El Clasico፡ ባርሴሎና Vs ሪያል ማድሪድ

ከዳዊት ጋሻው

በስፔን ላሊጋ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠውና በዓለም ስፖርት አፍቃሪያን ዘንድ በጉጉት የሚጠበቀው ኤልክላሲኮ አዳዲስ ፊቶችን ጨምሮ ከጥቂት ሰአታት በኋላ በኑካምፕ ይጀመራል፡፡ ኤልክላሲኮው ከሌሎች ዓመታት የተለየ ትኩረት ተሰጥቶታል።
የ2013/14 የውድድር ዓመት ኤልክላሲኮ ከሌሎቹ ዓመታት በተለየ ልዩ ትኩረት የተሰጠው በተለያዩ ምክንያቶች ነው ። ከነዚህ መካከል ሁለቱ ኃያላን የስፔን ክለቦች ባርሴሎናና ሪያል ማድሪድ ከሁለቱ የዓለም ምርጥ ተጫዋቾች በተጨማሪ ሌሎች ሁለት ተጫዋቾችን ማስፈረማቸውና ባርሴሎና ፔፕ ጋርዲዮላን ወደ ባባርያኑ ሸኝቶ አርጀንቲናዊውን ጄራርዶ ማርቴኔዝ ታታን መተካቱ እንዲሁም ማድሪድ አወዛጋቢው ጆዜ ሞሪንሆን ወደ ስታንፎርድ ብሪጅ በመሸኘት ካርሎ አንቸሎቲ ከሀብታሙ ፒኤስ ጅ መምጣታቸው ጨዋታውን ልዩ አድርጎታል ።

በዚህ መሰረት ሁለቱም ክለቦች በአዳዲስ አሰልጣኞች ይገናኛሉ ማለት ነው ። ቀደም ሲል በሜሲና ሮናልዶ ላይ ብቻ የነበረው ትኩረት ወደ አዳዲሶቹም ይዞራል ተብሎ ይጠበቃል። ይሁን እንጂ ቀድሞም የሚጠበቀው የሮናልዶና ሜሲ ፍልሚያም ሌሎች ጎበዞች በተጨመሩበት አሁንም በጉጉት ይጠበቃል።
ከብራዚሉ ሳንቶስ ክለብ በ48 ነጥብ 6ሚሊዮን ፓውንድ ወደ ስፔኑ ባርሴሎና የተቀላቀለው ብራዚላዊው አጥቂ ኔይማርና የዓለም የእግር ኳስ ተጫዋቾችን የዝውውር ዋጋ ክብረ ወሰን በሆነ 85 ነጥብ 3 ሚሊዮን ፓውንድ ዋጋ ቤርናባ የገባው ዌልሳዊው ጋሪዝ ቤል በኤል ክላሲኮ ይፈተሻሉ ።
በጉጉት እየተጠበቀ ባለው በዕለቱ ጨዋታ ሁለቱ ታላላቅ ተጫዋቾች ለየክለቦቻቸው በሜዳ ላይ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከወዲሁ በበርካታ የስፖርት አፍቃሪያን ዘንድ ከፍተኛ ግምት አግኝቷል።
እስከዛሬ በተደረጉት የኤልክላሲኮ ጨዋታዎች የፖርቱጋሉ ክርስቲያኖ ሮናልዶና የአርጀንቲናው ሊኦኔል ሜሲ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ነበር ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ። አሁን ግን የዓለም እግር ኳስ አፍቃሪያን ሌላ የሚጠበቅ ክስተት ለማየት አይናቸውን ቤርናባው ላይ ይተክላሉ ።
በቅርቡ ወደ ስፔን የገቡት አዳዲሶቹ ተጫዋቾችም በመጀመሪያው የኤልክላሲኮ ጨዋታ ለዓለም ህዝብ ምን ያሳያሉ የሚለውም እንዲሁ ልብ አንጠልጣይ ሆኗል። ይህ የሆነውም ብራዚላዊው ኔይማር በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ለብራዚል ብሔራዊ ቡድን ያደረገው እንቅስቃሴና ዌልሳዊው ጋሬዝ ቤል በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ለቶተንሀም ሆትስፐርግ ያደርግ የነበረው እንቅስቃሴ የዛሬውን ጨዋታ ከጨዋታም በላይ አድርጎታል፡፡ምናልባትም በዛሬው ጨዋታ የማይሰለፈው የባርሴሎና ተከላካይ ጄራርድ ፒኬ ጨዋታው ዋንጫውን ማን ያነሳል የሚለውንም ይወስናል ሲል አዲሱ ልጅ ኔይማር ደግሞ በታላቁ ኤልክላሲኮ መጫወትን እፈልጋዋለሁ ብሏል፡፡
አዳዲሶቹን ፈራሚዎች ኔይማርና ቤልን ስናነጻጽራቸው ኔይማር ከሳንቶስ በ48 ነጥብ 6 ሚሊዮን ፓውንድ የተዛወረ ሲሆን ቤል ደግሞ በ85 ነጥብ 3ሚሊዮን ፓወንድ ከኋይት ሀርት ሌን ወደ ቤርናባው ተቀላቅሏል።ኔይማር ባርሴሎናን ከተቀላቀለ በኋላ 13 ጊዜ ሲጫወት ቤል ባጋጠመው ጉዳት ሳቢያ አራት ጨዋታዎችን ብቻ ነው ለማድሪድ ተሰልፎ የተጫወተው።
የማድሪድ ደጋፊ የሆነው ማርካ ቤልን የዓለም ምርጥ ሲለው ኔይማርን ደግሞ ካለስራው የተጋነነ ብሎታል ።በሌላ በኩል የካታሎኑ ሙንዶ ዲፖርቲቮ የዚህን ተቃራኒ ለአንባቢዎቹ እነሆ ብሏል ሲል በስፔን የሚገኘው የቢቢሲው እግር ኳስ ጸሀፊ አንዲ ዌስት ጽፏል። ጨዋታው ከምሽቱ ልክ 12 ሰዓት ላይ ቤርናባው በሚነፋው ፊሽካ ይጀመራል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ የመጀመርያዋ ሴት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሆኑ

ማን ያሸንፋል?

1 Comment

Comments are closed.

Share