያለፈበትን ታሪክ ለመመልክት አልቻለም።የደርግን ብሎም የዛን የገዳይ የመንግስቱን ዲስኩር ለማስታወስ አልሞከረም። ከዚያም ወዲህ የመለስንና የአብይን ድርጅታዊ ትስስር አላጤነም።በሚሰማው ዲስኩር ብቻ ናላው ዞሯል።ካለፈው ጥፋቱ አልተማረም።

ዶር /ኮሎኔል አብይ አህመድ የወያኔ መራሹ ኢሕአዴግ የተባለው የጎሳ ስብስብ ያሳደገው፣ አባልና ስርዓቱ ለፈጸመው ብዙ ወንጀል ተሳታፊና ተጠያቂ የሆነ ግለሰብ ነው።የስርዓቱ ተንከባካቢና ጠባቂ፣ተቃዋሚውን የሚያሳድድና የሚገል የደህንነት ተቋሙ መሪና አደራጅ የነበረ ሰው ነው። አሁን በሊቀ መንበርነት ለመምራትና ለማገልገል ምሎ የተነሳውም ያንኑ አገር አጥፊ የኢሕአዴግ ጎሰኛ ፖለቲካና ድርጅት ነው።አሁን በየቦታው እየሄደ የሚያሰማው ዲስኩር ማንነቱን ሊደብቅለትና ሊቀይረው አይችልም።

ኢትዮጵያ ብዙ ቋንቋና ባህል ያላቸው የአንድ አገር ዜጎች በህብረት የፈጠሯትና የሚኖሩባት አገር ነች።ለኢሕአዴግ አባላት ዶር/ኮሎኔል አብይን ጨምሮ አትዮጵያ ማለት አንድ ጎሳ ሌላውን እረግጦ በሃይል ሰብስቦ የያዘባት፣በወረራ የተፈጠረች አገር ነች።ስለዚህ በነጻነትና በእኩልነት ስም ሁሉም በየጎሳው የራሱን ክልልና መንግሥት ፈጥሮ በአንቀጽ 39 መሰረት መፈራረስ አለባት።ይህንን እምነትና አቋም በመቀበልም ነው የራሱ ጎሳ ድርጅት አባልና የአመራር አባል በመሆን ሲሰራ የኖረው።ይህንን አቋሙን ሳይለውጥ በሚናገረው ብቻ የለውጥ ሃዋርያ አድርጎ መቁጠርና ማጨብጨብ፣በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ መጥቷል እያሉ ተጭበርብሮ ማጭበርበር “ሊበሉ ያሰቧትን አሞራ ጅግራ ናት ይሏታል” የማለት ያህልና ለመጠጋጋት የሚቀርብ ሰንካላ ምክንያት እንጂ በማስረጃ የተደገፈ እውነት አይደለም።ዶር/ኮሎኔል አብይ አህመድ እንደሌሎቹ ትናንትም፣ዛሬም፣ነገም የኢሕአዴግ አባል ነው፤ከኢሕአዴግ አቋምም አያፈገፍግም።

የዶር/ኮሎኔል አብይን በአራት ኪሎ ቤተመንግሥት ውስጥ መግባት የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ የተመለሰለት አድርገውም የሚመለከቱ ብዙ ናቸው።የሃይለማርያም ደሳለኝ በዚያ ቦታ ለስድስት ዓመት በመቀመጡ ለደቡብ ሕዝብ የሰጠው ጥቅም የለም።የአብይም ለኦሮሞ ሕዝብ በስሙ ስልጣን ከመያዙ ባሻገር የሚሰጠው ጥቅም አይኖርም።ኦሮሞው የበላይነቱን አገኘ ብለው የሚደሰቱም ካሉ ማሰብ የሚኖርባቸው ከአሁን በዃላ በጎሳ ፖለቲካ አንዱ ጎሳ በሌላው ጎሳ ስር የማይተዳደርበት ጊዜ መሆኑን ነው።ሁሉም ሕዝብ እንደልማዱ በድህነት ቀንበር ውስጥ ከመኖሩ በተረፈ የስርዓት ለውጥ ኖሮ በሰላም የሚኖርበትን ዕድል አይፈጥርለትም።አድራጊ ፈጣሪው የወያኔ ቡድንና እሱ አባል የሆነበት የኢሕአዴግ ድርጅት ነው።

ዶር ኮሎኔል አብይ አህመድ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንም ላይ ከአቦይ ስብሃትና ከመለስ በጥቅሉ ከኢሕአዴግ መሪዎች የተለዬ አመለካከትና አቋም የለውም።ከሃምሳ ዓመት ወዲህ በነጮች አማካኝነት ሰርጎ ገብቶ ለአገራችን አንድነትና ለሕዝቡ አብሮነት ጠንክ የሆነውን ኦነግ የተባለውን ጸረ ኢትዮጵያ የጎሳ ድርጅት ለመፍጠር ዋና ሚና የተጫወተው የፕሮቴስታንት(የጴንጤ) እምነት መሆኑ አይካድም። ዶር /ኮሎኔል አብይ አህመድ የዚሁ እምነት ተከታይ በመሆኑ ሊወቀስ አይገባም፤መብቱ የተጠበቀ ነው።የዚህን እምነት መስፋፋት ሃምሳኛ ዓመት በዓል ምክንያት በማድረግ በተደረገው ድግስ ላይ ተገኝቶ ባደረገው ንግግር ላይ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃይማኖት ሳይኖረው የኖረ በሚመስል መልኩ የፕሮቴስታንቱን እምነት ሲያወድስ፣እግረ መንገዱንም ፕሮቴስታንት እንደመሆኑ ቃላት በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ላይ ያላቸውን ትችትና ንቀት በአደባባይ ደግሞታል።የእምነቱ ተከታዮች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአምላክን አስርቱ ቃላት( ትዕዛዝ) በጽላት (በታቦት) ላይ ቀርጻ ማኖርና ማክበሯን፣ለአማልክቱና ለቅዱሳን መታሰቢያ ቀን መድባ እንዲዘከሩ ማድረጓን፣ለተወለደ ጥምቀትን፣ለሞተ ፍታትንና ተዝካርን ማድረሷ፣በስጋዎ ደሙ ማቁረቧን፣በስርዓተ እምነት መመራቷን ፣በከበሮና በጽናጽን ታጅባ መዝሙረ ውዳሴ ማሰማቷን እንደ ኮተት ወይም ቅራቅንቦ ተሸካሚ አድርገው በዃላ ቀርነት ይወንጅሏታል።ይህንኑ ትችት ነበር ዶር አብይ “እግዚአብሔር የቅራቅንቦ አምላክ አይደለም” ሲል የተሰበሰበው የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ በጭብጨባው ከዳር እስከዳር ያስተጋባው።የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የዚህን የፕሮቴስታንት ሰርጎ መግባትና መስፋፋት፣ሊያስከትል የሚችለውንም ብሔራዊ አደጋ ቀድሞ በመረዳት ለመቋቋም ያደረገችውንም ትግል “የተከፈተው የአንበሳ መንጋጋ በአምላክ እርዳታ ባይከደን ኖሮ ይህንን በዓል ለማክበር አንበቃም ነበር” በማለት ከአውሬ ጋር የተደረገ ግብ ግብ አስመስሎ አቅርቦታል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለኢትዮጵያ አንድነት እንደ አንድ ወታደራዊ ተቋም በጦር ሜዳ ተሰልፋ የጸሎት ትግል ከማድረጓም በላይ ህዝቡ ከጠላት ጎን እንዳይሰለፍ በማስተማርና በመገዘት ለነጻነት ትግሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጋለች።ከዚያም በላይ ፊደልን ቀርጻና አስቆጥራ ከመሃይምነት ጨለማ ለማውጣት ግንባር ቀደም ሚና የተጫወተች፣ለታሪክና ለባህላችን መስተዋት ለአንድነታችን ገመድ የሆነች ባለውለታ ነች።በረሃና እርቀት ሳይገድባት ከዳር እስከ ዳር ተንቀሳቅሳ በስነምግባር አንጻ ከአውሬነት ወደ ሰብአዊነት አመለካከት ወንጌልን ሰብካ የመለሰች ባለውለታ ነች።እሷን ማዳከም ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የሚደረገውን ጥረት ያጠናክረዋል፣ያፋጥነዋልም ተብሎ ስለሚታመንበት ጠላቶች የሚረባረቡባት የመጀመሪያ ኢላማ ወረዳ ነች።ኢትዮጵያዊ ሙስሊሙም ለአገሩ አንድነት ብዙ ድርሻ ነበረው፣አሁንም አለው።እሱም የጥቃቱ ሰለባ ሆኗል።በሰርጎ ገብ የሙስሊም እምነት እየተበረዘና ያገር ወዳድነቱ መንፈስ እንዲላላ ወያኔ ሌት ተቀን የሚተጋበት ሆኗል። በሚያደርገው የመውሊድ፣ የአረፋ፣ሰደቃና ዘካ በጎ ምግባርና ድግስ እንደ ዃላ ቀር ተቆጥሮ በበኩሉ አፍራሽ ዘመቻ እየተካሄደበት ነው።እሱም ኮተታም ሳይባል እንደማይቀር እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል።በጴንጤዎች እምነት ከነሱ በላይ ለአምላክ የቀረበ፣ትክክለኛ እምነት አይኖርምና!

የፕሮቴስታንት እምነት አነሳሱ የካቶሊክን ወግ አጥባቂነት በመቃወም ለዘመናዊ ስርዓተ እምነት ለውጥ ለማምጣት ሆኖ ሳለ በኢትዮጵያ ግን አንድነቷን ለማናጋት የጥፋት መሳሪያ ሆኗል።የዚህ እምነት ተከታዮች እንክርዳዱን ከስንዴ የመለዬት አላፊነት አለባቸው።ከእምነቱ ጀርባ በኢትዮጵያ አገራቸው ላይ የሚካሄደውን ሴራ ሊገነዘቡት ይገባል።የሚከተለሉትን ጥያቄዎች እንደመመዘኛ ቢጠቀሙና ቢያጤኑት የጠ/ሚኒስትር አብይን ሚና ለማወቅ ይረዳቸዋል።

እዚህ ላይ ግን መካድ የማይገባው ነገር ቢኖር የዚሁ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተከታይ የሆኑ ብዙ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ክብርና አንድነት የህይወት ዋጋ የከፈሉ መኖራቸውን ነው።ማንም ዜጋ የፈለገውን እምነት የመከተል ወይም ያለመከተል መብት እንዳለው በንጉሥ ሃ/ሥላሴ ዘመን የተከበረ ነበር።ችሎታ እያለው በሚከተለው እምነት ምክንያት ከሚገባው የሥራ ድርሻና ስልጣን የታገደ አልነበረም።ስለሆነም የፕሮቴስታንትም ሆነ የሌላ እምነት ተከታዮች በከፍተኛ ያመራር ስልጣን ላይ ነበሩ። አሁንም በኢትዮጵያዊነት፣ለኢትዮጵያ አንድነት የቆሙ መኖራቸውን መዘንጋት አይገባም።የሚጠላውና የሚኮነነው እምነትን ተገንና ሽፋን አድርጎ አገርን የሚጎዳ ተግባር ማካሄዱ ነው።ለዚህም ነው የኦነግ አባላት በእምነታቸው ሳይሆን ባላቸው ጸረ ኢትዮጵያ አቋማቸው ሊወገዙና ሊወገዱ ይገባቸዋል የሚባለው።ከኑግ የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ እንዳይሆን ሌሎቹ አገር ወዳድ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች በአገር አጥፊዎቹ በኦነጎችና መሰሎቻቸው ዓይን መታዬት አይኖርባቸውም።

ለመሆኑ አምላክ በአምሳሉ የፈጠረውን ሰው ግደሉ፣በጎሳ ከፋፍላችሁ አጫርሱ፣አገር አፍርሱ፣ዝረፉ ብሎ ያበረታታበት ወይም ትእዛዝ የሰጠበት ቃል በየትኛው የእምነት መጽሃፍ ውስጥ ሰፍሮ ይገኛል?ይህንንስ የሚፈጽምና የሚያስፈጽም ሃይል ጋር የተሰለፈ ሰው እንዴት ለእግዚአብሔር ያደረ ነው ይባላል?ዶር/ኮሎኔል አብይ አህመድ በሰው ልጆች ላይ ይህንን ሁሉ ግፍ የፈጸመ ድርጅት የኢሕአዴግ አባል ነው።ዶር/ኮሎኔል አብይ አህመድን በቅዱስ ጳውሎስም የሚመስሉት አልጠፉም።ግን ቅዱስ ጳውሎስ ከነበረበት የአረመኔዎች ተግባር እርቆና ሲያገለግል የነበረውን ስርዓት ተቃውሞ ከጉዳተኞቹ ጎን የተሰለፈ የክርስቶስ ተከታይ መሆንን የመረጠ ሰው ነው። እስከመጨረሻው የቄሳር አገልጋይና የጦር መሪ ወይም ካድሬ ሆኖ ክርስቲያኖችን ሲያሳድድ አልኖረም።ዶር አብይ ይህንን የመሰለ ተጋድሎ ያበረከተ ሰው ነውን?አሁን የት ላይ ቆሞ ይገኛል?

በሌሎቹም አንደበት ከቻይናው የለውጥ ጠንሳሽ ከሊሻዎ ፒንግ ጋር እያመሳሰሉት ሲተቹ ይደመጣል።እነዚህኞቹ የዘነጉት ነገር ቢኖር ሊ ሻዎፒንግ አገር ወዳድና በአንድ ቻይና የሚያምን፣አነሳሱ ቻይና አሁን ላለችበት እድገት ላበቃት የፖለቲካ መስመር የታገለ መሆኑ ነው።ዶር/ኮሎኔል አብይ አህመድ ግን ከኢትዮጵያ በላይ የጎሳንና የክልል ስርዓት የሚቀበል፣ያ ካልሆነ ኢትዮጵያ ገደል ትግባ የሚል፣የአንዱ ጎሳ መሪና ተወካይ የሆነ ሰው ነው።ዱባና ቅል አበቃቀሉ ለየቅል!

የዶር/ኮሎኔል አብይ አህመድን በስልጣን ላይ መውጣት ለኢትዮጵያ ብስራት አድርገው የሚቆጥሩ የዋሆች ማየትና መገንዘብ፣መጠየቅም የተሳናቸው ነገር ቢኖር አብይ ማን ነው? ከየት መጣ?እዚህ ደረጃ ላይ እንዴት ደረሰ?የፖለቲካ አቋሙ ምንድን ነው?አማካሪዎቹ እነማን ናቸው?እስከ አሁን ድረስ በምን የሥራ መስክ ላይ ተሰማርቶ ነበር?ያደረሰው ጉዳት ወይም የሰጠው ጥቅም ምን ይመስላል?በዲስኩር የሚረጨውን የተስፋ ቃል በተግባር ሊተረጉም ይችላል ወይ? አሁንስ ስልጣን ካለውና ከኢሕአዴግ የተለዬ ከሆነ በየቦታው የሚካሄደውን የሕዝብ ጭፍጨፋ ለምን አላስቆመም? የሕዝቡን ትግልና ጥያቄ የጥቂቶች እረብሻ አድርጎ ከመቁጠር የተለዬ አመለካከት አለው ወይ? አፋኝ ህጎችን ለምን አልሻረም?በግፍ የታሰሩትን ሁሉንም እስረኞች ለምን እንዲፈቱ አላደረገም?አሁንስ ለምን ሲታሰሩ በዝምታ ያያል?አሳሪና ገዳዮቹን ማን ነው የሚያሰማራው? የመሳሰሉትን ሁሉ መጠዬቅ ማንነቱንና ለምን ዓላማ እንደቆመ ለማወቅ የሚረዱ ፈተናዎች ናቸው።

እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ ሰው በራሱ እምነት የሚመራ ሳይሆን በወያኔ ትእዛዝና ፍላጎት የሚሽከረከር ነው።በስተጀርባ የሚነዱት በአማካሪነት የተመደቡት የወያኔ ቱባ መሪዎች አባይ ጸሃዬ፣አርከበ እቁባይ፣ስዩም መስፍን፣አቦይ ስብሃት፣በረከት ስምኦንና ሌሎቹ ናቸው። የሚናገረው ንግግር በቅድሚያ ተዘጋጅቶ የሚሰጠው ለእሱ ብቻ ሳይሆን በሚሄድበት ቦታም ተቀብለው ለሚያስተናግዱትና ጥያቄ ለሚያቀርቡት ሰዎች ሳይቀር ትእዛዝና መመሪያ የሚሰጣቸው ወያኔ ነው።ያማ ባይሆን ኖሮ እንዴት ቢሆን ነው ሕዝብ ፊት ለፊት ለጠየቀው ጥያቄ ቀድሞ በተዘጋጀ ጽሁፍ ላይ የሰፈረ መልስ የሚሰጠው?እንዴትስ ተደርጎ ነው ሕዝቡ በሚናገረው ቋንቋ ለተደረገለት አቀባበል በማያውቀው ቋንቋ ወረቀት ላይ የሰፈረ ምስጋና ሊያቀርብ የሚችለው?የአዋሳውን ጉብኝቱን ማዬቱ ለዚያ ማስረጃ ነው።።የሕዝቡ አቀባበልና ጥያቄ በቅድሚያ የሚታወቅና የተዘጋጀ በመሆኑ ለዚያ ተመጣጣኝ የሆነ ምላሽም ከዶር/ኮሎኔል በኩል እንዲወጣ ቅድመ ዝግጅት መደረጉ በቀጥታ ስርጭቱ በታዬው ድራማ በግልጽ ታይቷል።በተጨማሪም በአቀባበሉ ስነስርዓት ላይ ለሚሳተፉ ካድሬዎችና የቀበሌ ነዋሪዎች የቀን አበል እንደሚሰጣቸው መዘንጋት አያስፈልግም።ውሻ በበላበት ይጮሃል እንዲሉ!ለዚያ የተመረጠው የማህበረሰብ ክፍል ያዘዙትን ሲያደርግ መታዬቱ አያስደንቅም።

አብይን ከኢሕአዴግ ነጥሎ ታላቅ መሪና ልዩ ዜጋ አድርጎ መቁጠር ስህተት ነው።ካለፈውም ጥፋት አለመማር ይሆናል። አሁን አብይ አብይ ብሎ ማጨብጨብ ነገ አብይ የሚወክለው ድርጅት ወያኔ መራሹ ኢሕአዴግ የበለጠ ጉዳት ሲያደርስ መጮሁ ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ ይሆናል።የአሁኑ ዝምታ ወይም ምስጋናና ውዳሴ ለነገው ወቀሳ የሚመች አይሆንም።ያ ከመድረሱና አዳጋች ከመሆኑ በፊት ለዚያ ሂደት መሳሪያ የሆነውን አብይን ከመቀበል ይልቅ ተቀምጠው የሰቀሉት ቆመው ማውረድ ያዳግታል የሚለውን በሳል ምክር ከግምት ውስጥ አስገብቶ መንቀሳቀስ ተገቢ ነው።

የዘረፋ ስርዓቱን ለማስቀጠል ኢሕአዴግ ከዚህ ቀጥሎም በሌላ ስምና አደረጃጀት ሊመጣ ስለሚችል በንቃት መጠበቅና ዳግመኛ በምንም አይነት ይህ ጎሰኛ ቡድን በኢትዮጵያ ውስጥ የስልጣን ባለቤት እንዳይሆን ለመከላከል ብሎም ወንጀለኛ አባላቱ በሕግ እንዲጠየቁ ለማድረግ የአንድነት ሃይሉ ህብረቱን ማጠንከር ይኖርበታል።በሰላማዊ ድርድርና ብሔራዊ እርቅ ሽፋን ወንጀለኛ ከሕግ በላይ እንዲሆን ማድረግ የበለጠ ወንጀል ነው።

እውነተኛ እርቅና ሰላም ከተፈለገ

1 አሁን የሰፈነው የኢሕአዴግ የጎሳ ፖለቲካ አደረጃጀትና ክልል ፈርሶ አገሪቱ በቀድሞው ክፍላተ ሃገር መልሳ መዋቀር ይኖርባታል፣ወደፊትም በጎሳና በሃይማኖት የፖለቲካ ድርጅት መፍጠርና መንቀሳቀስ መከልከል አለበት።ለአገሪቱ አንድነትና ለህዝቡ ዘላቂ ሰላምና እድገት የሚጥሩ፣በፍልስፍና ላይ መሰረት ያደረገ ራእይ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ካለምንም ገደብ እንዲንቀሳቀሱ መብታቸው ተከብሮ ለደህንነታቸውም ዋስትና ሊሰጣቸው ይገባል።አላስፈላጊ የሆኑ ድርጅቶች እንዲዋዋጡ ወይም ቁጥራቸው እንዲቀንስ መደረግ አለበት።በአገራችን ከሶስት ያልበለጡ የፖለቲካ ድርጅቶች ባይኖሩ ይመረጣል።

2 በእስር ቤት የሚገኙት ተቃዋሚዎች ካለምንም ቅድመ ሁኔታ መለቀቅ ይኖርባቸዋል፣ለደረሰባቸው የአካልና የስነልቦና ስብራትና ጉዳት ሊካሱ ይገባል፤ የሕዝብ መብትና ነጻነትን የሚያግዱ ሕጎች መሻር አለባቸው፤ሕዝብ ለማሸበርና ለማፈን የተቋቋሙ ድርጅቶችም ሊታገዱ ይገባል፤የሰብአዊና የዴሞክራሲ መብቶች ያለገደብ በተግባር መከበር አለባቸው።

3 በአገርና በሕዝብ ላይ በደል የፈጸሙ፣የገደሉ፣ያስገደሉ፣የዘረፉ ወንጀለኞች ለፍርድ መቅረብ ይኖርባቸዋል፤በውጭ አገር የኮበለለው ገንዘብና ንብረት መመለስ አለበት

4 ሕዝብ ከኖረበት ቦታ የማፈናቀሉና ቦታውን የመንጠቁ ተግባር መቆም አለበት ፤ለተነጠቁትም ተመጣጣኝ ካሳ ሊከፈላቸው ይገባል፣ዜጋ በኢትዮጵያዊነቱ እንጂ በጎሳው እንዳይጠቀም ወይም እንዳይጎዳ መሆን አለበት፤አንዱ ዜጋ ከሌላው ዜጋ እንዳይለይ በሕግ መከልከል ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል።ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አገር ስለሆነች በፈለጉበት የአገሪቱ ክፍለሃገር የመኖር፣የመስራትና ሃብት የማፍራት መብት በተግባር መረጋገጥ ይኖርበታል፤ያንን የሚጻረር ሕጋዊ እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል።

5 በየትኛውም አካባቢ የሚገኘው የተፈጥሮ ሃብትና የልማት እንቅስቃሴዎች፣ከግለሰቦች ያገልግሎት ይዞታ በመለስ ለሁሉም ሕዝብ ጥቅም የሚውሉ የጋራ ሃብት መሆናቸው ሊረጋገጥ ይገባል፤ባለስልጣኖች የሚወስኑበትና የሚፈነጩበት ወይም አንድ ክልል የሚቆጣጠረው፤ለውጭ ባለሃብቶችና የጎረቤት መንግሥታት አሳልፈው የሚሰጡት ገጸ በረከት እንዳልሆነ አምኖ መቀበል።

በጥቂቱ እነዚህን ጥያቄዎች መፍታት ለብሔራዊ የእርቅና ሰላም ሂደት መሳካት ዋስትና ይሆናል።

የአንድነቱ ጎራ የኢሕአዴግ አጃቢ ከመሆንና በሱ ፈቃድ ለመንቀሳቀስ ደጅ ከመጥናት ይልቅ እራሱን የኢሕአዴግ ተቃዋሚነቱን አጉልቶና አጠንክሮ ለዴሞክራሲያዊ ሽግግር ሕዝቡን ማሰለፍና ማዘጋጀት ይጠበቅበታል።ከግለሰብ የበለጠ ድርጅታዊ አመራር ለመስጠት ብቃት ያለው የጋራ አካል መፍጠር ይበልጥ አስተማማኝ ነው።

የኢሕአዴግ መሳሪያ የሆነውን ዶር/ኮሎኔል አብይን መቃወም ለወያኔ ዱላ ማቀበል ነው፤ጸረ ለውጥ መሆን ነው፤ የሚሉ ወገኖች አልጠፉም። ያልተረዱት ነገር ቢኖር፣ ለወያኔ ዱላ ማቀበል ማለት ሳይቃወሙ እያጨበጨቡ ለውጥ መጥቷል ወይም ይመጣል ብለው ሕዝብ ከትግል እንዲያፈገፍግ በመስበክ ወያኔ በዚያ ሂደት መልሶ እንዲጠናከርና እንዲያንሰራራ ማድረግ መሆኑን ነው።ለዘላቂውና ለአስተማማኙ ስር ነቀል ለውጥ፣ለኢትዮጵያ አንድነት የተነሳው ወገን በፍርሃትና በአሉቧልታ ትጥቁን ሊፈታ አይገባውም።ያለበትን አንድ ያለመሆንና የመበታተን ድክመቱን አሶግዶ ለዓላማው ተሰባስቦ መቆም ይኖርበታል።

ኢትዮጵያን ከተደጋጋሚ ጥፋት እንታደግ!

አገሬ አዲስ

Go toTop