ሰሞኑን ፌስቡኩን ያጨናነቀው አብይ የኦሮሞ ብሔረተኝነት ኦሮሞን ከነበረበት ክብር አወረደው ብሎ ተናግሯል በሚል ብዙዎች እንዴት እንዲህ ይናገራል በሚል ሌላ ጦርነት የከፈቱ ይመስላል፡፡ እኔ ይህን ሲናገር አልሰማሁትም በምን አግባብም እንደተናገር አላውቅም፡፡ ግን ተናግሮትም ከሆን እኔን እንደሚገባኝ አንደም የተሳሳተው ነገር የለም፡፡ እውነት ነው፡፡ ችግሩ ማስተዋል አቅቶን በዘረኝነት ስለተለከፍን ብሔረተኝነትን የሚያገን ወሬ እንጂ እንደ ሰው ማሰብ አልቻልንም፡፡ አሁን በአለን አስተሳሰብ 27 ዓመት የገነባንው ዘረኝነት እውነታውን ፍጹም እንዳናስተውል አድርጎናል፡፡
አብይ አንድ ወጣት በባሕርዳር ስብሰባው ወቅት አማራ አማራ አማራ ያለበትን እንዲሁም ብዙዎች በአማራ ክልል ጉብኝቱ አማራ ማለትን ስላበዙበት እንደወረደ ፊት ለፊት ነው የነገራቸው፡፡ አማራ አማራ አማራ እንዴት ሆነን ነው ኢትዮጵያዊ የምንሆነው በዚህ የዘረኝነት ልክፍት አእምሮአችን አይነት መልዕክት ነበር ፊት ለፊት የነገራቸው፡፡ አጀቴን ቅቤ ከአጠጡት መልስ አንዱ ነበር፡፡ በአጠቃላይ በባህርዳሩ ንግግሩ ኢላማ ያደረገው የዘረኝነትን አስተሳሰብ መምታት ይመስል ነበር፡፡ አንዷ ተነስታ የእረሶ ብሔር በወለጋ አማሮችን እያሰቃየ ነው አለችው፣ ሌላው ተነስቶ አማራ አማራ አማራ በየቦታው …… አለው፡፡ ስለኢትዮጵያዊነት እናወራለን እያሉ ሁሉም በራሱ ዘር ልክ ነው የሚያስበው፡፡ የኢትዮጵያን ጠ/ሚኒሰቴር የእርሶ ብሔር እያሉ መናገር ብምን ሒሳብ ነው ዘረኝነት የማይሆነው? ቀላል ወረደናል እዴ ተዋርደናል እንጂ፡፡
እስኪ አብይ አነሳው የተባለውን የኦሮሞ ብሔረተኝነትን ውጤት ከመሠረቱ ጀምረን እንየው፡፡ እየሆነ ያለው እኮ ግልጽ ነው፡፡ ከዛሬ 50 ዓመት ገደማ ጀምሮ የኦሮሞ ነጻነትን እናመጣለን ብለው የተንቀሳቀሱ ቡድኖች ዛሬ ሕዝቡን የት ነው ያደረሱት? ኢትዮጵያዊነቱን እየሸረሸሩ ፍፁ አገር የሌለው ኦሮሞ አደረጉት፡፡ ይሄ አፍጦ የምናየው እውነት እንጂ ታሪክም ተረትም አደለም፡፡ ከ50 ዓመት በፊት በመንግስትም ሆን በኢኮኖሚ ትልቁን ቦታ ይዞ የሚገኘው እራሳቸውን ኦሮሞ ብለው በአልጠሩ በዛሬው የብሄረተኝነት(ዘረኝነት) መስፈረት በማያሻማ ሁኔታ ኦሮሞ የሆኑ ነበሩ፡፡ በኃይለስላሴ ጊዜ ለትምህርት ወደ ውጭ ሄደው የተመለሱ ብዙዎች ያመጡት የዘረኝነት ልክፍት ቀጥሎ እንደ ልዩ እውቀት አጠቃለይ የ60ዎቹን ትውልድ እንዳለ በከለው ውጤቱም አይሄው እስከዛሬም ልንወጣው አልቻልንም፡፡
የብሔር ጭቆና ደረሰ ብለው ሁሉም አማራ የተባለን ብሔር ጨቋኝ ሌላው ተጨቋኝ አርጎ አዲስ የመርግት ርዕዮት ወደዚህች አገር ገባ፡፡ ሁሉም ሽምጥጥ አድርጎ እነትን ካደ፡፡ ከሁሉም ግን የኦሮሞን ሕዝብ ትልቅ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ በጨቋኝነት ከተመደበ ሁለት ጨቋኞች ተባብረው ሴራችንን ያበላሹብናል በሚል ኦሮሞን ከተጨቆኑት ምድብ ከተቱት፡፡ ከዛ እስከዛሬም ማቆሚያ የሌለውን የቁልቁሊት አዋረዱት፡፡ ከዛም አልፈው ኢትዮጵያዊ አደለህም፣ አበሻ አደለህም ከአብሻ ጋር ምንም ኽብረት የልህም ብለው በገዛ አገሩ አገር አልባ አድርገው አባዘኑት፡፡ አስከፊውን እውነት አየን ኦሮሞ ከኢትዮጵያዊነት ወጣ አባቶቹ የሰሯትን አገር አገሬ አደለችም ብሎ ካደ፡፡ አባቶቹንም አላውቃቸውም ብሎ ካደ፡፡ የአገሪቱን ባለቤት ጎበናን ብቻ ሳይሆን ዘሩን ሁሉ ረገመ፡፡ ሰኚ ጎበና አለ፡፡ እንግዲህ ሚኒሊክ አማራ ስለተባሉ የኦሮሞ ጠላትነታቸው ሁለት እጥፍ ነው በዛሬው የመከውነው ትውልድ አስተሳሰብ፡፡ሚኒሊክም ሆኖ ጎበና በእርግጥ እኔ አማራ፣ እኔ ኦሮሞ አላሉም፡፡ የእርግማኑ ትውልድ ነው ኦሮሞነት አማራነት የሰጣቸው፡፡
የሆነው ሁሉ ወደ ኋላ አስተውሉ፡፡ በዚህ ሁሉ ኦሮሞ እውነትን በካደው ልክ እጅግ ተዋረደ፡፡ ሴረኞቹ አገሩን ነጥቀው ቤቱም እንዳይኖር ቤቱን እስር ቤት፣ በገዛ አገሩ ስደት አደረጉት፡፡ ኦሮሞ ኦሮሞ ኦሮሞ እያለ በጮኸ ቁጥር ቁልቁልቁለቱን አፋጠነ፡፡ በእርግጥም ሴረኞቹ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ኦሮሞን ኢላማ ማድረጋቸው ትክክል ነበር፡፡ ዛሬ ኦሮሞ የት ነው ያለው? እስር ቤት፣ ከቄየው ተፈናቅሎ በየከተማው? ይህ እንግዲህ አሮሞነትን የጠነጠኑት ኦሮሞ ነን የሚሉ የሥራቸው ውጤት ነው፡፡ ዛሬ ኦሮሞ በሁሉም ብሔረሰብ በተባሉት የሚታየው በበጎ አደለም፡፡
አማራ ተብዬው ከመጀመሪያውም ጨቋኝ ተብሎ ሁሉም እሱ ላይ ተረባረበ፡፡ ብዙ ሆነ፡፡ ከበደኖ እስከ ጉራፈርዳ፣ እስከ ቤኒሻንጉል፡፡ የሆነው ሆነ፡፡ ምንም የማያውቅ ሚስኪን ገበሬ ጨቋኝ በሚል ብዙ ግፍ ደረሰበት፡፡
በመጨረሻ በዛሬው ሂሳብ ትልልቅ የሚባሉት ብሄረሰብ ተብዬዎች አማራና ኦሮሞ እኩል መከራ ገፈት ቀማሽ ሆኑ፡፡ እንደውም ከጨቋኙ አማራ ወደ ተጨቋኙ ኦሮሞ መከራ እያየለ መጣ፡፡ ትንንሾቹ በተሻለ ይኖራሉ፡፡ ጭራሽም ዋና የጥቃት አድራሽ ሆነዋል፡፡ ብሔረተኝነት እንዲህ ያደርጋል፡፡ ትልቁን ትንሽ በጣም አናሳ፡፡ ትንሹን ደግሞ ያተልቃል፡፡ ዘረኝነት/ቤሄረትኝነት ማለት ይሄ ነው፡፡ ኦሮሞ በብሔረተኝነቱ ምክነያት ኢትዮጵያዊነቱን ስለተወ ነው ዛሬ እየሆነበት ያለው ሁሉ የሚሆነው፡፡ አማራውን በጨቋኝነት ለብቻው ማንነት ሰጡት፡፡ ስለዚህ 70 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ሕዝብ ሽባ ሆነ፡፡ ኦሮሞ፣ አማራ ነኝ አዎ ብሔረተኝነት ዘረኝነት ነው፡፡
እስኪ አስተውሉ አሁን እነለማ በፈጠሩት ጭላኝጭል የኢትዮጵያዊነት መንፈስ እየሆነ ያለውን፡፡ ኦሮሞ ኦሮሚያ ከን ኦሮሞቲ ሲል የከረመ ዛሬ ኢትዮጵያን አባቶቻችን ያቆዮልን አገር ማለት ሲጀምር ነው የሴረኞቹን ውል ያጠፋው፡፡ እራሳችንን አጥበን ከለልን ዛሬ ከዚህ አታልፍም ከአንተ በኩል ይሄን ያህል ቦታ ወስደህብኛል በሚል ጭራሽ ከምንኖርበትም ተፈናቀልን፡፡
ለመሆኑ ብሔረተኛ ነን እያላችሁ የምታቅራሩ ዛሬ እባካችሁ ልንላችሁ ትፈልጋላችሁ፡፡ አዎ ዘረኞች ናችሁ እያልን እቅጩን እንነግራችኋለን፡፡ የኢትዮጵያዊነት መላላት ከእነጭርሱም መጥፋት ነው ዛሬ በሚሊየን የሚቆጠሩ በገዛ አገራቸው መከራ እየተቀበሉ ያሉት፡፡ እርግጥ ነው ይህ ብሔረተኝነቱ እየተቀማቸው ያሉ ብዙዎች አሉ፡፡ ብሔረተኝነት ከሌለ ከነጭርሱም መኖር የማይችሉም አሉ፡፡
አብረን የምናራግብ፣ እናስተውል፡፡ ነገሮችን አሁንም ወደ ኋላ ለመመለስ እንቅልፍ አጥተው የሚያሴሩ እየተሯሯጡ ነው፡፡ ሌላው የውሸት መላላስ መቆም አለበት፡፡ አካፋን አካፋ ዶማን ዶማ ከአላልንው ጆሮ ሰጥተን ከአደመጥናቸው ብዙ የሚያወሩ አሉ፡፡ ለዘመናት እርምጃ አለመውሰዳችን ነው ዛሬ ላይ የደረስነው፡፡ እርግጥ እንኳንም በዚህ ሁሉ ሂደት አለፍን፡፡ ማን ሊያምን ፈለገ ይሄ ነገር አይሆንም ሲሉ እኮ ብዙዎች እንደ ጠላት ተቆጥረዋል፡፡ በግርግር አገር ፈርሳም ቢሆን ከዚህ የከፋ ችግር ይደርስ ነበር፡፡ በአቋም ጽኑ፡፡ አብይ የኦሮሞ ብሔረተኝነት ኦሮሞን አውርዶታል ማለቱ ስህትት ሆኖ ሳይሆን ዘረኝነትን እንዝና መቁጠር ስለጀመርን ነው፡፡ አሳፋሪውን እያወደስን በተቀደሰውና በተከበረው ነገር የምናፍር ሆነናል፡፡
አብይ የተሳሳተ ነገር እንኳን ቢናገር የእሱን ንግግር እየጠበቁ መንቀፍ ለሴረኞች እድል መስጠት ነው፡፡ አስፈላጊ በሚሆንበት መድረክና አጋጣሚ የምንነቅፍበትን የምንነግረው ጊዜ ይኖራል፡፡ በዚህ ላይ 27 ኣመት ሁሉም በየራሱ ሆኖ እንዲያስብ የተደረግን ሕዝብ ሁሉ አንድነት ሊያረካ አይችልም፡፡ ይልቁንም ኢትዮጵያዊ ነን የምትሉ፣ እንዲህ ያሉ ነገሮቹን እንዲገፋበትና በነጻነት ወሳኝ ለውጥ ማምጣት የሚችልበትን እድል መፍጠር ነው፡፡ ለነገሩ ኢትዮጵያዊ ነኝ ባዩም ውስጡ ያው ነው፡፡ ግፋ ቢል ከአማራነት አያልፍም፡፡ እናስተውል እጅግ ወርደናል፡፡
አብይ እኮ በየቦታው እንዳይከፉ በሚል እየተናገረ ያለው ነገር ነው ችግር እየፈጠረ ለጠላቶቻችን እድል እየከፈተ ያለው፡፡ ከዚህ በኋላ እንደውም ይሄ ብሔረሰብ እየጠራ የሚናገረውን ነገር ማቆም አለበት፡፡ በተጓዘበት ቦታ ሁሉ ብሄረሰብ ለማስደሰት የሌለ ነገር ሁሉ ይናገራል፡፡ እስኪ አስተውሉት፡፡ እንደው እንደምሳሌ አማራው የተባለው ክልል የአማራው ሕዝብ እያለ ነበር ሲናገር የነበረው፡፡ ይሄ ብሔረተኝነት አንዴ አቅላችንን አስጥሎ አእምሮአችንን ደፍቶት እንጂ እኮ አማራ ክልል ራሱ ስንት ብሄረስብ ነው ያለው? ቢያንስ በክልሉ የኢትዮጵያ ታሪክ ባለቤትና መሠረት የሆነው የአገው ሕዝብ አለ፡፡ እንግዲህ ሥማቸው ያልተጠራው ደግሞ የእኛ ሥም አልተጠራም በሚል ሊያኮርፉ ነው፡፡
መጀመሪያ ሎጂካል እንሁን፣ አንዳንዶቻችን ትልልቅ ብሔረሰብ አለን ብለን እናቅራራ ይሆናል፡፡ በዚህ ላይ የእኛ ብቻ እንጂ ሌላውን ፈጽሞ እንዳናሰብ ተደፍኖብናል፡፡ ብሔረተኝነት እንግዲህ እኔን እንደሚገባኝ ይሄ ነው፡፡ መረጃ በመስጠት ራሴን ማባከን አልፈለኩም፡፡ እስኪ ሁሉንም እያስተዋልን፡፡ እግዚአብሔር ማስተዋሉን ይስጠን!
ልዑል እግዚአብሔር ወደልቦናችን ይመልሰን! ከዚህ የዘር ልክፍት ያላቀን! ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይቀድስ! አሜን!
ሰርፀ ደስታ