በሀገራችን የተከሰተውን የፓለቲካ ቀውስ በሚመለከት ሰሞኑን በዲያስፓራ የዓረና ትግራይ ድጋፍ ኮሚቴ ባዘጋጀው ቴሌኮንፈረንስ መላ አባላቱንና ደጋፊዎች እንዲሁም፣ ጥሪ የተደረገላቸው አንጋፋ ምሁራንና በርካታ ወጣቶችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች የተሳተፉበት ውይይት በማካሄድ ከዚህ ቀጥሎ ያለውን የጋራ የአቋም መግለጫና ውሳኔ አውጥቷል::
የህወሓት አምባ ገነን መሪዎች ዙሪያቸውን በወታደራዊ ሐይል ተከቦ ሲያዩት ልባቸውን በትዕቢትና በትምክህት ስለሚሞላ ነገ ፈራሽ መሆናቸውን ከታሪክ አይማሩም:: ሰብኣዊ ርህራሄንና የይቅርታ መንፈስን ስለሌላቸው የህዝቡን ጥያቄና ጭኾት ጉዳያቸውም አይደለም:: የህልውናቸውን መሰረት ሕብረተሰቡን በዘር፣ በሀይማኖት፣ በጥላቻና በቂም በቀል ለያይተህ ፣አደንቁረህና አደንዝዘህ ግዛ የሚል መርህ ስለሆነ የህዝቡን ነፃ እንቅስቃሴ፣ አንድነትና መደራጀት ከጦር በላይ ይፈሩታል:: ራሳቸውን ልዩ ፍጡራንና ልዩ ጀግኖች አድርገው በመመልከትም ከሀገርና ከሕግ በላይ በመሆን የሰው ህይወት የዶሮን ያህል ግምት አይሰጡትም:: የዓይን ብሌየናቸውም ሀገርና ህዝብ ሳይሆን ገንዘብና ስልጣን ነው:: መቋደሻቸውም በየስድስት ወሩ ባሩድ ባሩድ ሲሸታቸው ስለሆነ የንፁሃንን ደም በአስፋልቱ ላይ ተጥለቅልቆ ሲያዩት እንደጀግንነት በመቁጠር ይረካሉ:: በርስትነትና በሞኖፓልነት የያዙት የብዙሃኑ መገናኛ አውታሮች አማካኝነት ነጋ ጠባ የሚያስተጋቡት የጉራ ነጋሪትም በለው፣ ፍለጠው፣ ርግጠው፣ ቁረጠው፣ ግደለው ከሚል ቀረርቶ በስተቀር የህዝቡን ብሶት የማዳመጥና አርቆ የማየት ዓቅም፣ ሞራል፣ ብቃትና ተፈጥሮ የላቸውም:: ይህ በመሆኑም የህዝቡን ዓመፅ ቤተ መንግስታቸው አፋፍ ላይ ደርሶ እንደ እሳተ ጎመራ እስከሚለበልባቸው ድረስ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀልበማለት እስከመጨረሻ ህልፈታቸው ድረስ የዘረፉትን ሀብት ተንተርሰው ሀገርንና ህዝብን አጥፍተው መጥፋትን መርጧል::
ዛሬ በሀገራችን የፈነዳው ቀውስም ድንገት የተከሰተ ችግር ሳይሆን ውስጡ ውስጡን እንደ ረመጥ እሳት እየተብላላ ቆይቶ በሕብረተሰቡ ውስጥ ያለው ማሕበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ ብሶት የወለደው የፍትሕና የፓሊሲ መዛባት ውጤት ነው:: አንድ አምባ ገነን ቡድን ሁሉንም ነገር በሞኖፓል ጠቅልሎ በመያዝ 90 ሚሊዮኑን የኢትዮያ ህዝብ የበይ ተመልካች በማድረግ አግላይና አፋኝ ፓለሲ የወለደው የዓመፅ ነበልባል ነው:: በዚህ ምክንያት ዛሬ ህዝቡ በተለይም ወጣቱ ትውልድ በያለበት ከጫፍ እስከጫፍ እያስተጋባ ያለው የጋራ ጭኾትም “ሕገ መንግስት ይከበር ፣ የህወሓት ሞኖፓላዊ የአፈ ሙዝ አገዛዝ ያብቃ፣ ግድያና አፈና ይቁም ፣ የህሊና እስረኞች ይፈቱ ፣ ድምፃችን ይሰማ፣ ፍትሓዊ የሀብት ክፍፍል ይኑር ፣ በዘር በሀይማኖትና በክልል እየከፋፈሉ ወገን ከወገን ጋር ማባላት ይቁም፣ እኛም የሀገራችንና የህዝባችን ጉዳይ ያገባናል፣ “ የሚል የፍትሕ የመብትና የሰብኣዊ ነፃነት ጥያቄ ነው:: ይሁን እንጂ ችግሩን ተገንዝቦ የህዝቡን ጥያቄ በማዳመጥ ምላሽ የሚሰጥ መንግስት ባለመኖሩ ይኸውና እንደተለመደው ከህዝብ ጋር እልህ በመግባት ዛሬም ትዕቢት በተሞላበት እምቢ ያለ ሰው ጥይት አጉረሰው በሚል የተለያዩ አሸባሪ አዋጆችን በማውጣት በንፁሃን ወገኖቻችን ላይ የቀቢፀ ተስፋ እርምጃቸውን በመውሰድ ላይ ይገኛሉ::
የሁሉንም ችግሮች ምንጭ የሆኑት የስርዓቱን ቁንጮ የትግራይ ህዝብን ልዩ ተቆርቋሪ ፣ ጠበቃና ነፃ አውጪ በመመሰል በህዝቡ ስምና ደም እየነገዱ ለጥቃት ለስደት ለውርደትና ለዓፈና እየዳረጉት ያሉት እንደ እሾኽ አሜኬላ በትግራይ ምድር የበቀሉ የህወሓት መሪዎች መሆናቸውን ከራሱ ከህዝቡ በላይ ሌላ ምስክር አይኖርም:: ለዘመናት በሀገሩንና በማንነቱን ኰርቶ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር ተግባብቶና ተፋቅሮ ይኖር የነበረውን ህዝብ ዛሬ ወርቃማ ታሪኩን በማንቋሸሽ ፣ አኩሪ ባህሉን በማራከስ ፣ ማሕበራዊ ፋብሪኩንና ብሄራዊ እሴቶቹን እንዳልነበሩ በማድረግ ፣ ሀይሉን በመበታተንና ኢትዮያዊነት ማንነቱን በማዳከም የጥላቻ ማዕከል ሆኖ እንዲታይ አድርገውታል:: ከዚህም በላይ “የትግራይ ህዝብን የፈጠረ ህወሓት ነው” በማለት ህዝቡ በደደቢት በረሃ እንደጭቃ ተጠፍጥፎ የተፈጠረ የህወሓት ውጤት አድርገው ለማሳመን ያልፈነቀሉት ድንጋይ ፣ ያልሰሩት ተንኰልና ያላካሄዱት ፕሮፓጋንዳ የለም:: ከዚሁ ምትሓታዊ ተግባራቸው የተነሳም ህወሓትን ከሰማይ የወረደ መልኣክ አስመስለው በመቅረፅ በሁሉም መስክ በአብያተ ምእመናንም ሳይቀር ይሰበሆ እየተባሉ እንደ ልደተ ክርስቶስ እየተዘመረላቸው ያደጉ መሪዎች ናቸው ዛሬ ዕድሜ ልክ ስልጣንን በርስትነት ይዘው በትግራይ ህዝብ ጫንቃ ላይ ተቀምጠው የሚገኙት::
በሀገራችን በተከሰተው የፓለቲካ ቀውስ ሳቢያም አልፎ አልፎ የሚታዩ በቋንቋ ላይ የተመሰረቱ አንዳንድ ግጭቶችም መነሻቸውና እንጂነሮቹ እነሱ ራሳቸው ከመጋረጃው በስተጀርባ ሆነው የሚጭሩት እሳትና የሚሰሩት ተንኰል ውጤቶች ናቸው:: ጭቁኑ የትግራይ ህዝብ ዙሪያውን ሁሉ በዘር ጥላቻ ታጥሮ በማያውቀው ጉዳይ የጥቃት ዒላማ ሆኖ በስጋት እንዲኖርና አማራጭ መንገድን አጥቶ ሳይወድ በግድ “የሌላ ጅብ ከሚበላኝ የወንዜን ጅብ ይብላኝ” ብሎ እንዲወስን ጫና በመፍጠር የጥቂት መሪዎችን ዘላለማዊ ስልጣን ማስጠበቂያ መሳሪያ ሆኖ እንዲኖር ተደርጓል:: ውጤቱም እንደምናው ነው:: ህወሓት ለዓመታት የዘራውን የከፋፍለህ ግዛ መርዝ እያጨደ ይገኛል:: ይህ በመሆኑም ምኞታቸውን ተሳክቶላቸው የትግራይ ህዝብ ከወንጀለኛ መሪዎች ጋር ተደምሮ እንደጠላት እንዲታይ በማድረግ አይዞህ የሚለው ወንገንና የሕግ ከለላ አጥቶ እኖሆ ዛሬ በሁለት ዱላ እየተቀጠቀጠ ራሱ መስዋእትነትን ከፍሎ ባቆያት ሀገር ላይ የቁም እስረኛና የጥቃት ዒላማ ሆኖ ዳግም ሲያለቅስ ማየታችን እጅጉን አሳዝኖናል:: አስቆጥቶናልም::
የተከበራችሁ ሀገር ወዳድ ወገኖች ሆይ
ዛሬ ለሕግ ተገº የሆነ መንግስት በሌለበት ፣ እርስ በርስ መደማመጥ በታጣበት፣ ትግሉን አቅጣጫ አስይዞ የሚያስተባብር ሁነኛ መሪ ድርጀት ባልተጠናከረበት፣ በአጠቃላይ የሀገራችን ፓለቲካ ምስቅልቅሉ ወጥቶ መተማመንና መተባበርን በጠፋበት ሁኔታ ላይ ሆኖ እየተካሄደ ያለው የተበጣጠሰና መልክ ያልያዘ ዓመፅ ሀገራችንን በመስቀለኛ መንገድ ላይ እንድትቆም አድርጓታል:: አፋጣኝ መፍትሄሔ ካልተገኘለት ደግሞ “የሚበላው ያጣ ህዝብ መሪዎቹን ይበላል ወይም እርስ በርሱ ይባላል” እንደተባለው ነገ ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመቱ አያዳግትም:: በልቡ የሸፈተ፣አንጀቱን የደማና አማራጭ ያጣ ህዝብ የሰራዊት ጋጋታና አፈ ሙዝ እንደማይመልሰው በዓይናችን እያየን ነው:: ሰው እየገደልክ በሄድክ ቁጥር ደግሞ በየቀኑ ሽሕ ጠላት ከማፍራቱ ውጭ መፍትሄ ሊያመጣ እንደማይችል ከልምዳችን አይተኗል:: ስለዚህ ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ ቀውሱን ለመግታት የሰከነ አእምሮን ፣ ቆራጥነትን ፣ ኢትዮያዊነት ሃላፊነትን ፣ ብስለት ያለው አመራርን ፣ የነቃና የተደራጀ የህዝብ ተሳትፎን የሚጠይቅ ፈታኝ ወቅት ላይ ደርሰናል:: እኛ በውጭ ዓለም የምንገኘው የዓረና ትግራይ አባላትና ደጋፊዎችም ከላይ የተጠቀሰውን አደገኛ ሁኔታ በማጤን ሰሞኑን ባካሄድነው ረጅም ሰዓታት የፈጀ ቴሌኮንፈረንስ ከዚህ ቀጥሎ የተጠቀሱትን የጋራ ውሳኔዎች አስተላልፈናል::
- የትግራይ ህዝብ ከህወሓት ሞኖፓላዊ የባርነት አገዛዝንና ከቁም እስረኛነት ለመላቀቅ በሚያደርገው የተባበረና የተቀናጀ ትግል ከጎኑ እንደምንሰለፍ እናረጋግጣለን:: የትግራይ ህዝብ ላለፉት አርባና ሐምሳ ዓመታትን ያህል በህወሓት ሞኖፓላዊ አገዛዝ ስር ወድቆ በጅሆ (ሆስቴጅ) ተይዞ እንዲኖር የተፈረደበት ህዝብ ሆኖ ቆይቷል:: ይህ ሁነኛ ባለቤትና ከለላ ያጣ ህዝብ ከህወሓት መሪዎች የጅብ ምንጋጋ ተላቆ የሰላምና የነፃነት አየር እንዲተነፍስ ” ሕገ መንግስት በሰጠው መብት መሰረት ከማንኛውም ኢኮኖሚያዊና ማሕበረ ፓለቲካዊ ተፅዕኖና ጥቃት ነፃ በመሆን አማራጭ ሃሳብ የመስማት ” በነፃነት የመንቀሳቀስና የመደራጀት መብቱን እንዲከበርለት ህወሓት ከትግራይ ህዝብ ጫንቃ እጁን እንዲያነሳ እንጠይቃለን:: የካድሬ አገዛዝ አብቅቶ በምትኩ ለሕግ ተገዝ የሆነ መንግስትና በሕግ የሚዳኝ ሕብረተሰብ እንዲረጋገጥ የትግራይ ተወላጆች የትም ይኑሩ የትም የህዝቡን ደህንነትና የሀገርን አንድነት መጠበቅ ታሪካዊ ሃላፊነት ፣ ህዝባዊ አደራና የሞራል ግዴታ ስላለባቸው ከህዝቡ ጎን በመቆም የተባበረና የተቀናጀ ትግላቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን::
- ዓረና ትግራይ ጠንካራ አማራጭ ሀይል ሆኖ እንዲጎለብት ለማድረግ በሁሉም መስክ በገንዘብ በሀሳብና በሞራል ለመደገፍ ወስነናል:: በአንድ ሀገር ውስጥ በሰለጠነ አመለካከት ላይ የተመሰረተ ነፃና አማራጭ የፓለቲካ መድረክ መኖር ከሁሉም በላይ የነፃ ውድድሩን ተጠቃሚ የሚሆነው ህዝቡን ነው:: አማራጭ ያለው ህዝብ ሁሉጊዜ ይከበራል:: አማራጭ የሌለው ህዝብ ግን ቢለጉሙት ፈረስ ቢጭኑት አህያ ሆኖ ነው የሚኖረው:: በነፃ የገበያ ውድድር ላይ ጥራት ያለውን ዕቃ ማግኘት እንደሚቻል ሁሉ በነፃ የፓለቲካ መድረክም ብቃት ያላቸውን መሪዎች ይወለዳሉ:: ህዝቡ መብቱንና ግዴታውን አውቆ የስልጣን ባለቤት ለመሆን የሚችለው የራሱን ሃሳብ በነፃነት መንፈስ የሚያንሸራሽርበት አማራጭ መድረክ ሲኖረው ብቻ ነው:: በመሆኑም በትግራይ አማራጭ ሐይል መኖርና መጠናከር ማለት ደግሞ ከሞኖፓላዊ አገዛዝ መላቀቅ ብቻ ሳይሆን ለነገ ድልድይ በመሆን በሀገር ደረጃ የምንመኘውን ዴሞክራሲያዊ ሰርዓት ለመገንባት ህልውናችንና ዕድላችንን የምንወስንበት የማዕዝን ድንጋይ ነው ብለን እናምናለን:: በዚህ መሰረት አሁን ያለው የሀገራችን እውነታም የሚያሳየን በትግራይ አማራጭ ሀይልን ማጠናከር ዋል ዕድር የማይባል አጣዳፊ ጉዳይ መሆኑን ነው:: በዚህ መሰረት መስዋእትነትን እየከፈለ ሰላማዊ ትግል በማካሄድ ላይ የሚገኘው ዓረና ትግራይን እንደ አንድ አማራጭ ሐይል ሆኖ በነፃነት ለመንቀሳቀስ ይችል ዘንድ ከስርዓቱ ጥቃት ለመከላከልና ድርጅታዊ ዓቅሙን እንዲጎለብት በሃሳብ ፣ በገንዘብና በሞራል ለመደገፍ በጋራ ድምፅ ወስነናል::
- የጨካኝ ስርዓቱን ሰለባ በመሆን በትግራይ ምድር በጨለማ እስር ቤት ታጉረው በመሰቃየት ላይ የሚገኙትን የዓረና ትግራይ አባላትና ሌሎች የህሊና እስረኞችን ያላንዳች ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲፈቱ እንጠይቃለን:: በሀገር ውስጥ በሕግ ተመዝግበው፣ የመንግስት ሕግን አክብረው ፣ ብዕርንና ወረቀትን ብቻ ይዘው ፣ ህዝብን አምነው ፣ ባዶ እጃቸውን በሰላማዊ መንገድ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙትን የዓረና ትግራይ አባላትና ደጋፊዎች እንደጠላትና እንደሁለተኛ ዜጋ ተቆጥረው የሚደርስባቸውን ድርብ ድርብርብ በደል ተዝርዝሮ የሚያልቅ አይደለም:: ሌላውን ትተን እንቅስቃሴያቸውን ለመገደብ ሲባል ፅሕፈት ቤታቸውን በመዝጋት በመዝረፍና በመቦርቦር፣ የስብሰባ አዳራሽን እንዳይከራዩ በመከልከል ፣ የሚጠሩትን የህዝብ ስብሰባ በመበተን ፣ ትግራዋይ የዓረና አባል እንዳይሆንና እንዳይጠጋ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ማስፈራራት ማሸማቀቅና ማሰር የተለመዱ የህወሓት ካድሬዎች ተግባራት ናቸው:: ከዚህም አልፎ የዓረና ትግራይ አባል ደጋፊና ተባባሪ ሆኖ ከተገኘ ደግሞ “ሲሞት እንዳትቀብሩ ፣ እሳት እንዳታስጭሩ፣ ልቅሶ እንዳትደርሱ፣ ከነሱ ጋር ቡና ሻይ እንዳትሉ“ የሚል ማሕበራዊ ውግዘትና ማግለል እንዲደርስባቸው በማድረግ በተወለዱባትና እትብታቸውን በተቀበረባት ምድር ላይ የቁም ስቃያቸውን እያዩ ይገኛሉ:: ይህ ሰብኣዊ ርህራሄ የሌለበት እርምጃም ይቅርና ከአንድ ነፃ አውጪ ነኝ የሚል የፓለቲካ ድርጅት ቀርቶ የባዕድ ወራሪም ቢሆን ይፈፅሟል ብለን የምንጠብቀው አይደለም::
ድርጊቱም የዜጎችን አማራጭ ሃሳብ የመስማትና በነፃ የመደራጀት መብት ለመገደብ ብቻ ሳይሆን ለህዝቡ እኔን አይተህ ተቀጣ የሚል መልእክት በማስተላለፍ ተቃውሞ እንዳያነሳ ለማሸማቀቅና አንገቱን ለማስደፋት ሲባል ሆን ተብሎ የሚወሰድ የመቀጣጫ እርምጃ ነው:: በመሆኑም ይህንን ተግባር እንዳይደገም እያወገዝን በዓረና ትግራይ ላይ የሚደረገውን ማንኛውም የአካልና የስነ ልቦና ጥቃት፣ እስርና ግዲያ ሆን ተብሎ በህዝባችን ላይ የተቃጣ ጥቃት አድርገን እንወስዷለን:: ስለሆነም የአንድ የዓረና ትግራይ አባል መታሰር ማለት የህዝባችንም መታሰር ፣ የአንድ የዓረና አባል ሞት ማለት የህዝባችን ሞት መሆኑን ሊገነዘቡት ይገባል እንላለን:: ስለሆነም በተለያየ ጊዜ ሰበብ አሳባብ እየተፈለገባቸው ዛሬ በጨለማ እስር ቤት ታጉረው የሚገኙትን የዓረና ትግራይ አባላትና ሌሎች የህሊና እስረኞችን ያላንዳች ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ አበክረን እንጠይቃለን::
- 4. የአስአኳይ ጊዜ አዋጁ ሀገሪትዋን ወደ ባሰ ብጥብጥና የደም መፋሰስ እንድትገባ የሚጋብዝ ስለሆ በአስቸኳይ እንዲነሳ እንጠይቃለን:: በሀገራችን ፍትሕና ዴሞክራሲ ቢረጋገጥ ኖሮ ይህ ሁሉ ዓመፅና ደም በከንቱ ባልፈሰሰና የሀዝብና የሀገር ሀብትም ባልወደመ ነበር:: ፍትሕ ከሌለ ሚሊዮን ሰራዊት ቢሰለፍ ሰዎችን መግደል ይቻል ይሆናል እንጂ አስከፊ ጭቆና እስካለ ድረስ ለፍትሕ፣ ለነፃነት፣ ለዴሞክራሲና ለሰብኣዊ መብት መከበር የሚደረገውን ትግልና አላማ ግን በፍፁም መግደል አይቻልም:: አንዱ ቢሞት ሌላው አርማውን ይዞ ይቀጥላል:: አንደ ታጋይ ቢታሰር ሽሕ ታጋዮች ይፈጠራሉ:: ይህንን ሐቅ ማየትና መረዳት የተሳናቸው በፍቅረ ንዋይና በስልጣን ጥም የታወሩ የህወሓት መሪዎችም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በመደንገግና አሸባሪ እርምጃዎችን በመውሰድ የህዝቡን ጥያቄ ማፈን እንችላለን ከበሚል የተሳሳተ ስሌት በመነሳት የታሪክን ጎማ ወደሗላ ለማሽከርከር ጥረት ሲያደርጉ ይታያሉ::
ሐቁን ግን ሌላ ነው:: ወጣቱ ትውልድ እየጠየቀና እያሰበ ያለው በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ላይ አሁን ላለንበት ዘመን የሚመጥን የፓለቲካ ምሕዳር እንዲኖር ነው:: የህወሓት መሪዎች ግን እያሰቡና እየሰሩ ያሉት በድሮ በዘመነ ደደቢት የቀረፁትን አስተሳሰብና ፓሊሲ መሰረት በማድረግ ነው:: ስለዚህ የህወሓት መሪዎች እየተጋጩና እየተታኩሱ ያሉት ፍትሕ ከጠማው ህዝብ ጋር ብቻ አይደለም:: እየተላተሙና እየተጋጩ ያሉት ከጊዜ ጋርም ጭምር ነው:: ጊዜ ደግሞ ጎርፍ ነው ማንም ሊያቆመው አይችልም:: በቅርቡ ከተፈጠረው ቀውስ ጋር ተያይዞ ምናልባት ከስህተታቸው ተምረው ለራሳቸውም ጭምር ነፃ የሚያወጣ ሰላማዊ መፍትሄ ያመጡ ይሆናል ብለን ስንጠብቅ በአንፃሩ ለስልጣናቸው ማቆያ ብለው ያወጡትን የአስቸኳይ ጊዜ አስደንጋጭ አዋጅ ስንሰማ እጅጉን አሳዝኖናል:: አዋጁ ታጋሹን : ሰላም ወዳዱንና ሕግ አካባሪውን የኢትዮያ ህዝብ ክብር የሚዳፈርና የማይመጥን ከመሆኑም በላይ የባሰውኑ ትርምስና ደም መፋሰስን የሚጋብዝ ስለሆነ በአስቸኳይ እንዲነሳ እንጠይቃለን::
bega22601@comcast.net
ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮሃል። ከጳጳሱ እስከ ጠራጊው፣ ከቤተ መንግስት እስከ ቀበሮ ጉድጓድ በትግሬ ተወሮ ፥ የሃገሪቱ ባንክ በትግሬ ተነጥቆ ፥ የወርቅ ማዐድን ማውጫዎች በትግሬ ወረራ ተይዘው ፥ ቀሪውን የአገሪቱ ሕዝብ ትግሬ እየፈጀ እና እያስፈጀ ፤ አሁንም ለምዋች ሳይሆን ለገዳይ አልቅሱ ፣ ትግሬ ተጎድቱዋል መባል በጣም በጣም በጣም በጣም ያስቃል። መሸጥ የለመደች ምን ታስማማለች ይባላል። የበለጠ የሚያስቀው ግን < > የሚለው ሃረግ ነው። እውነት ነው ስዬ አብርሃ እና ዐረጋዊ ካልመሩት ትግሉ አቅጣጫ ኣይኖረቅም ፥ኢትዮጵያም መበጣጠስዋ ነው። በሉ እንግዲህ እግር እንይ…. ማለት አሁን ነው።
እጅግ የተዋጣለት አጻጻፍ”!
» የሕወሓት አምባ ገነን መሪዎች ዙሪያቸውን በወታደራዊ ሐይል ተከቦ ሲያዩት ልባቸውን በትዕቢትና በትምክህት ስለሚሞላ ነገ ፈራሽ መሆናቸውን ከታሪክ አይማሩም::ሕብረተሰቡን በዘር፣ በሀይማኖት፣ በጥላቻና በቂም በቀል ለያይተህ ፣አደንቁረህና አደንዝዘህ ግዛ የሚል መርህ ስለሆነ የህዝቡን ነፃ እንቅስቃሴ፣ አንድነትና መደራጀት ከጦር በላይ ይፈሩታል:: ራሳቸውን ልዩ ፍጡራንና ልዩ ጀግኖች አድርገው በመመልከትም ከሀገርና ከሕግ በላይ በመሆን የሰው ህይወት የዶሮን ያህል ግምት አይሰጡትም::
** ዛሬ በሀገራችን የፈነዳው ቀውስም ድንገት የተከሰተ ችግር ሳይሆን ውስጡ ውስጡን እንደ ረመጥ እሳት እየተብላላ ቆይቶ በሕብረተሰቡ ውስጥ ያለው ማሕበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ ብሶት የወለደው የፍትሕና የፓሊሲ መዛባት ውጤት ነው:: አንድ አምባ ገነን ቡድን ሁሉንም ነገር በሞኖፓል ጠቅልሎ በመያዝ 90 ሚሊዮኑን የኢትዮያ ህዝብ የበይ ተመልካች በማድረግ አግላይና አፋኝ ፓለሲ የወለደው የዓመፅ ነበልባል ነው::
** የትግራይ ህዝብ ላለፉት አርባና ሐምሳ ዓመታትን ያህል በህወሓት ሞኖፓላዊ አገዛዝ ስር ወድቆ በጅሆ (ሆስቴጅ) ተይዞ እንዲኖር የተፈረደበት ህዝብ ሆኖ ቆይቷል::
** የትግራይ ህዝብ ከወንጀለኛ መሪዎች ጋር ተደምሮ እንደጠላት እንዲታይ በማድረግ አይዞህ የሚለው ወንገንና የሕግ ከለላ አጥቶ እኖሆ ዛሬ በሁለት ዱላ እየተቀጠቀጠ ራሱ መስዋእትነትን ከፍሎ ባቆያት ሀገር ላይ የቁም እስረኛና የጥቃት ዒላማ ሆኖ ዳግም ሲያለቅስ ማየታችን እጅጉን አሳዝኖናል::አስቆጥቶናልም::
** በአንድ ሀገር ውስጥ በሰለጠነ አመለካከት ላይ የተመሰረተ ነፃና አማራጭ የፓለቲካ መድረክ መኖር ከሁሉም በላይ የነፃ ውድድሩን ተጠቃሚ የሚሆነው ህዝቡን ነው::
** ወጣቱ ትውልድ እየጠየቀና እያሰበ ያለው በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ላይ አሁን ላለንበት ዘመን የሚመጥን የፓለቲካ ምሕዳር እንዲኖር ነው:: የህወሓት መሪዎች ግን እያሰቡና እየሰሩ ያሉት በድሮ በዘመነ ደደቢት የቀረፁትን አስተሳሰብና ፓሊሲ መሰረት በማድረግ ነው::
» በሀገራችን ፍትሕና ዴሞክራሲ ቢረጋገጥ ኖሮ ይህ ሁሉ ዓመፅና ደም በከንቱ ባልፈሰሰና የሀዝብና የሀገር ሀብትም ባልወደመ ነበር:: ፍትሕ ከሌለ ሚሊዮን ሰራዊት ቢሰለፍ ሰዎችን መግደል ይቻል ይሆናል እንጂ አስከፊ ጭቆና እስካለ ድረስ ለፍትሕ፣ ለነፃነት፣ ለዴሞክራሲና ለሰብኣዊ መብት መከበር የሚደረገውን ትግልና አላማ ግን በፍፁም መግደል አይቻልም::አራት ነጥብ።