በኢትዮጵያ የድርቅ ተጎጂዎች ቁጥር መጨመሩ ታወቀ

ኢትዮጵያውያንን እያጠቃ የሚገኘው ድርቅ፣ የተረጂዎችን ቁጥር ሳይጨምር እንደማይቀር መረጃዎች ጠቆሙ፡፡ በኢትዮጵያ ያለው የተረጂዎች ቁጥር 8 ነጥብ 5 ሚሊዬን የነበረ ሲሆን፣ እንደ መረጃዎች ገለጻ ይህ ቁጥር ወደ 8 ነጥብ 9 ከፍ ብሏል፡፡ ጉዳዩን መንግስት እያድበሰበሰው እንደሚገኝ የሚጠቁሙት የመረጃ ምንጮች፣ መረጃው ይፋ መደረግ እንዳለበት ይናገራሉ፡፡ የተረጂዎችን ቁጥር መደበቅ ወይም ይፋ አለማድረግ በእርዳታ አሰጣጥ ሂደት ላይ ከባድ ፈተና እንደሚፈጥር የሚያሳስቡ ታዛቢዎች፣ የተረጂዎች ቁጥር በትክክለኛ ሁኔታ መገለጽ እንዳለበትም ያሰምሩበታል፡፡

ቁጥር ነክ የሆኑ መረጃዎችን በማድበስበስ የሚታወቀው ገዥው መንግስት፣ በድርቅ ተጎጂዎች ቁጥር ላይም ተመሳሳይ አቋም መያዙ እየተስተዋለ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የድርቅ ተጎጂዎች ቁጥር መጨመር በሌሎች አካላት ይፋ ከተደረገ በኋላ ነበር መንግስት የተረጂዎች ቁጥር መጨመሩን ይፋ ያደረገው፡፡ አሁን ላይም ቁጥሩ ከፍ እያለ እንጂ እየቀነሰ ባለመምጣቱ፣ ወቅታዊው የተረጂዎች ቁጥር ይፋ መደረግ እንዳለበት ይታመናል፡፡ የረድኤት ተቋማት እርዳታ ሊያቀርቡ የሚችሉት በድርቅ ተጎጂዎች ቁጥር ልክ በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ የድርቅ ተጎጂዎች ትክክለኛ ቁጥር መነገር አለበት ይላሉ-የመንግስትን ስንኩል ባህርይ የሚያውቁ ታዛቢዎች፡፡

በኦሮሚያ፣ ሶማሌ፣ አፋር እንዲሁም በደቡብ ክልሎች የተከሰተው ይኸው ድርቅ በሚሊዬን የሚቆጠሩ ወገኖችን እያጠቃ ሲሆን፣ ለተጎጂዎች እየተደረገ ያለው የድጋፍ ዓይነትም ውስን እና በቂ አለመሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የተከሰተው ድርቅ፣ የረድኤት ተቋማት ለኢትዮጵያ የሚያቀርቡትን የእርዳታ መጠን እንዲቀንሱ እንዳስገደዳቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ፣ በኬንያ፣ በደቡብ ሱዳን እና በሶማሊያ ተመሳሳይ የድርቅ አደጋ መከሰቱ ይታወቃል፡፡ (BBN)

ተጨማሪ ያንብቡ:  የደብረማርቆስ ከተማ አስተዳደር ኮምዩኒኬሽን በጎንደር ላይ እየተፈጸመ ያለውን ድርጊት እያየን ዝም አንልም አለ
Share