በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ


(BBN) የጎንደር ዩኒቨርሰቲ ተማሪዎች ከፍተኛ ተቃውሞ አሰሙ፡፡ ተማሪዎቹ በዛሬው ዕለት ተቃውሞ እያሰሙ ከግቢው ለመውጣት ሲሞክሩ፣ ግቢውን በከበቡት ታጣቂ ፖሊሶች እና ወታደሮች ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተቃውሞ መነሻ፣ የትግራይ ተወላጅ በሆኑ የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተፈጸመው ጥቃት ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲው ተማሪ የሆኑ የትግራይ ተወላጅ ተማሪዎች፣ በአማራ እና ኦሮሞ ተወላጆች ላይ ጥቃት መፈጸማቸው ያስቆጣቸው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ ድርጊቱን በመኮነን ተቃውሞ ማሰማታቸውን እማኞች ገልጸዋል፡፡

ተቃዉሞን ተከተሎ የክልሉ ልዩ ኃይል ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚወስዱ አውራ መንገዶችን በመዘጋጋት፣ አስለቃሽ ጭስ ሲተኩስ እንደነበር የገለጹት የዓይን እማኞች፣ ፖሊስ በወሰደው የኃይል እምርጃም ተማሪዎች መጎዳታቸውን እማኞቹ አክለው ተናግረዋል፡፡ በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ በወንድሞቻችን ላይ የተከፈተው ጥቃት ይቁም በማለት ትምህርታቸውን ትተው ለተቃውሞ የወጡት የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፣ ጥያቄያቸው መልስ እስኪያገኝ ድረስ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንደማይመለሱም አስታውቀዋል፡፡

ከአዲግራት ዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ በአክሱም ዩኒቨርሲቲም ተመሳሳይ እና ዘር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እየተፈጸመ እንደሚገኝ የገለጹት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ ጥቃቱ ያነጣጠረውም የአክሱም ዩኒቨርሰቲ ተማሪ በሆኑ የኦሮሞ እና አማራ ተወላጆች ላይ መሆኑን በመግለጽ፣ ድርጊቱን አውግዘዋል፡፡ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተነሳውን የተማሪዎች ተቃውሞ ተከትሎም፣ ዩኒቨርሲቲው ትምህርት መስጠት ማቆሙን ለማወቅ ተችሏል፡፡ እስከ ምሽቱ ድረስም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በፖሊሶች ከበባ እንደተፈጸመበት ይገኛል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በየመን በአስከፊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተገለጸ

1 Comment

Comments are closed.

Share