(ዘ-ሐበሻ) አዲሱ የኢህአዴግ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚ/ር የሚሆነው ሰው በዚህ ሳምንት የሚታወቅ ሲሆን አዲስ በሚመረጠው ሰው ላይ ገና ማንነቱን ሳያውቁ ተስፋ ለሚያደርጉ ሰዎች ድርጅቱ ምንም የተለየ ነገር አትጠብቁ ሲል መግለጫ ሰጠ::
የኢህአዴግ የአዲስ አበባ ፌስቡክ ገጽ ላይ ድርጅቱ አቋሙን እንደገለጸው “ከኢህአዴግ የተለየ ፕሮግራም የሚፈፅም ጠቅላይ ሚኒስቴር ሊመጣ የሚችለው ከኢህአዴግ ውጪ ብቻ ነው!” ሲል በግልጽ ለውጥ እንደማይኖር አስታውቋል::
“በምርጫ አሸንፎ ይህችን ሃገር የመምራት ሃላፊነት የተረከበው ኢህአዴግ ነው፡፡ ተወዳድሮ ያሸነፈው የኢህአዴግ ፕሮግራም ነው፡፡ ስለሆነም ጠቅላይ ሚኒስቴር የሚሆነውም ኢህአዴግ ነው፡፡ ሰው በሰው ሊተካ ይችላል፡፡ ተተክቷልም! የሚቀጥለው ግን መስመሩና የድርጅቱ ፖሊሲና ስትራቴጂ ነው፡፡” የሚለው ይኸው መግለጫ “ለውጥ የሚያመጣውም ግለሰብ ሳይሆን የጠራውና በተግባር ተፈትኖ ውጤታማነቱ የተረጋገጠው የልማታዊ ዲሞክራሲያዊ መስመር ብቻ ነው! ስለዚህም ነው ለኢህአዴጎች የጠቅላይ ሚኒስቴር ምርጫ ትልቅ አጀንዳቸው ሊሆን የማይችለው፡፡ በኢህአዴግ ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስቴርነት የስምሪት ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ፕሮግራም ፤ከሁሉም በላይ መስመር፤ ከሁሉም በላይ ውድ ዋጋ የተከፈለበት የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር፡፡” ብሏል::
ኢህ አዴግ ይህን መግለጫ በሰጠበት ገጽ ላይ ደቤ ለማ የሚባሉ አስተያየት ሰጪ እንዲህ ብለዋል “ግለሰብ ሚና የለውም ታዲያ ግለሰብ ሚና ከሌለው ኃ/ማሪያም መምራት አቅቶት ሀገር ለምን ተበጣበጠች ይሄ የማስ አካሄድ ግለሰብ አቅሙም እውቀቱም ዋጋ የማሳጣት ነገር ለምንድነው ኢህዴግን ብቻ ከዓለም የተለየ የሚያደርገው እኔ እስከሚገባኝ በእስከአሁን አካሄድ አይተናል የኩዱማኖች ስብስብ መስመራችን ዓላማችን ቡድናችን ምናምን የሚለው ማወናበጃ ብዙ አያስከደንም አዎን ወሳኝ አቅም ያለው ሁሉን ማነቃነቅ የሚችል ተቀባይነቱና ተፅዕኖ ፈጣሪነቱ የተመሰከረለት አሁን ገገባንበት አዘቅጥ መንጭቆ የሚያወጣን ጠቅላይ ሚኒስቴር ያስፈልገናል፡፡”
ዳኛቸው የተባሉ ሰውም “27 ዓመት በግንባር እንጂ በፓርቲ ሳንመራ እናም ግንባር ሁሌም እንዳሸነፈ ነው፡፡ ምረጡኝ ይላል ሲሸነፍ አፈ ሙዝ ያነሳል፡፡ ተቀናቃኞቹን ድራሻቸውን ያጠፋል፡፡ ከዛ ብቻውን ይወዳደራል፡፡ 100 % አሸነፍኩ ይላል፡፡ ልክ ነው ያሸነፈው ኢህአዴግ ነው iii”በማለት ተሳልቀዋል::