በጋምቤላ ክልል የህንድ ኩባንያ ንብረት በእሳት ወደመ

(ሪፖርተር) በተደጋጋሚ ለመንግሥት ጥያቄ ቢያቀርቡም በቂ ምላሽ ባለማግኘታቸው እንደ ተበሳጩ የሚነገርላቸው የጋምቤላ ክልል ጐደሬ አካባቢ ነዋሪዎች፣ የህንዱን ኩባንያ ንብረት በእሳት ማጋየታቸውን ምንጮች ገለጹ፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ጥቅምት 12 ቀን 2006 ዓ.ም. ምሽት ላይ የህንድ ኩባንያ የሆነው ቬርዳንታ ሀርቨስት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ይዞታ ላይ እሳት መነሳቱን በሥፍራው የነበሩ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ በቃጠሎው በርካታ ጣውላዎች፣ መጋዘኖች፣ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ነዳጅ የያዙ በርሜሎች፣ ትራክተርና ኤክስካቫተር የመሳሰሉ ንብረቶች ከጥቅም ውጪ ሆነው መውደማቸው ተገልጿል፡፡
የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት ጋት ሉክየጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ጋትሉዋክ ቱት በኩባንያው ንብረት ላይ ቃጠሎ መድረሱን አረጋግጠው፣ ዘጠኝ አባላት ያሉት አጣሪ ቡድን ወደ ሥፍራው መላካቸውንም አስታውቀዋል፡፡ አቶ ጋትሉዋክ ጨምረው እንደገለጹት፣ ድርጊቱን ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ይገኛሉ፡፡ ጉዳዩን ለማጣራት በሥፍራው የተገኘው የጋምቤላ ክልል ልዑካን ብቻ ሳይሆን፣ የጋምቤላና የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎችና ከግብርና ሚኒስቴር የተውጣጡ አካላት ይገኙበታል፡፡
ከግብርና ሚኒስቴር የተውጣጣውን አጣሪ ልዑክ እየመሩ ወደ ሥፍራው የተጓዙት የግብርና ኢንቨስትመንት ድጋፍ ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ አበራ ሙላት ናቸው፡፡ የስልክ ኔትወርክ ችግር በመኖሩ አቶ አበራን በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡
የግብርና ሚኒስቴር ለህንዱ ኩባንያ ቬርዳንት ሀርቨስት ከአምስት ዓመት በፊት ለሻይ ቅጠል ልማት የሚሆን 3,012 ሔክታር መሬት በ50 ዓመት የሊዝ ዘመን በመረከብ ውል ፈጽሟል፡፡ ነገር ግን የግብርና ሚኒስቴር ከክልሎች በውክልና የእርሻ መሬት እየተረከበ መስጠት ከመጀመሩ በፊት ኩባንያው የጋምቤላ ክልልን መሬት ጠይቆ ስለነበር፣ በወቅቱ የጋምቤላ ክልል ያስረከበው መሬት አምስት ሺሕ ሔክታር መሬት መሆኑ ተገልጿል፡፡
የህንዱ ኩባንያ ቬርዳንታ ሀርቨስት በዚህ መሬት ላይ ለሚያካሂደው የሻይ ልማት ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ 89.5 ሚሊዮን ብር ብድር አግኝቷል፡፡ ለተሰጠው መሬት በሔክታር 111 ብር የሚከፍል ሲሆን፣ ለጠቅላላ መሬቱ 16.7 ሚሊዮን ብር በመክፈል ለሚቀጥሉት 50 ዓመታት መጠቀም የሚያስችለውን ውል ፈጽሟል፡፡ በየዓመቱም 334,332 ብር ይከፍላል፡፡
በአካባቢው የሚኖሩ የሸኪቾ ብሔረሰብ አባላት መንግሥት ለዚህ ኩባንያ የሰጠው ቦታ ትክክለኛነቱ አላሳመናቸውም፡፡ በጋምቤላ ክልል ጐደሬ ወረዳ ጉማሬና ኩቡ በሚባሉ አካባቢዎች በኢትዮጵያ የደን ክልል ተብለው ከተከለሉ 58 ብሔራዊ ደኖች ተቀዳሚው ነበር፡፡ አካባቢው የውኃ ማማ መሆኑ በጥናት የተረጋገጠ በመሆኑ ሊጠበቅ ይገባል የሚሉ በርካታ የአካባቢ ተሟጋቾች አሉ፡፡
የአካባቢው ማኅበረሰብ ደን የመጠበቅ ጥንታዊ ልማድ ያለው በመሆኑ የአካባቢው ማኅበረሰብ ከደን የሚገኙ የግብርና ምርቶችን ማለትም ማር፣ ቅመማ ቅመምና ቡና የመሳሰሉ ምርቶች ሲተዳደር መቆየቱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ነገር ግን መንግሥት ለዚህ ኩባንያ በዚህ የደን ክልል ውስጥ መሬቱን ለሻይ ልማት መስጠቱ እነዚህ ነዋሪዎች አልተዋጠላቸውም፡፡ ምክንያቱም የሻይ ልማት ሙሉ በሙሉ ደኑ ከተመነጠረ በኋላ የሚካሄድ በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡
ይህንን ልማት የተቃወሙ የአካባቢ ነዋሪዎች ፊርማ አሰባስበው ለቀድሞው ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ተቃውሟቸውን ገልጸው ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ግርማም ለግብርና ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበው መሬቱ ደን ውስጥ ስለሚገኝ ማሻሻያ እንዲደረግ ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡ ነገር ግን የግብርና ሚኒስቴርም ሆነ የጋምቤላ ክልል መንግሥት ቦታው ለእርሻ ልማት የተከለለና ቁጥቋጧማ ነው በሚል ጥያቄውን ሳይቀበሉት ቀርተዋል፡፡ ምላሾቹ ሙሉ በሙሉ ያልተዋጠላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች፣ በአካባቢው ያለው ቁጥቋጦ ሳይሆን ደን መሆኑን ለማሳየት የተለያዩ ሙከራዎችን አድርገዋል፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት ቬርዳንታ ሀርቨስት ከጀመረው የሻይ ልማት ጋር የማይገናኝ ተግባር ውስጥ መግባቱ ተረጋግጧል፡፡ ኩባንያው በይዞታው ላይ የሚገኘውን ደን እየጨፈጨፈ በጣውላ ማምረት ሥራ ላይ በመሰማራቱ፣ የጉማሬ ወረዳ በአካባቢው ነዋሪዎች ጥቆማ ክትትል አድርጐ አንድ ሺሕ የሚጠጋ ጣውላ በከባድ ተሽከርካሪዎች ተጭኖ ሲወጣ በቁጥጥር ሥር ማዋሉ ተገልጿል፡፡
የጋምቤላው ፕሬዚዳንት ይህ ጣውላ ለሽያጭ የሚውል አይደለም የሚል ምላሽ ከኩባንያው ማግኘታቸውን ቢገልጹም፣ በደቡብ ክልል ሜጢ ከተማ በኩል በርካታ ጣውላ እየወጣ ወደ አዲስ አበባ እንደሚጓጓዝ የአካባቢው ማኅበረሰብ ባገኘው አጋጣሚ ሲያስረዳ መስፈርት በግማሽ ሔክታር መሬት ላይ ቁመቱፋኦቆይቷል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብና እርሻ ድርጅት ከአምስት ሜትር የሚበልጥ ዛፍ ደን ይበላል፡፡ በጉማሬ አካባቢ ያለው ደን ስፋት በሺሕ ሔክታር የሚቆጠር ከመሆኑም በላይ፣ ቁመታቸው ከአሥር ሜትር በላይ የሆኑ ግዙፍ ዛፎች የሚገኙበት ነው፡፡ ይህ አካባቢ ደን አለመባሉና ቀጣይ ህልውናቸውን ለአደጋ እንደሚዳርገው የተገነዘቡ ነዋሪች ባገኙት አጋጣሚ ሲቃወሙ ቆይተዋል፡፡
በተለያዩ ጊዜያት በዚህ ጉዳይ ሲብሰከሰኩ የቆዩ የአካባቢው ነዋሪዎች እሳት ለቀውበታል ሲሉ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ሲገልጹ፣ የአጣሪ ኮሚቴው አባላት በንብረቱ ላይ እሳት የለቀቀውን አካል በማጣራት ላይ ነን በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ለጉዳዩ ቅርበት ያላችው ባለሙያዎች ሁለት መሠረታዊ ጥያቄዎችን እያነሱ ነው፡፡ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለህንዱ ኩባንያ ላበደረው ብድር በቂ መያዣ አለው ወይ የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ አጣሪ ኮሚቴው የአካባቢው ነዋሪዎች የሚስማሙበትን ዘላቂ መፍትሔ ይዞ ይቀርባል ወይ የሚል ነው፡፡
የልማት ባንክ ብድርን በሚመለከት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ባህረን ለማነጋገር የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡
የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች ግን ዘላቂ መፍትሔን በሚመለከት መንግሥት የተፈጥሮ ሀብት ባለሙያዎች ያሉበት ኮሚቴ አዋቅሮ ዘለቄታዊ መፍትሔ እንዲያመጡለት ሁኔታዎችን ያመቻች ይላሉ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዋልያዎቹ የዋንጫ ጉዟቸውን ጨረሱ

ምንጭ ሪፖርተር ጋዜጣ የእሁድ ኦክቶበር 27 ዕትም።

Share