አዲስ አድማስ
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
ሰሸዋንዳኝ የአልበም ምርቃት የተጋበዙት ሠራዊት ፍቅሬና ሰይፉ ፋንታሁንም ተከልክለዋል
በሸራተን አዲስ ጋዝ ላይት ክለብ ከትናንት በስቲያ ሰተካሄደው የድምፃዊ ሸዋንዳኝ ኃይሉ “ስጦታሽ” አልበም ምርቃት በክብር እንግድነት የተጠራው ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)፤ ሰዓት አርፍዶ በመድረሱ እንዳይገባ ተከልክሎ ከበር ተመለሰ፡፡
ቴዲ አፍሮ ከምሽቱ 5፡30 ላይ የምርቃት ስነስርዓቱ ወደሚካሄድበት ጋዝ ላይት ክለብ ሊገባ ሲል የጥበቃ ሰራተኞች “ጥሪው 4 ሰዓት እንጂ 5፡30 ሰዓት አይደለም” በማለት እንዳይገባ እንደከለከሉት ለማወቅ ተችሏል። አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬና ሰይፉ ፋንታሁንን ጨምሮ በርካታ ያረፈዱ እንግዶች ወደ ጋዝ ላይት ክለብ እንዳይገቡ መከልከላቸውን የዓይን እማኞች ገልፀዋል፡፡ ሸዋንዳኝ፤ ቴዲ አፍሮ እንዳይገባ መከልከሉን የሰማው መድረክ ላይ ሆኖ እንደሆነ የገለፁት ምንጮች፤ በዚህም ማዘኑን ተናግረዋል። አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች፤ ሁለቱ እንዳላቸው ቅርበት ቴዲ አፍሮ በፕሮግራሙ ላይ ቀድሞ መገኘት ነበረበት ብለዋል፡፡ ድምፃዊ ሸዋንዳኝን ስለ ጉዳዩ በስልክ ጠይቀነው፣ መልስ ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡
ከትላንት በስቲያ ምሽት በተካሄደው የምርቃት ስነ ስርዓት ላይ ሸዋንዳኝ ከአዲሱ አልበም አስር ዘፈኖችን የተጫወተ ሲሆን የተዘጋጀለትን አዲካ እና ኤም ጂ ፕሮሞሽን ያዘጋጁለቱንም ኬክ በዚያው ፕሮግራም ላይ ቆርሷል፡፡ ሸዋንዳኝና ቴዲ አፍሮ በአንድ የሙዚቃ ባንድ ውስጥ ለረጅም አመታት አብረው የሰሩ ሲሆን ቴዲ አፍሮ ሲያገባ ሸዋንዳኝ ሚዜው ነበር፡፡
ማርፈድ የስንፍና ምልክት መሆኑን የተናገረው አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ፤ሸራተን ስንደርስ የሆቴሉ ስራ አስኪያጅ በሩን ዘግተው እንደሄዱ ተነግሮናል ብሏል፡፡ “በሌሎች አገሮችም የተለመደ ነው፤ናይት ክለብ ከሞላ ሰው እስኪቀንስ መግባት አይቻልም” ያለው ሰራዊት፤ “እኛ ታዋቂ ስለሆንን ለምን ተከለከልን የሚል ቅሬታ አላደረብንም” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
addis admas